የቃል ሕግ በጽሑፍ የሰፈረው ለምን ነበር?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን የኢየሱስን መሲሕነት ሳይቀበሉ የቀሩት ለምንድን ነው? አንድ የዓይን ምሥክር እንዲህ ሲል ዘግቧል:- “[ኢየሱስ] ወደ መቅደስም ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ወደ እርሱ ቀረቡና:- በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት።” (ማቴዎስ 21:23) በእነርሱ አመለካከት ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ለአይሁዳውያኑ ብሔር ቶራህን (ሕጉን) ሰጥቷል፤ ይህም ሕግ ለአንዳንዶች ሥልጣን ሰጥቷቸው ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ሥልጣን ነበረው?
ኢየሱስ ለቶራህም ሆነ በዚያ በኩል እውነተኛ ሥልጣን ላገኙ ሰዎች ጥልቅ አክብሮት አሳይቷል። (ማቴዎስ 5:17–20፤ ሉቃስ 5:14፤ 17:14) ይሁን እንጂ የአምላክን ትእዛዛት የሚተላለፉትን ሰዎች በተደጋጋሚ ጊዜ አውግዟል። (ማቴዎስ 15:3–9፤ 23:2–28) እንዲህ ያሉት ሰዎች የቃል ሕግ በመባል የሚታወቀውን ወግ የሚከተሉ ነበሩ። ኢየሱስ የዚህን ወግ ሥልጣን አልተቀበለም። ከዚህም የተነሣ ብዙዎች እርሱ መሲሕ መሆኑን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆኑም። የአምላክ ድጋፍ የሚኖረው ከእነርሱ መካከል ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ያወጡትን ወግ የሚደግፍ ሰው ብቻ ነው የሚል እምነት ነበራቸው።
ይህ የቃል ሕግ የመነጨው ከየት ነው? አይሁዳውያን ይህ ሕግ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሚገኘው በጽሑፍ የሰፈረ ሕግ ጋር እኩል ሥልጣን እንዳለው አድርገው እንዲመለከቱት ያደረጋቸው ምንድን ነው? በቃል የሚተላለፍ ወግ ብቻ እንዲሆን የታሰበ ከነበረ በኋላ በጽሑፍ የሰፈረውስ ለምንድን ነው?
ወጉ የመነጨው ከየት ነበር?
እስራኤላውያን በ1513 ከዘአበ በሲና ተራራ ከይሖዋ አምላክ ጋር ቃል ኪዳን አደረጉ። በሙሴ አማካኝነት የቃል ኪዳኑን ሕግ ተቀብለዋል። (ዘጸአት 24:3) እነዚህን መመሪያዎች መከተላቸው ‘አምላካቸው ይሖዋ ቅዱስ እንደሆነ እነርሱም ቅዱስ መሆናቸውን እንዲያሳዩ’ የሚያስችላቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 11:44) በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር ለይሖዋ የሚቀርበው አምልኮ ለዚሁ ተብለው በተመደቡ ካህናት አማካኝነት መሥዋዕት ማቅረብን ይጨምር ነበር። አንድ የአምልኮ ማዕከልም መኖር ነበረበት። ከጊዜ በኋላ በኢየሩሳሌም ያለው ቤተ መቅደስ ማዕከል ሆኖ አገልግሏል።—ዘዳግም 12:5–7፤ 2 ዜና መዋዕል 6:4–6
የሙሴ ሕግ እስራኤላውያን በብሔር ደረጃ ለይሖዋ አምልኮ የሚያቀርቡበትን አጠቃላይ መዋቅር አስገኝቷል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮች ተተንትነው አልተቀመጡም። ለምሳሌ ያህል ሕጉ በሰንበት መሥራትን ይከለክል ነበር እንጂ በሥራና በሌሎች እንቅስቃሴዎች መካከል ስላለው ልዩነት አይተነትንም።—ዘጸአት 20:10
