ምዕራፍ 14
ወደ ሰማይ እነማን ይሄዳሉ? ለምንስ?
1. ‘ወደ ሰማይ የሚሄዱት እነማን ናቸው፣ ለምንስ’ ለሚለው ጥያቄ የብዙ ሰዎች መልስ ምንድን ነው?
ብዙ ሰዎች ‘ጥሩ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ’ ብለው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ለምን ወደ ሰማይ ይሄዳሉ? ተብለው ሲጠየቁ ‘ከአምላክ ጋር ለመሆን ነው’ ወይም ‘የጥሩ ሰዎች ሽልማት እርሱ ስለሆነ ነው’ ይሉ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ነገር ምን ያስተምራል?
2, 3. (ሀ) አንዳንድ ሰዎች ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ እርግጠኞች ለመሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) የትኛው ጥያቄ መልስ ማግኘት ያስፈልገዋል?
2 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ከሞት እንደ ተነሣና ወደ ሰማይ እንደሄደ ግልጽ ያደርግልናል። በተጨማሪም ሌሎች ሰዎች ወደዚያው እንደሚወሰዱ ይነግረናል። ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ እንዲህ አላቸው:- “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።”— ዮሐንስ 14:1-3
3 ኢየሱስ ሐዋርያቱ ከእርሱ ጋር ለመሆን ወደ ሰማይ እንደሚወሰዱ መናገሩ እንደሆነ ግልጽ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለጥንት ክርስቲያኖች ስለዚህ አስደናቂ ተስፋ ብዙ ጊዜ ይነግራቸው ነበር። ለምሳሌም ያህል እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን።” (ፊልጵስዩስ 3:20, 21፤ ሮሜ 6:5፤ 2 ቆሮንቶስ 5:1, 2) እንደነዚህ ያሉትን ተስፋዎች መሠረት በማድረግ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሳባቸውን በሰማያዊ ሕይወት ላይ አድርገዋል። ይሁን እንጂ ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉን?
ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉን?
4, 5. ዳዊትና ኢዮብ ወደ ሰማይ እንዳልሄዱ ምን ማስረጃ አለ?
4 ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሐዋርያው ጴጥሮስ ተሰብስበው ለነበሩት አይሁዳውያን:- “ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና” ብሎ ነገራቸው። (ሥራ 2:29, 34) ስለዚህ ጥሩ ሰው የነበረው ዳዊት ወደ ሰማይ አልወጣም። ጻድቁ ኢዮብስ ወደዚያ ሄዷልን?
5 በሥቃይ ላይ በነበረበት ጊዜ ኢዮብ ወደ አምላክ እንዲህ ሲል ጸለየ:- “በሲኦል [በመቃብር] ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ! ቁጣህ እስኪያልፍ ድረስ በሸሸግኸኝ ኖሮ! ቀጠሮም አድርገህ ምነው ባሰብኸኝ ኖሮ!” ኢዮብ ሲሞት በመቃብር ውስጥ ምንም የማይሰማ በድን እንደሚሆን ይጠብቅ ነበር። ወደ ሰማይ እንደማይሄድም ያውቅ ነበር። ይሁን እንጂ ቀጥሎ እንደተናገረው ተስፋ የሚያደርገው ነገር ነበረው “በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን? መለወጤ እስኪመጣ ድረስ የሰልፌን ዘመን ሁሉ (በመቃብር ውስጥ የሚያሳልፈውን የተወሰነ ዘመን) በትዕግሥት በተጠባበቅሁ ነበር። በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር”።— ኢዮብ 14:13-15
6, 7. (ሀ) ከክርስቶስ በፊት ከሞቱት መካከል ወደ ሰማይ የሄደ ማንም ሰው እንዳልነበረ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ከክርስቶስ በፊት የሞቱት ታማኞች ሁሉ ምን ይሆናሉ?
