የመናፍቃን ቡድኖች ምንድን ናቸው?
የካቲት 28, 1993 በርካታ ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕፃናት የሚገኙበትን አንድ ሕንፃ ቁጥራቸው ከመቶ በላይ የሆኑ የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ከበቡ። የከበባው ዓላማ በሕገ ወጥነት የተያዙ የጦር መሣሪያዎችን ለመፈተሽና ወንጀለኛ ነው ተብሎ የተጠረጠረን ሰው ለመያዝ ነበር። ይሁን እንጂ ጸጥታ አስከባሪዎቹ እንደ ደረሱ ከሕንፃው ውስጥ የጥይት መዓት ስለ ዘነበባቸው ተደናገጡ። እነርሱም መልሰው ተኮሱ።
በዚህ ግጭት ሳቢያ አሥር ሰዎች ሲሞቱ ብዙዎች ቆሰሉ። በሚቀጥሉት 50 ቀኖች ውስጥ በመቶ የሚቆጠሩ የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች አነስተኛ ጦርነት ለመክፈት የሚበቃ ጦር መሣሪያ ይዘው ዙሪያውን ከበቡ። ከበባው 17 ሕፃናትን ጨምሮ የ86 ሰዎችን ሕይወት በማጥፋት አከተመ።
ይሁን እንጂ ከበባ የተደረገበት ጠላት ማን ነበር? የዕፅ አስተላላፊ ቡድን ነበርን? የደፈጣ ተዋጊዎች ቡድን ነበርን? አልነበረም። ከበባ የተደረገበት “ጠላት” የሃይማኖታዊ አክራሪዎች ኑፋቄ እንደሆነ ሳታውቅ አትቀርም። በወቅቱ በዓለም ዜና ከፍተኛውን ቦታ ይዞ የነበረው አሠቃቂ እልቂት የደረሰው በአሜሪካን በቴክሳስ ክፍለ ሀገር በአንድ ሰዋራ መንደር ውስጥ ነበር። የዜና ማሰራጫዎች አክራሪ ኑፋቄዎች ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋዎች በሚዘግቡ፣ በሚመረምሩና በሚተቹ ጽሑፎችና የሬዲዮ ፕሮግራሞች ተሞልተው ነበር።
የዜና ተከታታዮች ቀደም ባሉት ዓመታት መናፍቃን መሪዎችን በመከተላቸው ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችን እንዲያስታውሱ ተደርገዋል። ከእነዚህም መካከል በ1969 በካሊፎርኒያ ውስጥ ማንሰን የገደላቸው፤ በ1978 በጉያና ጆንስታውን ውስጥ ራሳቸውን እንዲገድሉ የተደረጉ የኑፋቄ አባላት፤ በ1987 ፓክ ሱን ጃ የተባለች ኰሪያዊት የመናፍቃን መሪ ባቀነባበረችው እርስ በርስ የመገዳደል ቃል ኪዳን ራሳቸውንና ሌሎች ሰዎችን የገደሉት 32 የኑፋቄ አባላት ይገኛሉ። የሚያስገርመው እነዚህ ሰዎች ክርስቲያኖች እንደሆኑና በመጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያምኑ መናገራቸው ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚቀበሉ ብዙ ሰዎች እነዚህ መናፍቃን አለምንም እፍረት በቅዱሳን ጽሑፎች አላግባብ ሲጠቀሙ በማየታቸው አዝነዋል። ከዚህም የተነሣ ባለፉት ዓመታት መናፍቃንን ለመቆጣጠርና አደገኛ ድርጊቶቻቸውን ለማጋለጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ድርጅቶች ተቋቁመዋል። የመናፍቃንን ባሕርይ የሚያጠኑ ባለሙያዎች የአዲሱ ሺህ ዓመት መባቻ መቅረብ ለመናፍቃን ድርጅቶች መብዛት ምክንያት እንደሚሆን ይተነብያሉ። አንድ የዜና መጽሔት ፀረ መናፍቃን ድርጅቶች እንደሚሉት “የሰዎችን ሰውነትና አእምሮ ለመቆጣጠር፣ ነፍሳቸውንም ለማበላሸት ዝግጁ የሆኑ በሺህ የሚቆጠሩ መናፍቃን ቡድኖች አሉ። . . . ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ የታጠቁ ሲሆኑ አብዛኞቹ አደገኞች እንደሆኑ ተደርገው የሚቆጠሩ ናቸው። ያታልላሉ፣ ይበዘብዛሉ፣ ያጋባሉ፣ ሥርዓተ ቀብር ይፈጽማሉ” በማለት አትቷል።
የመናፍቃን ቡድን ምንድን ነው?
