ይሖዋ ዓላማውን እንደሚፈጽም ሙሉ እምነት ይኑራችሁ
“ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29
1. ይሖዋ ለሰዎችና ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
ይሖዋ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የሆኑትን አዳምንና ሔዋንን ፍጹም አድርጎ ሠርቷቸው ነበር። ሕጎቹን ከታዘዙ በምድር ላይ ለዘላለም መኖር እንዲችሉ አድርጎም ፈጥሯቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:26, 27፤ 2:17) ከዚህም በተጨማሪ አምላክ ገነት በሆነ አካባቢ አኖራቸው። (ዘፍጥረት 2:8, 9) ይሖዋ “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም” አላቸው። (ዘፍጥረት 1:28) ስለዚህ ዘሮቻቸው ከጊዜ በኋላ በምድር ሁሉ ላይ ስለሚሰራጩ ይህች ፕላኔት ፍጹም በሆኑ ደስተኛ የሰው ዘሮች የተሞላች ገነት ትሆን ነበር። ሰብአዊው ቤተሰብ የተጀመረው በጣም ግሩም በሆነ ሁኔታ ነበር። “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፣ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ።”—ዘፍጥረት 1:31
2. ሰዎች ያሉበት ሁኔታ ምን ጥያቄዎች ያስነሣል?
2 ይሁን እንጂ የሰው ልጅ በኖረባቸው በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ያሳለፋቸው ሁኔታዎች ከአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ጋር ምንም ዓይነት ተመሳሳይነት የላቸውም። የሰው ዘር ከፍጽምናና ከደስተኛነት እጅግ በጣም የራቀ ነው። የዓለም ሁኔታዎች አስጨናቂ ከመሆናቸውም በላይ በጊዜያችን በትንቢት እንደተነገረው እጅግ በጣም ተባብሰዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5, 13) ታዲያ አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ በቅርብ ጊዜ ተፈጻሚነቱን ያገኛል ብለን እንዴት በሙሉ ልብ ልንተማመን እንችላለን? አስጨናቂዎቹ ሁኔታዎች ወደፊትም ለረዥም ዘመናት ይቆዩ ይሆንን?
መጥፎ ሁኔታዎች እንዲኖሩ ምክንያት የሆነው ምንድን ነው?
3. ይሖዋ የሰውን ዘር ዓመፅ ወዲያውኑ ያላስቆመው ለምንድን ነው?
3 በመንፈስ አነሣሽነት ስለ ተጻፈው የአምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት ያላቸው ሰዎች እነዚህ መጥፎ ሁኔታዎች በምድር ላይ እንዲኖሩ ይሖዋ የፈቀደበትን ምክንያት ያውቃሉ። እነዚህን መጥፎ ሁኔታዎች እንዴት እንደሚያስወግድም ጭምር ያውቃሉ። እነዚህ ሰዎች የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አምላክ ለሰው ልጆች የሰጣቸውን አስደናቂ የሆነ የነፃ ምርጫ ስጦታ አላግባብ እንደተጠቀሙበት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከሰፈረው ታሪክ ተረድተዋል። (ከ1 ጴጥሮስ 2:16 ጋር አወዳድር።) በተሳሳተ መንገድ ከአምላክ ነፃ ለመሆን መረጡ። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 2 እና 3) የሠሩት ዓመፅ እንደሚከተሉት ያሉትን ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ጥያቄዎች አስነሥቷል። የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ሰዎችን የመግዛት መብት አለውን? ለእነርሱስ የሚሻላቸው የአምላክ አገዛዝ ነውን? ሰዎች ከአምላክ ቁጥጥር ውጭ ሆነው ራሳቸውን ማስተዳደራቸው ያዋጣቸዋልን? ለእነዚህ ጥያቄዎች የተረጋገጠ ምላሽ ለማግኘት የሚቻለው የሰው አገዛዝ ለብዙ መቶ ዘመናት እንዲቀጥል ከተፈቀደ ብቻ ነው። ውጤቱ ሰዎች ከፈጣሪያቸው ተነጥለው ራሳቸውን ማስተዳደራቸው የተሳካ ውጤት እንደማያስገኝ በማያሻማ መንገድ አረጋግጧል።
4, 5. (ሀ) ሰዎች የአምላክን አገዛዝ አንቀበልም ማለታቸው ምን ውጤት አስከተለ? (ለ) ረዘም ያለ ጊዜ እንዲያልፍ መፈቀዱ በማያሻማ መንገድ ያሳየው ነገር ምንድን ነው?
