ይሖዋ የሚገዛው በርኅራኄ ነው
በታሪክ ዘመናት በሙሉ ብዙ ሰብዓዊ ገዥዎች የጨበጡትን ሥልጣን አሳቢነት በጎደለው መንገድ በመጠቀም ተገዥዎቻቸውን ለሥቃይ ዳርገዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ አንድን ብሔር ማለትም እስራኤልን በመምረጥና በርኅራኄ በማስተዳደር ከሰብዓዊ ገዥዎች የተለየ መሆኑን አሳይቷል።
እስራኤላውያን፣ ገና በጥንቷ ግብጽ ባርነት ሥር በነበሩበት ጊዜ ይሖዋ እንዲረዳቸው ያቀረቡለትን ልመና ሰምቷል። “በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፣ . . . በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው።” (ኢሳይያስ 63:9) ይሖዋ እስራኤላውያንን አድኗል፣ በተአምር መግቧቸዋል እንዲሁም የራሳቸው የሆነ ምድር ሰጥቷቸዋል።
በተጨማሪም ይሖዋ ለዚህ ብሔር በሰጠው ሕግ ውስጥ ርኅሩኅ ባሕሪውን በግልጽ መመልከት ይቻላል። ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ልጆችን፣ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶችንና መፃተኞችን በርኅራኄ እንዲይዟቸው እስራኤላውያንን አዟቸው ነበር። አካለ ስንኩል ከሆኑ ሰዎች ተገቢ ያልሆነ ጥቅም መውሰድ አልነበረባቸውም።
ችግረኞች ለሆኑ ሰዎች ርኅራኄ እንዲያሳዩ ሕጉ ያዝዝ ነበር። ድሆች ከመከር አጨዳ በኋላ የቀረውን መቃረም ይችሉ ነበር። ዕዳ በሰንበት (በሰባተኛው) ዓመት ይሰረዝ ነበር። ተሽጦ የነበረ የውርስ መሬት በኢዮቤልዩ (በ50ኛው) ዓመት ላይ ለወራሹ መመለስ ነበረበት። ኤንሸንት ኢዝራኤል—ኢትስ ላይፍ ኤንድ ኢንስቲቱሺንስ እንዲህ ይላል:- “በእስራኤል ውስጥ በጊዜያችን እንዳለው ዓይነት ማኅበራዊ ልዩነት ፈጽሞ አልነበረም።” “በሰፈራ መኖር በጀመሩባቸው ጊዜያት ሁሉም እስራኤላውያን ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ የሆነ የኑሮ ደረጃ ነበራቸው።”—ዘሌዋውያን 25:10፤ ዘዳግም 15:12-14፤ 24:17-22፤ 27:18
የይሖዋን ርኅራኄ መኮረጅ
የአምላክ አገልጋዮች የእሱን ርኅራኄ ተላብሰዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በታሪክ ዘመናት በሙሉ አንዳንድ አዳዲስ ነገሥታት ሥልጣን ላይ ሲወጡ በሕይወት የቀሩትን የቀድሞ ንጉሣዊ ቤተሰብ አባላት ገድለዋል። የይሖዋ አገልጋይ የነበረው ዳዊት ግን እንዲህ አላደረገም። ዳዊት ንጉሥ ሳኦል ከሞተ በኋላ የሳኦል የልጅ ልጅና ወራሽ የነበረውን ሜምፊቦስቴን በሕይወት ተጠብቆ እንዲኖር አድርጓል። “ንጉሡም የሳኦልን ልጅ የዮናታንን ልጅ ሜምፊቦስቴን ራራለት።”—2 ሳሙኤል 21:7 NW
የኢየሱስን ያህል የይሖዋን ርኅራኄ የኮረጀ ማንም ሰው የለም። የፈጸማቸው ብዙዎቹ ተአምራት በአምላካዊ ርኅራኄ ተገፋፍቶ ያደረጋቸው ነበሩ። በአንድ ወቅት አንድ ለምጻም “ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት ለመነው። ኢየሱስ አዘነለትና እጁን ዘርግቶ በመዳሰስ “እወድዳለሁ ንጻ አለው።” (ማርቆስ 1:40-42) በሌላ ወቅት ደግሞ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ኢየሱስን ይከተሉት ነበር። በዚያ ሁካታ መሀል የኢየሱስን ትኩረት የሳቡ ሁለት ዕውሮች እንዲህ በማለት ጮኹ:- “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ማረን። . . . ኢየሱስም አዘነላቸውና ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ፣ ወዲያውም አዩ።”—ማቴዎስ 20:29-34
የሕዝብ መብዛት ኢየሱስ ለሌሎች ሰዎች ያለውን የአሳቢነት ስሜት አላደበዘዘውም። በአንድ ወቅት እሱን ይከተሉት የነበሩት ሕዝብ ምንም ሳይበሉ ረዘም ላለ ጊዜ ቆይተው ስለነበር ‘ለሕዝቡ አዝንላቸዋለሁ’ በማለት ተናግሯል። ስለዚህም በተአምር መገባቸው። (ማርቆስ 8:1-8) ኢየሱስ ከቦታ ቦታ በሚዘዋወርበት ጊዜ ሕዝቡን ማስተማር ብቻ ሳይሆን ለሚያስፈልጋቸው ነገርም ንቁ ነበር። (ማቴዎስ 9:35, 36) አንድ ጊዜ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ዓይነት ጉዞ ካደረጉ በኋላ ለማረፍ ቀርቶ ለመብላት እንኳ ፋታ ማግኘት አልቻሉም ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “በታንኳም ብቻቸውን ወደ ምድረ በዳ ሄዱ። ሰዎችም ሲሄዱ አዩአቸው ብዙዎችም አወቁአቸውና ከከተሞች ሁሉ በእግር እየሮጡ ወዲያ ቀደሙአቸው ወደ እርሱም ተሰበሰቡ። ኢየሱስም ወጥቶ ብዙ ሕዝብ አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፣ ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር።”—ማርቆስ 6:31-34
የኢየሱስን ስሜት የነካው ሕዝቡ ያለባቸው ሕመምና ድህነት ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ሁኔታቸውም ነበር። መሪዎቻቸው መጠቀሚያ አድርገዋቸው ስለነበር ኢየሱስ “አዘነላቸው።” “አዘነላቸው” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ከአንጀት መራራት” ማለት ነው። በእርግጥም ኢየሱስ ርኅሩኅ ሰው ነበር!
