መዳን በእርግጥ ምን ማለት ነው?
‘ድነሃል?’ ብዙውን ጊዜ ይህን ጥያቄ የሚጠይቁ ሰዎች ‘ኢየሱስን እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው ስለተቀበሉ’ ድነናል ብለው ያስባሉ። ሌሎች ሰዎች ደግሞ ወደ መዳን የሚወስዱ የተለያዩ መንገዶች ስላሉ ‘ኢየሱስ በልብህ ውስጥ እስካለ’ ድረስ የፈለግኸውን ብታምን ወይም የየትኛውም ቤተ ክርስቲያን አባል ብትሆን ምንም ለውጥ አያመጣም ብለው ያስባሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ” የአምላክ ፈቃድ መሆኑን ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) ስለሆነም የእሱን ፈቃድ የሚቀበሉ ሁሉ መዳንን ሊያገኙ ይችላሉ። ሆኖም መዳን ሲባል ምን ማለት ነው? በአንተ በኩል ትንሽ ጥረት በማድረግ ወይም ምንም ጥረት ሳታደርግ እንዲያው በቀላሉ ልታገኘው የምትችለው ነገር ነውን?
“መዳን” የሚለው ቃል “ከአደጋ ወይም ከጥፋት መትረፍ” የሚል ትርጉም አለው። ስለዚህ እውነተኛ መዳን በእርጋታ ከተሞላ የአእምሮ ሁኔታ የበለጠ ነገርን የሚያጠቃልል ነው። ከዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ጥፋትና በመጨረሻም ከሞት ጭምር መትረፍ ማለት ነው! ይሁን እንጂ አምላክ የሚያድነው ማንን ነው? ለዚህ መልስ ይሆነን ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዚህ ጉዳይ ያስተማረውን እንመርምር። ስለዚህ ጉዳይ ስንመረምር የምንደርስበት መደምደሚያ ያስገርምህ ይሆናል።
መዳን—በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ ይገኛልን?
በአንድ ወቅት ኢየሱስ ከአንዲት ሳምራዊት ሴት ጋር ተወያይቶ ነበር። ይህች ሴት አይሁዳዊት ባትሆንም “ክርስቶስ የሚባል” መሲህ እንደሚመጣ በትክክል ታምን ነበር። (ዮሐንስ 4:25) ይህ እምነቷ ለመዳን ብቁ ያደርጋት ነበርን? ኢየሱስ ለሳምራዊቷ ሴት “እናንተ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ” ሲል በድፍረት በመናገር ብቁ ሊያደርጋት እንደማይችል ገልጿል። ኢየሱስ ይህች ሴት መዳንን ለማግኘት ከፈለገች የአምልኮ መንገዷን ማስተካከል እንዳለባት ያውቅ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ በማለት ተናገረ:- “ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና።”—ዮሐንስ 4:22, 23
ኢየሱስ መዳንን በተመለከተ ያለውን አመለካከት የገለጸበት ሌላው አጋጣሚ ደግሞ የአይሁድ እምነት ዋነኛ ክፍል የሆኑትን ፈሪሳውያንን በሚመለከት የተናገረው ነበር። ፈሪሳውያን የራሳቸውን የአምልኮ ሥርዓት አቋቁመው የነበረ ሲሆን ሥርዓቱንም አምላክ ተቀብሎታል ብለው ያምኑ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ፈሪሳውያንን ምን እንዳላቸው አዳምጡ:- “እናንተ ግብዞች፣ ኢሳይያስ ስለ እናንተ:- ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፣ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ።”—ማቴዎስ 15:7-9
ዛሬ ስላሉትና በክርስቶስ እናምናለን ስለሚሉት በርካታ የሃይማኖት ቡድኖች ምን ለማለት ይቻላል? ኢየሱስ ሁሉንም የሃይማኖት ቡድኖች መዳንን የሚያስገኙ ትክክለኛ መንገዶች አድርጎ ይቀበላቸዋልን? ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት በግልጽ ስለተናገረ ይህን በተመለከተ የመላምት ሀሳብ መስጠት አያስፈልገንም:- “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፣ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። በዚያ ቀን ብዙዎች:- ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፣ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፣ በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም:- ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።”—ማቴዎስ 7:21-23
