የማስታወስ ችሎታህን ማሻሻል ትችላለህ
ይሖዋ አምላክ የሰውን አንጎል አስደናቂ የሆነ የማስታወስ ችሎታ እንዲኖረው አድርጎ ፈጥሮታል። አንጎላችን ብዙ መረጃዎችን መዝግቦ እንዲይዝ እንዲሁም በውስጡ የተከማቸውን መረጃ በተፈለገው ጊዜ መስጠት እንዲችል ሆኖ ተፈጥሯል። የአንጎላችን ንድፍ ሰዎች ለዘላለም ይኖሩ ዘንድ አምላክ ካለው ዓላማ ጋር የሚስማማ ነው።—መዝ. 139:14፤ ዮሐ. 17:3
ይሁን እንጂ አእምሮህ በየጊዜው ከሚሰበስበው መረጃ መካከል አብዛኛው ከጊዜ በኋላ እንደማይገኝ ይሰማህ ይሆናል። ለማስታወስ ስትፈልግ ፈጽሞ አይመጣልህም። ታዲያ የማስታወስ ችሎታህን ለማሻሻል ምን ማድረግ ትችላለህ?
ትኩረት መስጠት
የማስታወስ ችሎታህን በማሻሻል ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወተው ለጉዳዩ የምትሰጠው ትኩረት ነው። በደንብ የምናስተውልና ለሰዎችም ሆነ በአካባቢያችን ለሚከናወኑት ነገሮች ትኩረት የምንሰጥ ከሆነ አእምሮአችንን እናሠራዋለን። ይህ ደግሞ በሕይወታችን ላይ ለውጥ ሊያመጡ ስለሚችሉ ነገሮች ስናነብብም ሆነ ስንሰማ ቶሎ ማስተዋል እንድንችል ይረዳናል።
ብዙዎች የሰው ስም የማስታወስ ችግር አለባቸው። ይሁንና ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ለክርስቲያን ወንድሞቻችንም ሆነ ለምንመሰክርላቸው ሰዎች ወይም በዕለታዊ እንቅስቃሴዎቻችን ለምናገኛቸው፣ በአጠቃላይ ለሁሉም ሰዎች ከፍ ያለ ግምት መስጠት እንዳለብን እናውቃለን። ልናስታውሳቸው የሚገቡንን ስሞች እንዳንረሳ ምን ሊረዳን ይችላል? ሐዋርያው ጳውሎስ ለአንድ ጉባኤ መልእክት ሲልክ በዚያ ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ 26 ወንድሞችንና እህቶችን ስም ጠቅሶ ጽፏል። ብዙዎቹን በስም ከመጥቀስም አልፎ ስለ እነርሱ አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮችን መግለጹ በደንብ ያውቃቸው እንደነበር የሚያሳይ ነው። (ሮሜ 16:3-16) ዛሬም አንዳንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች በየሳምንቱ ከጉባኤ ጉባኤ የሚዘዋወሩ ቢሆንም የብዙ ወንድሞችን ስም ያስታውሳሉ። ለዚህ የረዳቸው ምንድን ነው? ከአንድ ሰው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተው ሲነጋገሩ ደጋግመው በስሙ ይጠሩት ይሆናል። የሰውዬውን ስም ከመልኩ ጋር ለማዛመድ ይጥራሉ። ከዚህም በተጨማሪ ከተለያዩ ግለሰቦች ጋር አብረው የማገልገልና የመመገብ አጋጣሚ አላቸው። የሰዎችን ስም በቀላሉ ማስታወስ ትችላለህ? ካልሆነ መጀመሪያ ስትተዋወቅ ስሙን ለማስታወስ ሊረዳህ ከሚችል አንድ ነገር ጋር ለማያያዝና ከላይ የተጠቀሱትን አንዳንድ ሐሳቦች ለመጠቀም ሞክር።
በተጨማሪም የምታነብበውን ነገር ማስታወስህ በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ ችሎታህን እንድታሻሽል ምን ሊረዳህ ይችላል? ስለ ርዕሰ ጉዳዩ የማወቅ ጉጉትና የመረዳት ችሎታ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። በምታነብበው ነገር ለመመሰጥ ከፈለግህ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ የማወቅ ልባዊ ፍላጎት ሊያድርብህ ይገባል። እያነበብክ ሳለ ልብህ ሌላ ቦታ የሚሄድ ከሆነ ያነበብከውን ማስታወስ አትችልም። የምታነብበውን ሐሳብ ከአሁን ቀደም ከምታውቀው ጋር የማዛመድ ልማድ ካለህ አንብቦ የመረዳት ችሎታህ ይሻሻላል። ‘ይህንን እውቀት እንዴትና መቼ ልሠራበት እችላለሁ? ሌላ ሰው ልረዳበት የምችለውስ እንዴት ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። በተጨማሪም ቃላትን በተናጠል ከማንበብ ይልቅ ሐረጎችን ማንበብ የመረዳት ችሎታን ለማሻሻል ያግዛል። ይህም ሐሳቡን በቀላሉ ለማግኘትና ዋና ዋና ነጥቡን ለመለየት ስለሚያስችልህ ያነበብከውን አትረሳም።
ለመከለስ ጊዜ መድብ
