አምላክና ቄሣር
“እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ።”—ሉቃስ 20:25
1. (ሀ) ይሖዋ ምን የላቀ ቦታ አለው? (ለ) ለቄሣር ፈጽሞ ልንሰጠው የማንችለውና ለይሖዋ ብቻ የምንሰጠው ነገር ምንድን ነው?
ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን መመሪያ ሲሰጥ የአምላክ አገልጋዮች አምላክ የሚፈልግባቸው ነገር ቄሣር ወይም መንግሥት ከሚፈልግባቸው ማንኛውም ነገር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን በአእምሮው ይዞ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። መዝሙራዊው ለይሖዋ ያቀረበው የሚከተለው ጸሎት እውነት መሆኑን ኢየሱስ ከማንም በላይ ጠንቅቆ ያውቃል፦ “መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፣ ግዛትህም [ሉዓላዊነትህም]a ለልጅ ልጅ ነው።” (መዝሙር 145:13) ዲያብሎስ በምድር ባሉት መንግሥታት ሁሉ ላይ ሥልጣን ልስጥህ ባለው ጊዜ ኢየሱስ “ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል” ሲል መልሶለታል። (ሉቃስ 4:5-8) ቄሣር የሚለው ቃል የሚያመለክተው የሮማ ንጉሠ ነገሥትን፣ አንድን ሌላ ሰብዓዊ ገዥንም ሆነ ፖለቲካዊ መንግሥትን፣ አምልኮ ፈጽሞ “ለቄሣር” ሊሰጥ አይችልም።
2. (ሀ) ሰይጣን በዚህ ዓለም ላይ ያለው ሥልጣን ምንድን ነው? (ለ) ሰይጣን ሥልጣኑን የያዘው በማን ፈቃድ ነው?
2 ኢየሱስ የዓለም መንግሥታት የሰይጣን ንብረት መሆናቸውን አልካደም። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” ብሎ ጠርቶታል። (ዮሐንስ 12:31፤ 16:11) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ መገባደጃ ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ “ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደተያዘ እናውቃለን” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:19) ይህ ማለት ይሖዋ በምድር ላይ ያለውን ሉዓላዊነት አሳልፎ ሰጥቷል ማለት አይደለም። ሰይጣን የፖለቲካ መንግሥታትን የመግዛት ሥልጣን ለኢየሱስ ልስጥህ ባለው ጊዜ “ይህ ሥልጣን ሁሉ . . . ለእኔ ተሰጥቶአል . . . ለአንተ እሰጥሃለሁ” ብሎ መናገሩን አስታውሱ። (ሉቃስ 4:6) ሰይጣን በዓለም መንግሥታት ላይ ሥልጣን ሊኖረው የቻለው አምላክ ስለፈቀደ ብቻ ነው።
3. (ሀ) መንግሥታት በይሖዋ ፊት ምን ሥልጣን አላቸው? (ለ) ለዚህ ዓለም መንግሥታት መገዛት ማለት የዚህ ዓለም አምላክ ለሆነው ለሰይጣን ራስን ማስገዛት ማለት አይደለም ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?
