ለማንበብ ትጋ
አሁን አንተ እያደረግህ ያለኸውን ነገር እንስሳት ሊያደርጉት አይችሉም። በዛሬው ጊዜ ከ6 ሰዎች አንዱ ማንበብ አይችልም። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የትምህርት ዕድል አለማግኘት ነው። ማንበብ ከሚችሉት መካከልም ቢሆን ብዙዎቹ አዘውትሮ የማንበብ ልማድ የላቸውም። ይሁንና ማንበብ መቻልህ ስለ ሌሎች አገሮች ለማወቅ፣ ከሌሎች ሰዎች የሕይወት ልምድና ተሞክሮ ለመማር እንዲሁም በሕይወትህ የሚገጥሙህን አሳሳቢ ነገሮች ለመወጣት የሚረዳ ተግባራዊ እውቀት ለመገብየት ያስችልሃል።
አንድ ወጣት በትምህርት ዓለም ከሚያሳልፈው ጊዜ የሚያገኘው ጥቅም በማንበብ ችሎታው ላይ የተመካ ነው። የማንበብ ችሎታው ሥራ ሲፈልግ ሊያገኝ በሚችለው የሥራ ዓይነት ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል። ወይም ደግሞ ኑሮውን ለማሸነፍ ምን ያህል መሥራት እንዳለበትም ሳይቀር የሚወስን ሊሆን ይችላል። ጥሩ የማንበብ ልማድ ያላቸው የቤት እመቤቶች ቤተሰባቸው የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ በማድረግ፣ ቤታቸውን በንጽሕና በመያዝና የቤተሰባቸውን አባላት ከበሽታ በመጠበቅ ረገድ የተሻለ ብቃት ይኖራቸዋል። አንባቢ የሆኑ እናቶችም በልጆቻቸው የአእምሮ ብስለት ረገድ በጎ ተጽእኖ ሊኖራቸው ይችላል።
እርግጥ ከሁሉ የላቀው የማንበብ ጥቅም የአምላክን እውቀት ማግኘት የሚያስችልህ መሆኑ ነው። (ምሳሌ 2:5) አምላክን የምናገለግልባቸው ብዙዎቹ መንገዶች የማንበብ ችሎታ የሚጠይቁ ናቸው። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ይነበባሉ። ንባብ በመስክ አገልግሎት በሚኖርህ ውጤታማነት ረገድ የሚኖረውም ድርሻ ከፍተኛ ነው። ለእነዚህ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምታደርገው ዝግጅትም ቢሆን ማንበብን ይጠይቃል። ከዚህ የተነሣ መንፈሳዊ እድገትህ በንባብ ልማድህ ላይ በእጅጉ የተመካ ነው ማለት ይቻላል።
አጋጣሚውን በሚገባ ተጠቀምበት
ዛሬ የአምላክን መንገድ እየተማሩ ካሉት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ያላቸው የትምህርት ደረጃ ውስን ነው። እነዚህ ሰዎች መንፈሳዊ እድገታቸውን ለማሻሻል ማንበብን መማር ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ወይም ደግሞ የንባብ ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ በግል እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸው ይሆናል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ጉባኤዎች መሠረተ ትምህርት የሚሰጥበት ዝግጅት ሊያደርጉ ይችላሉ። በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከዚህ ዝግጅት ብዙ ተጠቅመዋል። ጥሩ የንባብ ችሎታ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ አንዳንድ ጉባኤዎች የንባብ ችሎታቸውን ማሻሻል የሚያስፈልጋቸውን ለመርዳት ሲሉ ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ጎን ለጎን ተጨማሪ ዝግጅት ያደርጋሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ ዝግጅቶች ባይኖሩም እንኳ አንድ ሰው በየዕለቱ ጮክ ብሎ ለማንበብ ጊዜ በመመደብና በትምህርት ቤቱ አዘውትሮ እየተገኘ ተሳትፎ በማድረግ የንባብ ችሎታውን ማሻሻል ይችላል።
የሚያሳዝነው ግን አስቂኝ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ከሌሎች ነገሮች ጋር ተዳምረው ንባብ በብዙ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ቦታ እንዲነፈገው ምክንያት ሆነዋል። አንድ ሰው አዘውትሮ ቴሌቪዥን የሚመለከትና እምብዛም የማያነብብ ከሆነ የማንበብ ችሎታው ብቻ ሳይሆን በትክክል የማሰብና የማመዛዘን እንዲሁም ሐሳቡን አቀነባብሮ የመግለጽ ችሎታው ይዳከማል።
