ሁልጊዜ ትዘገያለህን?
ሁለት ወጣቶች ቅዳሜ ዕለት በ8 ሰዓት በቤታቸው ውስጥ ለሚደረገው ግብዣ የመጥሪያ ወረቀቶችን እያዘጋጁ ነበር። ሁለቱ ጓደኞቻቸው ግን ብዙውን ጊዜ ዘግይተው እንደሚደርሱ በማሰብ አንደኛው ልጅ:- “በእነርሱ የጥሪ ወረቀት ላይ 7 ሰዓት ብለን ለምን አንጽፍም? መዘግየታቸው ስለማይቀር ልክ በሰዓቱ በ8 ሰዓት ላይ ይደርሳሉ” አለ። በእርግጥም እርሱ ያለው ነገር እውነት ሆነ!
መዘግየት የሚያስከትላቸው ችግሮች በሙሉ ይህን የመሰለ ቀላል መፍትሔ የሚያገኙ አይደሉም። እንዲያውም በሰዓቱ ለመገኘት አለመቻል ዘግይቶ በሚመጣውም ሰው ላይ ሆነ እርሱን ለመጠበቅ በሚገደዱት ሰዎች ላይ ከባድ ችግር ሊፈጥር ይችላል። እውነት ነው፣ ሰዓትን ጠብቆ ስለመገኘት አጥብቀው የሚያስቡት በሁሉም ባሕሎች ሥር የሚኖሩ ሰዎች አይደሉም። ይሁንና የምትኖረው የትም ይሁን የት ለአይሮፕላን በረራ፣ ለመደበኛ ስብሰባዎች፣ ለሥራና ለአንዳንድ ማሕበራዊ ቀጠሮዎች በጊዜ ስለመገኘት አጥብቀህ ማሰብ ይገባሃል።
ስለዚህ አርፍዶ መድረስን የምታዘወትር ከሆነ በሰዓትህ ለመገኘት ምን ሊረዳህ ይችላል? ሌሎች ሰዎች ብዙ ሰዓት የሚያስጠብቁህ ከሆነስ በአብዛኛዎቹ ሰዎች ዘንድ የተለመደውን ይህንን ችግር ለመቋቋም ምን ሊረዳህ ይችላል?
ዘግይተህ መገኘትን ልማድ አድርገሃልን? በመጀመሪያ የችግሩን መንስኤ ለይተህ ለማወቅ ጣር። ትኩረትህ በቀላሉ ወደ ሌሎች ጉዳዮች ያዘነብላልን? ራስህንም ሆነ ቤተሰብህን በማደራጀት በኩል ትልቅ ችግር አለብህን? እንደዚህ ያሉትን የሚያዘገዩ ምክንያቶች ንቁ ክትትልና ጥረት በማድረግ ማሸነፍ ይቻላል። ለምሳሌ ዘወትር በየዕለቱ ለምታከናውናቸው የተለመዱ ሥራዎች ጊዜ ወስንና ሥራዎቹን ከተመደበላቸው ጊዜ አስቀድመህ ለመጨረስ የሚያስችል እቅድ አ ውጣ። ያወጣኸውን የጊዜ ገደብ ጠብቀህ እንደሆነና እንዳልሆነ በየአንድ ሰዓቱ ወይም በተመሳሳይ የጊዜ ልዩነት አረጋግጥ። በጣም አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች ለያዝከው ቀጠሮ ልክ በሰዓቱ ለመድረስ ከመሞከር ይልቅ ትንሽ ቀደም ብለህ ለመገኘት ግብ አውጣ። ይሁን እንጂ ዘግይቶ የመገኘት ቸግርህ ከዚህ ይበልጥ ሥር የሰደደ ሊሆን ይችላል።
ስነ ልቦናዊ ምክንያቶች
አንዳንድ ጊዜ ዘግይቶ ለመድረስ ምክንያት የሚሆኑ የተደበቁ ዓላማዎች ይኖራሉ። ደስ ከማይሉ ሁኔታዎች ለመራቅ፣ ተፈላጊ መሆናቸውን ለማሳየት፣ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ወይም ደግሞ ቀደም ብሎ ሄዶ ሌሎችን ላለመጠበቅ ሲባል የሚዘገዩ ሰዎች አሉ።
ዶክተር ድሩ ስኮት ከዚህ ይበልጥ ረቀቅ ስላለ የመዘግየት ምክንያት ተናግረዋል:- “አንድ የንግድ ሰው ከደንበኛው ጋር በያዘው በጣም አስፈላጊ የሆነ ቀጠሮ ላይ ለመገኘት ሁሉን ነገር አስተካክሎ ከቢሮው ከወጣ በኋላ ‘አንድ ቦታ ብቻ ስልክ ልደውል’ ብሎ እንደገና ይመለሳል። በአይሮፕላን ተሳፍራ ለመሄድ ጉዞ የጀመረች ጠበቃ ‘አንድ ደብዳቤ ብቻ’ ለመጻፍ መዘግየት እንዳለባት ሆኖ ይሰማታል። እንዲህ ካለው ወላዋይነት አሉታዊ የሆነ አንቀሳቃሽ ግፊት ያገኛሉ። ይህም የሚያስደስታቸውን የመጨረሻ ደቂቃ መሯሯጥ ይፈጥርላቸዋል።”
