ክርስቲያኖች ሊሰውሩት የማይገባ ምሥጢር!
“እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ . . . በስውርም ምንም አልተናገርሁም።”— ዮሐንስ 18:20
1, 2. ሚስቴሪዮን የሚለው የግሪክኛ ቃል በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ምን ትርጉም ተሰጥቶታል?
በግሪክኛ ሚስቴሪዮን የሚለው ቃል በአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ውስጥ 25 ጊዜ “ሴክረድ ሴክሬት” [ቅዱስ ምሥጢር] 3 ጊዜ ደግሞ “ሚስትሪ” [ምሥጢር] ተብሎ ተተርጉሟል። መቼም አንድ ምሥጢር ቅዱስ ተብሎ የሚጠራው ከበድ ያለ ቢሆን ነው! እንዲህ ያለውን ምሥጢር ለማወቅ የታደለ ሰው ደግሞ ከአጸናፈ ዓለሙ ታላቅ አምላክ ጋር ይህንን ምሥጢር ለመካፈል በመብቃቱ ትልቅ ክብር እንዳገኘ ሊሰማው ይገባል።
2 በቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ በአብዛኛው “ሚስትሪ” ከሚለው ቃል ይልቅ “ሴክረድ ሴክሬት” የሚለው አተረጓጎም ይበልጥ ተገቢ እንደሚሆን አረጋግጧል። ሚስቴሪዮን የሚለውን ቃል በሚመለከት እንዲህ ብሏል:- “[በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ] የሚያስተላልፈው መልእክት (ሚስትሪ እንደሚለው የእንግሊዝኛ ቃል) ምሥጢራዊነትን ሳይሆን ያለምንም እርዳታ በተፈጥሮ ችሎታ ሊደረስበት የማይችል፣ በመለኮታዊ ራእይ ብቻ የሚገለጥ፣ አምላክ በቀጠረው ጊዜና በፈለገው ሁኔታ እንዲሁም የመንፈሱ ብርሃን ለፈነጠቀላቸው ሰዎች ብቻ የሚታወቅ መሆኑን የሚያመለክት ነው። በተለመደው ፍቺው ሚስትሪ [ምሥጢር] የሚለው ቃል ከሌሎች የተሰወረን እውቀት ያመለክታል፤ በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ ግን የሚያመለክተው የተገለጠን እውነት ነው። በመሆኑም ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዘው የሚመጡት ቃላት ‘ታወቀ፣’ ‘ገሃድ ሆነ፣’ ‘ተገለጠ፣’ ‘ተሰበከ፣’ ‘መረዳት ተቻለ፣’ ‘ተሠራጨ’ የሚሉት ናቸው።”
3. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው ክርስቲያን ጉባኤ ከአንዳንድ ምሥጢራዊ የሃይማኖት ቡድኖች ይለይ የነበረው እንዴት ነው?
3 ይህ ማብራሪያ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብቅ ባሉት ምሥጢራዊ የሃይማኖት ቡድኖችና ገና መመሥረቱ በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ መካከል ያለውን ትልቅ ልዩነት ጎላ አድርጎ ያሳያል። በምሥጢር ለሚንቀሳቀሱ ሃይማኖታዊ ቡድኖች የሚመለመሉት ሰዎች ሃይማኖታዊ ትምህርቶቻቸውን በድብቅ ለመያዝ የምሥጢር ጠባቂነት ቃለ መሐላ የሚፈጽሙ ሲሆን ክርስቲያኖች ግን እንዲህ ዓይነት እገዳ የለባቸውም። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በቅዱስ ምሥጢር ውስጥ ያለውን የአምላክ ጥበብ’ ‘የተሰወረ ጥበብ’ ብሎ መጥራቱ ባይካድም ይህ የተሰወረው ‘ከዚህ ዓለም ገዥዎች’ ነው። ለክርስቲያኖች ግን ለሌሎች ሰዎች እንዲያሳውቁት ሲባል በአምላክ መንፈስ አማካኝነት ተገልጦላቸዋል።— 1 ቆሮንቶስ 2:7-12፤ ከምሳሌ 1:20 ጋር አወዳድር።
‘ቅዱሱ ምሥጢር’ ተገለጠ
4. ‘ቅዱሱ ምሥጢር’ ያተኮረው በማን ላይ ነው? እንዴትስ?
