የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
በአምላክ ፊት ዋጋ አላችሁ!
“በአብዛኛው የሕይወቴ ዘመን የማልረባ ሰው ነኝ የሚል ስሜት ሲያሰቃየኝ ኖሯል። ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር ወይም እርሱን ለማገልገል የማደርገው ጥረት ምንም ያህል ቢሆን ምንጊዜም በቂ እንዳልሆነ ይሰማኛል” ስትል አንዲት ክርስቲያን ጽፋለች።
ለምንም ነገር የምበቃ ሰው አይደለሁም ወይም ምንም ዋጋ የለኝም ከሚል ሥር የሰደደ ስሜት ጋር የሚታገል ሰው ታውቃለህ? ወይም አንተ ራስህ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ስሜት ያድርብሃል? ይህ ስሜት በአምላክ ታማኝ አምላኪዎች ላይም እንኳ ሳይቀር መከሰቱ እንግዳ ነገር አይደለም። ማንኛውም ሰው በዚህ “የሚያስጨንቅ ዘመን” ውስጥ መኖር ከሚያስከትላቸው ተጽእኖዎች ነፃ አይደለም። ብዙዎች “በመጨረሻው ቀን” በእጅጉ ተስፋፍተው የሚገኙ ባሕርያት በሚታዩባቸው ማለትም ‘ራሳቸውን በማይገዙ፣ ጨካኝ በሆኑና መልካም የሆነውን በማይወዱ’ ግለሰቦች ችላ ይባላሉ እንዲሁም ጥቃት ይደርስባቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) እንደዚህ ዓይነት አሳዛኝ ገጠመኞች ስር የሰደደ የስሜት ጠባሳ በመተው ሙሉ በሙሉ የባዶነት ስሜት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
በሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ አሉታዊ ስሜቶች የሚከሰቱት ሰዎች ከልክ በላይ ከፍተኛ የሆኑ መስፈርቶችን ለራሳቸው በማውጣታቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል። እነዚህ መስፈርቶች ላይ መድረስ አለመቻላቸው ምንጊዜም ብቁ እንዳልሆኑ የሚሰማቸውን ስሜት ያባብሰዋል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ካደረባቸው የከንቱነት ስሜት ጋር የሚታገሉ ሰዎች አምላክ ወይም ሌላ ማንኛውም ሰው እነርሱን የሚያፈቅርበት ምክንያት አልታይ ሊላቸው ይችላል። እንዲያውም ፈጽሞ ተወዳጅ እንዳልሆኑ ሊሰማቸውም ይችላል።
ሆኖም ይሖዋ አምላክ እንዲህ ዓይነት ስሜት የለውም! ይሖዋ የእርሱ ተቀናቃኝ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ከሚጠቀምባቸው “የማታለያ ዘዴዎች” ራሳችንን እንድንጠብቅ በቃሉ አማካኝነት አስጠንቅቆናል። (ኤፌሶን 6:11 ጁውሽ ኒው ቴስታመንት) ሰይጣን አምላካችንን ማምለክ እንድናቆም ለማድረግ የማታለያ ዘዴዎቹን ይጠቀማል። ይህን ለማሳካት ሰይጣን የማንረባ እንደሆንንና በይሖዋ ዘንድ ጨርሶ ተወዳጅ መሆን እንደማንችል እንዲሰማን ለማድረግ ይሞክራል። ይሁን እንጂ ሰይጣን “ሐሰተኛ” ብቻ ሳይሆን “የሐሰትም አባት” ነው። (ዮሐንስ 8:44) በመሆኑም በእርሱ የማታለያ ዘዴዎች መታለል የለብንም! ይሖዋ ያለውን ስሜት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመግለጽ በእርሱ ፊት ዋጋ እንዳለን አረጋግጦልናል።
ስለ ራሳችን ዋጋማነት ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ
መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ መቁረጥ ሊያስከትልብን ስለሚችለው አሉታዊ ተጽእኖ ይናገራል። ምሳሌ 24:10 “በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው” ሲል ይገልጻል። በውስጣችን ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ አሉታዊ ስሜት ማሳደራችን ደካማና ለአደጋ የተጋለጥን እንድንሆን በማድረግ አቅም ሊያሳጣን ይችላል። ሰይጣን ይህን አሳምሮ እንደሚያውቅ አትጠራጠሩ። ልባችን በከንቱነት ስሜት መዋጡ ራሱ አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጥራል። ሆኖም ሰይጣን በእንዲህ ዓይነቱ ስሜት ለመጠቀም ሲሞክር ሁኔታውን ከበፊቱ የባሰ አዳጋች ያደርገዋል።
