የተቀበሩ ፈንጂዎች የሚያስከትሉትን ኪሣራ መመዘን
ታኅሣሥ 26 ቀን 1993 የስድስት ዓመት ልጅ የነበረው አውጉስቶ የአንጎላ ዋና ከተማ በሆነችው በሉዋንዳ አቅራቢያ በሚገኝ መስክ ላይ ሲጫወት በድንገት አንድ የሚያብረቀርቅ ነገር መሬት ላይ ተመለከተ። ይህ የሚያብረቀርቅ ነገር ስላጓጓው አንስቶ ለማየት ወሰነ። ከዚያ ቀጥሎ ያደረገው ነገር አንድ የተቀበረ ፈንጂ እንዲፈነዳ ምክንያት ሆነ።
በዚህ ፍንዳታ ምክንያት የአውጉስቶ ቀኝ እግር ለመቆረጥ በቃ። በአሁኑ ጊዜ 12 ዓመት የሆነው ሲሆን አብዛኛውን ጊዜውን በጋሪ ወንበር ላይ ለማሳለፍ ከመገደዱም በላይ ዓይነ ሥውር ሆኗል።
አውጉስቶ የአካል ጉዳተኛ የሆነው በፀረ ሰው ፈንጂ ነው። ይህ ዓይነቱ ፈንጂ ፀረ ሰው የተባለበት ምክንያት ዋነኛ ዒላማው ታንክ ወይም ወታደራዊ ተሽከርካሪ ሳይሆን ሰው በመሆኑ ነው። እስከ ዛሬ ድረስ ከ350 የሚበልጡ የፀረ ሰው ፈንጂ ዓይነቶች ከ50 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ እንደሚሠሩ ይገመታል። ከእነዚህ ፈንጂዎች መካከል ብዙዎቹ እንዲገድሉ ሳይሆን እንዲያቆስሉ ሆነው የተሠሩ ናቸው። ለምን? ምክንያቱም ቁስለኛ ወታደሮች እርዳታ ስለሚያስፈልጋቸውና በፈንጂ የተቆረጠ ወታደር በወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተጽእኖ ስለሚኖረው ነው። ይህ ደግሞ ጠላት የሚፈልገው ነገር ነው። ከዚህም በላይ ቁስለኛ ወታደር የሚያሰማው የመቃተት ጩኸት በጓዶቹ ላይ ከፍተኛ ፍርሃት ያሳድራል። ስለዚህ የተቀበሩ ፈንጂዎች ይበልጥ ውጤታማ እንደሆኑ ተደርገው የሚታዩት ተጎጂው ሰው በሕይወት በሚተርፍበት ጊዜ ነው።
ይሁን እንጂ ባለፈው ርዕስ እንደተገለጸው አብዛኞቹ የተቀበረ ፈንጂ ሰለባዎች ወታደሮች ሳይሆኑ ሲቪሎች ናቸው። ይህ የሚሆነው ሁልጊዜ እንደ አጋጣሚ አይደለም። ላንድ ማይንስ —ኤ ዴድሊ ሌጋሲ የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው አንዳንድ ፈንጂዎች “ሆን ተብለው በሲቪል ሰዎች ላይ የታለሙ ናቸው። ይህም የሆነው አንዳንድ አካባቢዎችን ሰው አልባ ለማድረግ ወይም የምግብ ማግኛ ምንጮችን ለማጥፋት ወይም የስደተኞች ፍልሰት እንዲፈጠር ለማድረግ አለበለዚያም ፍርሃት ለመልቀቅ ሲባል ነው።”
አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያክል በካምቦዲያ በነበረው ግጭት ፈንጂዎች በጠላት መንደሮች ዙሪያ ይቀበሩና በመንደሮቹ ላይ የመድፍ እሩምታ እንዲወርድ ይደረግ ነበር። ሲቪል ነዋሪዎች ከመድፉ ተኩስ ለመሸሽ ሲሉ በቀጥታ ፈንጂዎቹ ወደተቀበሩበት ቀጠና ይገባሉ። በዚሁ ላይ የክሜር ሩዥ አባሎች መንግሥት ከእነርሱ ጋር እንዲደራደር ለማስገደድ ሲሉ በሩዝ እርሻ ውስጥ ፈንጂዎችን በመቅበራቸው ገበሬዎች ከፍተኛ ፍርሃት አድሮባቸው የግብርና ሥራ ሙሉ በሙሉ ሊቆም ችሏል።
በ1988 በሶማሊያ የተፈጸመው ሁኔታ ከዚህ በጣም የከፋ ነበር። ሐርጌሳ በቦምብ በተደበደበች ጊዜ ነዋሪዎቹ ከአካባቢው ለመሸሽ ተገደው ነበር። ከዚያም ወታደሮች ሰው አልባ በሆኑት ቤቶች ውስጥ ፈንጂዎችን ቀበሩ። ጦርነቱ አልቆ ስደተኞቹ ወደ ቀዬአቸው ሲመለሱ ተሰውረው በተቀበሩት ፈንጂዎች ምክንያት ለሞት ወይም ለአካል ጉዳተኝነት ተዳርገዋል።
ይሁን እንጂ የተቀበሩ ፈንጂዎች ጉዳት የሚያደርሱት በሕይወት፣ በእጅና በእግር ላይ ብቻ አይደለም። እነዚህ አደገኛ መሣሪያዎች የሚያስከትሏቸውን ሌሎች ጉዳቶች ተመልከት።
ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኪሣራ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ኮፊ አናን እንደሚከተለው ብለዋል:- “አንድ የተቀበረ ፈንጂ መኖሩ ሌላው ቀርቶ ሊኖር ይችላል የሚለው ፍርሃት እንኳ አንድ ሙሉ ማሳ ሳይታረስ ጦሙን እንዲያድር ሊያደርግ፣ የአንድን ሙሉ መንደር መተዳደሪያ ሊያጠፋና አንድ አገር ለመልሶ ግንባታና ለእድገት የሚያደርገውን ጥረት ሊያደናቅፍ ይችላል።” በመሆኑም በአፍጋኒስታንና በካምቦዲያ ገበሬዎች አንዳንድ አካባቢዎችን ለመርገጥ ባይፈሩ ኖሮ 35 በመቶ የሚያክል ተጨማሪ መሬት ሊታረስ ይችል ነበር። አንዳንዶች አደጋውን ለመጋፈጥ ደፍረዋል። አንድ የካምቦዲያ ገበሬ ግን “ፈንጂዎችን በጣም እፈራለሁ። ይሁን እንጂ ወጥቼ ሣር ካላጨድኩና ቀርከሃ ካልቆረጥኩ ለመኖር አንችልም” ብሏል።
በተቀበሩ ፈንጂዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ከባድ የገንዘብ ችግር ይገጥማቸዋል። ለምሳሌ ያህል በአንድ አዳጊ አገር አንድ እግሩን በአሥር ዓመት እድሜው ያጣ ልጅ በሕይወት ዘመኑ ውስጥ 15 የሚያክሉ ሰው ሠራሽ አካሎችን መለወጥ ያስፈልገዋል። እያንዳንዱ ሰው ሠራሽ አካል በአማካይ እስከ 125 ዶላር ያወጣል። ይህ ገንዘብ ለአንዳንዶች ብዙ ላይሆን ይችላል። እንደ አንጎላ ባሉ አገሮች ለሚኖሩ ብዙ ሰዎች ግን 125 ዶላር ማለት ከሦስት ወር ደሞዝ በላይ ነው!