4 የይሖዋ ‘ቅዱስ ምሥጢር’ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያተኮረ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “[ይሖዋ] በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፣ የፈቃዱን ምሥጢር [“ቅዱስ ምሥጢር፣” NW] አስታውቆናልና፤ በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።” (ኤፌሶን 1:9, 10) ጳውሎስ “የአምላክ ቅዱስ ምሥጢር ትክክለኛ እውቀት የሆነውን ክርስቶስን” የማወቅን አስፈላጊነት አስመልክቶ በጻፈ ጊዜ ስለዚህ “ቅዱስ ምሥጢር” ምንነት ይበልጥ ግልጽ አድርጎ ተናግሯል።— ቆላስይስ 2:2 NW
5. ‘ቅዱሱ ምሥጢር’ ምን ነገሮችንም ይጨምራል?
5 ይሁን እንጂ ይህ “ቅዱስ ምሥጢር” ብዙ ዘርፎች ያሉት ምሥጢር በመሆኑ ከዚህም የበለጠ ነገር ያመለክታል። ይህ ቅዱስ ምሥጢር ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት ዘር ወይም መሲህ መሆኑን ብቻ የሚያመለክት ሳይሆን በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውንም ሚና ይጨምራል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር [“ቅዱስ ምሥጢር፣” NW] ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፣ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም” በማለት በግልጽ እንደተናገረው አንድን ሰማያዊ መንግሥት ማለትም የአምላክን መሲሐዊ መንግሥትም የሚያካትት ነው።— ማቴዎስ 13:11፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።
6. (ሀ) ይህ “ቅዱስ ምሥጢር” ‘ለረጅም ጊዜ ተሰውሮ ቆይቷል’ መባሉ ትክክል የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ቀስ በቀስ እየተገለጠስ የሄደው እንዴት ነው?
6 አምላክ ለመሲሐዊው መንግሥት መሠረት ለመጣል ዓላማ እንዳለው መጀመሪያ ከገለጸ በኋላ ‘ቅዱሱ ምሥጢር ወደ ፍጻሜው’ እስኪመጣ ድረስ በመካከሉ ረጅም ዘመን አልፏል። (ራእይ 10:7፤ ዘፍጥረት 3:15) ራእይ 10:7ን እና 11:15ን በማወዳደር መረዳት እንደምንችለው ይህ ቅዱስ ምሥጢር ወደ ፍጻሜው የሚመጣው የአምላክ መንግሥት ሲቋቋም ነው። እርግጥ ነው፣ የመንግሥቱ ተስፋ በኤደን ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሰጠ በኋላ እጩው ንጉሥ በ29 እዘአ እስኪገለጥ ድረስ 4,000 የሚያክሉ ዓመታት አልፈዋል። በ1914 መንግሥቱ በሰማይ እስኪቋቋም ድረስ ደግሞ ሌላ 1,885 ዓመታት አልፈዋል። በዚህ መንገድ ‘ቅዱሱ ምሥጢር’ 6,000 በሚያክሉ ዓመታት ውስጥ ቀስ በቀስ ተገልጧል። (ገጽ 16ን ተመልከት።) በእርግጥም ጳውሎስ ‘ለብዙ ዘመናት ተሰውሮ ከጊዜ በኋላ ስለታየውና ስለታወቀው ቅዱስ ምሥጢር’ መናገሩ ትክክል ነበር።— ሮሜ 16:25-27፤ ኤፌሶን 3:4-11
7. በታማኝና ልባም ባሪያ ላይ ከፍተኛ ትምክህት ሊኖረን የሚችለው ለምንድን ነው?
