የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
አንድን ሰው ጥሩ ዜጋ የሚያሰኘው ምንድን ነው?
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ ራሳቸውን ጥሩና ሕግ አክባሪ ዜጎች አድርገው የሚቆጥሩ በአውሮፓና በጃፓን የሚኖሩ በርካታ ሰዎች በጦር ወንጀለኝነት ተከስሰው ጥፋተኞች ሆነው ተገኝተዋል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ ሳይንቲስቶችና በሌላ የሙያ መስክ እውቅናን ያተረፉ ሰዎች ይገኙበታል። ከማንኛውም ጥሩ ዜጋ እንደሚጠበቀው ሁሉ እነርሱም የተሰጣቸውን ትእዛዝ ያከበሩ መሆናቸውን በመግለጽ ያደረጉት ነገር ምንም ስህተት እንደሌለው ለማሳመን ሙከራ አድርገዋል። ይሁን እንጂ ራሳቸውን እንደ ጥሩ ዜጋ አድርገው የቆጠሩበት መንገድ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ይህ ነው የማይባል ወንጀል እንዲፈጽሙ አድርጓቸዋል።
በሌላው በኩል ደግሞ የመንግሥትን ሥልጣን ከመጤፍ የማይቆጥሩ ሰዎችም አሉ። አንዳንዶቹ የመንግሥትን ሥልጣን በገሃድ ሲጥሱ ሌሎች ደግሞ ችግር ውስጥ የማይከታቸው ሆኖ እስከተሰማቸው ድረስ ሕግ ከማፍረስ ወደኋላ አይሉም። እርግጥ ነው፣ ለባለ ሥልጣናት መታዘዝ ያለውን አስፈላጊነት የሚክድ ሰው አይኖርም። አለዚያ ሁከትና ብጥብጥ እንደሚከተል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ አንድ ሰው የዜግነት ግዴታውን የሚወጣውና ሕግን የሚታዘዘው እስከ ምን ድረስ ነው? የሚለው ጥያቄ ይነሳል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በመንግሥት ዘንድ ያለባቸውን ግዴታ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መመልከት ይችሉ ዘንድ የረዷቸውን አንዳንድ ዋና ዋና መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመልከት።
ክርስቲያኖች ለባለ ሥልጣናት ያለባቸው ተገዥነት
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ‘የበላይ ባለ ሥልጣናት’ ማለትም በጊዜው ይገዙ የነበሩት መንግሥታት ላወጧቸው ሕግጋትና ደንቦች በፈቃደኝነት ይገዙ ነበር። (ሮሜ 13:1) ክርስቲያኖች ‘ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች መገዛትና መታዘዝ’ ተገቢ መሆኑን ያምኑ ነበር። (ቲቶ 3:1) ክርስቶስ ሰማያዊው ንጉሣቸው እንደሆነ የሚያውቁ ቢሆንም ለሰብዓዊ ገዥዎቻቸው የሚታዘዙ ከመሆናቸውም በላይ ለአገር ደህንነት ምንም ዓይነት ስጋት የሚፈጥሩ አልነበሩም። እንዲያውም በማንኛውም ወቅት ‘ንጉሥን እንዲያከብሩ’ ተበረታተው ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:17) እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን እንዲህ በማለት አበረታቷቸዋል:- “እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፣ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ።”—1 ጢሞቴዎስ 2:1, 2
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በአንዳንድ ወቅት ከአቅማቸው በላይ እንዲከፍሉ ቢጠየቁ እንኳን ማንኛውንም ግብር ሳያሰልሱ ይከፍሉ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት ተገፋፍቶ “ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ . . . ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን” በማለት በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጠውን መመሪያ ይከተሉ ነበር። (ሮሜ 13:7) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሮማ መንግሥትንና የመንግሥቱን ሹማምንቶች በአምላክ ፈቃድ እንደሚገዙና በኅብረተሰቡ ውስጥ በተወሰነ መጠን ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የሚያደርጉ “የእግዚአብሔር አገልጋዮች” እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸው ነበር።—ሮሜ 13:6
“ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ”
