ወጣቶች—የዓለምን መንፈስ ተቋቋሙ
“ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።” —1 ቆሮንቶስ 2:12
1, 2. (ሀ) በዓለም ባሉት ወጣቶችና በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ባሉት ወጣቶች መካከል ምን ልዩነት ይታያል? (ለ) ለአብዛኛዎቹ የይሖዋ ምሥክር ወጣቶች ምን ሞቅ ያለ ምሥጋና ሊቀርብላቸው ይችላል?
“ዛሬ ያለው ወጣት ትውልድ ወኔ የከዳው፣ ተቀባይ ያጣና ዓመፀኛ ሆኗል።” ይህን ያለው ዘ ሰን-ሄራልድ የተባለው የአውስትራሊያ ጋዜጣ ነበር። ጋዜጣው በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “በከባድ ጥፋት ተወንጅለው ፍርድ ቤት የሚቆሙት ወጣቶች ቁጥር [ካለፈው ዓመት] 22 በመቶ እንደጨመረ ከፍርድ ቤት መዛግብት መረዳት ተችሏል። . . . የገዛ ሕይወታቸውን የሚያጠፉት ትናንሽ ልጆች ቁጥር በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ ይታይ ከነበረው በሦስት እጥፍ ጨምሯል። . . . እንዲሁም በተለያየ ትውልድ መካከል ያለው የአስተሳሰብ ልዩነት እየሰፋ ሄዶ እንደ ጥልቅ ገደል ሆኗል። ቁጥራቸው ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የሚሄድ ወጣቶችም በአደገኛ ዕፆችና በአልኮል ሱስ በመጠመድ እንዲሁም ራስን ለጥፋት የሚዳርግ ጎዳና በመከተል መጨረሻው ወደማይታወቅ አዘቅት እየወረዱ ነው።” ይህ በአንድ አገር ብቻ የሚታይ ሁኔታ አይደለም። በዓለም ዙሪያ ወላጆች፣ መምህራንና የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች ወጣቶችን በሚመለከት ምሬታቸውን ሲገልጹ ይደመጣል።
2 ዛሬ ባሉት በአብዛኞቹ ወጣቶችና በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ በሚገኙት የታረሙ ወጣቶች መካከል ያለው ልዩነት እንዴት የሚያስገርም ነው! በጉባኤዎቹ ውስጥ ያሉት ወጣቶች ፍጹም ስለሆኑ አይደለም። እነርሱም ቢሆኑ ‘ከጎልማሳነት ምኞቶች’ ጋር ይታገላሉ። (2 ጢሞቴዎስ 2:22) ይሁን እንጂ በቡድን ደረጃ ሲታይ እነዚህ ወጣቶች ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለማድረግና ለዓለም ተጽእኖ እጃቸውን ላለመስጠት ድፍረት የሚጠይቅ አቋም ወስደዋል። ከሰይጣን ‘መሠሪ ዘዴዎች’ ጋር በሚደረገው ትግል ድል እየተቀዳጃችሁ ያላችሁትን ወጣቶች በሙሉ ከልባችን ልናመሰግናችሁ እንወዳለን። (ኤፌሶን 6:11 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) እኛም እንደ ሐዋርያው ዮሐንስ “ጐበዞች [“ወጣቶች፣” የ1980 ትርጉም] ሆይ፣ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ” እንጽፍላችኋለን ለማለት እንገደዳለን።—1 ዮሐንስ 2:14
3. “መንፈስ” የሚለው ቃል ምን ትርጉም ሊኖረው ይችላል?