ስለ ኢየሱስ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ለመዳን የግድ አስፈላጊ ነው
እነዚህ የኢየሱስ ቃላት ትልቅ ቁም ነገር ያዘሉ ናቸው። እነዚህ ቃላት ቅንዓት ያላቸው ብዙ ሰዎች ‘የአባቱን ፈቃድ ለማድረግ’ አለመቻላቸውን ያመለክታሉ። ታዲያ አንድ ሰው እውነተኛ መዳንን ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነው? አንደኛ ጢሞቴዎስ 2:3, 4 (NW) እንዲህ በማለት መልስ ይሰጣል:- “[የአምላክ] ፈቃድ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና ወደ ትክክለኛ የእውነት እውቀት እንዲደርሱ ነው።”—ከቆላስይስ 1:9, 10 ጋር አወዳድር።
እንዲህ ዓይነቱ እውቀት መዳንን ለማግኘት የግድ አስፈላጊ ነው። ሮማዊው የወህኒ ቤት ጠባቂ ሐዋርያው ጳውሎስንና ጓደኛውን ሲላስን “እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህም ትድናላችሁ” በማለት መለሱለት። (ሥራ 16:30, 31) ታዲያ ይህ ማለት የወህኒ ቤት ጠባቂውና ቤተሰቡ ሊያደርጉት የሚገባቸው ብቸኛ ነገር አንድ የሆነ ስሜት በልባቸው ውስጥ ማሳደር ነውን? እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ ማን እንደነበረ፣ ምን እንዳደረገና ምን እንዳስተማረ የሚገልጽ የተወሰነ ማስተዋል እስከሌላቸው ድረስ ከልብ ‘በጌታ በኢየሱስ ለማመን’ አይችሉም።
ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ስለ ሰማያዊው መንግሥት ማለትም ስለ ‘አምላክ መንግሥት’ መቋቋም አስተምሯል። (ሉቃስ 4:43) ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርንና ጠባይን አስመልክቶም መመሪያዎችን ሰጥቷል። (ማቴዎስ ምዕራፍ 5-7) ደቀ መዛሙርቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሊወስዱት የሚገባቸውን አቋም ገልጾላቸዋል። (ዮሐንስ 15:19) ዓለም አቀፍ የሆነ የማስተማር መርሐ ግብር የዘረጋ ሲሆን ተከታዮቹንም በዚህ መርሐ ግብር ተካፋይ እንዲሆኑ አዟቸዋል። (ማቴዎስ 24:14፤ ሥራ 1:8) አዎን፣ ‘በኢየሱስ ማመን’ ስለ ብዙ ነገሮች ማስተዋል ማግኘት ማለት ነው! ስለዚህ ጳውሎስና ሲላስ “ለእርሱና [ለወህኒ ቤቱ ጠባቂና] በቤቱም ላሉት ሁሉ የእግዚአብሔርን [“የይሖዋን፣” NW] ቃል” የነገሯቸው እነዚህ አዲስ አማኞች ከመጠመቃቸው በፊት መሆኑ አያስገርምም።—ሥራ 16:32, 33
ስለ አምላክም ትክክለኛ እውቀት ማግኘት የግድ አስፈላጊ ነው
በኢየሱስ ከልብ የማመን አንዱ አስፈላጊ ክፍል ኢየሱስ ራሱ የሚያመልከውን አምላክ ማምለክን ይጨምራል። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጸልዮአል:- “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።”—ዮሐንስ 17:3
የአምላክ ልጅ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ሁልጊዜ የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሱ ሳይሆን ወደ አባቱ ይመራ ነበር። ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ ብሎ አያውቅም። (ዮሐንስ 12:49, 50) ኢየሱስ በተለያዩ ወቅቶች የአባቱ የበታች መሆኑን በመናገር በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ያለውን ቦታ ገልጿል። (ሉቃስ 22:41, 42፤ ዮሐንስ 5:19) እንዲያውም ኢየሱስ “ከእኔ አብ ይበልጣል” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:28) ቤተ ክርስቲያንህ በአምላክ እና በክርስቶስ መካከል ያለውን ትክክለኛ ዝምድና አስተምሮሃል? ወይስ ኢየሱስ ራሱ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው ብለህ እንድታምን ተደርገሃል? መዳንህ ትክክለኛ ማስተዋል በማግኘትህ ላይ የተመካ ነው።