ስለዚህ ስለ ራሳችን ዋጋማነት ጤናማ የሆነ ሚዛናዊ አመለካከት መያዛችን አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል አጥብቆ አሳስቧል:- “እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ . . . እናገራለሁ።” (ሮሜ 12:3) አንድ ሌላ ትርጉም እነዚህን ቃላት በዚህ መንገድ አስቀምጧቸዋል:- “ማንም ስለራሱ ዋጋማነት በልክ እንዲያስብ እንጂ የተጋነነ አመለካከት እንዳይኖረው እላለሁ።” (ቻርለስ ቢ ዊልያምስ) ስለዚህ ቅዱስ ጽሑፉ ስለራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ያበረታታናል። በአንድ በኩል ራሳችንን ከትዕቢት መንፈስ መጠበቅ ያለብን ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ሌላኛው ጽንፍ ላለመሄድ መጣር አለብን። ምክንያቱም ጳውሎስ ጤናማ አስተሳሰብ እንዲኖረን ሲመክረን ስለራሳችን አንድ ዓይነት ግምት መያዝ አስፈላጊ እንደሆነ መናገሩ ነበር። አዎን፣ ጳውሎስ በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት እያንዳንዳችን በይሖዋ ፊት ዋጋ እንዳለን ገልጿል።
ኢየሱስ “ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ” ሲል የተናገራቸው ቃላትም ለራስ ዋጋ ስለመስጠት ሚዛናዊ አመለካከት መያዝን የሚጠቁሙ ናቸው። (ማቴዎስ 22:39) “እንደ ነፍስህ” የሚሉት ቃላት በተወሰነ መጠን ለራሳችን የዋጋማነት ወይም የአክብሮት ስሜት ሊኖረን እንደሚገባ ያሳያሉ። ጉድለት እንዳለብንና ስህተት እንደምንሠራ የታወቀ ነው። ሆኖም አምላክን ለማስደሰት ስንጥር፣ በሠራናቸው ስህተቶች ስናዝንና ምህረቱን ስንለምን በተወሰነ መጠን ለራሳችን ጥሩ ግምት ይኖረናል። ወቀሳ የሚያበዛው ልባችን ለራሳችን ያለንን ጥሩ ግምት እንድናጣ ሊገፋፋን ቢችልም ‘እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ መሆኑን’ መርሳት የለብንም። (1 ዮሐንስ 3:20) በሌላ አባባል ይሖዋ እኛን የሚያየው እኛ ራሳችንን ከምናይበት መንገድ ፈጽሞ በተለየ ሁኔታ ሊሆን ይችላል።
የተሰበረ ልብና የተደቆሰ መንፈስ
መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፣ መንፈሳቸው የተሰበረውንም [“የተደቆሰውንም፣” NW] ያድናቸዋል።” (መዝሙር 34:18) ማቲው ሄንሪስ ኮሜንታሪ ኦን ዘ ሆል ባይብል በዚህ ጥቅስ ላይ ሐሳብ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል:- “ብዙውን ጊዜ የጻድቃን . . . ልብ የተሰበረ ከመሆኑም በላይ መንፈሳቸው በሐዘን የተደቆሰ ነው። በኃጢአት የተነሳ ራሳቸውን አቅልለው የሚመለከቱና የባዶነት ስሜት የሚሰማቸው ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የሚመለከቱ ሲሆን ባላቸው መልካም ባሕርይ አይመኩም።”
‘ልባቸው የተሰበረ’ ወይም ‘መንፈሳቸው የተደቆሰ’ ሰዎች ይሖዋ ከእነርሱ በጣም እንደራቀ ሆኖ ሊሰማቸው የሚችል ከመሆኑም በላይ ከቁብ የሚቆጠሩ ባለመሆናቸው ይሖዋ ለእነርሱ ሊያስብ እንደማይችል አድርገው ያስቡ ይሆናል። ሆኖም ጉዳዩ የዚህ ተቃራኒ ነው። ይሖዋ “ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የሚመለከቱ” ሰዎችን እንደማይተው የዳዊት ቃላት ያረጋግጡልናል። ሩኅሩኅ የሆነው አምላካችን በእንዲህ ዓይነቱ ወቅት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ እንደምንፈልገው ስለሚያውቅ ከጎናችን ይሆናል።
