ምዕራፍ 7
ንጉሥ የሚሆነውን መሲሕ ለይቶ ማወቅ
1. ነገሮች የሚከናወኑበትን ጊዜ ስለ መወሰን ትንቢት እንዲናገር ይሖዋ በዳንኤል መጠቀሙ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
በምድራዊው የአምላክ መንግሥት ዝግጅት ተካፋይ ለመሆን ትንሣኤ ከሚያገኙት መካከል አንዱ ነቢዩ ዳንኤል ይሆናል። ዳንኤል ይሖዋን በማገልገል ያሳለፈውን ረጅሙን የሕይወት ዘመኑን ሲፈጽም “አንተ ታርፋለህ፣ በቀኖቹም መጨረሻ በዕጣ ክፍልህ ትቆማለህ” ተብሎ ተነግሮታል። ዳንኤል ልክ በዛሬው ጊዜ እንደምንገኘው እንደ እኛ ስለ “ፍጻሜው ዘመን” እና በዚያን ጊዜ ስለሚሆኑት “ድንቅ ነገሮች” ለማወቅ ጥልቅ ስሜት አድሮበት ነበር። ስለዚህ ታላቁ የጊዜ ጠባቂ ይሖዋ አምላክ ስለ መንግሥቲቱ ‘መምጣት’ የሚገልጸውን የጊዜ ሰሌዳ ለመስጠት በነቢዩ ዳንኤል መጠቀሙ ተገቢ ነበር። — ዳንኤል 12:4, 6, 13፤ 11:27, 35፤ ከአሞጽ 3:7፤ ከኢሳይያስ 46:9–11 አወዳድር።
“የኢየሩሳሌም መፍረስ”
2. (ሀ) በ539 ከዘአበ በድንገት የተፈጸመው የትኛው ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት ነው? እንዴትስ? (ለ) ኤርምያስ 25:11, 12 ልክ በሰዓቱ እንዲፈጸም ምን ተአምር አስፈልጎ ነበር?
2 አያሌ መቶ ዘመናት ቀደም ብሎ በተነገረው የይሖዋ ትንቢት መሠረት የባቢሎን ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት በፋርሳዊው ቂሮስና በሜዶናዊው ዳርዮስ ተንኮታኮተ። (ኢሳይያስ 44:24, 27, 28፤ 45:1, 2) ዳርዮስ በቀድሞው የባቢሎን ግዛት ላይ ንጉሥ ሆነ። ይህ የሆነው በ539 ከዘአበ ነበር። ይህ ሲሆን የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደስዋን ካጠፋ፣ የይሁዳን ምድር ባድማ ካደረገ እንዲሁም በሕይወት የተረፉትን አይሁዶች ወደ ባቢሎን ካጋዘ 68 ዓመታት አልፈው ነበር። ስለሆነም አረጋዊው ዳንኤል ዳርዮስ መግዛት በጀመረ በመጀመሪያው ዓመት ላይ “እኔ ዳንኤል የኢየሩሳሌም መፍረስ የሚፈጸምበትን ሰባውን ዓመት፣ ይሖዋ በቃሉ ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረውን የዓመቱን ቁጥር በመጽሐፍ አስተዋልሁ” በማለት በከፍተኛ ጉጉት የጻፈው በዚህ ምክንያት ነበር። (ዳንኤል 9:2፤ ኤርምያስ 25:11, 12) ምርኮኞቹ አይሁዶች በሁለት ዓመታት ውስጥ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው የይሖዋን አምልኮ እንደገና ለመጀመር በምን ተአምር ይችሉ ነበር?
3. ስለዚህ ዳንኤል ምን የጋለ ጸሎት አቀረበ?
3 ዳንኤል የሕዝቡን ኃጢአት በይሖዋ ፊት በግልጽ በመናገርና ይሖዋ ምሕረት እንዲያደርግላቸው በመጠየቅ ስለ ሕዝቡ የጋለ ልመና አቀረበ። ከሁሉም በላይ ደግሞ የእስራኤል አጎራባች አገሮች በታላቁ ስሙ ላይ የቆለሉትን ነቀፋ እንዲያስወግድ ጠየቀ። አምላኩን እንዲህ በማለት ተማጸነ:- “አቤቱ [ይሖዋ አዓት] ስማ አቤቱ ይቅር በል አቤቱ አድምጥና አድርግ፤ አምላኬ ሆይ፣ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቷልና ለራስህ ስትል አትዘግይ።” — ዳንኤል 9:4–19
4. ይሖዋስ ያንን ጸሎት የሰማው እንዴት ነው?
