የዓለም ፍጻሜ ምን ያህል ቀርቧል?
ብዙ ክፍሎች ያሉት ጥምር ምልክት
አንድ የህንድ ተረት አንድ ዝሆን ለማየት ስለ ሄዱ ስድስት የኢንዱስታን ዓይነ ስውሮች ይናገራል። አንደኛው የዝሆኑን ጎን ዳስሶ “የፈጣሪ ያለህ! ዝሆን ልክ ግድግዳ ይመስላል” አለ። ሁለተኛው ዓይነ ስውር የዝሆኑን ጥርስ ይዳስስና “ዝሆን ልክ ጦር ይመስላል” አለ። ሦስተኛው ኩንቢውን ይዳስስና “ዝሆን ከእባብ ጋር በጣም ይመሳሰላል” ይላል። አራተኛው ደግሞ የእግሩን ጉልበት ይዳብስና “ዝሆን ዛፍ እንደሚመስል ምንም ጥርጥር የለውም” አለ። አምስተኛው የዝሆኑን ጆሮ ይዳስስና “ይህ ዝሆን የሚባለው አስደናቂ እንስሳ ማራገቢያ ይመስላል” አለ። ስድስተኛው ደግሞ የዝሆኑን ጅራት ይይዝና “ለካስ ዝሆን ገመድ የሚመስል እንስሳ ነው!” ይላል። ስድስቱም ዓይነ ስውራን ዝሆን ይህን ይመስላል፣ ያን ይመስላል እያሉ ለረዥም ጊዜ እየተጯጯሁ ሲከራከሩ ቆዩ። ይሁን እንጂ አንዳቸውም ቢሆኑ ትክክለኛውን የዝሆን መልክ ሊያውቁ አልቻሉም ነበር። ያልተሟላ መረጃ የተሟላ ግንዛቤ ሊያስገኝ አይችልም።
የክርስቶስን መገኘት በሚያረጋግጡት ምልክቶችም ረገድ ተመሳሳይ ችግር ይፈጠራል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ “ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድን ነው?” በማለት ላቀረቡለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል። “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፣ ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ሥፍራ ቸነፈር፣ ራብም ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:3፤ ሉቃስ 21:10, 11) ይሁን እንጂ ሰዎች እነዚህ ምልክቶች ብቻ ኢየሱስ በ1914 እንደመጣ የሚያረጋግጡ ምልክቶች ናቸው ተብሎ ሲነገራቸው “ጦርነት፣ ረሀብ፣ ቸነፈርና የምድር መናወጥ ያልነበረበት ጊዜ ኖሮ አያውቅም” ይላሉ። ትክክልም ናቸው።
እነዚህ ጥቂት ምልክቶች በጣም ከፍተኛ ጭንቀትና እልቂት ያስከተሉ ቢሆኑም ለብዙ ሰዎች የክርስቶስን መመለስ ለማረጋገጥ የሚበቁ ምልክቶች አይደሉም። ምልክቱ የተሟላና የማያሳስት እንዲሆን ተጨማሪ ነገር ያስፈልጋል። ከምልክቱ ክፍሎች በአንዱ ወይም በጥቂቶቹ ብቻ ተመሥርቶ የዓለም ፍጻሜ ቀርቧል ብሎ ማወጅ የሐሰት ማስጠንቀቂያ ከመሆን አያልፍም። አንደኛው ወይም ጥቂቶቹ ብቻ ሳይሆኑ ኢየሱስ ስለሚመለስበት ጊዜ የተናገረው ምልክት ክፍሎች በሙሉ መፈጸም ይኖርባቸዋል። ኢየሱስ ስለመገኘቱ የሰጠው ምልክት የተለያዩ ምልክቶች ጥምር ነው። እነዚህ የተለያዩ የምልክቱ ክፍሎች አንድ ላይ ተጣምረውና ተቀናጅተው ኢየሱስ የሚገኝበትን ጊዜ በማያሻማ ሁኔታ ያረጋግጡልናል።
