የአምላክን ትንቢታዊ ቃል በትኩረት ተከታተል
“ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ . . . ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ [“በትኩረት በመከታተላችሁ፣” NW ] መልካም ታደርጋላችሁ።”—2 ጴጥሮስ 1:19
1, 2. ሐሰተኛ መሲሖችን በሚመለከት ምን ምሳሌ መጥቀስ ትችላለህ?
ለብዙ መቶ ዓመታት ሐሰተኛ መሲሖች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለመተንበይ ሙከራ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በአምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ራሱን ሙሴ ብሎ ይጠራ የነበረ አንድ ሰው በቀርጤስ ደሴት የነበሩትን አይሁድ፣ ከጭቆና ነፃ የሚያወጣቸው መሲሕ እርሱ እንደሆነ አሳመናቸው። ነጻ ትወጣላችሁ የተባሉበት ቀን ሲደርስ እርሱን ተከትለው የሜዲትራንያንን ባሕር ቁልቁል ወደሚያዩበት ከፍተኛ ቦታ ላይ ወጡ። ራሳቸውን ወደ ባሕሩ ቢወረውሩ ባሕሩ ለሁለት እንደሚከፈልላቸው ነገራቸው። ራሳቸውን ወደ ውኃው ከወረወሩት መካከል ብዙዎች በዚያው ሰጥመው ቀሩ፤ ሐሰተኛውም መሲሕ ደብዛውን አጠፋ።
2 በ12ኛው መቶ ዘመን አንድ “መሲሕ” በየመን አገር ብቅ አለ። ከሊፋው ወይም የአገሩ ገዥ መሲሕነቱን የሚያረጋግጥ አንድ ምልክት እንዲያሳይ ጠየቀው። “መሲሑም” ከሊፋው ራሱን ቢያስቆርጠው ወዲያው እንደሚነሳና ይህም ለመሲሕነቱ ምልክት እንደሚሆን ተናገረ። ከሊፋው በእቅዱ ተስማማና አስቆረጠው። ይህም “የመሲሑ” ፍጻሜ ሆነ።
3. እውነተኛው መሲሕ ማን ነው? አገልግሎቱስ ምን አረጋግጧል?
3 ሐሰተኛ መሲሖችም ሆኑ ትንበያዎቻቸው ምንም አልተሳካላቸውም። የአምላክን ትንቢታዊ ቃል በትኩረት በመከታተል ግን ለብስጭት ፈጽሞ አንዳረግም። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እውነተኛ መሲሕ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ለምሳሌ ያህል የወንጌል ጸሐፊው ማቴዎስ የኢሳይያስን ትንቢት በመጥቀስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፣ የባሕር መንገድ፣ በዮርዳኖስ ማዶ፣ የአሕዛብ ገሊላ፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፣ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ። ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ:- መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር።” (ማቴዎስ 4:15-17፤ ኢሳይያስ 9:1, 2) ይህ “ታላቅ ብርሃን” ኢየሱስ ሲሆን ያከናወነውም አገልግሎት ሙሴ ትንቢት የተናገረለት ነቢይ እርሱ መሆኑን አረጋግጧል። ኢየሱስን ለማዳመጥ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሁሉ እንደሚጠፉ ተነግሯል።—ዘዳግም 18:18, 19፤ ሥራ 3:22, 23
4. ኢየሱስ ኢሳይያስ 53:12 ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደረገው እንዴት ነው?
4 በተጨማሪም ኢየሱስ በኢሳይያስ 53:12 ላይ የሚገኘውን የትንቢት ቃል ፈጽሟል:- “ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፣ ከዓመፀኞችም ጋር ተቆጥሮአልና፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፣ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።” ኢየሱስ ብዙም ሳይቆይ ሰብዓዊ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ እንደሚሰጥ ያውቅ ስለነበር የደቀ መዛሙርቱን እምነት አጠንክሮላቸዋል። (ማርቆስ 10:45) ይህን ካደረገባቸው መንገዶች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው በተአምራዊ መንገድ መለወጡ ነው።
የኢየሱስ ተአምራዊ መለወጥ እምነት ይገነባል
5. የኢየሱስን ተአምራዊ ለውጥ በራስህ አባባል እንዴት ትገልጸዋለህ?
