“ከታላቁ መከራ” በፊት ደህንነት ወደሚገኝበት ስፍራ መሸሽ
“ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ . . . በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ።”—ሉቃስ 21:20, 21
1. አሁንም ገና የዓለም ክፍል የሆኑ ሁሉ በአፋጣኝ መሸሽ ያለባቸው ለምንድን ነው?
የሰይጣን ዓለም ክፍል የሆኑ ሁሉ በአፋጣኝ መሸሽ ይኖርባቸዋል። የአሁኑ የነገሮች ሥርዓት ከምድር ገጽ ላይ ተጠራርጎ በሚጠፋበት ጊዜ ከጥፋቱ በሕይወት ለመትረፍ ከፈለጉ ከይሖዋ ጎን መሰለፋቸውንና ሰይጣን ገዥ የሆነለት ዓለም ክፍል አለመሆናቸውን የሚያረጋግጥ አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል።—ያዕቆብ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 2:17
2, 3. በማቴዎስ 24:15-22 ላይ ከተመዘገቡት የኢየሱስ ቃላት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቀጥሎ የምንወያይባቸው የትኞቹ ጥያቄዎች ናቸው?
2 ኢየሱስ ስለ ነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ በተናገረው ታላቅ ትንቢት ላይ ከማንኛውም የሐሰት ሃይማኖት ንክኪ መራቅን የሚጨምረው ይህ ዓይነቱ ሽሽት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አበክሮ ገልጿል። በማቴዎስ 24:4-14 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ትንቢት ብዙ ጊዜ እንጠቅሳለን። ቀጥሎ ባሉት ቁጥሮች ላይ የሚገኘውም ትንቢት ከዚያ ያላነሰ አስፈላጊ ትርጉም አለው። መጽሐፍ ቅዱሳችሁን አውጥታችሁ ከ15 እስከ 22 ያሉትን ቁጥሮች እንድታነቡ እናበረታታችኋለን።
3 ይህ ትንቢት ምን ትርጉም አለው? በመጀመሪያው መቶ ዘመን ‘ጥፋት የሚያመጣው ርኩሰት’ ምን ነበር? “በተቀደሰችው ስፍራ” መቆሙስ ምን ያመለክት ነበር? ለእኛስ ምን ትርጉም አለው?
“አንባቢው ያስተውል”
4. (ሀ) ዳንኤል 9:27 አይሁዶች መሲሑን አንቀበልም ማለታቸው ምን እንደሚያስከትልባቸው ይናገራል? (ለ) ኢየሱስ ይህንን ሲናገር “አንባቢው ያስተውል” ያለው ለምንድን ነው?
4 ኢየሱስ በማቴዎስ 24:15 ላይ የጠቀሰው በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈውን መሆኑን ልብ በሉ። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ላይ ስለ መሲሑ መምጣትና የአይሁድ ብሔር መሲሑን ባለመቀበሉ ስለሚደርስበት ፍርድ ይተነብያል። የቁጥር 27 የመጨረሻ ክፍል “በርኩሰትም ጫፍ ላይ አጥፊው ይመጣል” ይላል። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) የጥንት የአይሁድ አፈ ታሪክ ይህ የዳንኤል ትንቢት ክፍል በኢየሩሳሌም የነበረው የይሖዋ ቤተ መቅደስ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በአንቲዮከስ አራተኛ በመርከሱ ፍጻሜውን እንዳገኘ ይናገራል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “አንባቢው ያስተውል” በማለት አስጠንቅቋል። አንቲዮከስ አራተኛ ቤተ መቅደሱን ማርከሱ ጸያፍ ነገር ቢሆንም ለኢየሩሳሌምም ሆነ ለቤተ መቅደሱ ወይም ለአይሁድ ብሔር መጥፋት ምክንያት አልሆነም። ስለዚህ ኢየሱስ ይህ ትንቢት ገና ወደፊት የሚፈጸም እንጂ ያለፈ ነገር እንዳልሆነ አድማጮቹ እንዲገነዘቡ ማስጠንቀቁ ነበር።
5. (ሀ) የወንጌል ዘገባዎችን ማነጻጸር በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን ‘የጥፋት ርኩሰት’ ለማወቅ የሚያስችለን እንዴት ነው? (ለ) በ66 እዘአ ሴስትየስ ጋለስ የሮም ሠራዊትን ወደ ኢየሩሳሌም ያዘመተው ለምንድን ነው?
5 በትኩረት ነቅተው መጠባበቅ የነበረባቸው ‘የጥፋት ርኩሰት’ ምን ነበር? የማቴዎስ ዘገባ “የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ” እንደሚል ልናስተውል ይገባል። ሆኖም ስለዚሁ ጉዳይ የሚተርከው ሉቃስ 21:10 “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ” ይላል። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) በ66 እዘአ በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ኢየሱስ የተናገረው ይህ ትንቢት ሲፈጸም ተመልክተዋል። ኢየሩሳሌም በአይሁድና በሮማውያን ባለ ሥልጣኖች መካከል ተፈጥረው በነበሩ በርካታ ግጭቶች ምክንያት በሮም ላይ ይደረግ የነበረው ዓመፅ የሚጠነሰስባት ከተማ ሆና ነበር። በዚህም ምክንያት በይሁዳ፣ በሰማርያ፣ በገሊላ፣ በዴካፖሊስ፣ በፊንቄ እንዲሁም በስተሰሜን በሶርያና በስተደቡብ እስከ ግብጽ ድረስ የተነሳው ዓመፅ ተፋፍሞ ነበር። ከሶርያ የመጣ በሴስትየስ ጋለስ የሚመራ የሮማ ሠራዊት በዚህ የሮማ ግዛት ክፍል መጠነኛ ሰላም ለማስፈን ሲል አይሁዳውያን “ቅድስት ከተማ” ብለው ይጠሯት ወደነበረችው ወደ ኢየሩሳሌም ዘመተ።—ነህምያ 11:1፤ ኢሳይያስ 52:1
6. ጥፋት ሊያመጣ የሚችል ‘ርኩስ ነገር’ ‘በተቀደሰው ቦታ’ የቆመው እንዴት ነበር?
6 የሮማ ሠራዊት አርማ የመያዝ ልማድ ነበረው። ይህን አርማ ሮማውያኑ እንደ ቅዱስ ነገር ሲቆጥሩት አይሁዳውያን ግን እንደ ጣዖት ይመለከቱት ነበር። በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ‘የጥፋት ርኩሰት’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በዋነኛነት የሚሠራበት ጣዖታትንና የጣዖት አምልኮን ለማመልከት ነው።a (ዘዳግም 29:17) አይሁዳውያን ለመቋቋም ጥረት ቢያደርጉም ይህ ጣዖታዊ አርማ ይዞ የዘመተው የሮማ ሠራዊት በኅዳር ወር 66 እዘአ ወደ ኢየሩሳሌም ዘልቆ ከገባ በኋላ በላይኛይቱ ከተማ፣ በስተ ምዕራብ በኩል ሠፍሮ የቤተ መቅደሱን ሰሜናዊ ቅጥር ማፍረስ ጀመረ። በኢየሩሳሌም ላይ ጥፋት ሊያመጣ የሚችል ‘ርኩስ ነገር’ ‘በተቀደሰ ቦታ ቆሞ እንደነበረ’ የሚያጠራጥር ነገር አልነበረም! ታዲያ አንድ ሰው እንዴት መሸሽ ይችላል?
በጥድፊያ መሸሽ ያስፈልግ ነበር!
7. የሮማ ሠራዊት ምን ያልታሰበ እርምጃ ወሰደ?
