ሰዓት አክባሪ ሁን!
“ዘግይቶ መድረስ የአስተዳደር ሹማምንትን የተጠናወተ ሥር የሰደደ ችግር ነው” በማለት ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። ዘገባው በ2,700 የአስተዳደር ሹማምንት ላይ የተካሄደን አንድ ጥናት በመጥቀስ “ከ10 ስብሰባዎች ውስጥ ለስድስቱ የሚደርሱት ዘግይተው ነው” ሲል አክሎ ተናግሯል።
በሥራ ዓለም ባሉ ሰዎች ዘንድ ዘግይቶ መድረስ እንደ መጥፎ ልማድ ብቻ ተደርጎ የሚታይ ነገር አይደለም። ሥራ ለመቀጠር ባመለከቱ 81,000 አመልካቾች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንደጠቆመው “ዘግይቶ በመድረስና ያለ ፈቃድ ከሥራ በመቅረት የሚባክኑ ሰዓቶች ዋናዎቹ የገንዘብ ኪሣራ መንስኤዎች ናቸው።” እርግጥ ነው፣ ዘግይቶ መድረስ ችግር የሚፈጥረው በሥራ ዓለም ብቻ አይደለም። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራን ላይ የተደረገ አንድ ጥናት “በተማሪዎች ላይ አዘውትሮ የሚከሰተው ዋናው የዲሲፕሊን ጉድለት ዘግይቶ መድረስ” እንደሆነ ገልጿል።
ፈጣሪያችን የጊዜ ጥቅም የሚገባን ሰዎች እንድንሆን ይፈልጋል። “ሁለት ታላላቅ ብርሃናት” ማለትም ፀሐይንና ጨረቃን ያደረገልን ጊዜን ለመቁጠር እንዲረዱን ብሎ ነው። (ዘፍጥረት 1:14-16) በአሁኑ ጊዜ ዘመናዊ የሆኑ የጊዜ መቁጠሪያዎች ጊዜን በደቂቃና በሴኮንድም ሳይቀር ከፋፍለን ለመቁጠር ያስችሉናል። ሆኖም በቴክኖሎጂ ብዙ መሻሻል ቢደረግም ብዙዎቻችን አሁንም ወደ ሥራ፣ ወደ ትምህርት ቤት ወይም ወደ ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች በሰዓቱ ለመድረስ እንቸገራለን።
ታዲያ ችግሩ የጊዜ እጦት ብቻ ነው? ሥራና የቤተሰብ ኃላፊነት ጊዜያችንን ሊያጣብቡብን እንደሚችሉ እሙን ነው። ሆኖም ዋንዳ ሮዝላንድ የተባለች ተቀጥራ የምትሠራ አንዲት እናት እንደሚከተለው ብላለች:- “ሁሉም ሰው በቀን ውስጥ ያለው ጊዜ ያው 24 ሰዓት መሆኑን ስገነዘብ በቂ ጊዜ የለኝም እያልኩ ማማረሬን አቆምኩ። በጉዳዩ ላይ ካሰብኩበት በኋላ በዘመናችን ጊዜ እንዳጠረን ሆኖ የሚሰማን ያለን ጊዜ አንሶ ሳይሆን ብዙ የሚያባክኑና ሐሳብ የሚበታትኑ ነገሮች በመኖራቸው እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ።”
የአምስት ልጆች እናት የሆነችውን ረኔa የተባለች የይሖዋ ምሥክር እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “ልጆቼ ትንንሾች ሳሉ እነሱን ለትምህርት ቤትና ለስብሰባዎች ማዘጋጀት ከባድ ሥራ ነበር። ያም ሆኖ በሰዓት የመድረስ ችግር አልነበረብኝም። አሁን ግን ሁሉም አድገው ራሳቸውን ሲችሉ የመዘግየት መጥፎ አመል ተጠናወተኝ።” አንተም እንዲህ ያለ መጥፎ አመል አለብህ? ካለብህ ይህን አመል ማስወገድ ትችላለህ! ልታደርጋቸው የምትችላቸው ነገሮች ከዚህ በታች ቀርበዋል።
● መዘዙን አስብ። ሥር የሰደደ የማርፈድ ልማድ ቀላል ነገር መስሎ ይታይ ይሆናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “የሞቱ ዝንቦች ሽቶን እንደሚያገሙ፣ ትንሽ ሞኝነትም ጥበብንና ክብርን ያቀላል” ይላል። (መክብብ 10:1) አዎን፣ ለሌሎች አሳቢነት ባለማሳየት የሚገለጽ “ትንሽ ሞኝነት” በመምህርህ ወይም በአሠሪህ ዘንድ የሚኖርህን መልካም ስም ሊያበላሽብህ ይችላል።
