በይሖዋ ታመን!
“ በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን።” — ምሳሌ 3:5
1. የምሳሌ 3:5 ጥቅስ አንድን ወጣት የነካው እንዴት ነበር? እንዴትስ ያለ ለረጅም ጊዜ የቆየ ውጤት አስገኘለት?
አንድ ለረጅም ጊዜ በሚስዮናዊነት አገልግሎት የቆየ ወንድም እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “‘በሙሉ ልብህ በጌታ ታመን፤ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ።’ ለጥየቃ በሄድኩበት አንድ ቤት ውስጥ በፍሬም ተደርገው ግድግዳ ላይ ተሰቅለው የነበሩት እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ትኩረቴን ስበውት ነበር። በዚያን ቀን እነዚህን ቃላት ሳሰላስል ዋልኩ። በሙሉ ልቤ በአምላክ መታመን እችላለሁን? በማለት ራሴን ጠየቅሁ።” ይህ ሰው በዚያን ጊዜ 21 ዓመቱ ነበር። አሁን 90 ዓመት የሆነውና በፐርዝ አውስትራሊያ ሽማግሌ ሆኖ በታማኝነት በማገልገል ላይ የሚገኝ ሲሆን በሲሎን (በአሁኗ ሲሪላንካ)፣ በበርማ (በአሁኗ ማያንማር)፣ በማላያ፣ በታይላድ፣ በሕንድና በፓኪስታን ተመድቦ አዳዲስ ክልሎችን በሚስዮናዊነት ያቀናባቸውን 26 ዓመታት ጨምሮ በሙሉ ልቡ በይሖዋ ላይ መታመኑ ባስገኘው ፍሬ የበለጸገውን ሕይወቱን ወደኋላ መለስ ብሎ በእርካታ መመልከት ይችላል።a
2. ምሳሌ 3:5 በውስጣችን ምን ትምክህት ይገነባል?
2 “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] ታመን።” እነዚህ በምሳሌ 3:5 ላይ የሚገኙት ቃላት እርሱ እንደተራራ ያሉ እንቅፋቶችን እንኳን ለማሸነፍ የሚያስችለንን ጠንካራ እምነት እንደሚሰጠን በመተማመን ሕይወታችንን በሙሉ ልብ ለይሖዋ በመስጠት እንድንቀጥል ሊገፋፉን ይገባል። (ማቴዎስ 17:20) እስቲ ምሳሌ 3:5ን በዙሪያው ካሉት ሐሳቦች ጋር አቀናጅተን እንመርምረው።
አባታዊ መመሪያ
3. (ሀ) ከመጀመሪያዎቹ የምሳሌ መጽሐፍ ዘጠኝ ምዕራፎች ምን ማበረታቻ ይገኛል? (ለ) ለምሳሌ 3:1, 2 ትልቅ ትኩረት መስጠት የሚኖርብን ለምንድን ነው?
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ የመጀመሪያ ዘጠኝ ምዕራፎች አባታዊ መመሪያዎች የተሰጠባቸው ምዕራፎች ናቸው። ገነት በምትሆነው ምድር ላይ “ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት” የመድረስ ወይም በሰማይ የአምላክን ልጅነት የማግኘት ተስፋ ላላቸው ሁሉ የሚጠቅም ከይሖዋ የመጣ የጥበብ ምክር ይዘዋል። (ሮሜ 8:18–21, 23) ወላጆች ልጆቻቸውን በማሳደግ ረገድ ሊጠቀሙበት የሚችሉት የጥበብ ምክር በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ይገኛል። ከእነዚህ ምክሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚታየው በምሳሌ ምዕራፍ 3 ላይ የሚገኘው ምክር ነው። እሱም “ልጄ ሆይ፣ ሕጌን አትርሳ፣ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ” በሚል ማስጠንቀቂያ ይጀምራል። የሰይጣን ክፉ ዓለም የመጨረሻ ቀኖች ወደ ፍጻሜያቸው እየገሰገሱ በሄዱ መጠን ለይሖዋ ማሳሰቢያዎች ከምንጊዜውም የበለጠ ትኩረት እንስጥ። የተጓዝንበት መንገድ ካሰብነው የበለጠ ረጅም ሆኖብን ይሆናል። ይሁን እንጂ ለሚጸኑ ሁሉ “ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ ሰላምም ይጨምሩልሃልና” የሚል ተስፋ ተሰጥቷል። ይህም በይሖዋ አዲስ ሥርዓት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ ማለት ነው። — ምሳሌ 3:1, 2
4, 5. (ሀ) በዮሐንስ 5:19, 20 ላይ የተገለጸው የትኛው አስደሳች ዝምድና ነው? (ለ) በዘዳግም 11:18–21 ላይ ያለው ምክር እስከ ዘመናችን ድረስ የሚሠራው እንዴት ነው?