በመማር ማስተማሩ የሙያ መስክ የተሠማሩ ሰዎች መከለስ ያለውን ጠቀሜታ አበክረው ይናገራሉ። አንድ የኮሌጅ ፕሮፌሰር በጥናት እንዳረጋገጡት አንድ ደቂቃ ወስዶ ያነበቡትን ወዲያው መከለስ የምናስታውሳቸውን ነጥቦች መጠን በእጥፍ ያሳድጋል። ስለዚህ ዋና ዋና ነጥቦቹን ማስታወስ እንድትችል ንባብህን እንደጨረስክ ወይም የተወሰነውን ክፍል እንዳነበብህ እነዚህን ነጥቦች በአእምሮህ ከልስ። ከንባብህ ያገኘሃቸውን አዳዲስ ነጥቦች በራስህ አባባል ለሌሎች ሰዎች እንዴት እንደምታስረዳ አስብ። ከንባብህ በኋላ ወዲያው በአእምሮህ ያለውን እውቀት መፈተሽህ ነጥቡን ይበልጥ ለረጅም ጊዜ እንድታስታውስ ይረዳሃል።
ከዚያም በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ያነበብከውን ለሌሎች ሰዎች በመንገር መከለስ የምትችልበትን አጋጣሚ ፈልግ። ምናልባት ለቤተሰብህ አባል፣ በጉባኤ ውስጥ ላለ ሰው፣ ለሥራ ባልደረባህ፣ አብሮህ ለሚማር ልጅ፣ ለጎረቤትህ ወይም በአገልግሎት ለምታገኘው ሰው ያነበብከውን በመንገር መከለስ ትችል ይሆናል። ቁልፍ የሆኑትን ነጥቦች ብቻ ሳይሆን ከዚያ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን የጥቅስ ማስረጃዎችም አስታውሰህ ለመናገር ሞክር። ይህን ማድረግ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለማስታወስ የሚረዳህ ከመሆኑም ሌላ ሐሳቡን የምታካፍላቸው ሰዎችም ይጠቀማሉ።
ጠቃሚ በሆኑ ነገሮች ላይ አሰላስል
ያነበብከውን ከመከለስና ለሌሎች ከመንገር በተጨማሪ በተማርካቸው ገንቢ ነገሮች ላይ ማሰላሰልህ ጠቃሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን የመጻፍ ድርሻ የነበራቸው አሳፍና ዳዊትም እንዲሁ አድርገዋል። አሳፍ እንዲህ ብሏል:- “የእግዚአብሔርን ሥራ አስታወስሁ፤ የቀደመውን ተአምራትህን አስታውሳለሁና፤ በምግባርህም ሁሉ እናገራለሁ፣ በሥራህም እጫወታለሁ።” (መዝ. 77:11, 12) ዳዊትም በተመሳሳይ “በመኝታዬም አስብሃለሁ” እንዲሁም “የቀድሞውን ዘመን አሰብሁ፣ ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ” ሲል ጽፏል። (መዝ. 63:6፤ 143:5) አንተስ እንዲህ ታደርጋለህ?
ስለ ይሖዋ ሥራዎች፣ ስለ ባሕርያቱ እንዲሁም ስለ ፈቃዱ በዚህ መንገድ በጥልቀት ማሰላሰልህ ከንባብህ ያገኘውን ሐሳብ እንዳትረሳ ከመርዳት የበለጠም ጠቀሜታ ይኖረዋል። በዚህ መልኩ የማሰላሰል ልማድ ማዳበርህ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነጥቦች በልብህ ውስጥ ተቀርጸው እንዲቀሩ ይረዳሃል። ውስጣዊ ማንነትህን ይለውጠዋል። የልብህ ዝንባሌ የሚወሰነው በውስጥህ ተቀርጸው በሚቀሩት ነገሮች ነው።—መዝ. 119:16
የአምላክ መንፈስ የሚጫወተው ሚና
ስለ ይሖዋ ሥራዎችና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች አንዳንድ እውነቶችን ለማስታወስ በምናደርገው ጥረት መንፈስ ቅዱስ ይረዳናል። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ለተከታዮቹ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- ‘ከእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው ረዳት እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያስታውሳችኋል።’ (ዮሐ. 14:25, 26) ኢየሱስ ይህን ሲናገር ከሰሙት ሰዎች መካከል ማቴዎስና ዮሐንስ ነበሩ። በእርግጥ ኢየሱስ እንዳለው መንፈስ ቅዱስ ረድቷቸዋልን? አዎን፣ ረድቷቸዋል! ማቴዎስ ከስምንት ዓመታት ገደማ በኋላ ስለ ክርስቶስ ሕይወት ብዙ ዝርዝሮችን የያዘውን የመጀመሪያ ዘገባ ጽፎ አጠናቅቋል። ይህ ዘገባ የተራራውን ስብከት እንዲሁም ስለ ክርስቶስ መገኘትና ስለ ሥርዓቱ ፍጻሜ የሚናገሩትን ዝርዝር ምልክቶች አካትቷል። ኢየሱስ ከተገደለ ከስድሳ አምስት ዓመት በኋላ ደግሞ ሐዋርያው ዮሐንስ ጌታ ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠቱ በፊት ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት የተናገራቸውን ዝርዝር ጉዳዮች አካትቶ የያዘውን ወንጌል ጽፏል። ማቴዎስም ሆነ ዮሐንስ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር በነበረ ጊዜ ያደረጋቸውንና የተናገራቸውን ነገሮች ጥሩ አድርገው ያስታውሱ እንደነበር ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ይሖዋ በቃሉ ውስጥ እንዲካተቱ የሚፈልጋቸውን ዝርዝር ጉዳዮች እንዲያስታውሱ በማድረግ ረገድ መንፈስ ቅዱስ ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
ዛሬስ መንፈስ ቅዱስ የአምላክ አገልጋዮችን ይረዳል? አዎን፣ ይረዳል! እርግጥ መንፈስ ቅዱስ ጨርሶ የማናውቃቸው ነገሮች እንዲከሰቱልን ያደርጋል ማለት አይደለም። ይሁንና ከዚህ ቀደም ያጠናናቸውን አንዳንድ አስፈላጊ ነገሮች እንድናስታውስ ይረዳናል። (ሉቃስ 11:13፤ 1 ዮሐ. 5:14) ከዚያም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ‘በቅዱሳን ነቢያት ቀድሞ የተባለውን ቃል እንዲሁም የጌታንና የመድኃኒትን ትእዛዝ እንድናስታውስ’ ይረዳናል።—2 ጴጥ. 3:1, 2
“እንዳትረሳ”
ይሖዋ በተደጋጋሚ ጊዜ እስራኤላውያንን ‘እንዳትረሳ’ ሲል አስጠንቅቋቸዋል። ሁሉንም ነገር አንድ በአንድ እንዲያስታውሱ ይጠብቅባቸው ነበር ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ በግል ጉዳዮቻቸው ተጠላልፈው ይሖዋ ያደረገላቸውን ጨርሶ መዘንጋት አልነበረባቸውም። ይሖዋ እነርሱን ነፃ ለማውጣት መልአኩን ልኮ የግብጽን በኩር ሁሉ በሰይፍ ስለት እንደገደለ፣ ቀይ ባሕርን ከፍሎ እንዳሻገራቸውና በኋላም ፈርዖንንና ሠራዊቱን እዛው እንዳሰጠማቸው ተመልክተዋል። ይህ ከአእምሮአቸው ሊጠፋ የሚገባ ታሪክ አልነበረም። እስራኤላውያን አምላክ ሕጉን በሲና ተራራ እንደሰጣቸውና በምድረ በዳ እየመራ ተስፋይቱ ምድር እንዳስገባቸውም ማስታወስ ነበረባቸው። መርሳት የለባቸውም ሲባል ስለ እነዚህ ክንውኖች ያላቸው ትዝታ ምንጊዜም በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ላይ በጎ ተጽእኖ ሊያሳድር ይገባ ነበር ማለት ነው።—ዘዳ. 4:9, 10፤ 8:10-18፤ ዘጸ. 12:24-27፤ መዝ. 136:15
እኛም እንዳንረሳ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ከዕለት ተዕለት የሕይወት ውጣ ውረድ ጋር ስንታገል ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ እንዲሁም ፍጹም የሆነ ዘላለማዊ ሕይወት እንድናገኝ ሲል ልጁን በመስጠት ፍቅር እንዳሳየን መዘንጋት የለብንም። (መዝ. 103:2, 8፤ 106:7, 13፤ ዮሐ. 3:16፤ ሮሜ 6:23) ይህ ውድ እውነት ምን ጊዜም ከአእምሮአችን እንዳይጠፋ ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎችና በመስክ አገልግሎት በትጋት መሳተፍ ያስፈልገናል።
ከባድም ይሁን ቀላል፣ ውሳኔ የሚጠይቅ ሁኔታ ሲያጋጥምህ የተማርከውን ውድ እውነት ለማስታወስና በዚያ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ለማድረግ ጣር። አትርሳ። ይሖዋ የሚሰጠውን መመሪያ ለማግኘት ሞክር። ነገሩን ከራስህ ስሜት አንጻር ከማየት ወይም ፍጹም ያልሆነው ልብህ በሚያሳድረው ግፊት ከመመራት ይልቅ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘በአምላክ ቃል ውስጥ ይህን ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳኝ ምን ምክር ወይም መሠረታዊ ሥርዓት አገኛለሁ?’ (ምሳሌ 3:5-7፤ 28:26) ከዚህ በፊት ያላነበብከውን ወይም ያልሰማኸውን ልታስታውስ አትችልም። ይሁን እንጂ ትክክለኛ እውቀት እያካበትህ ስትሄድ የአምላክ መንፈስ ብዙ የሚያስታውስህ ነገር ይኖራል። ለይሖዋ ያለህ ፍቅር እያደገ መሄዱ ደግሞ ከዚያ ጋር የሚስማማ ውሳኔ እንድታደርግ ያነሳሳሃል።