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በጌታ ጸሎት ላይ “ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ አሳስቧቸዋል። (ማቴዎስ 6:9) አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የአምላክን ስም “ጌታ” በሚለው ቃል በመተካት በግልጽ እንዳይታወቅ አድርገዋል። ይሁን እንጂ በጥንቶቹ “የብሉይ ኪዳን” ቅጂዎች የአምላክ ስም ከስድስት ሺህ ጊዜ በላይ ተጽፎ ይገኛል! ይህም በመሆኑ መዝሙር 83:18 (NW) እንዲህ ይላል:- “ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ በምድር ሁሉ ላይ አንተ ብቻ ልዑል እንደሆንክ ሰዎች ሁሉ ይወቁ።” ይሖዋ በሚለው የአምላክ ስም መጠቀም እንዳለብህ ተምረሃልን? ካልሆነ “የጌታን [“የይሖዋን፣” NW] ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል” ስለሚል መዳንህ በሚያሰጋ ሁኔታ ላይ ይገኛል!—ሥራ 2:21፤ ከኢዩኤል 2:32 ጋር አወዳድር።
በመንፈስና በእውነት
ኢየሱስ ክርስቶስ የሰዎችን ትኩረት የአምላክ ቃል ወደ ሆነው ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ጭምር ይመራ ነበር። ስለ አንዳንድ ጉዳዮች አምላክ ያለውን አመለካከት ሲያብራራ ብዙውን ጊዜ “ተብሎ ተጽፎአል” ይል ነበር። (ማቴዎስ 4:4, 7, 10፤ 11:10፤ 21:13) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ተከታዮቹን በሚመለከት እንዲህ ብሎ ጸልዮአል:- “በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው።”—ዮሐንስ 17:17
ስለዚህ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት ትምህርቶች ትክክለኛ ማስተዋል ማግኘት ለመዳን ሌላው አስፈላጊ ነገር ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) የሕይወት ትርጉም ምንድን ነው? አምላክ ክፋት ለዚህን ያህል ረጅም ጊዜ እንዲቆይ የፈቀደው ለምንድን ነው? አንድ ሰው ሲሞት ምን ይሆናል? በእርግጥ አምላክ በእሳታማ ሲኦል ሰዎችን ያሰቃያል? አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?a ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ የሚሰጠው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ኢየሱስ “በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል” በማለት ስለተናገረ አንድ ሰው እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ትክክለኛ ማስተዋል እስካላገኘ ድረስ አምላክን በተገቢው መንገድ ለማምለክ አይችልም።—ዮሐንስ 4:23
እምነት ለተግባር ያንቀሳቅሳል
ለመዳን እውቀት መሰብሰብ ብቻ በቂ አይደለም። ከአምላክ የሚገኝ ትክክለኛ እውቀት አድናቂ በሆነ ልብ ውስጥ እምነት ያፈራል። (ሮሜ 10:10, 17፤ ዕብራውያን 11:6) ይህን የመሰለው እምነት አንድን ሰው ለተግባር ያንቀሳቅሰዋል። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ “እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፣ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም” በማለት ይመክረናል።—ሥራ 3:19