6 ኢየሱስን ያጠመቀው ዮሐንስም ጥሩ ሰው ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ:- “በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል” ብሏል። (ማቴዎስ 11:11) ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት መጥምቁ ዮሐንስ ወደ ሰማይ ስለማይሄድ ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ይኸውም አዳምና ሔዋን ካመፁ ከ4, 000 ዓመታት በኋላ እንዲህ አለ:- “ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።”— ዮሐንስ 3:13
7 ስለዚህም በኢየሱስ አነጋገር መሠረት እርሱ ወደ ምድር እስከመጣበት ጊዜ በነበሩት የ4, 000 ዓመታት የሰው ታሪክ ዘመናት ውስጥ ወደ ሰማይ የሄደ ማንም ሰው አልነበረም። ዳዊት ኢዮብና መጥምቁ ዮሐንስ በምድር ላይ ለመኖር ትንሣኤ ያገኛሉ። እንዲያውም ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት የሞቱት ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ሁሉ ተስፋ ያደረጉት በሰማይ ሳይሆን በምድር ላይ እንደገና ሕያው ለመሆን ነበር። እነርሱ የአምላክ መንግሥት ምድራዊ ተገዥዎች ለመሆን ትንሣኤ ያገኛሉ።— መዝሙር 72:7, 8፤ ሥራ 17:31
አንዳንድ ታማኝ ሰዎች ወደ ሰማይ የሚሄዱበት ምክንያት
8. ለየትኞቹ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልሶች በጣም አስፈላጊ ናቸው? ለምንስ?
8 ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሄደው ለምንድን ነው? እዚያ ምን የሚያከናውነው ሥራ አለው? ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልሶች በጣም አስፈላጊ ናቸው ምክንያቱም ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ በሚሠራው ሥራ የሚካፈሉ በመሆናቸው ነው። ወደ ሰማይ የሚሄዱት ለዚሁ ዓላማ ነው።
9, 10. በዳንኤል ትንቢት መሠረት ከክርስቶስ ሌላ በአምላክ መንግሥት ውስጥ ገዥ የሚሆኑት እነማን ናቸው?
9 ባለፉት ምዕራፎች ውስጥ ኢየሱስ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ በመሆን በገነቲቱ አዲስ ምድር ላይ እንደሚገዛ ተምረን ነበር። ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከብዙ ጊዜ በፊት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ “የሰው ልጅ” “ግዛት” እንደሚሰጠው ተተንብዮአል። “የሰው ልጅ” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ማርቆስ 14:41, 62) ዳንኤል ትንቢቱን በመቀጠል እንዲህ አለ:- “ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።”— ዳንኤል 7:13, 14
10 ይሁን እንጂ በዚህ የዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ “የሰው ልጅ” የሚገዛው ብቻውን እንዳልሆነ መጠቀሱን ማወቁ አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “መንግሥትም ግዛትም . . . ለልዑሉ ቅዱሳን ሕዝብ ይሰጣል፤ [መንግሥታቸውም (አዓት)] የዘላለም መንግሥት ነው።” (ዳንኤል 7:27) እነዚህ “ሕዝብ” እና “መንግሥታቸው” የሚሉት ቃላት በአምላክ መንግሥት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር ሌሎችም እንደሚገዙ ለማወቅ ይረዱናል።
11. የክርስቶስ የመጀመሪያ ተከታዮች አብረውት እንደሚገዙ የሚያሳየው ምንድን ነው?
11 ኢየሱስ ከአሥራ አንዱ ታማኝ ሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ እነርሱም ጭምር በአምላክ መንግሥት ውስጥ ከእርሱ ጋር ገዥዎች እንደሚሆኑ ገልጿል። እንዲህ አላቸው:- “ነገር ግን እናንተ በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር የተጣበቃችሁ ናችሁ። አባቴ ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን እንዳደረገ እኔም ከእናንተ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን አደርጋለሁ።” (ሉቃስ 22:28, 29 አዓት) ከዚያም ቆየት ብሎ ሐዋርያው ጳውሎስና ጢሞቴዎስ በዚህ ለመንግሥት በተደረገ ቃል ኪዳን ወይም ስምምነት ውስጥ ተጨምረዋል። በዚህ ምክንያት ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ:- “ብንጸና፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን” በማለት ጽፎለታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:12) በተጨማሪም ሐዋርያው ዮሐንስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ‘በምድር ላይ ነገሥታት ሆነው ስለሚገዙት’ ጽፎአል።— ራእይ 5:9, 10፤ 20:6
12. ክርስቶስ ተባባሪ ገዥዎች እንደሚኖሩት የአብርሃምን “ዘር” የሚመለከት የትኛው ሁኔታ ያሳያል?
