በመከራ ጊዜ መዳን
በኮርያ ዋና ከተማ በሴኡል የሚገኝ አንድ ባለ አምስት ፎቅ የገበያ አዳራሽ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በውስጡ እንዳሉ በድንገት ፈረሰ! ሕይወት አድን ሠራተኞች ቀንና ሌሊት በመሥራት በተቻለ መጠን ብዙ ሕይወት ለማትረፍ ጣሩ። ቀናት እያለፉ በሄዱ ቁጥር ከዚያ የፍርስራሽ ክምር ውስጥ በሕይወት ያሉ ተጨማሪ ሰዎችን የማግኘቱ ተስፋ እየደበዘዘ ሄደ።
በሕይወት ያሉ ሰዎችን የማግኘቱ ተስፋ ባከተመበት ወቅት እጅግ የሚያስደንቅ አንድ ነገር ተከሰተ። በጣም የሚያሳዝን የሰለለ ድምፅ ከፍርስራሹ ክምር ሥር ተሰማ። ሕይወት አድን ሠራተኞች ለ16 ቀናት ከነሕይወቷ ተቀብራ የነበረችን አንዲት የ19 ዓመት ልጅ ለማውጣት በጥድፊያና በጭንቀት ስሜት ያለምንም መሣሪያ በእጃቸው ፍርስራሹን ፈነቃቀሉ። ልጅቷ ለአሳንሱር መውጫና መውረጃ ተብሎ በተሰራው ባዶ ቦታ ውስጥ ስለነበረች ከላይ ከነበረው የፍርስራሽ ክምር ልትጠበቅ ችላለች። ክፉኛ የቆሰለችና በሰውነቷ ውስጥ ያለው ፈሳሽ የተሟጠጠ ቢሆንም ከሞት ልታመልጥ ችላለች!
በዛሬው ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ኃይለኛ ማዕበል፣ የእሳተ ጎሞራ ፍንዳታና ሌሎች አደጋዎች ስላደረሱት የሕይወትና የንብረት ጥፋት በዜና ሳይሰማ ያለፈበት አንድም ወር የለም ለማለት ይቻላል። ሕይወት ለማዳን ስለተደረጉ ጥረቶችና በሕይወት ለመትረፍ ስለቻሉ ሰዎች የሚነገሩ ወሬዎች ዜና የሚከታተሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ትኩረት የሚስቡና የሚማርኩ ናቸው። ይሁን እንጂ ወደፊት ስለሚመጣውና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱት ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ስለሆነው ጥፋት የሚነገረው ማስጠንቀቂያ ጆሮ ተነፍጎታል። (ማቴዎስ 24:21) መጽሐፍ ቅዱስ መጪውን ጥፋት እንደሚከተለው በማለት ይገልጸዋል:- “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- እነሆ፣ ክፉ ነገር ከሕዝብ ወደ ሕዝብ ይወጣል፣ ጽኑም ዐውሎ ነፋስ ከምድር ዳርቻ ይነሣል። በዚያም ቀን የእግዚአብሔር ግዳዮች ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይሆናሉ፤ አይለቀስላቸውም፤ በምድር ላይ እንደ ጉድፍ ይሆናሉ እንጂ አይከማቹም አይቀበሩምም።”—ኤርምያስ 25:32, 33
አስደንጋጭ ቃላት! ነገር ግን ይህ ጥፋት እንደ ተፈጥሮ አደጋዎችና ሌሎች አሳዛኝ ክስተቶች ማንንም ሳይለይ የሚጨርስ አይደለም። እንዲያውም በሕይወት መትረፍ ይቻላል። አዎን፣ አንተም ጭምር በሕይወት ልትተርፍ ትችላለህ!
