“ልብህ ከልቤ ጋር በቅንነት ነውን?”
“ከእኔ ጋር ና፣ ለእግዚአብሔርም መቅናቴን እይ።” —2 ነገሥት 10:16
1, 2. (ሀ) የእስራኤል ሃይማኖታዊ ሁኔታ እየከፋ የሄደው እንዴት ነበር? (ለ) በ905 ከዘአበ እስራኤል ውስጥ ምን ከፍተኛ ለውጦች ሊካሄዱ ተቃርበው ነበር?
ዘጠኝ መቶ አምስት ከዘአበ በእስራኤል ከፍተኛ ለውጥ የተካሄደበት ዓመት ነው። ከዚህ አንድ መቶ ዓመት ገደማ ቀደም ብሎ ሰሎሞን ክህደት በመፈጸሙ ምክንያት ይሖዋ አንድ የነበረው የእስራኤል መንግሥት እንዲከፋፈል አድርጎ ነበር። (1 ነገሥት 11:9-13) ከዚያ በኋላ ደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ሲተዳደር ሰሜናዊውን የእስራኤል መንግሥት ደግሞ ኤፍሬማዊው ንጉሥ ኢዮርብዓም መግዛት ጀመረ። የሚያሳዝነው የሰሜናዊው መንግሥት ጅምር አላማረም። ኢዮርብዓም በእርሱ መንግሥት ሥር ያለው ሕዝብ ወደ ዳዊት ቤት የመመለስ ሐሳብ ይመጣበታል ብሎ ስላሰበ በቤተ መቅደሱ አምልኮ ለማካሄድ ሲሉ ወደ ደቡባዊው መንግሥት መሄዳቸውን አልወደደውም። ከዚህ የተነሣ በእስራኤል የጥጃ አምልኮ በማቆም በሰሜኑ መንግሥት ታሪክ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ የዘለቀ የጣዖት አምልኮ መሠረተ።—1 ነገሥት 12:26-33
2 የዘምበሪ ልጅ አክዓብ በነገሠ ጊዜ ደግሞ ሁኔታው ይባስ የከፋ ሆኖ ነበር። ከባዕድ አገር ያገባት ሚስቱ ኤልዛቤል የበኣልን አምልኮ በማስፋፋት የይሖዋን ነቢያት ገደለች። ኤልያስ ግልጽ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም አክዓብ እርሷን ለመግታት ምንም እርምጃ አልወሰደም። ይሁን እንጂ በ905 ከዘአበ አክዓብ ሞተና ልጁ ኢዮራም በፋንታው ነገሠ። አሁን ምድሪቷ የምትጸዳበት ጊዜ ደርሶ ነበር። የጦር አዛዥ የነበረው ኢዩ ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን ይሖዋ እንደቀባው በኤልያስ እግር የተተካው ኤልሳዕ ነግሮታል። የኢዩ ተልእኮ ምን ነበር? ኃጢአተኛውን የአክዓብ ቤት ማጥፋትና ኤልዛቤል ያፈሰሰችውን የነቢያት ደም መበቀል ነበር!—2 ነገሥት 9:1-10
3, 4. ኢዮናዳብ ልቡ ‘ከኢዩ ልብ ጋር በቅንነት’ እንደነበረ ያሳየው እንዴት ነው?
