እርስ በርስ መተማመን እንዲሰፍን ማድረግ ይቻላል!
በጊዜያችን እርስ በርስ መተማመን መጥፋቱ “በመጨረሻው ቀን” እንደምንኖር የሚያሳይ ምልክት ቢሆንም በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊትም ይኸው ችግር ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በመጀመሪያ የተከሰተው ይሆናል ተብሎ በማይጠረጠርበት ቦታ ይኸውም በገነት ውስጥ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ቦታውን በሚመለከት እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው። እግዚአብሔር አምላክም ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፣ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በገነትም መካከል የሕይወትን ዛፍ፣ መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውንም ዛፍ አበቀለ።”—ዘፍጥረት 2:8, 9
ቀጣዮቹ ቁጥሮች ይህ ነገር በዛሬው ዘመን ካለው እርስ በርስ አለመተማመን ጋር እንዴት እንደሚያያዝ ለመረዳት ያስችሉናል። እንዲህ እናነባለን:- “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው:- ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።” (ዘፍጥረት 2:16, 17) አዳም፣ ይሖዋ የነገረውን ነገር የሚጠራጠርበት ምክንያት ነበረውን?
ቀጥሎ እንዲህ የሚል እናነባለን:- “እባብም እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠረው ከምድር አውሬ ሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነበረ። ሴቲቱንም:- በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት። ሴቲቱም ለእባቡ አለችው:- በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፣ እግዚአብሔር አለ:- እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም። እባብም ለሴቲቱ አላት:- ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ። ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፣ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፣ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።”—ዘፍጥረት 3:1-6
አዳምና ሔዋን አምላክ የሰጣቸውን ግልጽ ማስጠንቀቂያ ችላ በማለታቸው በይሖዋ እንደማይተማመኑ አሳይተዋል። በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን ያነጋገራትን የአምላክ ጠላት የሆነውን የሰይጣንን ባሕርይ አንጸባረቁ። ሰይጣን በይሖዋ አገዛዝ ሳይታመን ቀርቷል። በይሖዋ ሳይታመን በመቅረቱ እንዲሁም ኩሩና የሥልጣን ምኞት ያበቀለ ልብ ስለነበረው በአምላክ ላይ ዓመፀ፤ ሰዎችም እርሱን እንዲከተሉት አደረገ። አምላክ የሚታመን አይደለም ብለው እንዲያስቡ ተጽእኖ አደረገባቸው።
ውጤቱስ ምን ሆነ? የሻከረ ግንኙነት
ሌሎችን ማመን የሚከብዳቸው ሰዎች ከሌሎች ጋር ያላቸውን ጓደኝነት አጽንተው መያዝ እንደሚያቅታቸው ሳታስተውል አትቀርም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖር የነበረው የላቲን ደራሲ ፑብሊሊዩስ ሲይሩስ “ብቸኛው የጓደኝነት ማሰሪያ መተማመን ነው” ሲል ጽፏል። አዳምና ሔዋን የዓመፅ ተግባር በመፈጸም በአምላክ እንደማይታመኑ አሳይተዋል። በመሆኑም አምላክ እነሱን የሚያምንበት ምንም ምክንያት አልነበረውም። መተማመን በመጥፋቱ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ወዳጅነት አጡ። በማመፃቸው ምክንያት ይሖዋ ከፈረደባቸው በኋላ ከእነሱ ጋር የተነጋገረበት ጊዜ መኖሩን የሚገልጽ ምንም ዘገባ የለም።
በአዳምና በሔዋን መካከል የነበረውም ግንኙነት ሻክሯል። ይሖዋ “በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፣ እርሱም ገዥሽ ይሆናል” ሲል አስጠንቅቋታል። (ዘፍጥረት 3:16፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ዘ ጀሩሳሌም ባይብል “እርሱም አዛዥሽ ይሆናል” ይላል። የአምላክ የመጀመሪያ እቅድ አዳም የራስነት ሥልጣኑን ፍቅራዊ በሆነ መንገድ እንዲጠቀምበት ቢሆንም አዳም አለቃዋና አዛዥዋ ሆነ።
ኃጢአት ከሠሩ በኋላ አዳም ስህተቱን በሚስቱ ላይ ለማላከክ ሞከረ። በእሱ አመለካከት ፍጹም ከሆነች ገነት ተባርረው ወደ አፈር እስኪመለሱ ድረስ ባልለማው ምድር ላይ ፍጽምና በጎደለው ሁኔታ ሥር እንደ ባሪያ እንዲኖሩ የተፈረደባቸው በእርሷ ምክንያት ነበር። (ዘፍጥረት 3:17-19) ይህ በሁለቱ መካከል መቃቃር እንዲፈጠር መንስኤ እንደሚሆን ልንገምት እንችላለን። አዳም ከአሁን በኋላ ሔዋን የምትለውን ፈጽሞ አልሰማም በማለት በቁጣ ተናግሮ ይሆናል። ምናልባትም ‘ከአሁን በኋላ አለቃሽ እኔ ነኝ!’ ማለቱ ተገቢ እንደሚሆን ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ሔዋን፣ አዳም የቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን ያለውን ሚና በሚገባ ለመወጣት አለመቻሉን መመልከቷ በእሱ ላይ ያላትን እምነት እንድታጣ አድርጓት ይሆናል። በዚያም ሆነ በዚህ ሰዎች በአምላክ ሳይተማመኑ በመቅረታቸው ከእሱ ጋር ያላቸውን ዝምድና ከማጣታቸውም በላይ እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት አደጋ ላይ ወድቋል።
ማንን ማመን እንችላለን?
