በሪኢንካርኔሽን ታምናለህን?
ሙካንድባይ በዩናይትድ ስቴትስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ለሆነው ልጁ እንዲህ ሲል ይጽፍለታል:- “እዚህ ሕንድ በነበርክበት ጊዜ ልጅ ሳለህ አፍቅረሃት የነበረችውን የጎረቤታችንን ልጅ ታስታውሳታለህ? ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ልታገባ ነው። ይህን ጉዳይ ማወቅ እንዳለብህ ይሰማኛል።”
አባትየው ለልጁ ይህን ነገር የነገረው ለምንድን ነው? እንዲያውም ከዓመታት በፊት ያ የልጅነት ፍቅር ባጭር እንዲቀጭ ያደረገው ሙካንድባይ ራሱ ነበር። ከዚህም በላይ ልጁ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከፍተኛ ትምህርት መከታተል ከጀመረ ስድስት ዓመት ሆኖታል። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ይህችን ልጅ አግኝቷት አያውቅም፤ ይህንን ደግሞ ሙካንድባይ ራሱም ያውቃል።
ታዲያ ጉዳዩ ለምን አሳሰበው? በሪኢንካርኔሽን ወይም እንደገና በመወለድ ያምን ስለነበር ነው።a በሁለቱ መካከል ለነበረው የልጅነት ፍቅር ምክንያቱ በቀደመው ሕይወታቸው ባልና ሚስት ሆነው መኖራቸው ከሆነ አሁን ለጋብቻ በደረሱበት ዕድሜያቸው እነዚህን ልጆች ማለያየት ግፍ ይሆናል። በመሆኑም ሙካንድባይ ይህች ልጅ በዚህኛው ሕይወት የሌላ ሰው ሚስት ከመሆኗ በፊት ልጁ ስለ ጉዳዩ እንዲያውቅ ፈልጓል።
ሌላ ምሳሌ ደግሞ ተመልከት። አንዲት የአራት ዓመት ልጅ በሕንድ ሙምባይ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ በሕመም በጣም ስትሰቃይ ትሰነብታለች። ችግሩ የልቧ ቫልቭ በትክክል አለመሥራቱ ነበር። ባለጸጋ የሆኑት ወላጆቿ በልጃቸው ስቃይ በጣም ተረብሸው ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል:- “ሐቁን አምነን መቀበል ይኖርብናል። በቀደመው ሕይወቷ ለዚህ ቅጣት የሚዳርግ ነገር ሠርታ መሆን አለበት።”
የሪኢንካርኔሽን እምነት በሂንዱ፣ በቡድሃ፣ በጄይን፣ በሲክና በሌሎች ከሕንድ በመነጩ ሃይማኖቶች ውስጥ ባሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው። በፍቅር ከመጎዳኘት አንስቶ እስከ ከፍተኛ ስቃይ ድረስ ያሉት የሕይወት ገጠመኞች በቀድሞው ሕይወት ወይም ሕይወቶች ውስጥ የተፈጸሙት ተግባራት ውጤት እንደሆኑ ተደርጎ ይታመናል።
በምዕራባውያን አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎችም በሪኢንካርኔሽን መሠረተ ትምህርት ይማረካሉ። አሜሪካዊቷ የፊልም ተዋናይ ሻርሊ ማክሌን በዚህ መሠረተ ትምህርት እንደምታምን ተናግራለች። በካናዳ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ በቫንኩቨር ከተማ ውስጥ የምትገኘው ደራሲ ላውረል ፌላን ካሁን ቀደም ስላሳለፈቻቸው 50 ሕይወቶች ትዝታ እንዳላት ተናግራለች። በ1994 ሲ ኤን ኤን እና ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ በመተባበር ባካሄዱት ጥናት ከ1,016 አዋቂዎች መካከል 270 የሚያክሉት በሪኢንካርኔሽን እንደሚያምኑ ተናግረዋል። ኒው ኤጅ ሙቭመንት የተባለውም ሃይማኖታዊ ቡድን በሪኢንካርኔሽን ያምናል። ይሁን እንጂ ይህንን እምነት የሚደግፍ ምን ማስረጃ አለ?
“የቀድሞ ሕይወት ትዝታዎች” ለዚህ እምነት ማስረጃ እንደሆኑ በሪኢንካርኔሽን የሚያምኑ ሰዎች ይናገራሉ። ከዚህም የተነሣ በባንኮክ የምትኖረው የሦስት ዓመቷ ራትና “በ60 ዓመቷ የሞተች ሃይማኖታዊ ሰው ሆና ስላሳለፈችው የቀድሞ ሕይወቷ” ትዝታ መናገሯን አብዛኞቹ ታዛቢዎች ለሪኢንካርኔሽን ጠንካራ ማስረጃ እንደሆነ አድርገው ተቀብለውታል።
ይሁን እንጂ ይህ ጥርጣሬዎችን ሁሉ ያስወግዳል ማለት አይደለም። ከዚህም በተጨማሪ የቀድሞ ሕይወት ትዝታ ናቸው የሚባሉት ነገሮች ሌላ ማብራሪያም ሊሰጣቸው ይቻላል።b የሂንዱ ፈላስፋ የሆኑት ኒኪላነንዳ ሂንዱይዝም:- ኢትስ ሚኒንግ ቱ ዘ ሊበሬሽን ኦቭ ዘ ስፒሪት በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ ‘ከሞት በኋላ ስላሉት ገጠመኞች አሳማኝ ምክንያቶችን በማቅረብ ማስረዳት አይቻልም’ ሲሉ ተናግረዋል። ይሁንና “እንደገና መወለድ ይቻላል የሚለው መሠረተ ትምህርት ከኢተዓማኒነቱ ይልቅ ተዓማኒነቱ ያመዝናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ትምህርት ይደግፋልን? በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ስለ ሙታን ምን ተስፋ ይሰጣል?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ ስለ “ሪኢንካርኔሽን” ሲገልጽ “ነፍስ አንድ ጊዜ ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ተከታታይ ጊዜያት ሰው፣ እንስሳ ወይም አንዳንድ ጊዜ ዕጽዋት ሆና እንደገና ትወለዳለች” የሚል እምነት ነው ይላል። ይህንኑ ክስተት ለመግለጽ “እንደገና መወለድ” የሚለውም ቃል የሚያገለግል ሲሆን በአብዛኛው ግን የሚሠራበት “ሪኢንካርኔሽን” የሚለው ቃል ነው። በሕንድ ቋንቋ የተዘጋጁ በርካታ መዝገበ ቃላት እነዚህን ሁለት ቃላት በተወራራሽነት ይጠቀሙባቸዋል።
b ሰኔ 8, 1994 የእንግሊዝኛ ንቁ! ገጽ 5-7ን ተመልከት።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
እየተሰቃየች ያለችው በቀድሞው ሕይወቷ በፈጸመችው ኃጢአት ምክንያት ነውን?