7 የይሖዋ ዕድሜ እንደ ሰዎች ውስን አይደለም፤ ጊዜ ያንሰኝ ይሆናል ብሎ ምሥጢሩን ያለጊዜው ለመግለጥ አይጣደፍም። ዛሬ ለአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች የሚያረካ መልስ ማግኘት ባንችል ይህ ሐቅ ትዕግሥታችን እንዳይሟጠጥ ሊጠብቀን ይገባል። ለክርስቲያን ቤተሰብ በጊዜው ምግብ የማቅረብ ተልእኮ የተሰጠው ታማኝና ልባም ባሪያ ቦታውን የሚጠብቅ መሆኑ ገና አሁንም ግልጽ ስላልሆኑት ነገሮች በችኩልነት የመጣለትን ግምታዊ ሐሳብ እንዳይሰነዝር ይጠብቀዋል። የባሪያው ክፍል ቀኖናዊነትን አይከተልም። ምሳሌ 4:18ን በሚገባ ስለሚያስታውስ በአሁኑ ጊዜ ለሁሉም ጥያቄዎች መልስ መስጠት እንደማይችል አምኖ ለመቀበል አይከብደውም። ይሁን እንጂ ይሖዋ በራሱ ጊዜና በራሱ መንገድ ከዓላማው ጋር የተዛመዱ ምሥጢሮችን እየገለጠ እንደሚሄድ ማወቁ ምንኛ የሚያስደስት ነው! ትዕግሥት የለሾች በመሆን ምሥጢርን ከሚገልጠው አምላክ ቀድመን ለመሄድ በመሞከር አስተዋይነት የጎደለው እርምጃ መውሰድ የለብንም። ዛሬ ይሖዋ የሚጠቀምበት መገናኛ መስመር እንዲህ እንደማያደርግ ማወቁ ምንኛ መንፈስን የሚያረጋጋ ነው! በእርግጥም ታማኝ እና ልባም ነው።— ማቴዎስ 24:45፤ 1 ቆሮንቶስ 4:6
የተገለጠው ምሥጢር ሊነገር ይገባል!
8. ‘ቅዱሱ ምሥጢር’ በስውር የሚያዝ ነገር አለመሆኑን እንዴት እናውቃለን?
8 ይሖዋ ‘ቅዱስ ምሥጢሩን’ ለክርስቲያኖች የገለጠላቸው ሰውረው እንዲይዙት አይደለም። ይህ ምሥጢር የተገለጠው ኢየሱስ ለጥቂት ቀሳውስት ሳይሆን ለተከታዮቹ በሙሉ ከሰጠው ከሚከተለው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በሚስማማ መንገድ በሰፊው እንዲታወቅ ነው። “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።”— ማቴዎስ 5:14-16፤ 28:19, 20
9. ኢየሱስ አንዳንዶች እንደሚሉት አብዮተኛ እንዳልነበረ የሚያረጋግጠው ምንድን ነው?
9 ኢየሱስ ድብቅ ዓላማ የሚያራምዱ ተከታዮች ያሉት ኅቡዕ ድርጅት የማቋቋም አብዮታዊ ሐሳብ አልነበረውም። ኧርሊ ክርስቺያኒቲ ኤንድ ሶሳይቲ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ሮበርት ኤም ግራንት፣ በሁለተኛው መቶ ዘመን ስለ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሽንጡን ገትሮ የተከራከረው ሰማዕቱ ጀስቲን የተናገረውን የመከራከሪያ ነጥብ በማንሳት “ክርስቲያኖች አብዮተኞች ቢሆኑ ኖሮ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ተደብቀው በቀሩ ነበር” ሲሉ ጽፈዋል። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ‘የሚደበቁ’ ከሆነ እንዴት ‘በተራራ ላይ እንዳለች ከተማ’ ሊሆኑ ይችላሉ? ብርሃናቸውን ከዕንቅብ በታች ሊያኖሩት አይገባም ነበር! እኒሁ ጸሐፊ “ሰላምንና ሥርዓታማነትን በማስፈን በኩል ክርስቲያኖች የንጉሠ ነገሥቱ የቅርብ ረዳቶች ናቸው” ሲሉ እንደገለጹት መንግሥት ስለሚሠሩት ሥራ ምንም ዓይነት ስጋት ሊያድርበት አይገባም ነበር።
10. ክርስቲያኖች ማንነታቸውን መሰወር የማይገባቸው ለምንድን ነው?
