ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ
“ከአንጀት በመዋደድ ርኅራኄንና ደግነትን ልበሱ።”—ቆላስይስ 3:12 አዓት
1. በዛሬው ጊዜ ርኅራኄ በእጅጉ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
በታሪክ ውስጥ የዛሬውን ያህል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ርኅራኄ የታከለበት እርዳታ አስፈልጓቸው አያውቅም። በሽታ፣ ረሀብ፣ ሥራ አጥነት፣ ወንጀል፣ ጦርነቶች፣ ሕገ ወጥነትና የተፈጥሮ አደጋዎች የተጋረጡባቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ይሁን እንጂ ከዚህም ይበልጥ አስከፊ የሆነ ችግር አለ። እርሱም የሰው ዘር የሚገኝበት አስጊ መንፈሳዊ ሁኔታ ነው። ጥቂት ጊዜ እንደቀረው የሚያውቀው ሰይጣን ‘ዓለሙን ሁሉ እያሳተ ነው።’ (ራእይ 12:9, 12) ስለዚህ በተለይ ከእውነተኛ ክርስቲያን ጉባኤ ውጪ ያሉት ሕይወታቸውን ሊያጡ በሚችሉበት አደገኛ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በመጪው የአምላክ የፍርድ ቀን ለሚቀጡት ሰዎች ምንም ዓይነት የትንሣኤ ተስፋ አይሰጥም።—ማቴዎስ 25:31–33, 41, 46፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6–9
2. ይሖዋ በክፉዎች ላይ የሚወስደውን የማጥፋት እርምጃ ያዘገየው ለምንድን ነው?
2 ሆኖም ይሖዋ አምላክ በዚህ ባለቀ ሰዓትም ውለታ ቢስና ክፉ ለሆኑ ሰዎች ትዕግሥትና ርኅራኄ ማሳየቱን ቀጥሏል። (ማቴዎስ 5:45፤ ሉቃስ 6:35, 36) ይህን ያደረገበት ምክንያትና ታማኝ ሆኖ ያልተገኘውን የእስራኤል ሕዝብ ከመቅጣት የዘገየበት ምክንያት ተመሳሳይ ነው። “እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ተመለሱ፣ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ?”—ሕዝቅኤል 33:11
3. ይሖዋ ሕዝቡ ላልሆኑት ሰዎች ርኅራኄ እንዳለው የሚያሳይ ምን ምሳሌ አለን? እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን?
3 ይሖዋ ለክፉዎቹ የነነዌ ሰዎችም ርኅራኄውን አሳይቷል። ጥፋት ሊመጣባቸው መሆኑን እንዲያስጠነቅቃቸው ይሖዋ ነቢዩን ዮናስን ላከው። የነነዌ ሰዎች ለዮናስ ስብከት አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ንስሐ ገቡ። ይህም ርኅሩኁ አምላክ ይሖዋ በዚያን ጊዜ ከተማዋን ከማጥፋት እንዲታቀብ አደረገው። (ዮናስ 3:10፤ 4:11) አምላክ የትንሣኤ ተስፋ የማግኘት አጋጣሚ ለነበራቸው የነነዌ ሰዎች ካዘነላቸው በዛሬው ጊዜ ዘላለማዊ ጥፋት ለሚጠብቃቸው ሰዎችማ ምንኛ የላቀ ርኅራኄ ይሰማው ይሆን!—ሉቃስ 11:32
ታይቶ የማይታወቅ የርኅራኄ ሥራ
4. ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ላሉት ሰዎች ርኅራኄ እያሳየ ያለው እንዴት ነው?