በተጨማሪም ፈንጂዎች የሚያስከትሉትን ማኅበራዊ ኪሳራ እንመልከት። ለምሳሌ ያህል በአንድ የእስያ አገር የሚኖሩ ሰዎች “መጥፎ ዕድል” ያጋጥመናል ብለው ስለሚፈሩ እጃቸው ወይም እግራቸው ከተቆረጡ ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ማኅበራዊ ግንኙነት አያደርጉም። አንድ የአካል ጉዳት የደረሰበት ሰው ጋብቻ የመመሥረት ዕድሉ በጣም አነስተኛ ነው። በተቀበረ ፈንጂ ከቆሰለ በኋላ እግሩ የተቆረጠ አንድ አንጎላዊ “ለማግባት አላስብም። ሊሠራ የማይችል ባል የምትፈልግ ሴት እንዴት ዓይነት ሴት ነች?” ሲል በምሬት ተናግሯል።
ብዙ የአካል ጉዳተኞች ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅ ማለቱ የሚጠበቅ ነገር ነው። አንድ ካምቦዲያዊ “ከእንግዲህ ቤተሰቤን መመገብ አልችልም። ይህም በጣም ያሳፍረኛል” ብሏል። አንዳንድ ጊዜ እጅ ወይም እግር ከማጣት ይበልጥ የሚጎዳው እንዲህ ያለው ስሜት ነው። “ከሁሉ የከፋው የደረሰብኝ ስሜታዊ ጉዳት እንደሆነ ይሰማኛል” ይላል በሞዛምቢክ በፈንጂ ምክንያት አካሉን ያጣ አርቱር የተባለ ሰው። “ብዙ ጊዜ አንድ ሰው እንዲሁ ስላየኝ ብቻ እናደዳለሁ። ማንም ሰው የሚያከብረኝ መስሎ አይሰማኝም። ከእንግዲህ ወዲህ እንደ በፊቱ ያለ ጤናማ ሕይወት የምኖር አይመስለኝም።”a
ፈንጂዎችን የመጥረጉ ጥረትስ?
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አገሮች በፈንጂዎች መጠቀምን እንዲያግዱ የተጧጧፈ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። በተጨማሪም አንዳንድ መንግሥታት አደገኛ የሆነውን የተቀበሩ ፈንጂዎች የመጥረጉን ሥራ ተያይዘውታል። ይሁን እንጂ በርካታ የሆኑ እንቅፋቶች አጋጥሟቸዋል። አንደኛው እንቅፋት ፈንጂዎችን የመጥረግ ሥራ በጣም አዝጋሚና ብዙ ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑ ነው። እንዲያውም ፈንጂ ጠራጊዎች እንደሚገምቱት በአማካይ አንድ ፈንጂ ለማስወገድ ያንኑ ፈንጂ ለመቅበር ከፈጀው ጊዜ እስከ መቶ እጥፍ የሚደርስ ጊዜ ያስፈልጋል። ሌላው እንቅፋት ደግሞ የገንዘብ ወጪ ነው። አንድ ፈንጂ ከ3 እስከ 15 ዶላር የሚያወጣ ሲሆን ያንኑ ፈንጂ ለማስወገድ ግን እስከ 1, 000 ዶላር ወጪ ይጠይቃል።
ስለዚህ ሙሉ በሙሉ ፈንጂዎችን ማስወገድ የሚቻል ነገር አይደለም። ለምሳሌ ያህል በካምቦዲያ የተቀበሩትን ፈንጂዎች በሙሉ ለማስወገድ በዚያች አገር የሚኖር እያንዳንዱ ሰው የሚያገኘውን ገንዘብ በሙሉ በመጪዎቹ በርካታ ዓመታት ለዚህ ተግባር ብቻ ማዋል ይኖርበታል። ገንዘቡ ቢገኝ እንኳ በዚያ የተቀበሩትን ፈንጂዎች በሙሉ ለማስወገድ ከመቶ ዓመት በላይ እንደሚፈጅ ይገመታል። በሌሎቹ የዓለም ክፍሎች ያለው ሁኔታ ከዚህ የበለጠ አስቸጋሪ ነው። በአሁኑ ጊዜ በሚሠራበት ቴክኖሎጂ በመጠቀም መላይቱን ምድራችንን ከፈንጂ ለማጽዳት ከ33 ቢልዮን ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ ሲጠይቅ ከአንድ ሺህ የሚበልጥ ዓመት ይፈጃል!