10 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንደ አንድ ሃይማኖታዊ ኑፋቄ አባላት ማንነታቸውን ሰውረው እንዲንቀሳቀሱ አልፈለገም። (ሥራ 24:14፤ 28:22) ዛሬ ብርሃናችንን ሳናበራ ብንቀር ክርስቶስም ሆነ ምሥጢርን የሚገልጠው አባቱ የሚያዝኑ ከመሆናቸውም ሌላ እኛም ደስታ አናገኝም።
11, 12. (ሀ) ይሖዋ ክርስትና እንዲታወቅ የሚፈልገው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ የተወልን እንዴት ነው?
11 ይሖዋ ‘ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርስ እንጂ ማንም እንዲጠፋ’ አይፈልግም። ( 2 ጴጥሮስ 3:9፤ ሕዝቅኤል 18:23፤ 33:11፤ ሥራ 17:30) ንስሐ የገቡ ሰዎች የኃጢአት ይቅርታ የሚያገኙት ለጥቂቶች ብቻ ሳይሆን “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ” ሲል ራሱን ቤዛ አድርጎ በሰጠው በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመናቸው ነው። (ዮሐንስ 3:16) በመጪው የፍርድ ወቅት ሰዎች ፍየሎች ሳይሆን በጎች ናቸው ተብሎ እንዲፈረድላቸው የሚያስችል እርምጃ እንዲወስዱ መርዳታችን የግድ አስፈላጊ ነው።— ማቴዎስ 25:31-46
12 እውነተኛው ክርስትና በተገኘው አመቺ አጋጣሚ ሁሉ ሌሎች እንዲያውቁት የሚደረግ እንጂ ተሸሽጎ የሚቀመጥ ነገር አይደለም። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ራሱ ግሩም ምሳሌ ትቷል። ሊቀ ካህናቱ ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ በጠየቀው ጊዜ እንዲህ አለ:- “እኔ በግልጥ ለዓለም ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኵራብና በመቅደስ እኔ ሁልጊዜ አስተማርሁ፣ በስውርም ምንም አልተናገርሁም።” (ዮሐንስ 18:19, 20) ኢየሱስ ከተወው ከዚህ ምሳሌ አንጻር አምላክ ለሕዝብ የገለጠውን መልእክት ለመሰወር የሚያስብ ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው ይኖራልን? ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን ‘እውቀት መክፈቻ’ ለመሰወር የሚደፍር ማን አለ? እንዲህ ማድረጉ ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ሃይማኖታዊ ግብዞች ጋር ያስመድበዋል።— ሉቃስ 11:52፤ ዮሐንስ 17:3
13. ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ መስበክ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
13 የይሖዋ ምሥክሮች እንደ መሆናችን መጠን የአምላክን መንግሥት መልእክት በምሥጢር ይዟል ብሎ የሚከሰን ሰው እንዲኖር ከቶ መፍቀድ አይኖርብንም! ሰዎች መልእክቱን ተቀበሉትም አልተቀበሉት እንደተሰበከ ማወቅ ይኖርባቸዋል። (ከሕዝቅኤል 2:5፤ 33:33 ጋር አወዳድር።) እንግዲያውስ ሰዎችን በምናገኝበት ቦታ ሁሉ የእውነትን መልእክት በመናገር እያንዳንዱን አጋጣሚ መልእክቱን ለሁሉም ሰዎች ለማዳረስ እንጠቀምበት።
በሰይጣን መንጋጋ ልጓም ማስገባት
14. በአምልኮአችን በኩል ግልጽ ለመሆን ማመንታት የማይገባን ለምንድን ነው?