‘ታማኝና ልባም ባሪያ’ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የሚያስችሉንን ጽሑፎች ያቀርብልናል። እነዚህ ጽሑፎች ለመንፈሳዊነታችን ወሳኝ የሆነ ብዙ ትምህርት ይዘው ይወጣሉ። (ማቴ. 24:45፤ 1 ቆሮ. 2:12, 13) ዓበይት ስለሆኑ የዓለም ክንውኖችና እነዚህ ክንውኖች ስላላቸው ትርጉም ይነግሩናል፣ ከተፈጥሮ ጋር ይበልጥ እንድንተዋወቅ ይረዱናል እንዲሁም የሚያሳስቡንን አንዳንድ ጉዳዮች እንዴት መወጣት እንደምንችል ያስተምሩናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማገልገልና የእርሱን ሞገስ ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ በጥልቀት ያብራሩልናል። እንዲህ ያለው የሚገነባ ንባብ መንፈሳዊ ሰው እንድትሆን ይረዳሃል።
እርግጥ ካልተጠነቀቅን ማንበብ ምንም አደጋ የለውም ማለት አይደለም። ይህን ችሎታ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል። እንደምንመገበው ምግብ ሁሉ የምናነበውንም ነገር መምረጥ ይኖርብናል። ምንም ጠቀሜታ የሌለውን ወይም ሊመርዝህ የሚችልን ምግብ የምትመገብበት ምን ምክንያት ይኖራል? በተመሳሳይም ልብህንና አእምሮህን የሚበክል መረጃ የያዘ ጽሑፍ ከሆነ በአጋጣሚ ያገኘኸውም እንኳ ቢሆን ልታነብበው አይገባም። የምናነብባቸውን ነገሮች በመምረጥ ረገድ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ልንመራ ይገባል። አንድ ጽሑፍ ለማንበብ ከመወሰንህ በፊት እንደሚከተሉት ያሉትን ጥቅሶች አስብ:- መክ. 12:12, 13፤ ኤፌ. 4:22-24፤ 5:3, 4፤ ፊልጵ. 4:8፤ ቆላ. 2:8፤ 1 ዮሐ. 2:15-17 እንዲሁም 2 ዮሐ. 10
ስታነብብ ተገቢው የልብ ዝንባሌ ይኑርህ
በምናነብበት ጊዜ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል የሚለው ነጥብ በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ መጻሕፍትን ጠንቅቀው የሚያውቁት የሃይማኖት መሪዎች ላቀረቡት መሰሪ ጥያቄ መልስ ከመስጠቱ በፊት “አላነበባችሁምን?” እንዲሁም “ከቶ አላነበባችሁምን?” እያለ ይጠይቃቸው እንደነበር በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ተጠቅሶ እናገኛለን። (ማቴ. 12:3, 5፤ 19:4፤ 21:16, 42፤ 22:31) ስናነብብ ትክክለኛው የልብ ዝንባሌ ከሌለን ወደተሳሳተ መደምደሚያ ልናመራ ወይም ጨርሶ ነጥቡን ልንስት እንደምንችል ከዚህ ታሪክ እንማራለን። ፈሪሳውያን በመጻሕፍት አማካኝነት የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉ ስለመሰላቸው ቅዱሳን ጽሑፎችን ያነብቡ ነበር። ኢየሱስ ለይሖዋ ፍቅር የሌላቸውና አምላክ ያደረገውን የመዳን ዝግጅት የማይቀበሉ ሰዎች ይህን ሽልማት እንደማያገኙ ጠቁሟል። (ዮሐ. 5:39-43) ፈሪሳውያኑ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለመመርመር የተነሡበት ዓላማ ከራስ ወዳድነት የመነጨ ነበር። በዚህ ምክንያት የደረሱባቸው ብዙዎቹ መደምደሚያዎች የተሳሳቱ ነበሩ።
የአምላክን ቃል እንድናነብብ የሚገፋፋን ዋነኛው ነገር ለይሖዋ ያለን ፍቅር መሆን አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር “ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል” ስለሚል ለይሖዋ ያለን እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ስለ ፈቃዱ እንድንማር ያነሳሳናል። (1 ቆሮ. 13:6) ከዚህ ቀደም የማንበብ ፍላጎት ያልነበረን ሰዎች ብንሆንም እንኳ ይሖዋን ‘በፍጹም አሳባችን’ የምንወድድ ከሆነ የአምላክን እውቀት ለመቅሰም እንጥራለን። (ማቴ. 22:37) ፍቅር ለአንድ ነገር ጉጉት እንዲያድርብን ያደርጋል፤ ይህ ጉጉት ደግሞ የማወቅ ፍላጎት ያሳድርብናል።