4 በአባትና በልጅ መካከል የሚኖር አስደሳች ዝምድና ከፍተኛ ግምት ሊሰጠው ይችላል። እንደዚህ እንዲሆን ያደረገው ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከይሖዋ ጋር ስላለው በጣም የተቀራረበ ዝምድና እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። አብ ወልድን ይወዳልና፣ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል።” (ዮሐንስ 5:19, 20) ይሖዋ በእሱና ምድር ላይ ባለው ቤተሰቡ መካከል እንዲሁም በሰብአዊ አባቶችና በልጆቻቸው መካከል ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የተቀራረበ ዝምድና እንዲኖር ዓላማው ነው።
5 በጥንት እስራኤል በቤተሰብ ውስጥ የመቀራረብና የመተማመን ዝምድና እንዲኖር ይፈለግ ነበር። ይሖዋ እንዲህ ሲል አባቶችን መክሯል:- “እንግዲህ እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ፤ እነርሱንም ለምልክት በእጃችሁ ላይ እሰሩአቸው፣ በዓይኖቻችሁም መካከል እንደ ክታብ ይሁኑ። ልጆቻችሁንም አስተምሩአቸው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም ስትነሣም አጫውቱአቸው። እርስዋንም እንዲሰጣቸው እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ በማለላቸው ምድር፣ እንደ ሰማይ ዘመን በምድር ላይ፣ ዘመናችሁ የልጆቻችሁም ዘመን ይረዝም ዘንድ በቤትህ መቃኖችና በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።” (ዘዳግም 11:18–21) እነዚህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ የታላቁ ፈጣሪያችን የይሖዋ አምላክ ቃላት በእርግጥም ከወላጆችና ከልጆቻቸው እንዲሁም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከሚያገለግሉት ሌሎች ሰዎች ጋር በጣም የተቀራረበ ግንኙነት እንዲኖር ያስችላሉ። — ኢሳይያስ 30:20, 21
6. በአምላክና በሰው ፊት ሞገስ ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው?
6 ለአረጋውያንም ሆነ ለወጣት የአምላክ ሕዝቦች የሚሆን አባታዊ የጥበብ ምክር በምሳሌ ምዕራፍ 3 ቁጥር 3 እና 4 ላይ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ምሕረትና [ፍቅራዊ ደግነትና አዓት] እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው በልብህም ጻፋቸው።” ፍቅራዊ ደግነትንና እውነትን በማሳየት ረገድ ይሖዋ አምላክ ከሁሉ የላቀ ነው። መዝሙር 25:10 እንደሚገልጸው “የይሖዋ መንገድ ሁሉ ፍቅራዊ ደግነትና እውነት ነው።” [አዓት] እኛም ይሖዋን በመምሰል እነዚህን ባሕሪዎችና እነዚህ ባሕርዮች ያላቸውን ከክፉ አድራጎት የመከላከል ኃይል እንደ ውድ ንብረት መቁጠር ይኖርብናል። ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው የአንገት ሐብል መጠበቅና ሊፋቅ በማይችል ሁኔታ ልባችን ላይ እንዲቀረጹ ማድረግ ይገባናል። ስለዚህ “አቤቱ ይሖዋ . . . ፍቅራዊ ደግነትህና እውነትህ ዘወትር ይጠብቁኝ” በማለት ከልባችን ልንጸልይ እንችላለን። — መዝሙር 40:11 አዓት
ዘላቂነት ያለው መታመኛ
7. ይሖዋ ትምክህት የሚጣልበት መሆኑን ያሳየው በምን መንገዶች ነው?
