የዓለምን መንፈስ ሳይሆን የአምላክን መንፈስ ተቀበሉ
“አምላክ በደግነት የሰጠንን ነገሮች ማወቅ እንችል ዘንድ ከአምላክ የሆነውን መንፈስ ተቀበልን እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።”—1 ቆሮ. 2:12
1, 2. (ሀ) እውነተኛ ክርስቲያኖች ጦርነት ላይ ናቸው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
እውነተኛ ክርስቲያኖች ጦርነት ላይ ናቸው! ጠላታችን ኃይለኛ፣ መሠሪና ልምድ ያለው ተዋጊ ነው። የሚጠቀምበት መሣሪያ በጣም ውጤታማ ስለሆነ አብዛኛውን የሰው ዘር ማንበርከክ ችሏል። ያም ቢሆን ግን ከአቅማችን በላይ እንደሆነ ወይም የማሸነፍ ተስፋ እንደሌለን ሊሰማን አይገባም። (ኢሳ. 41:10) ፈጽሞ የማይደፈርና የማይበገር መከላከያ አለን።
2 ይህ ቃል በቃል የሚደረግ ጦርነት ሳይሆን መንፈሳዊ ውጊያ ነው። ባላጋራችን ሰይጣን ዲያብሎስ ሲሆን የሚጠቀምበት ዋነኛ መሣሪያ ደግሞ ‘የዓለም መንፈስ’ ነው። (1 ቆሮ. 2:12) የሚሰነዝርብንን ጥቃት ለመከላከል የሚረዳን ቁልፍ መሣሪያ የአምላክ መንፈስ ነው። ከዚህ ጦርነት በሕይወት መትረፍና በመንፈሳዊ ንቁዎች ሆነን መቀጠል ከፈለግን አምላክ መንፈሱን እንዲሰጠን መጠየቅና የመንፈሱን ፍሬ በሕይወታችን ውስጥ ማፍራት ያስፈልገናል። (ገላ. 5:22, 23) ለመሆኑ የዓለም መንፈስ ምንድን ነው? ይህን ያህል ተጽዕኖ የማሳደር ኃይል ሊኖረው የቻለውስ እንዴት ነው? የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ እያሳደረብን እንደሆነና እንዳልሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክን መንፈስ በመቀበልና የዓለምን መንፈስ በመቃወም ረገድ ከኢየሱስ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
የዓለም መንፈስ ይህን ያህል የተስፋፋው ለምንድን ነው?
3. የዓለም መንፈስ ምንድን ነው?
3 የዓለም መንፈስ የሚመነጨው “የዚህ ዓለም ገዥ” ከሆነው ከሰይጣን ሲሆን ከአምላክ ቅዱስ መንፈስ ጋር ይቃረናል። (ዮሐ. 12:31፤ 14:30፤ 1 ዮሐ. 5:19) ይህ መንፈስ በዓለም ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኝ ዝንባሌ ከመሆኑም ሌላ ሰዎች ለአንድ ዓይነት ተግባር እንዲነሳሱ ያደርጋል። ይህ መንፈስ ሰብዓዊው ኅብረተሰብ ከአምላክ ፈቃድ ወይም ዓላማ ጋር የሚቃረን ድርጊት እንዲፈጽም የሚገፋፋ ኃይል ነው።
4, 5. ሰይጣን የሚያመነጨው መንፈስ ይህን ያህል ሊስፋፋ የቻለው እንዴት ነው?
