የጥናት ርዕስ 44
መዝሙር 33 ሸክማችሁን በይሖዋ ላይ ጣሉ
ኢፍትሐዊ ድርጊት ሲፈጸምብን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
“በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ።”—ሮም 12:21
ዓላማ
ኢፍትሐዊ ድርጊት ሲፈጸምብን ችግሩን የሚያባብስ ነገር ሳናደርግ ሁኔታውን መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
1-2. ሁላችንም በተለያዩ መንገዶች ፍትሕ የጎደለው ነገር ሊፈጸምብን የሚችለው እንዴት ነው?
ኢየሱስ ስለ አንዲት መበለት የሚገልጽ ምሳሌ ተናግሮ ነበር። ይህች መበለት አንድን ዳኛ ፍትሕ እንድታገኝ እንዲያደርግ ትወተውተው ነበር። ብዙዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህ ታሪክ ልባቸውን ነክቶት መሆን አለበት፤ ምክንያቱም በዚያ ዘመን የነበሩት ብዙዎቹ ሰዎች የፍትሕ መጓደል ያጋጥማቸው ነበር። (ሉቃስ 18:1-5) ይህ ታሪክ የእኛንም ልብ የሚነካ ነው፤ ምክንያቱም ሁላችንም በተለያዩ ጊዜያት ኢፍትሐዊ ድርጊት ይፈጸምብናል።
2 በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ጭፍን ጥላቻ፣ አድልዎና ጭቆና የተለመደ ነገር ነው። ስለሆነም ፍትሕ የጎደለው ነገር ሲፈጸምብን እምብዛም አንገረምም። (መክ. 5:8) ይሁንና ወንድሞቻችን ወይም እህቶቻችን በደል ያደርሱብናል ብለን ላንጠብቅ እንችላለን፤ ሆኖም እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል። እርግጥ ነው፣ ከተቃዋሚዎቻችን በተለየ መልኩ ወንድሞቻችን በደል የሚያደርሱብን ሆን ብለው ሳይሆን ፍጹማን ስላልሆኑ ነው። ኢየሱስ ክፉ የሆኑ ተቃዋሚዎች ግፍ ሲፈጽሙበት ከሰጠው ምላሽ ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ግፍ የሚፈጽሙብንን ተቃዋሚዎች በትዕግሥት መያዝ የምንችል ከሆነ የእምነት አጋሮቻችንንማ ይበልጥ በትዕግሥት መያዝ እንደሚጠበቅብን ምንም ጥያቄ የለውም! በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሰዎችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ፍትሕ የጎደለው ነገር ሲፈጽሙብን ይሖዋ ምን ይሰማዋል? ይህ ጉዳይ ያሳስበዋል?
3. ይሖዋ የሚደርስብን ኢፍትሐዊ ድርጊት ያሳስበዋል? ለምንስ?
3 ይሖዋ ሌሎች እኛን የሚይዙበት መንገድ በጥልቅ ያሳስበዋል። “ይሖዋ ፍትሕን ይወዳል።” (መዝ. 37:28) በተገቢው ጊዜ አገልጋዮቹ “በቶሎ ፍትሕ እንዲያገኙ” እንደሚያደርግ ኢየሱስ ዋስትና ሰጥቶናል። (ሉቃስ 18:7, 8) በቅርቡ ደግሞ እስካሁን የደረሰብንን ጉዳት በሙሉ ያስተካክላል፤ እንዲሁም ማንኛውንም ዓይነት የፍትሕ መጓደል ያስወግዳል።—መዝ. 72:1, 2
4. ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ምን ዓይነት እርዳታ ይሰጠናል?
4 ጽድቅ የሚሰፍንበትን ጊዜ በምንጠባበቅበት ወቅት ይሖዋ የሚፈጸሙብንን ኢፍትሐዊ ድርጊቶች እንድንቋቋም ይረዳናል። (2 ጴጥ. 3:13) ኢፍትሐዊ ድርጊት ሲፈጸምብን ጥበብ የጎደለው ነገር ከማድረግ መቆጠብ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል። ይህን የሚያደርግበት አንዱ መንገድ ልጁ በተወው ፍጹም ምሳሌ አማካኝነት ነው። በተጨማሪም ፍትሕ የጎደለው ነገር ሲያጋጥመን ምን ማድረግ እንደምንችል ተግባራዊ ምክር ይሰጠናል።
ለፍትሕ መጓደል ስለምትሰጡት ምላሽ ተጠንቀቁ
5. ለፍትሕ መጓደል ስለምንሰጠው ምላሽ መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው?
