“ከጭንቀት ቀን” ማን ያመልጥ ይሆን?
“የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።”—ኢዩኤል 2:32
1. በዳንኤልና በሚልክያስ ትንቢቶች መሠረት “የመከራ ዘመን” በሚመጣበት ጊዜ በመዳን መንገድ ላይ የሚገኙት ሰዎች የሚለዩበት ምልክት ምን ይሆናል?
ነቢዩ ዳንኤል የእኛን ዘመን አሻግሮ በመመልከት “ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል፤ በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል” በማለት ጽፏል። (ዳንኤል 12:1) በእርግጥ የሚያጽናኑ ቃላት ናቸው! ሚልክያስ 3:16 “የዚያን ጊዜ [ይሖዋን (አዓት)] የሚፈሩ እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ፤ [ይሖዋም (አዓት)] አደመጠ፣ ሰማም፣ [ይሖዋንም (አዓት)] ለሚፈሩ ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ ተጻፈ” በማለት እንደሚናገረው የይሖዋን ሞገስ ያገኙ ሕዝቦች በእርሱ ይታሰባሉ ወይም ይታወሳሉ።
2. የይሖዋን ስም ከማሰብ ምን ውጤት ይገኛል?
2 ስለ ይሖዋ ስም ማሰብ ስለ እርሱ፣ ስለ ክርስቶስና ስለ ታላላቅ የመንግሥት ዓላማዎቹ ትክክለኛ ዕውቀት ወደ ማግኘት ያደርሳል። በዚህም መንገድ ሕዝቦቹ ለእርሱ አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳየትን፣ ለእርሱ ብቻ የተወሰኑ በመሆን ከእርሱ ጋር ወደተቀራረበ ዝምድና መግባትንና ‘በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም፣ በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኃይልም እርሱን መውደድን’ ይማራሉ። (ማርቆስ 12:33፤ ራዕይ 4:11) ይሖዋ የምድር ትሑታን የዘላለም ሕይወት ያገኙ ዘንድ በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት የምሕረት ዝግጅት አድርጓል። ስለዚህ እነዚህ የምድር ትሑታን ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ ሰማያዊው ጭፍራ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለበጎ ፈቃድ ሰዎች” በማለት አምላክን ያመሰገኑባቸውን ቃላት በሙሉ ትምክህት ሊያስተጋቡ ይችላሉ።—ሉቃስ 2:14
3. ሰላም ወደዚች ምድር ከመምጣቱ በፊት መፈጸም ያለበት የትኛው የይሖዋ እርምጃ ነው?
3 ዛሬ ይህ ሰላም አብዛኞቹ ሰዎች ከሚያስቡት ይበልጥ ቀርቦአል። ይሁን እንጂ አስቀድሞ በብልሹው ዓለም ላይ የይሖዋ የቅጣት ፍርድ መፈጸም ይኖርበታል። ነቢዩ ሶፎንያስ እንደሚከተለው ብሏል፦ “ታላቁ [የይሖዋ (አዓት)] ቀን ቀርቦአል፤ የ[የይሖዋ (አዓት)] ቀን ድምፅ ቀርቦአል እጅግም ፈጥኖአል።” ይህ ቀን ምን ዓይነት ቀን ነው? ትንቢቱ በመቀጠል “ኃያሉም በዚያ በመራራ ልቅሶ ይጮኻል። ያ ቀን የመዓት ቀን፣ የመከራና የጭንቀት ቀን፣ የመፍረስና የመጥፋት ቀን፣ የጨለማና የጭጋግ ቀን፣ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን፣ በተመሸጉ ከተሞችና በረዘሙ ግንቦች ላይ የመለከትና የሰልፍ ጩኸት ቀን ነው። በ[ይሖዋ (አዓት)] ላይ ኃጢአት ሠርተዋልና እንደ ዕውር እስኪሄዱ ድረስ ሰዎችን አስጨንቃለሁ” ይላል።—ሶፎንያስ 1:14-17፤ በተጨማሪም ዕንባቆም 2:3፤ 3:1-6, 16-19ን ተመልከቱ።
4. በዛሬው ጊዜ አምላክን እንዲያውቁና እንዲያገለግሉት ለቀረበላቸው ጥሪ ምላሽ እየሰጡ ያሉት እነማን ናቸው?
