ምዕራፍ አሥራ ስምንት
“ከዓለም አይደሉም”
1. (ሀ) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ስለ ደቀ መዛሙርቱ ምን ብሎ ጸልዮአል? (ለ) ‘የዓለም ክፍል አለመሆን’ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ኢየሱስ ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽት ስለ ደቀ መዛሙርቱ ጸልዮ ነበር። ሰይጣን ከባድ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርባቸው ስላወቀ እንዲህ ሲል ወደ አባቱ ጸልዮአል:- “የምለምንህም ከክፉው እንድትጠብቃቸው እንጂ፣ ከዓለም እንድታወጣቸው አይደለም። እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ፣ እነርሱም ከዓለም አይደሉም።” (ዮሐንስ 17:15, 16) ከዓለም መለየት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የዚህ ዓለም ገዥ ሰይጣን ስለሆነ ነው። ክርስቲያኖች በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም ክፍል መሆን አይፈልጉም።—ሉቃስ 4:5-8፤ ዮሐንስ 14:30፤ 1 ዮሐንስ 5:19
2. ኢየሱስ የዓለም ክፍል አለመሆኑን ያሳየው በምን መንገዶች ነው?
2 ኢየሱስ የዓለም ክፍል አለመሆኑ ለሌሎች ፍቅር እንደሌለው የሚያሳይ አይደለም። እንዲያውም የታመሙትን ፈውሷል፣ የሞቱትን አስነስቷል እንዲሁም ስለ አምላክ መንግሥት አስተምሯል። አልፎ ተርፎም ለሰው ዘር ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል። ሆኖም የሰይጣንን ዓለም መንፈስ የሚያንጸባርቁ ሰዎች ያላቸውን መጥፎ አመለካከትም ሆነ ይፈጽሙት የነበረውን ክፉ ድርጊት ይጠላ ነበር። በመሆኑም ሰዎች የጾታ ብልግና ምኞት፣ ፍቅረ ንዋይና ከሌሎች ልቆ የመታየት ፍላጎት እንዳያድርባቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 5:27, 28፤ 6:19-21፤ ሉቃስ 20:46, 47) ስለዚህ ኢየሱስ ከዓለም የፖለቲካ ጉዳዮችም መራቁ አያስደንቅም። አይሁዳዊ የነበረ ቢሆንም በሮምና በአይሁዶች መካከል በነበረው የፖለቲካ ውዝግብ ወገናዊ ለመሆን አልሞከረም።
“የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም”
3. (ሀ) የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ኢየሱስን በተመለከተ ለጲላጦስ ምን ክስ አቀረቡ? ለምንስ? (ለ) ኢየሱስ ሰብዓዊ ንጉሥ የመሆን ፍላጎት እንዳልነበረው የሚያሳየው ምንድን ነው?
3 የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ኢየሱስን ይዘው የሮማ ገዥ በሆነው በጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት ባቀረቡት ጊዜ የተፈጸመውን ሁኔታ ተመልከት። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስ ግብዝነታቸውን ስላጋለጠባቸው በጣም ተበሳጭተው ነበር። ገዥው በኢየሱስ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ለማነሳሳት “ይህ ሰው ሕዝባችንን ሲያስት፣ ለቄሳር ግብር እንዳይከፈል ሲከለክል፣ ደግሞም፣ ‘እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ’ ሲል አገኘነው” በማለት ከሰሱት። (ሉቃስ 23:2) ይህ ዓይን ያወጣ ውሸት እንደሆነ ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም ከአንድ ዓመት በፊት ኢየሱስ ሕዝቡ ሊያነግሡት በፈለጉበት ወቅት ንጉሥ ለመሆን ፈቃደኛ እንዳልነበረ ታይቷል። (ዮሐንስ 6:15) ወደፊት በሰማይ ንጉሥ እንደሚሆን ያውቅ ነበር። (ሉቃስ 19:11, 12) ከዚህም በተጨማሪ የሚያነግሡት ሰዎች ሳይሆኑ ይሖዋ ነው።
4. ኢየሱስ ግብር መክፈልን በተመለከተ ምን አመለካከት ነበረው?