5 የኢየሱስ ተአምራዊ ለውጥ ትንቢታዊ ክንውን ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ . . . እውነት እላችኋለሁ፣ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።” (ማቴዎስ 16:27, 28) ታዲያ ከሐዋርያቱ መካከል ኢየሱስ በመንግሥቱ ሲመጣ የተመለከቱ ነበሩ? ማቴዎስ 17:1-7 እንዲህ ይላል:- “ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ።” እንዴት ያለ የሚያስገርም ክንውን ነው! “ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፣ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፣ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።” እንዲሁም “ብሩህ ደመና ጋረዳቸው።” አምላክ ራሱም “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” ብሎ ሲናገር ሰሙ። “ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር። ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና:- ተነሡ አትፍሩም አላቸው።”
6. (ሀ) ኢየሱስ ተአምራዊ ለውጡን ራእይ ብሎ የጠራው ለምንድን ነው? (ለ) መለወጡ የምን ነገር ነጸብራቅ ነበር?
6 ይህ ዕጹብ ድንቅ ክንውን የተፈጸመው ኢየሱስና ሦስቱ ሐዋርያት ሌሊቱን ባሳለፉበት ከሔርሞን ተራራ ሸንተረሮች በአንዱ ላይ ሳይሆን አይቀርም። የኢየሱስ ተአምራዊ ለውጥ የታየው ሌሊት እንደነበረ አያጠራጥርም። ይህም ይበልጥ አንጸባራቂና አስደናቂ እንዲሆን አድርጎታል። ኢየሱስ ይህን ምልክት ራእይ ብሎ የጠራበት አንዱ ምክንያት ከሞቱ ብዙ ጊዜ ሆኗቸው የነበሩት ሙሴና ኤልያስ በዚያ ቦታ የተገኙት ቃል በቃል ባለመሆኑ ነው። በዚያ ቦታ በእውን ተገኝቶ የነበረው ክርስቶስ ብቻ ነው። (ማቴዎስ 17:8, 9 NW ) ኢየሱስ እንዲህ ባለ አንጸባራቂ ሁኔታ መለወጡ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ኢየሱስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ በሚገኝበት ጊዜ የሚኖረውን ግርማ በጥቂቱ እንዲመለከቱ አስችሏቸዋል። ሙሴና ኤልያስ የኢየሱስን ቅቡዓን ተባባሪ የመንግሥት ወራሾች የሚያመለክቱ ሲሆን ራእዩ ኢየሱስ ስለ መንግሥቱና ስለ ወደፊት ንግሥናው የሰጠውን ምሥክርነት አጠናክሮታል።
7. ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ተአምራዊ መለወጥ የነበረው ትዝታ ሕያው እንደነበር እንዴት እናውቃለን?
7 የኢየሱስ ተአምራዊ ለውጥ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ግንባር ቀደም የሥራ ድርሻ የሚኖራቸውን የሦስቱ ሐዋርያት እምነት ለማጠንከር ረድቷል። ያበራው የኢየሱስ ፊት፣ ነጭ ሆኖ ያንጸባረቀው ልብሱና ኢየሱስ ተወዳጅ ልጁ እንደሆነና እርሱንም መስማት እንዳለባቸው ሲናገር የተሰማው የአምላክ ድምፅ የታቀደላቸውን ዓላማ በተሳካ ሁኔታ አከናውነዋል። ይሁን እንጂ ሐዋርያቱ ኢየሱስ እስኪነሣ ድረስ ስለዚህ ራእይ ለማንም መናገር አልነበረባቸውም። ይህ ራእይ ከ32 ዓመታት በኋላ እንኳን በጴጥሮስ አእምሮ ውስጥ ገና ትናንት እንደተፈጸመ ነገር ሕያው ሆኖ ተስሎ ነበር። ጴጥሮስ ስለ ራእዩና ራእዩ ስላለው ትርጉም በመግለጽ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ። ከገናናው ክብር:- በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ያ ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን።”—2 ጴጥሮስ 1:16-18
8. (ሀ) አምላክ ስለ ልጁ የተናገረው ነገር በምን ላይ ያተኮረ ነበር? (ለ) ኢየሱስ በተአምር በተለወጠ ጊዜ የታየው ደመና ምን ያመለክታል?