አዎን፣ በመጨረሻ ደቂቃ ላይ የሚደረግ ሩጫ አስደሳች ባይሆንም እንደነዚህ ያሉት ሰዎች የሚፈልጉትን የስሜት መቀስቀስ ያስገኛል። ከእንዲህ ዓይነቱ ሩጫ ለሚገኘው ደስታ ሱሰኛ እንደሆንክ ሆኖ ከተሰማህ እንዴት ልታሸንፈው ትችላለህ? ድሩ ስኮት እንዲህ ሲሉ ሐሳብ ይሰጣሉ:- “ለሥራ የሚያንቀሳቅስ ግፊት ሁላችንም የሚያስፈልገን ነገር ነው። ይህንን መፈለግ ያለመብሰል ምልክት አይደለም። ጤናማ የሆኑ ሰብዓዊ ፍጡራን የዚህን አስፈላጊነት ይገነዘባሉ። በአግባቡ እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉም ያውቃሉ።”
በሌላ አነጋገር በሳምንቱ ውስጥ ልትሠራ ያወጣሃቸውን እቅዶች ተመልከት። በዚያ ውስጥ የሚያዝናኑ ወይም የሥራ ስሜት የሚቀሰቅሱ ገንቢ እንቅስቃሴዎች ተካተዋል ወይስ ፕሮግራምህ የተለመዱትንና አሰልቺ የሆኑትን ሥራዎች ብቻ የያዘ ነው? የሚሠራቸውን ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠር የሚችል ማንም ሰው የለም፤ ቢሆንም ግን በምትችልበት አጋጣሚ ሁሉ ራስህን የሚያነቃቃ ሥራ ለመሥራት ትኩረት ከሰጠህ ዘግይተህ ከመጣደፍ የሚገኘው ማነቃቂያ ሳያስፈልግ የሕይወትን የዕለት ተዕለት ተግባራት ይበልጥ በቀላሉ ለማከናወን ትችል ይሆናል።
“ስጣደፍ የተሻለ ሥራ እሠራለሁ”
አንዳንድ ሰዎች እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ቆይተው በጥድፊያ ሲሠሩ የተሻለ ሥራ እንደሚሠሩ ይናገራሉ። አንተም እንደነዚህ ሰዎች ከሆንክ ጥሩ ነው። ግን ለራስህ ታማኝ ሁን። በእርግጥ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ቆይተህ በጥድፊ ስትሠራ የተሻለ ሥራ መሥራት ትችላለህን?
ሚካኤል ሌቦይፍ ዎርኪንግ ስማርት በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ የታዘቡትን ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “ምናልባት በጥድፊያ ስንሠራ የተሻለ ሥራ ልንሠራ የምንችል ብንኖር እንኳ የግል እምነታችን ምንም ይሁን ምን ይህን ለማድረግ የምንችለው ጥቂቶች ነን። አንደኛ ነገር፣ በጥድፊያ ለመሥራት ከተገደድክ ስህተት የምትሠራበት አጋጣሚ ከፍተኛ ይሆናል። . . . ሁለተኛ . . . ሌላ ይበልጥ አስቸኳይ ነገር ይመጣና ልትሠራ ላሰብከው ሥራ የመደብከውን ውድ ጊዜ ሊወስድብህ ይችል ይሆናል። . . . ሦስተኛ ደግሞ ሁሉንም ነገር ጥሩ አድርገህ ልትሠራና በትንሽ ጊዜ ውስጥ ብዙ ነገር ልታከናውን ብትችልም እንኳን ይህ የሚያረጋግጠው ውጤታማ ሥራ ለመሥራት እንደምትችልና በጭንቀት ካልተወጠርክ በስተቀር በዚህ ችሎታህ ለመጠቀም እንደማትፈልግ ብቻ ነው። ባለህ ችሎታ ሙሉ በሙሉ ስለማትጠቀም ራስህን ታታልላለህ።
ሌሎችን መጠበቅ ትጠላለህን?