7 በድንገት፣ የሮማ ሠራዊት ኢየሩሳሌምን በቀላሉ ሊይዝ ሲችል በሰብዓዊ ዓይን የሚታይ ምንም ምክንያት ሳይኖር ወደ ኋላው አፈገፈገ። የአይሁዳውያን አማፂ ኃይል ወደኋላቸው ያፈገፈጉትን የሮማውያን ወታደሮች ከኢየሩሳሌም 50 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ እስከምትገኘው እስከ አንቲጳጥሪስ ካሳደዱ በኋላ ተመለሱ። ወደ ኢየሩሳሌም እንደተመለሱም በቤተ መቅደሱ ተሰብስበው የጦር ስልት መንደፍ ጀመሩ። ምሽጎችንና የጦር ኃይሎችን ለማጠናከር ሲባል ወጣቶች ለውትድርና ተመለመሉ። ክርስቲያኖች በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ተካፍለው ነበርን? በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ባይካፈሉም እንኳን የሮማውያን ሠራዊት በሚመለስበት ጊዜ አደገኛ በሆነው አካባቢ ይቆዩ ይሆንን?
8. ክርስቲያኖች የኢየሱስን ትንቢታዊ ቃላት በመታዘዝ ምን አጣዳፊ እርምጃ ወሰዱ?
8 በኢየሩሳሌምና በመላው ይሁዳ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጣቸው ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ መሠረት አደገኛ ከነበረው ቀጠና ሸሽተው ወጡ። በጥድፊያ መሸሽ ያስፈልግ ነበር! ወደ ተራራማው አካባቢ ተሰደዱ። አንዳንድ ክርስቲያኖች በፍርጊያ አውራጃ፣ በፔላ አካባቢ ሳይሰፍሩ አልቀሩም። የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ ልብ ያሉ ሁሉ በሞኝነት ወደኋላቸው ተመልሰው ንብረታቸውን ለመሰብሰብ አልሞከሩም። (ከሉቃስ 14:33 ጋር አወዳድር።) እንዲህ ባለ ሁኔታ በእግር መጓዝ ለእርጉዞችና ለሚያጠቡ እናቶች ቀላል አልነበረም። ሽሽታቸው በሰንበት ምክንያት በሚጣለው እገዳ አልተደናቀፈም። በተጨማሪም የክረምቱ ወራት የቀረበ ቢሆንም ገና አልገባም። የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ ሰምተው በአስቸኳይ የሸሹ ሁሉ ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ውጭ ስለሚሆኑ ምንም ዓይነት አደጋ አይደርስባቸውም። ሕይወታቸው የተመካው የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ በመስማት ላይ ነበር።—ከያዕቆብ 3:17 ጋር አወዳድር።
9. የሮማ ሠራዊት ከምን ያህል ጊዜ በኋላ ተመለሰ? ምንስ አስከተለ?
9 በሚቀጥለው ዓመት ማለትም በ67 እዘአ ሮማውያን በአይሁዳውያን ላይ የሚያካሂዱትን የጦር ዘመቻ እንደገና ጀመሩ። በመጀመሪያ ገሊላ ተያዘች። በሚቀጥለው ዓመት ይሁዳ ተገነጠለች። በ70 እዘአ የሮማውያን ሠራዊት ራሷን ኢየሩሳሌምን ከበበ። (ሉቃስ 19:43) ረሃቡ በጣም እየከፋ መጣ። በከተማይቱ ውስጥ ተከበው የተያዙት ሰዎች እርስ በርሳቸው መገዳደል ጀመሩ። ከከተማይቱ ለማምለጥ የሞከሩም ተገደሉ። የደረሰባቸው ሁኔታ ልክ ኢየሱስ እንዳለው “ታላቅ መከራ” ነበር።—ማቴዎስ 24:21
10. በማስተዋል የምናነብ ከሆነ ምን ሌላ ነገር እንገነዘባለን?