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች መንግሥት የጣለውን የዜግነት ግዴታ እንዲቀበሉ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ደቀ መዛሙርቱ በአንዳንድ ወቅቶች የሕዝብ ባለ ሥልጣናት ከሚጠይቋቸው የበለጠ ነገር ለማድረግ ፈቃደኞች እንዲሆኑ መክሯቸዋል። “ማንም [“በሥልጣን ላይ ያለ፣” NW] ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ” ብሏል። (ማቴዎስ 5:41) ክርስቲያኖች ይህን ምክር በመከተል በምላሹ ምንም ነገር ሳያበረክቱ በሠለጠነ ኅብረተሰብ መካከል መኖር የሚያስገኘውን ጥቅም ብቻ ለማግኘት የሚጥሩ አለመሆናቸውን አሳይተዋል። ሁልጊዜ “ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ” ነበሩ።—ቲቶ 3:1፤ 1 ጴጥሮስ 2:13-16
ጎረቤቶቻቸውን ከልባቸው ይወዱ ነበር እንዲሁም እነርሱን ለመርዳት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ይፈልጉ ነበር። (ማቴዎስ 22:39) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ይህን ፍቅር ማሳየታቸውና ከፍተኛ የሥነ ምግባር አቋም መጠበቃቸው በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ አድርጓቸዋል። ጎረቤቶቻቸው ከክርስቲያኖች ጋር ተጎራብተው መኖር በመቻላቸው የሚደሰቱበት በቂ ምክንያት ነበራቸው። (ሮሜ 13:8-10) ክርስቲያኖች ፍቅራቸውን ያሳዩ የነበረው መጥፎ ነገር ከመሥራት በመታቀብ ብቻ አልነበረም። ልክ ኢየሱስ ክርስቶስ ያደርግ እንደነበረው “[ለእምነት ባልደረቦቻቸው ብቻ ሳይሆን] ለሰው ሁሉ . . . መልካም” እንዲያደርጉ፣ ተግባቢዎች እንዲሆኑና ሌሎችን የሚጠቅም ተግባር እንዲያከናውኑ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል።—ገላትያ 6:10
‘ከሰው ይልቅ እግዚአብሔርን ታዘዙ’
ሆኖም ሰብዓዊ ባለ ሥልጣናትን ይታዘዙ የነበረው በገደብ ነበር። ሕሊናቸውን የሚያስጥስ ወይም ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና የሚያበላሽ ምንም ነገር አያደርጉም ነበር። ለምሳሌ ያህል በኢየሩሳሌም የነበሩት ሃይማኖታዊ ባለ ሥልጣናት ስለ ኢየሱስ መስበካቸውን እንዲያቆሙ ሐዋርያትን ባዘዟቸው ጊዜ ትእዛዛቸውን ለመፈጸም ፈቃደኞች አልነበሩም። “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” በማለት መለሱ። (ሥራ 5:27-29) ክርስቲያኖች ንጉሠ ነገሥትን ማምለክን በመሰለ የጣዖት አምልኮ ውስጥ ለመሳተፍ አሻፈረኝ ብለዋል። (1 ቆሮንቶስ 10:14፤ 1 ዮሐንስ 5:21፤ ራእይ 19:10) ታዲያ ይህ አቋማቸው ምን አስከተለባቸው? “ውግዘት አስከትሎባቸዋል” በማለት ታሪክ ጸሐፊው ጄ ኤም ሮበርትስ ተናግረዋል፤ “ይህ የደረሰባቸው ክርስቲያን ስለሆኑ ሳይሆን ሕጉ የሚያዘውን ለመፈጸም አሻፈረን በማለታቸው ነበር።”—ሾርተር ሂስትሪ ኦቭ ዘ ዎርልድ
በዚህ ወቅት ‘ሕጉ የሚያዝዘውን ለመቀበል አሻፈረን ያሉት’ ለምን ነበር? ‘የበላይ ባለ ሥልጣናት’ ሥልጣናቸውን ያገኙት በአምላክ ፈቃድ እንደሆነና ሕግንና ሥርዓትን በማስጠበቅ ረገድ “የእግዚአብሔር አገልጋይ” መሆናቸውን ይገነዘባሉ። (ሮሜ 13:1, 4) ያም ሆኖ ግን ክርስቲያኖች እንደ መጨረሻ ባለ ሥልጣን አድርገው የሚመለከቱት የአምላክን ሕግ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱ ተከታይ ለመሆን ለሚፈልጉ ሁሉ የሚከተለውን ሚዛኑን የጠበቀ መሠረታዊ ሥርዓት ሰጥቷቸዋል:- “እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው።” (ማቴዎስ 22:21) ለአምላክ ያለባቸው ግዴታ ቄሣር ከሚጠይቅባቸው ነገር ይበልጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነበር።
ክርስቲያን ነን የሚሉ በርካታ ሰዎች እነዚህን ግሩም መሠረታዊ ሥርዓቶች ችላ ባሉ ጊዜ የተከሰተው ነገር ትክክለኛው አካሄድ ይህ መሆኑን ያሳያል። ለምሳሌ ያህል የሕዝበ ክርስትና ከሃዲ መሪዎች “በተለይ የጦር ኃይላትን በመቀስቀስና ድጋፍ በመስጠት ለሕዝባዊ መስተዳደር እንደ መሣሪያ ሆነው የሚያገለግሉ አድር ባዮች ሆነዋል” በማለት የውትድርና ታሪክ ጸሐፊ የሆኑት ጆን ኪገን ተናግረዋል። በዚህም የተነሳ ተከታዮቻቸው የብዙ ንጹሐን ሰዎችን ደም እንደ ጎርፍ ባፈሰሱ ጦርነቶች ውስጥ ጎራ ለይተው እንዲሻኮቱ አድርጓቸዋል። “ወኔያቸው በሚቀሰቀስበት ጊዜ የአምላክ ሕግ ፈጽሞ ትዝ አይላቸውም” ሲሉ ኪገን ተናግረዋል።
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ትክክለኛውን ሚዛን በመጠበቅ ረገድ አንጸባራቂ ምሳሌ ትተዋል። ጥሩ ዜጎች ነበሩ። ሕዝባዊ ግዴታዎቻቸውንና ኃላፊነቶቻቸውን በሚገባ ፈጽመዋል። ሆኖም በሁሉም የኑሮ ዘርፎቻቸው በግልጽ የሰፈሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጠብቀዋል እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ ሕሊናቸውን ተከትለዋል።—ኢሳይያስ 2:4፤ ማቴዎስ 26:52፤ ሮሜ 13:5፤ 1 ጴጥሮስ 3:16
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ”