የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች ሆኖ ማገልገል
“ሰላምንም የሚያወራ . . . እግሩ በተራሮች ላይ እጅግ ያማረ ነው።”— ኢሳይያስ 52:7
1, 2. (ሀ) በኢሳይያስ 52:7 ላይ አስቀድሞ እንደተነገረው መታወጅ ያለበት ምሥራች ምንድን ነው? (ለ) የኢሳይያስ ትንቢታዊ ቃላት ለጥንቶቹ እስራኤላውያን ምን ትርጉም ነበራቸው?
መታወጅ ያለበት ምሥራች አለ! ይህ ምሥራች የሰላም፣ የእውነተኛ ሰላም ዜና ነው። ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጽ የመዳን መልእክት ነው። ከብዙ ዘመናት በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ ምሥራች የጻፈው ቃል በኢሳይያስ 52:7 ላይ ተመዝግቦ ቆይቶልናል። እንዲህ እናነባለን:- “የምስራች የሚናገር፣ ሰላምንም የሚያወራ፣ የመልካምንም ወሬ የምስራች የሚናገር፣ መድኃኒትንም የሚያወራ፣ ጽዮንንም:- አምላክሽ ነግሦአል የሚል ሰው እግሩ በተራሮች ላይ እጅግ ያማረ ነው።”
2 ይሖዋ ለጥንቶቹ እስራኤላውያንና ለእኛ ጥቅም ሲል ነቢዩ ኢሳይያስ ይህን ቃል እንዲጽፍ በመንፈሱ አነሳስቶታል። ታዲያ ይህ ምን ማለት ነው? ኢሳይያስ እነዚህን ቃላት በጻፈበት ጊዜ የሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት በአሦራውያን ወደ ግዞት ተወስዶ መሆን አለበት። የደቡቡ የይሁዳ መንግሥት ነዋሪዎችም ቆየት ብለው ወደ ባቢሎን ይማረካሉ። የእስራኤል ብሔር ለይሖዋ ያልታዘዘበትና በዚህም ምክንያት ከአምላክ ጋር የነበረውን ሰላም ያጣበት ጊዜ ስለነበረ የሐዘንና የጭንቀት ዘመን ነበር። ይሖዋ ራሱ እንደነገራቸው ኃጢአተኛ የሆነው አካሄዳቸው ከአምላካቸው እያራራቃቸው ነበር። (ኢሳይያስ 42:24፤ 59:2-4) ይሁን እንጂ ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል የባቢሎን በሮች ጊዜው ሲደርስ ወለል ብለው እንደሚከፈቱ አስቀድሞ ተናግሯል። የአምላክ ሕዝቦች ነፃ ወጥተው ወደ አገራቸው ይመለሱና የይሖዋን ቤተ መቅደስ ዳግመኛ ይሠራሉ። ጽዮን መልሳ ትቋቋማለች፤ የእውነተኛው አምላክ አምልኮም እንደገና በኢየሩሳሌም መከናወኑን ይቀጥላል።— ኢሳይያስ 44:28፤ 52:1, 2
3. እስራኤላውያን ወደ አገራቸው ተመልሰው እንደሚቋቋሙ የተሰጠው የተስፋ ቃል የሰላም ትንቢትም ነበር ለማለት የሚቻለው እንዴት ነው?
3 ይህ የነጻነት ተስፋ የሰላም ትንቢትም ነበር። እስራኤላውያን ይሖዋ ወደ ሰጣቸው ርስት ተመልሰው መግባታቸው የአምላክን ምሕረትና እነርሱ ንስሐ የገቡ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። ከአምላክ ጋር ሰላም መፍጠራቸውን ያመለክታል።—ኢሳይያስ 14:1፤ 48:17, 18
“አምላክሽ ነግሦአል”
4. (ሀ) በ537 ከዘአበ ‘ይሖዋ ነግሦአል’ ሊባል የሚችለው በምን መንገድ ነው? (ለ) ይሖዋ በኋለኞቹ ዓመታት ለሚመጡት ሕዝቦቹ ጥቅም ሲል ነገሮችን ያስተካከለው እንዴት ነው?
4 ይሖዋ በ537 ከዘአበ ይህን የማዳን ሥራ በፈጸመ ጊዜ ለጽዮን “አምላክሽ ነግሦአል” የሚል ማስታወቂያ ሊነገር ችሏል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ “የዘላለም ንጉሥ” ነው። (ራእይ 15:3 አዓት) ይሁን እንጂ ይህ ሕዝቦቹ ያገኙት ነጻነት የይሖዋ ሉዓላዊነት በአዲስ መልክ የተገለጸበት አጋጣሚ ነው። እስከዚያ ዘመን ከተነሱት የዓለም ኃያል መንግሥታት በሙሉ ታላቅ ከነበረው ግዛት የሚበልጥ ኃይል እንዳለው በአስደናቂ ሁኔታ አሳይቷል። (ኤርምያስ 51:56, 57) በሕዝቦቹ ላይ የተሸረቡ ሌሎች ሤራዎችም በይሖዋ መንፈስ አሠራር እንዲከሽፉ ተደርገዋል። (አስቴር 9:24, 25) ይሖዋ በተደጋጋሚ ጊዜያት ጣልቃ በመግባት የሜዶ ፋርስ ነገሥታት ሉዓላዊ ፈቃዱን በመፈጸሙ ሥራ እንዲተባበሩ አድርጓል። (ዘካርያስ 4:6) በእነዚያ ዘመናት የተፈጸሙት አስደናቂ ክንውኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆኑት በዕዝራ፣ በነህምያ፣ በአስቴር፣ በሐጌና በዘካርያስ መጻሕፍት ተመዝግበዋል። እነዚህን መለስ ብሎ መከለስ እንዴት እምነት የሚያጠነክር ነው!
5. በኢሳይያስ 52:13 እስከ 53:12 ላይ የተገለጹት ጉልህ ክስተቶች ምንድን ናቸው?
5 ይሁን እንጂ በ537 ከዘአበና ከዚያ በኋላ የተፈጸሙት ነገሮች የመጀመሪያ ክንውኖች ብቻ ነበሩ። ኢሳይያስ በምዕራፍ 52 ላይ ከሚገኘው የተሐድሶ ትንቢት በማስከተል ስለ መሲሑ መምጣት ጽፏል። (ኢሳይያስ 52:13 እስከ 53:12) ይሖዋ መሲሕ ሆኖ በተገለጠው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በ537 ከዘአበ ፍጻሜ ካገኘው የበለጠ የነፃነትና የሰላም መልእክት ያቀርባል።
ከሁሉ የላቀው የይሖዋ የሰላም መልእክተኛ
6. ከሁሉ የላቀው የይሖዋ የሰላም መልእክተኛ ማን ነው? የትኛውስ ተልእኮ ለእርሱ እንደሚሠራ ተናግሯል?
6 ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁሉ የሚበልጥ የይሖዋ የሰላም መልእክተኛ ነው። እርሱ የአምላክ ቃል፣ ማለትም የይሖዋ የግል ቃል አቀባይ ነው። (ዮሐንስ 1:14) ኢየሱስም በዮርዳኖስ ከተጠመቀ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከዚህ አባባል ጋር በሚስማማ ሁኔታ በናዝሬት ወደሚገኘው ምኩራብ ገብቶ የመጣበትን ተልእኮ ለማስታወቅ ኢሳይያስ ምዕራፍ 61ን አነበበ። ኢየሱስ እንዲሰብክ የተላከው “መፈታትን፣” ለዕውሮችም “ማየትን” እንዲሁም በይሖዋ ፊት ተቀባይነት የማግኘት አጋጣሚ መከፈቱን የሚያካትት መልእክት እንደሆነ ያነበበው የኢሳይያስ ጥቅስ በግልጽ አስቀምጦታል። ይሁንና ኢየሱስ የሰላም መልእክት ከማወጅ የበለጠ ነገርም አከናውኗል። አምላክ የላከው ዘላቂ ሰላም የሚገኝበትንም መሠረት እንዲጥል ነበር።— ሉቃስ 4:16-21
7. በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ከአምላክ ጋር ሰላም መፍጠር ምን ውጤት ያስገኛል?