4 ይሖዋ ከርኅራኄ ባሕርይው ጋር በመስማማት ምሥክሮቹ ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ ይዘው በመሄድ ዘወትር ሰዎችን እንዲያነጋግሩ አዟቸዋል። (ማቴዎስ 24:14) ሰዎች ይህን ሕይወት አድን ሥራ በአድናቆት ሲቀበሉ ይሖዋ የመንግሥቱን መልእክት መጨበጥ እንዲችሉ ልባቸውን ይከፍትላቸዋል። (ማቴዎስ 11:25፤ ሥራ 16:14) እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላካቸውን በመምሰል ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተመልሰው በማነጋገርና የሚቻል በሚሆንበትም ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት በመርዳት ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ያሳያሉ። በመሆኑም በ1993 ከአራት ሚልዮን ተኩል በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በ231 አገሮች ውስጥ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ በመስበክና ከሰዎች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ከአንድ ቢልዮን ሰዓታት በላይ አሳልፈዋል። እነዚህ ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎች በአጸፋው ሕይወታቸውን ለይሖዋ የመወሰንና ከተጠመቁት ምሥክሮቹ ጋር የመደመር አጋጣሚ አላቸው። እነርሱም በበኩላቸው ወደፊት ደቀ መዛሙርት ሊሆኑ የሚችሉትን ሰዎች ከተያዙበት ጠፊ የሰይጣን ዓለም ለማላቀቅ የሚደረገውን ይህን ታይቶ የማይታወቅ የርኅራኄ ሥራ የማከናወን ኃላፊነት ይቀበላሉ።—ማቴዎስ 28:19, 20፤ ዮሐንስ 14:12
5. መለኮታዊ ርኅራኄ ተሟጥጦ ሲያልቅ አምላክን በሐሰት የወከለ ሃይማኖት ምን ይደርስበታል?
5 በቅርቡ ይሖዋ “ተዋጊ” ሆኖ እርምጃ ይወስዳል። (ዘጸአት 15:3) ይሖዋ ለስሙና ለሕዝቡ ባለው ርኅራኄ የተነሣ ክፋትን አስወግዶ ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለምን ይመሠርታል። (2 ጴጥሮስ 3:13) የአምላክ የቁጣ ቀን የመጀመሪያ ቀማሾች የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ይሆናሉ። በኢየሩሳሌም የነበረውን የራሱን ቤተ መቅደስ እንኳ ከባቢሎን ንጉሥ እጅ እንዳላስጣለ ሁሉ እርሱን በሐሰት የወከሉትን ሃይማኖታዊ ድርጅቶችም አያስጥልም። አምላክ የተባበሩት መንግሥታት አባላት ሕዝበ ክርስትናንና ሌሎች የሐሰት ሃይማኖቶችን ጠራርገው ለማጥፋት እንዲነሳሡ ያደርጋቸዋል። (ራእይ 17:16, 17) ይሖዋ “እኔም ደግሞ በዓይኔ አልራራም አላዝንምም፣ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ” ሲል ተናግሯል።—ሕዝቅኤል 9:5, 10
6. የይሖዋ ምሥክሮች ርኅራኄ ማሳየታቸውን የቀጠሉት በምን በምን መንገዶች ነው?
6 ሆኖም አሁንም ቢሆን ጊዜው ባለመሟጠጡ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን የመዳን መልእክት በቅንዓት በመስበክ ለሰዎች ርኅራኄ ማሳየታቸውን ቀጥለዋል። አቅማቸው በፈቀደ መጠን ቁሳዊ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ጭምር እንደሚረዱ ግልጽ ነው። ሆኖም በዚህ ረገድ ተቀዳሚው ኃላፊነታቸው የቅርብ የቤተሰብ አባሎቻቸውና በእምነት የሚዛመዷቸው ሰዎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማሟላት ነው። (ገላትያ 6:10፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:4, 8) የይሖዋ ምሥክሮች የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች የደረሱባቸውን መሰል አማኞች ለመርዳት ሲሉ ያከናወኗቸው ብዙ ተልእኮዎች ከፍተኛ ትኩረትን የሳቡ የርኅራኄ ምሳሌዎች ሆነዋል። ያም ሆነ ይህ ክርስቲያኖች ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ የሚያሳዩት አንድ ከባድ ችግር ሲከሰት ብቻ አይደለም። በዕለት ተዕለት የኑሮ ውጣ ውረዶችም ይህን ባሕርይ ያሳያሉ።
የአዲሱ ሰውነት ክፍል ነው
7. (ሀ) በቆላስይስ 3:8–13 ላይ ርኅራኄ ከአዲሱ ሰውነት ጋር የተያያዘው እንዴት ነው? (ለ) ከአንጀት መዋደድ ክርስቲያኖች ምን ማድረግ እንዲቀላቸው ያደርጋል?
7 በኃጢአት የተበከለው ተፈጥሮአችንና የሰይጣን ዓለም መጥፎ ተጽዕኖ ከአንጀታችን ርኅራኄ እንዳናሳይ እንቅፋት እንደሚሆኑብን አሌ አይባልም። መጽሐፍ ቅዱስ “ቁጣንና ንዴትን ክፋትንም፣ . . . ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር” እንድናስወግድ የሚመክረን በዚህ ምክንያት ነው። ከዚህ ይልቅ በአምላክ ምሳሌ የተፈጠረውን ‘አዲሱን ሰውነት እንድንለብስ’ ተመክረናል። በመጀመሪያ ደረጃ “ከአንጀት በመዋደድ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትንና ትዕግሥትን” እንድንለብስ ታዘናል። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ባሕርያት ማሳየት የሚቻልበትን ተግባራዊ መንገድ ያሳየናል። “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ በነፃ ይቅር ተባባሉ፤ ይሖዋ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።” ለወንድሞቻችን “ከአንጀት በመዋደድ ርኅራኄን” ከኮተኮትን ይቅር ባይ መሆን ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል።—ቆላስይስ 3:8–13 አዓት
8. የይቅር ባይነት መንፈስ መያዝ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
8 በሌላ በኩል ደግሞ ርኅራኄ የታከለበት ይቅር ባይነት ማሳየት ከተሳነን ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና ይሻክራል። ይህ ሁኔታ ጌታው “ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ” ዘብጥያ ስላወረደው ይቅር ያላለ ባሪያ ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ ጠበቅ ተደርጎ ተገልጿል። ይህ ባሪያ ምሕረት እንዲያደርግለት ሲማጸነው ለነበረው ባሪያ ርኅራኄ ሳያደርግለት በመቅረቱ ይህ ፍርድ የሚበዛበት አልነበረም። ኢየሱስ እንዲህ በማለት ምሳሌውን አጠቃሏል፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፣ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።”—ማቴዎስ 18:34, 35
9. ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ከአዲሱ ሰውነት ዐቢይ ገጽታ ጋር የተዛመደው እንዴት ነው?
9 ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ማሳየት አንዱ ዐቢይ የፍቅር ዘርፍ ነው። ፍቅር ደግሞ የእውነተኛ ክርስትና መለያ ምልክት ነው። (ዮሐንስ 13:35) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አዲሱ ሰውነት የሚሰጠውን መግለጫ እንዲህ በማለት ያጠቃልላል፦ “በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ [ፍጹም የአንድነት ማሰሪያ አዓት] የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።”—ቆላስይስ 3:14
የርኅራኄ እንቅፋት የሆነው ቅናት
10. (ሀ) ቅናት በልባችን ውስጥ ሥር እንዲሰድ ሊያደርግ የሚችለው ምንድን ነው? (ለ) ቅናት ምን መጥፎ ውጤቶችን ሊያስከትል ይችላል?
10 በኃጢአት በተበከለው ሰብዓዊ ተፈጥሮአችን የተነሣ የቅናት ስሜቶች በቀላሉ በልባችን ውስጥ ሥር መስደድ ይችላሉ። አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት በተፈጥሮ ያገኘው(ችው) ልዩ ተሰጥኦ ሊኖረው(ራት) ይችላል። ወይም እኛ የሌለን ቁሳዊ ሀብት ሊኖራቸው ይችላል። አለዚያም ደግሞ ምናልባት አንድ ሰው ልዩ መንፈሳዊ በረከቶችንና መብቶችን አግኝቶ ሊሆን ይችላል። በእንደነዚህ ዓይነት ወንድሞችና እህቶች የምንቀና ከሆነ ከአንጀት በመነጨ ርኅራኄ ልንይዛቸው እንችላለንን? እንጃ፣ ያጠራጥራል። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ሰዎችን አስመልክቶ ሲናገር “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና” ባለው መሠረት የቅናት ስሜቶች ቀስ በቀስ በትችት ወይም በክፋት ድርጊቶች ራሳቸውን ይፋ ሊያወጡ ይችላሉ። (ሉቃስ 6:45) ሌሎች ደግሞ ከእንዲህ ዓይነቶቹ ትችቶች ጎን ሊወግኑ ይችላሉ። በዚህ መንገድ የአንድ ቤተሰብ ወይም የአንድ የአምላክ ሕዝብ ጉባኤ ሰላም ሊደፈርስ ይችላል።
11. የዮሴፍ አሥር ወንድሞች በልባቸው ውስጥ ለርኅራኄ የሚሆን ቦታ እንዲጠፋ ያደረጉት እንዴት ነበር? ምን ውጤትስ አስከተለ?