ይሖዋ እንደዚያ ማድረጉን አስፈላጊ ሆኖ ቢያገኘው ኖሮ እያንዳንዱን ሊነሣ የሚችል ጥያቄ የሚዳስስ ዝርዝር መመሪያ ሊያወጣ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ሰዎችን የፈጠራቸው ሕሊና ሰጥቶና ከሕጉ ሳይወጡ በተወሰነ መጠን ነፃነት ኖሯቸው በራሳቸው ተነሳሽነት እንዲያገለግሉት አድርጎ ነው። ሕጉ ፍርድ ነክ ጉዳዮች በካህናቱ፣ በሌዋውያኑና በዳኞች የሚታዩበትን ዝግጅት አድርጎ ነበር። (ዘዳግም 17:8–11) የሚታዩት የፍርድ ጉዳዮች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ አንዳንድ ደንቦች ወጥተው የነበረ ሲሆን እነዚህም ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገሩ እንደሄዱ አያጠያይቅም። በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ የክህነት ሥራዎች የሚከናወኑበት መንገድም ከአባት ወደ ልጅ እየተላለፈ የሚሄድ ነበር። የብሔሩ የጋራ የሕይወት ተሞክሮ እየሰፋ በሄደ ቁጥር ብዙ ወጎችም እንደዚያው ተጨምረዋል።
ይሁን እንጂ ለሙሴ በጽሑፍ የተሰጠው ሕግ የእስራኤላውያን አምልኮ እምብርት ሆኖ ቀጥሏል። ዘጸአት 24:3, 4 እንዲህ ይላል:- “ሙሴም መጣ ለሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃሎች ሁሉ ሥርዓቱንም ሁሉ ነገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ድምፅ:- እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ። ሙሴም የእግዚአብሔርን ቃሎች ጻፈ።” አምላክ ከእስራኤላውያን ጋር የገባው ቃል ኪዳን የተመካው እነዚህን በጽሑፍ የሰፈሩ ትእዛዛት በመጠበቃቸው ላይ ነበር። (ዘጸአት 34:27 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እንዲያውም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አንድም ቦታ ስለ ቃል ሕግ ተጠቅሶ አናገኝም።
“ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?”
የሙሴ ሕግ ሃይማኖታዊ ሥልጣንንና የማስተማርን ሥራ በመጀመሪያ ደረጃ የሰጠው ለካህናት ማለትም ለአሮን ልጆች መሆኑ ግልጽ ነው። (ዘሌዋውያን 10:8-11፤ ዘዳግም 24:8፤ 2 ዜና መዋዕል 26:16–20፤ ሚልክያስ 2:7) ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናት አንዳንድ ካህናት እምነት የሚያጎድሉና ብልሹ ሆነዋል። (1 ሳሙኤል 2:12–17, 22–29፤ ኤርምያስ 5:31፤ ሚልክያስ 2:8, 9) በግሪክ ቁጥጥር ሥር በነበሩበት ጊዜም ብዙ ካህናት ሃይማኖታዊ አቋማቸውን አላልተዋል። በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ደግሞ የካህናቱ ቡድን አመኔታ እንዲያጣ ያደረገው አዲሱ የአይሁድ እምነት ቡድን አባላት የሆኑት ፈሪሳውያን ሌላውም ሰው ጭምር እንደ ካህናት ራሱን ቅዱስ አድርጎ ሊቆጥር የሚችልባቸውን ወጎች ማዋቀር ጀመሩ። ወጎቹ የብዙዎችን ቀልብ ስበው የነበረ ቢሆንም ተቀባይነት የሌላቸው የሕጉ ጭማሪ ናቸው።—ዘዳግም 4:2፤ 12:32 (13:1 በአይሁዳውያኑ እትሞች)
ፈሪሳውያን የሕጉ አዲስ ሊቃውንት ሆነው ብቅ አሉና ካህናቱ ሊሠሩት አልቻሉም ብለው ያሰቡትን ሥራ መሥራት ጀመሩ። የሙሴ ሕግ እንዲህ ያለ ሥልጣን ስለማይሰጣቸው የፈለጉትን ነገር በስውር በመጥቀስ እንዲሁም የእነርሱን አመለካከት ይደግፋሉ ያሏቸውን ሌሎች መንገዶች በመጠቀም ለቅዱሳን ጽሑፎች ትርጓሜ የሚሰጡበትን አዲስ ዘዴ ፈጠሩ።a የእነዚህ ወጎች ግንባር ቀደም ተንከባካቢዎችና አራማጆች እነርሱ እንደመሆናቸው መጠን በእስራኤል ውስጥ አዲስ የሥልጣን መሠረት ጥለዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ላይ ፈሪሳውያን በአይሁድ እምነት ውስጥ ጠንካራ ተደማጭነት ያላቸው ወገኖች ሆነው ነበር።