7 መታመን የሚለው ቃል በዌብስተርስ ኒው ኮሌጄየት ዲክሽነሪ መሠረት “አንድ ሰው ወይም አንድ ነገር ባለው ባሕርይ፣ ችሎታ፣ ጥንካሬ ወይም እውነተኝነት ላይ እርግጠኛ መሆን ወይም መመካት” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። የይሖዋ ባሕርይ በፍቅራዊ ደግነቱ ላይ በጥብቅ የተመሠረተ ነው። እንዲሁም የገባውን ቃል ለመፈጸም ባለው ችሎታ ላይ ሙሉ ትምክህት ሊኖረን ይችላል። ምክንያቱም ይሖዋ የሚለው ስሙ ራሱ ትልቅ ዓላማ ያለው መሆኑን የሚያሳውቅ ነው። (ዘጸአት 3:14፤ 6:2–8) ይሖዋ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን የብርታትና የኃይል ሁሉ ምንጭ እርሱ ነው። (ኢሳይያስ 40:26, 29) ‘አምላክ ሊዋሽ ስለማይችል’ የእውነት አብነት ነው። (ዕብራውያን 6:18) ስለዚህ አምላካችንና የእውነት ሁሉ ምንጭ በሆነው እንዲሁም በእርሱ የሚታመኑትን ሁሉ ለመጠበቅ ታላላቅ ዓላማዎቹን ወደ ክብራማ ፍጻሜያቸው ለማድረስ የሚያስችል ኃይል ባለው በይሖዋ ላይ የማያወላውል ትምክህት እንድንጥል ተመክረናል። — መዝሙር 91:1, 2፤ ኢሳይያስ 55:8–11
8, 9. በዓለም ላይ በሚያሳዝን ሁኔታ መተማመን የጠፋው ለምንድን ነው? የይሖዋ ሕዝቦችስ ከዚህ ተቃራኒ የሆኑት እንዴት ነው?
8 በዙሪያችን ባለው ወራዳ ዓለም ውስጥ መተማመን በሚያሳዝን ሁኔታ እየጠፋ ነው። ከዚህ ይልቅ ስግብግብነትና በሥልጣን መባለግ በጣም ተስፋፍቷል። ዎርልድ ፕሬስ ሪቪው የተባለው መጽሔት በግንቦት 1993 እትሙ በፊት ለፊት ሽፋኑ ላይ “የሥልጣን ብልግና መስፋፋት፣ በአዲሱ ዓለም ሥርዓት ውስጥ ከአግባብ ውጭ በሆኑ ዘዴዎች ገንዘብ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት” የሚል መልዕክት ይዞ ወጥቶ ነበር። አለአግባብ ገንዘብ ለማግኘት ሲባል በሥልጣን መባለግ ከብራዚል እስከ ጀርመን፣ ከዩናይትድ ስቴትስ እስከ አርጀንቲና፣ ከስፔይን እስከ ፔሩ፣ ከኢጣሊያ እስከ ሜክሲኮ፣ ከቫቲካን እስከ ሩስያ ድረስ ተስፋፍቷል። አዲሱ የዓለም ሥርዓት ተብሎ የሚጠራው የሰው ሥርዓት በጥላቻ፣ በስግብግብነትና በአለመተማመን ላይ የተመሠረተ ስለሆነ የሰውን ዘር መከራዎች ከማባባስ በቀር ምንም የሚያስገኘው ፋይዳ የለም።
9 የይሖዋ ምስክሮች ግን ከፖለቲካ ብሔራት በተለየ ሁኔታ “ይሖዋ አምላኩ የሆነለት ሕዝብ” በመሆናቸው ደስተኞች ናቸው። እንደ እውነቱ ከሆነ በአሜሪካ ገንዘብ ላይ እንደሚገኘው ጽሑፍ “በአምላክ እንታመናለን” ለማለት የሚችሉት እነሱ ብቻ ናቸው። እያንዳንዳቸው “በእግዚአብሔር ቃሉን አመሰግናለሁ . . . በእግዚአብሔር ታመንሁ፣ አልፈራም” በማለት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በደስታ ሊናገሩ ይችላሉ። — መዝሙር 33:12፤ 56:4, 11
10. ብዙ ወጣት ክርስቲያኖች ፍጹም አቋማቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ ያበረታታቸው ምንድን ነው?