10 ይሁን እንጂ የኢየሱስ ትንቢት በዚሁ ብቻ ተፈጽሞ አብቅቷልን? አላበቃም። ብዙ ነገር መፈጸም ነበረበት። ኢየሱስ አድማጮቹን እንዳስጠነቀቀው ቅዱሳን ጽሑፎችን አስተውለን ብናነብ ይህ ትንቢት ዳግመኛ ፍጻሜ እንደሚኖረው ማስተዋል አያዳግተንም። በተጨማሪም በሕይወታችን ላይ ስለሚኖረው ትርጉም በጥሞና እናስባለን።
የዘመናችን ‘የጥፋት ርኩሰት’
11. ዳንኤል በየትኞቹ ሌሎች ሁለት ቦታዎች ላይ ‘የጥፋት ርኩሰት’ የሚለውን ሐረግ ጠቅሷል? እዚያስ ላይ የሚናገረው ስለየትኛው ጊዜ ነው?
11 ቀደም ሲል በዳንኤል 9:27 ላይ ከተመለከትነው በተጨማሪ በዳንኤል 11:31 እና 12:11 ላይ ‘የጥፋት ርኩሰት’ የሚለው ሐረግ የተጠቀሰ መሆኑን አስተውሉ። በእነዚህ የኋለኞቹ ጥቅሶች ላይ ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋት የተነገረ ነገር የለም። እንዲያውም በዳንኤል 12:11 ላይ የሚገኘው ቃል ስለ “ፍጻሜው ዘመን” ከሚናገረው ጥቅስ ሁለት ቁጥሮች ብቻ ዝቅ ብሎ ይገኛል። (ዳንኤል 12:9) ከ1914 ወዲህ የምንኖረው በዚህ “የፍጻሜ ዘመን” ውስጥ ነው። ስለዚህ የዘመናችን ‘የጥፋት ርኩሰት’ ምን እንደሆነ ለይተን ለማወቅና ለአደጋ ከተጋለጠው አካባቢ ለመውጣት ንቁዎች መሆን ይኖርብናል።
12, 13. የቃል ኪዳኑ ማኅበር የዘመናችን ‘የጥፋት ርኩሰት’ ነው ቢባል ተስማሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?
12 ይህ የዘመናችን ‘የጥፋት ርኩሰት’ ምንድን ነው? ማስረጃው ዓለም ወደ መጨረሻው ጊዜ ከገባበት ከጥቂት ዓመታት በኋላ ማለትም በ1920 የተቋቋመው የቃል ኪዳኑ ማኅበር እንደሆነ ያሳያል። ሆኖም የቃል ኪዳኑ ማኅበር ‘ጥፋት የሚያመጣው ርኩሰት’ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
13 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ርኩስ ነገር’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በዋነኛነት የሚያመለክተው ጣዖታትንና የጣዖት አምልኮን እንደነበረ አስታውሱ። ታዲያ የቃል ኪዳኑ ማኅበር እንደ ጣዖት ተመልኮ ነበርን? በእርግጥ ተመልኳል! ቀሳውስት ይህን ድርጅት ‘በቅዱስ ስፍራ’ ከማስቀመጣቸውም በላይ ተከታዮቻቸው በከፍተኛ ስሜት አምልከውታል። በአሜሪካ የክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት ፌደራላዊ ጉባኤ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር “በምድር ላይ የአምላክ መንግሥት ፖለቲካዊ መግለጫ” እንደሚሆን አሳውቆ ነበር። የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የመንግሥታት ማኅበርን ቃል ኪዳን እንዲያጸድቅ የሚያሳስቡ በርካታ ደብዳቤዎች ከሃይማኖታዊ ቡድኖች ደርሰውታል። በብሪታንያ የባፕቲስቶች፣ የኮንግርጌሽናሊስቶችና የፕሪስብተሪያውያን ጠቅላይ ጉባኤ “[በምድር ላይ ሰላም] ለማስፈን የሚያስችል ብቸኛ መሣሪያ” ሲል አወድሶታል።—ራእይ 13:14, 15ን ተመልከት።
14, 15. የቃል ኪዳኑ ማኅበር በኋላም የተባበሩት መንግሥታት ‘በተቀደሰው ሥፍራ’ የቆሙት በምን መንገድ ነው?
