እውነተኛው ኢየሱስ
ኢየሱስ፣ ሰዎች ስለ እርሱ ያላቸውን አመለካከት ከሐዋርያቱ ከተረዳ በኋላ “እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” በማለት ጠየቃቸው። የማቴዎስ ወንጌል “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” በማለት ሐዋርያው ጴጥሮስ የሰጠውን መልስ ዘግቧል። (ማቴዎስ 16:15, 16 አ.መ.ት ) ሌሎችም ተመሳሳይ አመለካከት ነበራቸው። ከጊዜ በኋላ ሐዋርያ የሆነው ናትናኤል ኢየሱስን “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” ብሎታል። (ዮሐንስ 1:50) ኢየሱስ ራሱ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት የሚጫወተውን ሚና ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ዮሐንስ 14:6) በተለያዩ አጋጣሚዎች ራሱን “የእግዚአብሔር ልጅ” በማለት ጠርቷል። (ዮሐንስ 5:24, 25፤ 11:4) ይህን አባባሉንም ተአምር በመሥራትና ሙታንን እንኳ ሳይቀር በማስነሣት አረጋግጧል።
መሠረት ያላቸው ጥርጣሬዎች?
ታዲያ ስለ ኢየሱስ በሚናገሩት የወንጌል ዘገባዎች ላይ እምነት መጣል እንችላለን? ወንጌሎች ኢየሱስን በትክክል ይገልጹታል? እንግሊዝ ውስጥ በሚገኘው የማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ የመጽሐፍ ቅዱስ ሃያሲና ተንታኝ የነበሩት ሟቹ ፕሮፌሰር ፍሬድሪክ ኤፍ ብሩስ እንደሚከተለው በማለት ገልጸዋል:- “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ባለ አንድ ጥንታዊ ታሪክ ውስጥ የሚገኘውን እያንዳንዱን ዝርዝር ሐሳብ ታሪካዊ ማስረጃ ተጠቅሞ ለማረጋገጥ መሞከር አብዛኛውን ጊዜ ያዳግታል። አንድ ጸሐፊ እምነት የሚጣልበት ስለመሆኑ በተወሰነ መጠን ከተማመን በቂ ነው። ይህ ዝርዝሮቹ እውነት ለመሆናቸው ሌላ ማስረጃ የማያሻው ማረጋገጫ ይሆናል። . . . አዲስ ኪዳን በክርስቲያኖች ዘንድ ‘ቅዱስ’ መጽሐፍ ተደርጎ መታየቱ ታሪካዊ ተዓማኒነቱን አይቀንሰውም።”
ዩ ኤስ ኤ ኖርዝ ዳኮታ ውስጥ በሚገኘው የጄምስታውን ኮሌጅ የሃይማኖት ፕሮፌሰር የሆኑት ጄምስ አር ኤድዋርድስ በወንጌሎች ውስጥ የተገለጸውን ኢየሱስ አስመልክቶ የሚነሱትን ጥርጣሬዎች ከመረመሩ በኋላ የሚከተለውን ጽፈዋል:- “ወንጌሎች የኢየሱስን ትክክለኛ ማንነት በተመለከተ ትርጉም ያላቸውን በርካታ ማስረጃዎች እንደያዙ አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን። . . . ወንጌሎች ኢየሱስን ስለሳሉበት መንገድ ለሚነሳው ጥያቄ የሚሰጠው ምክንያታዊ መልስ ኢየሱስ ራሱ በወንጌሎች ውስጥ የተገለጸውን ዓይነት ሰው ነበር የሚል ነው። ወንጌሎች፣ ኢየሱስ በተከታዮቹ አእምሮ ውስጥ ትቶ ያለፈውን አሻራ ማለትም በአምላክ የተላከና የአምላክ ልጅ እንዲሁም አገልጋይ የመሆን ሥልጣን የተሰጠው ስለመሆኑ የሚገልጸውን እውነታ በትክክል ጠብቀው አቆይተዋል።”a
ኢየሱስን ለማግኘት የሚደረግ ፍለጋ