10 በሺህ የሚቆጠሩ ወጣት ምስክሮች በታሰሩባትና በአሰቃቂ ሁኔታ በተገረፉባት በአንድ የእስያ አገር ውስጥ ብዙዎች በይሖዋ በመታመናቸው ለመጽናት ችለዋል። አንድ ሌሊት በእስር ቤት ውስጥ አሰቃቂ ግርፋት የደረሰበት አንድ ወጣት ምስክር ከዚህ በላይ በታማኝነት ሊጸና እንደማይችል ተሰማው። ይሁን እንጂ አንድ ሌላ ወጣት እንዳይታይ በጨለማ ተደብቆ መጣና “ተስፋ አትቁረጥ፤ እኔ ክጄ ምንም አላገኘሁም። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ምንም የአእምሮ ሰላም የለኝም” ሲል በሹክሹክታ ነገረው። የመጀመሪያው ወጣትም ጸንቶ ለመቆም ያደረገውን ውሳኔ አደሰ። ሰይጣን ፍጹም አቋማችንን ለመሸርሸር የሚያደርገውን ማንኛውንም ጥረት ታግለን እንድናሸንፍ ይሖዋ እንደሚረዳን ሙሉ ትምክህት ልንጥልበት እንችላለን። — ኤርምያስ 7:3–7፤ 17:1–8፤ 38:6–13, 15–17
11. በይሖዋ ላይ እንድንታመን የተበረታታነው እንዴት ነው?
11 ከትዕዛዞች ሁሉ ፊተኛው የሆነው ትዕዛዝ በከፊል እንዲህ ይነበባል:- “አንተም በፍጹም ልብህ . . . ጌታ [ይሖዋ አዓት] አምላክህን ውደድ።” (ማርቆስ 12:30) የአምላክን ቃል ስናሰላስል የምንማራቸው አስደናቂ እውነቶች ወደ ልባችን ጠልቀው ይገባሉ። በዚህ ጊዜ አስደናቂ አምላካችንና ሉዓላዊ ጌታ ለሆነው ለይሖዋ አገልግሎት ያለንን ሁሉ ለመስጠት እንገፋፋለን። በእርሱ ማዳን ላይ አላንዳች ማወላወል ለመታመን የምንገፋፋው ላስተማረን፣ እስከአሁን ላደረገልንና ወደፊትም ለሚያደርግልን ነገሮች ባለን አድናቆት ልባችን ሲሞላ ነው። — ኢሳይያስ 12:2
12. ባለፉት ዓመታት ብዙ ክርስቲያኖች በይሖዋ ላይ ያላቸውን ትምክህት ያሳዩት እንዴት ነው?
12 እንዲህ ዓይነቱ ትምክህት ቀስ በቀስ ሊኮተኮት ይችላል። ብሩክሊን በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ ከሚያዝያ 1927 ጀምሮ ከ50 ዓመት በላይ በታማኝነት ያገለገለ አንድ ትሑት የይሖዋ ምስክር እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በወሩ መጨረሻ ላይ ለወጪ መሸፈኛ የሚሆን 5 ዶላር፣ የምሳሌ 3:5, 6ን ጥቅስ ከያዘ የሚያምር ካርድ ጋር በፖስታ ታሽጎ ተሰጠኝ። በዋናው መሥሪያ ቤት ውስጥ መሆኔ ይሖዋ በዚህ ምድር ላይ የመንግሥቱን ፍላጎቶች የሚያስፈጽም ‘ታማኝና ልባም ባሪያ’ እንዳለው ለመገንዘብ ስላስቻለኝ በይሖዋ ላይ ለመታመን የሚያስችሉኝ ብዙ ምክንያቶች ነበሩኝ። ማቴዎስ 24:45–47።”b የዚህ ክርስቲያን ልብ ያተኮረው በገንዘብ ፍቅር ላይ ሳይሆን ‘ፈጽሞ ሊጠፋ የማይችል የሰማይ መዝገብ’ በመሰብሰብ ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ በምድር ዙሪያ በሚገኙት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የቤቴል ቤቶች ውስጥ የሚያገለግሉ በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች በድህነት ለመኖር ሕጋዊ መሐላ ይገባሉ። ይሖዋ ዕለታዊ ፍላጎታቸውን እንደሚያሟላላቸው ያምናሉ። — ሉቃስ 12:29–31, 33, 34
በይሖዋ ላይ ተደገፍ
13, 14. (ሀ) ጥሩ ምክር ልናገኝ የምንችለው ከየት ብቻ ነው? (ለ) ስደት ሲያጋጥመን በታማኝነት ለመጽናት የትኛውን ባሕርይ ማስወገድ ያስፈልጋል?
