ምዕራፍ 23
ኢየሱስ በቅፍርናሆም ታላላቅ ሥራዎችን አከናወነ
ማቴዎስ 8:14-17 ማርቆስ 1:21-34 ሉቃስ 4:31-41
ኢየሱስ ጋኔን አስወጣ
የጴጥሮስ አማት ተፈወሰች
ኢየሱስ አራት ደቀ መዛሙርቱን ይኸውም ጴጥሮስን፣ እንድርያስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ሰው አጥማጆች እንዲሆኑ ጋብዟቸዋል። ከዚያም በሰንበት ቀን ሁሉም በቅፍርናሆም ወደሚገኝ ምኩራብ ሄዱ። ኢየሱስ በምኩራቡ ውስጥ ማስተማር ጀመረ፤ እዚህም ባስተማረበት መንገድ ሕዝቡ ተገረሙ። ምክንያቱም የሚያስተምረው እንደ ጸሐፍት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ነው።
በዚህ የሰንበት ቀን ጋኔን የያዘው አንድ ሰው ምኩራቡ ውስጥ ተገኝቷል። ሰውየው እዚያው ምኩራቡ ውስጥ እንዲህ ብሎ በኃይል ጮኸ፦ “የናዝሬቱ ኢየሱስ፣ እኛ ከአንተ ጋር ምን ጉዳይ አለን? የመጣኸው ልታጠፋን ነው? ማን እንደሆንክ በሚገባ አውቃለሁ፤ አንተ የአምላክ ቅዱስ አገልጋይ ነህ!” ኢየሱስ ግን በሰውየው ላይ ያደረውን ጋኔን “ዝም በል፤ ከእሱም ውጣ!” ብሎ ገሠጸው።—ማርቆስ 1:24, 25
ርኩሱም መንፈስ ሰውየውን ጥሎ ካንፈራገጠው በኋላ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ሆኖም ሰውየውን “ምንም ሳይጎዳው ለቆት ወጣ።” (ሉቃስ 4:35) በምኩራቡ ውስጥ ያሉት ሰዎች በጣም ተገረሙ! “ይህ ምንድን ነው? . . . ርኩሳን መናፍስትን እንኳ ሳይቀር በሥልጣን ያዛል፤ እነሱም ይታዘዙለታል” ተባባሉ። (ማርቆስ 1:27) ስለዚህ አስገራሚ ክንውን የሚገልጽ ወሬ በመላዋ ገሊላ ተዳረሰ።
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከምኩራቡ ወጥተው ወደ ስምዖን (ወይም ጴጥሮስ) ቤት ሄዱ። እዚያም የጴጥሮስ አማት ኃይለኛ ትኩሳት ይዟት በጣም ታምማ አገኟት። በመሆኑም እንዲረዳት ኢየሱስን ለመኑት። ስለዚህ ኢየሱስ ወደ እሷ ሄደና እጇን ይዞ አስነሳት። ወዲያው ተፈወሰች፤ ከዚያም ኢየሱስንና ከእሱ ጋር ያሉ ደቀ መዛሙርቱን ማገልገል ምናልባትም ለእነሱ ምግብ ማዘጋጀት ጀመረች!
ፀሐይ ልትጠልቅ አካባቢ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ሰዎች ሕመምተኞቻቸውን እየያዙ ወደ ጴጥሮስ ቤት መጉረፍ ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ የከተማው ሰው ሁሉ ጴጥሮስ ደጃፍ ላይ ተሰበሰበ! ሰዎቹ የመጡት ለምንድን ነው? ፈውስ ፈልገው ነው። “ሰዎች በተለያየ በሽታ የተያዙ ሕመምተኞቻቸውን ወደ እሱ አመጡ። እሱም በእያንዳንዳቸው ላይ እጁን በመጫን ፈወሳቸው።” (ሉቃስ 4:40) በሽታቸው ምንም ይሁን ምን ኢየሱስ በትንቢት በተነገረው መሠረት የታመሙትን ሁሉ ፈወሰ። (ኢሳይያስ 53:4) አጋንንትን እንኳ ከሰዎች አስወጣ። አጋንንቱ፣ ሰዎቹን ለቀው ሲወጡ “አንተ የአምላክ ልጅ ነህ” እያሉ ይጮኻሉ። (ሉቃስ 4:41) ኢየሱስ ግን የገሠጻቸው ሲሆን ከዚያ በኋላ እንዳይናገሩ ከለከላቸው። አጋንንቱ እሱ፣ ክርስቶስ እንደሆነ ያውቃሉ፤ ሆኖም እውነተኛውን አምላክ የሚያገለግሉ እንዲመስሉ አልፈለገም።