4 ኢየሱስ ከመያዙ ከሦስት ቀናት በፊት ፈሪሳውያን ከግብር ጋር በተያያዘ ሊያስወነጅለው የሚችል ነገር እንዲናገር ለማድረግ ሞክረው ነበር። ሆኖም ኢየሱስ “እስቲ አንድ ዲናር [የሮማውያን ሳንቲም] አሳዩኝ፤ በላዩ ያለው የማን መልክና ጽሕፈት ነው?” አላቸው። “የቄሳር ነው” ሲሉት “እንግዲያውስ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” ሲል መለሰላቸው።—ሉቃስ 20:20-25
5. (ሀ) ኢየሱስ በተያዘበት ወቅት ለደቀ መዛሙርቱ ምን ትምህርት ሰጥቷል? (ለ) እንደዚያ ያደረገበትን ምክንያት የገለጸው እንዴት ነው? (ሐ) በመጨረሻስ ምን ተፈረደበት?
5 ኢየሱስ ሰዎች በሰብዓዊ ባለ ሥልጣናት ላይ እንዲያምጹ አላስተማረም። ወታደሮችና ሌሎች ሰዎች ኢየሱስን ሊይዙት በመጡ ጊዜ ጴጥሮስ ሰይፉን መዝዞ የአንደኛውን ሰው ጆሮ ቆረጠው። ሆኖም ኢየሱስ “በል ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” ብሎታል። (ማቴዎስ 26:51, 52) ኢየሱስ በቀጣዩ ቀን ጲላጦስ ፊት በቀረበ ጊዜ ይህን ያደረገበትን ምክንያት ሲገልጽ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም፤ ቢሆንማ ኖሮ አይሁድ እንዳይዙኝ ሎሌዎቼ በተከላከሉልኝ ነበር” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 18:36) ጲላጦስም ኢየሱስ ‘ምንም ወንጀል እንዳልሠራ’ አምኗል። ሆኖም ሕዝቡ ላሳደረበት ተጽዕኖ በመሸነፍ ኢየሱስ እንዲሰቀል አድርጓል።—ሉቃስ 23:13-15፤ ዮሐንስ 19:12-16
ደቀ መዛሙርቱ የኢየሱስን አመራር ይከተላሉ
6. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ከዓለም መንፈስ እንደሚርቁ ሆኖም ሰዎችን እንደሚወዱ ያሳዩት እንዴት ነው?
6 በዚህ መንገድ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የዓለም ክፍል አለመሆን ምን ማድረግን እንደሚጠይቅ ተገንዝበዋል። በሮማውያን ትርኢት ማሳያ ቦታዎችና ቲያትር ቤቶች ይቀርቡ የነበሩትን ዓመጽ የሞላባቸውን እንዲሁም ሥነ ምግባር የጎደላቸውን መዝናኛዎች ጨምሮ በዓለም ላይ ካለው መጥፎ መንፈስና ድርጊት መራቅ ይጠይቅባቸው ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ከእንዲህ ዓይነቶቹ መዝናኛዎች ይርቁ ስለነበር ሰዎችን እንደሚጠሉ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር። እነሱ ግን ሰዎችን ከመጥላት ይልቅ አምላክ ካደረገው የመዳን ዝግጅት እንዲጠቀሙ ለመርዳት ተግተው ይሠሩ ነበር።
7. (ሀ) የጥንቶቹ ደቀ መዛሙርት የዓለም ክፍል ባለመሆናቸው ምን ደርሶባቸዋል? (ለ) የፖለቲካ ገዥዎችንና ግብር መክፈልን በተመለከተ ምን አመለካከት ነበራቸው? ለምንስ?
