ለመዳን የሚያበቃ የሕዝብ ምሥክርነት መስጠት
“የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።”—ሮሜ 10:13 NW
1. በታሪክ ዘመናት ሁሉ የትኞቹ ማስጠንቀቂያዎች ተነግረዋል?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበው ታሪክ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ጊዜያት ተከስተው ስለነበሩት ‘የይሖዋ ቀኖች’ ይገልጻል። በኖኅ ዘመን የደረሰው የጥፋት ውኃ፣ የሰዶምና የገሞራ ጥፋት፣ በ607 ከዘአበ እና በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው ጥፋት ታላቅና የሚያስፈሩ የይሖዋ ቀኖች ነበሩ። እነዚህ ጊዜያት በይሖዋ ላይ ባመፁ ሰዎች ላይ ፍትሃዊ ፍርድ የተላለፈባቸው ወቅቶች ናቸው። (ሚልክያስ 4:5፤ ሉቃስ 21:22) በእነዚህ ጊዜያት ብዙ ሰዎች በክፉ ድርጊታቸው የተነሳ ጠፍተዋል። አንዳንዶች ግን ድነዋል። ይሖዋ ክፉ ሰዎች የሚመጣባቸውን መቅሰፍት እንዲያውቁ ለማድረግና ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች ደህንነት የሚያገኙበትን አጋጣሚ ለመክፈት ማስጠንቀቂያዎችን አስነግሯል።
2, 3. (ሀ) በጰንጠቆስጤ ዕለት የትኛው ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ ተጠቅሷል? (ለ) በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ የይሖዋን ስም ለመጥራት ምን ያስፈልግ ነበር?
2 በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው ጥፋት ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። ነቢዩ ኢዩኤል 900 ከሚያክሉ ዓመታት በፊት እንዲህ ሲል ትንቢት ተናግሯል:- “በላይ በሰማይ ድንቆችን አሳያለሁ፣ በታች በምድርም ደምና እሳት የጢስም ጭጋግ። ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል።” አንድ ሰው እንዲህ ካለው አስፈሪ ጊዜ በሕይወት መትረፍ የሚችለው እንዴት ነው? ኢዩኤል በመንፈስ ተነሳስቶ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እንዲህም ይሆናል፤ የእግዚአብሔርን [“የይሖዋን፣” NW] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ፣ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም መድኃኒት ይገኛል [“የሚድኑ ሰዎች ይገኛሉ፣” NW]። ደግሞም እግዚአብሔር የጠራቸው፣ የምሥራች የሚሰበክላቸው ይገኛሉ።”—ኢዩኤል 2:30-32
3 በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ሐዋርያው ጴጥሮስ በኢየሩሳሌም ተሰብስበው ለነበሩት አይሁድና ወደ አይሁድ ተለውጠው ለነበሩ ሰዎች በሚናገርበት ጊዜ አድማጮቹ በጊዜያቸው የሚፈጸም አንድ ነገር መጠባበቅ እንዲችሉ ለማድረግ የኢዩኤልን ትንቢት በመጥቀስ እንዲህ አለ:- “ድንቆችን በላይ በሰማይ፣ ምልክቶችንም በታች በምድር እሰጣለሁ፤ ደምም እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል፤ ታላቅ የሆነ የተሰማም የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። የጌታን [“የይሖዋን፣” NW] ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል።” (ሥራ 2:16-21) ጴጥሮስን ያዳምጡ የነበሩት የተሰበሰቡት ሰዎች በሙሉ በሙሴ ሕግ ሥር ስለነበሩ የይሖዋን ስም ጠንቅቀው ያውቁ ነበር። በዚህም የተነሳ ጴጥሮስ የይሖዋን ስም መጥራት ከዚህ የበለጠ ነገርን የሚያካትት እንደሆነ አብራራ። ይህም በሞተውና ከዚያም የማይጠፋ ሰማያዊ ሕይወት ይዞ ከሞት በተነሳው በኢየሱስ ስም መጠመቅን የሚጨምር እንደሆነ ግልጽ በሆነ መንገድ አብራራ።—ሥራ 2:37, 38
4. ክርስቲያኖች በሰፊው ያወጁት የትኛውን መልእክት ነበር?