4 ባሁኑ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክን እንዲያውቁና እንዲያገለግሉት የሚቀርብላቸውን ጥሪ በመቀበል ላይ መሆናቸው በጣም ያስደስታል። ወደ አዲሱ ኪዳን ስለገቡት ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና ይላል [ይሖዋ (አዓት)]” የሚል ትንቢት ተነግሮ ነበር። (ኤርምያስ 31:34) እነርሱም በዘመናዊው የስብከት ሥራ ግንባር ቀደም ሆነዋል። አሁን ደግሞ ምድራዊ ሕይወታቸውን የሚፈጽሙት ቅቡዓን ቀሪዎች ቁጥር እየጨመረ በሄደ መጠን የ“ሌሎች በጎች” “እጅግ ብዙ ሰዎች” በአምላክ መቅደስ መሰል ድርጅት ‘ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት ሊያቀርቡለት’ እየቀረቡ ነው። (ራዕይ 7:9, 15፤ ዮሐንስ 10:16) አንተስ በዚህ ከፍተኛ ግምት በሚሰጠው መብት ከሚደሰቱት ሰዎች አንዱ ነህን?
“የተመረጠው ዕቃ” እንዴት እንደሚመጣ
5, 6. አሕዛብ በሙሉ በጥፋት ከመንኮታኮታቸው በፊት ምን የማዳን ሥራ መፈጸም ይኖርበታል?
5 አሁን ደግሞ ይሖዋ መንፈሳዊ የአምልኮ ቤቱን የሚመለከት ትንቢት ወደተናገረበት ወደ ሐጌ 2:7 ዘወር እንበል። ይሖዋ “አሕዛብን ሁሉ አናውጣለሁ፣ በአሕዛብ የተመረጠውም ዕቃ ይመጣል፤ ይህንንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ” ይላል። ‘አሕዛብ መናወጣቸው’ ይሖዋ በአሕዛብ ላይ የቅጣት ፍርድ እንደሚያስፈጽም የሚያመለክት መሆኑን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ያሳያሉ። (ናሆም 1:5, 6፤ ራዕይ 6:12-17) ስለዚህ በሐጌ 2:7 ላይ የተተነበየው የይሖዋ እርምጃ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚደርሰው አሕዛብ ተንኮታኩተው ከሕልውና ውጭ በሚሆኑበት ጊዜ ነው። “ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጡት ዕቃዎችስ” ምን ይሆናሉ? ያ የመጨረሻ አጥፊ መናወጥ እስኪያመጣቸው ድረስ ይጠብቃሉን? በፍጹም መጠበቅ አይኖርባቸውም።
6 ኢዩኤል 2:32 “[የይሖዋን (አዓት)]ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል፤ [ይሖዋም (አዓት)] እንደተናገረ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም መድኃኒት ይገኛል። ደግሞም [ይሖዋ (አዓት)] የሚጠራቸው፣ የምሥራች የሚሰበክላቸው ይገኛሉ” በማለት ይናገራል። ይሖዋ ስቦ ስለሚያመጣቸው ከታላቁ መከራ የመደምደምያ ነውጥ በፊት በኢየሱስ መሥዋዕት በማመን የይሖዋን ስም ይጠራሉ። (ከዮሐንስ 6:44፤ ሥራ 2:38, 39 ጋር አወዳድሩ) በአሁኑ ጊዜ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሆኑት ውዶቹ እጅግ ብዙ ሰዎች ይሖዋ በአርማጌዶን ‘አሕዛብን ሁሉ የሚያናውጥበትን’ ጊዜ በተስፋ በመጠባበቅ ወደ አምልኮ ቤቱ ‘መጥተዋል።’—ራዕይ 7:9, 10, 14
7. ‘የይሖዋን ስም መጥራት’ ምንን ያጠቃልላል?
7 እነዚህ ከጥፋት የሚተርፉ ሰዎች የይሖዋን ስም የሚጠሩት እንዴት ነው? ያዕቆብ 4:8 “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች እጆቻችሁን አንጹ” በማለት የይሖዋን ስም የሚጠሩበትን መንገድ ይጠቁመናል። ከአርማጌዶን የሚተርፉት እጅግ ብዙ ሰዎች መንገዱን እንዳሳዩአቸው ቅቡዓን ቀሪዎች ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል። ከጥፋት ለመዳን የምትፈልግ ከሆነ የይሖዋን የሚያነጻ ቃል በጉጉት መጠጣትና የጽድቅ ሥርዓቶቹንም በሕይወትህ በሥራ ላይ ማዋል አለብህ። ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ ሕይወትህን ለይሖዋ መወሰንና ይህንንም ውሳኔህን በውኃ ጥምቀት ማሳየት ይገባሃል። የይሖዋን ስም በእምነት መጥራት ስለእርሱ መመስከርንም ይጨምራል። በመሆኑም በሮሜ ምዕራፍ 10 ቁጥር 9 እና 10 ላይ ጳውሎስ “ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መሥክሮ ይድናልና” በማለት ጽፏል። ከዚያም ሐዋርያው በቁጥር 13 ላይ የኢዩኤልን ትንቢት ጠቅሶ “[የይሖዋን (አዓት)] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” በማለት አጥብቆ ያሳስባል።
‘ፈልጉ፣ ፈልጉ፣ ፈልጉ’
8. (ሀ) ነቢዩ ሶፎንያስ በተናገረው መሠረት ለመዳን ይሖዋ የሚፈልግብን ምንድን ነው? (ለ) በሶፎንያስ 2:3 ላይ “ምናልባት” የሚለው ቃል ምን ማስጠንቀቂያ ያስተላልፍልናል?