13 ሰማያዊው አባታችን “በራስህ ማስተዋል አትደገፍ” በማለት ይመክረናል። (ምሳሌ 3:5) ዓለማዊ አማካሪዎችና የሥነ ልቦና ጠበብቶች (ሳይኮሎጂስቶች) የይሖዋን ጥበብና ማስተዋል ሊተካከሉ አይችሉም። “ለጥበቡም ቁጥር የለውም።” (መዝሙር 147:5) በዓለም ታላላቅ ሰዎች ጥበብ ወይም ዕውቀት በሚጎድለው የራሳችን ስሜት ላይ ከመደገፍ ይልቅ ከይሖዋ፣ ከቃሉና በጉባኤ ውስጥ ከሚገኙ ሽማግሌዎች ወደሚገኘው ጥሩ ምክር ዞር እንበል። — መዝሙር 55:22፤ 1 ቆሮንቶስ 2:5
14 ሰብአዊ ጥበብ ወይም ታዋቂነት በፍጥነት እየቀረበ ባለው የመከራ ጊዜ ከምንም ነገር አያድነንም። (ኢሳይያስ 29:14፤ 1 ቆሮንቶስ 2:14) በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጃፓን አገር አንድ ጥሩ ችሎታ የነበረው ነገር ግን ትዕቢተኛ የሆነ የአምላክ ሕዝቦች እረኛ በራሱ ማስተዋል ለመደገፍ መረጠ። አንዳንድ ተጽዕኖዎች በደረሱበት ጊዜ ከሐዲ ሆነ። አብዛኞቹም የመንጋው አባሎች በስደቱ ምክንያት እንቅስቃሴያቸውን አቆሙ። አንዲት ታማኝ ጃፓናዊት እኅት በአንዲት ቆሻሻ ጠባብ ክፍል ውስጥ ታስራ የደረሰባትን አሰቃቂ ሁኔታ በድፍረት ተቋቁማ ከወጣች በኋላ እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “በስደቱ ወቅት እስከ ዘለቄታው በታማኝነታቸው የጸኑት ልዩ ችሎታ ያላቸው ወይም ጎላ ብለው የሚታዩ አልነበሩም። ሁላችንም ዘወትር በሙሉ ልባችን በይሖዋ ላይ መታመን ይኖርብናል።”c
15. ይሖዋን ለማስደሰት ከፈለግን ምን አምላካዊ ባሕርይ ያስፈልገናል?
15 በራሳችን ማስተዋል ከመደገፍ ይልቅ በይሖዋ ለመታመን ትሕትና ያስፈልጋል። ትሕትና ይሖዋን ለማስደሰት ለሚፈልጉ ሁሉ ምንኛ አስፈላጊ ነው! አምላካችን የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ጌታ ቢሆንም የማሰብ ችሎታ ካላቸው ፍጥረቶቹ ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ ትሑት ነው። ለዚህም አመስጋኞች ልንሆን ይገባናል። እርሱ “በሰማይና በምድር የተዋረዱትን የሚያይ፤ . . . ችግረኛውን ከመሬት የሚያነሣ” ነው። (መዝሙር 113:6, 7) ከመሐሪነቱ የተነሳ ለሰው ዘር ከሰጣቸው ስጦታዎች በሙሉ በሚበልጠው በተወዳጅ ልጁ በክርስቶስ ኢየሱስ ክቡር ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ድካሞቻችንን ይቅር ይለናል። ለዚህ ይገባናል ለማንለው ደግነት አመስጋኞች መሆን አይገባንምን?
16. ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ ላሉ መብቶች ለመድረስ ሊጣጣሩ የሚችሉት እንዴት ነው?
16 ኢየሱስ ራሱ “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፣ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል” በማለት ያሳስበናል። (ማቴዎስ 23:12) የተጠመቁ ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ ላሉ ኃላፊነቶች ለመብቃት በትሕትና መጣጣር ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ የበላይ ተመልካቾች የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንደማዕረግ መመልከት የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ” ብሎ የተናገረው ኢየሱስ እንዳደረገው የተሰጣቸውን ኃላፊነት በትሕትና፣ በአድናቆትና በጉጉት ለመሥራት እንደሚያስችላቸው አጋጣሚ አድርገው መመልከት ይኖርባቸዋል። — ዮሐንስ 5:17፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3
17. ሁላችንም ምን ነገር መገንዘብ ይኖርብናል? ይህስ ወደ ምን ዓይነት እንቅስቃሴ ይመራናል?
