ምዕራፍ 53
የተፈጥሮ ኃይሎችን መቆጣጠር የሚችል ገዢ
ማቴዎስ 14:22-36 ማርቆስ 6:45-56 ዮሐንስ 6:14-25
ሕዝቡ ኢየሱስን ሊያነግሡት ፈለጉ
ኢየሱስ በውኃ ላይ ተራመደ፤ ነፋሱንም ጸጥ አሰኘ
ኢየሱስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በተአምር መመገብ መቻሉ ሕዝቡን በጣም አስደነቀ። ሕዝቡ “ወደ ዓለም እንደሚመጣ ትንቢት የተነገረለት ነቢይ [መሲሑ] በእርግጥ ይህ ነው” ብለው ደመደሙ፤ እንዲሁም ጥሩ ገዢ እንደሚሆን እርግጠኞች ሆኑ። (ዮሐንስ 6:14፤ ዘዳግም 18:18) ስለዚህ ኢየሱስን ይዘው ሊያነግሡት አሰቡ።
ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሰዎቹ ምን እንዳሰቡ አወቀ። በመሆኑም ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን ጀልባቸው ላይ እንዲሳፈሩ አዘዛቸው። የሚጓዙት ወዴት ይሆን? የትኛውን አቅጣጫስ ተከተሉ? የሚሄዱት በቤተሳይዳ በኩል አድርገው ወደ ቅፍርናሆም ነው። ኢየሱስ ግን በዚያ ምሽት ብቻውን ለመጸለይ ወደ ተራራ ወጣ።
ጎህ ከመቅደዱ በፊት ኢየሱስ በጨረቃዋ ብርሃን ከሩቅ ጀልባዋን ተመለከታት። ኃይለኛ ነፋስ ባሕሩን እያናወጠው ነው፤ ሐዋርያቱም ‘ነፋሱ ከፊት ለፊታቸው እየነፈሰ በመሆኑ ለመቅዘፍ ሲታገሉ’ አያቸው። (ማርቆስ 6:48) ኢየሱስ ከተራራው ወረደና ሞገዱ በሚያናውጠው ባሕር ላይ እየተራመደ ወደ እነሱ መሄድ ጀመረ። በዚህ ወቅት ደቀ መዛሙርቱ “አምስት ወይም ስድስት ኪሎ ሜትር ገደማ” ቀዝፈዋል። (ዮሐንስ 6:19) ደቀ መዛሙርቱ፣ ኢየሱስ አልፏቸው የሚሄድ መሰላቸው፤ በዚህ ጊዜ በፍርሃት ተውጠው “ምትሃት ነው!” ብለው ጮኹ።—ማርቆስ 6:49
ኢየሱስም “አይዟችሁ! እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” በማለት አረጋጋቸው። ጴጥሮስ መልሶ “ጌታ ሆይ፣ አንተ ከሆንክ በውኃው ላይ እየተራመድኩ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” አለ። ኢየሱስም “ና!” አለው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ከጀልባው ላይ ወርዶ በውኃው ላይ እየተራመደ ወደ ኢየሱስ አመራ። ሆኖም ጴጥሮስ አውሎ ነፋሱን ሲያይ ስለፈራ መስጠም ጀመረ። “ጌታ ሆይ፣ አድነኝ!” ብሎ ጮኸ። ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ! ለምን ተጠራጠርክ?” አለው።—ማቴዎስ 14:27-31
ጴጥሮስና ኢየሱስ ጀልባው ላይ ከወጡ በኋላ አውሎ ነፋሱ ቆመ። ደቀ መዛሙርቱም በአድናቆት ስሜት ተዋጡ፤ ይሁንና ይህ ሊያስደንቃቸው ይገባል? “የዳቦውን ተአምር ትርጉም” ይኸውም ኢየሱስ ከጥቂት ሰዓታት በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በመመገብ የፈጸመውን ተአምር ቢያስተውሉ ኖሮ በውኃ ላይ መራመድ መቻሉና ነፋሱን ጸጥ ማሰኘቱ ይህን ያህል ባላስደነቃቸው ነበር። በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ “አንተ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነህ” ብለው ሰገዱለት።—ማርቆስ 6:52፤ ማቴዎስ 14:33
ብዙም ሳይቆይ ከቅፍርናሆም በስተ ደቡብ ወደምትገኘው ጌንሴሬጥ የተባለች ውብና ፍሬያማ ምድር ደረሱ። በዚያም ጀልባዋን አቁመው ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወጡ። ሕዝቡ ኢየሱስን ስላወቁት በዚያ አገርና በአካባቢው ያሉ የታመሙ ሰዎችን ይዘው ወደ እሱ መጡ። ሕመምተኞቹ የኢየሱስን ልብስ ዘርፍ ሲነኩ ብቻ እንኳ ሙሉ በሙሉ ጤነኞች ሆኑ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ተአምራዊ በሆነ መንገድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲመገቡ በቦታው የነበረው ሕዝብ፣ ኢየሱስ አካባቢውን ለቆ እንደሄደ ተገነዘበ። ስለዚህ ከጥብርያዶስ የተነሱ ትናንሽ ጀልባዎች ወደዚህ አካባቢ ሲደርሱ ሰዎቹ ተሳፈሩና ኢየሱስን ለማግኘት ወደ ቅፍርናሆም መጡ። ኢየሱስን ሲያገኙትም “ረቢ፣ መቼ ወደዚህ መጣህ?” ብለው ጠየቁት። (ዮሐንስ 6:25) ኢየሱስ ግን እነዚህን ሰዎች ወቀሳቸው፤ ቀጥሎ እንደምንመለከተው ይህን ማድረጉ ተገቢ ነው።