11 በአንድ ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ ምን እንደ ተከሰተ ተመልከት። የያዕቆብ አሥር ወንዶች ልጆች አባታቸው ታናሽ ወንድማቸውን ዮሴፍን ከሁሉም አብልጦ ይወደው ስለነበረ በእርሱ ላይ ቅናት አደረባቸው። በዚህም የተነሣ “በሰላም ይናገሩትም ዘንድ አልቻሉም።” ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ የይሖዋን ሞገስ እንዳገኘ የሚያረጋግጡ መለኮታዊ ሕልሞችን አየ። ይህም ወንድሞቹ “እንደገና በብዙ” እንዲጠሉት አደረጋቸው። በልባቸው የበቀለውን ቅናት ከነሥሩ መንግለው ስላላወጡት ለርኅራኄ የሚሆን ቦታ በልባቸው ውስጥ አልነበረም። ይህም ከባድ ኃጢአት ወደ መፈጸም አደረሳቸው።—ዘፍጥረት 37:4, 5, 11
12, 13. የቅናት ስሜቶች ወደ ልባችን ሲገቡ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
12 ያለ ምንም ርኅራኄ ዮሴፍን ለባርነት ሸጡት። የፈጸሙትን ክፉ ድርጊት ለመደበቅ ሲሉ ዮሴፍ በዱር አውሬ እንደተበላ በማስመሰል አባታቸውን አታለሉት። ዓመታት ካለፉ በኋላ በወቅቱ ተከስቶ በነበረው ረሀብ ሳቢያ እህል ለመግዛት ወደ ግብጽ ለመሄድ በተገደዱበት ጊዜ ኃጢአታቸው ገሀድ ወጣ። ዮሴፍ መሆኑን ያላወቁት የእህሉ አስተዳዳሪ ልትሰልሉ ነው የመጣችሁት ብሎ ከሰሳቸው። እንዲሁም ታናሹን ወንድማችሁን ብንያምን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ የእኔን እርዳታ እንዳትሹ ሲል ነገራቸው። በዚህ ወቅት አባታቸው ከሁሉ አብልጦ ይወደው የነበረው ብንያምን ነበር፤ በተጨማሪም ያዕቆብ አብሯቸው እንዲሄድ እንደማይፈቅድላቸው ያውቁ ነበር።
13 ስለዚህ በዮሴፍ ፊት ቆመው እያሉ ሕሊናቸው የሚከተለውን አምነው እንዲቀበሉ አደረጋቸው፦ “በእውነት ወንድማችንን [ዮሴፍን] በድለናል፣ እኛን በማማጠን ነፍሱ ስትጨነቅ አይተን አልሰማነውምና፤ ስለዚህ ይህ መከራ መጣብን።” (ዘፍጥረት 42:21) ርኅራኄ የተሞላበት ቢሆንም ቆራጥ አቋም በመውሰድ ዮሴፍ ወንድሞቹ ከልብ መጸጸታቸውን እንዲያረጋግጡ ረድቷቸዋል። ከዚያም ማንነቱን ገልጾላቸዋል፤ እንዲሁም በደግነት ይቅር ብሏቸዋል። የቤተሰቡ አንድነት እንደገና ተመለሰ። (ዘፍጥረት 45:4–8) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ከዚህ ትምህርት መቅሰም ይኖርብናል። ቅናት የሚያመጣቸውን መጥፎ መዘዞች በማወቅ የቅናት ስሜቶችን ‘ከአንጀት በመዋደድ በርኅራኄ’ መተካት እንድንችል እንዲረዳን ወደ ይሖዋ መጸለይ ይኖርብናል።
ሌሎቹ የርኅራኄ እንቅፋቶች
14. አላግባብ ራሳችንን ለዓመፅ ከማጋለጥ መቆጠብ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