8 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ወደሆነው የሶፎንያስ መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ቁጥር 2 እና 3 ስንመለስ ለመዳን ይሖዋ ከእኛ ምን እንደሚፈልግብን እናነባለን፦ “የ[የይሖዋም (አዓት)] ቁጣ ትኩሳት ሳይመጣባችሁ፣ የ[የይሖዋም (አዓት)] ቁጣ ቀን ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ፣ ተከማቹም። እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ [ይሖዋን (አዓት)] ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንም [ገርነትን (አዓት)] ፈልጉ፤ ምናልባት በ[ይሖዋ (አዓት)] ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።” “ምናልባት” የሚለውን ቃል ልብ በሉት። አንድ ጊዜ የዳነ ለሁልጊዜ ዳነ እንደሚባለው አይደለም። በዚያ ቀን ለመሰወር መቻላችን የተመካው እነዚህን ሦስት ነገሮች ማድረጋችንን በመቀጠላችን ላይ ነው። [ይሖዋን (አዓት)] መፈለግ፣ ጽድቅን መፈለግ፣ እንደዚሁም ገርነትን መፈለግ አለብን።
9. ገርነትን የሚፈልጉ ሰዎች ምን አይነት ሽልማት ያገኛሉ?
9 ገርነትን የመፈለግ ሽልማት በእርግጥም አስደናቂ ነው! በመዝሙር 37 ቁጥር 9-11 ላይ “[ይሖዋን (አዓት)] ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ። ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል” እንደሚል እናነባለን። ጽድቅን መፈለግ የሚያስገኘው ሽልማትስ ምንድን ነው? ቁጥር 29 “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት ይናገራል። ይሖዋን መፈለግ የሚያስገኘውን ሽልማት በተመለከተም ቁጥር 39 እና 40 “የጻድቃን መድኃኒታቸው [ከይሖዋ (አዓት)] ዘንድ ነው፤ በመከራቸውም ጊዜ መጠጊያቸው እርሱ ነው። [ይሖዋ (አዓት)] ይረዳቸዋል፣ ያድናቸዋልም፣ ከኃጢአተኞችም እጅ ያወጣቸዋል፣ ያድናቸዋልም፣ በእርሱ ታምነዋልና” በማለት ይነግረናል።
10. ይሖዋን ለመፈለግና ትሕትናን ለመፈለግ እምቢተኛ በመሆናቸው የታወቁት እነማን ናቸው?
10 የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ኑፋቄዎች ይሖዋን ሳይፈልጉ ቀርተዋል። እንዲያውም ቄሶቻቸው ውድ ስሙን ክደዋል፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው ውስጥ ስሙን እስከማጥፋት ተዳፍረዋል። ስም የለሽ የሆነ ጌታ ወይም አምላክ ለማምለክ መርጠዋል። የአረማውያን አምላክ የሆነውን ሥላሴ ያመልካሉ። ከዚህም በላይ ሕዝበ ክርስትና ጽድቅን አትፈልግም። ከተከታዮቿ መካከል የሚበዙት ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ልቅ አኗኗር የሚከተሉ ወይም የሚደግፉ ናቸው። እንደ ኢየሱስ ገርነትን ከመፈለግ ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነው የቅንጦት ኑሮአቸው እንዲታይላቸው ይፈልጋሉ። ቀሳውስት መንጎቻቸውን እየበዘበዙ ራሳቸውን አወፍረዋል። ያዕቆብ 5:5 ‘በምድር ላይ ተቀማጥለዋል፣ በሴሰኝነትም ኖረዋል።’ የይሖዋ ቀን ሲደርስ “በቁጣ ቀን ሀብት አትረባም” የሚሉት በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ቃላት በእነርሱ ላይ እንደተፈጸሙባቸው ይገነዘባሉ።—ምሳሌ 11:4
11. የአመጽ ሰው ማን ነው? በራሱስ ላይ ከፍተኛ የደም ዕዳ የከመረው እንዴት ነው?