4 ይሖዋ ለዚህ ጸሎት መልስ ሰጥቷልን? በእርግጥ ሰጥቷል! ይህንን በማድረግ ትንቢቱንም ፈጽሞታል። በዳርዮስ እግር የተተካውን የፋርሱን ቂሮስ እስራኤላውያን ቀሪዎች ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄዱና የይሖዋን ቤተ መቅደስ እንደገና እንዲሠሩ ትእዛዝ እንዲያወጣ አድርጎታል። “ሰባዎቹ ዓመታት” በ537 ከዘአበ እንደተፈጸሙ እነዚያ ከምርኮ የተመለሱ አይሁዶች በኢየሩሳሌም ውስጥ እንደገና በተሠራው መሠዊያ ላይ ለይሖዋ መሥዋዕቶችን ማቅረብ ጀመሩ። — 2 ዜና. 36:17–23፤ ዕዝራ 3:1፤ ኢሳይያስ 44:28፤ 45:1
መሲሑ መጀመሪያ የሚመጣበትን ጊዜ መወሰን
5. (ሀ) ቀጥሎ ምን ነገር ተከተለ? (ለ) በዳንኤል 9:24–27 ላይ ጎላ የተደረገው የትኛው ጊዜ ነው?
5 ዳንኤል ያቀረበው ጸሎት የሚያስከትለው ፈጣን ውጤትም ነበረው። መልአኩ ገብርኤል እንደ ሰው ሥጋ ለብሶ በፊቱ ቆመና ያናግረው ጀመር። ዳንኤል “ለይሖዋ እጅግ የተወደደ” መሆኑን መልአኩም ገለጸና ለእርሱ ተጨማሪ ‘ጥልቅ ማስተዋል ከመረዳት ጋር’ መስጠቱን ቀጠለ። (ዳንኤል 9:20–23) መልአኩ ለዳንኤል የገለጠለት ነገር ጨርሶ አዲስና ትኩስ ነበር። ‘በሰባ ዓመታት’ ሳይሆን ‘በሰባ ሳምንታት’ ጊዜ ውስጥ የሚፈጸሙ ድርጊቶችን የሚመለከት አስደናቂ ትንቢት ነገረው። ዝርዝር ሐሳቡን በሙሉ ለማወቅ እስቲ እባክህ ዳንኤል 9:24–27ን አንብበው። የትንቢቱ ትርጉም ምንድን ነው?
6. ‘የሰባዎቹ ሳምንታት’ ርዝመት ምን ያህል ነው?
6 ትንቢቱ ከዳዊት የትውልድ መሥመር ይመጣል የተባለለት ንጉሥ ይኸውም ‘አለቃው መሲሕ’ እንዲመጣ “ሰባ ሣምንታት” የተቀጠሩ መሆናቸውን ይናገራል። ታዲያ እነዚህ ቃል በቃል የሚወሰዱ ሳምንታት ነበሩን? አልነበሩም፤ ምክንያቱም የተነገሩት ትንቢቶች ሁሉ በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ አይችሉም። እያንዳንዱ ቀን እንደ አንድ ዓመት የሚቆጠርባቸው “ሳምንታት” ናቸው። (ከዘሌዋውያን 25:8 ጋር አወዳድር) እንዲያውም በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በዳንኤል 9:24 ላይ “ሰባ የዓመታት ሣምንታት” በሚል አገላለጽ ይጠቀማሉ። (አን አሜሪካን ትራንስሌሽን፤ ሞፋት፤ ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን፤ እንዲሁም በሮዘርሃም፣ በኒው አሜሪካን ባይብል፣ በጀሩሳሌም ባይብል ላይ የሚገኙትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት።) “ሰባዎቹ ሳምንታት” ቃል በቃል 490 ዓመታት መሆናቸው ግልጽ ነው።
7, 8. (ሀ) “ሰባዎቹ ሳምንታት” የቂሮስ ትእዛዝ ከወጣበት ጊዜ መቆጠር የማይጀምሩት ለምንድን ነው? (ለ) የነህምያ ጸሎት መልስ ያገኘው እንዴት ነበር? (ሐ) አይሁዶች የንጉሡን “ቃል” ሲሰሙ ምን አሉ? (መ) ይህ የሆነው መቼ ነው?