4 አዳምና ሔዋን አምላክን ከተዉ በኋላ በፍጽምና እንዲኖሩ አላደረጋቸውም። የእርሱን ድጋፍ ስላጡ ማርጀት ጀመሩ። ውጤቱ አለፍጽምና፣ እርጅናና በመጨረሻም ሞት ሆነ። በዘር ውርሻ ሕግ መሠረት የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ለዘሮቻቸው በሙሉ፣ ለእኛም ጭምር ይህንኑ ጎጂ ባሕርይ አስተላለፉ። (ሮሜ 5:12) በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት የቆየው የሰው አገዛዝስ ውጤቱ ምን ሆነ? መክብብ 8:9 “ሰው ሰውን ለመጉዳት ገዢ የሚሆንበት ጊዜ አለ” በማለት እንደ ተናገረው ከፍተኛ ችግር አስከትሏል።
5 ያለፉት ዘመናት ሰዎች ከፈጣሪያቸው ተነጥለው በተሳካ ሁኔታ ጉዳዮቻቸውን ሊመሩ እንደማይችሉ ሙሉ በሙሉ አረጋግጠዋል። በመንፈስ ተነሣስቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን መጽሐፍ የጻፈው ኤርምያስ “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” በማለት ተናግሯል።—ኤርምያስ 10:23፤ ዘዳግም 32:4, 5፤ መክብብ 7:29
የአምላክ ዓላማ አልተለወጠም
6, 7. (ሀ) በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ያለፈው የሰው ታሪክ የይሖዋን ዓላማ ለውጦታልን? (ለ) በይሖዋ ዓላማ ውስጥ የተካተተው ነገር ምንድን ነው?
6 በሰው ታሪክ ውስጥ በክፋትና በመከራ የተሞሉት ያለፉት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት የአምላክ ዓላማ እንዲለወጥ አድርገዋልን? ቃሉ “ሰማያትን የፈጠረ እግዚአብሔር፣ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፣ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ” መሆኑን ይናገራል። (ኢሳይያስ 45:18) ስለዚህ አምላክ ምድርን የሠራት የሰዎች መኖሪያ እንድትሆን በማሰብ ስለነበረ እስከ አሁን ድረስ የእሱ ዓላማ አልተለወጠም።
7 ይሖዋ ምድር የሰው መኖሪያ እንድትሆን ብቻ ሳይሆን ፍጹማን የሆኑ ደስተኛ ሕዝቦች የሚኖሩባት ገነት እንድትሆን ዓላማው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ጽድቅ የሚኖርባት አዲስ ምድር” ማለትም አዲስ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ እንደሚቋቋም ትንቢት የተናገረው ለዚህ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:13) በተጨማሪም በራእይ 21:4 ላይ የአምላክ ቃል በአዲሱ ዓለም ውስጥ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኞቻቸው [ከሰው ልጆች ዓይን] ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም” በማለት ይነግረናል። ኢየሱስ በምድር ላይ የሚመጣውን አዲስ ዓለም “ገነት” ብሎ ሊጠራ የቻለው በዚህ ምክንያት ነው።—ሉቃስ 23:43
8. ይሖዋ ዓላማውን ሙሉ በሙሉ እንደሚፈጽም እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
8 ይሖዋ ሁሉን ቻይና ሁሉን የሚያውቅ የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ ስለሆነ ማንም ዓላማውን ሊያጨናግፍበት አይችልም። “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሎአል፦ እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፣ እንደ አሰብሁም እንዲሁ ይቆማል።” (ኢሳይያስ 14:24) ስለዚህ አምላክ ይህችን ምድር በፍጹማን ሰዎች የምትሞላ ገነት አደርጋታለሁ ካለ ይህ ቃሉ ሳይፈጸም አይቀርም። ኢየሱስ “የዋሆች ብፁዓን [ደስተኞች አዓት] ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና” ብሏል። (ማቴዎስ 5:5፤ ከመዝሙር 37:29 ጋር አወዳድር።) በዚህ ተስፋ ሙሉ በሙሉ ልንታመንና በእርግጠኝነት ልንጠብቅ እንችላለን። እንዲያውም ለዚህ ተስፋ ስንል ሕይወታችንን እንኳ እስክንሠዋ ድረስ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
በይሖዋ ተማምነው ነበር
9. አብርሃም በይሖዋ ላይ እንደሚተማመን የሚያሳይ ምን ነገር አደረገ?