3 በተመሳሳይም የፖለቲካ መንግሥት ሥልጣን ሊኖረው የቻለው የሁሉ የበላይ ገዥ የሆነው አምላክ ስለፈቀደ ብቻ ነው። (ዮሐንስ 19:11) በመሆኑም ‘አሁን ያሉት ባለ ሥልጣኖች አንፃራዊውን ሥልጣን ያገኙት በአምላክ ነው’ ብሎ መናገር ይቻላል። ይሖዋ ካለው ከሁሉ የላቀ ሥልጣን አንጻር ሲታይ ሥልጣናቸው በጣም አነስተኛ ነው። ይሁን እንጂ አስፈላጊ የሆኑ ግልጋሎቶችን ስለሚሰጡ፣ ሕግና ሥርዓት ስለሚያስጠብቁና ክፉ አድራጊዎችን ስለሚቀጡ “የእግዚአብሔር አገልጋይ” ማለትም “በአምላክ ፈቃድ የሚሠሩ የሕዝብ አገልጋዮች [አዓት]” ናቸው። (ሮሜ 13:1, 4, 6) ስለዚህ ክርስቲያኖች ሰይጣን የዚህ ዓለም ወይም ሥርዓት የማይታይ ገዥ ስለሆነ ብቻ ለመንግሥት አንጻራዊ በሆነ መንገድ ሲገዙ ራሳቸውን ለሰይጣን እያስገዙ እንዳሉ ሆኖ ሊሰማቸው አይገባም። አምላክን እየታዘዙ ነው። በዚህ በ1996 ዓመትም ቢሆን ፖለቲካዊው መንግሥት ‘የአምላክ ዝግጅት’ አንዱ ክፍል ነው። አምላክ እንዲኖር የፈቀደው ጊዜያዊ ዝግጅት ነው። የይሖዋ ምድራዊ አገልጋዮችም በዚህ መልኩ ሊያዩት ይገባል።—ሮሜ 13:2
በጥንት ዘመን የነበሩ የይሖዋ አገልጋዮችና ፖለቲካዊ መንግሥት
4. ዮሴፍ በግብፅ መንግሥት ላይ ትልቅ ሥልጣን እንዲይዝ ይሖዋ የፈቀደው ለምንድን ነው?
4 በቅድመ ክርስትና ዘመን ይሖዋ አንዳንድ አገልጋዮቹ ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን እንዲይዙ ፈቅዶ ነበር። ለምሳሌ ያህል በ18ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ዮሴፍ በመግዛት ላይ ከነበረው ፈርዖን ቀጥሎ ያለውን ከፍተኛ ሥልጣን በመያዝ የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ነበር። (ዘፍጥረት 41:39-43) ከዚያ በኋላ ከተከናወኑት ሁኔታዎች በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ይህ እንዲሆን ያደረገው ይሖዋ ነው፤ ይህንንም ያደረገው ዓላማዎቹ ይፈጸሙ ዘንድ ‘የአብርሃምን ዘር’ ማለትም ዝርያዎቹን ከጥፋት ለማዳን ዮሴፍን መሣሪያ አድርጎ ሊጠቀምበት ስለ ፈለገ ነው። እርግጥ እዚህ ላይ፣ ዮሴፍ ወደ ግብፅ ለባርነት ተሸጦ እንደነበረና በዚያ ጊዜ የአምላክ አገልጋዮች የሙሴ ሕግም ሆነ ‘የክርስቶስ ሕግ’ እንዳልነበራቸው ማስታወስ ይገባል።—ዘፍጥረት 15:5-7፤ 50:19-21፤ ገላትያ 6:2
5. ተማርከው የነበሩት አይሁዳውያን የባቢሎንን ‘ሰላም እንዲፈልጉ’ የታዘዙት ለምን ነበር?
5 ብዙ ዘመናት ካለፉ በኋላ ታማኙ ነቢይ ኤርምያስ በይሖዋ መንፈስ ተገፋፍቶ በባቢሎን በግዞት የነበሩት አይሁዳውያን ለገዥዎቹ እንዲገዙና ለከተማዋ ሰላም እንዲጸልዩ ነግሯቸዋል። ለእነሱ በላከው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ላስማረክኋቸው ምርኮኞች ሁሉ እንዲህ ይላል፦ . . . በእርስዋ ሰላም ሰላም ይሆንላችኋልና ወደ እርስዋ ላስማረክኋችሁ ከተማ ሰላምን ፈልጉ፣ ስለ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ።” (ኤርምያስ 29:4, 7) ምንጊዜም የይሖዋ ሕዝቦች ይሖዋን ለማምለክ ነፃነት ማግኘት ይችሉ ዘንድ ለራሳቸውም ሆነ ለሚኖሩበት አገር ‘ሰላምን የሚፈልጉበት’ በቂ ምክንያት አላቸው።—1 ጴጥሮስ 3:11
6. ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም እንኳ ለይሖዋ ሕግ ያላቸውን አቋም ለማላላት ፈቃደኞች ያልሆኑት በምን በምን መንገዶች ነው?
