በራእይ ምዕራፍ 13 ላይ የተገለጸው ሰባት ራሶች ያሉት አውሬ ምን ያመለክታል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በራእይ 13:1 ላይ የተገለጸው ሰባት ራሶች ያሉት አውሬ በዓለም ላይ ያለውን የፖለቲካ ሥርዓት በሙሉ ያመለክታል።
አውሬው ሥልጣን፣ ኃይል እና ዙፋን እንዳለው መገለጹ ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነገርን እንደሚያመለክት ያሳያል።—ራእይ 13:2
“በነገድ፣ በሕዝብ፣ በቋንቋና በብሔር ሁሉ ላይ” ስለሚገዛ የአንድን አገር መንግሥት ብቻ ሊያመለክት አይችልም።—ራእይ 13:7
አውሬው በዳንኤል 7:2-8 ላይ የተገለጹት አራት አራዊት ያላቸውን ገጽታ አጣምሮ የያዘ ነው፤ ለምሳሌ የነብር መልክ አለው፤ እግሮቹ የድብ ናቸው፤ አፉ የአንበሳ ከመሆኑም ሌላ አሥር ቀንዶች አሉት። በዳንኤል ትንቢት ላይ የተጠቀሱት አራዊት፣ ነገሥታትን ወይም ፖለቲካዊ መንግሥታትን እንደሚያመለክቱ ተገልጿል፤ እነዚህ መንግሥታት በየተራ የሚነሱ ሲሆን ሰፊ ግዛቶችን ያስተዳድራሉ። (ዳንኤል 7:17, 23) በመሆኑም በራእይ ምዕራፍ 13 ላይ የተገለጸው አውሬ በርካታ ፖለቲካዊ ድርጅቶችን በቡድን ደረጃ የሚወክል ነው።
አውሬው የወጣው “ከባሕር” ነው፤ ባሕሩ የሚያመለክተው ዓመፀኛ የሆነውን አብዛኛውን የሰው ዘር ሲሆን ሁሉም መንግሥታት የሚነሱት ከዚህ የሰው ዘር ማኅበረሰብ ነው።—ራእይ 13:1፤ ኢሳይያስ 17:12, 13
መጽሐፍ ቅዱስ የአውሬው ቁጥር ወይም ስም 666 እንደሆነ ይህም “የሰው ቁጥር” መሆኑን ይገልጻል። (ራእይ 13:17, 18) ይህ አገላለጽ በራእይ ምዕራፍ 13 ላይ የተገለጸው አውሬ መንፈሳዊ አካልን ወይም አጋንንትን የሚወክል ሳይሆን ከሰዎች ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይጠቁማል።
በተለያዩ አገሮች የሚገኙ መንግሥታትና አገዛዞች በብዙ ነገሮች ባይስማሙም እንኳ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር አለ፤ ሁሉም ለአምላክ መንግሥት ከመገዛት ይልቅ ሥልጣናቸውን ይዘው መቆየት ይፈልጋሉ። (መዝሙር 2:2) በተጨማሪም በአርማጌዶን ጦርነት ላይ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራውን የአምላክን ሠራዊት ለመግጠም ሁሉም በኅብረት ይወጣሉ፤ ነገር ግን በዚህ ጦርነት ላይ ሁሉም ይጠፋሉ።—ራእይ 16:14, 16፤ 19:19, 20
“አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች”
በራእይ ምዕራፍ 13 ላይ የተገለጸው አውሬ “አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች” ምን እንደሚያመለክቱ በትክክል ለማወቅ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በሌላ ቦታ ላይ የተገለጸውን ‘የአውሬውን ምስል’ ማንነት ማወቃችን አስፈላጊ ነው፤ የአውሬው ምስል፣ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች እንዳሉት የተገለጸ ሲሆን ቀለሙም ደማቅ ቀይ ነው። (ራእይ 13:1, 14, 15፤ 17:3) መጽሐፍ ቅዱስ፣ የዚህ ቀይ አውሬ ሰባት ራሶች “ሰባት ነገሥታት” ወይም መንግሥታት እንደሆኑ ይገልጻል።—ራእይ 17:9, 10
በተመሳሳይም በራእይ 13:1 ላይ የተገለጸው አውሬ ሰባት ራሶች ሰባት መንግሥታትን ይወክላሉ፤ እነዚህ መንግሥታት በታሪክ ገናና የነበሩና በአምላክ ሕዝብ ላይ ጭቆና ያደረሱ የዓለም ኃያል የፖለቲካ ኃይሎችን ያመለክታሉ፤ እነሱም ግብፅ፣ አሦር፣ ባቢሎን፣ ሜዶ ፋርስ፣ ግሪክ፣ ሮምና አንግሎ አሜሪካ ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ቁጥሮች ምሳሌያዊ ትርጉም አላቸው። ለምሳሌ፣ አሥር ሙላትን በሌላ አባባል አንድን ነገር ሙሉ በሙሉ ይወክላል። በመሆኑም አሥሩ ቀንዶች፣ ትናንሽና ትላልቅ ሉዓላዊ መንግሥታትን በሙሉ ያመለክታሉ ብለን መደምደም እንችላለን፤ በእያንዳንዱ ቀንድ ላይ ዘውድ መኖሩ ደግሞ እነዚህ ሉዓላዊ መንግሥታት የራሳቸው ሥልጣን እንዳላቸውና በወቅቱ በሥልጣን ላይ ካለው የዓለም ኃያል መንግሥት ጋር ተመሳሳይ በሆነ ጊዜ ላይ እንደሚገዙ እንደሆኑ ያመለክታል።