4 ሰይጣን የሚያመነጨው መንፈስ ይህን ያህል ሊስፋፋ የቻለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ሰይጣን በኤደን ገነት ሔዋንን አሳሳታት። የአምላክን መመሪያ ችላ በማለት ራሷን በራሷ ብትመራ የተሻለ ሕይወት እንደሚኖራት አሳመናት። (ዘፍ. 3:13) ይህ እንዴት ያለ ውሸት ነው! (ዮሐ. 8:44) ሰይጣን በሔዋን ተጠቅሞ አዳምም የይሖዋን ትእዛዝ እንዲጥስ አደረገ። አዳም ባደረገው ምርጫ ምክንያት የሰው ዘር ለኃጢአት ተሸጠ፤ በዚህም የተነሳ የሰይጣንን የዓመፀኝነት መንፈስ የመከተል ዝንባሌ ወርሷል።—ኤፌሶን 2:1-3ን አንብብ።
5 ሰይጣን በበርካታ መላእክት ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ሲሆን እነዚህ መላእክት ከጊዜ በኋላ አጋንንት ሆነዋል። (ራእይ 12:3, 4) በአምላክ ላይ እንዲህ ያለ ክህደት የተፈጸመው በኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ ከመምጣቱ ቀደም ብሎ ነበር። እነዚህ መላእክት በሰማይ የነበራቸውን ቦታ ትተው ወደ ምድር በመምጣት ተፈጥሯዊ ያልሆነ ፍላጎታቸውን ልቅ በሆነ መንገድ ቢያረኩ የተሻለ ሕይወት እንደሚኖራቸው አመኑ። (ይሁዳ 6) ሰይጣን በአሁኑ ጊዜ በመንፈሳዊው ዓለም በሚገኙት በእነዚህ አጋንንት በመታገዝ “መላውን ዓለም እያሳሳተ” ነው። (ራእይ 12:9) የሚያሳዝነው አብዛኛው የሰው ዘር አጋንንት ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ አልተገነዘበም።—2 ቆሮ. 4:4
የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ እያሳደረባችሁ ነው?
6. የዓለም መንፈስ ሊበክለን የሚችለው ምን ካደረግን ብቻ ነው?
6 ብዙዎች የሰይጣንን ተጽዕኖ አያስተውሉም፤ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን የእሱን ዕቅዶች ያውቋቸዋል። (2 ቆሮ. 2:11) እኛ ካልፈቀድንለት በስተቀር የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን አይችልም። የምንመራው በአምላክ መንፈስ ነው ወይስ በዓለም መንፈስ? የሚለውን ለማወቅ የሚረዱንን አራት ጥያቄዎች ከዚህ ቀጥሎ እንመረምራለን።
7. ሰይጣን እኛን ከይሖዋ ለማራቅ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ ምንድን ነው?
7 የመዝናኛ ምርጫዬ ስለ እኔ ምን ይጠቁማል? (ያዕቆብ 3:14-18ን አንብብ።) ሰይጣን ዓመፅን እንድንወድ በማድረግ እኛን ከአምላክ ለማራቅ ይሞክራል። ይሖዋ ዓመፅን የሚወድን ማንኛውንም ሰው እንደሚጠላ ዲያብሎስ ያውቃል። (መዝ. 11:5) በመሆኑም ሰይጣን ጽሑፎችን፣ ፊልሞችን፣ ሙዚቃዎችንና የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችን አጓጊ በሆነ መንገድ ያቀርብልናል፤ ከእነዚህ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች አንዳንዶቹ ሰዎች በጨዋታው ላይ ልቅ የሆነ የሥነ ምግባር ብልግና ወይም የጭካኔ ድርጊት እንዲፈጽሙ የሚያነሳሱ ናቸው። ሰይጣን፣ በአንድ ልባችን እሱ የሚያስፋፋቸውን መጥፎ ነገሮች እስከወደድን ድረስ ትክክል የሆነውን ነገርም ብንወድ ግድ የለውም።—መዝ. 97:10
8, 9. መዝናኛን በተመለከተ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይገባናል?