ፈሪሳውያኑ የቃል ወጎቻቸውን ሲያሰባስቡና በአብዛኛው የእነርሱ ፈጠራ የሆነና ጥቂት ቅዱስ ጽሑፋዊ አንድምታ ብቻ ያለው ነገር ለመፍጠር ሲጥሩ ለሥራቸው ተጨማሪ ሥልጣን ማግኘት እንዳለባቸው ተሰማቸው። የእነዚህን ወጎች አመጣጥ በተመለከተ አዲስ ንድፈ ሐሳብ ብቅ አለ። ረቢዎች እንደሚከተለው ብለው ማስተማር ጀመሩ:- “ሙሴ ቶራህን በሲና ተቀብሎ ለኢያሱ አስተላለፈው፣ ኢያሱም ለሽማግሌዎች፣ ሽማግሌዎችም ለነቢያት። ነቢያትም እንዲሁ በታላቁ ጉባኤ ላሉ ወንዶች ሰጡት።”—አቮት 1:1, ሚሽና
ረቢዎች ‘ሙሴ ቶራህን ተቀበለ’ ሲሉ በጽሑፍ የሰፈረውን ሕግ ብቻ ሳይሆን የቃል ወጎቻቸውንም በሙሉ ማለታቸው ነበር። እነዚህን በሰዎች የተፈጠሩና እየዳበሩ የሄዱ ወጎቻቸውን ሙሴ በሲና ከአምላክ የተቀበላቸው ናቸው ይሉ ነበር። እንዲሁም አምላክ የሕጉን ክፍተት የመሙላቱን ሥራ ለሰዎች አልተወውም ይልቁንም በጽሑፍ የሰፈረው ሕግ ምንም የማይናገርባቸውን ጉዳዮች በቃሉ ግልጽ አድርጓል ብለው ያስተምሩ ነበር። እንደ እነርሱ አባባል ከሆነ ሙሴ ይህንን የቃል ሕግ ያስተላለፈው ከአባት ወደ ልጅ እንጂ በካህናት ወይም በሌሎች መሪዎች በኩል አልነበረም። ፈሪሳውያን ራሳቸው የዚህ “የማይበጠስ” የሥልጣን ሰንሰለት ወራሾች የመሆን መብት እንዳላቸው ይናገሩ ነበር።
ቀውስ ውስጥ የገባው ሕግ—አዲስ መፍትሔ
ከአምላክ ያገኘውን ሥልጣን በሚመለከት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ክርክር ያስነሱበት ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ እንደሚጠፋ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 23:37–24:2) ሮማውያን ቤተ መቅደሱን በ70 እዘአ ካጠፉ በኋላ መሥዋዕት ማቅረብንና የክህነት አገልግሎትን የሚጠይቀው የሙሴ ሕግ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም። አምላክ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት አዲስ ቃል ኪዳን አቋቁሞ ነበር። (ሉቃስ 22:20) የሙሴ የሕግ ቃል ኪዳን ወደ ፍጻሜው መጥቶ ነበር።—ዕብራውያን 8:7–13
ፈሪሳውያኑ እነዚህ ክንውኖች ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች መሆናቸውን አምነው ከመቀበል ይልቅ ሌላ መፍትሔ ፈለጉ። ቀደም ብሎም ቢሆን አብዛኛውን የክህነቱን ሥልጣን አላግባብ ይዘው ነበር። ቤተ መቅደሱ ሲጠፋ ደግሞ ሌላም ነገር አድርገዋል። በያቭኔህ የሚገኘው የረቢዎች የትምህርት ተቋም፣ መልሶ የተደራጀው ሳንሄድሪን ማለትም የአይሁዳውያን ከፍተኛ ሸንጎ ማዕከል ሆነ። በዮሃናን ቤን ዛኪ እንዲሁም በገማልያል ዳግማዊ አመራር የአይሁድ እምነት በያቭኔህ ሙሉ በሙሉ በድጋሚ ተመሠረተ። በቤተ መቅደስ ውስጥ በካህናቱ የበላይነት ይከናወን የነበረው አምልኮ በረቢዎች በሚካሄደው የምኩራብ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተተካ። መሥዋዕቶቹ በጸሎቶች በተለይም በሥርየት ቀን በሚቀርቡት ጸሎቶች ተተኩ። ፈሪሳውያኑ ለሙሴ በሲና የተሰጠው የቃል ሕግ እነዚህን ሁሉ ነገሮች አስቀድሞ ግምት ውስጥ በማስገባት ይህን ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።
የረቢዎች የትምህርት ተቋማት ስማቸው ይበልጥ እየገነነ ሄደ። የሥርዓተ ትምህርታቸው ዋነኛ ክፍል መጠነ ሰፊ ውይይት፣ ሽምደዳና የቃልን ሕግ በተግባር ማዋል ነበር። ቀደም ሲል የቃል ሕጉ መሠረት ከቅዱሳን ጽሑፎች ትርጓሜ ማለትም ከሚድራሽ ጋር የተሳሰረ ነበር። አሁን ግን በየጊዜው በቁጥር እየጨመሩና እየተከማቹ የሚሄዱትን የቃል ሕግጋት ለብቻቸው በትምህርት መልክ መስጠትና ማደራጀት ተጀመረ። እያንዳንዱ የቃል ሕግ ተጨምቆ ለማስታወስ በሚያስችል መንገድ በአጭሩ ብዙውን ጊዜ ለሙዚቃ በሚመች መልኩ እንዲዘጋጅ ይደረግ ነበር።
የቃል ሕጉን በጽሑፍ ማስፈር ለምን አስፈለገ?
