ጥናት 2
ቃላትን አጥርቶ መናገር
ሐሳብህን ጥሩ አድርገህ ለመግለጽ ጥርት አድርገህ መናገር ያስፈልግሃል። ለመናገር የፈለግኸው ሐሳብ የሚስብ ምናልባትም በጣም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ቃላቱን ሰዎች በቀላሉ መረዳት የማይችሉ ከሆነ የምትናገረው አብዛኛው ነገር መና ይቀራል ማለት ነው።
ሰዎች ለተግባር የሚነሳሱት መልእክቱ በደንብ ከገባቸው ነው። አንድ ሰው በቀላሉ ሊሰማ የሚችል ኃይለኛ ድምፅ ቢኖረውም ሲናገር ቃላቱን የሚውጥ ከሆነ ንግግሩ ሌሎችን ለተግባር ሊያነሳሳ አይችልም። አድማጮቹ በማያውቁት ባዕድ ቋንቋ የሚናገር ያህል ይሆናል። (ኤር. 5:15) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ያሳስበናል:- “ደግሞም መለከት የማይገለጥን ድምፅ ቢሰጥ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል? እንዲሁ እናንተ ደግሞ የተገለጠውን ቃል በአንደበት ባትናገሩ ሰዎች የምትናገሩትን እንዴት አድርገው ያስተውሉታል? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁና።”—1 ቆሮ. 14:8, 9
ቃላት በግልጽ እንዳይሰሙ የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል? ምናልባት ስትናገር አፍህ በደንብ አይከፈት ይሆናል። የመንገጭላ ጡንቻዎችህና ከንፈሮችህ እንደልብ የማይንቀሳቀሱ ከሆነ ስትናገር የምታጉተመትም ሊመስል ይችላል።
በተጨማሪም ስትናገር የምትፈጥን ከሆነ ምን እንዳልህ መረዳት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ይህ አንድን በቴፕ የተቀዳ ንግግር በፍጥነት ከማጫወት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ቃሎቹ ቢኖሩም አብዛኛው ነገር የማይጨበጥ ይሆናል።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ንግግሩ በግልጽ የማይሰማው በአንደበት ክፍሎች ላይ እክል ሲኖር ነው። እንዲህ ዓይነት እክል ያለባቸውም እንኳ ቢሆኑ በዚህ ጥናት ውስጥ የተሰጡትን ሐሳቦች ሥራ ላይ በማዋል ብዙ ለውጥ ማድረግ ይችላሉ።
ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ አንድ ንግግር ግልጽ እንዳይሆን የሚያደርገው ቃላትን መዋጥ ማለትም ለመረዳት በሚቸግር መልኩ አንድ ላይ ጨፍልቆ መናገር ነው። ችግሩ ቁልፍ ሚና ያላቸውን ወይም በቃላቱ መጨረሻ ላይ የሚገኙ ፊደላትን መዝለል ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው ቃላቱን ለመለየት በሚያስቸግር ሁኔታ አንድ ላይ ጨፍልቆ የሚጠራቸው ከሆነ አድማጮቹ የሚይዙት የተወሰነውን ሐሳብ ብቻ ስለሚሆን የቀረውን ለመገመት ይገደዳሉ። እንግዲያው አንድ ሰው ቃላትን አጥርቶ መናገር አለመቻሉ በማስተማር ሥራው ውጤታማ እንዳይሆን እንቅፋት ሊሆንበት ይችላል።
አጥርቶ መናገር የሚቻለው እንዴት ነው? ቃላትን አጥርቶ ለመናገር ከሚያስችሉት ቁልፍ ነገሮች አንዱ የቋንቋህን የቃላት አወቃቀር መረዳት ነው። በብዙ ቋንቋዎች ቃላት በቀለማት (syllables) የተዋቀሩ ናቸው። ቀለማት ደግሞ እንደ አንድ አሃድ ሆነው ሊነበቡ የሚችሉ አንድና ከዚያም በላይ ሆሄያትን የያዙ ናቸው። ቋንቋው በዚህ መልክ የተዋቀረ በሚሆንበት ጊዜ ለሁሉም ቀለማት እኩል አጽንኦት ይሰጣል ማለት ባይሆንም በንግግር ወቅት እያንዳንዱ ቀለም ይደመጣል። ጥርት አድርጎ የመናገር ችሎታህን ማሻሻል ከፈለግህ ረጋ ብለህ እያንዳንዱን ቀለም በሚገባ ለመጥራት ሞክር። መጀመሪያ አካባቢ ከልክ በላይ የምትጠነቀቅ ሊያስመስልብህ ይችላል። እየተለማመድህ ስትሄድ ግን ንግግርህ ጥርት ያለ እየሆነ ይሄዳል። ለንግግር ቅልጥፍና ስትል የተወሰኑ ቃላትን አንድ ላይ አጣምረህ ልትጠራ እንደምትችል ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ የቃላቱ መልእክት እንዲሰወር የሚያደርግ ከሆነ ይህን ከማድረግ መቆጠብ ይኖርብሃል።