6 እስራኤላውያን በባቢሎን ግዞት ሥር በነበሩበት ዘመን ዳንኤልና ወደ ባቢሎን ለባርነት ተማርከው የተወሰዱ ሌሎች ሦስት የታመኑ አይሁዳውያን መንግሥት የሰጣቸውን ሥልጠና በታዛዥነት ከተቀበሉ በኋላ በባቢሎን ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ሆነው ሠርተዋል። (ዳንኤል 1:3-7፤ 2:48, 49) ይሁን እንጂ ሥልጠናው እየተሰጣቸው በነበረበት ጊዜም እንኳ አምላካቸው ይሖዋ በሙሴ በኩል የሰጠውን ሕግ እንዲጥሱ ሊያደርጉ የሚችሉ ከምግብ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ቆራጥ አቋም ወስደዋል። በዚህም ተባርከውበታል። (ዳንኤል 1:8-17) ንጉሥ ናቡከደነፆር የአገሩ ሕዝብ እንዲያመልከው አንድ ምስል ሠርቶ ባቆመ ጊዜ የዳንኤል ጓደኞች የሆኑት ሦስቱ ዕብራውያን እንደነሱ በመንግሥት ላይ ከተሾሙ አስተዳዳሪዎች ጋር ሆነው በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዲካፈሉ ተገደው ነበር። ሆኖም የአገሩ ሕዝብ እንዲያመልከው በተሠራው በዚህ ጣዖት ፊት ‘ለመስገድና ለማምለክ’ ፈቃደኞች አልሆኑም። ይሖዋም የጸና አቋም በመያዛቸው ዳግመኛ ክሷቸዋል። (ዳንኤል 3:1-6, 13-28) በተመሳሳይ ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች ለሚኖሩበት አገር ሰንደቅ ዓላማ አክብሮት አላቸው፤ ሆኖም ለሰንደቅ ዓላማው አምልኮታዊ አክብሮት አያሳዩም።—ዘጸአት 20:4, 5፤ 1 ዮሐንስ 5:21
7. (ሀ) ዳንኤል በባቢሎን መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ቢሆንም እንኳ ምን ግሩም አቋም ወስዷል? (ለ) በክርስትና ዘመን ምን ለውጦች ተደርገዋል?
7 ሦስተኛዋ የዓለም ኃይል የነበረችው ባቢሎን ከወደቀች በኋላ ዳንኤል በወደቀው መንግሥት በተተካው በአዲሱ የሜዶንና ፋርስ ጥምር መንግሥት ሥር በባቢሎን ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ተሰጠው። (ዳንኤል 5:30, 31፤ 6:1-3) ሆኖም ያገኘው ከፍተኛ ሥልጣን የያዘውን የጸና አቋም እንዲያላላበት አልፈቀደም። መንግሥት ይሖዋን ሳይሆን ንጉሥ ዳርዮስን እንዲያመልክ የሚያዝ ሕግ ባወጣ ጊዜ ዳንኤል ሕጉን አልተቀበለውም። በዚህም ምክንያት ወደ አንበሶች ጉድጓድ የተጣለ ቢሆንም ይሖዋ አድኖታል። (ዳንኤል 6:4-24) እርግጥ ይህ የሆነው በቅድመ ክርስትና ዘመን ነበር። የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላ ግን የአምላክ አገልጋዮች ‘ከክርስቶስ ሕግ በታች’ ሆነዋል። በአይሁድ ሥርዓት ይፈቀዱ የነበሩ ብዙ ነገሮች አሁን ይሖዋ ከሕዝቡ ጋር ካለው ግንኙነት አንጻር ለየት ባለ ሁኔታ መታየት ይኖርባቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 9:21፤ ማቴዎስ 5:31, 32፤ 19:3-9
ኢየሱስ ለፖለቲካዊ መንግሥት የነበረው አመለካከት
8. ኢየሱስ ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ለመራቅ ቆራጥ አቋም ወስዶ እንደነበረ የሚያሳየው የትኛው ሁኔታ ነው?