4 ከጰንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ ክርስቲያኖች ትንሣኤ ስላገኘው ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ቃል በሰፊው አዛመቱ። (1 ቆሮንቶስ 1:23) ሰዎች የይሖዋ አምላክ መንፈሳዊ ልጆችና ‘የይሖዋን በጎነት በሰፊው የሚያውጅ’ የመንፈሳዊ ብሔር ማለትም የአዲሱ ‘የአምላክ እስራኤል’ ክፍል መሆን እንደሚችሉ በስፋት አሳወቁ። (ገላትያ 6:16፤ 1 ጴጥሮስ 2:9) እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ሆነው የቆዩ በሰማያዊው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር ተባባሪ ገዥዎች ሆነው የማይጠፋ ሰማያዊ ሕይወት ይወርሳሉ። (ማቴዎስ 24:13፤ ሮሜ 8:15, 16፤ 1 ቆሮንቶስ 15:50-54) ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ክርስቲያኖች ወደፊት የሚመጣውን ታላቁንና አስፈሪውን የይሖዋ ቀን ማወጅ ነበረባቸው። በኢየሩሳሌምና የአምላክ ሕዝብ ነን በሚሉ ሰዎች ላይ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ መከራ እንደሚመጣ ለአይሁድ ኅብረተሰብ ማስጠንቀቅ ነበረባቸው። ሆኖም በሕይወት የሚተርፉ ይኖራሉ። እነማን? የይሖዋን ስም የሚጠሩ በሕይወት ይተርፋሉ።
“በመጨረሻው ቀን”
5. በዛሬው ጊዜ የትኛው ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ ነው?
5 በዚያን ጊዜ ደርሰው የነበሩት ሁኔታዎች በዛሬው ጊዜ ለምናያቸው ነገሮች በብዙ አቅጣጫ ጥላ ናቸው። የሰው ልጅ ከ1914 ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስ የ“ፍጻሜ ዘመን፣” “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ፣” እና “የመጨረሻ ቀን” ብሎ በሚጠራው በጣም ልዩ በሆነ ጊዜ ውስጥ ይኖራል። (ዳንኤል 12:1, 4፤ ማቴዎስ 24:3-8 NW፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13) እኛ ባለንበት መቶ ዘመን የደረሱት አሰቃቂ ጦርነቶች፣ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ዓመፅ እንዲሁም በማኅበረሰብና በአካባቢ ላይ የደረሱት ብልሽቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው አስደናቂ ትንቢት ፍጻሜ ናቸው። እነዚህ ሁሉ በሰው ልጅ ላይ ወሳኝና የመጨረሻ የሆነው አስፈሪው የይሖዋ ቀን መድረሱን የሚያሳዩ ኢየሱስ በተናገራቸው ትንቢቶች ውስጥ የሚገኙ ምልክቶች ናቸው። ይህም “ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ” የመጨረሻው ከፍተኛ ደረጃ በሆነው በአርማጌዶን ጦርነት ሁሉም ነገር ወደ ድምዳሜው ይደርሳል።—ማቴዎስ 24:21፤ ራእይ 16:16
6. (ሀ) ይሖዋ ቅን የሆኑ ሰዎችን ለማዳን ምን ዓይነት እርምጃ ወስዷል? (ለ) መዳን የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ጳውሎስ የሰጠው ምክር የት ላይ ይገኛል?
6 ጥፋቱ ከምን ጊዜውም ይበልጥ እየቀረበ ስለመጣ ይሖዋ ቅን የሆኑ ሰዎች መዳን እንዲያገኙ እርምጃ በመውሰድ ላይ ነው። በዚህ ‘የመጨረሻ ቀን’ መንፈሳዊ የአምላክ እስራኤል የመጨረሻ አባላት ከሰበሰበ በኋላ ከ1930ዎቹ ጀምሮ ምድራዊ አገልጋዮቹ “አንድ እንኳ ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” ወደ መሰብሰቡ ሥራ እንዲያዞሩ አደረገ። እነዚህ ሰዎች በቡድን ደረጃ ‘ከታላቁ መከራ በሕይወት ያለፉ ናቸው።’ (ራእይ 7:9, 14) ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ወይም የራሷን ሕይወት መትረፍ ማረጋገጥ የሚችለው ወይም የምትችለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። በሮሜ ምዕራፍ 10 ላይ በእርሱ ዘመንም ሆነ በእኛ ዘመን የሚሠራ በሕይወት ለመትረፍ የሚያስችል ግሩም ምክር ሰጥቷል።
ለመዳን የሚያበቃ ጸሎት
7. (ሀ) በሮሜ 10:1, 2 ላይ የተገለጸው ተስፋ ምንድን ነው? (ለ) በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ በሰፊው መታወጅ ያለበት “ምሥራች” ሊኖረው የቻለው አንዴት ነው?