3 ኢዩ የአምላክን መመሪያ በመታዘዝ ክፉ የነበረችው ኤልዛቤል እንድትገደል ከማድረጉም በላይ የአክዓብን ቤት በማጥፋት እስራኤልን ማጽዳቱን ተያያዘው። (2 ነገሥት 9:15, 10:14, 17) ኢዩ በሚወስደው እርምጃ የሚደግፈውም ሰው አገኘ። “ከዚያም በሄደ ጊዜ የሬካብን ልጅ ኢዮናዳብን ተገናኘው [“ወደ እርሱ ሲወጣ አገኘው፣” NW]፤ ደህንነቱንም ጠይቆ:- ልቤ ከልብህ ጋር እንደሆነ ያህል ልብህ ከልቤ ጋር በቅንነት ነውን? አለው፤ ኢዮናዳብም:- እንዲሁ ነው አለው። ኢዩም:- እንዲሁ እንደ ሆነስ እጅህን ስጠኝ አለ። እጁንም ሰጠው፤ ወደ ሰረገላውም አውጥቶ ከእርሱ ጋር አስቀመጠውና:- ከእኔ ጋር ና፣ ለእግዚአብሔርም መቅናቴን እይ አለው። በሰረገላውም አስቀመጠው።”—2 ነገሥት 10:15, 16
4 ኢዮናዳብ (ወይም ዮናዳብ) እስራኤላዊ አልነበረም። የሆነ ሆኖ (“ይሖዋ ፈቃደኛ ነው፣” “ይሖዋ ታላቅ ነው” ወይም “ይሖዋ ለጋስ ነው” የሚል ትርጉም ያለው) ስሙ ይሖዋን የሚያመልክ ሰው እንደነበር ይጠቁማል። (ኤርምያስ 35:6) ኢዩ ‘ለይሖዋ የነበረውን ቅንዓት ለማየት’ ለየት ያለ ፍላጎት እንደነበረው የተረጋገጠ ነው። ይህን እንዴት እናውቃለን? ከእጩው የእስራኤል ንጉሥ ጋር የተገናኘው እንዲሁ በአጋጣሚ አልነበረም። ኢዮናዳብ ‘ሊገናኘው ወደ እርሱ’ መውጣቱ ነበር፤ ይህ የሆነው ኢዩ ኤልዛቤልንና በአክዓብ ቤት ያሉትን ሁሉ ከገደለ በኋላ ነው። ኢዮናዳብ ወደ ሰረገላው እንዲወጣ ኢዩ ያቀረበለትን ግብዣ ሲቀበል ምን ነገር እየተፈጸመ እንዳለ ያውቅ ነበር። በሐሰተኛና በእውነተኛው አምልኮ መካከል በተነሳው በዚህ ፍጥጫ ውስጥ ኢዮናዳብ ያላንዳች ማወላወል ከኢዩና ከይሖዋ ጎን ቆሟል።
የዘመናችን ኢዩና የዘመናችን ኢዮናዳብ
5. (ሀ) በቅርቡ በመላው የሰው ዘር ሁኔታ ላይ ምን ዓይነት ለውጥ ይመጣል? (ለ) ታላቁ ኢዩ ማን ነው? እርሱንስ በምድር ላይ የሚወክለው ማን ነው?
5 በ905 ከዘአበ በእስራኤል ከፍተኛ ለውጥ እንደተካሄደ ሁሉ ዛሬ ያለውም መላው የሰው ዘር በቅርቡ ከፍተኛ ለውጥ ሲከናወን ያያል። ይሖዋ የሐሰት ሃይማኖትን ጨምሮ የሰይጣን ተጽዕኖ ያስከተላቸውን መጥፎ ውጤቶች በሙሉ ከዚህች ምድር ላይ የሚያጸዳበት ጊዜ ቀርቧል። የዘመናችን ኢዩ ማን ነው? የሚከተሉት ትንቢታዊ ቃላት ከተነገሩለት ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም:- “ኃያል ሆይ፣ በቁንጅናህና በውበትህ ሰይፍህን በወገብህ ታጠቅ። ስለ ቅንነትና ስለ ጽድቅም አቅና ተከናወን ንገሥም።” (መዝሙር 45:3, 4) ኢየሱስ በምድር ላይ የሚወከለው ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በሚጠብቁት የኢየሱስም ምስክር ባላቸውና’ ‘የአምላክ እስራኤል’ በሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ነው። (ገላትያ 6:16፤ ራእይ 12:17) እነዚህ የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች ከ1922 አንስቶ ስለ መጪው የይሖዋ የፍርድ እርምጃ ያላንዳች ፍርሃት ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።—ኢሳይያስ 61:1, 2፤ ራእይ 8:7–9:21፤ 16:2-21
6. ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ለመርዳት ከአሕዛብ ወጥተው የመጡት እነማን ናቸው? እነዚህስ በታላቁ ኢዩ ሠረገላ ላይ እንደወጡ ተደርገው ሊገለጹ የሚችሉት እንዴት ነው?