14 ርኅሩኅ እንዳንሆን እንቅፋት የሚሆንብን ሌላው ነገር አላግባብ ራሳችንን ለዓመፅ ማጋለጣችን ነው። ዓመፅን የሚያሳዩ ስፖርቶችና መዝናኛዎች ሰዎች ደስታ እንደሚያስገኝላቸው በማሰብ ለዓመፅ ከፍተኛ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደርጋሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አረማውያን ሰዎች ከሰውና ከእንስሳ ጋር የሚታገሉባቸውን ውድድሮችና ሰዎች የሚሠቃዩባቸውን ሌሎች ዓይነት ጨዋታዎችን በሮማ ግዛት ስታድየሞች ውስጥ ዘወትር ይመለከቱ ነበር። አንድ ታሪክ ጸሐፊ እንዳሉት እንዲህ ያሉት መዝናኛዎች “የሰውን ልጅ ከእንስሳት የሚለየውን ለሌላው ሥቃይ የማዘንን ስሜት አጥፍቶታል።” በጊዜያችን ባለው ዘመናዊ ዓለም ውስጥ ያለው አብዛኛው መዝናኛ ተመሳሳይ የሆነ ውጤት አስከትሏል። ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ለማሳየት የሚጥሩት ክርስቲያኖች የሚያነቡትን ነገር፣ የሚያዩአቸውን ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በጥንቃቄ መምረጥ ይኖርባቸዋል። “ዓመፅን የሚወድ ሰው በ[ይሖዋ] ዘንድ ፈጽሞ የተጠላ ነው” የሚሉትን የመዝሙር 11:5 [አዓት] ቃላት በጥበብ በአእምሮአቸው ማኅደር ውስጥ ያስቀምጣሉ።
15. (ሀ) አንድ ሰው ርኅራኄ በጣም እንደጎደለው ሊታይበት የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) እውነተኛ ክርስቲያኖች መሰል አማኞችና ሌሎች ሰዎች ለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ምላሽ የሚሰጡት እንዴት ነው?
15 በተጨማሪም ራስ ወዳድ የሆነ ሰው ርኅራኄ እንደማይኖረው የታወቀ ነው። ይህ በቸልታ የሚታይ ነገር አይደለም። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፣ ወንድሙም የሚያስፈልገውን ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን፣ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል?” (1 ዮሐንስ 3:17) ኢየሱስ ሰው ወዳድ ስለሆነው ሳምራዊ በተናገረው ምሳሌ ላይ የተገለጹት ራሱን ያመጻድቅ የነበረው ካህንና ሌዋዊው ተመሳሳይ የሆነ የርኅራኄ ጉድለት አሳይተዋል። እነዚህ ሰዎች በሕይወትና በሞት መካከል ወድቆ የነበረው አይሁዳዊ ወንድማቸው የደረሰበትን መጥፎ ሁኔታ ባዩ ጊዜ ወደ ሌላኛው መንገድ ተሻግረው ጉዞአቸውን ቀጠሉ። (ሉቃስ 10:31, 32) ከዚህ በተቃራኒው ርኅሩኅ ክርስቲያኖች ለወንድሞቻቸው ቁሳዊና መንፈሳዊ ችግር በአፋጣኝ አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣሉ። እንዲሁም በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተገለጸው ሳምራዊ የማያውቋቸው ሰዎች ለሚያስፈልጓቸው ነገሮችም ያስባሉ። በመሆኑም ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጥሪታቸውን በደስታ ደቀ መዛሙርት ለማድረጉ ሥራ ያውሉታል። በዚህ ሁኔታ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች መዳን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።—1 ጢሞቴዎስ 4:16
ለታመሙት ርኅራኄ ማሳየት
16. ሕመምን በመቋቋም ረገድ ከአቅማችን በላይ የሆኑ ምን ነገሮች ያጋጥሙናል?
