ፍጽምና በሌለው ዓለም ውስጥ እምነት የሚጣልብህ ሰው መሆን
“የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም።” አንተም እንደዚህ ይሰማሃልን? ሐዋርያው ጳውሎስም ተመሳሳይ ችግር እንደነበረው ማወቅህ ያጽናናሃል፤ ይሁንና ጳውሎስ የጸና አቋም በመያዝ ረገድ በምሳሌነት ጎላ ብሎ የሚጠቀስ ክርስቲያን ነበር። ይህ ነገር እርስ በእርሱ አይቃረንም? ጳውሎስ በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ችግሩ ምን እንደሆነ እንደሚከተለው ሲል አብራርቷል:- “የማልወደውን የማደርግ ከሆንሁ ግን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፣ በእኔ የሚኖር ኃጢአት ነው እንጂ።” ሐዋርያው ጳውሎስ እዚህ ላይ የጠቀሰው ስለምን ዓይነት ኃጢአት ነው? የአቋም ጽናት ያለው ሰው ነው ለመባል የበቃውስ ይህንን ኃጢአት እንዴት አሸንፎ ነው?— ሮሜ 7:19, 20
ጳውሎስ ትንሽ ቀደም ሲል በዚሁ ደብዳቤው ላይ “ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” ሲል ጽፏል። ይህ “አንድ ሰው” አዳም ነው። (ሮሜ 5:12, 14) የሰው ዘር ለወረሰው አለፍጽምና መንስኤ የሆነውና የአቋም ጽናትን ፈታኝ ያደረገው ዋነኛው ምክንያት አዳማዊ ኃጢአት ማለትም የመጀመሪያው ሰው አዳም የሠራው ኃጢአት ነው።
በሃይማኖት ምሁራኑ ዘንድ የመጽሐፍ ቅዱስ የፍጥረት ዘገባ በዝግመተ ለውጥ ትምህርት ስለተተካ ጳውሎስ ስለ “መጀመሪያው ኃጢአት” (የአዳም ኃጢአት በዚህ መጠሪያ ይታወቅ ነበር) የተናገረው ነገር ዛሬ ለብዙዎቹ ሰዎች አይዋጥላቸውም። አንድ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ ስለ ሮሜ ምዕራፍ 5:12-14 እንዳለው “ምሁራኑ ጠቅላላውን ክፍል ገሸሽ አድርገውታል።” ይሁንና ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያዎች “አዳም ኃጢአት ሲሠራ . . . ዝርያዎቹን በሙሉ በእርሱ ኃጢአትና ይህ ኃጢአቱ ባስከተለው መዘዝ በክሏቸዋል” በማለት ደጋግመው ይጠቅሱ ነበር።a
የአቋም ጽናት ያልታየበት የመጀመሪያው ሁኔታ
ዛሬ ብዙ ሰዎች የመጀመሪያው ሰው አዳም በሕይወት የነበረ መሆኑን እንደማያምኑ ሁሉ የሰይጣን ዲያብሎስንም ሕልውና እንደ አፈ ታሪክ አድርገው ይመለከቱታል።b ይሁን እንጂ ጉዳዩን ጠንቅቆ የሚያውቀው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣን ‘በእውነት እንዳልቆመ’ በሌላ አባባል እምነት የሚጣልበት እንዳልሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:44) አዳምና ሚስቱ ሔዋንም በይሖዋ ላይ ያመፁትና በፈተና ወቅት የአቋም ጽናት ሳያሳዩ የቀሩት በሰይጣን ቆስቋሽነት ነው።— ዘፍጥረት 3:1-19
ሁላችንም የአዳም ልጆች በመሆናቸን ኃጢአት የመሥራትን ዝንባሌ ወርሰናል። ጠቢቡ ሰው ሰሎሞን “በምድር ላይ መልካምን የሚሠራ ኃጢአትንም የማያደርግ ጻድቅ አይገኝምና” ሲል ተናግሯል። (መክብብ 7:20) ያም ሆኖ ግን ማንኛውም ግለሰብ እምነት የሚጣልበት ሊሆን ይችላል። እንዴት? የጸና አቋም መያዝ ፍጹም መሆንን ስለማይጠይቅ ነው።
ለአቋም ጽናት መሠረት የሆነው ነገር
የእስራኤሉ ንጉሥ ዳዊት በመዝገብ ሰፍሮ የሚገኘውን ከቤርሳቤህ ጋር የፈጸመውን ምንዝር ጨምሮ ብዙ ስህተቶች ሠርቷል። (2 ሳሙኤል 11:1-27) ዳዊት የፈጸማቸው ብዙ ስህተቶች ፍጹም እንዳልነበረ ቁልጭ አድርገው አሳይተዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በሰው ውስጥ የሚመለከተው ነገር ምንድን ነው? ይሖዋ ለዳዊት ልጅ ለሰሎሞን ሲናገር ‘አባትህ በየዋህ [“የአቋም ጽናት ባለው፣” NW] ልብና በቅንነት እንደሄደ አንተ ደግሞ እንዲሁ ተመላለስ’ ብሎታል። (1 ነገሥት 9:4) ዳዊት ብዙ ስህተቶችን ቢፈጽምም እምነት የሚጣልበት ሰው መሆኑን ይሖዋ ተገንዝቦለታል። ለምን?