6 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻቸውን አልነበሩም። ኢዮናዳብ ኢዩን ሊገናኘው እንደወጣ ሁሉ ታላቁ ኢዩ ኢየሱስና ምድራዊ ወኪሎቹ ለእውነተኛው አምልኮ የወሰዱትን አቋም ለመደገፍ ብዙ ሰዎች ከየብሔራቱ ተውጣጥተው መጥተዋል። (ዘካርያስ 8:23) ኢየሱስ የእርሱ “ሌሎች በጎች” እንደሆኑ የተናገረላቸው እነዚህ ሰዎች በ1932 የጥንቱ ኢዮናዳብ ዘመናዊ አምሳያዎች መሆናቸው ታውቆ ወደ ዘመናችን የኢዩ ‘ሰረገላ እንዲወጡ’ ተጋብዘዋል። (ዮሐንስ 10:16) እንዴት? ‘የአምላክን ትእዛዛት በመጠበቅና’ ከቅቡዓኑ ጋር ‘ስለ ኢየሱስ በመመሥከሩ ሥራ’ በመካፈል ነው። ይህ በዛሬው ጊዜ ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ስለተሾመበት ስለ ተቋቋመው የአምላክ መንግሥት ምሥራች መስበክን ያመለክታል። (ማርቆስ 13:10) በ1935 እነዚህ “ኢዮናዳቦች” በራእይ 7:9-17 ላይ የተገለጹት “እጅግ ብዙ ሰዎች” መሆናቸው ታውቋል።
7. ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች ‘ልባቸው አሁንም ከኢየሱስ ልብ ጋር በቅንነት’ እንደሆነ ያሳዩት እንዴት ነው?
7 ከ1930ዎቹ አንስቶ እጅግ ብዙ ሰዎችና ቅቡዓን ወንድሞቻቸው እውነተኛውን አምልኮ እንደሚደግፉ በድፍረት አሳይተዋል። በምሥራቅና በምዕራብ አውሮፓ፣ በሩቅ ምሥራቅ እንዲሁም በአፍሪካ ውስጥ ባሉ አንዳንድ ቦታዎች ብዙዎቹ ለእምነታቸው ሞተዋል። (ሉቃስ 9:23, 24) በሌሎች አገሮች ደግሞ ታስረዋል፣ የሕዝብ ዓመፅ ተነስቶባቸዋል ወይም ደግሞ ተሰድደዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) ምንኛ አስደናቂ እምነት አሳይተዋል! ዛሬም ቢሆን የመጣው ቢመጣ አምላክን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረጉ የ1997 የአገልግሎት ዓመት ሪፖርት ያሳያል። ‘ልባቸው ከኢየሱስ ልብ ጋር በቅንነት ነው።’ በ1997 የነበሩት 5,599,931 የመንግሥቱ አስፋፊዎች በድምሩ 1,179,735,841 ሰዓታት ስለ ኢየሱስ በመመሥከሩ ሥራ ማሳለፋቸው ይህንኑ የሚያሳይ ነው። እነዚህ አስፋፊዎች ሁሉም “ኢዮናዳቦች” ናቸው ለማለት ይቻላል።
አሁንም በቅንዓት መስበክ
8. የይሖዋ ምሥክሮች ለእውነተኛ አምልኮ እንደሚቀኑ ያሳዩት እንዴት ነው?
8 ኢዩ ሠረገላውን በፍጥነት በመንዳት የሚታወቅ ሰው ነበር። ይህም ተልእኮውን ለመፈጸም ያለውን ቅንዓት የሚያሳይ ነው። (2 ነገሥት 9:20) ታላቁ ኢዩ ኢየሱስ በውስጡ ያለው ቅንዓት ‘እንደበላው’ ተገልጿል። (መዝሙር 69:9) በመሆኑም ዛሬ በሠረገላ ላይ እንዳሉ ተደርገው የተገለጹት እውነተኛ ክርስቲያኖችም ቅንዓታቸው በጉልህ መታየቱ ምንም አያስገርምም። በጉባኤ መካከልም ሆነ በሕዝብ ፊት ‘ቃሉን ይሰብካሉ፣ በጊዜውም አለጊዜውም በጥድፊያ ስሜት ይንቀሳቀሳሉ።’ (2 ጢሞቴዎስ 4:2 NW) በተለይ በ1997 መግቢያ ላይ የመንግሥት አገልግሎታችን የተቻለውን ያህል ብዙ ወንድሞችና እህቶች በረዳት አቅኚነት አገልግሎት እንዲካፈሉ ካበረታታ በኋላ ቅንዓታቸው በጉልህ ታይቷል። እያንዳንዱ አገር የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ረዳት አቅኚዎች የማግኘት ግብ ነበረው። የተሰጠው ምላሽ ምን ይመስላል? በጣም የሚያስገርም ነበር! ብዙዎቹ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ከግባቸው በላይ ረዳት አቅኚዎች አግኝተዋል። ኢኳዶር 4,000 ረዳት አቅኚዎች የማግኘት ግብ አውጥታ በመጋቢት ግን 6,936 ሪፖርት አድርጋለች። ጃፓን በእነዚያ ሦስት ወራት ውስጥ በድምሩ 104,215 ሪፖርት አድርጋለች። በዛምቢያ ግቡ 6,000 የነበረ ቢሆንም በመጋቢት 6,414 ረዳት አቅኚዎች፣ በሚያዝያ 6,532 እንዲሁም በግንቦት 7,695 ሪፖርት አድርገዋል። በምድር ዙሪያ በጠቅላላ የነበረው የረዳትና የዘወትር አቅኚዎች አዲስ ከፍተኛ ቁጥር 1,110,251 ሲሆን ከ1996 የ34.2 በመቶ ጭማሪ ነበረው!
9. የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተጨማሪ ለሰዎች የምሥራቹን ለመናገር በየትኞቹ ሌሎች መስኮችም ይጠቀማሉ?
9 ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ለነበሩት ሽማግሌዎች “በጉባኤም በየቤታችሁም አወራሁላችሁና አስተማርኋችሁ እንጂ፣ ከሚጠቅማችሁ ነገር አንዳች ስንኳ አላስቀረሁባችሁም” ብሏቸዋል። (ሥራ 20:20) ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች የጳውሎስን ምሳሌ በመከተል ምሥራቹን ከቤት ወደ ቤት በቅንዓት ይሰብካሉ። ይሁን እንጂ ሰዎችን በቤታቸው ማግኘት ቀላል ላይሆን ይችላል። በመሆኑም “ታማኝና ልባም ባሪያ” የመንግሥቱ አስፋፊዎች በማንኛውም ሥፍራ ማለትም በሥራ ቦታ፣ መንገድ ላይ፣ በባሕር ዳርቻዎችና፣ በሕዝብ መናፈሻ ቦታዎች የሚገኙ ሰዎችን ሁሉ እንዲያነጋግሩ ያበረታታል። (ማቴዎስ 24:45-47) ይህም ግሩም ውጤት አስገኝቷል።
10, 11. በሁለት አገሮች ውስጥ የሚገኙ አስፋፊዎች ቤታቸው ሊገኙ የማይችሉትን ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በመፈለግ ረገድ ግሩም ተነሳሽነት ያሳዩት እንዴት ነው?
10 በዴንማርክ ኮፐንሃገን የተወሰኑ አስፋፊዎች በቡድን ሆነው ከባቡር ጣቢያ ውጭ በሚገኝ ጎዳና ላይ ይመሠክራሉ። ከጥር እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ውስጥ 4,733 መጽሔቶችን ያበረከቱ ሲሆን አስደሳች ውይይቶችንና ተመላልሶ መጠየቆችን ለማድረግ ችለዋል። በዚያች አገር የሚገኙ በርካታ አስፋፊዎች ሱቆች ውስጥ ያሉ የመጽሔት ደንበኞችን አፍርተዋል። በየሳምንቱ ዓርብ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ለመገበያየት የሚመጡበት ትልቅ ገበያ የሚገኝባት አንዲት ትንሽ ከተማ አለች። በመሆኑም ጉባኤው በገበያ ውስጥ መመሥከር የሚያስችል ቋሚ ፕሮግራም አውጥቷል። በአንድ አካባቢ ደግሞ በተለይ ለትምህርት ቤት መምህራን የሚስማሙ ጽሑፎችን ይዘው ወደ ትምህርት ቤቶቹ ሄደዋል።
11 በሃዋይም እንዲሁ በቤታቸው ሊገኙ የማይችሉትን ሰዎች ለማነጋገር ጥረቶች ተደርገዋል። ልዩ የአገልግሎት ክልሎቹ የሕዝብ ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን (ጎዳናዎች፣ መናፈሻዎች፣ የመኪና ማቆሚያዎችና የአውቶቡስ ፌርማታዎች) የመሃል ከተማ አካባቢዎችን፣ የመገበያያ ቦታዎችን እንዲሁም የአውሮፕላን ማረፊያዎችን፣ በስልክ የሚደረግ ምሥክርነትን፣ የሕዝብ ማመላለሻን (በአውቶቡስ ላይ መስበክ) እንዲሁም የኮሌጅ ግቢዎችን ይጨምራል። በእያንዳንዱ የአገልግሎት ክልል የተመደቡት ምሥክሮች ቁጥር በቂ መሆኑና የተመደቡትም ተገቢውን ሥልጠና ያገኙ አስፋፊዎች በመሆናቸው ትኩረት ተሰጥቶታል። ሌሎች ብዙ አገሮችም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል የተቀናጀ ጥረት እንዳደረጉ ሪፖርት አድርገዋል። ከዚህ የተነሣ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ፈጽሞ የመገኘት አጋጣሚ ያልነበራቸው ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ተገኝተዋል።
ጸንቶ መቆም
12, 13. (ሀ) በ1997 ሰይጣን የይሖዋ ምሥክሮችን ለማጥቃት ምን ዘዴ ተጠቅሟል? (ለ) በአንዲት አገር የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ያልተጠበቀ ውጤት ያስገኘው እንዴት ነው?