7 የኢየሱስ ተከታዮች እሱ ስደት እንደደረሰበት ሁሉ እነሱም አብዛኛውን ጊዜ የተዛባ መረጃ በደረሳቸው የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ስደት ይደርስባቸዋል። ይሁን እንጂ በ56 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች “ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላሉት ሹማምንት [ለፖለቲካ ገዥዎች] መገዛት ይገባዋል፤ ከእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ሥልጣን የለምና” የሚል ማሳሰቢያ ጽፎላቸው ነበር። እንዲህ ሲባል ዓለማዊ መንግሥታትን ያቋቋመው ይሖዋ ነው ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የእሱ መንግሥት ብቻ ምድርን ሙሉ በሙሉ መግዛት እስከሚጀምርበት ጊዜ ድረስ ሕልውና እንዲኖራቸው ፈቅዷል ማለት ነው። በመሆኑም ጳውሎስ ክርስቲያኖች ዓለማዊ ባለ ሥልጣናትን እንዲያከብሩ እንዲሁም ግብር እንዲከፍሉ ማሳሰቡ ተገቢ ነው።—ሮሜ 13:1-7፤ ቲቶ 3:1, 2
8. (ሀ) ክርስቲያኖች የበላይ ባለ ሥልጣናትን መታዘዝ ያለባቸው እስከ ምን ድረስ ነው? (ለ) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የኢየሱስን አርዓያ የተከተሉት እንዴት ነው?
8 ይሁንና ክርስቲያኖች ለፖለቲካ ገዥዎች የሚገዙት ያለምንም ገደብ ሳይሆን በአንጻራዊ ሁኔታ ነው። ሰብዓዊ ሕጎች የይሖዋን ሕጎች በሚጻረሩበት ጊዜ የይሖዋ አገልጋዮች የእሱን ሕግ ይታዘዛሉ። ኦን ዘ ሮድ ቱ ሲቪላይዜሽን—ኤ ወርልድ ሂስትሪ የተባለው መጽሐፍ የጥንት ክርስቲያኖችን በተመለከተ ምን አስተያየት እንደሰጠ ተመልከት:- “ክርስቲያኖች የሮም ዜጎች ይፈጽሟቸው የነበሩትን አንዳንድ ግዴታዎች ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም። ክርስቲያኖች . . . ወታደራዊ አገልግሎት መስጠት እምነታቸውን የሚጻረር ድርጊት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት ነበር። ፖለቲካዊ ሥልጣን አይዙም፤ ንጉሠ ነገሥቱንም አያመልኩም ነበር።” የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደቀ መዛሙርቱ የስብከት ሥራቸውን እንዲያቆሙ ‘ጥብቅ ማስጠንቀቂያ’ በሰጣቸው ጊዜ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።—የሐዋርያት ሥራ 5:27-29
9. (ሀ) በ66 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ክርስቲያኖች ወደ ተራራ የሸሹት ለምንድን ነው? (ለ) እነሱ የወሰዱት እርምጃ ጥሩ ምሳሌ የሆነው በምን መንገድ ነው?
9 ደቀ መዛሙርቱ ከፖለቲካና ከወታደራዊ ውዝግቦች ሙሉ በሙሉ ገለልተኞች ነበሩ። በ66 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በይሁዳ የነበሩ አይሁዶች በቄሳር ላይ ዓመጹ። የሮማ ሠራዊት ወዲያውኑ ኢየሩሳሌምን ከበበ። በከተማዋ ውስጥ የነበሩ ክርስቲያኖች ምን አደረጉ? ኢየሱስ ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ የሰጣቸው ምክር ትዝ አላቸው። ሮማውያን ለጊዜው ወደኋላ ሲያፈገፍጉ ክርስቲያኖቹ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ፔላ ወደተባለ ተራራማ አካባቢ ሸሹ። (ሉቃስ 21:20-24) እነሱ የወሰዱት የገለልተኝነት አቋም ከእነሱ በኋላ ላሉት ታማኝ ክርስቲያኖች ጥሩ ምሳሌ ሆኖ አገልግሏል።
በመጨረሻው ዘመን ያሉ ገለልተኛ ክርስቲያኖች
10. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች በየትኛው ሥራ ተጠምደዋል? ለምንስ? (ለ) ከምን ነገርስ ገለልተኞች ናቸው?