11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ በ2 ተሰሎንቄ ምዕራፍ ሁለት ላይ እንደሚነግረን አንዳንድ ክርስቲያኖች “የይሖዋ ቀን” የመጣ መስሎአቸው ተደናግጠው ነበር። ጳውሎስ ግን አስቀድሞ ክህደቱ መምጣትና “የአመጽ ሰው” መገለጥ እንደሚኖርበት አስጠንቅቆአል። (2 ተሰሎንቄ 2:1-3) እኛ በዚህ በሃያኛው መቶ ዘመን የምንኖረው ይህ ክህደት ምን ያህል ሠፊ እንደሆነና የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትም በአምላክ ፊት ምን ያህል የከፉ አመጸኞች እንደሆኑ ለመገንዘብ ችለናል። በዚህ ከ1914 ወዲህ ባለው የመጨረሻ ጊዜ ቀሳውስት ሰው ሁሉ ‘ማረሻውን ወደ ሰይፍ እንዲለውጥ’ በማደፋፈርና በመደገፍ በራሳቸው ላይ ከፍተኛ የደም ዕዳ ከምረዋል። (ኢዩኤል 3:10) በተጨማሪም ስለ ነፍስ ዘላለማዊነት፣ ስለ መንጽሔ፣ ስለ ሲኦል ስቃይ፣ ስለ ሕፃናት ጥምቀት፣ ስለ ሥላሴና ስለመሳሰሉት የሐሰት መሠረተ ትምህርቶች ማስተማራቸውን ቀጥለዋል። ይሖዋ የቅጣት ፍርዱን በሚያመጣበት ጊዜ የት ይቆሙ ይሆን? ምሳሌ 19:5 “በሐሰትም የሚናገር አያመልጥም” ይላል።
12. (ሀ) በቅርቡ የሚደመሰሱት ሰብአዊ “ሰማያትና” “ምድር” ምንድን ናቸው? (ለ) በዚህ ክፉ ዓለም ላይ ከሚመጣው ጥፋት ምን እንማራለን?
12 በሁለተኛ ጴጥሮስ 3:10 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “[የይሖዋ (አዓት)] ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል። በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፣ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ይቀልጣል፣ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።” በሰው ልጆች ላይ እንደ ሰማይ ድንኳኑን ዘርግቶ የቆየው ብልሹ አገዛዝ ከዛሬው የበሰበሰ የሰው ልጆች ማህበረሰብ ዝንባሌና አኗኗር ጋር ከአምላክ ምድር ተጠርጎ ይጠፋል። የእልቂት መሣሪያዎችን የሚያመርቱና የሚነግዱ ሰዎች፣ አጭበርባሪ ነጋዴዎች፣ ግብዝ ሃይማኖቶችና ቄሶቻቸው፣ ብልግናን አመጽንና ወንጀልን የሚያስፋፉ ሁሉ በይሖዋ የቁጣ ቀን ትኩሳት ይቃጠላሉ። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ በቁጥር 11 እና 12 ላይ ለክርስቲያኖች የማስጠንቀቂያ ቃል ተናግሮአል። እንዲህ አለ፦ “ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኮላችሁ፣ በቅዱስ ኑሮና [ለአምላክ ያደራችሁ በመሆን (አዓት)] እንደምን ልትሆኑ ይገባችኋል?”
ሚካኤል እርምጃ ይወስዳል!
13, 14. የይሖዋ አገዛዝ ታላቅ ጠበቃ ማን ነው? ከ1914 ወዲህ የቆመውስ እንዴት ነው?