17 ሁላችንም በይሖዋ ዓይን ከአቧራ ቅንጣት በልጠን የማንታይ መሆናችንን ዘወትር በትሕትናና በጸሎት እናስብ። እንግዲያው “የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ፣ ጽድቁም በልጅ ልጆች ላይ” በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን ይገባናል! (መዝሙር 103:14, 17 አዓት) ሁላችንም ትጉህ የአምላክ ቃል ተማሪዎች መሆን ይኖርብናል። በየሳምንቱ ለግል ጥናትና ለቤተሰብ ጥናት እንዲሁም ለጉባኤ ስብሰባዎች የምናጠፋው ጊዜ በጣም ውድ እንደሆነ ነገር መቁጠር ይኖርብናል። በዚህ መንገድ ‘ስለ ቅዱሱ ያለንን እውቀት’ እንገነባለን። “ማስተዋል” ማለት ይህ ነው። — ምሳሌ 9:10
“በመንገድህ ሁሉ . . .”
18, 19. ምሳሌ 3:6ን በሕይወታችን ውስጥ በሥራ ላይ ልናውል የምንችለው እንዴት ነው?
18 የማስተዋል መለኮታዊ ምንጭ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ሲመራን ምሳሌ 3:6 እንዲህ ይላል:- “በምታደርገው ሁሉ እግዚአብሔርን አስቀድም። እርሱም በትክክለኛው መንገድ ይመራሃል።” (የ1980 ትርጉም ) ይሖዋን የሚያስቀድም ሰው ዘወትር ይጸልያል። የትም እንሁን፣ ምንም ዓይነት ሁኔታ ያጋጥመን በጸሎት አማካኝነት ወደ ይሖዋ ለመቅረብ እንችላለን። ዕለታዊ ተግባሮቻችንን ስናከናውን፣ ለመስክ አገልግሎት ስንዘጋጅ፣ መንግሥቱን ለማወጅ ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ ሥራችንን ሁሉ እንዲባርክልን ልንጸልይ እንችላለን። በዚህ መንገድ ፈሪሃ አምላክ ለነበራቸው ለሄኖክ፣ ለኖኅ እና እንደ ኢያሱና ዳንኤል ለመሳሰሉት ታማኝ እስራኤላውያን እንዳደረገው ‘መንገዳችንን እንደሚያቃናልን’ በመተማመን ከፍተኛ የሆነውን ‘አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር የማድረግ’ መብትና ደስታ ልናገኝ እንችላለን። — ዘፍጥረት 5:22፤ 6:9፤ ዘዳግም 8:6፤ ኢያሱ 22:5፤ ዳንኤል 6:23፤ በተጨማሪም ያዕቆብ 4:8, 10ን ተመልከት።
19 ልመናችንን ለይሖዋ ስናስታውቅ ‘አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችንንና አሳባችንን በክርስቶስ ኢየሱስ እንደሚጠብቅ’ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (ፊልጵስዩስ 4:7) ደስተኛ በሆነ ፊት የሚንጸባረቀው ይህ የአምላክ ሰላም በስብከት ሥራችን ወቅት የምናገኛቸው ሰዎች መልእክታችንን እንዲቀበሉ ሊያደርጋቸው ይችላል። (ቆላስይስ 4:5, 6) በተጨማሪም ቀጥሎ ያለው ታሪክ እንደሚያሳየው ዛሬ ባለው ዓለም ውስጥ በጣም በተለመደው ጭንቀት ወይም ግፍ የሚሰቃዩትን ሰዎች ሊያበረታታ ይችላል።d
20, 21. (ሀ) በናዚ ሽብር ወቅት የይሖዋ ምስክሮች ፍጹም አቋም ሌሎችን ያበረታታው እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ ድምፅ ምን ዓይነት ቁርጥ ውሳኔ እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል?