14 የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት በ1914 በሰማይ የተቋቋመ ቢሆንም ብሔራት ለየራሳቸው ሉዓላዊነት መዋጋታቸውን ቀጥለው ነበር። (መዝሙር 2:1-6) የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ለማቋቋም ሐሳብ በቀረበበት ጊዜ በመጀመሪያው ዓለም ጦርነት የተካፈሉት ብሔራትና የብሔራቱን ሠራዊቶች ባርከው ወደ ዘመቻ የላኩት ቀሳውስት የአምላክን ሕግ ፈጽመው የጣሉ መሆናቸውን አሳይተዋል። የክርስቶስን ንግሥና አልተቀበሉም። በዚህም ምክንያት የአምላክ መንግሥት ብቻ ሊያከናውን የሚችለውን ሥራ ለሰብዓዊ ድርጅት ሰጡ። የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርን በማይገባው ‘ቅዱስ ስፍራ’ አስቀመጡ።
15 የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ወራሽ የሆነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደግሞ ጥቅምት 24 ቀን 1945 ተቋቋመ። ከጊዜ በኋላ የሮማ ጳጳሳት ይህን ድርጅት “የመጨረሻው የሰላምና የስምምነት ተስፋ” እንዲሁም “ከፍተኛው የሰላምና የፍትሕ መድረክ” ሲሉ አወድሰውታል። አዎን፣ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርም ሆነ የእርሱ ተተኪ የሆነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአምላክና በሕዝቦቹ ዓይን ‘አስጸያፊ’ ሆኗል።
የሚሸሸው ከየት ነው?
16. በዛሬው ጊዜ ጽድቅ አፍቃሪዎች ከምን ነገር እንዲሸሹ ይፈለግባቸዋል?
16 ጽድቅ ወዳዶች ሁሉ ይህን ‘ሲመለከቱ’ ማለትም ይህ ዓለም አቀፍ ድርጅት ምን እንደሆነ ሲገነዘቡና እንዴት ባለ መንገድ በመመለክ ላይ እንደሆነ ሲያስተውሉ ደህንነት ወደሚገኝበት ሥፍራ መሸሽ ይኖርባቸዋል። የሚሸሹት ከየት ነው? የሚሸሹት የከዳተኛይቱ ኢየሩሳሌም ዘመናዊ ጥላ ከሆነችው ከሕዝበ ክርስትና፣ ብሎም ሕዝበ ክርስትና ዋነኛ ክፍል ከሆነችበት ከዓለም አቀፉ የሐሰት ሃይማኖት ሥርዓት ማለትም ከታላቂቱ ባቢሎን ነው።—ራእይ 18:4
17, 18. የጊዜያችን ‘የጥፋት ርኩሰት’ ምን እርምጃ ይወስዳል?