16 በሽታ ሟች የሆነውና ፍጽምና የጎደለው የሰው ዘር ዕጣ ፈንታ ነው። ክርስቲያኖችም ከዚህ አላመለጡም። ከእነርሱ መካከል አብዛኛዎቹ የሕክምና ጠበብቶች አይደሉም። ከክርስቶስና ከሐዋርያቱ ተአምር ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል እንደተቀበሉት እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖችም ተአምር አይፈጽሙም። የክርስቶስ ሐዋርያትና የቅርብ ተባባሪዎቻቸው ሲሞቱ ተአምር ለመፈጸም የሚያስችለው እንዲህ ዓይነቱ ኃይል አብሮ ከስሟል። በመሆኑም የአእምሮ ቀውስንና በገሀዱ ዓለም የሌሉ ነገሮችን በሐሳብ የማየትና የመስማት ሁኔታ የሚፈጥሩ ችግሮችን ጨምሮ በአካላዊ ሕመም የሚሠቃዩ ሰዎችን ለመርዳት ያለን ችሎታ ውስን ነው።—ሥራ 8:13, 18፤ 1 ቆሮንቶስ 13:8
17. ታሞና በከፍተኛ ሐዘን ላይ ወድቆ ለነበረው ኢዮብ አብረውት የነበሩት ሰዎች ካሳዩት ባሕርይ ምን ትምህርት እናገኛለን?
17 የመንፈስ ጭንቀት ብዙውን ጊዜ ከሕመም ጋር ተያይዞ ይመጣል። ፈሪሃ አምላክ የነበረው ኢዮብ በደረሰበት ከባድ ሕመምና ሰይጣን ባደረሰበት ጥፋት ከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ ገብቶ ነበር። (ኢዮብ 1:18, 19፤ 2:7፤ 3:3, 11–13) ከአንጀት በመነጨ ርኅራኄ የሚይዙትና ‘የሚያጽናኑት’ ጓደኞች ፈልጎ ነበር። (1 ተሰሎንቄ 5:14) ከዚህ ይልቅ ሦስት አጽናኝ ተብዬዎች ሊጠይቁት መጥተው ፈጥነው የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ደረሱ። ያ ሁሉ ጥፋት ሊመጣበት የቻለው አንድ የሆነ ስህተት በመፈጸሙ እንደሆነ በመግለጽ የኢዮብን ጭንቀት አባባሱት። ክርስቲያኖች መሰል አማኞች ሲታመሙ ወይም የመንፈስ ጭንቀት ሲደርስባቸው ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ በማሳየት እንዲህ ዓይነት ስህተት ከመፈጸም ይቆጠባሉ። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሰዎች የሚያስፈልጋቸው ዋናው ነገር በርኅራኄ የሚያዳምጧቸው፣ ችግራቸውን የሚረዱላቸውና ፍቅራዊ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር የሚሰጧቸው ሽማግሌዎች ወይም ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች ለጥቂት ጊዜያት በደግነት እየተመላለሱ መጠየቅ ሊሆን ይችላል።—ሮሜ 12:15፤ ያዕቆብ 1:19
ለደካሞች ርኅራኄ ማሳየት
18, 19. (ሀ) ሽማግሌዎች ደካሞችን ወይም ስህተት የፈጸሙ ሰዎችን በምን ዓይነት መንገድ ሊይዟቸው ይገባል? (ለ) ጉዳዩን የፍርድ ኮሚቴ እንዲያየው ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ቢገኝም እንኳ ሽማግሌዎች ኃጢአት የሠሩትን ሰዎች ከአንጀት በመነጨ ርኅራኄ መያዛቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