8 በሌላ በኩል ደግሞ የአምላክን መንፈስ የሚቀበሉ ሁሉ ንጹሓን፣ ሰላማውያንና ምሕረት የሞላባቸው እንዲሆኑ ይህ መንፈስ ያነሳሳቸዋል። ‘የምመርጠው መዝናኛ ጥሩ ባሕርያትን እንዳዳብር ይረዳኛል?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው። ከላይ የሆነው ጥበብ “ግብዝነት የሌለበት” ነው። በአምላክ መንፈስ የሚመሩ ክርስቲያኖች በአንድ በኩል ንጹሕና ሰላማዊ ስለ መሆን ለሰዎች እየሰበኩ በሌላ በኩል ዘግናኝ የዓመፅ ድርጊትና የሥነ ምግባር ብልግና በቤታቸው ቁጭ ብለው በመመልከት አይዝናኑም።
9 ይሖዋ እሱ ብቻ እንዲመለክ ይፈልጋል። ሰይጣን ግን ኢየሱስን እንደጠየቀው ሁሉ አንድ ጊዜ ብቻ ብናመልከው እንኳ ደስተኛ ነው። (ሉቃስ 4:7, 8) እንግዲያው እንደሚከተለው ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘የምመርጠው መዝናኛ አምላክን ብቻ እንዳመልክ የሚያስችለኝ ነው? የማደርገው ምርጫ የዓለምን መንፈስ መቋቋም ከባድ እንዲሆንብኝ የሚያደርግ ነው ወይስ የሚያቀልል? በመዝናኛ ምርጫዬ ረገድ ወደፊት ላስተካክለው የሚገባ ነገር አለ?’
10, 11. (ሀ) ከቁሳዊ ሀብት ጋር በተያያዘ የዓለም መንፈስ ምን ዓይነት አመለካከትን ያስፋፋል? (ለ) በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈው ቃሉ ምን አመለካከት እንድንይዝ ያበረታታል?
10 ለቁሳዊ ነገሮች ምን አመለካከት አለኝ? (ሉቃስ 18:24-30ን አንብብ።) “የዓይን አምሮት” ማለትም ስግብግብነትና ፍቅረ ንዋይ የዓለም መንፈስ ክፍል ናቸው። (1 ዮሐ. 2:16) ይህ መንፈስ ብዙዎች ሀብታም ለመሆን ቆርጠው እንዲነሱ አድርጓቸዋል። (1 ጢሞ. 6:9, 10) የዓለም መንፈስ፣ ቁሳዊ ሀብት ማካበት አስተማማኝ ሕይወት ለመምራት እንደሚያስችል ሊያሳምነን ይሞክራል። (ምሳሌ 18:11) ለገንዘብ ያለን ፍቅር ለአምላክ ካለን ፍቅር ከበለጠ ሰይጣን ተሳክቶለታል ማለት ነው። ‘ትኩረቴ ሁሉ ያረፈው የተንደላቀቀ ሕይወት በመምራትና ደስታ የሚያስገኙ ነገሮችን በማሳደድ ላይ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።
11 ከዓለም መንፈስ በተቃራኒ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት እንድናዳብርና ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ነገሮች ለማሟላት ጠንክረን እንድንሠራ ያበረታታናል። (1 ጢሞ. 5:8) የአምላክን መንፈስ የሚቀበሉ ሁሉ የይሖዋን የልግስና ባሕርይ እንዲያንጸባርቁ ይህ መንፈስ ይረዳቸዋል። እንዲህ ያሉ ግለሰቦች የሚታወቁት ተቀባዮች በመሆን ሳይሆን ሰጪዎች በመሆናቸው ነው። ከቁሳዊ ነገሮች ይልቅ ሰውን አስበልጠው የሚመለከቱ ሲሆን አቅማቸው የሚፈቅድላቸው ከሆነ ያላቸውን ለሌሎች በደስታ ያካፍላሉ። (ምሳሌ 3:27, 28) እንዲሁም ምንጊዜም ከገንዘብ ይልቅ አምላክን ያስቀድማሉ።
12, 13. ከዓለም መንፈስ በተቃራኒ የአምላክ መንፈስ ምን በጎ ተጽዕኖ ያሳድርብናል?