7 ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ መላእክት በቤተ ልሔም አቅራቢያ ለነበሩ እረኞች ተገልጠው “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” እያሉ አምላክን አወድሰዋል። (ሉቃስ 2:8, 13, 14 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) አዎን፣ አምላክ በልጁ በኩል ባደረገው ዝግጅት በማመናቸው ምክንያት አምላክ በጎ ፈቃዱን ያሳያቸው ሰዎች ሰላም ያገኛሉ። ታዲያ ይህ ሰላም ምን ማለት ይሆናል? የሰው ልጆች በኃጢአት የተወለዱ ቢሆኑም በአምላክ ዘንድ ንጹሕ አቋም ሊያገኙና ከእርሱም ጋር ተቀባይነት ያለው ዝምድና ሊመሠርቱ ይችላሉ ማለት ነው። (ሮሜ 5:1) በሌላ በምንም መንገድ ሊገኝ የማይችለውን ውስጣዊ እርጋታና ሰላም ሊያገኙ ይችላሉ ማለት ነበር። አምላክ በወሰነው ጊዜ በሽታንና ሞትን ጨምሮ ከአዳም የተወረሰው ኃጢአት ካስከተላቸው መዘዞች በሙሉ ነጻ ይወጣሉ። ከዚያ ወዲያ ዓይነ ስውር ወይም መስማት የተሳነው ወይም አካለ ስንኩል አይኖርም። ተስፋ አስቆራጭ ድካምና ቅስም የሚሰብር የአእምሮ መታወክ ለዘለቄታው ይወገዳሉ። በዚህ መንገድ ፍጹም ሆኖ ለዘላለም መኖር ይቻላል ማለት ነው።— ኢሳይያስ 33:24፤ ማቴዎስ 9:35፤ ዮሐንስ 3:16
8. አምላካዊ ሰላም የተሰጠው ለእነማን ነው?
8 አምላካዊ ሰላም የተሰጠው ለእነማን ነው? በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘አምላክ በመከራ እንጨት ላይ በፈሰሰው የኢየሱስ ደም አማካኝነት ሰላም በመፍጠር ሁሉንም በክርስቶስ በኩል ከራሱ ጋር ሊያስታርቅ ፈለገ’ ሲል ጽፏል። ሐዋርያው በመቀጠል ይህ እርቅ “በሰማያት ያሉትን፣” ማለትም ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ተባባሪ ወራሾች የሚሆኑትን እንደሚያቅፍ ገልጿል። በተጨማሪም “በምድር ያሉትን፣” ማለትም ምድር ሙሉ በሙሉ ገነት በምትሆንበት ጊዜ የዘላለም ሕይወት ውርሻ የማግኘት አጋጣሚ የሚኖራቸውን ሰዎች ያቅፋል። (ቆላስይስ 1:19, 20) እነዚህ ሁሉ ራሳቸውን የኢየሱስ ቤዛ ተጠቃሚዎች በማድረጋቸውና ከልባቸው አምላክን በመታዘዛቸው ከአምላክ ጋር ሞቅ ያለ ወዳጅነት ሊመሠርቱ ይችላሉ።— ከያዕቆብ 2:22, 23 ጋር አወዳድር።
9. (ሀ) ከአምላክ ጋር ሰላም መመሥረት የትኞቹን ሌሎች ግንኙነቶች ጭምር ይነካል? (ለ) ይሖዋ በሁሉም ቦታ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በማሰብ ለልጁ ምን ሥልጣን ሰጥቶታል?
9 ከአምላክ ጋር እንዲህ ዓይነት ሰላም መፍጠር በጣም አስፈላጊ ነው! ከአምላክ ጋር ሰላም ከሌለን በማንኛውም ዓይነት ሌላ ግንኙነትና ዝምድና ዘላቂ የሆነ ወይም ትርጉም ያለው ሰላም ልናገኝ አንችልም። ከይሖዋ ጋር ሰላም መፍጠር በምድር ላይ ለሚገኘው እውነተኛ ሰላም መሠረት ነው። (ኢሳይያስ 57:19-21) ኢየሱስ ክርስቶስ የሰላም ገዥ ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው። (ኢሳይያስ 9:6) የሰው ልጆች ከአምላክ ጋር ሊታረቁ የሚችሉት በኢየሱስ በኩል ሲሆን ይሖዋ የማስተዳደር ሥልጣንም ሰጥቶታል። (ዳንኤል 7:13, 14) ይሖዋ የኢየሱስ መስፍናዊ ግዛት ለሰው ልጆች የሚያስገኘውን ውጤት በተመለከተ ‘ለሰላሙ ፍጻሜ እንደማይኖረው’ ቃል ገብቷል።— ኢሳይያስ 9:7፤ መዝሙር 72:7
10. ኢየሱስ የአምላክን የሰላም መልእክት በማወጅ ረገድ ምሳሌ የሆነው እንዴት ነው?
10 የአምላክ የሰላም መልእክት ለሰው ልጆች በሙሉ የሚያስፈልግ መልእክት ነው። ኢየሱስ ራሱ ይህን መልእክት በቅንዓት በመስበክ ረገድ ምሳሌ ትቷል። በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ቅጥር ግቢ፣ በተራራና በጎዳና ላይ፣ በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ላገኛት አንዲት ሳምራዊት ሴት እንዲሁም በየሰዎች መኖሪያ ቤት እየሄደ ሰብኳል። ኢየሱስ ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ያገኘውን አጋጣሚ ስለ ሰላምና ስለ አምላክ መንግሥት ለመስበክ ተጠቅሞበታል።— ማቴዎስ 4:18, 19፤ 5:1, 2፤ 9:9፤ 26:55፤ ማርቆስ 6:34፤ ሉቃስ 19:1-10፤ ዮሐንስ 4:5-26
የክርስቶስን ፈለግ እንዲከተሉ የሠለጠኑ
11. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ያሠለጠናቸው ለየትኛው ሥራ ነው?
11 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱም የአምላክን የሰላም መልእክት እንዲያውጁ አስተምሯቸዋል። ኢየሱስ የይሖዋ “የታመነና እውነተኛ ምሥክር” እንደነበረ ሁሉ እነርሱም የመመስከር ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገንዝበው ነበር። (ራእይ 3:14፤ ኢሳይያስ 43:10-12) መሪያቸው አድርገው ይመለከቱ የነበረው ክርስቶስን ነው።
12. ጳውሎስ የስብከቱን ሥራ አስፈላጊነት የጠቆመው እንዴት ነው?
12 ሐዋርያው ጳውሎስ የስብከቱን ሥራ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጽ “መጽሐፍ:- በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላልና” በማለት ጽፏል። ኢየሱስ ክርስቶስ ይሖዋ ያዘጋጀው የመዳን ዝግጅት ዋነኛ ወኪል መሆኑን የሚያምን ሰው ሁሉ አያፍርም ማለት ነው። እንዲሁም በዘሩ ወይም በነገዱ ምክንያት ይህን ተስፋ ከመውረስ የሚከለከል ሰው አይኖርም፤ ምክንያቱም ሐዋርያው ጳውሎስ “በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፣ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው። የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና” በማለት ጽፏል። (ሮሜ 10:11-13) ይሁን እንጂ ሰዎች ስለዚህ ግሩም አጋጣሚ እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ?
13. ሰዎች የምሥራቹን እንዲሰሙ ምን ያስፈልግ ነበር? የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችስ በዚህ ረገድ ምን አድርገዋል?
13 ጳውሎስ እያንዳንዱ ክርስቲያን ሊያስብባቸው የሚገቡ ጥያቄዎችን በማንሳት ስለዚህ አስፈላጊ ጉዳይ ገልጿል። ሐዋርያው እንዲህ ሲል ጠይቋል:- “እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? . . . ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ?” (ሮሜ 10:14, 15) ክርስቶስና ሐዋርያቱ የተዉትን አርዓያ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች፣ ወጣቶችና አረጋውያን እንደተከተሉ የጥንቱ ክርስትና ታሪክ በማያሻማ ሁኔታ ይመሰክራል። ቀናተኛ የምሥራቹ ሰባኪዎች ሆነው ነበር። ልክ እንደ ኢየሱስ ሰዎችን ሊያገኙ በሚችሉባቸው ቦታዎች ሁሉ ሰብከዋል። አንድም ሰው ምሥራቹን የመስማት አጋጣሚ እንዳያመልጠው ይፈልጉ ስለነበረ አገልግሎታቸውን በአደባባዮችና ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ አከናውነዋል።— ሥራ 17:17፤ 20:20
14. የምሥራቹን የሚያውጁ “እግሮቻቸው ያማሩ” ናቸው የሚለው አባባል እውነት ሆኖ የተገኘው እንዴት ነው?