10 አሁን ባለንበት የመጨረሻ ዘመን ውስጥ የጥንቶቹን ክርስቲያኖች አርዓያ በመከተል ጠንካራ የሆነ የገለልተኝነት አቋም የያዙ ሰዎች እንዳሉ ታሪክ ይመሠክራል? አዎን፣ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ዓይነት አቋም ወስደዋል። በዚህ የመጨረሻ ዘመን የይሖዋ ምሥክሮች ጽድቅ ወዳድ ለሆኑ ሰዎች ዘላቂ ሰላም፣ ብልጽግናና ደስታ ሊያመጣ የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ሲሰብኩ ቆይተዋል። (ማቴዎስ 24:14) ይሁንና በብሔራት መካከል ከሚነሱት ግጭቶች ጋር በተያያዘ ፍጹም ገለልተኞች ሆነው ኖረዋል።
11. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው የገለልተኝነት አቋም ቀሳውስት ከሚፈጽሟቸው ድርጊቶች ፈጽሞ ተቃራኒ የሆነው እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎች ሰዎች ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ የሚወስዱትን እርምጃ በተመለከተ ምን አቋም አላቸው?
11 ከዚህ በተቃራኒው ግን በዚህ ዓለም ሃይማኖቶች ውስጥ የሚገኙ ቀሳውስት በፖለቲካ ጉዳዮች በእጅጉ ተጠላልፈዋል። በአንዳንድ አገሮች ምርጫ በሚካሄድበት ጊዜ ተመራጮቹን በመደገፍ አሊያም በመቃወም ቅስቀሳ አካሂደዋል። እንዲያውም አንዳንድ ቀሳውስት የፖለቲካ ሥልጣን እስከ መያዝ ደርሰዋል። ሌሎቹ ደግሞ እነሱ የሚፈልጉት ፖሊሲ ሥራ ላይ እንዲውል በፖለቲከኞች ላይ ጫና አሳድረዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ግን በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ፈጽሞ ጣልቃ አይገቡም። በተጨማሪም ሌሎች ሰዎች የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆኑ፣ ለፖለቲካ ሥልጣን እንዳይወዳደሩም ሆነ ድምፅ እንዳይሰጡ ለማከላከል አይሞክሩም። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የዓለም ክፍል እንደማይሆኑ ተናግሯል፤ ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ፖለቲካ ውስጥ አይገቡም።
12. የዚህ ዓለም ሃይማኖቶች ገለልተኞች አለመሆናቸው ምን አስከትሏል?
12 ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ብሔራት በተደጋጋሚ ጊዜያት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል። በአንድ አገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ አንጃዎች እንኳ ሳይቀሩ እርስ በርስ ተፋጅተዋል። (ማቴዎስ 24:3, 6, 7) የሃይማኖት መሪዎቹ ሁልጊዜ ማለት ይቻላል፣ አንደኛውን ብሔር ወይም አንጃ በመቃወም ሌላውን የሚደግፉ ሲሆን ተከታዮቻቸውም ይህንኑ እንዲያደርጉ ይቀሰቅሳሉ። ይህ ምን ውጤት አስከትሏል? የአንድ ሃይማኖት አባላት የሆኑ ሰዎች በአገር ወይም በጎሳ ስለሚለያዩ ብቻ እርስ በርስ ይገዳደላሉ። ይህ ደግሞ የአምላክን ፈቃድ የሚጻረር ድርጊት ነው።—1 ዮሐንስ 3:10-12፤ 4:8, 20
13. የይሖዋ ምሥክሮችን ገለልተኝነት በተመለከተ ያሉት ማስረጃዎች ምን ያሳያሉ?