የአዳምና የሔዋን ምሳሌ እንደሚያሳየው የምንተማመንበት ሁሉም ሰው አይሆንም። በማን መተማመን እንደሚቻልና በማን መተማመን እንደማይቻል እንዴት እናውቃለን?
መዝሙር 146:3 “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ። ነፍሱ ትወጣለች ወደ መሬቱም ይመለሳል” ሲል ይመክረናል። እንዲሁም በኤርምያስ 17:5-7 ላይ እንዲህ የሚል ቃል እናነባለን:- “በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው።” በሌላ በኩል ግን “በእግዚአብሔር የታመነ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው።”
እርግጥ ነው በሰዎች መተማመን ሁልጊዜ ስህተት ነው ማለት አይደለም። እነዚህ ጥቅሶች በአምላክ መተማመን ምን ጊዜም ትክክል መሆኑንና በሰዎች መተማመን ግን አንዳንድ ጊዜ ወደ ውድቀት ሊመራ እንደሚችል የሚጠቁሙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል እንደ ማዳን እንዲሁም ሰላምንና ደኅንነትን ማስፈን የመሳሰሉትን አምላክ ብቻ ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን ነገሮች ከሰዎች ለማግኘት የሚጠብቁ ሁሉ ያሰቡት ባለመሙላቱ ሐዘን ይገጥማቸዋል።—መዝሙር 46:9፤ 1 ተሰሎንቄ 5:3
ሰዎችና ሰብዓዊ ተቋሞች ትምክህት ሊጣልባቸው የሚገባው ከአምላክ ዓላማዎች ጋር ተስማምተው የሚሠሩና አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሚያንጸባርቁ ከሆነ ብቻ ነው። በመሆኑም ሌሎች እንዲተማመኑብን ከፈለግን እውነት በመናገር ሐቀኞችና እምነት የሚጣልብን ሆነን መገኘት አለብን። (ምሳሌ 12:19፤ ኤፌሶን 4:25፤ ዕብራውያን 13:18) ሌሎች እኛን የሚያምኑና በዚህም አንዳችን ለሌላው የብርታትና የማበረታቻ ምንጭ የምንሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተን የምንኖር ከሆነ ብቻ ነው።
እርስ በርስ መተማመን መልሶ እንዲሰፍን ማድረግ
የይሖዋ ምሥክሮች በአምላክ ለመታመንም ሆነ ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ ለማበረታታት የሚያበቃ ጠንካራ መሠረት አላቸው። ይሖዋ ምን ጊዜም የተናገረውን ሁሉ እንደሚያደርግ ትምክህት ሊጣልበት የሚችል ታማኝ አምላክ ነው። ምክንያቱም ‘እርሱ ሊዋሽ አይችልም።’ የፍቅር አምላክ በሆነው በይሖዋ ብንተማመን እርሱ አያሳፍረንም።—ዕብራውያን 6:18፤ መዝሙር 94:14፤ ኢሳይያስ 46:9-11፤ 1 ዮሐንስ 4:8
በይሖዋ በመታመን አንድነት ያገኙና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ተከትለው የሚኖሩ ሰዎች አንዳቸው በሌላው ላይም ለመታመን የሚያስችል ጠንካራ ዝንባሌ አላቸው። እርስ በርስ መተማመን በጠፋበት ዓለም ውስጥ እምነት የሚጣልባቸው ሰዎች ማግኘት እንዴት ያስደስታል! ሁሉም ሰው የሚናገረውን ወይም የሚያደርገውን ነገር ሙሉ በሙሉ ማመን ብንችል ኖሮ ዓለማችን ምን ዓይነት የተለየ መልክ ይኖራት እንደነበር እስቲ አስበው! አምላክ እንደሚመጣ በተናገረለት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖረው ሁኔታ ይህን የሚመስል ነው። ከዚያ በኋላ እርስ በርስ መተማመን አይጠፋም!
በዚህ ጊዜ መኖር ትፈልጋለህ? ለመኖር የምትፈልግ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ ለሕይወት ያወጣቸውን መስፈርቶች በሚመለከት ተጨማሪ ትምህርት በማግኘት በአምላክና በተስፋዎቹ ላይ ያለህን እምነት እንድታጠነክር ይጋብዙሃል። መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት አምላክ እንዳለ፣ ለሰው ልጅ ደኅንነት እንደሚያስብና በቅርቡም በመንግሥቱ አማካኝነት የዓለምን ችግሮች ለማስወገድ እርምጃ እንደሚወስድ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ማግኘት ይቻላል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአምላክና በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ትምክህት ማሳደር ችለዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ለሕዝብ የሚሰጡትን ነፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ኮርስ እንዴት እንደሚያካሂዱ በደስታ ሊያሳዩህ ይችላሉ። ወይም ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት ከፈለግህ ወደዚህ መጽሔት አዘጋጆች ጻፍ።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በአምላክ መታመን አለመቻል ከሰዎች ጋር ያሉን ግንኙነቶች እንዲሻክሩ ያደርጋል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ሰዎች ትምክህት ሊጣልባቸው የሚገባው ከአምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተው የሚመላለሱ ከሆነ ብቻ ነው