13 በዚያ “የጭንቀት ቀን” ማምለጥ የሚቻለው እንዴት ነው? ይሖዋ የማምለጫውን መንገድ እንዲያዘጋጅ ሥልጣን የሰጠው ለመላእክት አለቃ ሚካኤል ሲሆን የስሙ ትርጓሜ “እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” ማለት ነው። የይሖዋን እውነተኛ አምላክነትና የጽንፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ የመሆን ባለመብትነቱን በማስከበር የይሖዋን አገዛዝ የሚያረጋግጠው እርሱ መሆኑ ተገቢ ነው።
14 ራዕይ 12 ቁጥር ከ7 እስከ 17 ከ1914 ወዲህ ባለው “የጌታ ቀን” ስለሚፈጸሙ ነገሮች የሚናገረው ነገር በጣም አስደናቂ ነው! (ራዕይ 1:10) የመላእክት አለቃ ሚካኤል ከዳተኛውን ሰይጣንን ከሰማይ ወደ ምድር ይጥለዋል። በኋላም በራዕይ 19:11-16 ላይ እንደተገለጸው “የታመነና እውነተኛ” ተብሎ የተጠራው ‘ሁሉን የሚችል የእግዚአብሔርን የብርቱ ቁጣውን ወይን መጥመቂያ ይረግጣል’። ይህ ኃያል ሰማያዊ ጦረኛ “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ” ተብሎ ተጠርቷል። በመጨረሻም ራዕይ ምዕራፍ 20 ቁጥር 1 እና 2 ሰይጣንን ወደ ጥልቁ ጥሎ ሺህ ዓመት ስለሚያስረው አንድ ኃያል መልአክ ይነግረናል። እነዚህ ጥቅሶች በሙሉ የይሖዋን ሉዓላዊነት ደግፎ የሚቆመውንና ይሖዋ በ1914 በሰማይ የክብር ዙፋን ላይ ያስቀመጠውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያመለክቱ ግልጽ ነው።
15. ሚካኤል በቅርቡ በምን የተለየ መንገድ “ይቆማል”?
15 በዳንኤል 12:1 ላይ እንደተነገረው ሚካኤል በ1914 ንጉሥ ሆኖ ከቆመበት ጊዜ አንስቶ ስለ ይሖዋ ሕዝቦች “ቆሟል።” በቅርቡ ግን ሚካኤል ክፋትን ሁሉ ከምድር የሚያስወግድ የይሖዋ ወኪልና የአምላክ ሕዝቦች ምድር አቀፍ ማህበረሰብ አዳኝ ሆኖ በልዩ ሁኔታ “ይቆማል።” ያ “የጭንቀት ቀን” ምን ያህል ታላቅ እንደሚሆን ኢየሱስ ሲገልጽ በማቴዎስ 24:21, 22 ላይ እንዲህ ብሏል፦ “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።”
16. በታላቁ መከራ ጊዜ የሚድኑት የትኞቹ ሥጋ ለባሾች ናቸው?
16 በዚያ ጊዜ የሚድን ሥጋ ለባሽ በመኖሩ ምን ያህል ደስተኞች ልንሆን እንችላለን! እነዚህ የሚድኑ ሥጋ ለባሾች ግን በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ከተማ ተከብበው ከቆዩ በኋላ የሮማውያን ባሮች እንዲሆኑ ተማርከው እንደተወሰዱት አመጸኛ አይሁዳውያን ያሉ አይደሉም። “በፍጻሜ ዘመን” ከጥፋት የሚያመልጡት ሰዎች የመጨረሻው የኢየሩሳሌም ከበባ ሲጀምር ከኢየሩሳሌም ሸሽተው እንደወጡት የክርስቲያን ጉባኤ ይሆናሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩት እጅግ ብዙ ሰዎችና እስከዚያ ጊዜ ድረስ በምድር ላይ የሚቆዩት ቅቡዓን አንድ ላይ ሆነው የአምላክ ሕዝቦች ይሆናሉ። (ዳንኤል 12:4) እጅግ ብዙ ሰዎች የሚመጡት “ከታላቁ መከራ” ነው። ለምን? ምክንያቱም “ልብሳቸውን አጥበው በበጉ ደም ስላነጹ” ነው። በፈሰሰው የኢየሱስ ደም የመቤዠት ኃይል እምነት ያሳዩና ያንንም እምነት አምላክን በታማኝነት በማገልገል የገለጹ ናቸው። አሁንም እንኳን “በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው” ይሖዋ የመከላከያ ድንኳኑን በላያቸው ሲዘረጋ በጉ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ እረኛቸው ይሆናል፣ ወደ ሕይወትም ውሃ ምንጭ ይመራቸዋል።—ራዕይ 7:14, 15
17. እጅግ ብዙ ሰዎች በመጪው የመከራ ዘመን ለመሠወር እንዲችሉ በተለይ የተበረታቱት እንዴት ነው?
