የይሖዋ ምስክሮች መናፍቃን ናቸውን?
ኢየሱስ ክርስቶስ ጠጪ፣ በላተኛ፣ ሰንበት የማያከብር፣ ሐሰተኛ ምስክር፣ አምላክን የሚሳደብ እና የሰይጣን መልእክተኛ ተብሎ ተከስሶ ነበር። ሕዝቡን ያጣምማል ተብሎም ነበር።—ማቴዎስ 9:34፤ 11:19፤ 12:24፤ 26:65፤ ዮሐንስ 8:13፤ 9:16፤ 19:12
ከኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በኋላም በደቀ መዛሙርቱ ላይ ከባድ ክሶች ቀርበው ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበሩት ክርስቲያኖች መካከል ‘እነዚህ ሰዎች ዓለምን አውከዋል’ ብለው በሚጮሁ ሰዎች ተጐትተው ወደ ከተማይቱ ገዥዎች የቀረቡ ነበሩ። (ሥራ 17:6) በሌላም ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስና ጓደኛው ሲላስ ወደ ባለ ሥልጣኖች ተወስደው የፊልጵስዩስን ከተማ እጅግ አናውጠዋል ተብለው ተከስሰው ነበር።—ሥራ 16:20
ከዚያ ቆየት ብሎም ጳውሎስ “በሽታ ሆኖ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ሁከት” አስነሥቷል “መቅደስንም ደግሞ ሊያረክስ” ይሞክራል ተብሎ ተከስሶ ነበር። (ሥራ 24:5, 6) በሮም ይገኙ የነበሩት የአይሁድ ታላላቅ ሰዎች “ስለዚህ ወገን በየስፍራው ሁሉ እንዲቃወሙ በእኛ ዘንድ ታውቋል” በማለት የኢየሱስ ተከታዮች የነበሩበትን ሁኔታ በትክክል ገልጸዋል።—ሥራ 28:22
አንዳንድ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተውን ይህን አዲስ ቡድን በወቅቱ በኅብረተሰቡ የተለመደውንና ተቀባይነት ያገኘውን ምግባር የሚቃወም አክራሪ አመለካከትና ልማድ ያለው ሃይማኖታዊ ቡድን እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩ እንደነበረ ግልጽ ነው። ዛሬ የሚገኙ ብዙ ሰዎች እነዚህን ክርስቲያኖች ጉዳት የሚያደርሱ መናፍቃን ናቸው ሊሉ እንደሚችሉ አያጠራጥርም። ከሳሾቹ ብዙውን ጊዜ በኅብረተሰቡ ውስጥ የታወቁና የተከበሩ ሰዎች መሆናቸው ለክሱ ተጨማሪ ክብደት ሰጥቶታል። በኢየሱስና በደቀ መዛሙርቱ ላይ ተነሥተው የነበሩትን ክሶች ብዙ ሰዎች ተቀብለዋቸው ነበር። ይሁን እንጂ የተነሡት ክሶች በሙሉ ሐሰት እንደሆኑ የታወቀ ነው። እነዚህን ነገሮች ሰዎች ስለ ተናገሯቸው ብቻ እውነት ሊሆኑ አልቻሉም።
ዛሬስ? የይሖዋ ምስክሮች ከተለመደውና ተቀባይነት ካገኘው የማኅበረሰብ ጠባይ ጋር የሚጋጭ የከረረ አመለካከትና ልማድ ያላቸው የሃይማኖት ቡድን ናቸው ማለት ትክክል ነውን? የይሖዋ ምስክሮች የመናፍቃን ቡድን ናቸውን?
ማስረጃዎቹ ምን ያሳያሉ?