ብዙ ጊዜ ምናልባት አንተ በሰዓትህ ትደርስና በሰዓታቸው መገኘት በማይችሉ ሌሎች ሰዎች ምክንያት እንድትጠብቅ ትገደድ ይሆናል። የማርፈድ ልማድ ያላቸውን የቤተሰብ አባሎች፣ ጓደኞችህን ወይም የሥራ ባልደረቦችህን ልትረዳቸው ወይም ቢያንስ ከእነርሱ ጋር ተግባብተህ ለመኖር የምትችለው እንዴት ነው?
ዘግይቶ የመገኘት ልማድ ያለባቸውን ሰዎች ቀጠሮ እንዳላቸው ቀደም ብለህ በመንገር ወይም ችግሩን አንስተህ በግልጽ በመወያየት ልትረዳቸው ትችል ይሆናል። ምናልባትም የመዘግየት ልማድ ያለባቸው ሰዎች በአስተዳደጋቸው ምክንያት ወይም በራሳቸው ድክመት ምክንያት የሚደረግላችውን ርዳታ የማይቀበሉና ዘግይተው በመገኘት በሌሎች ላይ ችግር በመፍጠር የሚቀጥሉ ይሆናሉ። ያለህበት ሁኔታ ከእንደነዚህ ዓይነት ግለሰቦች ጋር እንድትኖር ወይም እንድትሠራ የሚጠይቅብህ ከሆነ መዘግየታቸውን የሕይወት ሐቅ አድርገህ በመቀበል ችግራቸውን ችለህ አብረህ ለመኖር የሚያስችልህን ዘዴ መቀየስ ትችላለህ።
ለምሳሌ ያህል ምን ያህል ሊያስጠብቁህ እንደሚችሉ አስበህ ይህንን ጊዜ እንዴት እንደምትጠቀምበት ልትዘጋጅ ትችላለህ። ምናልባትም የቀጠሮውን ቦታ በገበያ አዳራሽ ወይም በምግብ ቤት ውስጥ በማድረግ እየተዝናናህ ልትጠብቃቸው የምትችልበትን ሁኔታ ልታመቻች ትችላለህ። ወይም እነርሱን በምትጠብቅበት ጊዜ ለመጠቀም እንድትችል የምትሠራው ወይም የምታነበው ነገር ይዘህ ሂድ። እነርሱ በመዘግየታቸው ምክንያት ልትሄድበት ያሰብከው ሰዓት እንዳያልፍብህ ከእነርሱ ጋር የምትይዘውን የቀጠሮ ሰዓት ቀደም አድርገው። በአንዳንድ ሁኔታዎችም የመዘግየት ልማድ ያላቸውን ሰዎች በፕሮግራምህ ውስጥ እንዳታስገባ ለማድረግ የሚያስችልህ ጥሩ ውሳኔ ላይ ልትደርስ ትችል ይሆናል።
ጥሩ ባሕርይ ካሳየህ ለራስህ ሽልማት ስጥ
በተወሰነው ሰዓት የመድረስ ችግር ካለብህ ለዚህ ድካምህ ምንም ዓይነት ማሳበቢያ ምክንያት አትስጥ ወይም ሌሎች አንተን መጠበቅ እንደሚገባቸው በማሰብ ይህንን ጠባይህን በቸልታ አትለፈው። ስለሌሎች ሕይወትና ስሜት ግድየለሽ መሆን ነው። ለሠርጓ በተደረገው ዝግጅት ላይ ሦስት ሰዓት ዘግይታ የተገኘች ሙሽራ ነበረች። እርሷ በመዘግየቷ ምክንያት ፕሮግራሙን ወደ መኖሪያ ቤት ማዛወር ግዴታ ስለሆነ በሠርጉ ላይ ተገኝተው የነበሩ ከ200 የሚበልጡ ሰዎች ተጉላልተዋል። በእርግጥም ለሌሎች ያለን አሳቢነት ሰዓታችንን አክብረን ለመገኘት ሊገፋፋን ይገባል!