17 በተጨማሪም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የሮማውያን ሠራዊት ‘ርኩስ የሆነውን’ ጣዖታዊ አርማ ይዞ ‘ወደ ቅዱሱ ሥፍራ’ ማለትም ወደ አይሁድ ቅዱስ ከተማ ዘልቆ የገባው ኢየሩሳሌምንና የአምልኮ ሥርዓትዋን ለማጥፋት እንደነበረ አስታውሱ። በዘመናችን ጥፋት የሚመጣው በአንድ ከተማ ወይም በሕዝበ ክርስትና ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው ምድር በሚገኘው የሐሰት ሃይማኖት ሥርዓት ላይ ነው።—ራእይ 18:5-8
18 በራእይ 17:16 ላይ እንደተመዘገበው አንድ ቀይ አውሬ፣ ማለትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአመንዝራይቱ ታላቂቱ ባቢሎን ላይ እንደሚነሳና እንደሚያጠፋት ተተንብዮአል። ሥዕላዊ በሆኑ ቃላት በመጠቀም እንዲህ ይላል፦ “ያየሃቸው አሥር ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፣ ሥጋዋንም ይበላሉ፣ በእሳትም ያቃጥሉአታል።” ይህ ምን ውጤት እንደሚያስከትል መገመት እንኳ ይከብዳል። በየትኛውም የምድር ክፍል የሚገኝ የሐሰት ሃይማኖት ድምጥማጡ ይጠፋል። ይህም ታላቁ መከራ የጀመረ መሆኑን ያሳያል።
19. የተባበሩት መንግሥታት ከተመሠረተ ጀምሮ እነማን የዚህ ድርጅት አባል ሆነዋል? ይህስ ትኩረት የሚስብ የሆነው ለምንድን ነው?
19 የተባበሩት መንግሥታት በ1945 እንቅስቃሴውን ከጀመረ ወዲህ በአባል መንግሥታት መካከል በአምላክ የማያምኑ ፀረ ሃይማኖታዊ ኃይሎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ማስተዋል ይቻላል። እነዚህ ኃይላት በብዙ የምድር ክፍሎች፣ በተለያዩ ጊዜያት ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች በእጅጉ እንዲገደቡ ወይም ጭራሹኑ እንዲታገዱ አድርገዋል። ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በብዙ አገሮች መንግሥታት በሃይማኖታዊ ቡድኖች ላይ የሚያደርጉትን ተጽዕኖ ላላ አድርገዋል። አንዳንዶች ይህን በመመልከት በሃይማኖት ላይ አንዣብቦ የነበረው አደጋ ፈጽሞ የተወገደ ይመስላቸው ይሆናል።
20. የዓለም ሃይማኖቶች ምን ዓይነት ስም እያተረፉ ነው?
20 የታላቂቱ ባቢሎን ሃይማኖቶች በዓለም ውስጥ ግጭትና መለያየት መፍጠራቸውን ቀጥለዋል። የዜና ርዕሶች ተዋጊ ኃይሎችንና አሸባሪ ቡድኖችን ሲጠቅሱ ብዙውን ጊዜ የምን ሃይማኖት ተከታዮች እንደሆኑ ጭምር ይገልጻሉ። ፀጥታ አስከባሪ ፖሊሶችና ወታደሮች በተለያዩ ተቀናቃኝ የሃይማኖት ቡድኖች መካከል የሚደረጉ ግጭቶችን ለማስቆም ቤተ መቅደሶችን ወርረዋል። ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ፖለቲካዊ አብዮት እንዲካሄድ የገንዘብ ድጋፍ ይሰጣሉ። ሃይማኖታዊ ጥላቻ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተለያዩ ጎሣዎች መካከል ሰላም ለማስፈን የሚያደርገውን ጥረት አምክኖበታል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የሚገኙ ኃይላት ሰላምና ደህንነት እንዲሰፍን በሚያደርጉት ጥረት ማንኛውም ዓይነት ሃይማኖታዊ ተጽዕኖ እንቅፋት እንዲሆንባቸው አይፈልጉም።
21. (ሀ) ታላቂቱ ባቢሎን መቼ መጥፋት እንዳለባት የሚወስነው ማን ነው? (ለ) ታላቂቱ ባቢሎን ከመጥፋቷ በፊት ልናደርገው የሚገባ አጣዳፊ ነገር ምንድን ነው?