8 በጣም አስፈላጊ የነበረው “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚለው አምላክ የተናገረው ነገር ነበር። ይህ መግለጫ ፍጥረት ሙሉ በሙሉ ሊታዘዝለት የሚገባው አምላክ የሾመው ንጉሥ ኢየሱስ መሆኑን ያረጋግጣል። በዚህ ጊዜ የጋረዳቸው ዳመና የዚህ ትንቢታዊ ራእይ ፍጻሜ በዓይን የማይታይ መሆኑን የሚያመለክት ነበር። ኢየሱስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ በማይታይ ሁኔታ የመገኘቱን ‘ምልክት’ በሚገነዘቡ ሰዎች የማስተዋል ዓይን ብቻ የሚስተዋል ይሆናል። (ማቴዎስ 24:3) እንዲያውም ኢየሱስ የሰው ልጅ ከሙታን ከመነሣቱ በፊት ራእዩን ለማንም እንዳይናገሩ ሐዋርያቱን ማስጠንቀቁ የሚከብረውና ግርማ የሚቀዳጀው ሞቶ ከተነሣ በኋላ እንደሆነ ያመለክታል።
9. የኢየሱስ ተአምራዊ መለወጥ እምነታችንን የሚያጠናክር ሊሆን የሚገባው ምንድን ነው?
9 ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ተአምራዊ መለወጥ ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ፣ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ። ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጕም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።” (2 ጴጥሮስ 1:19-21) የኢየሱስ በተአምር መለወጥ የአምላክን ትንቢታዊ ቃል አስተማማኝነት በተጨባጭ የሚያስረዳ ነው። በትኩረት መከታተል ያለብን ይህንን ቃል እንጂ መለኮታዊ ድጋፍ ወይም ተቀባይነት የሌለውን “በብልሃት የተፈጠረውን ተረት” አይደለም። የኢየሱስ በተአምር መለወጥ በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክር ሊሆን ይገባዋል። ምክንያቱም በዚህ ራእይ ውስጥ በትንሹ የታየው የኢየሱስ ክብርና የመንግሥቱ ኃይል ዛሬ እውን ሆኗል። አዎን፣ በዛሬው ጊዜ ክርስቶስ ኃያል ሰማያዊ ንጉሥ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሊታበል የማይችል ማስረጃ አለን።
የንጋት ኮከብ የሚወጣው እንዴት ነው?
10. ጴጥሮስ የጠቀሰው “የንጋት ኮከብ” ማን ወይም ምንድን ነው? እንደዚህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
10 ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ፣ ሰው በጨለማ ስፍራ የሚበራን መብራት እንደሚጠነቀቅ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ።” ይህ “የንጋት ኮከብ” ማን ወይም ምንድን ነው? “የንጋት ኮከብ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው በአንድ ቦታ ላይ ብቻ ሲሆን ‘ከአጥቢያ ኮከብ’ ጋር ተመሳሳይ ነው። ራእይ 22:16 [NW ] ኢየሱስ ክርስቶስን “የሚያበራ አጥቢያ ኮከብ” ብሎ ይጠራዋል። በዓመቱ አንዳንድ ወቅቶች ላይ በስተ ምሥራቅ በኩል መጨረሻ ብቅ የሚሉት ከዋክብት እነዚህ ናቸው። ጀምበር ከመውጣቷ በፊት የሚታዩ በመሆናቸው አዲስ ቀን መጥባቱን ያበስራሉ። ጴጥሮስ “የንጋት ኮከብ” የሚለውን ቃል የተጠቀመው ንጉሣዊ ሥልጣን የተቀበለውን ኢየሱስን ለማመልከት ነው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ምድራችንን ጨምሮ በመላው አጽናፈ ዓለም ላይ ወጥቷል! መሲሐዊ የንጋት ኮከብ በመሆን ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች አዲስ ቀን፣ አዲስ ዘመን መጥባቱን ያበስራል።
11. (ሀ) ሁለተኛ 2 ጴጥሮስ 1:19 “የንጋት ኮከብ” የሚወጣው ቃል በቃል በሰው ልብ ውስጥ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ሁለተኛ 2 ጴጥሮስ 1:19ን እንዴት ትገልጸዋለህ?
