መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
‘ወንጀልና የገንዘብ ፍቅር ብዙ ሥቃይ አስከትሎብኛል’
የትውልድ ዘመን፦ 1974
የትውልድ አገር፦ አልባኒያ
የኋላ ታሪክ፦ ሌባ፣ የዕፅ አዘዋዋሪ እንዲሁም እስረኛ የነበረ
የቀድሞ ሕይወቴ
የተወለድኩት የአልባኒያ ዋና ከተማ በሆነችው በቲራና ሲሆን ቤተሰቦቼ ድሆች ነበሩ። አባቴ ጥሩ ሰው ነው፤ ቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት ረጅም ሰዓት ይሠራል። ሆኖም ኑሯችን ከእጅ ወደ አፍ ነበር። ትንሽ ልጅ ሳለሁ ድሃ መሆናችን በጣም ያስከፋኝ ነበር። በልጅነቴ ለብዙ ዓመታት ጫማ አልነበረኝም፤ የምራብባቸው ጊዜያትም ነበሩ።
ገና ትንሽ ልጅ ሳለሁ መስረቅ ጀመርኩ። ቤተሰቤን እየረዳሁ እንዳለ አስብ ነበር። ከጊዜ በኋላ ፖሊስ ያዘኝ። ከዚያም በ1988 በ14 ዓመቴ አባቴ ወደ ተሃድሶ ትምህርት ቤት ላከኝ። በዚያ ሁለት ዓመት ቆይቼ የብየዳ ሙያ ተማርኩ። ከዚያ ስወጣ ስርቆት ለመተው ወስኜ ነበር፤ ሆኖም ሥራ ማግኘት አልቻልኩም። አልባኒያ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ በመግባቷ ሥራ አጥነት ተስፋፍቶ ነበር። ተስፋ ስለቆረጥኩ ከቀድሞ ጓደኞቼ ጋር መዋልና እንደገና መስረቅ ጀመርኩ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እኔና ጓደኞቼ ተይዘን የሦስት ዓመት እስር ተፈረደብን።
ከእስር ከተፈታሁ በኋላም ወንጀል መሥራቴን ቀጠልኩ። የአልባኒያ ኢኮኖሚ የተንኮታኮተ ሲሆን አገሪቷም ከፍተኛ ትርምስ ውስጥ ገባች። በእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት ሕገ ወጥ የሆኑ ሥራዎች እየሠራሁ ብዙ ገንዘብ አገኘሁ። በአንድ ወቅት መሣሪያ ታጥቀን ከዘረፍን በኋላ ከግብረ አበሮቻችን መካከል ሁለቱ ታሰሩ፤ እኔም ተይዤ የረጅም ጊዜ እስር እንዳይፈረድብኝ ስለሰጋሁ አገሪቱን ለቅቄ ተሰደድኩ። በዚያ ወቅት ከባለቤቴ ከዩሊንዳ ጋር ትዳር መሥርተን አንድ ወንድ ልጅ ወልደን ነበር።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከባለቤቴና ከልጄ ጋር ወደ እንግሊዝ ሄድን። እዚያ አዲስ ሕይወት ለመጀመር አስቤ ነበር፤ ይሁንና ልማዶቼን በቀላሉ መተው አልቻልኩም። ብዙም ሳይቆይ ወንጀል ውስጥ እንደገና ተዘፈቅኩ፤ በዚህ ወቅት ዕፅ አዘዋውር ስለነበር ብዙ ገንዘብ ማንቀሳቀስ ጀመርኩ።
ዕፅ በማዘዋወር ሥራ ላይ በመሰማራቴ ዩሊንዳ ምን ተሰምቷት ይሆን? ዩሊንዳ እንዲህ ብላለች፦ “አልባኒያ ውስጥ ልጅ ሳለሁ ከድህነት የምላቀቅበትን ጊዜ አልም ነበር። የተሻለ ሕይወት ለመምራት ስል ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ አልልም። ገንዘብ ሕይወታችንን እንደሚለውጥ አስብ ስለነበር አርታን ገንዘብ ለማግኘት ሲል ሲዋሽ፣ ሲሰርቅ፣ ዕፅ ሲያዘዋውር ወይም ማንኛውም ነገር ሲያደርግ እተባበረው ነበር።”
ከዚያም በ2002 ሕይወታችን በድንገት ተለወጠ፤ የነበረን ዕቅድና ሕልም ሁሉ መና ቀረ። ከፍተኛ መጠን ያለው ዕፅ ይዤ ስለተገኘሁ እንደገና ታሰርኩ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?