5 የፍትሕ መጓደል ሲያጋጥመን ስሜታችን በጥልቅ ሊጎዳና ልናዝን እንችላለን። (መክ. 7:7) እንደ ኢዮብና ዕንባቆም ያሉ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችም እንደዚህ ተሰምቷቸው ነበር። (ኢዮብ 6:2, 3፤ ዕን. 1:1-3) እንዲህ ዓይነት ስሜት የሚሰማን መሆኑ የሚጠበቅ ነገር ቢሆንም የምንሰጠውን ምላሽ በተመለከተ ልንጠነቀቅ ይገባል፤ አለዚያ የሞኝነት ድርጊት ልንፈጽም እንችላለን።
6. ከአቢሴሎም ታሪክ ምን እንማራለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
6 የፍትሕ መጓደል ሲያጋጥመን በራሳችን ተገቢ ያልሆነ እርምጃ ለመውሰድ ልንፈተን እንችላለን። ይሁንና እንዲህ ማድረጋችን ችግሩን ወደከፋ ደረጃ ሊያደርሰው ይችላል። የንጉሥ ዳዊት ልጅ የሆነው አቢሴሎም ያደረገውን ነገር እንመልከት። ወንድሙ አምኖን እህቱን ትዕማርን አስገድዶ በደፈራት ጊዜ አቢሴሎም እጅግ ተበሳጭቶ ነበር። በሙሴ ሕግ መሠረት አምኖን ላደረገው ነገር ሞት ይገባው ነበር። (ዘሌ. 20:17) አቢሴሎም መበሳጨቱ የሚጠበቅ ነገር ቢሆንም በራሱ እንዲህ ያለውን እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን አልነበረውም።—2 ሳሙ. 13:20-23, 28, 29
7. መዝሙራዊው በዙሪያው ያየው የፍትሕ መጓደል ምን ስሜት ፈጥሮበት ነበር?
7 ኢፍትሐዊ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች ለድርጊታቸው ምንም ቅጣት እንዳልተቀበሉ ሲሰማን ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ጥቅም ያለው መሆኑን ልንጠራጠር እንችላለን። መዝሙራዊው፣ ክፉዎች ጻድቃንን ቢበድሉም እንኳ በሕይወታቸው ስኬታማ እንደሆኑ ተሰምቶት ነበር። “ክፉዎች እንደዚህ ናቸው፤ ሁልጊዜ ሳይጨናነቁ ይኖራሉ” ብሏል። (መዝ. 73:12) በተጨማሪም በዙሪያው የሚያየው የፍትሕ መጓደል በጣም ስላሳዘነው ይሖዋን ማገልገል ጥቅም ያለው መሆኑን መጠራጠር ጀምሮ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ለመረዳት በሞከርኩ ጊዜ፣ የሚያስጨንቅ ሆነብኝ።” (መዝ. 73:14, 16) እንዲያውም “እኔ ግን እግሮቼ ከመንገድ ሊወጡ ተቃርበው ነበር፤ አዳልጦኝ ልወድቅ ምንም አልቀረኝም” በማለት በሐቀኝነት ተናግሯል። (መዝ. 73:2) አልበርቶa የተባለ ወንድም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር።
8. አንድ ወንድም ያጋጠመው የፍትሕ መጓደል ምን ተጽዕኖ አሳደረበት?