11 ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በ2 ጴጥሮስ 1:19 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የሐዋርያው ጴጥሮስ ቃላት የሚያመለክቱት የሰዎችን ልብ ነው የሚል ሐሳብ ያስተላልፋሉ። የአንድ ሙሉ ሰው ልብ ከ250 እስከ 330 ግራም ይመዝናል። ታዲያ አሁን ሞት የማይደፍረው ባለ ግርማ በሰማይ የሚኖረው መንፈሳዊ ፍጡር ኢየሱስ ክርስቶስ በዚች አነስተኛ የሰው ብልት ውስጥ ሊወጣ የሚችለው እንዴት ነው? (1 ጢሞቴዎስ 6:16) እርግጥ፣ የአምላክን ትንቢታዊ ቃል በትኩረት የምንከታተለው በልባችን ስለሆነ ምሳሌያዊው ልባችንም በጉዳዩ ውስጥ ቦታ አለው። ይሁን እንጂ ልብ ብለህ ከተመለከትህ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በ2 ጴጥሮስ 1:19 ላይ “ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ እስኪወጣ ድረስ” የሚለውን ለብቻው የተቀመጠ ሐረግ “በልባችሁ” ከሚለው ቃል ለመለየት ነጠላ ሰረዝ ተጠቅሟል። ይህ ጥቅስ እንደሚከተለው ተብሎ ሊገለጽ ይችላል:- ‘ከእነርሱ ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ እናንተም ይህን ቃል ምድር እስኪጠባና የንጋት ኮከብ እስኪወጣ ድረስ፣ በጨለማ ስፍራ ማለትም በልባችሁ ውስጥ እንዳለ መብራት በትኩረት በመከታተላችሁ መልካም ታደርጋላችሁ።’
12. በጥቅሉ ሲታይ የሰው ልጆች ልብ ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል? ይሁን እንጂ የእውነተኛ ክርስቲያኖች ሁኔታ ምን ይመስላል?
12 በጥቅሉ ሲታይ ኃጢአተኛ የሆነው የሰው ዘር ምሳሌያዊ ልብ የሚገኝበት ሁኔታ ምን ይመስላል? ልባቸው በመንፈሳዊ ጨለማ ተውጧል! ይሁን እንጂ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሆንን በጨለማ ይዋጥ በነበረው ልባችን ውስጥ ብርሃን የበራልን ያህል ነው። በጴጥሮስ ቃላት ውስጥ እንደተገለጸው እውነተኛ ክርስቲያኖች ንቁ ሆነው እንዲቀጥሉና አዲሱ ቀን እስኪጠባ ድረስ በብርሃን እንዲመላለሱ የሚረዳቸው ብርሃን ሰጪ የሆነውን የአምላክ ትንቢታዊ ቃል መከታተላቸው ነው። የንጋት ኮከብ በሰዎች ልብ ውስጥ ሳይሆን በመላው ፍጥረት ፊት መውጣቱን እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል።
13. (ሀ) የንጋት ኮከብ እንደወጣ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ክርስቲያኖች ኢየሱስ በዚህ ዘመን እንደሚኖሩ የተናገራቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች በጽናት መቋቋም የሚችሉት ለምንድን ነው?