7 ጳውሎስ የሮሜን መጽሐፍ በጻፈበት ወቅት ይሖዋ እስራኤልን በብሔር ደረጃ ሕዝቡ አድርጎ ማየቱን ትቶ ነበር። ሐዋርያው “የልቤ በጎ ፈቃድና ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ልመናዬ እንዲድኑ ነው” በማለት ይሖዋ እስራኤልን መተዉን በድጋሚ አረጋግጧል። ምኞቱ እያንዳንዱ አይሁዳዊ ወደ መዳን የሚያደርሰውን ስለ አምላክ ፈቃድ የሚናገረውን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኝ ነበር። (ሮሜ 10:1, 2) እንዲሁም ዮሐንስ 3:16 “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” በማለት እንደሚያመለክተው ይሖዋ እምነት ያላቸው በመላው ዓለም የሚገኙ የሰው ዘሮች መዳንን እንዲያገኙ ልባዊ ምኞቱ ነው። የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ወደዚህ ታላቅ መዳን የሚያደርሰውን መንገድ ከፍቷል። በኖኅ ዘመንና ከዚያ በኋላ በነበሩት በሌሎች የፍርድ ቀናት እንደሆነው ሁሉ ይሖዋ መዳን የሚገኝበትን መንገድ የሚጠቁም መታወጅ ያለበት ‘ምሥራች’ አለው።—ማርቆስ 13:10, 19, 20
8. በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች የጳውሎስን ምሳሌ በመከተል በጎ ፈቃድ የሚያሳዩት ለእነማን ነው? እንዴትስ?
8 ጳውሎስ ለአይሁድም ሆነ ለአሕዛብ ያለውን በጎ ፈቃድ ለማሳየት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሰብኳል። “አይሁድንና የግሪክንም ሰዎች ያስረዳ ነበር።” በኤፌሶን ይገኙ ለነበሩት ሽማግሌዎች “ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን ለአይሁድና ለግሪክ ሰዎች እየመሰከርሁ በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፣ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም” በማለት ነግሯቸዋል። (ሥራ 18:4፤ 20:20, 21) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያን ነን ለሚሉ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሰዎች ሌላው ቀርቶ “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ለመስበክ ራሳቸውን አቅርበዋል።—ሥራ 1:8፤ 18:5
‘የእምነትን ቃል’ መናገር
9. (ሀ) ሮሜ 10:8, 9 የሚያበረታታው ምን ዓይነት እምነትን ነው? (ለ) ስለ እምነታችን መናገር ያለብን መቼና እንዴት ነው?
9 ለመዳን ጽኑ የሆነ እምነት ያስፈልጋል። ጳውሎስ ከዘዳግም 30:14 ላይ ጠቅሶ “በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል፤ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 10:8) ይህን “የእምነት ቃል” በሰበክን መጠን በልባችን ውስጥ የበለጠ ሥር እየሰደደ ይሄዳል። በጳውሎስ ሕይወትም ላይ የታየው ሁኔታ ይኸው ነው። በተጨማሪም ቀጥሎ የተናገራቸው “ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና” የሚሉት ቃላት ይህን እምነት ለሌሎች በማካፈል ረገድ እርሱን እንድንመስል ያለንን ቁርጠኝነት ሊያጠናክርልን ይችላል። (ሮሜ 10:9) ይህ በሌሎች ፊት ስትጠመቅ በምትሰጠው ምሥክርነት ብቻ የሚያበቃ አይደለም። የእውነትን ታላላቅ ገጽታዎች በቅንዓት በሕዝብ ፊት ማወጅህን መቀጠል ይኖርብሃል። እንዲህ ያለው እውነት ውድ በሆነው በሉዓላዊው ጌታ በይሖዋ ስም፣ መሲሐዊ ንጉሣችንና ቤዛችን በሆነው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስና አስደናቂ በሆኑት የመንግሥቱ ተስፋዎች ላይ የሚያተኩር ነው።
10. ከሮሜ 10:10, 11 ጋር በሚስማማ መንገድ ይህን “የእምነት ቃል” መያዝ ያለብን እንዴት ነው?
