የአንባብያን ጥያቄዎች
◼ 2 ጴጥሮስ 1:19 በአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ውስጥ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በተለየ መንገድ የተተረጎመው ለምንድንነው?
ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ የተጻፈው የአምላክ ቃል ያለውን ትልቅ ዋጋ ጠበቅ አድርጎ ሲያስገነዝብ እንዲህ ብሎአል፦ “በዚህ ምክንያት የትንቢቱ ቃል በይበልጥ እርግጠኛ ተደርጎልናል። እናንተም ቀኑ እስኪነጋና የቀን ኮከብ እስኪወጣ ድረስ በጨለማ ስፍራ የሚያበራን መብራት እንደምትይዙ አድርጋችሁ [የትንቢቱን ቃል] በልባችሁ ውስጥ በጥሞና በመከታተላችሁ መልካም ታደርጋላችሁ።”—2 ጴጥሮስ 1:19 አዓት
“ቀኑ እስኪነጋና የቀን ኮከብ እስኪወጣ ድረስ” የሚለው ሐረግ በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ውስጥ በነጠላ ሰረዝ (ኮማ) የተለያየ መሆኑን ማስተዋል ትችላላችሁ። አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንደዚያ አያደርጉም።
ለምሳሌ ያህል ዶክተር ጀምስ ሞፋት የዚህን ቁጥር የመጨረሻ ክፍል እንዲህ በማለት ተርጉመዋል። “. . . ቀኑ እስኪነጋና በልባችሁ ውስጥ የቀን ኮከብ እስኪወጣ ድረስ በጨለማ ሥፍራ እንዳለ መብራት ያበራል።” እንደዚህ ያለው አተረጓጎም የቀኑ ኮከብ በአማኞች ልብ ውስጥ እንደሚወጣና ይህም የሚሆነው አንድ ዓይነት መንፈሣዊ ብርሃን ሲያገኙ እንደሆነ የሚገልጽ ያስመስለዋል።
ይሁን እንጂ ገና ጥንት በሙሴ ዘመን እንኳን ’ከያዕቆብ ቤት ኮከብ እንደሚወጣ’ የሚያመለክት ፍንጭ ነበር። (ዘኁልቁ 24:17፤ ከመዝሙር 89:34-37 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ “እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፤ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ” ብሎአል።—ራዕይ 22:16
የንጋት ኮከቡን ወይም የጠዋት ኮከቡን ማንነት በዚህ ዓይነት መረዳታችን ሐዋርያው ጴጥሮስ ሊገልጽ ከፈለገው አጠቃላይ ሐሣብ ጋር ይስማማል። ጴጥሮስ ይህን ቃል ከመናገሩ ቀደም ብሎ ከ30 ዓመታት በፊት ስለተመለከተው የኢየሱስ ክብራማ መለወጥ ጠቅሶ ነበር። (ማቴዎስ 16:28 እስከ 17:9) ይህ ደማቅ ራዕይ ኢየሱስ በመንግሥቱ የሚመጣበትን ወይም በመንግሥቱ የሚከብርበትን ጊዜ የሚያመለክት ነበር። ጴጥሮስ የተመለከተው ነገር የአምላክን ቃል አስፈላጊነት አጉልቶ ገልጾአል። የዘመናችን ክርስቲያኖችም በተመሳሳይ ይህን ትንቢታዊ ቃል በጥሞና መከታተል ይኖርባቸዋል።
ጥንትም ሆነ ዛሬ የሰው ልጆች ልብ በአጠቃላይ በጨለማ ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም የእውነተኛ ክርስቲያኖች ልብ ግን በጨለማ ውስጥ መሆን የለበትም። ጨለማ ሊሆን ይችል በነበረው ልባቸው ውስጥ የሚያበራ መብራት እንዳላቸው ያህል ነው። ክርስቲያኖች ብርሃን ሰጪውን ትንቢታዊ ቃል በትኩረት ሲከታተሉ የአዲሱን ቀን ንጋት ነቅተው ሊጠብቁ እንደሚችሉ ጴጥሮስ ያውቅ ነበር። ይህ አዲስ ቀን “የንጋት ኮከብ” ወይም “የሚያበራው የንጋት ኮከብ” በንጉሣዊ ሥልጣን የሚገዛበት ጊዜ ይሆናል።
ኢ ደብልዩ ቡሊንገር ስለ 2 ጴጥሮስ 1:19 የሚከተለውን መጻፋቸውን ማስተዋል ይጠቅማል። “እዚህ ላይ የሚያበራው መብራት ትንቢት ሲሆን የንጋት ኮከቡና የቀኑ ንጋት ክርስቶስና የክርስቶስ መገለጥ ስለሆነ ቅንፍ መኖር ነበረበት። ክርስቶስ በልባችን እስኪገለጥ ድረስ የትንቢቱን ቃል አጥብቀን እንድንከታተል የሚያሳስበን ትርጉም ያለው ቃል እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። ከዚህ ይልቅ የትንቢቱ ቃል በክርስቶስ መገለጥ ወይም “የንጋት ኮከብ” ተብሎ የተጠራው በመውጣቱ እስኪፈጸም ድረስ በልባችን ጠንቅቀን እንድንጠብቀው የተሰጠን ምክር ነው።” መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቀምባቸው የአነጋገር ዘይቤዎች 1898
በዚህ መሠረት ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በ2 ጴጥሮስ 1:19 ላይ ቅንፍ ያስገባሉ።a የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም በግሪክኛው በኩረ ጽሑፍ የሚገኘውን የአቀራረብ ቅደም ተከተል ይጠቀማል። ይሁን እንጂ “ቀኑ እስኪነጋና የንጋት ኮከብ እስኪወጣ” የሚሉትን ሐረጎች በልባችሁ ውስጥ በጨለማ ሥፍራ እንደሚያበራ መብራት ቃሉን በጥሞና እንድንከታተል ከተሰጠው ምክር ለመለየት በነጠላ ሰረዝ (ኮማ) ተጠቅሞአል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ለምሳሌ ያህል ዘ ኒው ሰንቸሪ ኒው ተስታመንት (የ1904 እትም) ዘ ኢምፋቲክ ዳየግለት (የ1942 እትም) ኮንኮርዳንት ሊተራል ኒው ተስታመንት (1976) ተመልከት።