የተቀበሩ ፈንጂዎችን ለማስወገድ የሚረዱ አዳዲስ ዘዴዎች መገኘታቸው ይታወቃል። ፈንጂ ጠቋሚ የዝንብ ዝርያዎችን ከመጠቀም እስከ በራዲዮ ጨረር የሚነዱና ሁለት ሄክታር የሚያክል መሬት በአንድ ሰዓት ውስጥ ለማጽዳት እስከሚችሉ ግዙፍ ተሽከርካሪዎች የሚደርሱ የተለያዩ ዘዴዎች ተገኝተዋል። ይሁን እንጂ እንደ እነዚህ ያሉት ዘዴዎች በስፋት ሥራ ላይ ለመዋል ገና ብዙ ጊዜ የሚቀራቸው ሲሆን ተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉትም በሀብታሞቹ አገሮች ብቻ ይሆናል።
ስለዚህ በብዙ አካባቢዎች ፈንጂ የመጥረግ ሥራ የሚከናወነው ኋላ ቀር በሆነው የቆየ ዘዴ ነው። አንድ ሰው በሆዱ እየተሳበ ከፊቱ ያለውን አፈር በበትር መታ መታ እያደረገ በቀን ውስጥ ከ20 እስከ 50 ካሬ ሜትር ቦታ ብቻ ያጸዳል። ይህ አሠራር አደገኛ ነው? ምንም ጥያቄ የለውም! 5, 000 ፈንጂዎች በሚጠረጉበት ጊዜ አንድ ፈንጂ ጠራጊ ሲገደል ሁለቱ ደግሞ ጉዳት ይደርስባቸዋል።
ፈንጂዎችን ለማስወገድ የተደረገ የጋራ ጥረት
በታኅሣሥ ወር 1997 ከበርካታ አገሮች የተውጣጡ ተወካዮች ፀረ ሰው ፈንጂዎችን መጠቀምን፣ ማከማቸትን፣ ማምረትንና ማስተላለፍን የሚያግደውን ውል ተፈራረሙ። ይህ ውል የኦታዋ ስምምነት ተብሎም ይጠራል። የካናዳ ጠቅላይ ሚንስትር የሆኑት ዣን ክሬቲየ እንደተናገሩት “ይህ በዓለም አቀፍ የጦር መሣሪያ ቅነሳም ሆነ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግ ተወዳዳሪና አቻ የሌለው ውጤት ነው።”b ይሁን እንጂ እስከ አሁን ድረስ ታላላቆቹን ፈንጂ አምራቾች ጨምሮ 60 የሚያክሉ አገሮች ይህን ስምምነት አልፈረሙም።
የኦታዋው ስምምነት የተቀበሩ ፈንጂዎች የሚያስከትሉትን መቅሰፍት ለማስወገድ ይችል ይሆን? ምናልባት በመጠኑ ሊቀንስ ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ብዙዎች በዚህ ረገድ ጥርጣሬ አላቸው። በፈረንሳይ አገር የሚገኘው ሃንዲካምፕ ኢንተርናሽናል የተባለ ድርጅት ተባባሪ ዲሬክተር የሆኑት ክሎድ ሲሞኖ እንደሚከተለው ብለዋል:- “ሁሉም አገሮች የኦታዋውን ስምምነት ቢቀበሉና ቢያከብሩ እንኳን ዓለማችንን ከፈንጂ አደጋ ለማጽዳት ከሚደረገው ጥረት አንድ እርምጃ ብቻ ከመሆን አያልፍም።” ለምን? ሲሞኖ እንደሚሉት “በሚልዮን የሚቆጠሩ ፈንጂዎች መሬት ውስጥ ተቀብረው ጉዳት የሚያደርሱበትን ጊዜ በትዕግሥት መጠባበቃቸው አይቀርም።”
የውትድርና ታሪክ ምሁር የሆኑት ጆን ኬገን ሌላም ምክንያት ይጠቅሳሉ። ጦርነት “የሚመነጨው ኩራት ነግሦ ከሚገኝበት፣ የስሜት መነሳሳት ከሚኖርበትና ግብታዊነት ከሚነግሥበት . . . የሰዎች ልብ ነው” ሲሉ ጽፈዋል። በሰው ልብ ውስጥ ሥር ሰድደው የሚገኙት እንደ ጥላቻና ስግብግብነት ያሉት ጠባዮች በውሎችና በስምምነቶች ሊወገዱ አይችሉም። ይሁን እንጂ እንዲህ ስለ ተባለ የሰው ልጆች ዝንተ ዓለም የፈንጂ ተጠቂ እንደሆኑ ይኖራሉ ማለት ነውን?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በአካል ላይ ከሚደርስ ጉዳት እንዴት ማገገም እንደሚቻል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሐምሌ 1999 ንቁ! እትም “የአካል ጉዳተኞች ያላቸው ተስፋ” የሚለውን ርዕስ ከገጽ 3-10 ተመልከት።
b ስምምነቱ ከመጋቢት 1, 1999 ጀምሮ ሥራ ላይ ውሏል። እስከ ጥር 6, 2000 ድረስ 137 አገሮች ይህን ስምምነት የፈረሙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 90 የሚሆኑት አገሮች አጽድቀውታል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሁለት ጊዜ የገንዘብ ትርፍ ማግኘት?