8 አልበርቶ ከጉባኤው ሒሳብ ገንዘብ ሰርቋል በሚል በስህተት ተከሰሰ። በዚህም የተነሳ በጉባኤው ውስጥ ያሉትን መብቶች አጣ፤ ስለ ጉዳዩ የሰሙ በርካታ የጉባኤው አስፋፊዎችም ለእሱ ያላቸውን አክብሮት አጡ። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውስ “በጣም አዝኜና ተበሳጭቼ ነበር” ብሏል። የደረሰበት የስሜት ጉዳት በመንፈሳዊነቱ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ፈቀደ፤ እንዲያውም ለአምስት ዓመት ያህል ቀዝቅዞ ቆየ። ይህ ምሳሌ፣ የደረሰብን የፍትሕ መጓደል ስሜታችንን እንዲቆጣጠረው ከፈቀድን ምን ውጤት ሊመጣ እንደሚችል ያሳያል።
ኢየሱስ የፍትሕ መጓደልን የተቋቋመበትን መንገድ ኮርጁ
9. ኢየሱስ የትኞቹን ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ተቋቁሟል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
9 የፍትሕ መጓደልን መቋቋም ከሚቻልበት መንገድ ጋር በተያያዘ ኢየሱስ ፍጹም ምሳሌ ትቷል። ኢየሱስ በቤተሰቡም ሆነ በሌሎች ሰዎች ብዙ ኢፍትሐዊ ድርጊት ተፈጽሞበታል። አማኝ ያልሆኑት ዘመዶቹ አእምሮውን እንደሳተ ተናግረዋል፤ የሃይማኖት መሪዎቹ ሥራውን የሚያከናውነው በአጋንንት ኃይል እንደሆነ በመግለጽ ወንጅለውታል፤ ሮማውያን ወታደሮች ደግሞ አፊዘውበታል፤ አንገላተውታል፤ በስተ መጨረሻም ገድለውታል። (ማር. 3:21, 22፤ 14:55፤ 15:16-20, 35-37) ያም ቢሆን ኢየሱስ ምንም አጸፋ ሳይመልስ ይህን ሁሉ ግፍ ተቋቁሟል። ከእሱ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
10. ኢየሱስ ኢፍትሐዊ ድርጊት ሲፈጸምበት ምን አድርጓል? (1 ጴጥሮስ 2:21-23)
10 አንደኛ ጴጥሮስ 2:21-23ን አንብብ።b የፍትሕ መጓደል ሲያጋጥመን ማድረግ ያለብንን ነገር በተመለከተ ኢየሱስ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል። ኢየሱስ መቼ ዝም ማለት፣ መቼ ደግሞ መናገር እንዳለበት ያውቅ ነበር። (ማቴ. 26:62-64) የሐሰት ክስ በተሰነዘረበት ቁጥር ምላሽ አልሰጠም። (ማቴ. 11:19) በተናገረባቸው ጊዜያትም አሳዳጆቹን አልሰደባቸውም ወይም አልዛተባቸውም። ኢየሱስ ‘በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን በአደራ ስለሰጠ’ ራሱን መግዛት ችሏል። ኢየሱስ በዋነኝነት ሊያሳስበው የሚገባው የይሖዋ አመለካከት እንደሆነ ያውቅ ነበር። ያጋጠመውን የፍትሕ መጓደል ይሖዋ በትክክለኛው ጊዜ እንደሚያስተካክልለት ተማምኖ ነበር።
11. አንደበታችንን መቆጣጠር የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
11 የፍትሕ መጓደል ሲያጋጥመን አንደበታችንን በመቆጣጠር የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። አንዳንድ ጊዜ የሚፈጸሙብን ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ያን ያህል ከባድ ስላልሆኑ ሁኔታውን እንዲሁ ዝም ብለን ለማለፍ እንመርጥ ይሆናል። ወይም ደግሞ ሁኔታው እንዲባባስ የሚያደርግ ነገር ላለመናገር ስንል ዝም ለማለት ልንመርጥ እንችላለን። (መክ. 3:7፤ ያዕ. 1:19, 20) አንዳንድ ጊዜ ግን ሌሎች ኢፍትሐዊ ድርጊት ሲፈጸምባቸው ስናይ ወይም ለእውነት ጥብቅና መቆም ሲያስፈልገን መናገራችን የተሻለ ሊሆን ይችላል። (ሥራ 6:1, 2) በምንናገርበት ጊዜም እርጋታና አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ ለመናገር አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል።—1 ጴጥ. 3:15c
12. ‘በጽድቅ ለሚፈርደው ራሳችንን በአደራ መስጠት’ የምንችለው እንዴት ነው?