ጥምር ስለሆነ ምልክት ምሳሌ እንዲሆነን በኢየሱስ የመጀመሪያ ምጽአት ጊዜ እርሱ መሲሕ መሆኑን ስለሚያረጋግጡ ምልክቶች መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን እንመልከት። እነዚህ ምልክቶች በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስለ መሲሑ የተነገሩትን ብዙ ክንውኖች የሚያጠቃልሉ ናቸው። ኢየሱስ እነዚህን ጥቅሶች ለደቀ መዛሙርቱ ጠቅሶ ነበር። እነርሱ ግን የጥቅሶቹን ሙሉ ትርጉም በጊዜው አልተገነዘቡም። ደቀ መዛሙርቱ እንደተቀሩት አይሁዶች መሲሑ የሮምን መንግሥት ገልብጦ በእነርሱ ተባባሪነት መላውን ዓለም እንዲገዛ ይፈልጉ ነበር። በዚህም ምክንያት በተገደለ ጊዜ ግራ ተጋብተው የሚይዙት የሚጨብጡት ጠፋቸው። ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ እንዲህ አላቸው። “ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው። በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው።”—ሉቃስ 24:44, 45
ኪንግደም ኢንተርሊንየር ቁጥር 45ን በተረጎመው መሠረት ኢየሱስ መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ ያስቻላቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የዕብራይስጥ ክፍል ውስጥ ስለሚመጣው መሲሕ የአኗኗር ሁኔታና ክንውኖች የተነገሩትን ትንቢቶች ኢየሱስ በእነዚህ ትንቢቶች መሠረት ካደረጋቸው ነገሮች ጎን ለጎን አስቀምጦ በማስረዳት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስም ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን በማስረጃዎች ባረጋገጠበት ጊዜ በዚህ ዓይነት ዘዴ ተጠቅሟል። (ሥራ 17:3) እዚህም ላይ ኪንግደም ኢንተርሊንየር በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተነገሩትን መሲሐዊ ትንቢቶች ትንቢቶቹ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ከተፈጸሙባቸው ሁኔታዎች ጋር “ጎን ለጎን በማስቀመጥ በጥልቀት ገለጠላቸው” በማለት ጳውሎስ ያስረዳበትን መንገድ ይገልጽልናል። ከእነዚህ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ከተፈጸሙትና ኢየሱስ ትንቢት የተነገረለት መሲሕ መሆኑን ካረጋገጡት የዕብራይስጥ ትንቢቶች ውስጥ ብዙዎቹ በሚቀጥለው ገጽ ላይ ባለው ሣጥን ውስጥ ተዘርዝረዋል። ጥምር ምልክት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ የሚያስረዳ ጥሩ ምሳሌ ነው።
የክርስቶስ መገኘት ጥምር ምልክት
ለኢየሱስ ዳግም ምጽአት ወይም ይበልጥ ትክክለኛ በሆነው አነጋገር መሠረት ለኢየሱስ መገኘት ምልክት የሚሆነው ይህ ዓይነት ጥምር ምልክት ብቻ ነው። ብዙ ተርጓሚዎች በማቴዎስ 24:3 ላይ “መምጣት” ብለው የተረጎሙት ፓሩሲያ የተባለ የግሪክኛ ቃል የሚመጣበትን ወይም የሚደርስበትን ጊዜ የሚያመለክት ሳይሆን የደረሰ ወይም የተገኘ መሆኑን የሚያመለክት ቃል ነው። ኢየሱስ በማይታይ ሁኔታ ይሖዋ ያነገሠው ንጉሥ ሆኖ መገኘቱንና በሰማይ ሆኖ መግዛት መጀመሩን ያመለክታል። ይህም ኢየሱስ በዮሐንስ 14:19 ላይ “ገና ጥቂት ዘመን አለ፣ ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም” ሲል ከተናገረው ቃል ጋር ይስማማል። በአካል የሚታይበት ጊዜ ስለማይኖር ይሖዋ ያነገሠው ንጉሥ ሆኖ መመለሱንና በማይታይ ሁኔታ መገኘቱን የሚያሳይ ምልክት ሰጣቸው።