20 ማክስ ሊብስተር የተባለ አይሁዳዊ ሂትለር ካደረሰው እልቂት እንደ ተአምር በሚቆጠር ሁኔታ የተረፈ ነው። ወደ አንድ የናዚ የግድያ ካምፕ ያደረገውን ጉዞ በሚከተሉት ቃላት ገልጿል:- “ሁለት ሰው ብቻ ሊይዙ የሚችሉ በርካታ ትንንሽ ክፍሎች ባሉባቸው የባቡር ፉርጎዎች ውስጥ ተቆልፎብን ነበር። ወደ አንዱ ፉርጎ አዳፍተው ካስገቡኝ በኋላ በፊቱ ላይ የመረጋጋት መንፈስ የሚታይበት አንድ እስረኛ አገኘሁ። ይህ ሰው የታሰረው የአምላክን ሕግ ስላከበረ ነበር። የሌሎች ሰዎችን ደም ከማፍሰስ መታሰር ከዚያም ቢያልፍ ሞት መርጦ ነው። ይህ ሰው የይሖዋ ምስክር ነበር። ልጆቹ ከእሱ ተነጥለው ተወስደውበታል፤ ሚስቱም ተገድላበታለች። እሱም የእሷን እጣ ለመካፈል ይጠብቅ ነበር። የ14ቱ ቀን ጉዞ ለጸሎቴ መልስ አስገኘ። ምክንያቱም የዘላለም ሕይወት ተስፋ ያገኘሁት በዚሁ ወደ ሞት በሚደረገው ጉዞ ወቅት ነው።”
21 ከኦሽዊትዝ የናዚ ማጎሪያ ካምፕ፣ እሱ እንደሚጠራው “ከአንበሳ ጉድጓድ”፣ ከወጣና ከተጠመቀ በኋላ ይህ ወንድም በእስር ቤት የነበረችና አባቷ ደግሞ በዳካው ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የተሰቃየ አንዲት የይሖዋ ምስክር አገባ። አባቷ በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ሳለ ሚስቱና ወጣት ሴት ልጁ ተይዘው እንደታሰሩ ሰማ። የተሰማውን ስሜት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “በጣም ተጨንቄ ነበር። ከዚያም አንድ ቀን ገላዬን ለመታጠብ ተሰልፌ ሳለ ከምሳሌ 3:5, 6 ጠቅሶ የሚናገር አንድ ድምፅ ሰማሁ። ድምፁ ልክ ከሰማይ እንደሚመጣ ሆኖ ተሰማኝ። እንደገና ሚዛኔን እንድጠብቅ ያስቻለኝ ይህ ድምፅ ነበር።” በእርግጥ ድምፁ የሌላ እስረኛ ድምፅ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ አጋጣሚው የአምላክ ቃል ምን ያህል ኃይል ሊሰጠን እንደሚችል ያሳያል። (ዕብራውያን 4:12) ዛሬም የይሖዋ ድምፅ “በፍጹም ልብህ በይሖዋ ታመን” በሚሉት የ1994 የዓመት ጥቅሳችን አማካኝነት በጆሮአችን ያስተጋባ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በታኅሳስ 15, 1973 በእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 760–5 ላይ የወጣውን “በሙሉ ልቤ በይሖዋ መታመን” የሚለውን በክሎድ ኤስ ጉድማን የተነገረውን ርዕስ ተመልከት።
b በሐምሌ 15, 1968 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 437–40 ላይ የወጣውን “ይሖዋን ለማመስገን የተደረገ ቁርጥ ውሳኔ” የሚለውን በሐሪ ፔተርሰን የተነገረውን ርዕስ ተመልከት።
c በመጠበቂያ ግንብ 15–109 ገጽ 3–9 ላይ የወጣውን “ይሖዋ አገልጋዮቹን አይተዋቸውም” የሚለውን በማትስዌ ኢሺ የተነገረውን ርዕስ ተመልከት።
d በተጨማሪም በጥቅምት 1, 1978 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 20–4 “መዳን፣ አመስጋኝ መሆናችንን ማረጋገጥ (ደሊቨራንስ! ፕሩቪንግ አዎርሰልቭስ ግሬትፉል)” በሚል ርዕስ የወጣውን በማክስ ሊብስተር የተነገረውን ትረካ ተመልከት።
ክለሳ
◻ በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ምን ዓይነት ምክር ተሰጥቷል?
◻ በይሖዋ መታመን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
◻ በይሖዋ ላይ መደገፍ ምን ነገሮችን ያጠቃልላል?
◻ በመንገዳችን ሁሉ ይሖዋን ማወቅ ያለብን ለምንድን ነው?
◻ ይሖዋ መንገዳችንን የሚያቃናልን እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አስደሳቹ የመንግሥቱ መልእክት ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ይማርካል