ዳዊት “እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራልና፣ የነፍስንም ሁሉ ሐሳብ ያውቃልና” ሲል ለሰሎሞን በተናገረ ጊዜ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። (1 ዜና መዋዕል 28:9) ዳዊት ስህተቶች ቢፈጽምም ትሑት ነበር፤ ትክክል የሆነውንም ነገር ለማድረግ ይፈልግ ነበር። ብዙ ጊዜ ተግሣጽና እርማቶችን ተቀብሏል፤ ደግሞም እንዲሰጠው ጠይቋል። “አቤቱ ፍተነኝ፣ መርምረኝም፤ ኩላሊቴንና ልቤን ፍተን” ሲል ጠይቋል። (መዝሙር 26:2) በእርግጥም ደግሞ ዳዊት የተፈተነ ሰው ነበር። ለምሳሌ ያህል ከቤርሳቤህ ጋር በፈጸመው ኃጢአት ምክንያት የተዘፈቀባቸው አንዳንድ ችግሮች እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ዘልቀዋል። ያም ሆኖ ግን ዳዊት ጥፋቱን ትክክል አስመስሎ ለማቅረብ አልሞከረም። (2 ሳሙኤል 12:1-12) ከዚህም በላይ ከእውነተኛው አምልኮ ፈጽሞ ፈቀቅ ብሎ አያውቅም። በዚህ ምክንያትም ሆነ ከልቡ እውነተኛ ጸጸትና ንስሐ በማሳየቱ ይሖዋ ኃጢአቱን ይቅር ሊልለትና የጸና አቋም እንዳለው ሰው አድርጎ ሊቀበለው ዝግጁ ነበር።— በተጨማሪም መዝሙር 51ን ተመልከት።
ፈተና ቢደርስበትም እምነት የሚጣልበት ሆኗል
ሰይጣን ዲያብሎስ የኢየሱስን የጸና አቋም ለማስለወጥ በማቀድ ፈተናዎች አቅርቦለታል። መከራና ሥቃይ ቢደርስበትም የጸና አቋሙን ጠብቆ መገኘት ይፈለግበት ነበር። ከዚህ በተቃራኒ ፍጹም ሰው የነበረው አዳም የሚጠበቅበት ለተሰጠው መለኮታዊ መመሪያ ታዛዥ ሆኖ መገኘት ብቻ ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ የመላው የሰው ልጅ ከኃጢአት ነፃ መውጣት የተመካው በእርሱ የጸና አቋም ላይ እንደሆነ ማወቁ ተጨማሪ ውጥረት ፈጥሮበት ነበር።— ዕብራውያን 5:8, 9
ሰይጣን የኢየሱስን የጸና አቋም ለማስለወጥ ቆርጦ በመነሣት በጣም ተዳክሞ እያለ ወደ እርሱ መጣ፤ በዚህ ወቅት ኢየሱስ በማሰላሰልና በጾም 40 ቀናት በበረሃ አሳልፎ ነበር። በመጀመሪያ ድንጋዩን ዳቦ እንዲያደርግ ከዚያም መላእክት ጣልቃ ገብተው እንደሚያድኑትና መሲህ መሆኑንም በተዓምራዊ መንገድ ማረጋገጥ እንደሚችል በማሰብ ራሱን ከቤተ መቅደስ ጫፍ እንዲወረውር እንዲሁም ለእርሱ ወድቆ በመስገድ የዚህን ዓለም መንግሥታት ሁሉ የመግዛት ሥልጣን እንዲቀበል በመጋበዝ ሦስት ጊዜ ፈትኖታል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሦስቱንም ጊዜ ፈተናውን ውድቅ በማድረግ ይሖዋን በመደገፍ የጸና አቋም አሳይቷል።— ማቴዎስ 4:1-11፤ ሉቃስ 4:1-13
ኢዮብ ያሳየው የአቋም ጽናት
ኢዮብ በፈተና ወቅት የጸና አቋም በመያዝ የወሰደው እርምጃ በሰፊው የሚታወቅ ነው። የሚያስገርመው ደግሞ ኢዮብ ችግር የደረሰበት ለምን እንደሆነ እንኳ አልገባውም ነበር። ሰይጣን ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው ለጥቅሙ ማለትም ለራሱ ደህንነት ሲል ነው እንጂ ሆነ ብሎ የጸና አቋሙን ሊለውጥ ይችላል ብሎ ያለ ስሙ ስም እንደሰጠው አያውቅም ነበር። አምላክ የሰይጣንን ውሸታምነት ለማረጋገጥ ሲል ኢዮብ አንዳንድ ፈታኝ ሁኔታዎች እንዲደርሱበት ፈቅዷል።— ኢዮብ 1:6-12፤ 2:1-8