12 በ1997 የይሖዋ ምሥክሮች በጥቂት አገሮች ውስጥ በተንኮል የተጠነሰሱ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎች ተሰንዝረውባቸዋል፤ ይህም በእነርሱ ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር ታቅዶ የተደረገ እንደነበር ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ምሥክሮቹ አልተሸማቀቁም! (መዝሙር 112:7, 8) መዝሙራዊው ያቀረበውን ጸሎት አስታውሰዋል:- “ትዕቢተኞች በሐሰት ስሜን ያጠፋሉ፤ እኔ ግን ትእዛዝህን በሙሉ ልቤ እጠብቃለሁ።” (መዝሙር 119:69 የ1980 ትርጉም) ይህ የውሸት ልፈፋ እውነተኛ ክርስቲያኖች ኢየሱስ በትንቢት እንደተናገረው እንደሚጠሉ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (ማቴዎስ 24:9) አንዳንድ ጊዜም ያልተጠበቀ ውጤት አስገኝቷል። በቤልጂየም የሚገኝ አንድ ሰው በአንድ የታወቀ ዕለታዊ ጋዜጣ ላይ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚያንኳስስ ርዕስ ያነብባል። ሰውዬው ጋዜጣው ያሰፈረው የይሖዋ ምሥክሮችን ስም የሚያጠፋ ሐሳብ ስላስደነገጠው በሚቀጥለው እሁድ በአንድ መንግሥት አዳራሽ ውስጥ በተደረገው ስብሰባ ላይ ይገኛል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ዝግጅት አደረገና ፈጣን ለውጥ ማድረጉን ቀጠለ። ከዚያ ቀደም ይህ ሰው የአንድ የወንጀለኞች ቡድን አባል ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱ በአካባቢው ያሉ ሰዎች እስኪያስተውሉት ድረስ በሕይወቱ ላይ ለውጥ እንዲያደርግ ረድቶታል። ያንን የሚነቅፍ ርዕስ የጻፈው ሰው እንዲህ ዓይነት ውጤት ይገኛል ብሎ እንዳላሰበ የተረጋገጠ ነው!
13 በቤልጂየም ያሉ አንዳንድ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ይህን ሐቀኝነት የጎደለው ፕሮፓጋንዳ ተቃውመዋል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር የሚገኙበት ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች ላከናወኑት ነገር ጥልቅ አድናቆት እንዳላቸው ገልጸዋል። ሌላ የሕዝብ ባለ ሥልጣን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “አልፎ አልፎ ከሚነዛው ነቀፋ በተቃራኒ [የይሖዋ ምሥክሮች] ለመንግሥት ተቋማት ቅንጣት ታክል እንኳ ሥጋት የሚፈጥሩ ሰዎች ሆነው አይታዩኝም። ሰላም ወዳድ፣ ትጉህና ባለ ሥልጣናትን የሚያከብሩ ዜጎች ናቸው።” በእርግጥም ሐዋርያው ጴጥሮስ የተናገራቸው ቃላት ጥበብ የሞላባቸው ናቸው:- “ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፣ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፣ በሚጐበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን።”—1 ጴጥሮስ 2:12
የመታሰቢያው በዓል ግሩም በሆነ መንገድ ተከብሯል
14. በ1997 የተከበረውን የመታሰቢያ በዓል በሚመለከት የተገኙት አንዳንድ አስደሳች ሪፖርቶች ምንድን ናቸው?