7 “ሰባዎቹ ሳምንታት” የሚቆጠሩት ከመቼ ጀምሮ ነው? ዳንኤል 9:25:- “ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጊዜ ጀምሮ” ነው በማለት ይነግረናል። ይሁን እንጂ የቂሮስ ትእዛዝ ይህን የመሰለ ‘ትእዛዝ’ ያካተተ አልነበረም። ትእዛዙ መሠዊያውን ጨምሮ ‘የይሖዋ ቤት መልሶ ይሠራ’ የሚል ብቻ ነበር። (ዕዝራ 1:1–4) ከዚያ በኋላ ከ80 ለሚበልጡ ዓመታት ቅጥሮችዋ እንደ ወደቁ ሆነው ከተማዋ ‘እንደ ፈረሰች’ ቆይታለች። በዚያን ጊዜ ነህምያ የሚባል አንድ ታማኝ አይሁዳዊ መቀመጫው በሱሳ ግንብ የነበረው የፋርስ ንጉሥ የአርጤክስስ ጠጅ አሳላፊ ሆኖ ያገለግል ነበር። በኢየሩሳሌም ያሉት አይሁዶች በምን ዓይነት ችግር ላይ መሆናቸውን ሲሰማ ነህምያ ይህ በይሖዋ ስም ላይ የመጣ “ነቀፋ” እንዲወገድ ጸለየ። — ነህምያ 1:3, 11፤ 2:17
8 ነህምያ ለንጉሡ ወይን ጠጅ ሲያቀርብ በፊቱ ላይ የሐዘን መልክ ይታይ ነበር። አርጤክስስም እንዲህ ብሎ ጠየቀው:- “ሳትታመም ፊትህ ለምን አዘነ? ይህ የልብ ሐዘን ነው እንጂ ሌላ ነገር አይደለም።” ንጉሡ ምክንያቱን እንደተረዳ ወዲያውኑ ነህምያ የከተማይቱን “ቅጥሮች” እና “በሮች” ለመሥራት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለስ አዘዘ። ነህምያ አምላክ ያሳየውን ሞገስ ለማስታወቅና ንጉሡ “ኢየሩሳሌምን ለመጠገንና ለመሥራት ያወጣውን ትእዛዝ” ለማስተላለፍ እዚያ በደረሰ ጊዜ ሕዝቡ ምን አለ? “እንነሣና እንሥራ አሉ። እጃቸውንም ለበጎ ሥራ አበረቱ።” ይህ ሁሉ የሆነው “በንጉሡ በአርጤክስስ በሀያኛው ዓመት” ነበር። — ነህምያ 2:1–18
9. የአርጤክስስን 20ኛ የግዛት ዘመን እንዴት ለማስላት እንችላለን?
9 ይህ የትኛው ዓመት ነበር? ማስረጃው በአመዛኙ እንደሚያሳየው ይህ አርጤክስስ (ቀኝ እጁ ረጅም በመሆኑ ምክንያት “ሎንጊማነስ” ተብሎም ይጠራል) አባቱ ዘርሰስ ሲሞት በፋርስ ዙፋን ላይ ተቀመጠ። አርጤክስስ የነገሠው በ474 ከዘአበ ነበር። ስለሆነም ሀያኛው የግዛት ዓመቱ 455 ከዘአበ ይሆናል ማለት ነው።a
10. የመጀመሪያዎቹን ‘ሰባት ሳምንታት’ የሚመለከተው ትንቢት የተፈጸመው እንዴት ነበር?
10 እንግዲያው በዳንኤል 9:25 ላይ የተጠቀሱት “ሳምንታት” መቆጠር የሚጀምሩት ከ455 ከዘአበ ጀምሮ ይሆናል። እንዲህ እናነባለን:-
“ስለዚህ እወቅ አስተውልም፣ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሲሕ ድረስ ሰባት ሱባኤና (ሳምንታትና) ስድሳ ሁለት ሱባኤ (ሳምንታት) ይሆናል። እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች።”
ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው የመጀመሪያዎቹ “ሰባት ሳምንታት” ወይም 49 ዓመታት እስከ 406 ከዘአበ ያለውን ከተማይቱ በድጋሚ የተሠራችበትን ጊዜ ይሸፍናሉ። “የጭንቀት ዘመን” የሚለው ደግሞ ይህ የግንባታ ሥራ ከአጎራባች ሕዝቦች የመጣውን የከረረ ተቃውሞ ያመለክታል። (ነህምያ 4:6–20) ይሁን እንጂ ታሪክ እንደሚጠቁመው በዚያ መቶ ዘመን ማክተሚያ ላይ ኢየሩሳሌም ትልቅና የበለጸገች ከተማ ሆና ነበር።b
11. “አለቃው መሲሕ” ልክ በሰዓቱ የመጣው እንዴት ነው?