13 ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ከሁሉም ግጭቶች ገለልተኛ ሆነው ኖረዋል። የኅዳር 1, 1939 መጠበቂያ ግንብ “ከጌታ ጎን የተሰለፉ ሁሉ ብሔራት ከሚያደርጓቸው ውጊያዎች ገለልተኛ ይሆናሉ” ሲል ገልጾ ነበር። በሁሉም አገሮች ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ከዚህ አቋማቸው ፍንክች አይሉም። ሰዎችን የሚከፋፍሉት የዓለም ፖለቲካዎችም ሆኑ ጦርነቶች ዓለም አቀፍ የወንድማማች ኅብረታቸውን እንዲያናጉባቸው አይፈቅዱም። “ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጋሉ።” ገለልተኞች ስለሆኑ ጦርነትን አይማሩም።—ኢሳይያስ 2:3, 4፤ 2 ቆሮንቶስ 10:3, 4
14. የይሖዋ ምሥክሮች ከዓለም የተለዩ በመሆናቸው ምን ደርሶባቸዋል?
14 ገለልተኛ መሆናቸው ምን ውጤት አምጥቷል? ኢየሱስ “የዓለም አይደላችሁም፤ ዓለም የሚጠላችሁም ስለዚሁ ነው” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:19) በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ አገልጋዮች በመሆናቸው የተነሳ ለእስር ተዳርገዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት ክርስቲያኖች ላይ እንደደረሰው ሁሉ አንዳንዶች ተደብድበዋል አልፎ ተርፎም ተገድለዋል። ይህ የሆነው “የዚህ ዓለም አምላክ” የሆነው ሰይጣን የዓለም ክፍል ያልሆኑትን የይሖዋ አገልጋዮች ስለሚቃወም ነው።—2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ራእይ 12:12
15. (ሀ) ብሔራት በሙሉ ወዴት እያመሩ ነው? (ለ) ከዓለም የተለዩ መሆን አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው?
15 የዓለም ብሔራት በሙሉ በአርማጌዶን ወደሚደርስባቸው ጥፋት እያመሩ በመሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች የዚህ ዓለም ክፍል ባለመሆናቸው ደስተኞች ናቸው። (ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 16:14, 16፤ 19:11-21) ከዓለም የተለየን በመሆናችን ከዚህ ጥፋት እንድናለን። በምድር ዙሪያ የምንገኝ የይሖዋ ሕዝቦች በሙሉ አንድ ሆነን ከአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ጎን በታማኝነት እንቆማለን። እርግጥ ነው፣ የዓለም ክፍል ባለመሆናችን ሊፌዝብንና ስደት ሊደርስብን ይችላል። ይሁንና በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ይህ ክፉ ዓለም ለዘላለም ተጠራርጎ ስለሚጠፋ በቅርቡ ከዚህ ሁሉ እንገላገላለን። በሌላ በኩል ግን ይሖዋን የሚያገለግሉ ሁሉ በአምላክ መንግሥት በሚተዳደረው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም ይኖራሉ።—2 ጴጥሮስ 3:10-13፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17
የክለሳ ውይይት
• ኢየሱስ ‘የዓለም ክፍል አለመሆን’ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?
• የጥንቶቹ ክርስቲያኖች (ሀ) የዓለምን መንፈስ (ለ) ሰብዓዊ ገዥዎችን እና (ሐ) ግብር መክፈልን በተመለከተ ምን አመለካከት ነበራቸው?
• በዘመናችን ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋም እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው?
[በገጽ 165 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ እሱም ሆነ ተከታዮቹ ‘ከዓለም እንዳይደሉ’ ተናግሯል