በሩስያ ውስጥ አንድ የሴንት ፒተርስበርግ ከተማ የመንግሥት ባለ ሥልጣን “የይሖዋ ምስክሮች ጨለማን ተገን አድርገው የሚንቀሳቀሱ፣ ሕፃናትን የሚያርዱና ራሳቸውን የሚገድሉ ሕቡዕ ድርጅት ናቸው ተብሎ ይነገረን ነበር” ብለዋል። ይሁን እንጂ የሩስያ ሕዝብ በቅርብ ዓመታት ስለ ይሖዋ ምስክሮች ጠባይ በተሻለ ሁኔታ ለማወቅ የሚያስችለው አጋጣሚ አግኝቷል። ከላይ የተጠቀሱት ባለ ሥልጣን ከይሖዋ ምስክሮች ትልቅ ስብሰባ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጉዳዮችን ከፈጸሙ በኋላ “አሁን ከማንኛውም ሰው ያልተለዩ፣ ፈገግታ ያላቸው፣ እንዲያውም ከማውቃቸው ብዙ ሰዎች የተሻሉ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ሰላማውያንና ረጋ ያሉ ሰዎች ናቸው። እርስ በርሳቸው በጣም ይዋደዳሉ” በማለት የተመለከቱትን ተናግረዋል። ጨምረውም “ሰዎች ስለ እነርሱ እንደዚህ ያለ ውሸት ለምን እንደሚናገሩባቸው ሊገባኝ አይችልም” ብለዋል።
የይሖዋ ምስክሮች የአምልኮ ሥርዓት ብቻ የሚፈጸምበት ስብሰባ አያካሂዱም። አምልኮታቸውም በድብቅ የሚደረግ አይደለም። የይሖዋ ምስክር ያልሆኑት ጁልያ ሚሸል ኮርቤ የተባሉት ደራሲ “ብዙውን ጊዜ በሳምንት ከአንድ ጊዜ በላይ በመንግሥት አዳራሾቻቸው (የስብሰባ ቦታቸው ቤተ ክርስቲያን ተብሎ አይጠራም) ሲሰበሰቡ አብዛኛው የስብሰባ ጊዜ የሚያልፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ውይይት ነው” ብለዋል። በመሰብሰቢያ ቦታዎቻቸው ላይ ማንም ሊያነበው የሚችል ጽሑፍ ይደረግበታል። ስብሰባዎቹ ለሁሉም ሰው ክፍት ስለሆኑ ማንኛውም ሰው መሰብሰብ ይችላል። ሳይጋበዙ የሚመጡ እንግዶች ጥሩ አቀባበል ይደረግላቸዋል።
ኮርቤ ሪሊጅን ኢን አሜሪካ በተባለው መጽሐፋቸው “ምስክሮቹ በሐቀኝነታቸው፣ በትሕትናቸው እና በታታሪነታቸው ጥሩ ስም ያተረፉ ናቸው” በማለት ጨምረው ተናግረዋል። ምስክሮች ያልሆኑ ብዙ ሰዎች በይሖዋ ምስክሮች ዘንድ ስውር ወይም ቅጥ ያጣ ነገር እንደሌለ ለማወቅ ይችላሉ። አኗኗራቸው ኅብረተሰቡ ከለመደውና ከተቀበለው ጠባይ ጋር አይጋጭም። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ ምስክሮቹ “በግል ጠባያቸው ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃ መጠበቅ አለብን ይላሉ” በማለት በትክክል ተናግሯል።
በአሜሪካ አገር የሚገኙ የአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ የዜና እና የልዩ ዝግጅት ክፍል ዲሬክተር ስለ ምስክሮቹ የተዛባ ሪፖርት ይዞ ለ60 ደቂቃዎች ስለቀረበ የቴሌቪዥን ዜና እንዲህ በማለት ለይሖዋ ምስክሮች ጽፈው ነበር። “ብዙ ሰዎች በእናንተ እምነት ቢኖሩ ኖሮ አገሪቱ ዛሬ በምትገኝበት ሁኔታ ላይ አትወድቅም ነበር። ድርጅታችሁ በፍቅርና በፈጣሪ ላይ ባለው ጠንካራ እምነት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ የማውቅ ጋዜጠኛ ነኝ። ሁሉም ጋዜጠኞች የተጣመመ አመለካከት ያላቸው አለመሆናቸውን እንድታውቁ እፈልጋለሁ።”
በሰፊው የታወቀ ሃይማኖት ነው
የይሖዋ ምስክሮች በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ሃይማኖታዊ ቡድን ናቸው ማለት ተገቢ ነውን? የይሖዋ ምስክሮች ከአንዳንድ ሃይማኖቶች ጋር ሲወዳደሩ በቁጥር አነስተኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው” በማለት የተናገረውን አስታውስ።—ማቴዎስ 7:13, 14
ያም ሆነ ይህ ምስክሮቹ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ የመናፍቃን ስብስብ አይደሉም። በ1993 የፀደይ ወራት ከ11 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች ምስክሮቹ በሚያከብሩት የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተው ነበር። በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ዝና ያስገኘላቸው ግን ከቁጥራቸው ብዛት ይልቅ ጠባያቸውና ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ባሕርያቸው ነው። ብዙ አገሮች ሕጋዊ እውቅና ያገኘ ሃይማኖታዊ ድርጅት እንደሆነ እንዲመዘግቡ ያደረጋቸው ይህ ጠባያቸው ለመሆኑ ጥርጥር የለውም።
የአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በቅርቡ ያደረገው ውሳኔ ሊጠቀስ የሚገባው ነው። ምስክሮቹ የሐሳብ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት ነፃነት እንዲሁም ስለ እምነታቸው ለሌሎች የመናገርና የማስተማር መብት አላቸው በማለት ወስኗል። የይሖዋ ምስክሮች አታላዮችና ሥነ ምግባር በጎደለው ዘዴ አባሎቻቸውን የሚመለምሉ ወይም በተለያዩ ዘዴዎች የተከታዮቻቸውን አእምሮ የሚቆጣጠሩ ቢሆኑ ኖሮ የአውሮፓ ኮሚሽን እንደዚህ የመሰለ ውሳኔ አያስተላልፍም ነበር።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ብዙ ሰዎች የይሖዋ ምስክሮችን በደንብ ያውቃሉ። ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት ላይ ያሉትን ወይም በአንድ ወቅት ያጠኑ የነበሩትን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አእምሯችሁን ለማጠብ ወይም አስተሳሰባችሁን ለመቆጣጠር የተጠቀሙበት ዘዴ ነበርን? ብለን እንጠይቃለን። ምስክሮቹ አእምሯችሁን ለመቆጣጠር በሚያስችል ዘዴ ተጠቅመውባችሁ ነበርን? ግልጽ የሆነው መልሳችሁ “አልነበረም” የሚል እንደሚሆን አያጠራጥርም። እንደነዚህ ባሉ ዘዴዎች ተጠቅመው ቢሆን ኖሮ የይሖዋ ምስክሮች ጉዳት ያደረሱባቸው ብዙ ሰዎች ይኖሩ ነበር። የይሖዋ ምስክሮችን ደግፈው የሚናገሩ ሰዎች አይኖሩም ነበር።
“ሰዎችን በሚጠቅም ሥራ የተጠመዱ ናቸው”
የመናፍቃን ቡድን አባላት ብዙውን ጊዜ ከቤተሰብ፣ ከጓደኞችና በአጠቃላይ ከኅብረተሰቡ ራሳቸውን የሚያገልሉ ናቸው። የይሖዋ ምስክሮችስ እንዲህ ያደርጋሉን? በቼኮዝላቫኪያ ሪፑብሊክ የሚገኝ አንድ ጋዜጠኛ “እኔ የይሖዋ ምስክር አይደለሁም። ሆኖም [የይሖዋ ምስክሮች] በጣም ጠንካራ የሆነ ሥነ ምግባር እንዳላቸው ግልጽ ነው። . . . የመንግሥት ባለ ሥልጣኖችን አይቃወሙም። ይሁን እንጂ የሰው ልጆችን ችግሮች ሁሉ የማስወገድ ችሎታ ያላት የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነች ያምናሉ። እንዲህም ሆኖ ምክንያተ ቢሶችና ጭፍኖች አለመሆናቸውን ልብ በሉ። ሰዎችን በሚጠቅም ሥራ የተጠመዱ ናቸው” በማለት ጽፏል።
በተጨማሪም ራሳቸውን ከዘመዶችና ከሌሎች ሰዎች አግልለው ለብቻቸው አይኖሩም። የይሖዋ ምስክሮች ቤተሰቦቻቸውን ማፍቀርና መንከባከብ ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታቸው እንደሆነ ያምናሉ። ሁሉም ዓይነት ዘርና ሃይማኖት ካላቸው ሰዎች ጋር አብረው ይኖራሉ፣ አብረውም ይሠራሉ። የተፈጥሮ አደጋዎች ሲደርሱ የሚያስፈልጉትን ነፍስ አድን ቁሳቁሶችና ሌሎች ጠቃሚ እርዳታዎች ይዘው በአፋጣኝ ይደርሳሉ።
ከሁሉም በላይ የሚያካሂዱት የትምህርት ፕሮግራም ተወዳዳሪ የሌለው ነው። እያንዳንዱን የማኅበረሰብ አባል በተደራጀ ሁኔታ የመጐብኘት ፕሮግራም ያላቸው ሃይማኖቶች ስንት ናቸው? የይሖዋ ምስክሮች ከ200 በሚበልጡ አገሮችና ከ200 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይህንን ያደርጋሉ። በግልጽ እንደሚታየው የይሖዋ ምስክሮች “ሰዎችን በሚጠቅም ሥራ የተጠመዱ ናቸው።”
መጽሐፍ ቅዱስን በጥብቅ ይከተላሉ
የይሖዋ ምስክሮች ትምህርት በቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ ከሚሰጠው ትምህርት የተለየ መሆኑ የታመነ ነው። የይሖዋ ምስክሮች ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነና ኢየሱስ የይሖዋ ልጅ እንጂ የሥላሴያዊ አምላክ አንድ ክፍል አለመሆኑን ያምናሉ። እምነታቸው በሥቃይ ላይ ለሚገኘው የሰው ልጅ እፎይታ የምታመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነች ባላቸው እምነት ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ ብልሹ የነገሮች ሥርዓት በቅርቡ እንደሚጠፋ ሰዎችን ያስጠነቅቃሉ። አምላክ ለታዛዥ የሰው ልጆች ስለገባው ተስፋ ማለትም ገነት ስለምትሆነዋ ምድር ይሰብካሉ። መስቀልን እንደ ቅዱስ ነገር አያከብሩም። የገናን በዓል አያከብሩም። የሰው ነፍስ ሟች እንደሆነች ስለሚያምኑ የማሠቃያ ሲኦል አለ ብለው አያምኑም። ደም አይበሉም ወይም በደም ስራቸውም ቢሆን አይወስዱም። በፖለቲካ ውስጥ ከመጠላለፍና በጦርነት ከመካፈል ይርቃሉ። የይሖዋ ምስክሮች ትምህርት ከሌሎቹ የተለየ የሆነው ለምንድን ነው ብለህ ራስህን ጠይቀህ ታውቃለህን?
ዴይሊ ሃምሻየር ጋዜት የተባለው የማሳቹሴት ጋዜጣ “ጥብቅ የሆነው የይሖዋ ምስክሮች የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጐም ሌሎች መጥፎ እንደሆኑ የማይቆጥሯቸውን ድርጊቶች እንዳይፈጽሙ ይከለክላቸዋል። . . . ጥረታቸው ሁሉ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን ምሳሌና የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል መከተል ነው” በማለት አስረድቷል። ዘ ኢንሳይክሎፒድያ ኦቭ ሪሊጅን “እምነታቸው በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው። ስለ እያንዳንዱ እምነታቸው ‘የጥቅስ ድጋፍ’ ያቀርባሉ (ማለትም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ድጋፍ የሚሆን ጥቅስ ይጠቅሳሉ)። እንዲህ በማድረግም በወግ ፋንታ መጽሐፍ ቅዱስ የሚላቸውን ያለ ምንም ጥያቄ ይቀበላሉ” በማለት ተመሳሳይ ሐሳብ ይሰጣል። ሪሊጅን ኢን አሜሪካ የተባለው መጽሐፍ “ቡድኑ አንድም ጊዜ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከሚሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ዘወር ብሎ አያውቅም። ትምህርቶቹም ከቅዱሳን ጽሑፎች በብዛት በሚጠቀሱ ማስረጃዎች የተደገፈና የተብራራ ነው” በማለት ጽፏል።
መሪያቸው ማን ነው?
የይሖዋ ምስክሮች እንደ አብዛኞቹ የመናፍቃን ቡድኖች ሰብአዊ መሪዎችን ከመጠን በላይ የማያከብሩትና እንደ ጣዖት የማያመልኩት ቅዱሳን ጽሑፎችን በጥብቅ ስለሚከተሉ ነው። በካህናትና በምዕመናን መካከል የሚደረገውን ልዩነት አይቀበሉም። ዘ ኢንሳይክሎፒድያ ኦቭ ሪሊጅን ስለ ይሖዋ ምስክሮች ሲናገር በመካከላቸው “የካህናት መደብና በልዩ የማዕረግ ስሞች መጠራት የለም” ብሏል።
መሪያቸውና የክርስቲያን ጉባኤ ራስ አድርገው የሚከተሉት ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። “እናንተ ግን መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ። አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ። ሊቃችሁ [መሪያችሁ አዓት] አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና ሊቃውንት [መሪዎች አዓት] ተብላችሁ አትጠሩ” በማለት የተናገረው ኢየሱስ ነበር።—ማቴዎስ 23:8–12
ኢየሱስ በላተኛና ጠጪ እንዳልነበረ ሁሉ የይሖዋ ምስክሮችም የመናፍቃን ቡድን አለመሆናቸው ግልጽ ነው። ስለ ኢየሱስ እና ስለ ደቀ መዛሙርቱ ይነገር የነበረውን የሐሰት ወሬ የሰሙት ሰዎች በሙሉ በዚህ ስም የማጥፋት ወጥመድ ውስጥ እንዳልገቡ የታወቀ ነው። አንዳንዶቹ በተሳሳተ ወሬ የተታለሉ ነበሩ። ስለ ይሖዋ ምስክሮች ማንነትና ስለ እምነታቸው ጥያቄ ካለህ ጠጋ ብለህ ለማወቅ ለምን አትሞክርም? እውነትን ለሚፈልጉ ሁሉ የመንግሥት አዳራሾቻቸው ክፍት ናቸው።
ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ለማግኘት ከሚያደርጉት ጥንቃቄ የሞላበት ምርምር አንተም ልትጠቀምና “በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኗል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደነዚህ ያሉትን ይሻልና” በማለት ኢየሱስ ከተናገራቸው ቃሎች ጋር በመስማማት አምላክን እንዴት ልታመልከው እንደምትችል ተማር።—ዮሐንስ 4:23