11 ይሁን እንጂ ከዚህ ሌላ ከ455 ከዘአበ ጀምሮ “እስከ አለቃው እስከ መሲሕ ድረስ” ያለውን ጊዜ በጠቅላላው 69 የዓመታት ሳምንታት ወይም የ483 ዓመታት ርዝመት እንዲኖረው የሚያደርጉ “ስድሳ ሁለት ሳምንታት” መኖር ነበረባቸው። እነዚህ 455 ከዘአበን በከፊልና የመጨረሻውን ዓመት በከፊል የሚጨምሩት 483 ዓመታት እስከ 29 እዘአ ድረስ ይደርሳሉ። ታዲያ በዚህን ጊዜ መሲሑ መጥቷልን? ሉቃስ 3:1–3 “ጢባርዮስ ቄሣርም በነገሠ በአሥራ አምስተኛይቱ ዓመት” መጥምቁ ዮሐንስ “ጥምቀትን እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለችው አገር ሁሉ” እንደመጣ ይገልጻል። የታሪክ አዋቂዎች ጢባሪዮስ የሮማ ገዥ የሆነው በ14 እዘአ ነሐሴ 17 (በጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር) ላይ መሆኑን ያረጋገጡ ስለሆነ ዮሐንስ መስበክና ማጥመቅ የጀመረው በጢባርዮስ 15ኛ ዓመት በ29 እዘአ የጸደይ ወራት ላይ ይሆናል። በዚያው ዓመት የበልግ ወራት ላይ በ29 እዘአ ኢየሱስ ተጠመቀ፤ መንፈስ ቅዱስም ከሰማይ በመውረድ መሲሕ አድርጎ ቀባው። ይህም መለኮታዊው ትንቢት የሚፈጸምበት ትክክለኛው ሰዓት ነበር! — ሉቃስ 3:21, 22
12. (ሀ) ብዙ አይሁዶች በዚያን ጊዜ ምን ይጠብቁ ነበር? (ለ) የትንቢቱን ፍሬ ነገር የሳቱት ለምንድን ነው? (ሐ) ይሁን እንጂ እኛ ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
12 በእነዚያ ጊዜያት ብዙ አይሁዶች የመሲሑን መምጣት ይጠባበቁ ነበር። ይህም የሆነበት ከፊል ምክንያት ስለ “ሰባዎቹ ሳምንታት” ማወቃቸው እንደሆነ አያጠራጥርም። (ሉቃስ 3:15፤ ዮሐንስ 1:19, 20) ነገር ግን ብዙዎቹ ደንዳና ልብ ስለነበራቸው የትንቢቱን ፍሬ ነገር ሳይረዱ ቀሩ። (ማቴዎስ 15:7–9) ይሁን እንጂ እኛ ዛሬ ‘ለትንቢቱ ቃል’ የተለያዩ ገጽታዎች ትኩረት በመስጠት በእምነት ልንጠነክር እንችላለን። (2 ጴጥሮስ 1:19–21) ይህ “ቃል” የመሲሑን ማንነት ለይቶ ለማወቅ ከመርዳቱም በላይ በገጽ 67 ላይ በሚገኘው ቻርት እንደተገለጸው ‘በአለቃው መሲሕ’ መንግሥት ሥር የሚገኙትን ድንቅ በረከቶችም ይጠቁማል። — ኢሳይያስ 9:6, 7
ንጉሥ የሚሆነው መሲሕ “ተገደለ”
13, 14. የመሲሑ አመጣጥና የተከተለው መንገድ አይሁዶች ይጠብቁት ከነበረው በጣም የተለየው እንዴት ነበር?
13 “አለቃው መሲሕ” መገለጡ አይሁዶችን ወዲያውኑ ከጭቆና አላቋቸዋልን? ከሮማ ግዛት አስከፊ ባርነት የሚያላቅቃቸው ኃያል ጦረኛና ገዥ እንደሚሆን ጠብቀውት ነበር። (ዮሐንስ 6:14, 15) ይሁን እንጂ አባቱ ይሖዋ ከዚያ በተለየ መንገድ እንዲያድናቸው ዓላማ ነበረው።
14 ስለ “ሰባዎቹ ሣምንታት” በተናገረው ትንቢት ውስጥ ገብርኤል መሲሑ ታላቅ የፖለቲካ መሪ ከመሆን ይልቅ ‘ለእርሱ አንዳች ሳይኖረው እንደሚገደል’ ገልጾ ነበር። ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ዝና ወይም ሥጋዊ ሃብት ሳይኖረው የውርደት ሞት መሞት ነበረበት። ትንቢቱ እንዴት በሚያስደንቅ መንገድ ተፈጸመ! ኢየሱስ ሊሰቀል ሲል ልብሱን ሲያስወልቁት ወታደሮቹ በዚያች በቀረችው ንብረቱ ይኸውም በመጐናጸፊያው ላይ ዕጣ ጥለው ተከፋፈሉ። — ዳንኤል 9:26፤ ማቴዎስ 27:35
15. (ሀ) መሲሑ ‘የተገደለው’ መቼ ነበር? (ለ) ይህ የጊዜ ሰሌዳ ትክክለኛነቱ የተረጋገጠው እንዴት ነው?
15 ይህ ግድያ የተፈጸመው መቼ ነበር? ገብርኤል በመጨረሻው የዓመታት “ሳምንታት እኩሌታ” ይኸውም ኢየሱስ ከተጠመቀና ከተቀባ ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ በ33 እዘአ በዋለው የጸደይ ወራት እንደሚሆን ተናግሮ ነበር። ለትንቢቱ ትክክለኛነት ማስረጃ ይሆን ዘንድ የዮሐንስ ወንጌል ኢየሱስ በዚያን ጊዜ አራተኛውን የማለፍ በዓል በማክበር ላይ እንደነበር ያመለክታል። — ዳንኤል 9:27፤ ዮሐንስ 2:13፤ 5:1፤ 6:4፤ 13:1
16, 17. (ሀ) በዳንኤል 9:26 ላይ የሚገኙት ተጨማሪ ቃላት በአሳዛኝ ሁኔታ የተፈጸሙት እንዴት ነበር? (ለ) በዚያን ጊዜ የነበሩት የመሲሑ እውነተኛ ተከታዮች ለእኛ ምሳሌ የሚሆኑት እንዴት ነው?