አንድ ምሳሌ ተመልከት። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አንዲት እናት የሁለት ዓመት ልጅዋ ለቅዳ በተባለው (የመተንፈስ ችግር) ከባድ ሕመም እየተሰቃየ ስለነበረ በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል ወሰደችው። ዶክተሮቹ ልጁን ከመረመሩት በኋላ በዚያ ምሽት ልጁ ሆስፒታል ማደር እንዳለበት ለእናትየው ነገሯት። እናትየው የዚያን ዕለት ማታ የት አደረች? በሆስፒታሉ ክፍል ውስጥ የልጅዋ አልጋ አጠገብ ወንበር ላይ ተቀምጣ ነበር ያደረችው። ትንሹ ልጅዋ ታምሞ ስለነበር እዚያው ከጎኑ መሆን ነበረባት። በመልኩ ከፈጠረን ከአፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ደግሞ ከዚህ የበለጠ ልንጠብቅ እንችላለን! (ዘፍጥረት 1:26፤ ኢሳይያስ 49:15) ልብ የሚነኩት የመዝሙር 34:18 ቃላት ይሖዋ ‘ልባችን ሲሰበር’ ልክ እንደ አፍቃሪ ወላጅ ምንጊዜም ‘ቅርብ ሆኖ’ በንቃትና በትኩረት እንደሚከታተለንና እኛን ለመርዳት ዝግጁ እንደሆነ ያረጋግጡልናል።—መዝሙር 147:1, 3
“ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ”
ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ይሖዋ በምድር ስላሉ አገልጋዮቹ ያለውን ስሜት ጨምሮ ስለ እርሱ አስተሳሰብና ስሜት ብዙ ነገር ገልጿል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በይሖዋ ፊት ዋጋ እንዳላቸው በተደጋጋሚ አረጋግጦላቸዋል።—ማቴዎስ 6:26፤ 12:12
ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ በግለሰብ ደረጃ ዋጋ እንዳላቸው በምሳሌ ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል:- “ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም። የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር እንኳ ተቆጥሮአል። እንግዲህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ።” (ማቴዎስ 10:29-31) እነዚህ ቃላት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት የኢየሱስ አድማጮች ምን ትርጉም እንደነበራቸው ተመልከት።
ድንቢጦች ለምግብነት ያገለግሉ ከነበሩ ወፎች መካከል በጣም ርካሽ እንደነበሩ ግልጽ ነው። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ትንንሽ ወፎች ላባቸው ተነጭቶ ከእንጨት በተሠሩ ሜንጦዎች ይቆነጠጡና ልክ እንደ ተቆራረጠ ሥጋ ይጠበሱ ነበር። ኢየሱስ በገበያ ሥፍራ ድሃ ሴቶች ምን ያህል ድንቢጦች መግዛት እንደሚችሉ ለማወቅ ሳንቲማቸውን ሲቆጥሩ አይቶ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ወፎቹ በጣም አነስተኛ ዋጋ እንዳላቸው ስለሚታሰብ አንድ ግለሰብ አነስተኛ ዋጋ ባለው ሳንቲም (ቃል በቃል ከአምስት ሳንቲም ያነሰ ዋጋ ባለው አንድ አሳሪዮን) ሁለት ድንቢጦች መግዛት ይችል ነበር።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ትንሽ ለየት ባለ መንገድ ቢሆንም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ በድጋሚ ተናግሯል። በሉቃስ 12:6 መሠረት ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “አምስት ድንቢጦች በአሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን?” እስቲ ጉዳዩን አጢኑት። አንድ ገበያተኛ በአምስት ሳንቲም ሁለት ድንቢጦች መግዛት ይችላል። ሆኖም አሥር ሳንቲም ካወጣ አራት ሳይሆን አምስት ድንቢጦች ያገኝ ነበር። አምስተኛዋ ወፍ ምንም ዋጋ የሌላት ይመስል ምራቂ ሆና የምትሰጥ ነበረች። “ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ [ምራቂ ሆና የተሰጠችው ጭምር] በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም” ሲል ኢየሱስ ተናግሯል። ኢየሱስ ምሳሌውን በመጠቀም “ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ” በማለት ደምድሟል። (ሉቃስ 12:7) እነዚህ ቃላት አድማጮቹን ምንኛ አጽናንተዋቸው ይሆን!