ምንም እንኳ እኔ ባይታወቀኝም መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወቴ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ጀምሮ ነበር። በ2000 ዩሊንዳ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምራ ነበር። እኔ አሰልቺ እንደሆነ ስለሚሰማኝ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የመወያየት ፍላጎት አልነበረኝም። ዩሊንዳ ግን ውይይቱን ወደደችው። እንዲህ ብላለች፦ “ሃይማኖተኛ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ስላደግኩ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅርና አክብሮት ነበረኝ። ከድሮም ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ለማወቅ ስለምጓጓ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስጀምር በጣም ተደሰትኩ። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን አሳማኝ ሆነው አገኘኋቸው። የተማርኩት ነገር በሕይወቴ ላይ አንዳንድ ለውጦች እንዳደርግ አነሳሳኝ። ለገንዘብ ያለኝ አመለካከት የተለወጠው ግን አርታን ሲታሰር ነው። ይህ ሁኔታ እንደ ማንቂያ ደወል ሆነልኝ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገንዘብ የሚናገረው ነገር እውነት እንደሆነ ተገነዘብኩ። ሀብታም ለመሆን ያላደረግነው ነገር የለም፤ ሆኖም ደስታ አላስገኘልንም። በመሆኑም የአምላክን መመሪያዎች ሙሉ በሙሉ መከተል እንዳለብኝ ተረዳሁ።”
በ2004 ከእስር የተፈታሁ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ እንደ ቀድሞው ዕፅ ለማዘዋወር ጥረት ማድረግ ጀመርኩ። ሆኖም የዩሊንዳ አስተሳሰብ ተቀይሮ ነበር፤ የተናገረችው ነገር ቆም ብዬ እንዳስብ አደረገኝ። “የምታመጣውን ገንዘብ አልፈልግም። እኔ የምፈልገው ባለቤቴና የልጆቼ አባት አብሮን እንዲሆን ነው” አለችኝ። በጣም ደነገጥኩ፤ ያለችው ነገር ግን ልክ ነው። ከቤተሰብ ተለይቼ በርካታ ዓመታት አሳልፌያለሁ። ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ገንዘብ ሳሳድድ የደረሰብኝ ችግር ሁሉ ፊቴ ድቅን አለ። ስለዚህ አኗኗሬን ለመቀየርና ከቀድሞ ጓደኞቼ ጋር ያለኝን ግንኙነት ለማቋረጥ ወሰንኩ።
በሕይወቴ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣው ከባለቤቴና ከሁለት ልጆቼ ጋር በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ መገኘቴ ነው። እዚያ ያገኘኋቸው ሰዎች ያሳዩኝ ወዳጃዊ ስሜት ልቤን በጣም ነካው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ።
ብዙ ገንዘብ ካካበትን ደስተኛ እንደምንሆን አስብ ነበር
መጽሐፍ ቅዱስን ሳጠና ‘የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር እንደሆነና አንዳንዶች በዚህ ፍቅር ተሸንፈው ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ እንደወጉ’ ተማርኩ። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ይህ ጥቅስ ምን ያህል እውነት እንደሆነ በራሴ ሕይወት አይቻለሁ! ቀደም ሲል የሠራኋቸው ስህተቶች በራሴም ሆነ በቤተሰቤ ላይ ያስከተሉት ጉዳት በጣም እንድጸጸት አድርጎኛል። (ገላትያ 6:7) ይሖዋም ሆነ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ስላላቸው ፍቅር መማሬ በባሕርዬ ላይ ለውጥ እንዳደርግ አነሳሳኝ። ከራሴ ይበልጥ ለሌሎች ማሰብ ጀመርኩ፤ ይህ ደግሞ ከቤተሰቤ ጋር ሰፋ ያለ ጊዜ እንዳሳልፍ ረድቶኛል።
ያገኘሁት ጥቅም
“አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በጣም ጠቅሞኛል። (ዕብራውያን 13:5) አሁን ውስጣዊ ሰላምና ንጹሕ ሕሊና አለኝ። ይህም ከዚህ በፊት አግኝቼ የማላውቀውን ደስታ እንዳጣጥም አስችሎኛል። ትዳሬ ይበልጥ ተጠናክሯል፤ ቤተሰቤም በጣም ተቀራርቧል።
ብዙ ገንዘብ ካካበትን ደስተኛ እንደምንሆን አስብ ነበር። አሁን ግን ወንጀልና የገንዘብ ፍቅር ብዙ ሥቃይ እንዳስከተለብኝ ተገንዝቤያለሁ። ሀብታም ባንሆንም በሕይወታችን ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር እንዳገኘን ይሰማኛል፤ ከይሖዋ አምላክ ጋር ወዳጅነት መመሥረት ችለናል። ቤተሰባችን በአንድነት ይሖዋን ማምለክ መቻሉ እውነተኛ ደስታ አስገኝቶለታል።