16 አዎን፣ “አለቃው መሲሕ” ተገደለ። አይሁዶች ንጉሣቸውን አለማወቃቸው ምንኛ የሚያሳዝን ነው! ሆኖም ከዚህ የበለጠም ነገር መምጣት ነበረበት። ኢየሩሳሌም እንደገና መደምሰስ ነበረባት። የዳንኤል ትንቢት አስቀድሞ የሚከተለውን ተናግሮ ነበር፤
“የሚመጣውም አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ፤ ፍጻሜውም በጎርፍ ይሆናል፣ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተቀጥሮአል።” — ዳንኤል 9:26
17 ልክ በትንቢቱ ላይ እንደተገለጸው ከመሲሑ ‘መገደል’ በኋላ ያለው ጊዜ “እስከ መጨረሻ ድረስ” በጦርነት የተሞላ ጊዜ ነበር። በመጨረሻም በ70 እዘአ የሮማ ሠራዊት የተከበበችውን የኢየሩሳሌም ከተማ እንደ ጐርፍ አጥለቀለቀ። ከተማዋና ቤተ መቅደስዋ ፈረሱ፣ ‘ተደመሰሱ።’ ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ በዘገበው መሠረት በዚያ ታላቅ እልቂት 1, 100, 000 አይሁዶች ተደመሰሱ። የሚያስደስተው ግን በዚያን ጊዜ የነበሩት የመሲሑ እውነተኛ ተከታዮች የማስጠንቀቂያውን “ምልክት” ካዩ በኋላ ከጥፋቱ ለመዳን ከዮርዳኖስ ማዶ ወደሚገኙ ተራሮች ሸሽተው ነበር። (ማቴዎስ 24:3–16) ይህ ነገር መንግሥቲቱ በአሁኑ ክፉ የዓለም ሥርዓት ላይ ፍርድ ለመፈጸም ‘ከመምጣትዋ’ በፊት ለአምላክ ትንቢታዊ “ምልክት” ትኩረት መስጠታችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እኛንም አጥብቆ የሚያሳስበን ነው። — ሉቃስ 21:34–36
መሲሑ ብዙ ጥቅሞችን ያመጣልናል
18. በመሲሑ የመጀመሪያ መምጣት ምን ጠቃሚ ነገር ተከናውኗል?
18 ታዲያ መሲሑ በመጀመሪያ በሚመጣበት ጊዜ የሚያከናውነው ምንድን ነው? ገብርኤል ለዳንኤል እንዲህ በማለት ነግሮት ነበር:-
“ዓመፃን (መተላለፍን) ይጨርስ፣ ኃጢአትንም ይፈጽም፣ በደልንም ያስተሰርይ፣ የዘላለምን ጽድቅ ያገባ፣ . . . ዘንድ በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባኤ (ሳምንት) ተቀጥሮአል።” (ዳንኤል 9:24)
“አለቃው መሲሕ” ከመሞቱ በፊትና በሞቱ ወቅት ይህንን ሁሉ ያከናውናል። ይህም ፖለቲካዊ ነፃነት ሳይሆን ግሩም የሆነ መንፈሳዊ ነፃነት ይሆናል። መሥዋዕት የሆነው ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱ ባለው ከኃጢአት የማዳን ኃይል ኢየሱስ መሲሕነቱን ከሚቀበሉት ላይ ኃጢአትንና መተላለፍን ጨርሶ በማስወገድ መንፈሳዊ “የአምላክ እስራኤል” ሆነው ወደ “አዲስ ቃል ኪዳን” እንዲገቡ ያደርጋቸዋል። — ገላትያ 6:16፤ ኤርምያስ 31:31, 33, 34
19. መሲሑ ‘መሥዋዕቱንና ቁርባኑን ያስቀረው’ እንዴት ነው?
19 ስለዚህ ሙሴ መካከለኛ የሆነለት የሕጉ ቃል ኪዳን በእንስሳት መሥዋዕቶቹ አማካኝነት መፈጸም ያልቻለውን በመሲሑ መካከለኛነት የተቋቋመው አዲሱ ቃል ኪዳን “በሳምንቱ እኩሌታ” ላይ በቀረበው ፍጹም ሰብዓዊ መሥዋዕት አማካኝነት መፈጸም ቻለ። በዚህ መንገድ የእንስሳት “መሥዋዕቱንና ቁርባኑን (የስጦታ መሥዋዕቱን) ያስቀራል” ምክንያቱም የሕጉ መሥዋዕቶች ከዚያ በኋላ ዋጋ አይኖራቸውም። (ዳንኤል 9:27) ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት እንደገለጸው ነው:- “አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፣ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። ነገር ግን የሆነው ሁሉ፣ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው።” — 2 ቆሮንቶስ 5:17, 18
20. ለሰው ልጆች በተሰጠው በየትኛው ተስፋ ልትደሰት ትችላለህ?