ለንባብ ፍጥነትህ ትኩረት መስጠት
ንባብ ከቃላት ጋር የመተዋወቅ ጉዳይ ነው። አሁንም ቢሆን እያነበብህ ያለኸው ቃላቱን ስለምታውቃቸውና ትርጉማቸውን ስለምታስታውስ ነው። የምታውቃቸው ቃላት ብዛት እያደገ ከሄደ የንባብ ፍጥነትህ ሊጨምር ይችላል። እያንዳንዱን ቃል በተናጠል ከማየት ይልቅ ሁለት ሦስት ቃላትን በአንድ ጊዜ ለማየት ሞክር። ከቃላት ጋር ያለህ ትውውቅ እያደገና እየሰፋ ሲሄድ የምታነብበውን ነገር በቀላሉ መረዳት ትችላለህ።
ትምህርቱ ከበድ ያለ በሚሆንበት ጊዜ ግን የምታደርገው ጥረት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም ያስፈልግህ ይሆናል። ይሖዋ ቅዱሳን ጽሑፎችን ስለማንበብ ኢያሱን እንዲህ ሲል መክሮታል:- ‘የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፣ ድምፅህን ዝቅ አድርገህ አንብበው።’ (ኢያሱ 1:8 NW ) በአብዛኛው አንድ ሰው ድምፁን ዝቅ አድርጎ ብቻውን የሚያወራው በሚያሰላስልበት ጊዜ ነው። በመሆኑም ‘ዝቅ ባለ ድምፅ ማንበብ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ቃል “ማሰላሰል” ተብሎም ተተርጉሟል። (መዝ. 63:6 አ.መ.ት ፤ መዝ. 77:12 አ.መ.ት ፤ መዝ. 143:5) አንድ ሰው በሚያሰላስልበት ጊዜ ረጋ ብሎ ጥልቀት ባለው መንገድ ጉዳዩን ያብሰለስላል። እያሰላሰሉ ማንበብ የአምላክ ቃል በአእምሮና በልባችን ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ይረዳል። መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን፣ ምክሮችን፣ ምሳሌዎችን፣ ግጥሞችን፣ መለኮታዊ የፍርድ ብያኔዎችን፣ ስለ ይሖዋ ዓላማ የሚገልጹ ማብራሪያዎችን እንዲሁም የብዙ ሰዎችን የሕይወት ተሞክሮ አካትቶ ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት እነዚህ መልእክቶች በይሖዋ መንገድ መመላለስ ለሚፈልጉ ሁሉ እጅግ ጠቃሚ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስን በአእምሮና በልብህ ውስጥ እንዲቀረጽ በሚያስችል መንገድ ማንበብህ ምንኛ ጠቃሚ ነው!
ሐሳብህን መሰብሰብ ተማር
በምታነብበት ጊዜ ራስህን በታሪኩ ውስጥ እንዳለህ አድርገህ አስብ። ባለ ታሪኮቹን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳልና ራስህን በእነርሱ ቦታ በማስቀመጥ ስሜታቸውን ለመጋራት ሞክር። በ1 ሳሙኤል ምዕራፍ 17 ላይ የተገለጸውን የዳዊትንና የጎልያድን ታሪክ የመሰለ ዘገባ በምታነብበት ጊዜ ይህንን ማድረጉ ብዙም ላይከብድ ይችላል። ይሁን እንጂ ስለ ማደሪያው ድንኳን ግንባታ ወይም ስለ ክህነት አገልግሎቱ መቋቋም በዘጸአትና በዘሌዋውያን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘውን ዘገባ ስታነብም ቢሆን ስለ ድንኳኑ ስፋትና ጥቅም ላይ ስለዋሉት ቁሳቁሶች በዓይነ ሕሊናህ መሳልህ ወይም ስለ ዕጣኑ፣ ስለሚጠበሰው እሸት እንዲሁም ስለሚቃጠለው መሥዋዕት መዓዛ ማሰብህ ንባብህን ሕያው ሊያደርግልህ ይችላል። የክህነት አገልግሎት ማከናወን ምን ያህል ታላቅ መብት እንደነበር አስብ! (ሉቃስ 1:8-10) በምታነብበት ጊዜ ከላይ እንደተገለጸው መላ የስሜት ሕዋሳትህን በመጠቀም በንባቡ መመሰጥህ የምታነብበውን ነገር ጠቀሜታ እንድታስተውልና በኋላም እንዳትረሳው ይረዳሃል።