14 እርግጥ ነው፣ ክርስቲያን ሰባኪዎቹን በደግነት የተቀበላቸው ሁሉም ሰው አልነበረም። ቢሆንም ጳውሎስ ከኢሳይያስ 52:7 ጠቅሶ የተናገረው ቃል በትክክል ተፈጽሟል። ‘ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ?’ የሚል ጥያቄ ካቀረበ በኋላ በመቀጠል “መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው” ብሏል። አብዛኞቻችን እግሮቻችን ያማሩ ወይም ደስ የሚሉ ናቸው ብለን አናስብም። ታዲያ ይህ ምን ማለት ነው? አንድ ሰው ለሌሎች ሰዎች ሲሰብክ የሚንቀሳቀሰው በእግሮቹ እንደሆነ የታወቀ ነው። እንደነዚህ ያሉት እግሮች ሰውዬውን ይወክላሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከሐዋርያትና ከሌሎቹ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ምሥራቹን ለሰሙ ብዙ ሰዎች እነዚህ የጥንት ክርስቲያኖች ደስ የሚል እይታ እንደነበሩ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (ሥራ 16:13-15) ከዚህም በላይ በአምላክ ዓይን በጣም ውድ ነበሩ።
15, 16. (ሀ) የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች እውነተኛ የሰላም መልእክተኞች መሆናቸውን ያረጋገጡት እንዴት ነው? (ለ) ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ጋር በሚመሳሰል መንገድ አገልግሎታችንን ለመፈጸም የሚረዳን ምንድን ነው?
15 የኢየሱስ ተከታዮች ያሰሙ የነበረው የሰላም መልእክት ሲሆን ይህንኑ መልእክት ያቀረቡት በሰላማዊ መንገድ ነበር። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቷቸዋል:- “ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ:- ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ። በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፣ ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለዚያም ይመለስላችኋል።” (ሉቃስ 10:5, 6) ሻሎም ወይም “ሰላም” ማለት የአይሁዳውያን ባሕላዊ ሰላምታ አሰጣጥ ነው። ይሁን እንጂ የኢየሱስ መመሪያ በዚህ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። ደቀ መዛሙርቱ ‘የክርስቶስ አምባሳደሮች’ እንደመሆናቸው “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ” እያሉ ሰዎችን አጥብቀው አሳስበዋል። (2 ቆሮንቶስ 5:20 የ1980 ትርጉም) ኢየሱስ ከሰጠው መመሪያ ጋር በመስማማት ስለ አምላክ መንግሥትና ይህ መንግሥት ለሰዎቹ ምን ትርጉም እንደሚኖረው ተናግረዋል። እሺ ብለው ያዳመጡ ሁሉ በረከት ሲያገኙ እምቢ ያሉት ግን ትልቅ አጋጣሚ አምልጧቸዋል።
16 ዛሬም ቢሆን የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎታቸውን የሚፈጽሙት በተመሳሳይ መንገድ ነው። ለሰዎች የሚያደርሱት ምሥራች ከላካቸው አምላክ እንጂ ከራሳቸው የመጣ አይደለም። የእነርሱ ግዴታ መልእክቱን ማድረስ ነው። ሰዎች ከተቀበሉት በጣም አስደናቂ የሆኑ በረከቶች የመውረስ አጋጣሚ ያገኛሉ። አንቀበልም ካሉ ከይሖዋ አምላክና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሰላም መፍጠር አንፈልግም ማለታቸው ነው።— ሉቃስ 10:16
ሁከት በሞላበት ዓለም ውስጥ ሰላማዊ ሆኖ መኖር
17. የሚሳደቡ ሰዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ እንኳ ምን ዓይነት ጠባይ ማሳየት ይገባናል? ለምንስ?