12 ስለዚህ ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ወደዚያ የሚሄዱት በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ገዥዎች ሆነው ለማገልገል ነው። ኢየሱስ ዋነኛው የተስፋው “ዘር” ሲሆን አምላክ በመንግሥቱ ከኢየሱስ ጋር እንዲገዙ ከሰው ዘሮች መካከል ሌሎችንም መርጧል። በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ:- “እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ” በማለት እንደሚገልጸው እነርሱም ‘የዘሩ’ ክፍል ይሆናሉ።— ገላትያ 3:16, 29፤ ያዕቆብ 2:5
ወደ ሰማይ የሚሄዱት ስንት ናቸው?
13. (ሀ) ሕፃናት ወደ ሰማይ የማይሄዱት ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ መንግሥትን የሚቀበሉትን ሰዎች ቁጥር የገለጸው እንዴት ነው?
13 እነዚህ ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሰዎች ወደፊት በምድር ላይ የሚገዙ በመሆናቸው ታይተውና ተፈትነው ያለፉ የክርስቶስ ተከታዮች ይሆናሉ። ስለዚህም በክርስቲያናዊ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ያልተፈተኑ ሕፃናት ወይም ትንንሽ ልጆች ወደ ሰማይ አይወሰዱም ማለት ነው። (ማቴዎስ 16:24) ይሁን እንጂ እንደነዚህ ያሉት ትንንሽ ልጆች ቢሞቱ እንደገና በምድር ላይ በሕይወት ለመኖር የመነሣት ተስፋ አላቸው። (ዮሐንስ 5:28, 29) በዚህም ምክንያት በመንግሥቱ አገዛዝ ስር በምድር ላይ ሕይወት ከሚያገኙት ሰዎች ቁጥር ጋር ሲወዳደር ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር ትንሽ ይሆናል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ “አንተ ታናሽ መንጋ ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ” ብሎ ነግሯቸው ነበር።— ሉቃስ 12:32
14. ወደ ሰማይ የሚሄደው “ታናሽ መንጋ” ቁጥር ስንት ነው?
14 የእነዚህ የመንግሥት ገዥዎች ቡድን በቁጥር ምን ያህል ትንሽ ይሆናል? ሐዋርያትንና ሌሎችን የኢየሱስ የጥንት ተከታዮች ብቻ የሚጨምር ነውን? አይደለም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ታናሹ መንጋ’ ሌሎችንም እንደሚጨምር ያሳያል። በራእይ 14:1, 3 ላይ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “አየሁም፥ እነሆም፥ በጉ [ኢየሱስ ክርስቶስ] [በሰማያዊው] በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፥ ከእርሱም ጋር . . . መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ፤ እነርሱም ‘ከምድር የተዋጁ (የተወሰዱ) ናቸው።” እዚህ ላይ በሰማያዊው የጽዮን ተራራ ከበጉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የታዩት 144, 000 ሰዎች ብቻ እንደ ሆኑ ልብ በል። (ዕብራውያን 12:22) ስለዚህ ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ አይሄዱም፤ ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ የተፈተኑና ታማኝ የሆኑ 144, 000 ሰዎች ብቻ ከክርስቶስ ጋር ለመግዛት ወደ ሰማይ እንደሚወሰዱ ያሳያል።
ከምድር የተመረጡት ለምንድን ነው?
15. አምላክ የመንግሥቱን ገዥዎች ከሰው ዘር መካከል የመረጠው ለምንድን ነው?