14 የይሖዋ ምሥክሮች በብዙ ቦታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ የመገናኛ ብዙሐን መወያያ እየሆኑ መጥተዋል። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ካጋጠማቸው ሁኔታ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ብዙውን ጊዜ ያለ ስማቸው ስም የሚሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ አጠያያቂ ከሆኑ ሃይማኖታዊ ኑፋቄዎችና በምሥጢር የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጎራ ይመደባሉ። (ሥራ 28:22) በግልጽ መስበካችን ይበልጥ ለጥቃት የሚያጋልጠን ይሆንን? እርግጥ ራሳችንን አላስፈላጊ በሆነ ውዝግብ ውስጥ ማስገባታችን ጥበብ የጎደለው ድርጊት ከመሆኑም ሌላ ኢየሱስ ከሰጠውም ምክር ጋር የሚጋጭ ይሆናል። (ምሳሌ 26:17፤ ማቴዎስ 10:16) ይሁን እንጂ ጠቃሚ የሆነው የመንግሥቱ ስብከትና ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ የመርዳቱ ሥራ ሊሰወር አይገባም። ይህ ሥራ ሰዎች በይሖዋና በተቋቋመው መንግሥቱ ላይ እንዲያተኩሩ ስለሚያደርግ ይሖዋን ከፍ ከፍ የሚያደርግና የሚያስከብር ሥራ ነው። በቅርቡ በምሥራቅ አውሮፓና በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አስደሳች ምላሽ እንዲያሳዩ በከፊል አስተዋጽኦ ያደረገው በእነዚህ አካባቢዎች እውነት ይበልጥ በግልጽ መሰበክ መቻሉ ነው።
15, 16. (ሀ) ግልጽ መሆናችንና ያገኘነው መንፈሳዊ ብልጽግናችን ምን ውጤት ያስከትላል? ይህስ ሊያስጨንቀን ይገባልን? (ለ) ይሖዋ በሰይጣን መንጋጋ ልጓም የሚያስገባው ለምንድን ነው?
15 የይሖዋ ምሥክሮች በግልጽ የሚያካሂዱት ስብከት፣ ያሉበት መንፈሳዊ ገነት እንዲሁም በሰዎች ቁጥር ረገድም ሆነ በቁሳዊ ሃብት ያገኙት ብልጽግና በሌሎች ሰዎች ዓይን ውስጥ መግባቱ እንደማይቀር እሙን ነው። እነዚህ ነገሮች ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች የሚስቡ ሲሆኑ ተቃዋሚዎችን ደግሞ የሚያንገሸግሹ ሊሆኑ ይችላሉ። (2 ቆሮንቶስ 2:14-17) እንዲያውም ይህ ነገር በመጨረሻ የሰይጣን ኃይሎች በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ሊያነሳሳቸው ይችላል።
16 ይህ ጉዳይ ሊያሳስበን ይገባልን? ሕዝቅኤል ምዕራፍ 38 ላይ ከሚገኘው የይሖዋ ትንቢት አንጻር ካየነው ሊያሳስበን አይገባም። የማጎጉ ጎግ (ሰይጣን ዲያብሎስ የአምላክ መንግሥት በ1914 ተቋቁሞ ወደ ምድር አካባቢ ከተጣለ በኋላ የሚገኝበትን ሁኔታ የሚያመለክት መግለጫ ነው) በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሠነዝራል። (ራእይ 12:7-9) ይሖዋ ለጎግ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “እንዲህም ትላለህ:- ቅጥር ወደሌላቸው መንደሮች እወጣለሁ፤ ተዘልለው ወደሚኖሩ፣ ሁላቸው ሳይፈሩ ያለ ቅጥርና ያለ መወርወሪያ ያለ መዝጊያም ወደሚቀመጡ እገባለሁ፤ ምርኮን ትማርክ ዘንድ ብዝበዛንም ትበዘብዝ ዘንድ፣ ባድማም በነበሩ አሁንም ሰዎች በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ላይ፣ ከአሕዛብም በተሰበሰበ፣ ከብትና ዕቃንም ባገኘ፣ በምድርም መካከል በተቀመጠ ሕዝብ ላይ እጅህን ትዘረጋ ዘንድ።” (ሕዝቅኤል 38:11, 12) ይሁን እንጂ ቁጥር 4 እንደሚገልጸው የአምላክ ሕዝቦች ይህን ጥቃት የሚፈሩበት ምክንያት የለም፤ ምክንያቱም ይህንን የሚያደርገው ይሖዋ ራሱ ነው። ይሁንና አምላክ እንዲህ ያለ ኃይለኛ ጥቃት በሕዝቡ እንዲሰነዘር የሚፈቅደው አልፎ ተርፎም የሚያነሳሳው ለምንድን ነው? በቁጥር 23 ላይ ይሖዋ እንደሚከተለው ሲል የሰጠውን መልስ እናነባለን:- “ታላቅ እሆናለሁ እቀደስማለሁ በብዙ አሕዛብም ዓይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”
17. ጎግ በቅርቡ ስለሚሰነዝረው ጥቃት ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
17 በመሆኑም የይሖዋ ሕዝቦች ጎግ ስለሚሰነዝረው ጥቃት እያሰቡ በፍርሃት በመራድ ፋንታ የዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ በታላቅ ጉጉት ይጠባበቃሉ። ይሖዋ ምድራዊ ድርጅቱን በማበልጸግና በመባረክ በሰይጣን መንጋጋ ውስጥ ልጓም እንደሚያስገባና እርሱንም ሆነ ሠራዊቱን ለሽንፈት እንደሚዳርጋቸው ማወቁ ምንኛ የሚያስደስት ነው!— ሕዝቅኤል 38:4
ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ነው!
18. (ሀ) ብዙ ሰዎች ምን ነገር እየተገነዘቡ መጥተዋል? ለምንስ? (ለ) ሰዎች ለመንግሥቱ ስብከት የሚሰጡት ምላሽ ጠንካራ ቀስቃሽ ኃይል ሆኖ የሚያገለግለው እንዴት ነው?
18 በብዙ ሰዎች ዘንድ ተወዳጅ ባይሆንም እንኳ በዚህ ዘመን የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን አመለካከታቸውን በይፋ በማሳወቅ ላይ ናቸው። ሲጋራ ማጨስና አደንዛዥ ዕፆችን መጠቀም የሚያስከትለውን አደጋ፣ ልጆችን ስድ መልቀቅ አርቆ አስተዋይነት የጎደለው ድርጊት መሆኑን፣ የጾታ ብልግናና የዓመፅ ድርጊቶች የሞላባቸው መዝናኛዎች የሚያስከትሉትን ጠንቅ እንዲሁም ደም መውሰድ ያለውን አደገኛነት ላለፉት ብዙ አሥርተ ዓመታት ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። የዝግመተ ለውጥ ፅንሰ ሐሳብ እርስ በርሱ እንደማይስማማም አስረድተዋል። ዛሬ ቁጥራቸው ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የመጣ ሰዎች “የይሖዋ ምሥክሮች እውነታቸውን ሳይሆን አይቀርም” እያሉ ነው። አመለካከታችን በይፋ ባንገልጽ ኖሮ እንዲህ ባላሉ ነበር። ይህን ማለታቸው ራሱ “ሰይጣን፣ አንተ ውሸታም ነህ፤ ድሮም ይሖዋ ነው እውነተኛ” ወደ ማለት እንደተቃረቡ የሚያሳይ መሆኑን ልንዘነጋው አይገባም። ይህ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል የእውነትን ቃል በግልጽ መናገራችንን ለመቀጠል ምንኛ ሊያበረታታን ይገባል!— ምሳሌ 27:11
19, 20. (ሀ) በ1922 የይሖዋ ሕዝቦች ምን ቁርጥ አቋም እንዳላቸው ገልጸው ነበር? ዛሬስ እነዚህ ቃላት ይሠራሉን? (ለ) ለይሖዋ “ቅዱስ ምሥጢር” ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምን ዓይነት ነው?