ብዙ ሰዎች “መናፍቅ” የሚለው ቃል ውስጣዊ ትርጉም ሳይገባቸው እንዲሁ ይጠቀሙበታል። አንዳንድ የሃይማኖት ሊቃውንት ግራ መጋባት እንዳይኖር በማሰብ በቃሉ ከመጠቀም ይቆጠባሉ።
ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒድያ “በመሠረቱ ከልት የሚለው ቃል (የመናፍቃን ቡድን ተብሎ በአማርኛ የተተረጐመው ቃል) ማንኛውንም ዓይነት አምልኮ ወይም የአምልኮ ሥርዓት ያመለክታል” በማለት ያስረዳል። በዚህ መለኪያ መሠረት ሁሉም ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ከልት ወይም መናፍቆች ናቸው ሊባሉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ዛሬ ባለው አጠቃቀም “ከልት” የተባለው የእንግሊዝኛ ቃል የተለየ ትርጉም አለው። ይኸው ኢንሳይክሎፒድያ “ከ19 00ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ወዲህ ከልት የሚለው ቃል በጣም እየተለመደ በመምጣቱ ትርጉሙ ተቀይሯል። በዛሬው ጊዜ ቃሉ አዲስና እንግዳ የሆነ መሠረተ ትምህርትና ልማድ የሚያስተምር፣ አንድን በሕይወት ያለ መሪን የሚከተልን ቡድን ያመለክታል።”
ኒውስዊክ መጽሔት ብዙ ሰው የሚረዳውን የቃሉን አገባብ በመጠቀም “ብዙውን ጊዜ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ፣ ማንነታቸውንና ዓላማቸውን ከአንድ ተአምር አድራጊ ነኝ ከሚል ግለሰብ ጋር ያቆራኙና አክራሪ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ያሉበት ቡድን ነው” በማለት ያስረዳል። በተመሳሳይም ኤሽያዊክ የተባለው መጽሔት “[ከልት] የሚለው ቃል ትርጉም ግልጽ ባይሆንም ብዙውን ጊዜ ራሱን አምላክ ነኝ በሚል በአንድ ተአምር አድራጊ መሪ ላይ የተመሠረተን አዲስ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ያመለክታል” ይላል።
በአሜሪካን አገር የሚገኘው የሜሪላንድ ስቴት 100ኛ ጉባኤ ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ ከልት በሚለው ቃል የተጠቀመው በዚህ መጥፎነትን በሚያመለክተው ትርጉሙ ነው። የተላለፈው ውሳኔ “የመናፍቃን ቡድን ማለት ለአንድ ቡድን ወይም ለአንድ ሰው ወይም ሐሳብ ከልክ ያለፈ ስሜት ያለው፣ የመሪዎቹን ዓላማ ለማሳካት ሲል ከሥነ ምግባር ውጭ በሆኑ ዘዴዎች የሰዎችን አእምሮ የሚቆጣጠርና የሚያሳምን ቡድን ወይም እንቅስቃሴ ነው” ይላል።
የመናፍቃን ቡድኖች በአብዛኛው ከተለመዱትና ተቀባይነት ካገኙት የማኅበረሰቡ ጠባዮች ጋር የሚጋጩ ቅጥ የለሽ አመለካከቶችና ልማዶች ያሏቸው ሃይማኖታዊ ቡድኖች ተደርገው ይታያሉ። ብዙውን ጊዜ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴያቸውን የሚያካሂዱት በድብቅ ነው። እንደነዚህ ካሉት የመናፍቃን ቡድኖች አብዛኞቹ ራሳቸውን ከኅብረተሰቡ ያገልላሉ። ራሱን በራሱ ለሾመው ሰብአዊ መሪያቸው በግትርነትና አለምንም ማወላወል ይገዛሉ። ብዙውን ጊዜ እነዚህ መሪዎች በአምላክ እንደተመረጡ ወይም ራሳቸው መለኮታዊ ባሕርይ እንዳላቸው በትምክህት ይናገራሉ።
አልፎ አልፎ ፀረ መናፍቃን የሆኑ ድርጅቶች እና የዜና ማሰራጫዎች የይሖዋ ምስክሮችን የመናፍቃን ቡድን ናቸው ይላሉ። በቅርብ ጊዜ የታተሙ ጋዜጦች ምስክሮቹን በአጠያያቂ ድርጊቶቻቸው ከሚታወቁ የሃይማኖት ቡድኖች ጋር ደምረዋቸዋል። ነገር ግን የይሖዋ ምስክሮችን በቁጥር አነስተኛና እምብዛም ያልታወቀ ሃይማኖት አባላት እንደሆኑ አድርጎ መቁጠር ትክክል ነውን? የመናፍቃን ቡድን አባሎች ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን ከጓደኞቻቸው፣ ከቤተሰባቸው እና በአጠቃላይ ከማኅበረሰቡ ያገልላሉ። የይሖዋ ምስክሮች እንደዚህ ያደርጋሉን? ምስክሮቹ አባሎቻቸውን የሚመለምሉት አታላይና ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ዘዴ በመጠቀም ነውን?
የመናፍቃን ቡድን መሪዎች የተከታዮቻቻውን አእምሮ ለመቆጣጠር በሚያስችሉ ዘዴዎች እንደሚጠቀሙ የታወቀ ነው። የይሖዋ ምስክሮች እንዲህ እንደሚያደርጉ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ይኖራልን? አምልኮታቸውን የሚያከናውኑት ተደብቀው ነውን? አንድን ሰብአዊ መሪ የሚከተሉና የሚያከብሩ ናቸውን? በግልጽ ለመናገር ያህል፣ የይሖዋ ምስክሮች መናፍቃን ናቸውን?
[ምንጭ]
Jerry Hoefer/Fort Worth Star Telegram/Sipa Press