ማሪ የተባለች አንዲት ሴት በአካባቢዋ በሚገኝ ኮሌጅ አንዳንድ ኮርሶችን በምትወስድበት ወቅት አንዳንዶቹ የክፍል ጓደኞቿ “ስለ ጊዜ በጣም ግዴለሾች” እንደነበሩና አብዛኛውን ጊዜ ዘግይተው ወደ ክፍል ይገቡ እንደነበር አስተውላለች። “ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ይህን ልማዳቸውን ለመለወጥ ተገደዱ” በማለት ታስታውሳለች። “ከመምህራኑ መካከል ሁለቱ በሰዓት መድረስን በተመለከተ ጥብቅ አቋም ነበራቸው። ስለዚህ ማንኛውም ተማሪ ጥቂት ደቂቃዎች ዘግይቶ ቢደርስ በስም ጥሪው ላይ የቀሪ ምልክት ይደረግበት ነበር። ብዙ ጊዜ ቀሪ ተብሎ ከተመዘገበ ደግሞ ውጤቱ ሊቀነስበትና ሊወድቅ ይችላል።”
ሥር የሰደደ ዘግይቶ የመድረስ አመል በጓደኞችህና በእኩዮችህ ዘንድ ያለህን ስምም ሊያበላሽብህ ይችላል። በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ጆሴፍ የሚባል አንድ ሰው ከአሥርተ ዓመታት በፊት የሚያውቀውን አንድ የእምነት ባልደረባውን ያስታውሳል። ይህ ሰው በማስተማር ችሎታው የተከበረ ቢሆንም አንድ የሚያሳፍር ጉድለት ነበረበት። “ምንጊዜም እንዳረፈደ ነበር” በማለት ጆሴፍ ያስታውሳል። “ለሁሉም ነገር የሚደርሰው ዘግይቶ ነበር! የሚገርመው ደግሞ ይህ አመል ፈጽሞ የሚያሳስበው አይመስልም ነበር። ሰዎች በዚህ አመሉ የተነሳ ይቀልዱበት ነበር።” አንተም በሰዎች ዘንድ የምትታወቀው በአርፋጅነት ነው? ከሆነ ይህ አመል ሰዎች ያሉህን ሌሎች ጥሩ ባሕርያት እንዳይመለከቱ ሊያደርጋቸው ይችላል።
● ለሌሎች አሳቢ ሁን። ዘግይቶ መድረስ ሰውን አለማክበር ከመሆኑም በላይ ሌሎችን የሚያስቆጣ ድርጊት ነው። በተጨማሪም ራስህን ከሌሎች አስበልጠህ እንደምታይ ሊያስመስልብህ ይችላል። አንድ ነጋዴ ብዙ የአስተዳደር ሹማምንት ስብሰባዎች ላይ ለምን ዘግይተው እንደሚደርሱ ሲገልጽ “አብዛኞቻችን ትዕቢተኞች ስለሆንን ነው” ብሏል። በተቃራኒው ክርስቲያኖች ሌሎች ከእነሱ እንደሚበልጡ አድርገው ይቆጥራሉ። (ፊልጵስዩስ 2:3) በተጨማሪም ወርቃማውን ሕግ በሥራ ላይ በማዋል ለእነርሱ እንዲደረግላቸው የሚፈልጉትን ነገር ለሌሎችም ያደርጋሉ። (ማቴዎስ 7:12) ሰው ቀጥሮህ ብዙ ሰዓት ሲያስጠብቅህ አያበሳጭህም? እንግዲያው አንተም ሰው ቀጥረህ አትዘግይ።
● የጊዜ አጠቃቀም ችሎታን አዳብር። ዛሬ ነገ እያልክ ከቆየህ በኋላ በመጨረሻዋ ሰዓት ለመሥራት ትቻኮላለህ? በአጭር ጊዜ ብዙ ነገር ለመሥራት በማቀድ ትዋከባለህ? በመክብብ 3:1 ላይ የተጠቀሰው ‘ለሁሉ ጊዜ አለው’ የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ሊረዳህ ይችላል። ለምንሠራቸው ነገሮች “ጊዜ” መመደባችን ሁሉንም በቅደም ተከተል ማከናወን እንድንችል ይረዳናል።