3 የሆነ ሆኖ ከክፉው ጋር በምታደርጉት በዚህ ትግል በድል አድራጊነት ለመቀጠል መጽሐፍ ቅዱስ ‘የዓለም መንፈስ’ ብሎ የሚጠራውን ግፊት ለመቋቋም ታጥቃችሁ መነሣት ይኖርባችኋል። (1 ቆሮንቶስ 2:12) አንድ የግሪክኛ መዝገበ ቃላት “መንፈስ” ማለት “በማንኛውም ሰው ነፍስ ውስጥ የሚያድርና ነፍሱን የሚመራ ዝንባሌ ወይም ግፊት” ማለት ሊሆን ይችላል ብሏል። ለምሳሌ ያህል አንድ ቁጡ ሰው ስታዩ ይህ ሰው ጥሩ “መንፈስ” የለውም ትሉ ይሆናል። ‘መንፈሳችሁ፣’ ጠባያችሁ ወይም የአእምሮአችሁ ዝንባሌ በምታደርጉት ምርጫ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል እንዲሁም ድርጊታችሁንና ንግግራችሁን ይቆጣጠራል። የሚያስገርመው ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች የሚያንጸባርቁት የራሳቸው የሆነ “መንፈስ” አላቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለአንድ የክርስቲያኖች ቡድን:- “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን” ሲል ጽፏል። (ፊልሞና 25) ታዲያ ይህ ዓለም የሚያንጸባርቀው መንፈስ ምን ዓይነት ነው? ‘ዓለም በሞላው በክፉው’ በሰይጣን ዲያብሎስ ስለተያዘ የዓለም መንፈስ ፈጽሞ ጤናማ ሊሆን አይችልም። ይችላል እንዴ?—1 ዮሐንስ 5:19
የዓለምን መንፈስ ለይቶ ማወቅ
4, 5. (ሀ) የኤፌሶን ጉባኤ አባላት ወደ ክርስትና ከመምጣታቸው በፊት ምን ዓይነት መንፈስ ተጽእኖ አሳድሮባቸው ነበር? (ለ) ‘የአየሩ ሥልጣን አለቃ’ የተባለው ማን ነው? ‘አየሩስ’ ምንድን ነው?
4 ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፣ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፣ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው [“እንደ አየሩ ሥልጣን፣” NW] አለቃ ፈቃድ፣ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፣ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፣ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቊጣ ልጆች ነበርን።”—ኤፌሶን 2:1-3
5 በኤፌሶን የነበሩት ክርስቲያኖች ክርስትናን ከመማራቸው በፊት ባለማወቅ ‘የአየሩ ሥልጣን አለቃ’ ማለትም የሰይጣን ዲያብሎስ ተከታዮች ሆነው ነበር። ይህ “አየር” ሰይጣንና አጋንንቱ ቃል በቃል የሚኖሩበትን ቦታ የሚያመለክት አይደለም። ጳውሎስ እነዚህን ቃላት በጻፈበት ጊዜ ሰይጣን ዲያብሎስና አጋንንቱ ወደ ሰማይ የመግባት መብታቸውን ገና አልተነጠቁም ነበር። (ከኢዮብ 1:6 እና ከራእይ 12:7-12 ጋር አወዳድር።) “አየር” የሚለው ቃል የሰይጣንን ዓለም የተቆጣጠረውን መንፈስ ወይም አስተሳሰብ የሚያመለክት ነው። (ከራእይ 16:17-21 ጋር አወዳድር።) በዙሪያችን እንዳለው አየር ይህም መንፈስ በሁሉም ስፍራ ይገኛል።
6. ‘የአየሩ ሥልጣን’ ምንድን ነው? በብዙ ወጣቶችስ ላይ የሚሠራው እንዴት ነው?
6 ይሁን እንጂ ‘የአየሩ ሥልጣን’ የተባለው ነገር ምንድን ነው? ‘አየሩ’ በሰዎች ላይ ያለውን ብርቱ ተጽእኖ የሚያመለክት መግለጫ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ ይህ መንፈስ ‘በማይታዘዙት ልጆች ላይ’ እንደሚሠራ ተናግሯል። በመሆኑም የዓለም መንፈስ ያለመታዘዝንና የዓመፀኝነትን መንፈስ የሚዘራ ሲሆን ይህ ሥልጣን የሚንጸባረቅበት አንደኛው መስክ የእኩዮች ተጽእኖ ነው። አንዲት ወጣት የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብላለች:- “ትምህርት ቤት ውስጥ የምታገኙት ሁሉ በትንሹ ዓመፀኛ እንድትሆኑ ያበረታታችኋል። አንድ አጠያያቂ የሆነ ነገር ስታደርጉ ልጆቹ ለእናንተ ያላቸው አክብሮት ይጨምራል።”
የዓለም መንፈስ የሚንጸባረቅባቸው መስኮች
7-9. (ሀ) ዛሬ ባሉት ወጣቶች ዘንድ የዓለም መንፈስ ከሚንጸባረቅባቸው መንገዶች መካከል አንዳንዶቹን ጥቀስ። (ለ) ከእነዚህ መካከል በአካባቢያችሁ ያስተዋላችሁት ነገር አለ?