20 ጊዜው ሲደርስ የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጥቅሞች ጳውሎስ አባል ከሆነበት መንፈሳዊ እስራኤል ውጭ አልፈው ለሌሎችም ይደርሳሉ፤ ምክንያቱም ቀጥሎ “ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፣ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 5:19) አንተም የሰው ልጆች ዓለም ክፍል እንደመሆንህ በሰብዓዊ አለፍጽምና ምክንያት የፈጸምካቸው በደሎች አንተን ከአምላክ ጋር በሚያስታርቀው በዚህ መሥዋዕት መሠረት ይቅር ሊባልልህ መቻሉ አያስደስትህምን?
21, 22. (ሀ) 70ኛው ሳምንት ‘በራእይና በነቢይ ላይ ማህተም ያተመው’ እንዴት ነው? (ዳንኤል 9:24) (ለ) “ቅዱሰ ቅዱሳኑ” የተቀባው እንዴት ነው?
21 ይሁን እንጂ “ሰባኛው ሳምንት” “ጽድቅን ለዘላለም የሚያገባ” ብቻ አይደለም። ‘በራእይና በነቢይም ላይ ማህተም ያትማል።’ ራእይ 19:10 እንደሚገልጸው:- “ትንቢት የሚነገረው ስለ ኢየሱስ ለመመሥከር ሲባል ነው።” [አዓት] ኢየሱስ በመጀመሪያ መሲሕ ሆኖ በመጣ ጊዜ ባደረገውና በተናገረው ነገር በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ትንቢቶችን ቃል በቃል ፈጽሟል። ይህም እውነተኛና ትክክል እንደሆኑ ምንጫቸውም ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ መሆኑን ለማሳየት በእነዚያ ትንቢቶች ላይ የማይጠፋ ማህተም እንደ ማድረግ ያህል ነው። አሁን በመሲሑ አማካኝነት አምላክ ለሕዝቡ አመጣለሁ ብሎ ቃል የገባበት በረከት ሁሉ ይፈጸማል። “አምላክ የሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ ምንም ያህል ብዛት ቢኖረው በእርሱ (በመሲሑ በኢየሱስ) አዎን ሆኗል።” — ዳንኤል 9:24፤ 2 ቆሮንቶስ 1:20 አዓት
22 ሌላው በዚያ ‘ሰባኛ ሳምንት’ ውስጥ መፈጸም የነበረበት “ቅድስተ ቅዱሳኑን” የመቀባቱ ጉዳይ ነበር። በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረው ‘በእጅ የተሠራው ቅዱስ ቦታ’ የኃጢአት ይቅርታ በማስገኘት በኩል ከዚያ በኋላ የአምላክ ዓላማ ማስፈጸሚያ መሆኑ አከተመ። ይህ ቅዱስ ቦታ መሲሑ በ29 እዘአ ሲጠመቅ ሕልውና ላገኘው ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምሳሌ ብቻ ነበረ። ክርስቶስ ከሞተና ከተነሣ በኋላ አምላክ በአካል በሚገኝበት የሰብአዊ መሥዋዕቱን ዋጋ በፊቱ ‘ለአንዴና ለሁልጊዜ’ ለማቅረብ ወደዚያ ቅዱስ ስፍራ ማለትም ወደ ሰማይ ገባ። (ዕብራውያን 9:23–26) በዚህም መንገድ የአምላክ ሰማያዊ መኖሪያ አዲስ መልክ ያዘ። በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ ያለው ቅዱሰ ቅዱሳን ምሳሌ የሆነለት እውነተኛ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ በመሆን “ቅዱሰ ቅዱሳን” ሆኖ ተቀባ። ስለዚህ በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠ ቆስጤ ቀን ጀምሮ እስከ ‘ሰባኛው ሳምንት’ መጨረሻ ድረስ የአምላክን ዝግጅት የተቀበሉት እነዚያ አይሁዶች ሌላ ሰው ያላገኘውን አንድ ልዩ መብት አግኝተዋል። በዚያ “ቅዱሰ ቅዱሳን” ውስጥ በቀረበው የክርስቶስ መሥዋዕት መሠረት እነርሱም በአምላክ መንፈሳዊ መቅደስ ውስጥ የበታች ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ ተቀቡ።
23. (ሀ) አይሁዶች በተለይ በ70ኛው ሳምንት ሞገስ አግኝተው የነበሩት እንዴት ነው? (ለ) ‘ከሰባዎቹ ሳምንታት’ በኋላ ሌሎች ሞገስ ያገኙት እንዴት ነበር?