9 የሰው ልጅ በኖረባቸው ዘመናት ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ብዙ ሰዎች አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ ሙሉ በሙሉ እንደሚፈጽም እርግጠኞች ስለነበሩ ለዚህ ተስፋቸው ሕይወታቸውን እስከመሠዋት ደርሰዋል። የነበራቸው እውቀት የተመጠነ ቢሆንም በአምላክ ላይ ሙሉ በሙሉ ተማምነዋል። መላ ሕይወታቸው የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ እንዲያተኩር አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከ2,000 ዓመት በፊት፣ እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ መጻፍ ከመጀመሩ በፊት፣ አብርሃም የሚባል ሰው ነበር። ይሖዋ የሰጣቸውን ተስፋዎች እንደሚፈጽም እርግጠኛ ነበር። አብርሃም ስለ ፈጣሪ ሊያውቅ የቻለው ከኖኅ ከተማረው ከቅደመ አያቱ ከሴም ሳይሆን አይቀርም። ስለዚህ አምላክ ሀብታም የነበረችውን የከለዳውያንን ዑር ለቅቆ እንዲወጣና ወደማያውቀውና አደገኛ ወደሆነ ምድር እንዲሄድ ሲነግረው ይህ ጥንታዊ የእስራኤላውያን አባት በይሖዋ መተማመን እንደሚችል ስላወቀ ከተማዋን ትቶ ሄደ። (ዕብራውያን 11:8) በዚህ ጊዜ ይሖዋ “ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ” ብሎታል።—ዘፍጥረት 12:2
10, 11. አብርሃም አንድያ ልጁን ይስሐቅን ለመሠዋት ፈቃደኛ የሆነው ለምን ነበር?
10 አብርሃም ይስሐቅን ከወለደ በኋላስ? ዘሮቹ በዝተው ታላቅ ሕዝብ የሚሆኑት በይስሐቅ በኩል እንደሆነ ለአብርሃም ገለጸለት። (ዘፍጥረት 21:12) በዚህ ምክንያት ይሖዋ የአብርሃምን እምነት ለመፈተን አስቦ ልጁን ይስሐቅን እንዲሠዋ በነገረው ጊዜ እርስ በርሱ የሚጋጭ ሁኔታ ሆኖ ሳይታየው አልቀረም። (ዘፍጥረት 22:2) ይሁን እንጂ አብርሃም በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ ተማምኖ ከይሖዋ ትእዛዝ ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ ይስሐቅን ለማረድ ቢላዋውን አነሣ። መጨረሻዋ ደቂቃ ላይ አምላክ መልአኩን ልኮ አብርሃም ልጁን እንዳይሠዋ ከለከለው።—ዘፍጥረት 22:9–14
11 አብርሃም ይህን ያህል ታዛዥ የሆነው ለምንድን ነው? ዕብራውያን 11:17–19 “አብርሃም በተፈተነበት ጊዜ ይስሐቅን በእምነት አቀረበ፣ የተስፋን ቃል የተቀበለው፦ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል የተባለለት እርሱም አንድ ልጁን አቀረበ፤ እግዚአብሔር ከሙታን እንኳ ሊያስነሣው እንዲቻለው አስቦአልና፣ ከዚያም ደግሞ በምሳሌ አገኘው” በማለት ምክንያቱን ይገልጥልናል። ሮሜ 4:20, 21 በተመሳሳይ “[አምላክ] የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ . . . በአለማመን ምክንያት [አብርሃም] በእግዚአብሔር ተስፋ ቃል አልተጠራጠረም” በማለት ይገልጻል።
12. አብርሃም ላሳየው እምነት ምን ሽልማት አገኘ?