15 ይሁን እንጂ አምላክ እነዚህን ገዥዎች ከሰው ዘር ውስጥ የመረጠው ለምንድን ነው? መላእክት ከክርስቶስ ጋር እንዲገዙ ለምን አላደረገም? ምክንያቱም ይሖዋ ለመግዛት ያለው መብት ግድድር የደረሰበት በዚሁ ምድር ላይ ነው። ሰዎች የዲያብሎስ ተቃውሞ እየደረሰባቸው ለአምላክ ያላቸው ታማኝነት ሊፈተን የሚችለው እዚህ ምድር ላይ ነው። ኢየሱስም ተፈትኖ ለአምላክ ያለውን ታማኝነት ያረጋገጠውና ለሰው ዘሮች ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ የሰጠው እዚህ ምድር ላይ ነው። በመሆኑም ይሖዋ በሰማያዊው መንግሥት ከልጁ ጋር እንዲተባበሩ “ታናሽ መንጋ” የሆኑትን ሰዎች ለመውሰድ ዝግጅት ያደረገው ከምድር ነው። ለአምላክ ባሳዩት ታማኝነት ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት የስስት ጥቅም ለማግኘት ነው ብሎ ዲያብሎስ ያስነሣው ክስ ሐሰት መሆኑን ያስመሰከሩት እነዚህ ናቸው። እንግዲያው ይሖዋ ለክብሩ እነዚህን ሰዎች ቢጠቀምባቸው ትክክል ነው።— ኤፌሶን 1:9-12
16. የመንግሥቱ ገዥዎች ምድራዊ ሕይወት ያዩ በመሆናቸው አመስጋኝ ለመሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
16 በተጨማሪም በምድር ላይ ለአምላክ ታማኝ መሆናቸው የተረጋገጠ ገዥዎችን ማግኘታችን እንዴት ግሩም እንደሚሆን አስብ። ከእነርሱ ውስጥ ብዙዎቹ ስለ መንግሥቱ ሲሉ ሕይወታቸውን እንኳ ሳይቀር መሥዋዕት አድርገዋል። (ራእይ 12:10, 11፤ 20:4) መላእክት እንደነዚህ ያሉ ፈተናዎች አልደረሱባቸውም። በሰው ዘር ላይ ያሉትንም ችግሮች አልቀመሱም። ስለዚህ ኃጢአተኛ ሰው መሆን ምን ማለት እንደሆነ ወይም በእኛ በሰዎች ላይ ያሉት ችግሮች ምን እንደሆኑ ሙሉ በሙሉ ሊያውቁት አይችሉም። 144, 000ዎቹ ግን እነርሱ ራሳቸው እነዚህ ችግሮች ስለደረሱባቸው ይህንን ይገነዘባሉ። ከመሐከላቸው አንዳንዶቹ መጥፎ የሆኑ የኃጢአት ድርጊቶችን ማሸነፍ ስለነበረባቸው ይህንን ማድረጉ ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል ያውቃሉ። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) ስለዚህም ምድራዊ ተገዥዎቻቸውን ሲያስተዳድሩ ችግራቸውን ይረዱላቸዋል።— ዕብራውያን 2:17, 18
የአምላክ ጉባኤ
17. “ጉባኤ” የሚለው ቃል ምንን ያመለክታል?
17 መጽሐፍ ቅዱስ የጉባኤው ራስ ክርስቶስ እንደሆነና አባሎቹ ለኢየሱስ እንደሚገዙ ይነግረናል። (ኤፌሶን 5:23, 24) ስለዚህም “ቤተ ክርስቲያን” ወይም “የአምላክ ጉባኤ” የሚለው ቃል አንድን ሕንፃ አያመለክትም። ከዚያ ይልቅ የሚያመለክተው አንድን የክርስቲያኖች ቡድን ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:9) በዛሬው ጊዜ አብረናቸው የምንሰበሰበውን ሰዎች የክርስቲያኖች ጉባኤ ብለን እንጠራ ይሆናል። በተመሳሳይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የሎዶቅያ ሰዎች ጉባኤ” የሚል አጠራር እናገኛለን። ሐዋርያው ጳውሎስም ለፊልሞና በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‘በቤቱ ስለነበረችው ቤተ ክርስቲያን [ጉባኤ]’ ጠቅሷል።— ቆላስይስ 4:16፤ ፊልሞና 2
18. (ሀ) “የሕያው አምላክ ጉባኤ” አባላት እነማን ናቸው? (ለ) ይህ ጉባኤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምን ተጨማሪ መጠሪያዎች ተጠቅሷል?