10 ሐዋርያው “ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። መጽሐፍ:- በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላልና” በማለት እንደተናገረው ይህን “የእምነት ቃል” የማይቀበልና በሥራ ላይ የማያውል ማንኛውም ሰው መዳንን አያገኝም። (ሮሜ 10:10, 11) ይህን “የእምነት ቃል” በተመለከተ ትክክለኛ እውቀት ማግኘትና ለሌሎች ለመናገር ከውስጥ እንዲገፋፋን በልባችን ውስጥ ሥር እየሰደደ እንዲሄድ ማድረግ አለብን። ኢየሱስ ራሱ “በዚህም በዘማዊና በኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፣ የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር በመጣ ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል” በማለት ማሳሰቢያ ሰጥቷል።—ማርቆስ 8:38
11. ምሥራቹ ምን ያህል በሰፊው መታወጅ አለበት? ለምንስ?
11 ነቢዩ ዳንኤል እንደተነበየው በዚህ የፍጻሜ ዘመን የመንግሥቱ ምሥክርነት እስከ ምድር ዳር ድረስ በመስፋፋቱ “ጥበበኞች እንደ ሰማይ ጸዳል” ደምቀው ይታያሉ። “ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ” በመመለስ ላይ ናቸው። እንዲሁም ይህን የፍጻሜ ዘመን በማስመልከት በተነገሩት ትንቢቶች ላይ ይሖዋ ተጨማሪ ብርሃን በመፈንጠቁ በእርግጥም እውነተኛ እውቀት ተትረፍርፏል። (ዳንኤል 12:3, 4) በመሆኑም እውነትንና ጽድቅን የሚወድዱ ሰዎች ሁሉ በሕይወት ለመትረፍ እንዲችሉ ይህ እጅግ አስፈላጊ የሆነ የመዳን መልእክት እየተነገረ ነው።
12. ሮሜ 10:12 በራእይ 14:6 ላይ ከተገለጸው መልአክ ተልዕኮ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?
12 ሐዋርያው ጳውሎስ “በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፣ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው” በማለት ይቀጥላል። (ሮሜ 10:12) “ምስራቹ” ይበልጥ ስፋት ባለው ዓለም አቀፍ ሁኔታ ለሁሉም ሰዎች ማለትም እስከ ምድር ዳር ድረስ መሰበክ አለበት። በራእይ 14:6 ላይ የተገለጸው መልአክ ‘በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰበክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል’ ለእኛ በአደራ በመስጠት በሰማይ መካከል መብረሩን ቀጥሏል። ምላሽ ለሚሰጡ ሁሉ ይህ የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?
የይሖዋን ስም መጥራት
13. (ሀ) የ1998 የዓመት ጥቅሳችን ምንድን ነው? (ለ) ይህ የዓመት ጥቅስ ለአሁኑ ጊዜ ይበልጥ ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው?
13 ጳውሎስ ኢዩኤል 2:32ን በመጥቀስ “የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 10:13 NW) እነዚህ ቃላት በ1998 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት ጥቅስ እንዲሆኑ መመረጣቸው ምንኛ የተገባ ነው! ስሙንና ስሙ የቆመላቸውን ታላላቅ ዓላማዎች በማሳወቅ በይሖዋ ላይ በመታመን ወደፊት መግፋት እንደ አሁኑ ጊዜ አስፈላጊ የሆነበት ወቅት የለም! እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ በዚህ ብልሹ የነገሮች ሥርዓት የፍጻሜ ዘመን ውስጥም “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ” የሚለው ጥሪ እያስተጋባ ነው። (ሥራ 2:40) ይህ ጥሪ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ይሖዋ እነሱንና እነርሱ በሕዝብ ፊት ስለ ምሥራቹ የሚሰጡትን ምሥክርነት የሚሰሙ ሰዎችን ያድናቸው ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ከፍ ባለ ድምፅ የቀረበ ግብዣ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 4:16
14. መዳን ለማግኘት ልንጠራው የሚገባን ዓለት ማን ነው?