12 አብርሃም ላሳየው እምነት ያገኘው ሽልማት ይስሐቅ ከሞት መትረፉና በእርሱም አማካኝነት “ታላቅ ሕዝብ” መገኘቱ ብቻ አልነበረም። ሌላም ሽልማት አግኝቷል። አምላክ ለአብርሃም “የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፣ ቃሌን ሰምተሃልና” በማለት ነግሮታል። (ዘፍጥረት 22:18) እንዴት? የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ የሚመጣው በአብርሃም የትውልድ ሐረግ በኩል ይሆናል። ይህ መንግሥት በሰይጣን የሚገዛውን ይህንን ክፉ ዓለም ያወድማል። (ዳንኤል 2:44፤ ሮሜ 16:20፤ ራእይ 19:11–21) ከዚያ በኋላ በመንግሥቱ ግዛት ሥር በጸዳው ምድር ላይ ከዳር እስከ ዳር ገነት ይስፋፋና ከ“ሁሉም አሕዛብ” የተውጣጡ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎች ፍጹም ጤናና የዘላለም ሕይወት አግኝተው ይኖሩበታል። (1 ዮሐንስ 2:15–17) አብርሃም ስለ መንግሥቱ የነበረው እውቀት በጣም የተመጠነ ቢሆንም በአምላክ ተማምኗል። መንግሥቱም የሚመሠረትበትን ጊዜ በተስፋ ተጠባብቋል።—ዕብራውያን 11:10
13, 14. ኢዮብ በአምላክ የተማመነው ለምን ነበር?
13 ከሁለትና ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ ማለትም በ17ኛውና በ16ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ዛሬ የዐረቦች ምድር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ኢዮብ የሚባል ሰው ይኖር ነበር። እሱም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ከመጻፉ በፊት የኖረ ሰው ነው። ኢዮብ “ፍጹምና ቅን፣ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፣ ከክፋትም የራቀ ነበረ።” (ኢዮብ 1:1) ሰይጣን ኢዮብን በጣም በሚያሠቅቅና በሚያሠቃይ በሽታ በመታው ጊዜ ይህ ታማኝ ሰው በመከራው ዘመን ሁሉ “አንዲት የኃጢአት ቃል አልተናገረም።” (ኢዮብ 2:10 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ኢዮብ በይሖዋ ተማምኗል። ይህን ያህል መከራ የሚቀበልበትን ምክንያት ሙሉ በሙሉ ባያውቅም ለአምላክና አምላክ ለሰጣቸው ተስፋዎች ሲል ሕይወቱን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኗል።
14 ኢዮብ ቢሞትም እንኳ አምላክ በትንሣኤ አማካኝነት አንድ ቀን ሕይወቱን እንደሚመልስለት ያውቅ ነበር። በትንሣኤ ተስፋ ይተማመን እንደነበረ “በሲኦል [በመቃብር] ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ! . . . ቀጠሮም አድርገህ ምነው ባሰብኸኝ ኖሮ! በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን? . . . በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር” በማለት ለይሖዋ አምላክ ከተናገረው መረዳት እንችላለን። (ኢዮብ 14:13–15) በከፍተኛ ሥቃይ ላይ ያለ ቢሆንም “እስክሞት ድረስ ፍጹምነቴን ከእኔ አላርቅም” በማለት በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ እምነት እንደነበረው አሳይቷል።—ኢዮብ 27:5
15. ዳዊት በይሖዋ ዓላማ መተማመኑን የገለጸው እንዴት ነበር?