ኢየሱስ የተናገረው ልብ የሚነካ ምሳሌ የያዘውን ነጥብ አስተውለሃልን? ይሖዋ ትንንሽ ወፎች እንኳ ዋጋ እንዳላቸው ካሰበ ምድራዊ አገልጋዮቹ ለእርሱ ምን ያህል ውድ እንደሆኑ መገመት አያዳግትም! በይሖዋ ዘንድ ማናችንም ብንሆን አንረሳም። እያንዳንዳችን በይሖዋ ዘንድ ከፍተኛ ዋጋ ያለን ስለሆንን እኛን በተመለከተ በጣም ትንሿን ዝርዝር ጉዳይ ሳይቀር ይመለከታል። ራሳችን ላይ ያለው ፀጉር እንኳ አንድ በአንድ ተቆጥሯል።
እርግጥ ሰይጣን ይሖዋን ማገልገል እንድናቆም ዋጋ የለኝም የሚለውን ስሜት መሣሪያ አድርጎ መጠቀምን የመሳሰሉ “የማታለያ ዘዴዎቹን” መጠቀሙን ይቀጥላል። ሆኖም ሰይጣን እንዲያሸንፍህ አትፍቀድለት! መግቢያው ላይ የተጠቀሰችውን ክርስቲያን ሴት አስታውስ። ሰይጣን በስሜቶቻችን ለመጠቀም የሚያደርገውን ጥረት በተመለከተ በአንድ መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይ የወጣ ትምህርት በእጅጉ ጠቅሟታል።a እንዲህ ብላለች:- “ሰይጣን እኔን ተስፋ ለማስቆረጥ ባሉኝ ስሜቶች ለመጠቀም እንደሚሞክር ፈጽሞ አስቤ አላውቅም ነበር። ይህን ማወቄ እነዚህን ስሜቶች ለመዋጋት አነሳስቶኛል። አሁን በትምክህት እነዚህን ሰይጣናዊ ጥቃቶች መጋፈጥ እችላለሁ።”
ይሖዋ ‘ሁሉን ያውቃል።’ (1 ዮሐንስ 3:20) አዎን፣ በአሁኑ ጊዜ በጽናት እያሳለፍነው ያለነውን ነገር ያውቃል። በተጨማሪም ለራሳችን ያለንን አክብሮት ያሳጣንን ቀደም ሲል የደረሰብንን ነገር ያውቃል። ትልቁ ነገር ይሖዋ ለእኛ ያለው አመለካከት መሆኑን አትዘንጋ! ምንም ያህል ተወዳጅ እንዳልሆንን ወይም ዋጋ እንደሌለን ብናስብም ይሖዋ አገልጋዮቹ በሙሉ በእርሱ ዘንድ ዋጋ እንዳላቸው ያረጋግጥልናል። ይሖዋ ከባላጋራው በተለየ ሁኔታ “የማይዋሽ” አምላክ ስለሆነ እርሱ የተናገረውን ማመን እንችላለን።—ቲቶ 1:2
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በሚያዝያ 1, 1995 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 10-15 ላይ የወጣውን “በአምላክ ፊት ውድ ናችሁ!” የሚለውን ትምህርት ተመልከት።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ይሖዋ ልክ እንደ አፍቃሪ ወላጅ ልባቸው ለተሰበረ ሰዎች ቅርብ ነው
[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ይሖዋ ድንቢጥን የማይረሳ ከሆነ አንተን እንዴት ሊረሳ ይችላል?
[ምንጮች]
Lydekker
Illustrated Natural History