12 ባሕርዬና ምግባሬ የትኛውን መንፈስ ያንጸባርቃል? (ቆላስይስ 3:8-10, 13ን አንብብ።) የዓለም መንፈስ የሥጋ ሥራዎችን ያስፋፋል። (ገላ. 5:19-21) የምንመራው በየትኛው መንፈስ እንደሆነ በትክክል የሚታወቀው ነገሮች ሰላም በሆኑበት ጊዜ ሳይሆን ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ ነው፤ ለምሳሌ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ችላ ቢሉን፣ ቅር ቢያሰኙን አልፎ ተርፎም ቢበድሉን እውነተኛ ማንነታችን ይታያል። በተጨማሪም ቤት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ በየትኛው መንፈስ እንደምንመራ ግልጽ ይሆናል። በዚህ ረገድ ራሳችንን መመርመራችን ተገቢ ነው። ‘ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የክርስቶስን ዓይነት ስብዕና ይበልጥ እያንጸባረቅኩ ነበር ወይስ ቀድሞ የነበረኝ መጥፎ አነጋገርና ምግባር አገርሽቶብኛል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።
13 የአምላክ መንፈስ ‘አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፈን እንድንጥል’ እንዲሁም “አዲሱን ስብዕና” እንድንለብስ ይረዳናል። ይህም ይበልጥ አፍቃሪና ደጎች እንድንሆን ያደርገናል። ቅር እንድንሰኝ የሚያደርገን ምክንያት እንዳለን ቢሰማንም እርስ በርስ በነፃ ይቅር ለመባባል እንነሳሳለን። ተገቢ ያልሆነ ነገር እንደተፈጸመብን ሲሰማን “የመረረ ጥላቻ” በሚንጸባረቅበት እንዲሁም “ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ” በተቀላቀለበት መንገድ ምላሽ አንሰጥም። ከዚህ ይልቅ ‘ከአንጀት የምንራራ’ ለመሆን ጥረት እናደርጋለን።—ኤፌ. 4:31, 32
14. በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች የአምላክን ቃል የሚመለከቱት እንዴት ነው?
14 የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደንቦች ከፍ አድርጌ እመለከታለሁ? ለእነዚህ ደንቦችስ ፍቅር አለኝ? (ምሳሌ 3:5, 6ን አንብብ።) የዓለም መንፈስ በአምላክ ቃል ላይ ማመፅን ያበረታታል። በዚህ መንፈስ የሚመሩ ሰዎች ለእነሱ የማይጥሟቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ችላ በማለት ሰብዓዊ ወጎችንና ፍልስፍናዎችን ይከተላሉ። (2 ጢሞ. 4:3, 4) አንዳንዶች ደግሞ የአምላክን ቃል ከናካቴው አይቀበሉትም። እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚና ትክክለኛ መሆኑን ስለሚጠራጠሩ በራሳቸው ዓይን ጥበብ መስሎ የታያቸውን ጎዳና ይከተላሉ። ምንዝርን፣ ግብረ ሰዶምንና ፍቺን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ንጹሕ የሆነ መመሪያ ይበርዙታል። “ክፉውን መልካም፣ መልካሙን ክፉ” እንደሆነ አድርገው ያስተምራሉ። (ኢሳ. 5:20) እኛስ ይህ መንፈስ ተጽዕኖ አሳድሮብን ይሆን? ችግሮች ሲያጋጥሙን በሰብዓዊ ጥበብና በራሳችን አመለካከት እንመራለን? ወይስ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ እንጥራለን?
15. በራሳችን ጥበብ ከመመካት ይልቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
15 የአምላክ መንፈስ ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት እንድናዳብር ይረዳናል። ልክ እንደ መዝሙራዊው እኛም የአምላክን ቃል ለእግራችን መብራት እንዲሁም ለመንገዳችን ብርሃን እንደሆነ አድርገን እንመለከተዋለን። (መዝ. 119:105) ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ለመለየት በራሳችን ጥበብ ከመመካት ይልቅ በጽሑፍ በሰፈረው የአምላክ ቃል እንታመናለን። ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ከማዳበራችንም በተጨማሪ የአምላክን ሕግጋት እንወዳቸዋለን።—መዝ. 119:97
ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ተማሩ
16. ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ መያዝ ሲባል ምን ማለት ነው?
16 የአምላክን መንፈስ ለመቀበል ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ በውስጣችን ማዳበር ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 2:16) “ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ” እንዲኖረን ከፈለግን እሱ ያስተማረበትን መንገድ እንዲሁም ያደረጋቸውን ነገሮች ማወቅ ብሎም ምሳሌውን መከተል ያስፈልገናል። (ሮም 15:5፤ 1 ጴጥ. 2:21) ይህን ማድረግ የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት።
17, 18. (ሀ) ስለ ጸሎት ከኢየሱስ ምን እንማራለን? (ለ) ‘ደጋግመን መለመን’ ያለብን ለምንድን ነው?