8 ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ለተከታዮቹ ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎች አውጥቶላቸዋል፤ በተጨማሪም በማንኛውም ዓይነት ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ ጉዳይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አልሆነም። ኢየሱስ ብዙ ሺህ ሰዎችን በጥቂት ዳቦና በሁለት ትናንሽ ዓሦች ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከመገበ በኋላ የአይሁድ ሰዎች ፖለቲካዊ ንጉሥ ሊያደርጉት ፈልገው ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ወዲያውኑ ወደ ተራሮች በመሸሽ ከእነርሱ ተሰውሯል። (ዮሐንስ 6:5-15) ይህን ሁኔታ በተመለከተ ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ኮሜንታሪ ኦን ዘ ኒው ቴስታመንት እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “በዚያን ጊዜ የነበሩት አይሁዶች ብሔራዊ ነፃነት ለማግኘት ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው፤ ተአምሩ ሲፈጸም ካዩት አይሁዶች መካከል ብዙዎቹ ከሮማ ቀንበር ነፃ የሚያወጣቸው ከሁሉ የተሻለና በመለኮታዊ ኃይል የተሾመ መሪ እንደሆነ አድርገው እንደተመለከቱት ምንም ጥርጥር የለውም። ስለዚህ ንጉሥ ሊያደርጉት ቆርጠው ተነሥተው ነበር።” ኢየሱስ የፖለቲካ መሪ እንዲሆን የቀረበለትን ሐሳብ “ያላንዳች ማወላወል ሳይቀበለው ቀርቷል” በማለት መጽሐፉ አክሎ ገልጿል። ክርስቶስ አይሁዳውያን በሮማ አገዛዝ ላይ ላካሄዱት ለየትኛውም ዓመፅ ድጋፍ አልሰጠም። እንዲያውም ይህ ዓመፅ ከእሱ ሞት በኋላ በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ ይህ ነው የማይባል ወዮታ እንደሚያስከትልና ከተማዋ እንደምትጠፋ በመግለጽ ዓመፁ የሚያመጣውን ውጤት አስቀድሞ ተናግሯል።—ሉቃስ 21:20-24
9. (ሀ) ኢየሱስ የእሱ መንግሥት ከዓለም ጋር ያለውን ግንኙነት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ተከታዮቹ ከዚህ ዓለም ባለ ሥልጣኖች ጋር ሊኖራቸው የሚገባውን ግንኙነት በተመለከተ ምን መምሪያ ሰጥቷል?
9 ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ በይሁዳ ውስጥ የሮማ ንጉሠ ነገሥት ልዩ ወኪል ለነበረው ሰው እንዲህ ብሎታል፦ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፣ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም።” (ዮሐንስ 18:36) መንግሥቱ የፖለቲካ መንግሥታትን አገዛዝ እስኪያስወግድ ድረስ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የእሱን ምሳሌ ይከተላሉ። ለባለ ሥልጣናት የሚታዘዙ ቢሆንም በፖለቲካ ጉዳዮቻቸው ውስጥ ጣልቃ አይገቡም። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 4:8-10) ኢየሱስ “እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ መምሪያ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 22:21) ኢየሱስ ይህን ከመናገሩ ቀደም ብሎ በተራራው ስብከቱ ላይ “ማንም ሰው [“አንድ በሥልጣን ላይ ያለ ሰው፣” አዓት] አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ” ሲል ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 5:41) በዚህ ስብከት ላይ የተጠቀሱት በጥቅሱ ዙሪያ ያሉት ሐሳቦች ኢየሱስ ከሰው ጋር ባለን ግንኙነትም ሆነ መንግሥት እንድናሟላቸው በሚፈልጋቸው ነገሮች ረገድ ከአምላክ ሕግ ጋር ለሚስማሙና አግባብነት ላላቸው ነገሮች ራስን በፈቃደኝነት የማስገዛትን አስፈላጊነት የሚገልጸውን መሠረታዊ ሥርዓት እያብራራ እንደነበረ ያሳያሉ።—ሉቃስ 6:27-31፤ ዮሐንስ 17:14, 15
ክርስቲያኖችና ቄሣር
10. አንድ ታሪክ ጸሐፊ እንደተናገሩት የጥንት ክርስቲያኖች ከቄሣር ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ምን ጥንቃቄ የተሞላበት አቋም ወስደዋል?