12 ‘በጽድቅ ለሚፈርደው ራሳችንን በአደራ በመስጠትም’ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ሌሎች በተሳሳተ መንገድ ሲረዱን ወይም ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲያደርጉብን ይሖዋ እውነቱን እንደሚያውቅ እንተማመናለን። ይህን ማመናችን ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ለመቋቋም ይረዳናል፤ ምክንያቱም ይዋል ይደር እንጂ ይሖዋ ጉዳዩን እንደሚያስተካክል እናውቃለን። ጉዳዩን ለይሖዋ መተዋችን ቁጣና ጥላቻ በልባችን ውስጥ ሥር እንዳይሰድ ይረዳናል። እነዚህ ስሜቶች ተገቢ ያልሆነ ነገር እንድናደርግ፣ ደስታችንን እንድናጣ ብሎም ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት እንዲበላሽ ሊያደርጉ ይችላሉ።—መዝ. 37:8
13. የሚያጋጥመንን የፍትሕ መጓደል መቋቋም ከከበደን ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
13 እርግጥ ነው፣ መቼም ቢሆን የኢየሱስን ምሳሌ ፍጹም በሆነ መንገድ መከተል አንችልም። አንዳንድ ጊዜ፣ በኋላ ላይ የምንጸጸትበት ነገር ልንናገር ወይም ልናደርግ እንችላለን። (ያዕ. 3:2) በተጨማሪም የሚፈጸሙብን አንዳንድ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች ለመቋቋም የሚያዳግት አካላዊ ወይም ስሜታዊ ጠባሳ ትተውብን ሊያልፉ ይችላሉ። እናንተም እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟችሁ ከሆነ ይሖዋ ያላችሁበትን ሁኔታ እንደሚረዳ እርግጠኛ ሁኑ። በርካታ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን የተቋቋመው ኢየሱስም ስሜታችሁን ይረዳላችኋል። (ዕብ. 4:15, 16) ከኢየሱስ ፍጹም ምሳሌ በተጨማሪ ይሖዋ የፍትሕ መጓደልን እንድንቋቋም የሚረዱ ተግባራዊ ምክሮችን ሰጥቶናል። በዚህ ረገድ ሊረዱን የሚችሉ በሮም መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ጥቅሶችን እስቲ እንመልከት።
“ለቁጣው ዕድል ስጡ”
14. ለይሖዋ ‘ቁጣ ዕድል መስጠት’ ሲባል ምን ማለት ነው? (ሮም 12:19)
14 ሮም 12:19ን አንብብ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለይሖዋ ‘ቁጣ ዕድል እንዲሰጡ’ ክርስቲያኖችን መክሯቸዋል። ለይሖዋ ቁጣ ዕድል የምንሰጠው እሱ በመረጠው ጊዜና በመረጠው መንገድ ችግሩን እንዲያስተካክል በመፍቀድ ነው። ጆን የተባለ ወንድም ኢፍትሐዊ ድርጊት ከተፈጸመበት በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “በራሴ መንገድ ችግሩን ለማስተካከል ተፈትኜ ነበር። ሆኖም ሮም 12:19 ይሖዋን እንድጠብቅ ረድቶኛል።”
15. ችግሩን ይሖዋ እስኪያስተካክለው መጠበቅ የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው?