14 የይሖዋ ታላቅ ቀን በዚህ ምድር ላይ በሚፈነዳበት ጊዜ ምን ነገር ይከሰታል? ብዙዎች ለመዳን ወደ ይሖዋ ዞር አይሉም። የሰው ዘር በጥቅሉ “ተራራዎችንና ዓለቶችንም:- በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቊጣ ሰውሩን” ይላሉ። (ራእይ 6:15, 16) ተስፋቸውን የሚጥሉት በዚህ የነገሮች ሥርዓት ተራራ መሰል ድርጅቶችና ተቋሞች ላይ ይሆናል። ከዚህ ይልቅ ግን ተወዳዳሪ የማይገኝለት ዓለት በሆነው በይሖዋ አምላክ ላይ እምነታቸውን ቢጥሉ ምንኛ የተሻለ ይሆናል! (ዘዳግም 32:3, 4) ይሖዋን በተመለከተ ንጉሥ ዳዊት “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ዓለቴ፣ አምባዬ፣ መድኃኒቴ” ሲል ተናግሯል። ይሖዋ ‘መድኃኒታችን’ ነው። (መዝሙር 18:2፤ 95:1) ስሙ “የጸና ግምብ ነው”፤ ከሚመጣው ጥፋት ሊከልለን የሚችል በቂ ጥንካሬ ያለው “ግምብ” ነው። (ምሳሌ 18:10) ስለዚህም በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ካሉት ወደ ስድስት ቢልዮን ከሚጠጉ ሰዎች መካከል በተቻለ መጠን ብዙዎች በታማኝነትና በቅንነት የይሖዋን ስም መጥራት መማራቸው ወሳኝ ነው።
15. ከእምነት ጋር በተያያዘ ሮሜ 10:14 ምን ያመለክታል?
15 ሐዋርያው ጳውሎስ በመቀጠል “እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል?” ብሎ መጠየቁ የተገባ ነው። (ሮሜ 10:14) ‘የእምነትን ቃል’ የራሳቸው አድርገው ይሖዋን በመጥራት መዳን እንዲችሉ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ገና በርካታ ሰዎች አሉ። እምነት በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ በሌላ ደብዳቤ ላይ “ያለ እምነትም [አምላክን] ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 11:6) ታዲያ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአምላክ ላይ እምነት ሊያሳድሩ የሚችሉት እንዴት ነው? ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ?” በማለት ይጠይቃል። (ሮሜ 10:14) ይሖዋ መስማት የሚችሉበትን መንገድ ያዘጋጅላቸው ይሆን? እንደሚያዘጋጅላቸው ምንም ጥርጥር የለውም! ጳውሎስ በመቀጠል “ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?” በማለት የተናገራቸውን ቃላት ልብ በሉ።
16. በመለኮታዊ ዝግጅት ውስጥ ሰባኪዎች የግድ አስፈላጊ የሚሆኑት ለምንድን ነው?
16 የጳውሎስ አነጋገር ሰባኪዎች እንደሚያስፈልጉ በግልጽ የሚያሳይ ነው። ኢየሱስ ይህ ሁኔታ “እስከ ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን ድረስ” የሚዘልቅ እንደሆነ አመልክቷል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:18-20 NW) የስብከቱ ሥራ ሰዎች የይሖዋን ስም ጠርተው እንዲድኑ ለመርዳት ከተደረገው መለኮታዊው ዝግጅት መካከል ዋነኛው ክፍል ነው። ሌላው ቀርቶ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች ውድ የሆነውን የአምላክን ስም ለማክበር የሚያደርጉት ምንም ጥረት የለም። ብዙዎቹ ይሖዋን ሊብራራ ከማይችለው ከሁለቱ የሥላሴ ክፍሎች ጋር ያዛምዱታል። ሌሎች ደግሞ መዝሙር 14:1 እና 53:1 ላይ “ሰነፍ በልቡ:- አምላክ የለም ይላል” ብሎ ከገለጸው የሰዎች ቡድን ውስጥ ተሰልፈዋል። ይሖዋ ሕያው አምላክ መሆኑን ማወቅ ይኖርባቸዋል፤ እንዲሁም ሊመጣ ካለው ከታላቁ መከራ እንዲድኑ ስሙ የሚወክላቸውን ነገሮች በሙሉ ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው።
የሰባኪዎቹ ‘የሚያማምሩ እግሮች’
17. (ሀ) ጳውሎስ ተመልሶ ስለመቋቋም የሚናገረውን ትንቢት መጥቀሱ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ‘ያማሩ እግሮች’ እንዲኖሩን ምን ነገር ያስፈልጋል?