13 ዛሬ የንጋት ኮከብ ወጥቷል! ኢየሱስ ስለመገኘቱ የተናገረውን ታላቅ ትንቢት በትኩረት በመከታተል ስለዚህ ጉዳይ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ዛሬ በሚካሄዱት አስፈሪ ጦርነቶች፣ በረሃቡ፣ በምድር መንቀጥቀጡና በዓለም ዙሪያ በሚካሄደው ስብከት አማካኝነት የዚህን ትንቢት ፍጻሜ እያየን ነው። (ማቴዎስ 24:3-14) ኢየሱስ የተነበያቸው ነገሮች እኛን ክርስቲያኖችንም የሚነኩ ቢሆኑም ሰላምና ደስተኛ ልብ ኖሮን ልንጸና እንችላለን። ለምን? የአምላክን ትንቢታዊ ቃል በትኩረት ስለምንከታተልና ወደፊት ይመጣል ብሎ ቃል በገባው ተስፋ ላይ እምነት ስላለን ነው። ወደ ‘ፍጻሜው ዘመን’ እጅግ ጠልቀን ስለገባን ወደተሻለው ዘመን አፋፍ እንደተጠጋን እናውቃለን። (ዳንኤል 12:4) ዓለም በኢሳይያስ 60:2 ላይ በተተነበየው መውጫው የማይታወቅ አስጨናቂ ጊዜ ላይ ይገኛል። “እነሆ፣ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል።” ታዲያ አንድ ሰው ከዚህ አስፈሪ ጨለማ የሚያወጣውን መንገድ ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነው? ጊዜው ከማለቁ በፊት ዛሬውኑ ራሱን ዝቅ አድርጎ የአምላክን ትንቢታዊ ቃል በትኩረት መከታተል ይኖርበታል። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ሁሉ የሕይወትና የብርሃን ምንጭ ወደ ሆነው ወደ ይሖዋ አምላክ ዞር ማለት ይኖርባቸዋል። (መዝሙር 36:9፤ ሥራ 17:28) ማንኛውም ሰው እውነተኛ የእውቀት ብርሃን ሊያገኝና አምላክ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች የጠበቀውን አስደናቂ ሕይወት የማግኘት ተስፋ ሊኖረው የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው።—ራእይ 21:1-5
‘ብርሃን ወደ ዓለም መጥቷል’
14. መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርላቸውን ድንቅ ትንቢቶች ፍጻሜ ለማየት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
14 ኢየሱስ ክርስቶስ ባሁኑ ጊዜ ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ እንደሆነ ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ ያመለክታሉ። በ1914 ሥልጣኑን ስለጨበጠ ገና ፍጻሜያቸውን የሚያገኙ አስገራሚ ትንቢቶች ይኖራሉ። እነዚህ ትንቢቶች ሲፈጸሙ ለማየት የምንፈልግ ከሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ የምናምንና ባለማወቅ በፈጸምነው ኃጢአት የምንጸጸት ገር ሰዎች መሆናችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል። እርግጥ ጨለማን የሚወዱ ሁሉ የዘላለም ሕይወት አያገኙም። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፣ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።”—ዮሐንስ 3:19-21
15. አምላክ በልጁ አማካኝነት ያጸናውን መዳን ችላ ብንል ምን ይደርስብናል?
15 መንፈሳዊ ብርሃን ወደ ዓለም የመጣው በኢየሱስ በኩል በመሆኑ እርሱን ማዳመጥ የግድ አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፣ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን።” (ዕብራውያን 1:1, 2) ታዲያ አምላክ በልጁ አማካኝነት ያዘጋጀውን መዳን ችላ ብንል ምን እንሆናለን? ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ፣ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ፣ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፣ እንዴት እናመልጣለን? ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፣ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት፣ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም፣ መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ መሰከረለት።” (ዕብራውያን 2:2-4) አዎን፣ ለታወጀው ትንቢታዊ ቃል መሠረት የሆነው ኢየሱስ ነው።—ራእይ 19:10 NW
16. በይሖዋ አምላክ ትንቢቶች ሁሉ ላይ ሙሉ እምነት ሊኖረን የሚችለው ለምንድን ነው?