10 እነዚህ አጫጭር መምሪያዎች በክርስቲያኖችና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚወስኑ ናቸው። ታሪክ ጸሐፊው ኢ ደብሊው ባርንስ ዘ ራይዝ ኦቭ ክርስቲያኒቲ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ክርስቶስ ይህን መመሪያ ከሰጠ በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናት አንድ ክርስቲያን ለመንግሥት ያለበትን ግዴታ በተመለከተ ጥርጣሬ ሲገባው ክርስቶስ ይህን አስመልክቶ የሰጠውን ትምህርት መለስ ብሎ ይመለከታል። መንግሥት የጣለበት ቀረጥ ከባድ ቢሆንም እንኳ ይከፍላል። የምዕራቡ ዓለም ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዝ ከመውደቁ በፊት የነበረው ቀረጥ በጣም ከባድ ነበር። ሆኖም ክርስቲያኑ እንደምንም ብሎ ይከፍል ነበር። ለአምላክ መሰጠት ያለበትን ነገር ለቄሣር እንዲሰጥ እስካልተጠየቀ ድረስ መንግሥት የሚጠይቅበትን ሌሎች ግዴታዎችም ተቀብሎ ይፈጽማል።”
11. ጳውሎስ ክርስቲያኖች ከዓለማዊ ገዥዎች ጋር ሊኖራቸው የሚገባውን ግንኙነት በተመለከተ ምን ብሎ መክሯቸዋል?
11 ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቶስ ከሞተ ከ20 ዓመት በኋላ በሮም ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ” ብሏቸዋል። (ሮሜ 13:1) ከአሥር ዓመት ገደማ በኋላ ጳውሎስ ሮም ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ታስሮ ከመገደሉ ከጥቂት ጊዜ በፊት ለቲቶ እንዲህ ሲል ጽፎለታል፦ “ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፣ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ፣ ማንንም የማይሰድቡ፣ የማይከራከሩ፣ ገሮች፣ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ [የቀርጤስ ክርስቲያኖችን] አሳስባቸው።”—ቲቶ 3:1, 2
የ“በላይ ባለ ሥልጣኖች” ማን መሆናቸውን ደረጃ በደረጃ መረዳት
12. (ሀ) ቻርልስ ቴዝ ራስል አንድ ክርስቲያን ከመንግሥት ባለ ሥልጣኖች ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ሊኖረው የሚገባውን ትክክለኛ አቋም በተመለከተ ምን አመለካከት ነበረው? (ለ) በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በጦር ሠራዊት ውስጥ ማገልገልን በተመለከተ ምን የተለያየ አመለካከት ነበራቸው?
12 ገና በ1886 ቻርልስ ቴዝ ራስል ዘ ፕላን ኦቭ ዘ ኤጅስ (የዘመናት ቅያስ) በተባለው መጽሐፍ ላይ እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር፦ “ኢየሱስም ሆነ ሐዋርያት ለምድራዊ ገዥዎች በምንም መንገድ እንቅፋት አልሆኑም። . . . ቤተ ክርስቲያን ሕጎችን እንድታከብር፣ ባለ ሥልጣኖችንም በያዙት የሥልጣን ቦታ የተነሣ እንድታከብር፣ . . . የሚገባቸውን ቀረጥ እንድትከፍልና ከአምላክ ሕግጋት ጋር የሚቃረን እስካልሆነ ድረስ (ሥራ 4:19፤ 5:29) የትኛውንም ሕግ ለመቀበል አሻፈረኝ ማለት እንደሌለባት አስተምረዋል። (ሮሜ 13:1-7፤ ማቴ. 22:21) ኢየሱስና ሐዋርያት እንዲሁም የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ምንም እንኳ ከዚህ ዓለም መንግሥታት ጉዳዮች ገለልተኞች የነበሩና በእነዚህ ጉዳዮች ፈጽሞ ያልተሳተፉ ቢሆንም ሁሉም ሕግ አክባሪዎች ነበሩ።” ይህ መጽሐፍ ሐዋርያው ጳውሎስ የጠቀሳቸው የ“በላይ ባለ ሥልጣኖች” ሰብዓዊ የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች እንደሆኑ በትክክል አመልክቶ ነበር። (ሮሜ 13:1) በ1904 ዘ ኒው ክሪኤሽን (አዲስ ፍጥረት) የተባለው መጽሐፍ እውነተኛ ክርስቲያኖች “በዘመናችን በሕግ አክባሪነታቸው የላቀ ደረጃ ከሚሰጣቸው ሰዎች መካከል የሚጠቀሱ መሆን እንዳለባቸውና የለውጥ አራማጆች፣ ጠበኞችና እንከን ፈላጊዎች መሆን እንደሌለባቸው” ገልጾ ነበር። አንዳንዶች ይህ ማለት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጦር ሠራዊቶች ውስጥ አገልግሎት እስከ መስጠት ደረጃ ድረስ ለመንግሥት ሙሉ በሙሉ መገዛት ማለት እንደሆነ አድርገው ተረድተው ነበር። ይሁን እንጂ ሌሎች ይህ ድርጊት ኢየሱስ “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” ሲል ከተናገረው አባባል ጋር ይጋጫል የሚል አመለካከት አድሮባቸው ነበር። (ማቴዎስ 26:52) ክርስቲያኖች ለበላይ ባለ ሥልጣኖች የሚያሳዩትን ተገዥነት በተመለከተ የተሰጠውን ሐሳብ ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ መረዳት ያስፈልግ እንደነበረ ከሁኔታው መገንዘብ ይቻላል።
13. በ1929 የበላይ ባለ ሥልጣኖችን ማንነት በተመለከተ በነበረው አመለካከት ላይ ምን ለውጥ ተደርጎ ነበር? ይህ ጠቃሚ ሆኖ የተገኘው እንዴት ነው?
13 በ1929፣ የተለያዩ መንግሥታት አምላክ ያዘዛቸውን ነገሮች የሚከለክሉ ወይም የአምላክ ሕጎች የሚከለክሏቸውን ነገሮች እንዲደረጉ የሚያዙ ሕጎችን ማውጣት በጀመሩበት ወቅት የበላይ ባለ ሥልጣኖች የተባሉት ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ መሆን አለባቸው ተባለ።b ይህም የይሖዋ አገልጋዮች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊትና ጦርነቱ ይካሄድ በነበረበት ቀውጢ ወቅት እንዲሁም እርስ በርስ ተፈራርቶ የመኖርና የወታደራዊ ዝግጁነት መርሆ ያራምድ በነበረው በቀዝቃዛው ጦርነት መጀመሪያ ላይ የነበራቸው አመለካከት ነበር። ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት የይሖዋንና የክርስቶስን የበላይነት ከፍ ከፍ ያደረገው ይህ አመለካከት በእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት በሙሉ የአምላክ ሕዝቦች የገለልተኝነት አቋማቸውን አጥብቀው እንደያዙ ለመቀጠል እንደረዳቸው መገንዘብ እንችላለን።
አንፃራዊ ተገዥነት
14. በ1962 በሮሜ 13:1, 2 እና ከዚህ ጋር በተያያዙ ሌሎች ጥቅሶች ላይ ተጨማሪ የእውቀት ብርሃን የፈነጠቀው እንዴት ነው?
14 በ1961 የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ተተርጉሞ አለቀ። የትርጉም ሥራው ቅዱሳን ጽሑፎች የተጻፉበትን ሥነ ጽሑፋዊ ቋንቋ በጥልቀት መመርመርን የሚጠይቅ ነበር። በሮሜ ምዕራፍ 13 ላይ ብቻ ሳይሆን በቲቶ 3:1, 2 እና በ1 ጴጥሮስ 2:13, 17 ምንባቦች ላይ ያሉት ቃላት በትክክል በመተርጎማቸው የ“በላይ ባለ ሥልጣኖች” የሚለው አነጋገር የሁሉ የበላይ ባለ ሥልጣን የሆነውን ይሖዋንና ልጁን ኢየሱስን ሳይሆን ሰብዓዊ የመንግሥት ባለ ሥልጣኖችን የሚያመለክት እንደሆነ መረዳት ተችሏል። በ1962 መገባደጃ ላይ የሮሜ ምዕራፍ 13ን ትክክለኛ ማብራሪያ የያዙና በሲ ቲ ራስል ዘመን ከነበረው ይበልጥ ግልጽ የሆነ አመለካከት የሠፈረባቸው የመጠበቂያ ግንብ ርዕሶች ወጡ። እነዚህ ርዕሶች ክርስቲያኖች ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙት ፍጹም በተሟላ መንገድ እንዳልሆነ ጠቁመዋል። አንፃራዊ መሆን አለበት፤ የአምላክ አገልጋዮች ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙት ከአምላክ ሕጎች ጋር የሚያጋጫቸው እስካልሆነ ድረስ ብቻ ነው። በመጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡ ሌሎች ርዕሶችም ይህን አስፈላጊ ነጥብ ጠበቅ አድርገው ገልጸውታል።c