17 ሐዋርያው ጳውሎስ እጅግ አስፈላጊ የሆነ አንድ ተጨማሪ ጥያቄ አለው። “መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ?” (ሮሜ 10:15) ጳውሎስ እዚህ ላይ ጠቅሶ የተናገረው ከ1919 ወዲህ ፍጻሜውን ያገኘውን ኢሳይያስ 52:7ን ሲሆን ይህ ተመልሶ መቋቋምን በሚመለከት ከተነገሩት ትንቢቶች አንዱ ነው። ዛሬም ይሖዋ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ “የምስራች የሚናገር፣ ሰላምንም የሚያወራ፣ የመልካምንም ወሬ የምስራች የሚናገር፣ መድኃኒትንም የሚያወራ” ሰው ይልካል። የአምላክ ቅቡዓን ‘ጉበኞች’ እና ባልደረቦቻቸው በታዛዥነት በደስታ እየጮሁ ነው። (ኢሳይያስ 52:7, 8) በዛሬው ጊዜ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መዳንን የሚያወሩ ሰዎች እግሮች የዛሉ እንዲያውም በአቧራ የተሸፈኑ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም የፊታቸው ገጽታ በከፍተኛ የደስታ ስሜት የፈካ ነው! የሰላምን ምሥራች ለማወጅና የሚያለቅሱትን ለማጽናናት እንዲሁም እነዚህ ሰዎች ለመዳን እንዲችሉ የይሖዋን ስም እንዲጠሩ ለመርዳት ይሖዋ እንደላካቸው ያውቃሉ።
18. ምሥራቹን ማሰማት የሚያስገኘውን ውጤት በማስመልከት ሮሜ 10:16-18 ምን ይላል?
18 ሰዎች ‘የሰሙትን ነገር አመኑም’ አላመኑ። የሚከተሉት የጳውሎስ ቃላት እውነት መሆናቸው የተረጋገጠ ነው:- “ባይሰሙ ነው ወይ? እላለሁ። ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ።” (ሮሜ 10:16-18) በፍጥረት ሥራዎቹ ላይ እንደታየው “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር” እንደሚናገሩ ሁሉ በምድር ላይ ያሉት ምሥክሮቹም “የተወደደችውን የእግዚአብሔርን ዓመት አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን . . . የሚያለቅሱትንም ሁሉ” ለማጽናናት ማወጅ አለባቸው።—መዝሙር 19:1-4፤ ኢሳይያስ 61:2
19. ዛሬ ‘የይሖዋን ስም የሚጠሩ’ ወደፊት ምን ያገኛሉ?
19 ታላቁና አስፈሪው የይሖዋ ቀን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አሁን ወደ እኛ ቀርቧል። “ለቀኑ ወዮ! እርሱም ሁሉን ከሚችል ከአምላክ ዘንድ እንደ ጥፋት ይመጣል።” (ኢዩኤል 1:15፤ 2:31) ተጨማሪ እጅግ ብዙ ሰዎች ለምሥራቹ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡና ወደ ይሖዋ ድርጅት እንዲጎርፉ ጸሎታችን ነው። (ኢሳይያስ 60:8፤ ዕንባቆም 2:3) በኖኅና በሎጥ ዘመን እንዲሁም ከዳተኛ በነበሩት በእስራኤልና በይሁዳ ዘመን የይሖዋ ቀናት በክፉ ሰዎች ላይ ያመጡትን ጥፋት አስታውሱ። በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ዓውሎ ነፋስ ክፋትን ሁሉ ከዚህ ምድር ላይ ጠራርጎ በማጥፋት በምትኩ ዘላለማዊ ሰላም የሰፈነበት ገነት የሚመጣበትን ጎዳና የሚጠርግበት ከሁሉም የሚበልጠው ታላቅ መከራ የሚመጣበት የመጨረሻው ደፍ ላይ ቆመናል። በዚያን ጊዜ አንተም በታማኝነት ‘የይሖዋን ስም በሚጠሩ’ ሰዎች መካከል ትገኝ ይሆን? ከሆነ ደስ ይበልህ! እንደምትድን የሚናገረው አምላክ የገባው ቃል ለአንተም ይሠራል።—ሮሜ 10:13
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኋላ ምን አዳዲስ ነገሮች ታወጁ?
◻ ክርስቲያኖች “ለእምነት ቃል” ትኩረት መስጠት ያለባቸው እንዴት ነው?
◻ ‘የይሖዋን ስም መጥራት’ ሲባል ምን ማለት ነው?
◻ የመንግሥቱ መልእክተኞች ‘የሚያምሩ እግሮች’ አላቸው ሲባል ምን ማለት ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የአምላክ ሕዝቦች በፖርቶ ሪኮ፣ በሴኔጋል፣ በፔሩ፣ በፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ አዎን በመላው ዓለም የእርሱን በጎነት እያወጁ ነው