14 ስለ ክርስቶስ የሚመሠክሩ ሰዎች የሞቱን መታሰቢያ የዓመቱ ትልቅ ክንውን እንደሆነ አድርገው መመልከታቸው ተገቢ ነው። በ1997 መጋቢት 23 ዕለት የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር 14,322,226 ሰዎች ተገኝተው ነበር። ይህም ከ1996 የ1,400,000 ጭማሪ ነበረው። (ሉቃስ 22:14-20) በብዙ አገሮች ውስጥ የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች ቁጥር ከመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር በእጅጉ የሚበልጥ ሆኖ ተገኝቷል፤ ይህም ወደፊት ሊገኝ የሚችለውን ግሩም ጭማሪ የሚያመለክት ነው። ለምሳሌ ያህል በ1997 ሄይቲ 10,621 የደረሰ አዲስ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ስታገኝ በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙት ሰዎች ቁጥር ግን 67,259 ነበር። ከገጽ 18 እስከ 21 ድረስ ያለውን ዓመታዊ ሪፖርት በመመልከት ከአስፋፊዎቻቸው ቁጥር ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ ተሰብሳቢ የነበራቸው አገሮች የትኞቹ እንደሆኑ መመልከት ትችላለህ።
15. በአንዳንድ አገሮች ወንድሞቻችን የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር ከባድ ችግሮችን የተወጡት እንዴት ነው?
15 ለአንዳንዶች በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘት ቀላል አልነበረም። በአልባኒያ በነበረው ሕዝባዊ ዓመፅ የተነሣ ከምሽቱ 1:00 ጀምሮ የሰዓት ዕላፊ ገደብ ተጥሎ ነበር። በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙት 115 ትናንሽ ቡድኖች በሙሉ የመታሰቢያው በዓል 11:45 ላይ ተጀመረ። ፀሐይዋ የኒሳን 14 መጀመርን በማብሰር በ12:08 ጠለቀች። ምሳሌያዊዎቹን ቂጣና ወይን 12:15 ገደማ ላይ ማዞር ተጀመረ። በአብዛኛዎቹ ቦታዎች በ12:30 የመደምደሚያው ጸሎት ተጸልዮ ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ ከሰዓት ዕላፊው በፊት ወደየቤታቸው እየተጣደፉ ሄዱ። ያም ሆኖ ግን የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች ቁጥር 3,154 ሲሆን ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ግን 1,090 ነበር። በአፍሪካ ውስጥ በምትገኝ አንዲት አገር ከነበረው ዓመፅ የተነሣ ወደ መንግሥት አዳራሹ መሄድ አስቸጋሪ ስለነበር በዓሉ በትናንሽ ቡድኖች የሚከበርበትን ዝግጅት ለማድረግ ሁለት ሽማግሌዎች በአንድ ሌላ ሽማግሌ ቤት ስብሰባ ለማድረግ ወሰኑ። ሁለቱ ሽማግሌዎች ወደዚያ ቤት ለመድረስ አንድ የውኃ መውረጃ ቦይ ተሻግረው መሄድ ነበረባቸው። ሆኖም በአካባቢው ውጊያ ይካሄድ የነበረ ሲሆን አደጋ ጣዮችም ያንን ቦይ ለመሻገር በሚሞክር ሰው ላይ ይተኩሱ ነበር። አንዱ ሽማግሌ ፈጠን ብሎ ያለ ችግር ተሻገረ። ሁለተኛው ግን ሲሻገር ተኩስ ሰማ። ወደ መሬት ተወርውሮ በልቡ እየተሳበ ሲሄድ ጥይት በጭንቅላቱ ላይ እያፏጨ ያልፍ ነበር። የሽማግሌዎቹ ስብሰባ በተሳካ መንገድ በመከናወኑ ለጉባኤው የሚያስፈልጉት ነገሮች ተሟሉ።
“ከሕዝብና ከነገድ . . . ከቋንቋም ሁሉ”
16. ታማኝና ልባም ባሪያ ጥቂት ተናጋሪ ባሏቸው ቋንቋዎች ጭምር ምሥራቹ እንዲሠራጭ የሚያስችል ዝግጅት ያደረገው እንዴት ነው?