ኢየሱስ ክርስቶስን ስለሚጠቅሱ ታሪካዊ ማስረጃዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? እነዚህንስ መገምገም የሚቻለው እንዴት ነው? የታሲተስ፣ የስዊቶኒየስ፣ የጆሴፈስ፣ የታናሹ ፕሊኒና የሌሎች የዘመኑ ጸሐፊዎች ሥራ ውጤቶች ኢየሱስን ብዙ ጊዜ ይጠቅሳሉ። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ (1995) ስለ እነዚህ ታሪካዊ ማስረጃዎች ሲናገር እንዲህ ይላል:- “በጥንት ዘመን የነበሩ የክርስትና ተቃዋሚዎች እንኳ ኢየሱስ እርግጠኛ ታሪክ ያለው ሰው መሆኑን ተጠራጥረው እንደማያውቁ እነዚህ ገለልተኛ የታሪክ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። ሰዎች የኢየሱስን ታሪክ እርግጠኛነት አለበቂ ምክንያት መጠራጠር የጀመሩት በ18ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ፣ በ19ኛው መቶ ዘመንና በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው።”
የሚያሳዝነው የዘመናችን ምሁራን “እውነተኛውን” ወይም “በታሪክ የሚታወቀውን” ኢየሱስ ለማግኘት በሚያደርጉት ፍለጋ መሠረተ ቢስ በሆነ ግምታዊ አስተሳሰባቸው፣ በከንቱ ጥርጣሬያቸውና በማይጨበጥ ንድፈ ሐሳባቸው እውነተኛ ማንነቱ እንዲሰወር አድርገዋል ማለት ይቻላል። እነዚህ ምሁራን አፈ ታሪክ በመፍጠር የወንጌል ዘጋቢዎችን በሐሰት መወንጀላቸው ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። አንዳንዶቹ ዝና ለማትረፍና ስማቸውን ከአንድ አዲስና አስደናቂ ንድፈ ሐሳብ ጋር በተያያዘ ለማስጠራት ካላቸው ጉጉት የተነሣ ስለ ኢየሱስ የሚናገሩትን ማስረጃዎች በሃቀኝነት ሳይመረምሩ ይቀራሉ። በዚህም ምሁራዊ አእምሮ የፈጠረውን “ኢየሱስ” ይስላሉ።
እውነተኛውን ኢየሱስ ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሊያገኙት ይችላሉ። ኤምሪ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚገኘው የካንድለር ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤት የአዲስ ኪዳንና የክርስትና አመጣጥ ፕሮፌሰር የሆኑት ሉክ ጆንሰን በታሪክ የሚታወቀውን ኢየሱስ አስመልክቶ የሚደረገው አብዛኛው ምርምር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዓላማውን እንደሚስት ተናግረዋል። እኚሁ ፕሮፌሰር እንዳስቀመጡት የኢየሱስን ሕይወትና የኖረበትን ዘመን ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሥነ ስብዓታዊና ባሕላዊ ገጽታዎች መመርመሩ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ አክለው ሲናገሩ ምሁራን በታሪክ የሚታወቀውን ኢየሱስ የሚገልጹበት መንገድ ባሕርያቱን፣ መልእክቱንና ቤዛ በመሆን የሚጫወተውን ሚና “ጎላ አድርጎ ከሚገልጸው ቅዱስ ጽሑፍ ጋር ፈጽሞ አይጣጣምም” ብለዋል። ታዲያ የኢየሱስ እውነተኛ ባሕርይና መልእክት ምን ነበር?
እውነተኛው ኢየሱስ
በኢየሱስ ሕይወት ላይ ያተኮሩት አራቱ የወንጌል ዘገባዎች ኢየሱስን የሚያቀርቡት የሌሎችን ችግር የሚረዳ ሰው እንደሆነ አድርገው ነው። ርኅራኄውና አዘኔታው የታመሙትን፣ ማየት የተሳናቸውንና በሌሎች ሕመሞች የሚሰቃዩትን እንዲረዳ ገፋፍቶታል። (ማቴዎስ 9:36፤ 14:14፤ 20:34) የወዳጁ የአልዓዛር ሞትና ይህም በእህቶቹ ላይ ያስከተለውን ኃዘን መመልከቱ ‘እንዲያዝንና እንባውን እንዲያፈስስ’ አድርጎታል። (ዮሐንስ 11:32-36) እንዲያውም ወንጌሎች ኢየሱስ በተለያዩ ወቅቶች የተሰማውን ስሜት ይገልጻሉ፤ ከእነዚህም ውስጥ የሥጋ ደዌ ለያዘው ሰው የተሰማው ኃዘን፣ ደቀ መዛሙርቱ ስኬት ሲያገኙ የተሰማው ደስታ፣ ሕጉን ድርቅ ብለው በሚከተሉትና ርኅራሄ በሌላቸው ግለሰቦች ላይ ያደረበት ቁጣና ኢየሩሳሌም መሲሑን አልቀበልም በማለቷ የተሰማው ሐዘን ይገኙበታል።