15 ኢዮብ ከኖረበት ከስድስት መቶ ዘመናት በኋላና ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት ዳዊት አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ያለውን ሙሉ እምነት ገልጿል። በመዝሙሮቹ ውስጥ እንደዚህ ብሏል፦ “እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ። ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።” ዳዊት የማይናወጥ ተስፋ ስለነበረው “በእግዚአብሔር ታመን፣ . . . በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፣ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል” በማለት አጥብቆ መክሯል።—መዝሙር 37:3, 4, 9–11, 29
16. ‘እንደ ታላቅ ደመና የሆኑ ምስክሮች’ ምን ተስፋ ነበራቸው?
16 ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ ታማኝ የሆኑ ወንዶችና ሴቶች በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ነበራቸው። እንዲያውም ለይሖዋ ተስፋዎች ሕይወታቸውን የሠዉ ቃል በቃል ‘እንደ ደመና ያሉ ምስክሮች’ ነበሩ። በጥንት ዘመን የነበሩት ብዙዎቹ የይሖዋ ምስክሮች በእምነታቸው ምክንያት የተሠቃዩትና የተገደሉት “የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ” ብለው ነው። እንዴት? በአዲሱ ዓለም ውስጥ አምላክ የተሻለ ትንሣኤ አግኝተው ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ይሰጣቸዋል።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ ዕብራውያን 11:35፤ 12:1
ክርስቲያን ምስክሮች በአምላክ ይታመናሉ
17. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በይሖዋ ላይ ጽኑ እምነት የነበራቸው እንዴት ነበር?
17 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ይሖዋ አዲስ በተቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ በኩል ስለ መንግሥቲቱና መንግሥቲቱ ምድርን እንዴት እንደምትገዛ ዝርዝር ሐሳቦችን ገልጧል። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ዮሐንስን በመንግሥተ ሰማያት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚተባበሩት ሰዎች ቁጥር 144,000 መሆኑን እንዲጽፍ አነሣስቶታል። እነዚህ ሰዎች “ከሰዎች የተዋጁ” የታመኑ የአምላክ አገልጋዮች ይሆናሉ። (ራእይ 7:4፤ 14:1–4) ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ሆነው በምድር ላይ “ይነግሣሉ።” (ራእይ 20:4–6) ስለዚህ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ይሖዋ ለሰማያዊ መንግሥቱና ለምድራዊው ግዛቱ ያለውን ዓላማ እንደሚፈጽም ሙሉ እምነት ስለነበራቸው ለእምነታቸው ሲሉ ሕይወታቸውን ለሞት አሳልፈው ለመስጠት ፈቃደኛ ሆነዋል። ብዙዎቹም ለእምነታቸው ሲሉ ተገድለዋል።
18. የይሖዋ ምስክሮች ከብዙ ዘመን በፊት የነበሩትን የእምነት መሰሎቻቸውን አርዓያ የተከተሉት እንዴት ነው?
18 ዛሬም ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉ የይሖዋ ምስክሮች ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት እንደኖሩት የእምነት መሰሎቻቸው በአምላክ ላይ ተመሳሳይ እምነት አላቸው። እነዚህም የዘመናችን ምስክሮች አምላክ ለሰጣቸው ተስፋዎች ሲሉ ሕይወታቸውን ሠውተዋል። ሕይወታቸውን ለአምላክ ወስነዋል። እምነታቸውንም የሚያጠናክሩበት ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ አላቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:14–17) እነዚህ ዘመናዊ የይሖዋ ምስክሮች “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” በማለት የተናገሩትን የመጀመሪያውን መቶ ዘመን የኢየሱስ ተከታዮች አርዓያ ይከተላሉ። (ሥራ 5:29) በዚህ መቶ ዘመን ከእነዚህ ክርስቲያን ምስክሮች ብዙዎቹ በጭካኔ ተሰድደዋል። አንዳንዶቹም ለእምነታቸው ሲሉ ተገድለዋል። ሌሎች በበሽታ፣ በአደጋ ወይም በእርጅና ምክንያት ሞተዋል። ይሁን እንጂ ባለፉት ጊዜያት እንደነበሩት ታማኝ ምስክሮች አምላክ በትንሣኤ አማካኝነት በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንደገና በሕይወት ሊያኖራቸው እንደሚችል ስላወቁ በአምላክ ላይ ተማምነዋል።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሥራ 24:15፤ ራእይ 20:12, 13
19, 20. ስለ ዘመናችን ስለሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ምን ነገር እንገነዘባለን?