ኩባንያዎች ያመረቷቸው ምርቶች ጉዳት የሚያስከትሉ ከሆነ ካሣ የመክፈል ግዴታ የሚጣልባቸው መሆኑ መሠረታዊ የንግድ ሕግ ነው። በዚህ ምክንያት የፈንጂ አማካሪዎች ቡድን አባል የሆኑት ሉ ማክግራት “ፈንጂዎችን በማምረት ትርፍ ያገኙ ኩባንያዎች ካሣ የመክፈል ግዴታ ሊጣልባቸው ይገባል” ብለው ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ፈንጂ አምራቾች ፈንጂ ከመጥረግም ትርፍ የሚያገኙ መሆናቸው በጣም እንግዳ ነገር ሆኗል። ለምሳሌ ያህል ፈንጂ አምራች የሆነ አንድ የጀርመን ኩባንያ የመቶ ሚልዮን ዶላር ፈንጂ የመጥረግ ኮንትራት በኩዌት እንዳገኘ ሪፖርት ተደርጓል። በሞዛምቢክም 7.5 ሚልዮን ዶላር የሚያወጣ ጎዳናዎችን ከፈንጂ የመጥረግ ኮንትራት ለሦስት ኩባንያዎች የተሰጠ ሲሆን ሁለቱ ፈንጂ በመሥራት ሥራ ተሰማርተው የነበሩ ናቸው።
ፈንጂዎችን ያመርቱ የነበሩ ኩባንያዎች ፈንጂዎችን ከመጥረግም የገንዘብ ትርፍ የሚያገኙ መሆናቸው በጣም ከፍተኛ የሥነ ምግባር ጉድለት እንደሆነ አንዳንዶች ይሰማቸዋል። ፈንጂዎችን የሚሠሩ ድርጅቶች ሁለት ጊዜ ትርፍ እንደሚያገኙ ይሰማቸዋል። በዚያም ሆነ በዚህ የሚቀበሩ ፈንጂዎችን ማምረትም ሆነ ማስወገድ ብዙ ትርፍ የሚያስገኝ ንግድ እንደሆነ ቀጥሏል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ፈንጂ በብዛት በተቀበረባቸው ዘጠኝ አገሮች በአማካይ በ 2.5 ስኴር ኪሎ ሜትር ውስጥ የተቀበሩ ፈንጂዎች ብዛት
ቦስኒያ እና ሄርዜጎቪና 152
ካምቦዲያ 143
ክሮኤሺያ 137
ግብፅ 60
ኢራቅ 59
አፍጋኒስታን 40
አንጎላ 31
ኢራን 25
ሩዋንዳ 25
[ምንጭ]
ምንጭ:- የተባበሩት መንግሥት የሰብአዊ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት፣ 1996
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በካምቦዲያ፣ የተቀበሩ ፈንጂዎች መኖራቸውን የሚያስጠነቅቁ ሥዕላዊ መግለጫዎችና ምልክቶች
5, 000 የተቀበሩ ፈንጂዎች እንዲወጡ በተደረገ ቁጥር አንድ ፈንጂ ጠራጊ ሲገደል ሁለት ደግሞ ይቆስላሉ
[ምንጮች]
ከበስተጀርባ ያለው ሥዕል:- © ICRC/Paul Grabhorn
© ICRC/Till Mayer
© ICRC/Philippe Dutoit