17 የአምላክን መንፈስ ለማግኘት ጸልዩ። ኢየሱስ ፈተና ውስጥ ከመግባቱ በፊት የአምላክ መንፈስ እንዲረዳው ጸልዮአል። (ሉቃስ 22:40, 41) እኛም ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን አምላክን መጠየቅ ያስፈልገናል። ይሖዋ በእምነት ለሚጠይቁት ሁሉ መንፈሱን በነፃና በልግስና ይሰጣል። (ሉቃስ 11:13) ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል። የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋል፤ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ሁሉ ይከፈትለታል።”—ማቴ. 7:7, 8
18 ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠንና እንዲረዳን በምንሻበት ጊዜ መለመናችንን ቶሎ ማቋረጥ አይኖርብንም። አዘውትረን ብሎም ረዘም ላለ ጊዜ መጸለይ ያስፈልገን ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ ከመስጠቱ በፊት የምንጸልይለት ጉዳይ ምን ያህል በጥልቅ እንዳሳሰበንና እምነታችን ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ እንድናሳይ ይፈልጋል።a
19. ኢየሱስ ምንጊዜም ምን ያደርግ ነበር? እኛስ እሱን መምሰል የሚኖርብን ለምንድን ነው?
19 ይሖዋን በሙሉ ልባችሁ ታዘዙ። ኢየሱስ ምንጊዜም የሚያደርገው አባቱን የሚያስደስተውን ነገር ነበር። በአንድ ወቅት ላይ ኢየሱስ፣ አንድን ጉዳይ ሊይዝ ያሰበበት መንገድ አባቱ ከሚፈልገው የተለየ ነበር። ያም ሆኖ ለአባቱ “የእኔ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም” በማለት ምንም ሳያመነታ በሙሉ ልብ ተናግሮ ነበር። (ሉቃስ 22:42) ‘አምላክን መታዘዝ ቀላል በማይሆንበት ጊዜም እታዘዘዋለሁ?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። አምላክን መታዘዝ የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው። ይሖዋ ፈጣሪያችንና ሕይወት ሰጪያችን ከመሆኑም ሌላ በሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጉንን ነገሮች የሚሰጠን እሱ በመሆኑ በሙሉ ልብ ልንታዘዘው ይገባል። (መዝ. 95:6, 7) መታዘዝን በምንም ነገር መተካት አንችልም። ካልታዘዝን የአምላክን ሞገስ ማግኘት አንችልም።
20. የኢየሱስ ሕይወት ያተኮረው በምን ላይ ነበር? የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለውስ እንዴት ነው?
20 መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ እወቁ። ኢየሱስ ሰይጣን በእምነቱ ላይ የሰነዘረበትን ቀጥተኛ ጥቃት ለመቋቋም ከቅዱሳን መጻሕፍት ጠቅሶ ነበር። (ሉቃስ 4:1-13) ለሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎቹ ምላሽ ለመስጠት የአምላክን ቃል እንደ ባለሥልጣን አድርጎ ተጠቅሟል። (ማቴ. 15:3-6) የኢየሱስ መላ ሕይወት ያተኮረው የአምላክን ሕግጋት በማወቅና በመፈጸም ላይ ነበር። (ማቴ. 5:17) እኛም አእምሯችንን እምነትን የሚያጠናክረውን የአምላክን ቃል መመገብ እንፈልጋለን። (ፊልጵ. 4:8, 9) የግልና የቤተሰብ ጥናት ለማድረግ የሚያስችል ጊዜ ማግኘት ለአንዳንዶቻችን ፈታኝ ሊሆንብን ይችላል። ይሁንና ጊዜ ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ ለጥናት የሚሆነንን ጊዜ ማመቻቸት ይኖርብናል።—ኤፌ. 5:15-17
21. የአምላክን ቃል ይበልጥ ለማወቅና በተግባር ለማዋል እንድንችል በየትኛው ዝግጅት መጠቀም እንችላለን?