18 በተለይ ሽማግሌዎች ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ማሳየት አለባቸው። (ሥራ 20:29, 35) “እኛም ኃይለኞች የሆንን የደካሞችን ድካም እንድንሸከም . . . ይገባናል” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ያዛል። (ሮሜ 15:1) አለፍጽምና ስላለብን ሁላችንም እንሳሳታለን። (ያዕቆብ 3:2) “ሳያውቅ አንድ የተሳሳተ እርምጃ የወሰደን” ሰው በምንረዳበት ጊዜ ርኅራኄ ማሳየት ያስፈልጋል። (ገላትያ 6:1 አዓት) ሽማግሌዎች የአምላክን ሕግ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ይጠቀሙበት እንደነበሩት ተመጻዳቂ ፈሪሳውያን መሆን አይፈልጉም።
19 ከዚህ ይልቅ ሽማግሌዎች የይሖዋ አምላክንና የኢየሱስ ክርስቶስን ከአንጀት የመራራት ምሳሌዎች ይከተላሉ። ዋና ሥራቸው የአምላክን በጎች መመገብ፣ ማበረታታትና ማነቃቃት ነው። (ኢሳይያስ 32:1, 2) ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ደንቦች በማውጣት ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር ከመሞከር ይልቅ በአምላክ ቃል ውስጥ የሠፈሩትን ግሩም መሠረታዊ ሥርዓቶች ይመለከታሉ። በመሆኑም የሽማግሌዎች ሥራ የወንድሞቻቸውን ልብ ማነጽ፣ ማስደሰትና ለይሖዋ ደግነት አድናቆት እንዲያድርባቸው ማድረግ መሆን ይኖርበታል። አንድ መሰል አማኝ አነስተኛ ስህተት ቢሠራ ብዙውን ጊዜ አንድ ሽማግሌ በሌሎች ፊት አያርመውም። ስለጉዳዩ ማነጋገር አስፈላጊ ከሆነ ከአንጀት የመነጨ የርኅራኄ ስሜት ሽማግሌው ይህን ወንድም ወደ አንድ ጥግ ወስዶ ሌሎች በማይሰሙበት ሁኔታ ችግሩን እንዲያወያየው ያስገድደዋል። (ከማቴዎስ 18:15 ጋር አወዳድር።) አንድን ሰው ቀርቦ ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ማነጋገር በጣም አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ሽማግሌው በትዕግሥትና ሊያጽናና በሚችል መንገድ ሊቀርበው ይገባል። እንዲህ ዓይነቱን ሰው ከጉባኤ ለማስወገድ ሰበብ አይፈላልግም። ጉዳዩን በፍርድ ኮሚቴ ፊት ማየት በሚያስፈልግበትም ጊዜ እንኳ ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት ከሠራው ሰው ጋር በሚያደርጉት ውይይት ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ያሳያሉ። የደግነት አቀራረባቸው የሚያነጋግሩት ሰው ንስሐ እንዲገባ ሊረዳው ይችላል።—2 ጢሞቴዎስ 2:24–26
20. ስሜታዊ የሆኑ የርኅራኄ መግለጫዎችን ማሳየት ተገቢ የማይሆነው መቼ ነው? ለምንስ?
20 ይሁን እንጂ አንድ የይሖዋ አገልጋይ ርኅራኄ ሊያሳይ የማይችልባቸው ጊዜያት አሉ። (ከዘዳግም 13:6–9 ጋር አወዳድር።) አንድ ክርስቲያን፣ ከተወገደ የቅርብ ጓደኛው ወይም ዘመዱ ጋር የነበረውን ‘ወዳጅነት ማቋረጥ’ ትልቅ ፈተና ሊሆንበት ይችላል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች አንድ ክርስቲያን ለአዘኔታ ስሜቶች እጁን አለመስጠቱ በጣም አስፈላጊ ነው። (1 ቆሮንቶስ 5:11–13) እንዲያውም እንዲህ ዓይነት ቆራጥ አቋም መውሰድ ኃጢአት የሠራው ሰው እንዲጸጸት ሊገፋፋው ይችላል። ከዚህም በላይ ክርስቲያኖች ከተቃራኒ ፆታ ጋር ባላቸው ግንኙነት ወደ ፆታ ብልግና ሊመሩ የሚችሉ ተገቢ ያልሆኑ የርኅራኄ መግለጫዎችን ከማሳየት መቆጠብ አለባቸው።
21. በየትኞቹ ሌሎች መስኮችም ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ማሳየት ይገባናል? ይህስ ምን ጥቅሞችን ያስገኛል?