23 መንፈሳዊ እስራኤል የሚሆኑትን እነዚህን አይሁዶች አስመልክቶ ትንቢቱ እንዲህ ይላል:- “እርሱም ለብዙዎቹ ሰዎች ሲል ቃል ኪዳኑን ለአንድ ሳምንት እንዲቆይ ያደርጋል።” ይህ ጊዜ ሥጋዊ አይሁዶች የመንፈሳዊ ‘የአብርሃም ዘር’ ክፍል በመሆን በተለይ ልዩ ሞገስ ያገኙበት ከ29–36 እዘአ ያለው ‘የዓመታት ሳምንት’ ነው። (ዳንኤል 9:27) ከዚያ በኋላ ግን ጴጥሮስ ላልተገረዘውና አይሁዳዊ ላልሆነው ለቆርኔሌዎስ በመስበኩ አሕዛብ የሆኑ ያልተገረዙ ሰዎችም ወደ አብርሃሙ ቃል ኪዳን እንዲገቡ መንገድ ተከፈተላቸው። ይህን በተመለከተ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የአምላክ ልጆች ናችሁ። ወደ ክርስቶስ የተጠመቃችሁ ሁላችሁ ክርስቶስን ለብሳችኋልና። አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፣ ባሪያ ወይም ነፃ ሰው የለም፣ ወንድም ሴትም የለም ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና። ከዚህም ሌላ የክርስቶስ ከሆናችሁ በእርግጥ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።” — ገላትያ 3:26–29 አዓት፤ ሥራ 10:30–35, 44–48
24. (ሀ) ለአብርሃም የተሰጠው የተስፋ ቃል ለሌሎችም ሰዎች ምን አስደናቂ ዋስትና ይዟል? (ለ) በሉቃስ 9:23 ላይ እንደተመለከተው አንተም ተካፋይ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
24 ይሁን እንጂ ሰማያዊ ውርሻ የሚያገኘው ‘የታናሹ መንጋ’ ክፍል ለመሆን ያልተሰበሰቡት በቢልዮን የሚቆጠሩት የቀሩት የሰው ልጆችስ? “የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ [በአብርሃም ዘር] [ራሳቸውን ይባርካሉ (አዓት)]” በሚለው ተስፋ ውስጥ አምላክ እንደገለጸው ለአብርሃም የተሰጠው ተስፋ ለእነዚህም ቢሆን አስደናቂ ዋስትና ይዟል። (ዘፍጥረት 22:18) የዚህ በረከት ተካፋይ መሆኑ ያንተ ፍላጎት ነውን? ተካፋይ መሆን ትችላለህ፤ ይህም እንዲሆን ‘የአምላክ መንግሥት እንድትመጣ’ መጸለይ አለብህ። በተጨማሪም የአምላክን ቃል መመርመርህን ስትቀጥል ራስህን ለአምላክ በመወሰን ራስህን እንዴት ‘እንደምትክድ’ እና አለቃ የሆነውን መሲሕ እንዴት ‘ያለማቋረጥ’ መከተል እንደምትችል ትማራለህ። — ሉቃስ 9:23
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ጥቅምት 15, 1965 የወጣውን የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 629–631 ተመልከት፤ ኤይድ ቱ ባይብል አንደርስታንዲንግ ገጽ 1473 ተመልከት።
b ለምሳሌ በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖር የነበረው ታሪክ ጸሐፊ የአብደራው ሄክታኢየስ አጌንስት ኤፒየን በተባለው መጽሐፍ 1:22 ላይ እንዲህ ብሎ መጻፉን ጆሴፈስ ጠቅሶ ነበር:- “አይሁዳውያን በተለያዩት የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ብዙ አምባዎችና መንደሮች ሲኖሯቸው፣ ዙሪያዋ ወደ 33, 000 ጫማ የሆነችና መቶ ሃያ ሺህ ያህል ነዋሪዎች የሚኖሩባት አንዲት የተመሸገች ከተማ ብቻ አላቸው፤ እርስዋንም ኢየሩሳሌም ብለው ይጠሯታል።”
[በገጽ 67 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
“ሰባዎቹ ሳምንታት” ሲገባደዱ ‘አለቃውን መሲሕ’ በተመለከተ የተፈጸሙ ትንቢቶች
ትንቢት ፍሬ ሐሳቡ ፍጻሜው
