የአንባብያን ጥያቄዎች
በማቴዎስ 17:20 ዘገባ መሠረት ሐዋርያቱ የታመመውን ልጅ መፈወስ ያቃታቸው ‘እምነት ስላነሳቸው’ ነው። ሆኖም ማርቆስ 9:29 ላይ መፈወስ አለመቻላቸው ከጸሎት አስፈላጊነት ጋር ተያይዞ ተጠቅሷል። በእነዚህ የተለያዩ የወንጌል ትረካዎች ላይ የተለያዩ ምክንያቶች የተሰጡት ለምንድን ነው?
እንደ እውነቱ ከሆነ ሁለቱ ጥቅሶች እርስ በርሳቸው የሚደጋገፉ እንጂ የሚጋጩ አይደሉም። በመጀመሪያ ማቴዎስ 17:14-20ን እንመልከት። አንድ ሰው ወንድ ልጁ የሚጥል በሽታ እንደያዘውና የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ልጁን ሊያድኑት እንዳልቻሉ ይናገራል። ከዚያም ኢየሱስ ልጁን ያሰቃይ የነበረውን ጋኔን ለቆት እንዲወጣ በማድረግ ያድነዋል። ደቀ መዛሙርቱ እነርሱ ጋኔኑን ሊያወጡ ያልቻሉበትን ምክንያት ጠየቁት። በማቴዎስ ዘገባ መሠረት ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ:- “ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፣ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህን ተራራ:- ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም።”—በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
አሁን ደግሞ ተጨማሪ ዝርዝር ሐሳቦች የያዘውን ማርቆስ 9:14-29ን እንመልከት። ለምሳሌ ያህል ማርቆስ 9:17 ልጁ የያዘው የሚጥል በሽታ ክፉ መንፈስ ስላደረበት እንደሆነ ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስ በሌሎች ሥፍራዎች ላይ ኢየሱስ የሚጥል በሽታ የያዛቸውን እና አጋንንት ያደረባቸውን ሰዎች ማዳኑን እንደሚናገር ልብ ማለት ተገቢ ነው። (ማቴዎስ 4:24) ስለዚህ ልጁ ይወድቅ የነበረው ክፉ መንፈስ ስላደረበት በመሆኑ ይህ ሁኔታ ከወትሮው ለየት ያለ ነበር። ዶክተር ሉቃስም ይህን ሐቅ አረጋግጧል። (ሉቃስ 9:39፤ ቆላስይስ 4:14) አሁን በማርቆስ 9:18 ላይ የሚገኘውን “[ጋኔኑ] በያዘውም ሥፍራ ሁሉ” የሚለውን ሐረግ ልብ በሉ። ስለዚህ ጋኔኑ ልጁን ያሰቃየው የነበረው አልፎ አልፎ እንጂ ሁልጊዜ አልነበረም። ቢሆንም ደቀ መዛሙርቱ ጋኔኑን በማስወጣት ልጁን ሊያድኑት አልቻሉም። ሊያድኑ ያልቻሉት ለምን እንደሆነ በጠየቁት ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው:- “ይህ ወገን በጸሎትና በጦም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም።”
ሆኖም የማርቆስን ዘገባ በጥንቃቄ በማንበብ ማቴዎስ ከመዘገበው ጋር ፈጽሞ እንደማይጋጭ ማየት ይቻላል። በማርቆስ 9:19 ላይ ኢየሱስ ያ ትውልድ እምነት የለሽ እንደነበረ ተናግሯል። በቁጥር 23 ላይ ደግሞ ለልጁ አባት “ለሚያምን ሁሉ ይቻላል” ብሏል። ስለዚህ የማርቆስም ትረካ የእምነትን አስፈላጊነት ያጎላል። ልዩነት ያለ ያስመሰለው ማርቆስ በቁጥር 29 ላይ ማቴዎስም ሆነ ሉቃስ ያልጠቀሱትን ኢየሱስ ስለ ጸሎት የተናገረውን ቃል ጨምሮ መጻፉ ነው።
ታዲያ ምን ለማለት እንችላለን? በሌሎች ጊዜያት 12ቱ ሐዋርያትም ሆኑ 70ዎቹ ደቀ መዛሙርት ክፉ መናፍስትን ማውጣት ችለዋል። (ማርቆስ 3:15፤ 6:13፤ ሉቃስ 10:17) ሆኖም በዚህ ወቅት ደቀ መዛሙርቱ ጋኔኑን ማውጣት አልቻሉም። ለምን? በተለያዩ ወንጌሎች ውስጥ የሰፈሩትን ዝርዝር ሐሳቦች በማገናኘት ያንን ጋኔን ለማውጣት የሚያስችል በቂ ዝግጅት አልነበራቸውም ብለን ለመደምደም እንችላለን። አጋንንት የተለያየ ዓይነት ባሕርያት፣ ፍላጎቶችና ሌላው ቀርቶ የተለያየ ዓይነት ችሎታ ሊኖራቸው ስለሚችል የችግሩ አንዱ መንስዔ ልጁን የያዘው አጋንንት ዓይነት ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ያ ጋኔን የተለየ ዓይነት በመሆኑ ምክንያት ጠንካራ እምነትና ብዙ ጸሎት አስፈልጎ ሊሆን ይችላል። እርግጥ፣ ኢየሱስ ጠንካራ እምነት ነበረው። ጸሎት ሰሚ የሆነው የአምላክም ሙሉ ድጋፍ ነበረው። (መዝሙር 65:2) ኢየሱስ ልጁን የማዳን ችሎታ ስለነበረው አጋንንቱን በማውጣት አድኖታል።