16 ሐዋርያው ዮሐንስ “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ” የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች እንደሚመጡ ተናግሯል። (ራእይ 7:9) በመሆኑም የአስተዳደር አካሉ ጽሑፎች በተጨማሪ ብዙ ቋንቋዎች እንዲዘጋጁ አድርጓል። ከእነዚህም መካከል በጣም ርቀው የሚገኙ ጎሳዎች እና ጥቂት የሕዝብ ብዛት ያላቸው ቡድኖች የሚጠቀሙባቸው ቋንቋዎች ይገኙበታል። ለምሳሌ ያህል በሞዛምቢክ ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሕይወት የተባለው ትራክት በአምስት ተጨማሪ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ ወጥቷል። በኒካራጓ በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው ብሮሹር በሚስኪቶ ቋንቋ ተዘጋጅቶ የወጣ ሲሆን የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በዚህ ቋንቋ ጽሑፍ አዘጋጅቶ ሲያወጣ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነው። ብዙ የሚስኪቶ ሕንዳውያን በቋንቋቸው የተዘጋጀ ጽሑፍ በማግኘታቸው እጅግ ተደስተዋል። በ1997 ማኅበሩ በተጨማሪ 25 ቋንቋዎች ጽሑፎች እንዲዘጋጁ ፈቃድ የሰጠ ሲሆን ከአንድ ቢልዮን የሚበልጡ መጽሔቶችንም አትሟል።
17. በኮሪያ የትኛውን የቋንቋ ቡድን መርዳት ተችሏል? የቪዲዮ ክሮችስ ይህን የቋንቋ ቡድን ለመርዳት በእጅጉ እገዛ ያደረጉት እንዴት ነው?
17 በኮሪያ ሌላ የመግባቢያ ቋንቋ ያለውን አንድ ቡድን መርዳት ተችሏል። በ1997 ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሪያ የምልክት ቋንቋ የአውራጃ ስብሰባ ተካሂዷል። በኮሪያ 543 አስፋፊዎች ያሏቸው በምልክት ቋንቋ የሚጠቀሙ 15 ጉባኤዎች ያሉ ሲሆን በስብሰባው ላይ 1,174 ተገኝተው 21 ተጠምቀዋል። በቃል የሚነገረውን ወይም በጽሑፍ የሰፈረውን ቃል በቀላሉ መረዳት የማይችሉ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ለመርዳት ሲባል በ13 የተለያዩ የምልክት ቋንቋዎች ጽሑፎች በቪድዮ ካሴት እየተዘጋጁ ነው። በዚህ መንገድ መስማት የተሳናቸው ሰዎች የምሥራቹን “እንዲያነቡ” ብሎም እንዲያጠኑ መርዳት ተችሏል፤ ይህም ግሩም ውጤት አስገኝቷል። ቀደም ሲል ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ መስማት የተሳነው አንድ ሰው ለጥምቀት እስኪደርስ ድረስ እስከ አምስት ዓመት ይወስድበት ነበር። አሁን ግን በአሜሪካ የምልክት ቋንቋ የተዘጋጁ ብዙ የቪድዮ ክሮች በመኖራቸው አንዳንዶቹ መስማት የተሳናቸው ሰዎች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደዚህ ደረጃ መድረስ ችለዋል።
‘በሠረገላው ውስጥ መቆየት’
18. ኢዩ ከኢዮናዳብ ጋር ከተገናኘ በኋላ ምን ማድረጉን ተያያዘው?
18 ጥንት በ905 ከዘአበ ኢዮናዳብ ከጎኑ ከተሰለፈ በኋላ ኢዩ የሐሰት አምልኮን ማውደሙን ተያያዘው። ለበኣል አምላኪዎች በሙሉ “ለበኣል ዋና ጉባኤ ቀድሱ” የሚል ግብዣ አቀረበ። ከዚያም አንድም የበኣል አምላኪ አለመቅረቱን ለማረጋገጥ በምድሪቱ ሁሉ መልእክት ላከ። የተሰበሰበው ብዙ ሕዝብ ወደዚህ የሐሰት አምላክ ታላቅ ቤተ መቅደስ ሲጎርፍ የይሖዋ አምላኪ የሆነ ሰው በመሐል እንዳይገኝ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደረገ። በመጨረሻም ኢዩና ሠራዊቱ የበኣልን አምላኪዎች እንደ ቅጠል አረገፏቸው። በዚህ መንገድ “ኢዩ በኣልን ከእስራኤል አጠፋ።”—2 ነገሥት 10:20-28
19. በሰው ዘር ፊት ከተዘረጋው ሁኔታ አንጻር ምን ዓይነት መንፈስ ማሳየት ይገባናል? በምን ሥራስ በትጋት ልንጠመድ ይገባል?