17 በሚሊዮን የሚቆጠሩት እጅግ ብዙ ሰዎች ይሖዋን፣ ጽድቅንና ትሕትናን በሚፈልጉበት ጊዜ ለእውነት የነበራቸው የመጀመሪያ ፍቅር እንዲቀዘቅዝባቸው መፍቀድ አይገባቸውም! ከእነዚህ በግ መሰል ሰዎች አንዱ ከሆንክ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? በቆላስይስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 5-14 ላይ እንደተገለጸው “አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር [ሙሉ በሙሉ] ገፈህ” መጣል አለብህ። መለኮታዊ እርዳታ በመፈለግም ‘በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተውን አዲስ ሰው ለመልበስ’ ተጣጣር። በትሕትናም ይሖዋን በማመስገንና ታላላቅ ዓላማዎቹን ለሌሎች በማሳወቅ ረገድ ያለህን ቅንዓት አሳድግ። እንዳይቀዘቅዝም ጠብቀው። እንዲህ ካደረግህ “የይሖዋ የቁጣ ትኩሳት ቀን” በሆነው “የመከራ ቀን” ልትሰወር ትችላለህ።
18, 19. መጽናት ለመዳን አስፈላጊ የሆነው በምን መንገድ ነው?
18 ያ ቀን ቀርቦአል! ወደ እኛም ፈጥኖ እየገሰገሰ ነው። የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት የሚሆኑትን ሰዎች የመሰብሰቡ ሥራ እስከ አሁን ለ57 ዓመታት ቀጥሏል። ከእነርሱም በርካታ ቁጥር ያላቸው ሞተው ትንሣኤያቸውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ይሁንና እጅግ ብዙ ሰዎች በቡድን ደረጃ ከታላቁ መከራ በሕይወት አልፈው “የአዲሲቱ ምድር” ማህበረሰብ ቆርቋሪ እንደሚሆኑ የራዕይ ትንቢት አረጋግጧል። (ራዕይ 21:1) አንተስ በዚያ ትገኝ ይሆንን? ኢየሱስ በማቴዎስ 24:13 ላይ “እስከመጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” ስላለ ልትገኝ ትችላለህ።
19 የይሖዋ ሕዝቦች በዚህ አሮጌ ሥርዓት የሚያጋጥማቸው ውጥረት እየጨመረ ሊሄድ ይችላል። አስጨናቂው ታላቅ መከራ በሚጀምርበት ጊዜ ደግሞ ችግር ሊያንገላታቸው ይችላል። ነገር ግን ከይሖዋና ከድርጅቱ ጋር ተጣብቃችሁ ኑሩ። ነቅታችሁ ኑሩ! “መዓቴንና የቁጣዬን ትኩሳት ሁሉ አፈስስባቸው ዘንድ ፍርዴ አሕዛብን ለመሰብሰብ፣ መንግሥታትንም ለማከማቸት ነውና፣ ምድርም ሁሉ በቅንዓቴ እሳት ትበላለችና ስለዚህ ለመበዝበዝ እስከምነሣበት ቀን ድረስ ጠብቁኝ፣ ይላል [ይሖዋ (አዓት)]።”—ሶፎንያስ 3:8
20. የመደምደሚያው “የጭንቀት ቀን” እየቀረበ ሲመጣ ምን ማድረግ ይገባናል?
20 ይሖዋ እኛ ጥበቃና ማበረታቻ እንድናገኝ አስቦ በደግነቱ “አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው [ይሖዋን (አዓት)] ያገለግሉት ዘንድ” ስለመጪዋ መንግሥቱ የሚገልጸውን ታላቅ መልእክት የሚጨምረውን “ንጹሕ ልሳን” ለሕዝቦቹ እየሰጠ ነው። (ሶፎንያስ 3:9) የመደምደሚያው “የመከራ ዘመን” ወደማብቂያው እየተቻኮለ ሲሄድ ሌሎች ገሮች ሰዎችም ለመዳን ‘የይሖዋን ስም እንዲጠሩ’ በመርዳት በቅንዓት እናገልግል።
ታስታውሳላችሁን?
◻ ሰላም ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የሚቀድመው የትኛው የይሖዋ እርምጃ ነው?
◻ በኢዩኤል ትንቢት መሠረት አንድ ሰው ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርበታል?
◻ በሶፎንያስ ትንቢት መሠረት ትሑታን ከይሖዋ የቁጣ ትኩሳት ከለላ የሚያገኙት እንዴት ነው?
◻ “የአመጽ ሰው” ማን ነው? በራሱ ላይ የደም ዕዳ የከመረውስ እንዴት ነው?
◻ በመዳን ረገድ መጽናት ምን ያህል አስፈላጊ ነው?