ከዚያም ሦስት ጓደኛ ተብዬዎች ብቅ አሉ። ሆነ ብለው የአምላክን የአቋም ደረጃዎችና ዓላማዎች እያጣመሙ ይናገሩ ነበር። ሚስቱም የተነሣውን ከፍተኛ ክርክር ሳታስተውል በመቅረቷ ኢዮብ ከፍተኛ እርዳታ በሚፈልግበት በዚያ ወሳኝ ወቅት ሳታጽናናው ቀርታለች። (ኢዮብ 2:9-13) ይሁን እንጂ ኢዮብ ጸንቷል። “እስክሞት ድረስ ፍጹምነቴን ከእኔ አላርቅም [“የአቋም ጽናቴን አላላላም፣” NW]። ጽድቄን እይዛለሁ እርሱንም አልተውም፤ ከቀኖቼም ሁሉ ስለ አንዱ ልቤ አይዘልፈኝም።”— ኢዮብ 27:5, 6
ኢዮብ ያሳየው ግሩም ምሳሌነትም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው ሌሎች ብዙ የታመኑ ወንዶችና ሴቶች ያሳዩት የአቋም ጽናት ሰይጣን ውሸታም መሆኑን አረጋግጧል።
የአቋም ጽናትና ክርስቲያናዊ አገልግሎት
ይሖዋ ለአቋም ጽናት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ይህ ባሕርይ ለእርሱ እርካታ የሚያመጣለት ስለሆነ ብቻ ነውን? አይደለም። የአቋም ጽናት ለእኛ ለሰው ልጆች ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ኢየሱስ ‘አምላካችንን ይሖዋን በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችንና በፍጹም ሐሳባችን’ እንድንወድ ያሳሰበን ለእኛው ጥቅም ሲል ነው። በእርግጥም ይህ ‘ከትእዛዛት ሁሉ የሚበልጥ’ ትእዛዝ ሲሆን ይህንን ትእዛዝ ማክበር ወንድ፣ ሴት ወይም ልጅ ሳይል የጸና አቋም መያዝን ይጠይቃል። (ማቴዎስ 22:36-38) ይህ ምን ነገሮችን ይጨምራል? የሚያስገኘውስ ወሮታ ምንድን ነው?
የጸና አቋም ያለው አንድ ሰው በሌሎች ሰዎች ዘንድ ብቻ ሳይሆን ይበልጡኑ በአምላክም ፊት እምነት የሚጣልበት ሆኖ ይገኛል። የልብ ንጽሕናው በሚያደርገው ነገር ይንጸባረቃል፤ ግብዝነት የለበትም። አጭበርባሪ ወይም ምግባረ ብልሹ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኰል አንመላለስም የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን።”— 2 ቆሮንቶስ 4:2
ጳውሎስ የተናገረው ከክርስቲያናዊ አገልግሎት ጋር ግንኙነት ስላላቸው ባሕርያት እንደሆነ ልብ በል። አንድ ክርስቲያን አገልጋይ የገዛ እጆቹ ንጹሕ ካልሆኑና የጸና አቋም ከሌለው እንዴት ሌሎችን ሊያገለግል ይችላል? በቅርቡ ሥልጣናቸውን የለቀቁ አንድ የአየርላንድ የሃይማኖት አባት ሁኔታ ይህን ነጥብ ይበልጥ ግልጽ ያደርግልናል። “በልጆች ላይ የጾታ በደል የፈጸመ ቄስ ይህ ድርጊቱ ከታወቀም በኋላ ከልጆች ጋር እንዲሠራ ፈቅጄለት ነበር” ሲሉ እንደተናገሩ ዚ ኢንዲፐንደንት የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። ዘገባው እንደሚለው ከሆነ ይህ ቄስ ይህን የጾታ በደል ለ24 ዓመታት ሲፈጽም ቆይቷል። ቄሱ ለአራት ዓመታት ታስሯል፤ ይሁን እንጂ አባው ትክክለኛውን እርምጃ ለመውሰድ የጸና የሥነ ምግባር አቋም በማጣታቸው በእነዚያ ሁሉ ዓመታት ይህ ቄስ የጾታ በደል የፈጸመባቸው ልጆች ምን ያህል ሥቃይ እንደ ደረሰባቸው ገምት!