19 ዛሬ በሁሉም የሐሰት ሃይማኖቶች ላይ የሚወሰደው የመጨረሻ ፍርድ ቀርቧል። ክርስቲያኖች በመላእክት መሪነት ለሁሉም የሰው ዘር ምሥራቹን እያወጁና ፈሪሃ አምላክ በመኮትኮት ከሐሰት ሃይማኖት እንዲለዩ እያበረታቱ ነው። (ራእይ 14:6-8፤ 18:2, 4) ቅን ሰዎች ይሖዋ በሾመው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚተዳደረው መንግሥት ራሳቸውን እንዲያስገዙ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። (ራእይ 12:10) በዚህ አስደሳች ጊዜ ከእውነተኛው አምልኮ ጎን በመሰለፍ የምናሳየው ቅንዓት እንዲዳከም ልንፈቅድ አይገባም።
20. በ1998 የአገልግሎት ዓመት ምን ለማድረግ ቆርጣችኋል?
20 ንጉሥ ዳዊት ከባድ ተጽዕኖ በደረሰበት ጊዜ እንዲህ ሲል ጸልዮአል:- “ልቤ ጨካኝ [“ጽኑ፣” NW] ነው፣ አቤቱ፣ ልቤ ጨካኝ [“ጽኑ፣” NW] ነው። እቀኛለሁ፣ እዘምራለሁ። አቤቱ፣ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ።” (መዝሙር 57:7, 9) እኛም ጽኑ እንሁን። በ1997 የአገልግሎት ዓመት ብዙ ችግሮች የነበሩ ቢሆንም ለይሖዋ አምላክ ክብር ከፍተኛ የውዳሴ ድምፅ ሲያስተጋባ ቆይቷል። በያዝነው የአገልግሎት ዓመትም ተመሳሳይ አልፎ ተርፎም ከዚያ የላቀ የውዳሴ ድምፅ እንዲሰማ እንመኛለን። ሰይጣን እኛን ተስፋ ለማስቆረጥ ወይም ለመቃወም ምንም ያድርግ ምን ይሖዋን እናወድስ። በዚህ መንገድ ልባችን ከታላቁ ኢዩ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በቅንነት እንደሆነ ከማሳየታችንም ሌላ እንደሚከተለው ለሚለው በመንፈስ አነሳሽነት የተሰጠ ምክር በሙሉ ነፍሳችን ምላሽ እንሰጣለን:- “ጻድቃን ሆይ፣ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ፤ ልባችሁም የቀና ሁላችሁ እልል በሉ።”—መዝሙር 32:11
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ በ905 ከዘአበ በእስራኤል ምን ለውጦች ተከናውነዋል?
◻ ዘመናዊው ኢዩ ማን ነው? “እጅግ ብዙ ሰዎች” ‘ልባቸው ከእርሱ ልብ ጋር በቅንነት’ እንደሆነ ያሳዩት እንዴት ነው?
◻ ከዓመታዊው ሪፖርት ላይ በ1997 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩትን ቅንዓት የሚያረጋግጥ ምን አኃዛዊ ማስረጃ ማግኘት ይቻላል?
◻ ሰይጣን ምንም ያምጣ ምን በ1998 የአገልግሎት ዓመት ምን ዓይነት መንፈስ እናሳያለን?
[Chart on page 18-21]
የ1997 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ሪፖርት
(መጽሔቱን ተመልከት)
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኘው ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ወደፊት ግሩም ጭማሪ ሊገኝ እንደሚችል የሚያሳይ ነው
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢዮናዳብ ኢዩን እንደደገፈው ሁሉ ‘እጅግ ብዙ ሰዎችም’ ዛሬ ታላቁን ኢዩ ኢየሱስ ክርስቶስንና ቅቡዓን ወንድሞቹን ይደግፋሉ