17 ሰዎች መልእክቱን ተቀበሉም፣ አልተቀበሉ፣ የይሖዋ አገልጋዮች የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች መሆናቸውን ማስታወሳቸው በጣም አስፈላጊ ነው። የዓለም ሰዎች ካስቆጧቸው ሰዎች ጋር የከረረ ክርክር ያካሂዳሉ፤ በተጨማሪም በስድብ ወይም ስሜት የሚያቆስል ንግግር በመናገር ንዴታቸውን ይወጣሉ። አንዳንዶቻችንም ባለፉት ጊዜያት እንዲሁ አድርገን ይሆናል። ይሁን እንጂ አዲሱን ሰው ከለበስንና ከዚህ ዓለም ከተለየን በኋላ የእነርሱን ጎዳና አንከተልም። (ኤፌሶን 4:23, 24, 31፤ ያዕቆብ 1:19, 20) ሌሎች የፈለጋቸውን ሊያደርጉ ይችላሉ፤ እኛ ግን “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” የሚለውን ምክር ሥራ ላይ እናውላለን።— ሮሜ 12:18
18. አንድ የሕዝብ ባለ ሥልጣን ክፉ ቃል ቢናገረን ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት ይኖርብናል? ለምንስ?
18 አንዳንድ ጊዜ አገልግሎታችን በሕዝብ ባለ ሥልጣናት ፊት እንድንቆም ሊያደርገን ይችላል። በሥልጣናቸው በመጠቀም አንዳንድ ነገሮችን ለምን እንደምናደርግ ወይም በአንድ የተወሰነ እንቅስቃሴ ለምን እንደማንካፈል እንድንገልጽላቸው ‘ይጠይቁን’ ይሆናል። የሐሰት ሃይማኖትን የሚያጋልጥና ስለዚህ ሥርዓት ፍጻሜ የሚገልጽ መልእክት ለምን እንደምንሰብክ ለማወቅ ይፈልጉ ይሆናል። ክርስቶስ ለተወልን ምሳሌ ያለን አክብሮት ዝግተኛ መንፈስና ጥልቅ አክብሮት እንድናሳይ ይገፋፋናል። (1 ጴጥሮስ 2:23፤ 3:15 አዓት) እነዚህ ባለ ሥልጣኖች ብዙውን ጊዜ የሚቃወሙን የሃይማኖት መሪዎች ወይም አለቆቻቸው ግፊት ስለሚያደርጉባቸው ነው። ዝግ ብለን አክብሮት የተሞላበት መልስ ብንሰጣቸው ሥራችን በእነርሱም ሆነ በማኅበረሰቡ ሰላም ላይ ምንም ዓይነት ችግር እንደማያስከትል እንዲገነዘቡ ልንረዳቸው እንችል ይሆናል። እንዲህ ያለውን መልስ ለመቀበል ፈቃደኞች ከሆኑ የአክብሮት፣ የትብብርና የሰላም መንፈስ እንዲኖራቸው ያደርጋል።— ቲቶ 3:1, 2
19. የይሖዋ ምሥክሮች በየትኞቹ እንቅስቃሴዎች ጨርሶ እጃቸውን አያስገቡም?
19 የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ግጭቶች የማይካፈሉ ሰዎች መሆናቸው በመላው ዓለም የታወቀ ነው። በዘር፣ በሃይማኖት ወይም በፖለቲካ ምክንያት በሚነሱ ዓለማዊ ግጭቶች አይካፈሉም። (ዮሐንስ 17:14) የአምላክ ቃል ‘ለበላይ ባለ ሥልጣኖች እንድንገዛ’ ስለሚያዘን ፀረ መንግሥት በሆኑ አድማዎች በመካፈል የመንግሥት ፖሊሲዎችን የመቃወም ሐሳብ እንኳን ወደ አእምሯችን አይመጣም። (ሮሜ 13:1) የይሖዋ ምሥክሮች መንግሥት ለመገልበጥ በሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ተካፍለው አያውቁም። ይሖዋ ለክርስቲያን አገልጋዮቹ ያወጣውን የሥነ ምግባር መስፈርት ስለሚያከብሩ ደም በሚያፋስስ ድርጊት ወይም በጠብ መካፈል ለእነርሱ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው! እውነተኛ ክርስቲያኖች ስለ ሰላም መናገር ብቻ ሳይሆን ከሚሰብኩት መልእክትም ጋር በሚጣጣም መንገድ ይኖራሉ።
20. ሰላምን በሚመለከት ታላቂቱ ባቢሎን ያስመዘገበችው ታሪክ ምንድን ነው?