ጭካኔ በሞላበት ዓለም ውስጥ ርኅራኄ ማሳየት
በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ የይሖዋ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ ነው። በጥንቷ እስራኤል ያደርግ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም አምላክ ሕዝቡን የሚገዛው በርኅራኄ ነው። “እኔ በምሠራበት ቀን እነርሱ የእኔ ገንዘብ ይሆናሉ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ . . . እምራቸዋለሁ [“እራራላቸዋለሁ፣” NW]።”—ሚልክያስ 3:17
ይሖዋ ርኅራኄ እንዲያሳያቸው የሚፈልጉ ሁሉ የእርሱን መንገድ መኮረጅ አለባቸው። እርግጥ ዛሬ የምንኖረው የተቸገሩ ሰዎችን ከመርዳት ይልቅ ያላቸውን የኑሮ ደረጃ ጠብቀው ለመኖር የሚፈልጉ ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ነው። በሥልጣን ላይ የሚገኙ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ሠራተኞቻቸውንና ተጠቃሚውን ሕዝብ አደጋ ላይ በመጣል ጥቅም ለማግኘት ይጥራሉ። ከብዙ ሰዎች ልብ ውስጥ ርኅራኄ እንዲጠፋ ያደረገውን በጊዜያችን ያለውን የሥነ ምግባር ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-4 ላይ በትክክል ገልጾታል።
ያም ሆኖ ግን ርኅራኄ ማሳየት የምንችልባቸው አጋጣሚዎች ማግኘታችን አይቀርም። ለጎረቤቶቻችን አንዳንድ አስፈላጊ እርዳታ ማበርከት እንችል ይሆን? ልንጠይቀው የምንችል የታመመ ሰው ይኖር ይሆን? “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው፤ ደካሞችን እርዷቸው” የሚለውን ምክር በመከተል የተጨነቁ ሰዎችን ማጽናናት እንችል ይሆን?—1 ተሰሎንቄ 5:14
በተጨማሪም ርኅራኄ ሌሎች ሰዎች ስህተት በሚሠሩበት ጊዜ የሚጎዱ ቃላትን በመናገር አጸፋውን ከመመለስ ይጠብቀናል። “መራርነትና ንዴት ቊጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፣ እግዚአብሔርም በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ” ተብለናል።—ኤፌሶን 4:31, 32
ርኅራኄ ሥልጣናችንን አላግባብ ከመጠቀም ይጠብቀናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ” ይላል። (ቆላስይስ 3:12) ትሑቶች መሆናችን ራሳችንን በእኛ ሥር ባሉት ሰዎች ቦታ ላይ አድርገን ለማየት ያስችለናል። ርኅሩኅ ሰው ትሑትና ምክንያታዊ እንጂ ምንም ቢደረግለት የማያስደስተው አይደለም። ለሥራ ቅልጥፍና ሲባል ሰዎችን እንደ አንድ የማሽን ክፍል አድርጎ መመልከት አይገባም። በተጨማሪም በቤተሰብ ውስጥ ርኅሩኅ ባሎች ሚስቶቻቸው ተሰባሪ እቃዎች መሆናቸውን መዘንጋት አይኖርባቸውም። (1 ጴጥሮስ 3:7) ኢየሱስ ባሳየው ርኅራኄ ላይ ማሰላሰላችን በእነዚህ ሁሉ ሊረዳን ይችላል።
ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ለሰዎች በጣም ያዝን እንደነበረ ሁሉ አሁንም ሆነ ወደፊት ርኅሩኅ ገዥ እንደሚሆን ልንተማመን እንችላለን። በመዝሙር 72 ላይ ስለ እሱ የተነገረ ትንቢታዊ ቃል እንዲህ ይላል:- “ለችግረኞች ሕዝብ በጽድቅ ትፈርዳለህ፣ የድሆችንም ልጆች ታድናለህ፤ ክፉውንም ታዋርደዋለህ። ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፣ ከወንዝም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይገዛል። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል።”—መዝሙር 72:4, 8, 13
የአምላክ ቃል እንዲህ በማለት ይተነብያል:- “ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል፣ ለምድርም የዋሆች በቅንነት ይበይናል፤ . . . ክፉዎችን ይገድላል።” ጨካኝና የአውሬነት ጠባይ የነበራቸው ሰዎች እንኳ የአኗኗር መንገዳቸውን እንዴት እንደሚቀይሩ ከገለጸ በኋላ ትንቢቱ በመቀጠል “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና” ይላል። (ኢሳይያስ 11:4-9) ይህ ትንቢት ይሖዋን የሚያውቅና ርኅራኄውን የሚኮርጅ ምድር አቀፍ የሰዎች ኅብረተሰብ እንደሚኖር ተስፋ የሚሰጥ ነው!