19 የይሖዋ ሕዝቦች በዚህ ረገድ ያለባቸውን ግዴታ ከተገነዘቡ ረጅም ጊዜ ሆኗቸዋል። በ1922 በተካሄደው የማይረሳ የአውራጃ ስብሰባ ላይ በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ እንደሚከተለው በማለት አድማጮቹን ቀስቅሶ ነበር:- “አስተዋዮች ሁኑ፣ ንቁዎች ሁኑ፣ ትጉዎች ሁኑ፣ ደፋሮች ሁኑ። ለጌታ የታመናችሁና እውነተኛ ምሥክሮች ሁኑ። ባቢሎን ሙሉ በሙሉ ባድማ እስክትሆን ድረስ በትግሉ ወደፊት ግፉ። መልእክቱን በስፋት አውጁ። ይሖዋ አምላክ መሆኑን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ መሆኑን ዓለም ማወቅ አለበት። ይህ ከቀኖች ሁሉ የሚበልጥ ቀን ነው። እነሆ፣ ንጉሡ መግዛት ጀምሯል! እናንተ ስለ እርሱ የምታሳውቁ ወኪሎቹ ናችሁ። እንግዲያውስ መንግሥቱንና ንጉሡን አስታውቁ! አስታውቁ! አስታውቁ!”
20 ይህ ከተነገረ 75 ዓመት አልፏል። እነዚህ ቃላት በ1922 በጣም አስፈላጊ ከነበሩ ክርስቶስ ፈራጅና ደም ተበቃይ ሆኖ የሚገለጥበት ጊዜ በጣም በተቃረበበት በዚህ ወቅት ይበልጥ አስፈላጊ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም! ስለተቋቋመው የይሖዋ መንግሥትና የአምላክ ሕዝቦች ስላገኙት መንፈሳዊ ገነት የሚገልጸው መልእክት ባጭሩ ልንሰውረው የማይገባ ከፍተኛ ዋጋ ያለው “ቅዱስ ምሥጢር” ነው። ኢየሱስ ራሱ በግልጽ እንደተናገረው ተከታዮቹ በመንፈስ ቅዱስ እየታገዙ በይሖዋ ዘላለማዊ ዓላማ ውስጥ ስላለው ቁልፍ ሚና “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ” መመሥከር አለባቸው። (ሥራ 1:8፤ ኤፌሶን 3:8-12) እንዲያውም ምሥጢርን የሚገልጠው አምላክ የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ይህንን ምሥጢር ለራሳችን ብቻ ሰውረን ልንይዘው አይገባም!
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ‘ቅዱሱ ምሥጢር’ ምንድን ነው?
◻ ቅዱሱ ምሥጢር መታወጅ እንዳለበት እንዴት እናውቃለን?
◻ ጎግ በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር የሚያደርገው ምንድን ነው? ይህንንስ እንዴት ልናየው ይገባል?