ኢሳይያስ 40:3 አጥማቂው ዮሐንስ መንገድ አዘጋጀ ማቴዎስ 3:1–3
ሚክያስ 5:2 ኢየሱስ በቤተልሔም ተወለደ ማቴዎስ 2:1–6
ዘፍጥረት 49:10 ከይሁዳ ነገድ ሉቃስ 3:23–33
ኢሳይያስ 7:14 ከድንግል ማቴዎስ 1:23–25
ኢሳይያስ 9:7 የዳዊት ዘር፣ ወራሽ ማቴዎስ 1:1, 6–17
ኤርምያስ 31:15 ከተወለደ በኋላ ሕፃናት ተገደሉ ማቴዎስ 2:16–18
ሆሴዕ 11:1 ከግብጽ ተጠራ (ስደተኛ) ማቴዎስ 2:14, 15
ዳንኤል 9:25 69ኙ “ሳምንታት” ሲፈጸሙ መጣ ሉቃስ 3:1, 21, 22
መዝሙር 40:7, 8 የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን አቀረበ ማቴዎስ 3:13–15
ኢሳይያስ 61:1, 2 እንዲሰብክ በመንፈስ ተቀባ ሉቃስ 4:16–21
መዝሙር 2:7 ይሖዋ ኢየሱስን “ልጄ” ብሎ ተናገረለት ማቴዎስ 3:17
ኢሳይያስ 9:1, 2 በገሊላ ምድር ብርሃን ሆነ ማቴዎስ 4:13–16
መዝሙር 40:9 “ምሥራቹ”ን በድፍረት ሰበከ ማቴዎስ 4:17, 23
መዝሙር 69:9 ለይሖዋ ቤት ቀናተኛ ሆኗል ዮሐንስ 2:13–17
ኢሳይያስ 53:1, 2 አይሁዶች አላመኑበትም ዮሐንስ 12:37, 38
መዝሙር 78:2 በምሳሌ ተናገረ ማቴዎስ 13:34, 35
ዘካርያስ 9:9 በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ ወደ ከተማ ገባ ማቴዎስ 21:1–9
መዝሙር 69:4 ያለ ምክንያት ተጠላ ዮሐንስ 15:24, 25
ኢሳይያስ 42:1–4 የአሕዛብ ተስፋ፣ አልተከራከረም ማቴዎስ 12:14–21
መዝሙር 41:9 ከሀዲ ሐዋርያ አሳልፎ ሰጠው ዮሐንስ 13:18, 21–30
ዘካርያስ 11:12 ለ30 ብር ማቴዎስ 26:14–16
መዝሙር 2:1, 2 ገዥዎች በተቀባው ላይ ተነሡ ማቴዎስ 27: 1, 2
መዝሙር 118:22 የተናቀ፣ ነገር ግን አስተማማኝ መሠረት ማቴዎስ 21:42, 43
ኢሳይያስ 8:14, 15 የመሰናከያ ድንጋይ መሆኑ ሉቃስ 20: 18
መዝሙር 27:12 ሐሰተኛ ምሥክሮች መሰከሩበት ማቴዎስ 26: 59–61
ኢሳይያስ 53:7 በከሳሾቹ ፊት ዝም አለ ማቴዎስ 27:11–14
መዝሙር 22:16 እግሮቹና እጆቹ ተቸንክረው ተሰቀለ ዮሐንስ 20:25
ኢሳይያስ 53:12 ከአመጸኞች ጋር ተቆጠረ ሉቃስ 22:36, 37
መዝሙር 22:7, 8 እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሳለ ይሰድቡታል ማቴዎስ 27:39–43
መዝሙር 69:21 ከርቤ የተቀላቀለበት ወይን ሰጡት ማርቆስ 15:23, 36
ዘካርያስ 12:10 ተሰቅሎ ሳለ ወጉት ዮሐንስ 19:34
መዝሙር 22:18 በልብሱ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ ማቴዎስ 27:35
መዝሙር 34:20 ከአጥንቶቹ አንዱም አልተሰበረም ዮሐንስ 19:33, 36
መዝሙር 22:1 አምላክ በጠላቶቹ እጅ መተዉ ማቴዎስ 27:46
ዳንኤል 9:26, 27 ከ3 1/2 ዓመት በኋላ ተገደለc ዮሐንስ 19:14–16
ዘካርያስ 13:7 እረኛው ሲመታ፣ መንጋው ተበተነ ማቴዎስ 26:31, 56
ኤርምያስ 31:31 አዲስ ኪዳን፣ ኃጢአት መወገዱ ሉቃስ 22:20
ኢሳይያስ 53:11 የብዙዎችን ኃጢአት መሸከሙ ማቴዎስ 20:28
ኢሳይያስ 53:4 የሰውን ልጅ ሕመም መሸከሙ ማቴዎስ 8:16, 17
ኢሳይያስ 53:9 መቃብሩ ከሀብታሞች ጋር መሆኑ ማቴዎስ 27:57–60
መዝሙር 16:10 መበስበስን ሳያይ መነሣቱ ሥራ 2:24, 27
ዮናስ 1:17 በሦስተኛው ቀን ተነሣ ማቴዎስ 12:40
መዝሙር 110:1 ወደ አምላክ ቀኝ ከፍ ከፍ መደረጉ ሥራ 7:56
[የግርጌ ማስታወሻ]
c እዚህ መጽሐፍ ላይ ገጽ 61, 62 ተመልከት።