15 ይሖዋ ችግሩን እስኪያስተካክል መጠበቃችን ይጠቅመናል። እንዲህ ካደረግን፣ በራሳችን መንገድ ችግሩን ለመፍታት መሞከር ከሚያስከትለው ሸክምና ብስጭት እንጠበቃለን። ይሖዋ ሊረዳን ፈቃደኛ ነው። “ጉዳዩን ለእኔ ተዉት። እኔ ራሴ አስተካክለዋለሁ” እንዳለን ሊቆጠር ይችላል። ይሖዋ “እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” በማለት በገባው ቃል ከተማመንን እሱ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ችግሩን እንደሚያስተካክለው እርግጠኛ በመሆን ጉዳዩን ለእሱ መተው እንችላለን። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጆን እንዲህ ማድረጉ ረድቶታል። እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋን ከጠበቅኩ እሱ ከእኔ እጅግ በተሻለ መንገድ ጉዳዩን ይይዘዋል።”
“ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ”
16-17. ጸሎት ‘ምንጊዜም ክፉውን በመልካም እንድናሸንፍ’ የሚረዳን እንዴት ነው? (ሮም 12:21)
16 ሮም 12:21ን አንብብ። ጳውሎስ ‘ምንጊዜም ክፉውን በመልካም እንዲያሸንፉም’ ክርስቲያኖችን አበረታቷቸዋል። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ” ብሏል። (ማቴ. 5:44) እሱም ያደረገው ይህንኑ ነው። ሮማውያን ወታደሮች በእንጨት ላይ ሲቸነክሩት ከፍተኛ ሥቃይ ደርሶበታል። የደረሰበትን እንግልትና ውርደት ለመገመት እንኳ ያዳግታል።
17 ኢየሱስ የደረሰበት ግፍ እንዲያሸንፈው አልፈቀደም። እነዚያን ወታደሮች ከመርገም ይልቅ “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው” በማለት ጸልዮአል። (ሉቃስ 23:34) በደል ለሚያደርሱብን ሰዎች መጸለያችን የሚሰማንን ብስጭትና ቁጣ ለመቀነስ አልፎ ተርፎም በደል ላደረሱብን ሰዎች ያለንን አመለካከት ለመቀየር ሊረዳን ይችላል።
18. አልበርቶና ጆን የደረሰባቸውን የፍትሕ መጓደል እንዲቋቋሙ ጸሎት የረዳቸው እንዴት ነው?
18 ቀደም ሲል የተጠቀሱት ሁለት ወንድሞች ያጋጠማቸውን የፍትሕ መጓደል እንዲቋቋሙ ጸሎት ረድቷቸዋል። አልበርቶ እንዲህ ብሏል፦ “ፍትሕ የጎደለው ነገር ለፈጸሙብኝ ወንድሞች ጸለይኩ። የደረሰብኝን የፍትሕ መጓደል ለመርሳት እንዲረዳኝ ይሖዋን በተደጋጋሚ ለመንኩት።” ደስ የሚለው፣ አልበርቶ በድጋሚ ይሖዋን በታማኝነት እያገለገለ ነው። ጆን ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ለበደለኝ ወንድም ብዙ ጊዜ ጸለይኩለት። ለእሱ መጸለዬ በእሱ ላይ ከመፍረድ ይልቅ ለእሱ ሚዛናዊ አመለካከት እንዳዳብር ረድቶኛል። በተጨማሪም መጸለዬ የአእምሮ ሰላም ሰጥቶኛል።”
19. ይህ ሥርዓት እስኪያበቃ ድረስ ምን ማድረግ ይኖርብናል? (1 ጴጥሮስ 3:8, 9)
19 ይህ ሥርዓት እስኪያበቃ ድረስ ወደፊት ገና የትኞቹ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች እንደሚያጋጥሙን አናውቅም። ይሁንና ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ይሖዋ እንዲረዳን መጸለያችንን አናቋርጥ። በተጨማሪም ኢየሱስ ግፍ ሲደርስበት የሰጠውን ምላሽ መኮረጃችንንና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋላችንን እንቀጥል። እንዲህ ካደረግን የይሖዋን በረከት እንደምንወርስ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—1 ጴጥሮስ 3:8, 9ን አንብብ።
መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል
a ስሙ ተቀይሯል።
b ሐዋርያው ጴጥሮስ በመጀመሪያ ደብዳቤው ምዕራፍ 2 እና 3 ላይ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ በርካታ ክርስቲያኖች ጨካኝ በሆኑ ጌቶቻቸውና አማኝ ባልሆኑ ባሎቻቸው ኢፍትሐዊ ድርጊቶች እንደተፈጸሙባቸው ጠቅሷል።—1 ጴጥ. 2:18-20፤ 3:1-6, 8, 9
c ፍቅር እውነተኛ ሰላም የሚያስገኘው እንዴት ነው? የሚለውን ቪዲዮ jw.org ላይ ተመልከት።