21 ሌላም ልንዘነጋው የማይገባ አስፈላጊ ነገር አለ። ታላቂቱ ባቢሎንን የሚያጠፉት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ “ቀንድ” ያላቸው ኃይሎች ቢሆኑም ይህ ጥፋት የመለኮታዊ ፍርድ መግለጫ ነው። ፍርዱ አምላክ በቀጠረው ጊዜ ይፈጸማል። (ራእይ 17:17) ይህ እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ ምን ማድረግ ይኖርብናል? መጽሐፍ ቅዱስ “ከመካከልዋ ውጡ፣” ከታላቂቱ ባቢሎን ውጡ በማለት መልሱን ይሰጠናል።—ራእይ 18:4
22, 23. ከታላቂቱ ባቢሎን መሸሸ ምን ነገር ይጠይቃል?
22 ይህ ሽሽት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ኢየሩሳሌምን ትተው ሲሸሹ እንዳደረጉት የመኖሪያ አካባቢ መለወጥ አይደለም። ይህ ሽሽት ከሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች፣ አዎን፣ ከማንኛውም የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል መሸሽ ነው። ከሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች ብቻ ሳይሆን እነዚህ ድርጅቶች ከሚያራምዱት ባሕልና አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ መለየት ማለት ነው። ወደ ይሖዋ ቲኦክራሲያዊ ድርጅት ሸሽቶ ማምለጥ ማለት ነው።—ኤፌሶን 5:7-11
23 የይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮች ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የዘመናችን ርኩሰት እንደሆነና በማይገባው ቦታ እንደቆመ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገነዘቡ ምን እርምጃ ወሰዱ? ቀድሞውኑ ራሳቸውን ከሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አግልለው ነበር። ቢሆንም በመስቀል እንደመጠቀም፣ ገናን እና ሌሎች አረማዊ በዓላትን እንደማክበር ከመሳሰሉት አንዳንድ የሕዝበ ክርስትና ባሕሎችና ልማዶች ገና እንዳልተላቀቁ እየገባቸው መጣ። ስለ እነዚህ ልማዶች እውነቱን እንዳወቁ ወዲያው እርምጃ ወሰዱ። በኢሳይያስ 52:11 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ምክር ታዘዙ፦ “እናንተ የእግዚአብሔር ዕቃ የምትሸከሙ ሆይ፣ እልፍ በሉ፣ እልፍ በሉ፣ ከዚያ ውጡ፣ ርኩስን ነገር አትንኩ፣ ከመካከልዋ ውጡ፣ ንጹሐን ሁኑ።”
24. በተለይ ከ1935 ወዲህ እነማንም ጭምር እየሸሹ ነው?
24 በተለይ ከ1935 ወዲህ ቁጥራቸው እየጨመረ የሄደና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው እጅግ ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል። እነዚህም ‘የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰው ሥፍራ እንደቆመ ተመልክተዋል፤’ እንዲሁም ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስተውለዋል። ውሳኔ ካደረጉ በኋላ ስሞቻቸው የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል ከሆኑ ድርጅቶች የአባሎች መዝገብ እንዲሰረዝ አድርገዋል።—2 ቆሮንቶስ 6:14-17
25. አንድ ሰው ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ያለውን ማንኛውንም ግንኙነት ከማቆም በተጨማሪ ምን ይፈለግበታል?
25 ይሁን እንጂ ከታላቂቱ ባቢሎን ክፍል መሸሽ የሐሰት ሃይማኖትን ከመተው የበለጠ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። በትልልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት፣ በመንግሥት አዳራሾች በሚደረጉት ስብሰባዎች አልፎ አልፎ መገኘት ወይም በወር አንድ ወይም ሁለት ጊዜ መስክ አገልግሎት መውጣት ብቻ አይበቃም። አንድ ሰው በአካል ከታላቂቱ ባቢሎን ሊወጣ ይችላል። ነገር ግን በእርግጥ ከታላቂቱ ባቢሎን ወጥቷልን? ታላቂቱ ባቢሎን ዋነኛ ክፍል ከሆነችበት ዓለም ራሱን ሙሉ በሙሉ ለይቷልን? አሁንም የታላቂቱን ባቢሎን መንፈስ፣ ማለትም የአምላክን የጽድቅ ሕግጋት የሚያቃልለውን መንፈስ የሙጥኝ ብሏልን? የጾታ ሥነ ምግባርንና ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆንን አቅልሎ ይመለከታልን? ከመንፈሳዊ ፍላጎቶች ይልቅ ግላዊና ቁሳዊ ፍላጎቶችን ያስቀድማልን? ከታላቂቱ ባቢሎን የሸሸ ሰው ይህንን ሥርዓት መምሰል የለበትም።—ማቴዎስ 6:24፤ 1 ጴጥሮስ 4:3, 4
ሽሽትህን ምንም ነገር እንዲያደናቅፍብህ አትፍቀድ!
