ልጆቻችሁን አስተምሩ
ለሌሎች መናገር የምትችለው ሚስጥር
ከዚህ በፊት አንድ ሰው ሚስጥር ነግሮህ ያውቃል?—a አሁን እኔ ልነግርህ የምፈልገው አንድ ሚስጥር አለ። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሚስጥር ‘ለረጅም ዘመናት ተሰውሮ የቆየ ቅዱስ ሚስጥር’ በማለት ይጠራዋል። (ሮም 16:25) መጀመሪያ ላይ ይህንን “ቅዱስ ሚስጥር” የሚያውቀው አምላክ ብቻ ነበር። በኋላ ላይ ግን አምላክ ይህንን ሚስጥር ብዙ ሰዎች እንዲያውቁት ያደረገው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
እስቲ በመጀመሪያ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፤ “ቅዱስ” ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?— ቅዱስ ሲባል ንጹሕ ወይም በጣም ልዩ የሆነ ማለት ነው። ይህ ሚስጥር ደግሞ ቅዱስ ከሆነው አምላክ የተገኘ በመሆኑ ቅዱስ ሚስጥር ተብሎ ይጠራል። ይህን ልዩ ሚስጥር ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ያላቸው እነማን ይመስሉሃል?— አዎን፣ መላእክት ለማወቅ ይጓጓሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “መላእክትም እነዚሁኑ ነገሮች በቅርበት ለማየት ይጓጓሉ” ይላል። በእርግጥም መላእክት ይህንን ሚስጥር ለማወቅ ይፈልጋሉ።—1 ጴጥሮስ 1:12
ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣበት ወቅት ስለዚህ ቅዱስ ሚስጥር የተናገረ ከመሆኑም በላይ ማብራሪያ መስጠት ጀመረ። ደቀ መዛሙርቱን “ለእናንተ የአምላክ መንግሥት ቅዱስ ሚስጥር ተሰጥቷችኋል” ብሏቸዋል። (ማርቆስ 4:11) ይህ ሚስጥር ስለ ምን ጉዳይ እንደሚናገር ተገነዘብክ?— ይህ ሚስጥር ኢየሱስ እንድንጸልይለት ስላስተማረን ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገር ነው!—ማቴዎስ 6:9, 10
እስቲ አሁን ደግሞ ኢየሱስ ወደ ምድር መጥቶ ስለ አምላክ መንግሥት ማብራሪያ መስጠት እስኪጀምር ድረስ ይህ መንግሥት ‘ለረጅም ዘመናት ተሰውሮ የቆየው’ እንዴት እንደሆነ እንመልከት። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ሠርተው ከኤደን የአትክልት ስፍራ ከተባረሩ በኋላ የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች፣ አምላክ መላዋን ምድር ገነት እንድትሆን ያወጣው ዓላማ እንዳልተለወጠ ያውቁ ነበር። (ዘፍጥረት 1:26-28፤ 2:8, 9፤ ኢሳይያስ 45:18) እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች፣ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች አስደሳች ሕይወት እንደሚኖራቸው ጽፈዋል።—መዝሙር 37:11, 29፤ ኢሳይያስ 11:6-9፤ 25:8፤ 33:24፤ 65:21-24
እስቲ አሁን ደግሞ ስለ አምላክ መንግሥት ገዥ ቆም ብለህ አስብ። አምላክ የዚህ መንግሥት ገዥ እንዲሆን የመረጠው ማንን እንደሆነ ታውቃለህ?— “የሰላም ልዑል” የሆነውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የልዑል አገዛዝም በጫንቃው ላይ ይሆናል” በማለት ይናገራል። (ኢሳይያስ 9:6, 7 NW) እኔም ሆንኩ አንተ “የአምላክ ቅዱስ ሚስጥር ስለሆነው ስለ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት” ማግኘት ይኖርብናል። (ቆላስይስ 2:2) አምላክ መጀመሪያ የፈጠረውን መልአክ (መንፈሳዊ ልጅ) ሕይወት ወደ ማርያም ማህፀን እንዳዛወረ ማወቅ ይኖርብናል። አምላክ ኃያል መልአክ የነበረውን ይህን ልጁን መሥዋዕት እንዲሆን ወደ ምድር ላከው፤ በዚህም ምክንያት የዘላለም ሕይወት ተስፋ ማግኘት ችለናል።—ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16፤ 17:3
ይህን ሚስጥር ማወቅ አምላክ ልጁን የመንግሥቱ ገዥ አድርጎ መምረጡን ከማወቅ የበለጠ ነገርን ይጨምራል። የዚህ ቅዱስ ሚስጥር ሌላው ክፍል ደግሞ ወንዶችና ሴቶች ከሞት ከተነሳው ኢየሱስ ጋር በሰማይ የሚኖሩ መሆናቸው ነው። እነዚህ ሰዎች በሰማይ ሆነው ከኢየሱስ ጋር ይገዛሉ!—ኤፌሶን 1:8-12
አሁን ደግሞ በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ከሚገዙት ሰዎች መካከል የአንዳንዶቹን ስም እንመልከት። ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ፣ ለእነሱ ቦታ ለማዘጋጀት እንደሚሄድ ነግሯቸው ነበር። (ዮሐንስ 14:2, 3) የሚከተሉትን ጥቅሶች በማንበብ በአባቱ መንግሥት ከኢየሱስ ጋር ከሚገዙት ወንዶችና ሴቶች መካከል የጥቂቶቹን ስም ማወቅ ትችላለህ።—ማቴዎስ 10:2-4፤ ማርቆስ 15:39-41፤ ዮሐንስ 19:25
ለረጅም ጊዜ የዚህ መንግሥት ክፍል በመሆን ከኢየሱስ ጋር የሚገዙት ምን ያህል ሰዎች እንደሆኑ አይታወቅም ነበር። ይሁን እንጂ አሁን ቁጥራቸውን ማወቅ እንችላለን። አንተስ ቁጥራቸው ስንት እንደሆነ ታውቃለህ?— መጽሐፍ ቅዱስ 144,000 እንደሆነ ይናገራል። ይህም ቢሆን የቅዱሱ ሚስጥር ክፍል ነው።—ራእይ 14:1, 4
ታዲያ ይህ “የአምላክ መንግሥት ቅዱስ ሚስጥር” ማንኛውም ሰው ሊያውቀው ከሚችለው ሚስጥር ሁሉ እጅግ አስደናቂ ነው ቢባል አትስማማም?— ከሆነ በተቻለን መጠን ለብዙ ሰዎች መናገር እንድንችል ስለዚህ ሚስጥር ለማወቅ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናድርግ።
a ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ፣ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።