በመጀመሪያ ልትሠራቸው የሚገቡትን ነገሮች በዝርዝር ጻፍ። ቀጥሎም ‘ከሁሉ የሚሻለውን ለይተን እንድናውቅ’ የሚያበረታታውን በፊልጵስዩስ 1:10 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት አድርግ። አዎን፣ መቅደም የሚገባቸውን ነገሮች አስቀድም። የግድ መሠራት ያለበት ነገር ምንድን ነው? በይደር ብናስተላልፋቸው ጉዳት የማያስከትሉት ነገሮችስ የትኞቹ ናቸው? በመጨረሻም ልትሠራቸው ያሰብካቸውን ነገሮች ለማከናወን ምን ያህል ጊዜ እንደሚያስፈልግህና መቼ ልትሠራቸው እንደምትችል አስላ። ይህን ስታደርግ ተጨባጩን ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባትና ሚዛናዊ መሆን ይኖርብሃል። በትንሽ ጊዜ ውስጥ ብዙ ነገሮችን ለመሥራት ከማቀድ መቆጠብ ያስፈልግሃል።
ዶረቲ የምትባል አንዲት ሴት ወላጆቿ ሰዓት አክባሪ እንድትሆን እንዳስተማሯት ትናገራለች። እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “በክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከምሽቱ በ1:30 መድረስ ካለብን እናቴ ከስብሰባው ሰዓት አንድ ሰዓት ከ45 ደቂቃ ቀደም ብለን መሰናዳት እንድንጀምር ታደርገን ነበር። ራት ለመብላት፣ ከራት በኋላ ዕቃዎቹን ለማጣጠብ፣ ለመለባበስና ወደ ስብሰባ ቦታው በመኪና ለመሄድ ጊዜ መመደብ ነበረብን። በሰዓት መድረስ ልማዳችን ሆኖ ነበር።” አንዳንድ ጊዜ ላልተጠበቁ አጋጣሚዎችም ጊዜ መመደብ ጠቃሚ ነው። ዶረቲ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “በቅርቡ ጥቂት ሰዎችን ከያሉበት በመኪናዬ አሳፍሬ ወደ ስብሰባ ይዤ መሄድ ነበረብኝ። መንገድ ላይ እንዳለሁ የመኪናዬ ጎማ ተነፈሰ። ጎማውን አሠርቼ፣ ሰዎቹንም ይዤ በሰዓት ለመድረስ ቻልኩ። ለዚህ የጠቀመኝ፣ መኪናዬ ድንገት ቢበላሽ ወይም የመንገድ ጭንቅንቅ ቢያጋጥመኝ በሚል በቂ ጊዜ የምመድብ መሆኑ ነው።”
● የሌሎችን ምክር ተቀበል። መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 27:17 ላይ “ብረት ብረትን እንደሚስል፣ ሰውም ሌላውን ሰው እንደዚሁ ይስለዋል” ይላል። ከዚህ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በመስማማት ከአንተ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ቢኖራቸውም እንኳ ጉዳዮቻቸውን ለማከናወን በሰዓቱ የመድረስ ልማድ ያላቸውን ሰዎች ቀርበህ አነጋግር። ጠቃሚ የሆነ ምክር ሊለግሱህ ይችላሉ።
ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ረኔ ዘግይቶ የመድረስ ልማዷን ለመተው ቆርጣ ተነሳች። እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “በቅርቡ ለመሻሻል ቆርጬ ተነሳሁ። ቀላል ሆኖ ባላገኘውም መጠነኛ መሻሻል እያደረግሁ ነው።” ስለዚህ አንተም ለውጥ ማድረግ ትችላለህ። ትክክለኛ አመለካከት በመያዝና ጥረት በማድረግ በሰዓቱ የመድረስ ልማድ ማዳበር ትችላለህ!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሁልጊዜ ዘግይቶ የመድረስ ልማድ ያለው ሰው በአሠሪዎች ዘንድ መጥፎ ስም ሊያተርፍና ለሌሎች አሳቢነት እንደሌለው ተደርጎ ሊታይ ይችላል
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በፕሮግራም የምትመራ ከሆነ ጊዜ መቆጠብ ትችላለህ