21 “ታማኝና ልባም ባሪያ” በየሳምንቱ ለቤተሰብ አምልኮ የሚውል አንድ ምሽት እንድናገኝ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ለግልና ለቤተሰብ ጥናት የሚሆን ጊዜ እንዲኖረን ዝግጅት አድርጎልናል። (ማቴ. 24:45) ይህን ዝግጅት በሚገባ እየተጠቀማችሁበት ነው? የክርስቶስን አስተሳሰብ ማዳበር እንድትችሉ በመረጣችኋቸው ነጥቦች ላይ ኢየሱስ ምን እንዳስተማረ የምትመረምሩበት ቋሚ ጊዜ በጥናት ክፍለ ጊዜያችሁ ውስጥ ማካተት ትችሉ ይሆን? እያጠናችሁ ስላላችሁት ርዕስ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሚሰጣችሁን ጽሑፍ ለማግኘት በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) መጠቀም ትችላላችሁ። ለምሳሌ ያህል፣ ከ2008 እስከ 2010 ባሉት ዓመታት ውስጥ የሚበረከተው የመጠበቂያ ግንብ እትም “ከኢየሱስ ምን እንማራለን?” በሚል አምድ ሥር 12 ተከታታይ ርዕሶችን ይዞ ወጥቶ ነበር። እነዚህን ርዕሶች በጥናታችሁ ላይ ልትጠቀሙባቸው ትችላላችሁ። ከ2006 ጀምሮ “መልስህ ምንድን ነው?” የሚል አምድ በንቁ! መጽሔት ላይ ሲወጣ ቆይቷል። በዚህ አምድ ሥር የወጡት ጥያቄዎች ስለ አምላክ ቃል ሰፋ ያለና ጥልቀት ያለው እውቀት እንዲኖራችሁ ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ ነበሩ። እንዲህ ባሉት አምዶች ሥር የሚገኙትን ትምህርቶች አልፎ አልፎ በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ላይ ለምን አታካትቷቸውም?
ዓለምን ማሸነፍ እንችላለን
22, 23. ዓለምን ለማሸነፍ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
22 በአምላክ መንፈስ መመራት የምንፈልግ ከሆነ የዓለምን መንፈስ መቃወም አለብን። በእርግጥ ይህን መንፈስ መቃወም ቀላል አይደለም። ብርቱ ተጋድሎና ትግል ማድረግ ሊጠይቅብን ይችላል። (ይሁዳ 3) ይሁንና በትግሉ ማሸነፍ እንችላለን! ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “በዓለም ሳላችሁ መከራ ይደርስባችኋል፤ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ብሏቸዋል።—ዮሐ. 16:33
23 እኛም የዓለምን መንፈስ ከተቃወምንና የአምላክን መንፈስ ለማግኘት የምንችለውን ሁሉ ካደረግን ዓለምን ማሸነፍ እንችላለን። በእርግጥም “አምላክ ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?” (ሮም 8:31) የአምላክን መንፈስ የምንቀበልና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውን የመንፈሱን አመራር የምንከተል ከሆነ እርካታ፣ ሰላምና ደስታ እናገኛለን፤ በቅርቡ ደግሞ በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ይኖረናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 170-173 ተመልከት።
ታስታውሳለህ?
• የዓለም መንፈስ ይህን ያህል የተስፋፋው ለምንድን ነው?
• ራሳችንን የትኞቹን አራት ጥያቄዎች መጠየቅ ይገባናል?
• የአምላክን መንፈስ ከማግኘት ጋር በተያያዘ ከኢየሱስ የምንማራቸው ሦስት ነገሮች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንድ መላእክት አጋንንት የሆኑት እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰይጣን፣ ሰዎችን በቁጥጥሩ ሥር ለማድረግ የዓለምን መንፈስ ይጠቀማል፤ ሆኖም ከተጽዕኖው ራሳችንን ነፃ ማውጣት እንችላለን