ይሁንና ካልተጠነቀቅህ ለማንበብ ስትሞክር ሐሳብህ እየተበተነ ሊያስቸግርህ ይችላል። ዓይኖችህ የምታነበው ነገር ላይ ተተክለው ሐሳብህ ግን ሌላ ቦታ ሊሄድ ይችላል። ሙዚቃ ወይም ቴሌቪዥን ተከፍቷል? የቤተሰብ አባላት እያወሩ ነው? በተቻለ መጠን ፀጥ ያለ ቦታ ሆኖ ማንበብ የተሻለ ነው። ይሁን እንጂ ሐሳባችን እንዲበተን የሚያደርጉ ነገሮች ከራሳችንም ሊመነጩ ይችላሉ። ምናልባት በሥራ ተወጥረህ ውለህ ይሆናል። ከሆነ የቀኑ ውሎህ በተደጋጋሚ ወደ አእምሮህ እየመጣ ሊያስቸግርህ ይችላል! እርግጥ ውሎህን መለስ ብለህ መቃኘትህ ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ ያለብህ እያነበብክ ባለህበት ጊዜ አይደለም። ምናልባት ንባብህን የጀመርከው ሐሳብህን ሰብስበህ ወይም ደግሞ ጸልየህ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ማንበብህን ስትቀጥል ሐሳብህ መበተን ይጀምራል። እንደገና ሐሳብህን ለመሰብሰብ ሞክር። አእምሮህ እያነበብከው ባለኸው ነገር ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ ራስህን መግዛት ያስፈልግሃል። እንዲህ ካደረግህ ቀስ በቀስ እያሻሻልክ ትሄዳለህ።
አንድ የማታውቀው ቃል ሲያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ? የአንዳንድ እንግዳ የሆኑ ቃላት ፍቺ በዚያው በጽሑፉ ውስጥ ይገለጽ ወይም ማብራሪያ ይሰጥበት ይሆናል። ወይም ደግሞ በዙሪያው ካለው ሐሳብ የቃሉን ትርጉም መረዳት ትችል ይሆናል። ካልሆነ ግን መዝገበ ቃላት ተመልከት። ወይም ሌላ ሰው መጠየቅ እንድትችል ቃሉን ምልክት አድርግበት። ይህም የምታውቃቸውን ቃላት ብዛት ያሳድግልሃል እንዲሁም አንብቦ የመረዳት ችሎታህን ያጎለብትልሃል።
ለሌሎች ማንበብ
ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ለማንበብ እንዲተጋ ሲመክረው መጥቀስ የፈለገው ለሌሎች ስለ ማንበብ ነበር። (1 ጢሞ. 4:13) ለሌሎች በምናነብበት ጊዜ ንባባችንን ጥሩ ነው የሚያሰኘው ቃላቱን መጥራት መቻላችን ብቻ አይደለም። አንባቢው የቃላቱን ትርጉም እንዲሁም የሚያስተላልፉትን መልእክት ሊረዳ ይገባል። ሐሳቡን በትክክል መግለጽና ተገቢውን ስሜት ማንጸባረቅ የሚችለው ይህንን ሲያደርግ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ጥልቀት ያለው ዝግጅትና ልምምድ ይጠይቃል። በመሆኑም ጳውሎስ ‘ለማንበብ ትጋ ’ ሲል አጥብቆ አሳስቧል። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ውስጥ በዚህ ረገድ ግሩም ሥልጠና ታገኛለህ።
ለንባብ ጊዜ መድብ
“የትጉህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል፤ ችኮላም ወደ ድኽነት ያደርሳል።” (ምሳሌ 21:5 አ.መ.ት ) የማንበብ ፍላጎታችንን በተመለከተም ይህ አባባል በትክክል ይሠራል! ከንባባችን “ትርፍ” ለማግኘት ከፈለግን ሌሎች ነገሮች ለንባብ የሚሆን ጊዜ እንዳያሳጡን ትጋት የተሞላበት እቅድ ማውጣት ይኖርብናል።
የምታነብበው መቼ መቼ ነው? አንተ የምትመርጠው ጠዋት በማለዳ ተነስተህ ማንበብ ነው? ወይስ ይበልጥ ነቃ የምትለው ረፋዱ ላይ ነው? በየዕለቱ ቢያንስ 15 ወይም 20 ደቂቃ ለንባብ መመደብ ብትችል ከጊዜ በኋላ ምን ያህል እንዳነበብህ መለስ ብለህ ስታስበው በጣም ትገረማለህ። ቁልፍ የሆነው ነገር አዘውታሪ መሆንህ ነው።
ይሖዋ ታላቅ ዓላማው በጽሑፍ እንዲሰፍር የመረጠበት ምክንያት ምንድን ነው? ሰዎች ቃሉን አንብበው መመሪያ እንዲያገኙ ነው። ይህም የይሖዋን ድንቅ ሥራዎች ለመመርመር፣ ስለ ሥራዎቹም ለልጆቻቸው ለመንገርና አምላክ ያደረጋቸውን ነገሮች ሁልጊዜ ለማስታወስ ያስችላቸዋል። (መዝ. 78:5-7) እንዲህ ላለው የይሖዋ ልግስና ያለንን አድናቆት ለማሳየት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ሕይወት ሰጪ የሆነውን ቃሉን ለማንበብ መትጋት ነው።