21 በዕድሜ ከገፉ፣ የሚያፈቅሩት ሰው ከሞተባቸውና ከማያምኑ የትዳር ጓደኞች ተቃውሞ እየደረሰባቸው ካሉት ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ሁሉ ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ልናሳይ ይገባል። ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ልናሳይባቸው የሚገቡንን መስኮች በሙሉ ለመዳሰስ ቦታው አይበቃንም። ተግተው የሚሠሩ ሽማግሌዎችም እንደዚሁ ከአንጀት በመነጨ ርኅራኄ መያዝ ይገባቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:17) አክብሯቸው፤ ድጋፋችሁንም አትንፈጓቸው። (ዕብራውያን 13:7, 17) ሐዋርያው ጴጥሮስ “ሁላችሁም . . . ከአንጀታችሁ የምትራሩ ሁኑ” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 3:8 አዓት) ይህን ባሕርይ ማሳየትን በሚጠይቁ ሁኔታዎች ሁሉ እንዲህ በማድረግ በጉባኤ ውስጥ አንድነትንና ደስታን እናደረጃለን፤ ከክርስቲያን ጉባኤ ውጪ ያሉትንም ወደ እውነት እንስባለን። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከአንጀቱ የሚራራውን አባታችንን ይሖዋን እናከብረዋለን።
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ ይሖዋ ኃጢአተኛ ለሆነው የሰው ዘር ርኅራኄ ያሳየው እንዴት ነው?
◻ ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ እንዳናሳይ እንቅፋት የሚሆኑብን አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
◻ የታመሙትንና የመንፈስ ጭንቀት ያደረባቸውን ሰዎች መያዝ የሚኖርብን እንዴት ነው?
◻ በተለይ ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ማሳየት ያለባቸው እነማን ናቸው? ለምንስ?
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ርኃራኄ የሚባል ነገር የማያውቁት ፈሪሳውያን
የሰንበት ዕረፍት የአምላክ ሕዝብ በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ የሚባረክበት ቀን ነበር። ይሁን እንጂ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ብዙ ደንቦችን በማውጣት የአምላክን የሰንበት ሕግ ክብር አቃልለዋል፤ ሕዝቡም የሰንበት ሕግ እንደ ሸክም እንዲከብደው አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል ማንኛውም ሰው ድንገተኛ አደጋ ቢደርስበት ወይም በጠና ቢታመም ሕይወቱ አስጊ ሁኔታ ላይ እስካልደረሰ ድረስ በሰንበት ምንም ዓይነት እርዳታ ማግኘት አይችልም ነበር።
አንድ ዓይነት ሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርት የሚከተሉ ሰዎችን ያቀፈ አንድ የፈሪሳውያን ቡድን ለሰንበት ሕግ የሚሰጠው ትርጉም ውልፍት የማያደርግ ከመሆኑ የተነሣ እንዲህ ይል ነበር፦ “አንድ ሰው በሰንበት ለቀስተኞችን ማጽናናትም ሆነ የታመሙ ሰዎችን መጠየቅ አይችልም።” ሌሎች ሃይማኖታዊ መሪዎች እንደዚህ የመሰሉትን ጥየቃዎች ቢፈቅዱም “ማልቀስ የተከለከለ ነው” የሚል ደንብ ነበራቸው።
ስለዚህ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች እንደ ፍትሕ፣ ፍቅርና ምሕረት ያሉትን ሕጉ የሚጠይቃቸውን ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ገሸሽ በማድረጋቸው ኢየሱስ በቀጥታ አውግዟቸዋል። “ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሐርን ቃል ትሽራላችሁ” በማለት ፈሪሳውያንን መናገሩ ምንም አያስደንቅም!—ማርቆስ 7:8, 13፤ ማቴዎስ 23:23፤ ሉቃስ 11:42
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች በ231 አገሮች ውስጥ በሰዎች ቤት፣ በመንገዶች አልፎ ተርፎም በወህኒ ቤቶች ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የርኅራኄ ሥራ በማካሄድ ላይ ናቸው
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቴሌቪዥን እንደሚተላለፈው ላለ ዓመፅ ራስን ማጋለጥ ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን እንዳናሳይ ጠንቅ ይሆንብናል