7 ዛሬ ባሉት ወጣቶች ዘንድ ከሚታዩት የዓለም መንፈስ የሚንጸባረቅባቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? እምነት ማጉደልና ዓመፀኝነት ይገኙበታል። የአንድ መጽሔት ዘገባ እንዳለው ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ አንድ ዓመት ከቀራቸውና ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ከ70 በመቶ የሚበልጡት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳሉ የማጭበርበር ድርጊት ፈጽመዋል። ቡዋልት፣ ሽሙጥና የብልግና ንግግሮች በእጅጉ ተስፋፍተዋል። እርግጥ ኢዮብና ሐዋርያው ጳውሎስም የጽድቅ ቁጣቸውን ለመግለጽ ዛሬ አንዳንዶች እንደ ማሽሟጠጥ ሊቆጥሩት የሚችሉትን ነገር ተናግረዋል። (ኢዮብ 12:2፤ 2 ቆሮንቶስ 12:13) ይሁን እንጂ ዛሬ ከብዙ ወጣቶች አፍ የሚሰማው የሽሙጥ ንግግር ከስድብ ተለይቶ አይታይም።
8 ከልክ ያለፈ መዝናኛም እንዲሁ ሌላው የዓለም መንፈስ የሚንጸባረቅበት መስክ ነው። የወጣቶች የምሽት ዳንስ ቤቶችa እና አስረሽ ምችው የሚታይባቸው ሌሎች የጭፈራ ቦታዎችም በወጣቶች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ሆነዋል። በአለባበስና በፀጉር አበጣጠር ረገድ ቅጥ የለሽ ሆኖ መታየትም እንዲሁ በእጅጉ ተስፋፍቷል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ወጣቶች ከተንዘራፈፉት የራፕ አቀንቃኝ ልብሶች አንስቶ ሰውነትን እንደ መብሳት እስካሉት ድረስ ያሉትን የዓለም የዓመፀኝነት መንፈስ የሚንጸባረቅባቸው አስደንጋጭ ፋሽኖች ይከተላሉ። (ከሮሜ 6:16 ጋር አወዳድር።) ሌላው የዓለም መንፈስ የሚንጸባረቅበት መስክ ደግሞ ቁሳዊ ነገሮችን ለማግኘት ከልክ በላይ መጨነቅ ነው። አንድ የማስተማሪያ መጽሔት እንዳለው ከሆነ “የንግድ ሰዎች ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ዘዴዎችን በመጠቀምና በተለያዩ የምርት ውጤቶች ወጣቶችን ከየአቅጣጫው እያደናገሯቸው ነው።” በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያሉ ወጣቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ 360,000 ማስታወቂያዎችን ይመለከታሉ። እኩዮቻችሁም እንድትገዙ ተጽዕኖ ያሳድሩባችሁ ይሆናል። አንዲት የ14 ዓመት ልጃገረድ “‘ሹራብሽ፣ ጃኬትሽ ወይም ያደረግሽው ጂንስ የት የተሠራ ነው’ ብሎ የማይጠይቅ ሰው የለም” ብላለች።