የሰጣቸው ምልክት አንድ ወይም ጥቂት ክፍሎች ብቻ ያሉት ምልክት አይደለም። መሲሕ ሆኖ በመጣበት የመጀመሪያ ጊዜ እንደተፈጸመው ጥምር ምልክት እንደ አንድ ጥምር ምልክት የሚወሰዱ ብዙ ክፍሎች ያሉት ምልክት ነበር። በዚህ መንገድ በብዙ ክንውኖች ወይም ክስተቶች በሰማይ ይሖዋ ያነገሠው ንጉሥ በመሆንና ሥልጣኑንና ኃይሉን ወደ ምድር ጉዳዮች ዘወር በማድረግ በማይታይ ሁኔታ መገኘቱን በማያሳስት ሁኔታ ያመለክታል። ለሐሰተኛ ማስጠንቀቂያ ምክንያት የሚሆነው ጥምር ለሆኑት ጠቅላላ ምልክቶች ሳይሆን ለአንድ ወይም ለሁለት የተወሰኑ ምልክቶች ትኩረት ሲደረግ ነው። የኢንዱስታኑ ስድስት ዓይነ ስውራን እንዳደረጉት ማለት ነው። እያንዳንዳቸው አንዱን የተወሰነ የዝሆን አካል ክፍል ብቻ በመዳሰሳቸው የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።
ኢየሱስ የተናገረው ጥምር ምልክትና ሦስት ሐዋርያት የገለጿቸው ተጨማሪ ሁኔታዎች በአስደናቂ ሁኔታ መፈጸም የጀመሩት በ1914 ነው። እነዚህ ምልክቶችና የምልክቶቹ አፈጻጸም ከዚህ በታች ተዘርዝሯል።
ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል።” (ማቴዎስ 24:7) የመጀመሪያው ዓለም ጦርነት በ1914 ጀመረ። በጦርነቱ የተካፈሉት 28 ብሔራት ሲሆኑ 14 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ተገድለውበታል። ሁለተኛው ዓለም ጦርነት ተከተለ፤ በጦርነቱ 59 ብሔራት የተካፈሉ ሲሆን 50 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ተገድለዋል።
“በልዩ ልዩ ሥፍራ ቸነፈር” (ሉቃስ 21:11) የመጀመሪያው ዓለም ጦርነት እንዳበቃ 21 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በስፓኒሽ ፍሉ ሕይወታቸውን አጡ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በልብ በሽታ፣ በካንሰር፣ በኤድስና በሌሎች ወረርሽኝ በሽታዎች ሞተዋል።
“ራብም . . . ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:7) በታሪክ ዘመናት በሙሉ እጅግ አስከፊ የሆነው ረሀብ ዓለምን የመታው ከመጀመሪያው ዓለም ጦርነት በኋላ ነበር። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ደግሞ ሌላ አሰቃቂ የሆነ ረሀብ ተከስቷል። በአሁኑ ጊዜ ከጠቅላላው የዓለም ሕዝብ አንድ አምስተኛ የሚሆነው የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘት ይሠቃያል። በየዓመቱ 14 ሚልዮን የሚያክሉ ሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘት ምክንያት ይሞታሉ።
