ለሞት አንድ እርምጃ ቀረሽ
“አንዳንድ ጊዜ ምነው ሁለት እግር በኖረኝ ብዬ አስባለሁ። . . . ከበርካታ ዓመታት በፊት ገና ትንሽ ልጅ ሳለሁ ቤቴ አጠገብ ከጓደኞቼ ጋር ለመጫወት ወጣሁ። ድንገት የሆነ ነገር ፈነዳ። ወዲያው ቀኝ እግሬ በሙሉ ተቆርጦ በረረ።”—የ12 ዓመቷ ሶንግ ኮሳል ካምቦዲያ
በእያንዳንዱ ቀን በአማካይ 70 የሚያክሉ ሰዎች በተቀበሩ ፈንጂዎች ምክንያት ይገደላሉ ወይም ለአካል ጉዳተኝነት ይዳረጋሉ። በአብዛኛው በተቀበሩ ፈንጂዎች የሚገደሉት ወይም የሚጎዱት ወታደሮች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ሲቪሎች ማለትም ከብት የሚጠብቁ ሰዎች፣ ውኃ የሚቀዱ ሴቶች ወይም የሚጫወቱ ሕፃናት ናቸው። ለምሳሌ ያህል በዚህ መጽሔት ሽፋን ላይ የምትታየው የስምንት ዓመቷ ሩቂያ ለአካል ጉዳተኝነት የተዳረገችው ሦስት ወንድሞችዋንና አክስቷን በገደለባት የተቀበረ ፈንጂ ነው።
ፈንጂዎች ከተቀበሩ ከ50 ዓመት በኋላ እንኳን ፈንድተው ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ። ስለዚህ ዘ ዲፌንስ ሞኒተር የተባለው ጽሑፍ እንዳለው “ጦርነቱ እየተካሄደ ካለበት ጊዜ ይልቅ ጦርነቱ ካለቀ በኋላ ብዙ ሰዎችን የሚገድል ብቸኛ መሣሪያ ነው።” በመላው ዓለም ምን ያክል ፈንጂዎች ተቀብረው እንደሚገኙ በትክክል የሚያውቅ የለም። ቢያንስ ቢያንስ 60 ሚልዮን ይደርሳሉ የሚል ግምት በብዛት ሲሰነዘር ይሰማል። እርግጥ ነው፣ ብዙ የተቀበሩ ፈንጂዎች እንዲወጡ እየተደረገ ነው። ይሁን እንጂ አሁን በቅርቡ በ1997 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንዳደረገው “አንድ ፈንጂ እንዲመክን በተደረገ ቁጥር 20 ፈንጂዎች ይቀበራሉ። በ1994 በግምት 100, 000 የሚሆኑ የተቀበሩ ፈንጂዎች እንዲወጡ ሲደረግ 2 ሚልዮን ተጨማሪ ፈንጂዎች ተቀብረዋል።”
የሚቀበሩ ፈንጂዎች በብዙ ዘመናዊ የጦር አበጋዞች ዘንድ ተመራጭ መሣሪያዎች የሆኑት ለምንድን ነው? ምን ዓይነት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኪሣራ ያስከትላሉ? በእነዚህ ፈንጂዎች ምክንያት የሚቆስሉ ሰዎችስ ምን ዓይነት ቀውስ ይደርስባቸዋል? ምድራችንስ ከፈንጂዎች የምትጸዳበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© ICRC/David Higgs
Copyright Nic Dunlop/Panos Pictures