አጣዳፊ የሆነ ጊዜ
ይህን ሐቅ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት አንድ ሰው በመጀመሪያ ደረጃ ይህ ዓለም አቀፍ ጥፋት ለምን እንደሚከሰት ማወቅ ይኖርበታል። እንደ እውነቱ ከሆነ ለሰው ልጅ ችግሮች ብቸኛው መፍትሔ ይህ ነው። ዛሬ ያለስጋትና ያለፍርሃት የሚኖሩ ሰዎች ጥቂት ናቸው። ሳይንስ የተቻለውን ያህል ጥረት ቢያደርግም ተላላፊ በሽታዎች የምድርን ሕዝብ መፍጀታቸውን ቀጥለዋል። በሃይማኖት፣ በጎሳና በፖለቲካ ልዩነቶች ምክንያት የሚነሱ ጦርነቶች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፉ ናቸው። ረሃብ ንጹሐን ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ያለባቸውን ሥቃይና መከራ ያባብስባቸዋል። የሥነ ምግባር መበላሸት የኅብረተሰቡን መሠረት ውስጥ ውስጡን እየሸረሸረው ነው። ሌላው ቀርቶ ሕፃናት ሳይቀር ብልሹ እንዲሆኑ እየተደረጉ ነው።
ከ1,900 ዓመታት በፊት የተጻፈ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ዛሬ እኛ ያለንበትን ሁኔታ በሚያስደንቅ መንገድ በትክክል ገልጾታል። እንዲህ ይላል:- “በመጨረሻዎቹ ቀናት ጊዜው በአደገኛ ሁኔታዎች የተሞላ እንደሚሆን መገንዘብ አለባችሁ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1 በጄ ቢ ፊሊፕስ የተዘጋጀው ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ኢንግሊሽ፤ ከማቴዎስ 24:3-22 ጋር አወዳድር።
አፍቃሪ የሆነ አምላክ ለሚደርሱብን መከራዎች ግድ የለሽ ነው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ይመስልሃልን? መጽሐፍ ቅዱስ ‘እግዚአብሔር ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፣ መኖሪያ ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን አልፈጠራትም’ በማለት ይናገራል። (ኢሳይያስ 45:18) አዎን፣ ይህች ውብ ፕላኔት እንድትበላሽና ነዋሪዎቿም እንዲጠፉ ከመፍቀድ ይልቅ አምላክ ጣልቃ ይገባል። አሁን የሚነሳው ጥያቄ ይህን የሚፈጽመው እንዴት ነው? የሚል ይሆናል።
ሕይወትን ምረጥ!
መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 92:7 ላይ እንደሚከተለው በማለት መልስ ይሰጣል:- “ኃጢአተኞች እንደ ሣር ሲበቅሉ፣ ዓመፃ የሚያደርጉ ሁሉ ሲለመልሙ፣ ለዘላለም ዓለም እንደሚጠፉ ነው።” አምላክ ለምድር ችግሮች ያዘጋጀው መፍትሔ ክፋትን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ነው። ይህ ደግሞ ሰዎች ሁሉ መጥፋት አለባቸው ማለት አለመሆኑ ደስ ያሰኛል። መዝሙር 37:34 “እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፣ መንገዱንም ጠብቅ፣ ምድርን ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ኃጢአተኞችም ሲጠፉ ታያለህ” በማለት ዋስትና ይሰጠናል።
እነዚህ ቃላት የሰው ልጅ ከፊቱ ከሚጠብቀው ታላቅ መከራ የመዳን አጋጣሚ እንዳለው ያመለክታሉ። አምላክ ምርጫ ሰጥቶናል። ሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በዝግጅት ላይ የነበሩትን እስራኤላውያንን ለመምከር የተጠቀመባቸው ቃላት ለእኛም ዛሬ በትክክል ይሠራሉ:- “በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን አስቀምጫለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ።” (ዘዳግም 30:19) ይሁን እንጂ አንድ ሰው ‘ሕይወትን ሊመርጥ’ እና ሊድን የሚችለው እንዴት ነው? እውነተኛ መዳን በእርግጥ ምን ማለት ነው?
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
COVER: Explosion: Copyright © Gene Blevins/Los Angeles Daily News
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Yunhap News Agency/Sipa Press