አዎን፣ መዳን ከአምላክ የጠባይና የሥነ ምግባር መስፈርቶች ጋር ራስን ማስማማትን ይጨምራል። የአምላክ ቃል ባለው የመለወጥ ኃይል የዕድሜ ልክ ልማዶች የነበሩት መዋሸትና ማጭበርበር ለታማኝነትና ለሐቀኝነት ቦታቸውን ይለቃሉ። (ቲቶ 2:10) እንደ ግብረ ሰዶም፣ ምንዝርና ዝሙት የመሳሰሉት ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ድርጊቶች በንጹሕ አኗኗር ይተካሉ። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) ይህ በስሜት ተነሳስቶ ለጊዜው ብቻ ከመጥፎ ድርጊቶች መቆጠብ ሳይሆን የአምላክን ቃል በጥንቃቄ ከማጥናትና ተግባራዊ ከማድረግ የሚመጣ ዘላቂ ለውጥ ነው።—ኤፌሶን 4:22-24
ልበ ቅን የሆነ ሰው ለአምላክ ያለው አድናቆት ውሎ አድሮ ራሱን ለአምላክ እንዲወስንና እንዲጠመቅ ይገፋፋዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ሮሜ 12:1) የተጠመቁ ክርስቲያኖች በአምላክ ዓይን ድነዋል። (1 ጴጥሮስ 3:21) ይህ ክፉ ዓለም በሚጠፋበት ጊዜ ከሚኖረው መከራ አምላክ በሕይወት ጠብቆ ያድናቸዋል።—ራእይ 7:9, 14
መዳን ለአንተ ሊኖረው የሚገባው ትርጉም
መዳንን ለማግኘት ‘ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በልብ ውስጥ ማኖር’ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ከዚህ አጭር ማብራሪያ መገንዘብ ችለናል። ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት ማግኘትና በሕይወት ውስጥ ተፈላጊ የሆኑ ለውጦች ማድረግ ይጠይቃል። ይህን ማድረጉ አዳጋች ይመስልህ ይሆናል፤ ነገር ግን የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ጥረትህ ሊያግዙህ ፈቃደኞች ናቸው። በነፃ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት ወደ መዳን በሚወስደው ትክክለኛ መንገድ ላይ መጓዝ እንድትጀምር ሊረዱህ ይችላሉ።b
መጪው የአምላክ የፍርድ ቀን በጣም ስለቀረበ ይህን ማድረጉ ከምንጊዜውም በላይ አጣዳፊ ነው! “የእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ፣ ተከማቹም። እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንም ፈልጉ፤ ምናልባት በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል” የሚሉትን ትንቢታዊ ቃላት ለመፈጸም ጊዜው አሁን ነው።—ሶፎንያስ 2:2, 3
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a እነዚህን ርዕሰ ጉዳዮች በሚመለከት ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ እባክህ ተመልከት።
b የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምትፈልግ ከሆነ እባክህ በአቅራቢያህ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ጋር ተገናኝ። አለዚያም ለዚህ መጽሔት አታሚዎች ልትጽፍ ትችላለህ።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መዳን የሚገኘው . . .
◻ ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ ትክክለኛ እውቀት በማግኘት።—ዮሐንስ 17:3
◻ እምነት እንዳለን በማሳየት።—ሮሜ 10:17፤ ዕብራውያን 11:6
◻ ንስሐ በመግባትና በመመለስ።—ሥራ 3:19፤ ኤፌሶን 4:22-24
◻ ራስን በመወሰንና በመጠመቅ።—ማቴዎስ 16:24፤ 28:19, 20
◻ ያለማሰለስ ምሥራቹን ለሕዝብ በማወጅ።—ማቴዎስ 24:14፤ ሮሜ 10:10
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ የተማሩትን ተግባራዊ ማድረግ፣ ራስን መወሰን እና መጠመቅ ወደ መዳን የሚመሩ እርምጃዎች ናቸው