የረቢዎች የትምህርት ተቋማት መበራከትና የሚፈጥሯቸው ሕጎች ቁጥር መጨመር አዲስ ችግር ፈጠረ። የረቢ ምሁር የሆኑት ኤዲን ስታይንሳልትስ እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል:- “እያንዳንዱ አስተማሪ የራሱ የሆነ ዘዴ የነበረው ሲሆን በራሱ መንገድ የራሱን የቃል ሕግ ያረቅቅ ነበር። . . . አንድ ተማሪ የራሱን አስተማሪ ትምህርቶች ማወቁ ብቻ በቂ አልነበረም። ከሌሎች ምሁራን ሥራ ጋርም የመተዋወቅ ግዴታ ነበረበት። . . . ‘የሚያጥለቀልቅ የእውቀት ጎርፍ’ ስለነበር ተማሪዎቹ ብዙ ነገሮችን ሸምድደው እንዲይዙ ይፈለግባቸው ነበር።” ዝብርቅርቅ ባለ የመረጃ ባሕር ውስጥ የተማሪዎቹ አእምሮ ሊፈነዳ ይደርሳል።
በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ በባር ኮክባ የተመራውና በሮማውያን ላይ የተካሄደው የአይሁዳውያን ዓመፅ የረቢ ምሁራን ከፍተኛ ስደት እንዲደርስባቸው አድርጓል። ባር ኮክባን ይደግፍ የነበረውን እውቁን ረቢ አኪባን ጨምሮ ሌሎች ብዙ ግንባር ቀደም ምሁራን ተገደሉ። ረቢዎቹ አዲስ ስደት ቢነሳ የቃል ሕጋቸውን ሕልውና ሙሉ በሙሉ አደጋ ላይ ይጥለዋል ብለው ፈርተው ነበር። ወጎቹ ከመምህሩ ወደ ደቀ መዝሙሩ በቃል ቢተላለፉ የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት የነበራቸው ቢሆንም ሊረሱ ይችላሉ የሚል ስጋት ስላደረባቸው ከተፈጠሩት አዲስ ሁኔታዎች አንጻር የጠቢባኑን ትምህርት ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችል የተደራጀ መዋቅር ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት አጠናከሩ።
ከዚያ በኋላ በነበረውና ከሮም ጋር አንጻራዊ ሰላም ባገኙበት ዘመን የሁለተኛው መቶ ዘመን መጨረሻና የሦስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ግንባር ቀደም ረቢ የነበረው ጁዳ ሃ-ናሲ ብዙ ምሁራንን በመሰብሰብ ብዛት ያላቸውን የቃል ወጎች በስድስት ክፍሎች በማሳተም ያደራጀ ሲሆን እያንዳንዱ ክፍል በትናንሽ ክፍሎች በጠቅላላው ለ63 የተከፋፈለ ነበር። ይህ ሥራ ሚሽና የሚል ስያሜ አግኝቷል። ስለ ሕጉ ቃል የሚያጠኑት ኢፍሬም ረባክ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ሚሽና . . . ቶራህ ራሱ ካልሆነ በስተቀር ሌላ የትኛውም መጽሐፍ ያላገኘውን ዓይነት ተቀባይነትና ሥልጣን አግኝቷል።” መሲሑን አንቀበልም ብለውና ቤተ መቅደሱ ጠፍቶ የነበረ ቢሆንም የቃል ሕጉ ሚሽና በሚል ስያሜ በጽሑፍ ሰፍሮ እንዲጠበቅ በማድረጋቸው የአይሁድ እምነት አዲስ ምዕራፍ ጀምሯል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህን መሰሉ የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጓሜ አሰጣጥ ሚድራሽ በመባል ይታወቃል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙ አይሁዳውያን የኢየሱስን ሥልጣን ለመቀበል አሻፈረን ያሉት ለምን ነበር?