“ታላቅም የምድር መናወጥ . . . ይሆናል።” (ሉቃስ 21:11) ከ1914 ወዲህ ከተነሡት ዋና ዋና የምድር መናወጦች ጥቂቶቹን እንመልከት። በ1915 በኢጣልያ 32, 610 ሰዎች ሞተዋል። በ1920 በቻይና 200,000 ሰዎች ሞተዋል። በ1923 በጃፓን 143,000 ሰዎች ተገድለዋል። በ1939 በቱርክ 32,700 ሰዎች ተገደሉ። በ1970 በፔሩ 66,800 ሰዎች ሞተዋል። በ1976 በቻይና 240,000 ሰዎች (አንዳንዶች 800,000 ይላሉ) ሞተዋል። በ1988 በአርሜንያ 25,000 ሰዎች ተገድለዋል።
“የዓመፃ ብዛት” (ማቴዎስ 24:12) ከ1914 ወዲህ ዓመፅ ተስፋፍቷል። በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በዝቷል። ነፍስ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ዘረፋ፣ የቡድን ውጊያ ዋነኞቹ የዓለም ዜና ርዕሶች ሆነዋል። ፖለቲከኞች ሕዝቦቻቸውን ይመዘብራሉ፣ ወጣቶች ሰዎችን ለመግደል ጠመንጃ አንግተው ይዞራሉ፣ ተማሪዎች እርስ በርሳቸው ይባላሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች በቀን እንኳን መንገድ ላይ መዘዋወር አደገኛ ሆኗል።
“በምድር ላይም አሕዛብ . . . እያመነቱ ይጨነቃሉ። ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ።” (ሉቃስ 21:25, 26) ወንጀል፣ ዓመፅ፣ የዕፅ ሱሰኝነት፣ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት፣ ሥራ ማጣት፣ የችግሩን ዓይነት ዘርዝሮ መጨረስ የሚቻል አይመስልም። ከቀን ወደ ቀንም ይጨምራል። አንድ እውቅ ሳይንቲስት “ፍርሃት እንበላለን፣ በፍርሃት እንተኛለን፣ በፍርሃት እንኖራለን፣ በፍርሃት እንሞታለን” ሲሉ ጽፈዋል።
“በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ሐዋርያው ጳውሎስ የሥነ ምግባር ስሜታቸው ስለደነዘዘባቸው ሰዎች ተናግሯል። (ኤፌሶን 4:19 አዓት ) በተጨማሪም “በመጨረሻው ቀን” ይኖራል ብሎ ስለተነበየው የሥነ ምግባር መበላሸት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥቷል። ጳውሎስ የጻፈው ቃል ዛሬ የምንሰማውን ዕለታዊ ዜና ይመስላል። “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1–5
“በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ።” (2 ጴጥሮስ 3:3) ጋዜጦች፣ በቴሌቪዥን በሚቀርቡ ዜናዎች፣ መጽሔቶች፣ መጻሕፍትና ፊልሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይዘባበታሉ። ጴጥሮስ እንደተነበየውም “የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና” እያሉ የአምላክን ቃል በራሳቸው ነፃ አስተሳሰብ ላይ በተመሠረተው ፕሮፓጋንዳቸው ተክተዋል።—2 ጴጥሮስ 3:4
“እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ፣ ያሳድዱአችሁማል።” (ሉቃስ 21:12) የይሖዋ ምሥክሮች ከ1914 ወዲህ ባሉት ዓመታት በጭካኔ ታስረዋል፣ በሐሰት ተወንጅለዋል፣ በረብሸኞች ተደብድበዋል። በሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በሂትለር ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ተወርውረው ብዙ ሥቃይ ተቀብለዋል፣ ብዙዎቹ ተገድለዋል፣ አንዳንዶቹም ተሰይፈዋል። በዲሞክራቲክና በአምባ ገነኖች በሚተዳደሩ ሌሎች አገሮች ደግሞ ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ የመመሥከር ሥራቸው ታግዷል። በወህኒ ቤቶችም እንዲጣሉ ተደርጓል። ይህ ሁሉ የደረሰባቸው በኢየሱስ ትንቢት መሠረት ነው።—ማቴዎስ 5:11, 12፤ 24:9፤ ሉቃስ 21:12፤ 1 ጴጥሮስ 4:12, 13
“ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል።” (ማቴዎስ 24:14) ይህ የሚሰበከው ወንጌል ወይም ምሥራች የትኛው ነው? የክርስቶስ መንግሥት ሰማይ ሆኖ መግዛት የመጀመሩ ምሥራች ነው። ምክንያቱም ኢየሱስ ይህን ጥምር ምልክት እንዲናገር ያደረገው የዚህን መንግሥት መቋቋም የሚመለከት ጥያቄ ነው። ይህ ምሥራች ከ1914 ጀምሮ በይሖዋ ምሥክሮች ሲሰበክ ቆይቷል። በ1919 ይህን ምሥራች ይሰብኩ የነበሩት ሰዎች አራት ሺህ ሲሆኑ በ1990 ከአራት ሚልዮን በላይ፣ በ1993 አንድ ወር ላይ 4,709,889 ደርሶ ነበር። በ200 ቋንቋዎች የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች በ229 አገሮች ተሠራጭተዋል። ይኸኛው የጥምር ምልክቱ ክፍል ይህን የሚያክል ፍጻሜ ያገኘበት ሌላ ዘመን የለም።
“ምድርንም የሚያጠፉትን ታጠፋ ዘንድ ዘመን መጣ።” (ራዕይ 11:18) ስግብግብ ሰዎች ለስስት ጥቅማቸው ሲሉ ምድርን ለማጥፋት ፈቃደኛ ያልሆኑበት ጊዜ የለም። ምድርን ለማጥፋት የሚያስችላቸውን ኃይል ግን ያገኙት በዚህ በእኛ ትውልድ ነው። ከ1914 ወዲህ ባለው በዚህ ዘመን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ምድርን ለማጥፋት የሚያስችላቸውን ኃይል አስገኝቶላቸዋል። በዚህ ባገኙት ኃይል አለአግባብ በመጠቀም ላይ ናቸው። ምድርን በማበላሸት ላይ ይገኛሉ።
በዚህ ምክንያት ከደረሱት ጥፋቶች መካከል አንዳንዶቹ:- የአሲድ ዝናብ፣ የምድር ሙቀት መጨመር፣ የዖዞን ሽፋን መሳሳት፣ አደገኛ የሆኑ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች፣ የመርዛማ ቆሻሻዎች ማጠራቀሚያዎች፣ የቆሻሻ መብዛት፣ ከኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎች የሚወጡ ቆሻሻዎች፣ በውቅያኖሶች የሚፈሰው ነዳጅ ዘይት፣ ከየቤቱ ለሚወጡት ፍሳሾች መጣያ ማጣት፣ ሕይወት አልባ የሆኑ ሐይቆች፣ የደኖች መውደም፣ የከርሰ ምድር ውኃ መበከል፣ የአራዊትና የዕፀዋት ዝርያዎች እልቂት፣ የሰው ልጅ ጤና መታወክ ናቸው።
ባሪ ኮሞነር የተባሉት ሳይንቲስት እንዲህ ብለዋል:- “የምድር መበከል እልባት ካልተደረገለት ይህች ፕላኔታችን ለሰው ዘር መኖሪያነት አመቺ መሆንዋ ይቀራል። . . . ችግሩ የመጣው ሳይንሳዊ እውቀት ከማጣት ሳይሆን ሆን ብሎ ከመስገብገብ ነው።” ስቴት ኦቭ ዘ ወርልድ 1987 “የሰው ልጅ እንቅስቃሴ እየጨመረ መሄዱ የምድርን ለኑሮ አመቺነት ትልቅ አደጋ ላይ መጣል ጀምሯል” ይላል። በ1990 የተሠራጨ አንድ ተከታታይ የቴሌቪዥን ፕሮግራም “ፕላኔታችንን ለማዳን የሚደረግ ሩጫ” የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል።