15, 16. (ሀ) ሮሜ ምዕራፍ 13ን በተመለከተ የተገኘው አዲስ እውቀት ምን የተሻለ ሚዛናዊ አመለካከት አስገኝቷል? (ለ) መልስ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
15 ሮሜ ምዕራፍ 13ን በትክክል ለመረዳት ቁልፍ ሆኖ ያገለገለው ይህ ማብራሪያ የይሖዋ ሕዝቦች በቅዱስ ጽሑፉ ላይ ለሰፈሩት ወሳኝ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያላቸውን አቋም ሳያላሉ ለፖለቲካ ባለ ሥልጣኖች ሚዛናዊ የሆነ አክብሮት እንዲሰጡ አስችሏቸዋል። (መዝሙር 97:11፤ ኤርምያስ 3:15) ከአምላክ ጋር ስላላቸው ዝምድናና ከመንግሥት ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው አድርጓል። የቄሣርን ለቄሣር ሲያስረክቡ የአምላክን ለአምላክ የማስረከብ ኃላፊነታቸውን ችላ እንዳይሉ አድርጓቸዋል።
16 ይሁን እንጂ ለቄሣር መሰጠት ያለባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? መንግሥት ከአንድ ክርስቲያን ሊጠብቃቸው የሚችላቸው አግባብነት ያላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መዝሙር 103:22 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
b የሰኔ 1 እና 15, 1929 መጠበቂያ ግንብ
c ኅዳር 1 እና 15፣ ታኅሣሥ 1, 1962፤ ኅዳር 1, 1990፤ የካቲት 1, 1993፤ ሐምሌ 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ ተመልከት።
ፕሮፌሰር ኤፍ ኤፍ ብሩስ ሮሜ ምዕራፍ 13ን ሲያብራሩ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “በዚህ ምዕራፍ ዙሪያ ያለው ሐሳብና ከዚህ ጋር ዝምድና ያላቸው የሐዋርያት ጽሑፎች የያዙት ሐሳብ እንደሚያሳዩት መንግሥት የማዘዝ መብት ያለው በመለኮታዊ ፈቃድ ከተቋቋመበት ዓላማ ጋር በሚያያዙ ጉዳዮች ረገድ ብቻ ነው። በተለይ መንግሥት ለአምላክ ብቻ ሊሰጥ የሚገባውን የታማኝነት አቋም ለራሱ በሚጠይቅበት ጊዜ ተቃውሞ ሊገጥመው ይችላል፤ ደግሞም ሊገጥመው ይገባል።”
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ ለበላይ ባለ ሥልጣኖች መገዛት ለሰይጣን መገዛት ማለት ያልሆነው ለምንድን ነው?
◻ ኢየሱስ በዘመኑ ለነበረው ፖለቲካ ምን አመለካከት ነበረው?
◻ ኢየሱስ ተከታዮቹ ከቄሣር ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባው ግንኙነት ምን ምክር ሰጥቷቸዋል?
◻ ጳውሎስ ክርስቲያኖች ከብሔራት ገዥዎች ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባው ግንኙነት ምን ምክር ሰጥቷል?
◻ የበላይ ባለ ሥልጣኖችን በተመለከተ የነበረው ግንዛቤ ባለፉት ዓመታት ደረጃ በደረጃ ግልጽ እየሆነ የመጣው እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ፖለቲካዊ ሥልጣን ልስጥህ በማለት ሰይጣን ያቀረበለትን ጥያቄ አልተቀበለውም
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ራስል እውነተኛ ክርስቲያኖች “በዘመናችን በሕግ አክባሪነታቸው የላቀ ደረጃ ከሚሰጣቸው ሰዎች መካከል የሚጠቀሱ መሆን” አለባቸው ሲል ጽፏል