9 ሰይጣን ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንስቶ ሰዎችን ንጹሕ ላልሆኑ ድርጊቶች ለማነሳሳት ጤናማ ያልሆነ ሙዚቃን እንደ መሣሪያ አድርጎ ሲጠቀምበት ቆይቷል። (ከዘጸአት 32:17-19 ጋር አወዳድር፤ መዝሙር 69:12 የ1980 ትርጉም፤ ኢሳይያስ 23:16) ከዚህ አንጻር ስለወሲብ በግልጽም ይሁን በስውር የሚናገር ግጥምና ወራዳ ቃላት ያሉት እንዲሁም ድለቃ የበዛበትና ስሜት የሚያነሳሳ ሙዚቃ መስፋፋቱ ምንም አያስገርመንም። ይሁንና ሌላው የዚህ ዓለም ቆሻሻ መንፈስ መግለጫ የጾታ ብልግና ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል:- “በአሥራዎቹ ዕድሜ ላሉት ለብዙዎቹ ወጣቶች የጾታ ግንኙነት ተቀባይነት ለማግኘት ሲሉ የሚያደርጉት ነገር ሆኗል። . . . ከሁለት ሦስተኛ የሚበልጡት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎች የጾታ ግንኙነት ፈጽመዋል።” ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ላይ የወጣ አንድ ርዕስ “የጾታ ግንኙነት የሚፈጽሙ” ከ8 እስከ 12 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች ቁጥር እያደር እየጨመረ እንደመጣ የሚያሳይ ማስረጃ ጠቅሷል። አንድ በቅርቡ ጡረታ የወጡ የትምህርት ቤት አማካሪ “አሁን አሁን ነፍሰጡር የሆኑ ጥቂት የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች ማየት ጀምረናል” ብለዋል።b
የዓለምን መንፈስ መቃወም
10. በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ወጣቶች ለዓለም መንፈስ የተሸነፉት እንዴት ነው?
10 አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶችም ለዓለም መንፈስ መሸነፋቸው የሚያሳዝን ነው። አንዲት ጃፓናዊ ልጃገረድ እንዲህ በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች:- “በወላጆቼና በሌሎች ክርስቲያኖች ፊት ጥሩ ሰው ሆኜ እቀርባለሁ። ይሁን እንጂ የምኖረው ሁለት ዓይነት ኑሮ ነበር።” በኬንያ የምትገኝ አንዲት ወጣት ደግሞ እንዲህ ብላለች:- “ፓርቲ እየጨፈርኩ፣ የሮክ ሙዚቃ እያዳመጥኩና አጉል ጓደኞች ይዤ ለተወሰነ ጊዜ ሁለት ዓይነት ኑሮ ስመራ ቆይቻለሁ። ስህተት መሆኑ አልጠፋኝም፤ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ እተወዋለሁ በሚል ሐሳብ ችላ ብዬው ነበር። ሆኖም ባሰብኝ እንጂ አልተውኩትም።” በጀርመን የምትገኝ አንዲት ወጣትም እንደሚከተለው ብላለች:- “ነገሩ የጀመረው አጉል ጓደኞች በያዝኩ ጊዜ ነበር። ከዚያ ማጨስ ጀመርኩ። ወላጆቼን መጉዳት ፈልጌ ነበር። ይሁን እንጂ የጎዳሁት እነርሱን ሳይሆን ራሴን ነው።”
11. አሥሩ ሰላዮች መጥፎ ወሬ ይዘው በተመለሱ ጊዜ ካሌብ አብዛኛውን የመከተልን ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ያገኘው እንዴት ነበር?