19 የይሖዋ ምስክሮች ከሁሉም ብሔራት ተውጣጥተው አንድ ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር መመሥረታቸው አስቀድሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የተነገረ መሆኑን ይገነዘባሉ። (ኢሳይያስ 2:2–4፤ ራእይ 7:4, 9–17) በተጨማሪም ይሖዋ ሌሎች ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ ሞገሱና ወደ ጥበቃው እንዲሰበሰቡ የሚያስችላቸውን ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ እያሠራቸው ነው። (ምሳሌ 18:10፤ ማቴዎስ 24:14፤ ሮሜ 10:13) እነዚህ ሁሉ ይሖዋ በቅርቡ አዲሱን ዓለም እንደሚያመጣ እርግጠኞች በመሆን በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ ይታመናሉ።—ከ1 ቆሮንቶስ 15:58፤ ዕብራውያን 6:10 ጋር አወዳድር።
20 የአዲስ ታሪክ መክፈቻ ከሆነው ከ1914 ጀምሮ የሰይጣን ዓለም ወደ መጨረሻ ቀኖቹ ከገባ 80 ዓመት እንደሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ያመለክታሉ። ይህ ዓለም ሊጠፋ ተቃርቧል። (ሮሜ 16:20፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) የይሖዋ ምስክሮች በቅርቡ የአምላክ መንግሥት ምድርን ሙሉ በሙሉ እንደምትቆጣጠር ስለተገነዘቡ ደፋሮችና ቆራጦች ናቸው። አምላክ ይህንን ክፉ ዓለም አጥፍቶና ጻድቅ አዲስ ዓለም አምጥቶ ለብዙ መቶ ዘመናት በምድር ላይ ተንሠራፍቶ የኖረውን መጥፎ ሁኔታ ይሽራል።—ምሳሌ 2:21, 22
21. በመከራ ውስጥ ብንኖርም ልንደሰት የምንችለው ለምንድን ነው?
21 በዚያ ጊዜ አምላክ ባለፉት ጊዜያት የደረሱብንን ጉዳቶች በብዙ እጥፍ የሚያካክስ በረከት በማዝነብ ዘላለማዊ እንክብካቤ ያደርግልናል። በአዲሱ ዓለም ውስጥ አምላክ ብዙ መልካም ነገሮች ስለሚያደርግልን ያሳለፍነው ችግር ፈጽሞ አይታሰበንም። በዚያ ጊዜ ይሖዋ ‘እጁን ከፍቶ ሕይወት ላለው ሁሉ መልካምን ማጥገቡን’ እንደሚቀጥል ማወቃችን በጣም ያጽናናናል።—መዝሙር 145:16፤ ኢሳይያስ 65:17, 18
22. በይሖዋ ልንተማመን የሚገባን ለምንድን ነው?
22 በአዲሱ ዓለም ታማኝ የሰው ዘሮች “ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው” የሚለው የሮሜ 8:21 ትንቢት ሲፈጸም ይመለከታሉ። ኢየሱስ ተከታዮቹን “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ ያስተማራቸው ጸሎት መልስ ሲያገኝ ይመለከታሉ። (ማቴዎስ 6:10) እንግዲያው “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” የሚል የማይታበል ተስፋ ስለሰጠን በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ እንታመን።—መዝሙር 37:29
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ይሖዋ ለሰዎችና ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
◻ አምላክ በምድር ላይ መጥፎ ሁኔታዎች እንዲኖሩ ለምን ፈቀደ?
◻ በጥንት ዘመን የነበሩ ታማኝ ሰዎች በይሖዋ እንደሚተማመኑ ያሳዩት እንዴት ነበር?
◻ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በይሖዋ የሚተማመኑት ለምንድን ነው?
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል16]
አምላክ ሰዎችን ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም ተደስተው እንዲኖሩ ፈጥሯቸው ነበር
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል18]
ይሖዋ የሞቱትን ከሞት ለማስነሣት ችሎታ እንዳለው አብርሃም ሙሉ እምነት ነበረው