26. ሽሽቱን ከመጀመር አልፈን በተሳካ ሁኔታ ለመጨረስ ምን ነገር ይረዳናል?
26 ከጥፋት ለመትረፍ በምናደርገው ሽሽት ትተነው የመጣነውን ነገር በምኞት መመልከት አይኖርብንም። (ሉቃስ 9:62) አእምሯችንና ልባችን በአምላክ መንግሥትና ጽድቅ ላይ እንዳተኮረ እንዲቀጥል ማድረግ ያስፈልገናል። አምላክ እንዲህ ላለው የታዛዥነት አካሄድ ዋጋ እንደሚሰጥ እርግጠኛ ሆነን እነዚህን ነገሮች ከሁሉ አስቀድመን እንደምንፈልግ በማሳየት እምነታችንን በተግባር ለመግለጽ ቆርጠናልን? (ማቴዎስ 6:31-33) በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተው ጠንካራ እምነታችን ወደፊት በዓለም መድረክ የሚፈጸሙትን ታላላቅ ትርጉም ያላቸው ክንውኖች ግልጽ የሚሆኑበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቅን እንዲህ እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል።
27. እዚህ ላይ የቀረቡትን ጥያቄዎች በቁም ነገር ልናስብባቸው የሚገባን ለምንድን ነው?
27 መለኮታዊው ፍርድ በታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት ይጀምራል። ይህች አመንዝራ መሰል የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ለዝንተ ዓለም ከሕልውና ትደመሰሳለች። ይህ የሚሆንበት ጊዜ በጣም ቅርብ ነው! ይህ ታላቅ ቀን በሚመጣበት ጊዜ በግለሰብ ደረጃ እንዴት ባለ ሁኔታ እንገኝ ይሆን? የሰይጣን ክፉ ሥርዓት በሙሉ በሚወድምበት በታላቁ መከራ መቋጫ ላይ ከማን ጎን እንገኝ ይሆን? አሁኑኑ ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ በኩል የሚሰጠንን መመሪያ እየተከተልን አስፈላጊውን እርምጃ ከወሰድን ከሚድኑት ወገን እንደምንሆን የተረጋገጠ ነው። ይሖዋ “የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል፣ ከመከራም ሥጋት ያርፋል” ይለናል። (ምሳሌ 1:33) በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ዘመን ይሖዋን በታማኝነትና በደስታ ማገልገላችንን በመቀጠል ይሖዋን ለዘላለም ለማወደስ ብቁ መሆን እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል በተባለው (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 634-5 ተመልከት።
ታስታውሳለህን?
◻ የዘመናችን ‘የጥፋት ርኩሰት’ ምንድን ነው?
◻ ‘የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰችው ሥፍራ የቆመው’ በምን መንገድ ነው?
◻ ደህንነት ወደሚገኝበት ሥፍራ መሸሽ ምን ነገር ያጠቃልላል?
◻ እንደዚህ ያለው እርምጃ አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢየሱስ ተከታዮች ከጥፋቱ ለመትረፍ ከፈለጉ ዛሬ ነገ ሳይሉ መሸሽ አለባቸው