የአቋም ጽናት የሚያስገኘው ወሮታ
ሐዋርያው ዮሐንስ ደፋር ሰው ነበር። ከነበራቸው ከፍተኛ ቅንዓት የተነሣ እርሱንና ወንድሙን ያዕቆብን ኢየሱስ “የነጐድጓድ ልጆች” ሲል ጠርቷቸዋል። (ማርቆስ 3:17) የጸና አቋም በመያዝ ረገድ ግሩም ምሳሌ የሆነው ዮሐንስ ከጴጥሮስ ጋር ሆኖ ከኢየሱስ ጋር በነበሩበት ጊዜ ያዩአቸውን የሰሟቸውን ነገሮች ከመናገር ‘ዝም ይል ዘንድ እንደማይችል’ ለአይሁዳውያን ገዢዎች አስረድቷል። በተጨማሪም ዮሐንስ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” ካሉት ሐዋርያት አንዱ ነበር።— ሥራ 4:19, 20፤ 5:27-32
ዮሐንስ “ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር” ፍጥሞ በምትባል ደሴት ታስሮ የነበረው በ90ዎቹ ዕድሜው መገባደጃ ላይ ሳይሆን አይቀርም። (ራእይ 1:9) ዕድሜው በጣም ገፍቶ ስለነበር ከእንግዲህ አገልግሎቴን ፈጽሜያለሁ ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የራእይን ስሜት ቀስቃሽ ትዕይንቶች ለመመዝገብ ብቁ የሚሆነው የእርሱን ዓይነት የአቋም ጽናት ያሳየ ሰው ብቻ ነው። በዚህ ረገድ ዮሐንስ የታመነ ሆኖ ተገኝቷል። ይህ ለእርሱ እንዴት ያለ መብት ነው! ይሁን እንጂ በዚህ ብቻ አላበቃም ነበር። ትንሽ ቆየት ብሎም በኤፌሶን አቅራቢያ እያለ ሳይሆን አይቀርም ወንጌሉንና ሦስቱን መልእክቶች ጽፏል። እምነት የሚጣልበት ሆኖ ለ70 ዓመታት ያከናወነው አገልግሎት እነዚህን በመሳሰሉ ታላላቅ መብቶች ተቋጭቷል!
በአጠቃላይ የአቋም ጽናት ማሳየት ጥልቅ እርካታ ያስገኛል። በአምላክ ፊት እምነት የሚጣልብን ዓይነት ሰዎች ሆነን መገኘታችን ዘላለማዊ በረከቶችን ያስገኝልናል። ዛሬ እውነተኛ አምላኪዎች የሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይዘው ሰላምና ስምምነት ወደ ሰፈነበት አዲስ ዓለም ለመግባት እየተዘጋጁ ነው። (ራእይ 7:9) ይህ የነገሮች ሥርዓት የሚያመጣቸው ፈተናዎችና ሰይጣን ሊሰነዝራቸው የሚችላቸው ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም በጣም አስፈላጊ በሆኑት የሥነ ምግባርና የአምልኮ ጉዳዮች ረገድ የጸና አቋም መያዝ ይገባናል። ይሖዋ በሚሰጠው ኃይል ድል ልትቀዳጅ እንደምትችል እርግጠኛ ሁን!— ፊልጵስዩስ 4:13
መዝሙራዊው ዳዊት ለይሖዋ ባቀረበው የምስጋና ጸሎት ላይ ስለ አሁኑና ስለ ወደፊቱ ሁኔታ ሲናገር ለሁላችንም እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል:- “እኔን ግን ስለ ቅንነቴ [“ስለ አቋም ጽናቴ፣” NW] ተቀበልኸኝ፣ በፊትህም ለዘላለም አጸናኸኝ። . . . እግዚአብሔር ይባረክ። አሜን አሜን።”— መዝሙር 41:12, 13
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ዘ ኒው ቴስታመንት ኦቭ አወር ሎርድ ኤንድ ሴቪየር ጂሰስ ክራይስት አኮርዲንግ ቱ ዘ ኦቶራይዝድ ቨርሽን ዊዝ ኤ ብሪፍ ኮሜንታሪ ባይ ቫሪየስ ኦተርስ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ ሐሳብ።
b ሰይጣን የሚለው ስም “ተቃዋሚ” ማለት ሲሆን “ዲያብሎስ” ማለት ደግሞ “ስም አጥፊ” ማለት ነው።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳዊት ስህተቶች ቢፈጽምም እምነት የሚጣልበት ሰው መሆኑን አስመስክሯል
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ እምነት የሚጣልበት በመሆን ረገድ ከሁሉ የበለጠ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
እምነት የሚጣልብን ሰዎች መሆን ከፍተኛ እርካታ ያስገኝልናል