በሰዓትህ ለመገኘት የምታደርገው ጥረት ልክ በሰዓትህ ለመገኘት ብቻ ሳይሆን በአብዛኛዎቹ ቀጠሮዎችና ሥራዎችህ ላይ ቀደም ብለህ ለመገኘት እንደሚያስችልህ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ ሆኖ ሲገኝ አንድ ዓይነት የሚያስደስትህ ነገር በማድረግ ራስህን ሸልም። ዶክተር ስኮት እንዲህ ይላሉ:- “ጊዜ ማግኘት ማለት ገንዘብ ማግኘት ማለት ነው። ይህን ጊዜ በየቀኑ ለምታደርጋቸው የተለመዱ ሥራዎች አታውል። ከዚህ ይልቅ የሚያስደስትህን አንድ ዓይነት ነገር ለማድረግ ተጠቀምበት። ጠዋት ትርፍ አሥር ደቂቃ ብታገኝ ወይም በምሽት ግማሽ ሰዓት ቢኖርህ ወይም በቀኑ የትኛውም ክፍል ውስጥ ጥቂት ደቂቃዎች ብታገኝ ምን ልትሠራ እንደምትፈልግ አስብ። ሥራህን አስቀድመህ ከጨረስክ ባተረፍከው ጊዜ ምን ለማድረግ እንደምትፈልግ ቀደም ብለህ አስብ።”
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ቆይቶ በጥድፊያ የመሯሯጥን ችግር ማሸነፍ የሚቻልባቸው መንገዶች
1. በጣም ሰፊና ከባድ የሆኑትን ሥራዎች ወደ ትንንሽ ሥራዎች ከፋፍላቸው።
2. ሥራውን ለማከናወን የሚያስችልህን የመጀመሪያ አካላዊ እርምጃ ውሰድ። ለምሳሌ ያህል አንድ መጽሐፍ ለማንበብ ዛሬ ነገ እያልክ ዘግይተህ ከሆነ መጽሐፉን ከመደርደሪያ ውስጥ አውጣና በማንበቢያ ወንበርህ አጠገብ አስቀምጠው።
3. ልትሠራ ስላሰብከው ነገር ለሌላ ሰው ቃል ግባ። ለጓደኛህ ወይም ሥራህን በበላይነት ለሚቆጣጠረው ‘ይህን ሥራ በዚህ ጊዜ አጠናቅቀዋለሁ’ ብለህ ንገረው።
4. እያንዳንዱን የምትሠራውን ሥራ ትንንሽ ክፍል በጨረስክ ቁጥር የሚያስደስትህን ነገር በማድረግ ለራስህ ሽልማት ስጥ።
5. ዛሬ ነገ እያልክ እንደምታመነታ ከታወቀህ ‘ ጊዜህን እያባከንክ መሆኑን’ ራስህን አሳምን። ይህ ማሳሰቢያ በመጨረሻ ራስህን እንድትቆጣጠርና ዛሬ ነገ ማለትን ለማቆም ወደ መወሰን ሊመራህ ይችላል።
6. መዘግየትህ ምን ያህል ኪሳራ እያስከተለብህ እንዳለ አስላ። የሥራው ጫና እየጨመረ ይሄዳልን? የሚያስከትለው የገንዘብ ወጪ ይጨምራልን? የመጨረሻዋ ደቂቃ ላይ ስትደርስ ብትታመምስ? የምትሠራው ሥራ ካሰብከው በላይ ጊዜ ቢወስድብህስ? ምናልባት በተደጋጋሚ ሥራህን የሚያቋርጥ ነገር ቢያጋጥምህስ? በመጨረሻ ደቂቃ ላይ የምትሠራው ሥራ ጥራቱ አነስተኛ አይሆንምን? — በአላን ላኬይን ከተጻፈው “ሃው ቱ ጌት ኮንትሮል ኦቭ ዩር ታይም ኤንድ ዩር ላይፍ” ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።
[ሥዕሎች]
ወደ ቀጠሮህ ለመሄድ ከመውጣትህ በፊት ‘አንድ ተጨማሪ ነገር ብቻ’ መሥራት እንደሚያስፈልግህ ይሰማሃልን?
በእርግጥ ተጣድፈህ ስትሠራ የተሻለ ሥራ ታከናውናለህን?
የቀጠርከውን ሰው የምትጠብቅበትን ሰዓት ለመዝናናት ወይም ልትፈጽመው የፈለግኸውን ነገር በመሥራት ተጠቀምበት