◻ እያንዳንዳችን ምን ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ መውሰድ ይገባናል?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንድ “ቅዱስ ምሥጢር” ቀስ በቀስ ተገለጠ
◻ ከዘአበ ከ4026 በኋላ:- አምላክ ሰይጣንን የሚያጠፋ ዘር እንደሚያስነሳ ቃል ገባ።— ዘፍጥረት 3:15
◻ 1943 ከዘአበ:- የአብርሃም ቃል ኪዳን ጸደቀ፤ ይህም ዘሩ በአብርሃም በኩል እንደሚመጣ የሚያረጋግጥ ነበር።— ዘፍጥረት 12:1-7
◻ 1918 ከዘአበ:- የቃል ኪዳኑ ወራሽ የሆነው ይስሐቅ ተወለደ።— ዘፍጥረት 17:19፤ 21:1-5
◻ 1761 ከዘአበ ገደማ:- ይሖዋ ዘሩ በይስሐቅ ልጅ በያዕቆብ በኩል እንደሚመጣ አረጋገጠ።— ዘፍጥረት 28:10-15
◻ 1711 ከዘአበ:- ያዕቆብ ዘሩ በልጁ በይሁዳ በኩል እንደሚመጣ ገለጸ።— ዘፍጥረት 49:10
◻ 1070-1038 ከዘአበ:- ንጉሥ ዳዊት ዘሩ በእርሱ የዘር ሐረግ መስመር እንደሚመጣና ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ እንደሚገዛ ተገነዘበ።— 2 ሳሙኤል 7:13-16፤ መዝሙር 89:35, 36
◻ 29-33 እዘአ:- አስቀድሞ የተነገረለት ዘር፣ መሲሑ፣ የወደፊቱ ፈራጅና እጩ ንጉሥ ኢየሱስ እንደሆነ ግልጽ ሆነ።— ዮሐንስ 1:17፤ 4:25, 26፤ ሥራ 10:42, 43፤ 2 ቆሮንቶስ 1:20፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:16
◻ ኢየሱስ አብረውት ገዥዎችና ፈራጆች የሚሆኑ ሰዎች እንዳሉ፣ ሰማያዊው መንግሥት ምድራዊ ተገዥዎች እንዳሉት፣ ሁሉም ተከታዮቹ የመንግሥቱ ሰባኪዎች እንደሚሆኑ ገለጸ።— ማቴዎስ 5:3-5፤ 6:10፤ 28:19, 20፤ ሉቃስ 10:1-9፤ 12:32፤ 22:29, 30፤ ዮሐንስ 10:16፤ 14:2, 3
◻ ኢየሱስ መንግሥቱ በተወሰነ ጊዜ ላይ እንደሚቋቋምና ይህንንም የሚያመለክቱ የዓለም ሁኔታዎች እንደሚኖሩ ተናገረ።— ማቴዎስ 24:3-22፤ ሉቃስ 21:24
◻ 36 እዘአ:- ጴጥሮስ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎችም የመንግሥቱ ተባባሪ ወራሾች እንደሚሆኑ ተገነዘበ።— ሥራ 10:30-48
◻ 55 እዘአ:- ጳውሎስ ኢየሱስ በመንግሥት ሥልጣኑ በሚገኝበት ጊዜ የመንግሥቱ ተባባሪ ወራሾች የማይጠፋና የማይበሰብስ ሕይወት አግኝተው እንደሚነሱ ገለጸ።— 1 ቆሮንቶስ 15:51-54
◻ 96 እዘአ:- ከዚህ ቀደም ብሎ በቅቡዓን ተከታዮቹ ላይ መግዛት የጀመረው ኢየሱስ የቅቡዓኑ ጠቅላላ ቁጥር 144,000 እንደሚሆን ገለጸ።— ኤፌሶን 5:32፤ ቆላስይስ 1:13-20፤ ራእይ 1:1፤ 14:1-3
◻ 1879 እዘአ:- የጽዮን መጠበቂያ ግንብ 1914 በአምላክ “ቅዱስ ምሥጢር” አፈጻጸም ረገድ ትልቅ ትርጉም ያለው ዓመት እንደሆነ ገለጸ።
◻ 1925 እዘአ:- መጠበቂያ ግንብ የአምላክ መንግሥት በ1914 እንደተቋቋመና ስለ መንግሥቱ የሚናገረው “ቅዱስ ምሥጢር” መታወጅ እንዳለበት ገለጸ።— ራእይ 12:1-5, 10, 17
[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የይሖዋ ምሥክሮች እንደ መሪያቸው እንደ ኢየሱስ የይሖዋን መንግሥት በይፋ ያውጃሉ