11 አዎን፣ አሁንም ቢሆን የዓለምን መንፈስ መቋቋም ብሎም መቃወም ይቻላል። የጥንቱ ካሌብ የተወውን ምሳሌ ተመልከቱ። አሥሩ ፈሪ ሰላዮች ስለ ተስፋይቱ ምድር መጥፎ ሪፖርት ይዘው በተመለሱ ጊዜ እርሱና ኢያሱ ፈርተው ከብዙሃኑ ጋር ለመስማማት አልፈለጉም። በድፍረት እንደሚከተለው ሲሉ ተናግረዋል:- “ዞረን የሰለልናት ምድር እጅግ መልካም ናት። እግዚአብሔርስ ከወደደን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ወደዚች ምድር ያገባናል እርስዋንም ይሰጠናል።” (ዘኁልቁ 14:7, 8) ካሌብ ያንን ሁሉ ተጽዕኖ እንዲቋቋም ያስቻለው ነገር ምን ነበር? ይሖዋ “ሌላ መንፈስ ከእርሱ ጋር” እንደሆነ ተናግሮለት ነበር።—ዘኁልቁ 14:24
“ሌላ መንፈስ” ማሳየት
12. በንግግራችን ‘የተለየ መንፈስ’ ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
12 ዛሬም ከዓለም የተለየ ‘ሌላ መንፈስ’ ወይም አስተሳሰብ ማንጸባረቅ ድፍረትና ጥንካሬ ይጠይቃል። ይህን ማድረግ የምትችሉበት አንዱ መንገድ ሽሙጥና አክብሮት የጎደለው ንግግርን በማስወገድ ነው። የሚያስገርመው “ሽሙጥ” ተብሎ የተተረጎመው ሳርካዝም የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተገኘበት የግሪክኛ ግስ ቃል በቃል ሲተረጎም “እንደ ውሻ ሥጋን መቦጨቅ” ማለት ነው። (ከገላትያ 5:15 ጋር አወዳድር።) የአንድ ውሻ ጥርስ ከአጥንት ላይ ሥጋ መንጨት እንደሚችል ሁሉ ሽሙጥ የተቀላቀለበትም “ቀልድ” የሌሎችን ሰብዓዊ ክብር የሚገፍፍ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ቆላስይስ 3:8 “ቊጣንና ንዴትን ክፋትንም፣ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ” በማለት አጥብቆ ያሳስባችኋል። ምሳሌ 10:19 ደግሞ “በቃል ብዛት ውስጥ ኃጢአት ሳይኖር አይቀርም፤ ከንፈሩን የሚገታ ግን አስተዋይ ነው” ይላል። አንድ ሰው ቢሰድባችሁ በረጋና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በግል በማነጋገር ‘ሁለተኛውን ጉንጫችሁን’ የማዞር ያህል ራስን የመግዛት መንፈስ አሳዩ።—ማቴዎስ 5:39፤ ምሳሌ 15:1
13. ወጣቶች ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
13 ‘የተለየ መንፈስ’ የምናሳይበት ሌላው መንገድ ደግሞ ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት በመያዝ ነው። እርግጥ ጥሩ ጥሩ ነገሮች ለማግኘት መፈለግ ያለ ነገር ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ቢያንስ አንድ ጥራት ያለው ልብስ እንደነበረው እናውቃለን። (ዮሐንስ 19:23, 24) ይሁን እንጂ ያያችሁት ሁሉ የሚያምራችሁ ከሆነና ወላጆቻችሁ አቅማቸው የማይፈቅድላቸውን ነገር እንዲገዙላችሁ ነጋ ጠባ የምትወተውቱ ከሆነ ወይም ሌሎችን ወጣቶች ለመምሰል የምትፈልጉ ከሆነ የዓለም መንፈስ እናንተ ከምትገምቱት በላይ ተጽዕኖ እያሳደረባችሁ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም. . . እንጂ ከአባት” አይደለም። አዎን፣ የዓለም የፍቅረ ንዋይ መንፈስ አያሸንፋችሁ! ባላችሁ ነገር መርካትን ተማሩ።—1 ዮሐንስ 2:15, 16፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:8-10
14. (ሀ) በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት የአምላክ ሕዝቦች መዝናኛን በተመለከተ ሚዛናዊነት እንደጎደላቸው ያሳዩት እንዴት ነበር? (ለ) አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች በምሽት ዳንስ ቤቶችና ቅጥ የለሽ ጭፈራዎች ላይ በመገኘታቸው ምን ዓይነት አደጋ ገጥሟቸዋል?