እነዚህን የሚያክሉ ብዙ ሁኔታዎች በአንድ ትውልድ ዘመን ውስጥ እንደ አንድ ምልክት በአንድነት መፈጸማቸው እንዲሁ በአጋጣሚ የሆነ ነው ተብሎ ገሸሽ የሚደረግ ነገር አይደለም። የሁኔታዎቹ መጠን ከፍተኛ መሆኑ ራሱ በአሳሳቢነቱ ላይ ክብደት ይጨምራል። ከእነዚህ ምልክቶች መካከል እንደ ምሥራቹ መልእክት በዓለም በሙሉ መሰበክና እንደ ምድር መበላሸት ያሉት ምልክቶች ከፍጥረት ዘመን ጀምሮ ተፈጽመው የማያውቁ ናቸው። የክርስቶስ መገኘት ጥምር ምልክት በጣም የሚያስደንቅ ነው።
“የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።”—ማርቆስ 4:23
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የመሲሑን የመጀመሪያ ምጽአት ያመለከተ ጥምር ምልክት
ከይሁዳ ነገድ ይወለዳል (ዘፍጥረት 49:10)፣ ይጠላል፣ ከሐዋርያቱ አንዱ አሳልፎ ይሰጠዋል፣ በመጎናጸፊያው ላይ ዕጣ ይጣጣላሉ፣ ኮምጣጤና ሐሞት ይሰጠዋል፣ በእንጨት ላይ እንደተሰቀለ ይሰደባል፣ አጥንቶቹ አይሰበሩም፣ መበስበስን አያይም፣ ከሙታን ይነሣል። (መዝሙር 69:4፤ 41:9፤ 22:18፤ 69:21፤ 22:7, 8፤ 34:20፤ 16:10) ከድንግል ይወለዳል፣ የዳዊት ዘር ይሆናል፣ የእንቅፋት ድንጋይ ይሆናል፣ ሰዎች አይቀበሉትም፣ በከሳሾቹ ፊት አይናገርም፣ ሕማማችንን ይሸከማል፣ ከኃጢአተኞች ጋር ይቆጠራል፣ መሥዋዕት ሆኖ ይሞታል፣ ጎኑ ይወጋል፣ ከባለጠጎች ጋር ይቀበራል (ኢሳይያስ 7:14፤ 11:10፤ 8:14, 15፤ 53:3፤ 53:7፤ 53:4፤ 53:12፤ 53:5፤ 53:9) ከግብፅ ይጠራል (ሆሴዕ 11:1)፤ በቤተ ልሔም ይወለዳል (ሚክያስ 5:2)፣ ንጉሥ ሆኖ ይሰጣል፣ በአህያ ላይ ይቀመጣል፣ በ30 ብር ይሸጣል፣ ተከታዮቹ ይበተናሉ።—ዘካርያስ 9:9፤ 11:12፤ 13:7
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ኢየሱስ በዳግም ምጽአቱ በንጉሣዊ ክብሩ መገኘቱን የሚያመለክት ጥምር ምልክት
ዓለም አቀፍ ጦርነት፣ ረሀብ፣ ቸነፈር፣ የምድር መናወጥ (ማቴዎስ 24:7፤ ሉቃስ 21:10, 11፤ ራእይ 6:1–8) የዓመፃ መብዛት፣ እርስ በርስ መጠላላትና አሳልፎ መሰጣጣት፣ ለወላጆች አለመታዘዝ፣ የተፈጥሮ ፍቅር መጥፋት፣ ራስን አለመግዛት፣ ለመስማማት ፈቃደኛ አለመሆን፣ ገንዘብ ወዳድነት፣ ከአምላክ ይበልጥ ተድላ ወዳድ መሆን፣ ኃይሉን እየካዱ የአምልኮ መልክ መያዝ፣ ዘባችነት፣ ጨካኞች፣ የክርስቶስን ተከታዮች ማሳደድ፣ ወደ ሸንጎ ማቅረብና መግደል (ማቴዎስ 24:9, 10, 12፤ ሉቃስ 21:12፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) ስለ ኢየሱስ መገኘት መዘበት፣ ሁሉ ነገር ከፍጥረት ጀምሮ እንዳለ ነው ማለት (2 ጴጥሮስ 3:3, 4) የምድርን አካባቢ ማበላሸት—ራእይ 11:18