20 የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ወኪሎች ግን ከእውነተኛ ክርስቲያኖች በተቃራኒ የሰላም መልእክተኞች ሳይሆኑ ቀርተዋል። የታላቂቱ ባቢሎን ሃይማኖቶች በሙሉ፣ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናትም ሆኑ ከክርስትና ውጭ ያሉ ሃይማኖቶች በብሔራት መካከል የሚደረጉ ጦርነቶችን ፈቅደዋል፣ ደግፈዋል፣ ወይም በእነዚህ ጦርነቶች በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈዋል። በተጨማሪም በይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ላይ ስደትና ግድያ እንዲፈጸም አነሳስተዋል። በመሆኑም ራእይ 18:24 ስለ ታላቂቱ ባቢሎን ሲናገር “በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት” ይላል።
21. ቅን ልብ ያላቸው ብዙ ሰዎች በይሖዋ ምሥክሮችና የሐሰት ሃይማኖት በሚከተሉ ሌሎች ሰዎች አኗኗር መካከል ያለውን ልዩነት ሲመለከቱ ምን ያደርጋሉ?
21 እውነተኛ ሃይማኖት ግን ከሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶችና ከቀሩት የታላቂቱ ባቢሎን ክፍሎች በተቃራኒ እርስ በርስ የማስተባበርና አንድ የማድረግ ኃይል አለው። ኢየሱስ ክርስቶስ ለእውነተኛ ተከታዮቹ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 13:35) ይህ ፍቅር ዛሬ የቀረውን የሰው ዘር በመከፋፈል ላይ ያሉት ብሔራዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ጎሣዊ ድንበሮች የማያግዱት ፍቅር ነው። ይህንን ያስተዋሉ በምድር ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋን ቅቡዓን አገልጋዮች:- “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ” እያሉአቸው ነው።— ዘካርያስ 8:23
22. ገና ሊሠራ ስለሚገባው የስብከት ሥራ ምን ይሰማናል?
22 የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን እስካሁን ባገኘነው ውጤት በጣም ተደስተናል። ይሁን እንጂ ሥራው ገና አላለቀም። አንድ ገበሬ ማሳውን ካረሰና ዘሩን ከዘራ በኋላ ሥራውን አያቆምም። በተለይ መከሩ ለአጨዳ በሚደርስበት ጊዜ ሥራውን ያጧጡፋል። የመከር ጊዜ የማያቋርጥ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ወቅት ነው። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች ታላቅ መከር በመሰብሰብ ላይ ነው። ወቅቱ በእርግጥ የደስታ ጊዜ ነው። (ኢሳይያስ 9:3) ተቃውሞና ግዴለሽነት እንደሚገጥመን ምንም አይካድም። በግለሰብ ደረጃ ከከባድ በሽታ፣ የቤተሰብ ችግር ወይም ከባድ የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር እየታገልን ይሆናል። ቢሆንም ለይሖዋ ያለን ፍቅር እንድንጸና ግድ ይለናል። አምላክ እንድንሰብከው የሰጠን መልእክት ሰዎች መስማት የሚያስፈልጋቸው ነው። የሰላም መልእክት ነው። አዎን፣ ይህ መልእክት ኢየሱስ ራሱ የሰበከው የአምላክ መንግሥት ምሥራች ነው።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ኢሳይያስ 52:7 በጥንቶቹ እስራኤላውያን ላይ የተፈጸመው እንዴት ነው?
◻ ኢየሱስ ከሁሉ የላቀ የሰላም መልእክተኛ መሆኑን ያረጋገጠው እንዴት ነው?
◻ ሐዋርያው ጳውሎስ ኢሳይያስ 52:7ን ክርስቲያኖች ከሚሠሩት ሥራ ጋር አያይዞ የገለጸው እንዴት ነው?
◻ በጊዜያችን የሰላም መልእክተኛ ሆኖ ማገልገል ምንን ይጨምራል?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ልክ እንደ ኢየሱስ የይሖዋ ምሥክሮችም የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች ናቸው
[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት የሚሰጡት ምላሽ ምንም ይሁን ምን የይሖዋ ምሥክሮች ሰላማዊ ናቸው