14 መዝናኛዎችም ከልክ እንዳያልፉ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ስካርን ለመከተል በጥዋት ለሚማልዱ፣ የወይን ጠጅም እስኪያቃጥላቸው እስከ ሌሊት ድረስ ለሚዘገዩ ወዮላቸው! መሰንቆና በገና ከበሮና እምቢልታም የወይን ጠጅም በግብዣቸው አለ፤ የእግዚአብሔርን ሥራ ግን አልተመለከቱም፣ እጁም ያደረገችውን አልተመለከቱም።” (ኢሳይያስ 5:11, 12) አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች እንዲህ በመሰለ ቅጥ ያጣ ጭፈራ ውስጥ መገኘታቸው የሚያሳዝን ነው። በወጣቶች የዳንስ ምሽት ላይ ተገኝተው የነበሩ የተወሰኑ ክርስቲያን ወጣቶች በዚያ ስለሚታየው ሁኔታ እንዲገልጹ ሲጠየቁ አንዲት ወጣት “ሁልጊዜ ጠብ ይነሳል። እኔም ጠቡ ውስጥ የገባሁበት ጊዜ አለ” ብላለች። አንድ ወጣት ወንድም ደግሞ “መጠጣት፣ ማጨስና ሌሎች ነገሮችም አሉ” ብሏል። ሌላ ወጣት ወንድም ደግሞ እንዲህ ሲል ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “ሰዎች ይሰክራሉ። እንደ እብድ ያደርጋቸዋል! አደገኛ ዕፅም አለ። የማይሠራ የክፋት ዓይነት የለም። እዛ ሄጄ ምንም ሳልሆን እመለሳለሁ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው።” መጽሐፍ ቅዱስ ፈንጠዝያን ወይም ‘ቅጥ ያጣ ጭፈራን’ ‘ከሥጋ ሥራዎች’ መካከል መመደቡ ያለምክንያት አይደለም።—ገላትያ 5:19-21፣ ባይንግተን፤ ሮሜ 13:13
15. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መዝናኛ ምን ሚዛናዊ አመለካከት አለው?
15 ከጎጂ መዝናኛዎች ትርቃላችሁ ማለት ደስታ የሌለው ሕይወት ትመራላችሁ ማለት አይደለም። የምናመልከው በወጣትነታችሁ ደስ እንዲላችሁ የሚፈልገውን ‘ደስተኛ አምላክ’ ነው! (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW፤ መክብብ 11:9) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “ተድላ [“መዝናኛን፣” ላምሳ] የሚወድድ ድሀ ይሆናል” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 21:17) አዎን፣ መዝናኛን በሕይወታችሁ ውስጥ አንደኛውን ቦታ ከሰጣችሁት መንፈሳዊ ድህነት ይገጥማችኋል። እንግዲያውስ በመዝናኛ ምርጫችሁ ረገድ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተከተሉ። በሚያፈርሷችሁ ሳይሆን በሚያንጹአችሁ ነገሮች መደሰት የምትችሉባቸው ብዙ መንገዶች አሉ።c—መክብብ 11:10
16. ክርስቲያን ወጣቶች የተለዩ መሆናቸውን ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
16 በአለባበሳችሁና በፀጉር አበጣጠራችሁ ረገድ የዓለምን ፋሽን ወደጎን በመተው ልከኝነትን ማንጸባረቃችሁ የተለያችሁ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል። (ሮሜ 12:2፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:9) በሙዚቃም ረገድ መራጭ መሆን ተመሳሳይ ውጤት ይኖረዋል። (ፊልጵስዩስ 4:8, 9) አንድ ወጣት ክርስቲያን እንደሚከተለው ብሏል:- “ያሉኝን አንዳንድ ዘፈኖች መጣል እንዳለብኝ ይሰማኛል፤ ነገር ግን እወዳቸዋለሁ!” አንድ ሌላ ወጣትም እንደሚከተለው ብሏል:- “ለእኔ ወጥመድ የሚሆንብኝ ሙዚቃ ነው። ምክንያቱም ሙዚቃ በጣም እወዳለሁ። ሙዚቃው አንድ መጥፎ ነገር እንዳለበት ባውቅ ወይም ወላጆቼ ቢነግሩኝ በልቤ ሙዚቃውን ስለምወደው አእምሮዬ ልቤን እንዲያሳምን ራሴን ማስገደድ ይኖርብኛል።” ወጣቶች ሆይ ‘በሰይጣን ሐሳብ አትሞኙ’! (2 ቆሮንቶስ 2:11) ወጣቶች ከይሖዋ እንዲርቁ ለማድረግ ሙዚቃን እንደ መሣሪያ አድርጎ እየተጠቀመበት ነው! ስለ ራፕ፣ ሄቪ ሜታል እንዲሁም አንዳንድ የሮክ ሙዚቃዎች በመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ላይ ወጥቷል።d ይሁን እንጂ በየጊዜው ስለሚወጣው ስለ እያንዳንዱ አዳዲስ የሙዚቃ ዓይነት በመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ላይ አስተያየት መስጠት በጣም አስቸጋሪ ነው። በመሆኑም በሙዚቃ ምርጫችሁ ረገድ ‘የማሰብ ችሎታችሁንና’ ‘ማስተዋላችሁን’ ተጠቀሙ።—ምሳሌ 2:11 NW
17. (ሀ) ፖርኒያ ምንድን ነው? ምን ዓይነት ድርጊቶችንስ ይጨምራል? (ለ) ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን በተመለከተ የአምላክ ፈቃድ ምንድን ነው?
17 በመጨረሻም ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችሁን መጠበቅ ይኖርባችኋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከዝሙት ሽሹ” በማለት አጥብቆ ያሳስባል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) ዝሙት የሚል ትርጉም ያለው ፖርኒያ የተባለው የመጀመሪያው ግሪክኛ ቃል በጋብቻ ያልተሳሰሩ ሁለት ሰዎች የጾታ ብልቶቻቸውን ከሥነ ምግባር ውጭ ለሆነ የጾታ ተግባር መጠቀማቸውን የሚያመለክት ነው። ይህም በአፍ የሚደረግ ወሲብንና ሆን ብሎ የሌላውን የጾታ ብልት ማሻሸትን ይጨምራል። ብዙ ወጣቶች ዝሙት እንደመፈጸም አይቆጠርም ብለው በማሰብ እንዲህ ያለ ድርጊት ፈጽመዋል። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል በግልጽ እንዲህ ይላል:- “ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤ ከዝሙት እንድትርቁ፣ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፣ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ።”—1 ተሰሎንቄ 4:3, 4
18. (ሀ) አንድ ወጣት በዓለም መንፈስ እንዳይበከል ራሱን መጠበቅ የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ የምንወያየው ስለ ምን ነገር ይሆናል?
18 አዎን፣ በይሖዋ እርዳታ በዓለም መንፈስ ከመበከል ልትርቁ ትችላላችሁ! (1 ጴጥሮስ 5:10) የሆነ ሆኖ ሰይጣን ብዙውን ጊዜ ገዳይ የሆኑ ወጥመዶቹን ሸፋፍኖ ስለሚያቀርባቸው አንዳንድ ጊዜ አደጋውን አስቀድሞ ለማየት ትልቅ ማስተዋል ይጠይቃል። የሚቀጥለው ርዕስ ወጣቶች የማስተዋል ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንዶቹ የዳንስ ፓርቲዎች እስከ ንጋት ድረስ የሚዘልቁ ናቸው። ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . የዳንስ ፓርቲዎች ጉዳት የሌላቸው መዝናኛዎች ናቸውን?” የሚለውን የታኅሣሥ 22, 1997 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ተመልከት።
b 11 ዓመት ገደማ የሚሆናቸው ልጆች ማለት ነው።
c አማራጮችን ለመመልከት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 296-303 ድረስ ተመልከቱ።
d የሚያዝያ 15, 1993ን መጠበቂያ ግንብ ተመልከቱ።
ለክለሳ የቀረቡ ጥያቄዎች
◻ ‘የዓለም መንፈስ’ ምንድን ነው? በሰዎችስ ላይ ‘ሥልጣን’ ያለው እንዴት ነው?
◻ ዛሬ ባሉት ወጣቶች ዘንድ የዓለም መንፈስ ከሚንጸባረቅባቸው መንገዶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
◻ ክርስቲያን ወጣቶች መዝናኛንና አነጋገርን በተመለከተ ‘የተለየ መንፈስ’ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ ክርስቲያን ወጣቶች ሥነ ምግባርንና ሙዚቃን በተመለከተ ‘የተለየ መንፈስ’ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የብዙዎቹ ወጣቶች አድራጎት የዚህ ዓለም መንፈስ ‘ተጽዕኖ’ እንዳሳደረባቸው የሚያሳይ ነው
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በምትሰሙት ሙዚቃ ረገድ መራጮች ሁኑ
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የዓለምን መንፈስ መቋቋም ድፍረት ይጠይቃል