18 ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “የሕያው [አምላክ] ቤተ ክርስቲያን [ጉባኤ] ብሎ ሲናገር እየጠቀሰ ያለው አንድን የተለየ የክርስቶስ ተከታዮች ቡድን ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:15) በተጨማሪም እነርሱ ‘በሰማያት የተጻፉ የበኩራት ጉባኤ’ ተብለው ተጠርተዋል። (ዕብራውያን 12:23) ስለዚህ ይህ “የአምላክ ጉባኤ” በምድር ላይ የሚገኙትን የሰማያዊ ሕይወት ተስፋ ያላቸውን ክርስቲያኖች ያቀፈ ነው። በመጨረሻው ላይ “የአምላክ ጉባኤ” የሚሆኑት 144, 000 ሰዎች ብቻ ናቸው። በዛሬው ጊዜ ከእነዚህ ውስጥ ጥቂት ቀሪዎች ብቻ በምድር ላይ ይገኛሉ። በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉት ክርስቲያኖች መንፈሳዊ መመሪያ ለማግኘት ወደዚህ “የሕያው አምላክ ጉባኤ” ይመለከታሉ። ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን 144, 000 አባሎች ያሉትን ጉባኤ “የበጉ ሚስት ሙሽራይቱ”፣ “የክርስቶስ አካል”፣ “የአምላክ ቤተ መቅደስ”፣ “የአምላክ እስራኤል” እና “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” እያለ ይጠቅሰዋል።— ራእይ 21:9፤ ኤፌሶን 4:12፤ 1 ቆሮንቶስ 3:17፤ ገላትያ 6:16፤ ራእይ 21:2
በአምላክ ዓላማ ውስጥ የገባ አዲስ ነገር
19. አምላክ ለምድር የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ ለማስፈጸም ምን አዲስ ነገር አዘጋጀ?
19 አዳም ሰብዓዊው ዘር በኃጢአትና በሞት መንገድ ላይ እያሽቆለቆለ እንዲሄድ ማድረግ ከጀመረ በኋላም ቢሆን ይሖዋ አምላክ ለምድርና ለሰው ዘር ያለውን ዓላማ አልለወጠም። ቢለውጠው ኖሮ አምላክ የመጀመሪያ ዓላማውን ለመፈጸም አለመቻሉን የሚያሳይ ይሆን ነበር። ከመጀመሪያ ጀምሮ የነበረው ዓላማ ደስተኛና ጤናማ በሆኑ ሰዎች የተሞላች ምድር አቀፍ ገነት ለማስገኘት ነበር። ይህ ዓላማው አሁንም ቢሆን እንደጸና ነው። በአምላክ ዓላማ ውስጥ የገባው አዲስ ነገር ዓላማውን የሚያስፈጽም አዲስ መንግሥት ለማቋቋም ዝግጅት ማድረጉ ነው። ቀደም ብለን እንደ ተመለከትነው በዚህ መንግሥት ውስጥ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ዋነኛው ገዥ ነው። 144, 000 ሰዎችም በሰማይ ከእርሱ ጋር ለመግዛት ከሰው ዘሮች መካከል ይወሰዳሉ።— ራእይ 7:4
20. (ሀ) “አዲስ ሰማያት” እና “አዲስ ምድር” የሚሆኑት እነማን ናቸው? (ለ) የ“አዲስ ምድር” አባል ለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
20 እነዚህ በሰማይ የሚኖሩ ገዥዎች በአዲሱ የአምላክ ሥርዓት ውስጥ “አዲስ ሰማያት” ይሆናሉ። ሆኖም በምድር ላይ እንደነዚህ ያሉ ጻድቃን ገዥዎች የሚኖሩ ከሆነ እነርሱ የሚገዙአቸው ሰዎች መኖር እንዳለባቸው ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ሰዎች “አዲስ ምድር” ብሎ ይጠራቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:1-4) ኢዮብ፣ ዳዊትና አጥማቂው ዮሐንስ ፤ አዎን ፤ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የነበሩት ታማኝ ሰዎች በሙሉ ከእነዚህ መካከል ይሆናሉ። ከዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ የሚድኑትን ሰዎች ጨምሮ የ“አዲስ ምድር” ክፍል የሚሆኑ ሌሎች ብዙ ሰዎችም ይኖራሉ። አንተስ ከጥፋቱ ከሚተርፉት መካከል ትሆናለህን? የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆንስ ትፈልጋለህን? ከሆነ ልታሟላቸው የሚገቡህ ብቃቶች አሉ።
[በገጽ 121 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
እነዚህ ጥሩ ሰዎች ወደ ሰማይ ሄደዋልን?
ንጉሥ ዳዊት
ኢዮብ
አጥማቂው ዮሐንስ
[በገጽ 122 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ በአባቱ መንግሥት ውስጥ አብረውት ገዥዎች እንደሚሆኑ ነግሯቸዋል