አንድ ልታስብበት የሚገባ ጉዳይ አለ። አጥርቶ የመናገር ችሎታህን ለማሻሻል ስትል በምታነብበትም ሆነ በምትናገርበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ታደርግ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ የዘወትሩን የአነጋገር ልማድህን እንዲቀርጸው መፍቀድ የለብህም። እንደዚያ ካደረግህ ሌሎችን ኮርጀህ የምትናገር ሊመስል ይችላል።
ስትናገር የምታወጣው ድምፅ የታፈነ ከሆነ ራስህን በደንብ ቀና አድርገህ መናገርን ተለማመድ። ጥቅስ በምታነብበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስህን ከፍ አድርገህ ከያዝክ አድማጮችህን ቀና ብለህ አይተህ ወደ መጽሐፍ ቅዱስህ ስትመለስ ብዙ ማቀርቀር አያስፈልግህም። ይህም የምትናገራቸው ቃላት ጥርት ብለው እንዲሰሙ ያስችላል።
ሰውነትህን ዘና ማድረግ የምትችልበትን ዘዴ መማር ንግግርህን ለማሻሻል ሊረዳህ ይችላል። በፊት ጡንቻዎች ወይም አተነፋፈስን በሚቆጣጠሩ ጡንቻዎች ላይ የሚፈጠር ውጥረት የድምፅ አወጣጥ ሥርዓትን ሊያስተጓጉል ይችላል። በአእምሮ፣ በአንደበት ክፍሎችና በአተነፋፈስ ሥርዓት መካከል ጥሩ ቅንጅት ሊኖር ይገባል። ውጥረት ደግሞ ይህ ዓይነቱ ቅንጅት እንዳይኖር እንቅፋት ይሆናል።
የመንገጭላ ጡንቻዎች ከአንጎል ለሚተላለፈው ትእዛዝ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዲችሉ ዘና ማለት ይኖርባቸዋል። ከንፈሮችም ቢሆኑ ዘና ማለት አለባቸው። በአፍና በጉሮሮ ውስጥ የሚፈጠሩትን ብዙ ድምፆች ለማውጣት ይችሉ ዘንድ ከንፈሮች በቀላሉ መኮማተርና መለጠጥ መቻል ይኖርባቸዋል። በመንገጭላ ጡንቻዎችና በከንፈር አካባቢ ውጥረት ካለ አፍ በትክክል ስለማይከፈት ድምፅ በጥርሶች መካከል ተገፍቶ ለመውጣት ይገደዳል። ይህም ንግግሩ የተጉተመተመ፣ የታፈነና ግልጽ ያልሆነ እንዲሆን ያደርጋል። መንገጭላና ከንፈሮች ዘና እንዲሉ ማድረግ ሲባል እየተዘባነኑ መናገር ማለት አይደለም። ጡንቻዎችን ዘና የማድረጉ ጉዳይ ከድምፆች አወጣጥ ጋር ሚዛናዊ ሊሆን ይገባል።
ድምፅህን ከፍ አድርገህ ማንበብህ ሁኔታህን ለመገምገም ሊረዳህ ይችላል። ድንቅ የሆኑትን የአንደበት ክፍሎች እንዴት እየተጠቀምህባቸው እንዳለህ ለማስተዋል ሞክር። የምትናገራቸው ቃላት ያለ ምንም መደነቃቀፍ እንዲወጡ አፍህን በደንብ ትከፍታለህ? በንግግር ረገድ ምላስ ብዙ ድርሻ ቢኖረውም ብቸኛው የአንደበት ክፍል እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብሃል። አንገት፣ የታችኛው መንገጭላ፣ ከንፈር፣ የፊት ጡንቻዎችና የጉሮሮ ጡንቻዎች ሁሉ የየራሳቸው ድርሻ አላቸው። በምትናገርበት ጊዜ ፊትህ ላይ ምንም እንቅስቃሴ አይታይም? ከሆነ ንግግርህ ጥርት ብሎ ላይሰማ ይችላል።
ቴፕ ካለህ በመስክ አገልግሎት ካገኘኸው ሰው ጋር እንደምትወያይ ሆነህ እየተናገርህ ድምፅህን ቅዳ። በዚህ መልኩ እንደ ወትሮህ እየተናገርህ ለተወሰነ ደቂቃ የቀዳኸውን ድምፅህን ማዳመጥ አንዳንድ ቃላትን አጥርቶ በመናገር በኩል ያለብህን ችግር ለማስተዋል ሊረዳህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል የምትውጣቸው፣ አፍነህ የምታስቀራቸው ወይም አሳጥረህ የምትጠራቸው ቃላት ካሉ ትኩረት ልትሰጣቸው ይገባል። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር። ብዙውን ጊዜ ከላይ የተሰጠውን ሐሳብ ተግባራዊ በማድረግ እንዲህ ዓይነቶቹን ችግሮች ማስወገድ ይቻላል።
ስትናገር የመኮለታተፍ ችግር አለብህ? ከሆነ አፍህን ከወትሮው ይበልጥ ከፈት በማድረግ ቃላቱን በጥንቃቄ ለመጥራት ሞክር። ትንፋሽ ወደ ውስጥ ስበህ ሳንባህን በአየር በመሙላት ቀስ እያልክ ተናገር። ሲናገሩ የመኮለታተፍ ችግር ያለባቸው ብዙ ሰዎች ይህንን በማድረጋቸው በተሻለ ጥራት መናገር ችለዋል። ችግሩን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ባትችል እንኳ ተስፋ አትቁረጥ። ይሖዋ ለእስራኤል ሕዝብም ሆነ ለፈርዖን በጣም ወሳኝ የሆነውን መልእክት ለማድረስ የተጠቀመው ኮልታፋ በነበረው በሙሴ እንደነበር አስታውስ። (ዘጸ. 4:10-12) ፈቃደኛ ሆነህ ከተገኘህ ይሖዋ በአንተም ሊጠቀም ይችላል። በአገልግሎትህም ስኬታማ እንድትሆን ይረዳሃል።