16 ጴጥሮስ “በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጕም አልተፈቀደም” ሲል ተናግሯል። ማንኛውም ሰው ከራሱ አመንጭቶ እውነተኛ ትንቢት ሊናገር አይችልም። በአምላክ ትንቢቶች ሁሉ ላይ ግን ሙሉ በሙሉ ልንተማመን እንችላለን። እነዚህ ከራሱ ከይሖዋ አምላክ የመነጩ ናቸው። በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት አገልጋዮቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት ትንቢቶች እንዴት ፍጻሜያቸውን እያገኙ እንዳለ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። ከ1914 ወዲህ እንደነዚህ ያሉት ብዙ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ በመመልከታችን ይሖዋን እናመሰግነዋለን። ይህ ክፉ ዓለም ስለ መጥፋቱ የተናገራቸው የተቀሩት ትንቢቶችም አንድ በአንድ እንደሚፈጸሙ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ነን። ብርሃናችን ለሰው ሁሉ እንዲታይ እያደረግን መለኮታዊ ትንቢቶችን በትኩረት መከታተላችንን መቀጠላችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ማቴዎስ 5:16) የይሖዋ ቃል በዛሬው ጊዜ ምድርን በዋጠው ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ብርሃን እንዲታየን በማስቻሉ ምንኛ አመስጋኞች መሆን ይገባናል!—ኢሳይያስ 58:10
17. አምላክ የሚሰጠው መንፈሳዊ ብርሃን የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
17 የፀሐይ ብርሃን በመኖሩ ዓይናችን ማየት ችሏል። እንዲሁም ለምግብነት የሚውሉ የተለያየ ዓይነት ያላቸው አዝርዕት ሊበቅሉ ችለዋል። የፀሐይ ብርሃን ባይኖር ኖሮ በሕይወት መቆየት አንችልም ነበር። ስለ መንፈሳዊ ብርሃንስ ምን ማለት ይቻላል? መንፈሳዊ ብርሃን መመሪያ ይሰጠናል፤ እንዲሁም የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተነገረው ትንቢት አማካኝነት የወደፊቱን ጊዜ ያመለክተናል። (መዝሙር 119:105) ይሖዋ አምላክ በፍቅር ተገፋፍቶ ‘ብርሃኑንና እውነቱን ይልክልናል።’ (መዝሙር 43:3) እንዲህ ላለው ዝግጅት ጥልቅ አድናቆታችንን ማሳየት እንዳለብን የተረጋገጠ ነው። እንግዲያውስ ምሳሌያዊውን ልባችንን ያበራልን ዘንድ “የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን” ለመቅሰም የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።—2 ቆሮንቶስ 4:6፤ ኤፌሶን 1:18
18. በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ የንጋት ኮከብ ምን ለማድረግ ተዘጋጅቷል?
18 የንጋት ኮከብ የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ በ1914 በመላው ጽንፈ ዓለም ወጥቶ አስደናቂውን የመለወጥ ራእይ መፈጸም መጀመሩን በማወቃችን ምንኛ ተባርከናል! የይሖዋ የንጋት ኮከብ በተአምራዊ ሁኔታ መለወጡ ተጨማሪ ፍጻሜ መሠረት ‘ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ የአምላክን ዓላማ ለማስፈጸም በተጠንቀቅ ላይ ነው። (ራእይ 16:14, 16) ይህ አሮጌ ሥርዓት ተጠራርጎ ከጠፋ በኋላ ይሖዋ “አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር” እንደሚያመጣ የሰጠውን ተስፋ ሲፈጽም እንመለከታለን። በዚያም የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታና የእውነተኛ ትንቢት አምላክ የሆነውን ይሖዋን ከዘላለም እስከ ዘላለም ልናወድስ እንችላለን። (2 ጴጥሮስ 3:13) ያ ታላቅ ቀን እስኪመጣ ድረስ የአምላክን ትንቢታዊ ቃል በትኩረት በመከታተል በመለኮታዊ ብርሃን መመላለሳችንን እንቀጥል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• የኢየሱስን ተአምራዊ መለወጥ እንዴት ትገልጸዋለህ?
• የኢየሱስ መለወጥ እምነት የሚገነባ የሆነው እንዴት ነው?
• የይሖዋ የንጋት ኮከብ ማን ወይም ምንድን ነው? የወጣውስ መቼ ነው?
• የአምላክን ትንቢታዊ ቃል በትኩረት መከታተል የሚገባን ለምንድን ነው?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢየሱስን ተአምራዊ መለወጥ ትርጉም ማስረዳት ትችላለህ?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የንጋት ኮከብ ወጥቷል። እንዴትና መቼ እንደወጣ ታውቃለህ?