ብዙውን ጊዜ ኢየሱስ ተዓምር ሲሠራ ግለሰቡ የተጫወተውን ሚና ጎላ አድርጎ ይገልጽ ነበር። ለምሳሌ በአንድ ወቅት “እምነትሽ አድኖሻል” ብሏል። (ማቴዎስ 9:22) ናትናኤልንም “ተንኮል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው” በማለት አወድሶታል። (ዮሐንስ 1:48) አንዳንዶች፣ አንዲት ሴት አመስጋኝነቷን ለመግለጽ የሰጠችው ስጦታ አላግባብ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት እንደሆነ በመግለጽ ሲቃወሙ ከጎኗ የቆመ ከመሆኑም በተጨማሪ ይህ ልግስናዋ ለረዥም ጊዜ ሲታወስ እንደሚኖርም ተናግሯል። (ማቴዎስ 26:6-13) ተከታዮቹን ‘እስከ መጨረሻ በመውደድ’ እውነተኛ ጓደኛና አፍቃሪ ወዳጅ መሆኑን አስመስክሯል።—ዮሐንስ 13:1፤ 15:11-15
በተጨማሪም ወንጌሎች፣ ኢየሱስ የሚያገኛቸውን የአብዛኞቹን ሰዎች ፍላጎት ወዲያው ይረዳ እንደነበረም ይገልጻሉ። በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ካገኛት ሴት ጋርም ሆነ በአትክልት ቦታ ካገኘው ሃይማኖታዊ አስተማሪ አሊያም ሐይቅ ዳር ካገኘው ዓሳ አጥማጅ ጋር ባደረገው ውይይት ወዲያው ልባቸውን መንካት ችሏል። አብዛኞቹ ገና ውይይት ከመክፈቱ ልባቸው በመነካቱ ሐሳባቸውን ገልጸው ነግረውታል። በዚያ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ሥልጣን ካላቸው ጋር ብዙ መቀራረብ የማይፈልጉ ቢሆንም ኢየሱስን ግን ዙሪያውን ይከብቡት ነበር። ሰዎች ከኢየሱስ ጋር መሆን ያስደስታቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ ከእሱ ጋር ሲሆኑ ነጻነት ይሰማቸው ነበር። ልጆችም ከእርሱ ጋር መሆን ያስደስታቸው ነበር። አንድን ልጅ እንደ ምሳሌ አድርጎ በተጠቀመ ጊዜ ልጁን እንዲያው በደቀ መዛሙርቱ ፊት ከማቆም ይልቅ ‘እቅፍ አድርጎታል።’ (ማርቆስ 9:36፤ 10:13-16) በእርግጥም ወንጌሎች ኢየሱስን የሚያቀርቡት የሚመስጥ ንግግሩን ለማዳመጥ ሲሉ ሰዎች ለሦስት ቀን አብረውት እንዲቆዩ ያደረገ አንዳች የሚስብ ኃይል ያለው ሰው አድርገው ነው።—ማቴዎስ 15:32
ኢየሱስ ፍጹም መሆኑ አብረውት የሚኖሩትንና የሚሰብክላቸውን ፍጹማን ያልሆኑ ኃጢአት የተጫናቸውን ሰዎች ስህተት የሚለቃቅም ወይም ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግና የሚጨቁን እንዲሆን አላደረገውም። (ማቴዎስ 9:10-13፤ 21:31, 32፤ ሉቃስ 7:36-48፤ 15:1-32፤ 18:9-14) ኢየሱስ ከሌሎች ብዙ የሚጠብቅ አልነበረም። በሌሎች ላይ ሸክም ከመጫን ይልቅ “እናንተ ደካሞች . . . ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ” በማለት ተናግሯል። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን ‘የዋህና በልቡም ትሑት’ እንዲሁም ቀንበሩ ልዝብና ሸክሙም ቀሊል ሆኖ አግኝተውታል።—ማቴዎስ 11:28-30
በወንጌሎች ውስጥ የኢየሱስን ባሕርይ በተመለከተ እውነቱ በማያሻማ መንገድ ተገልጿል። አራት የተለያዩ ግለሰቦች አንድ እንግዳ የሆነ ገጸ ባሕርይ ፈጥረው በአራት የተለያዩ ታሪኮች ላይ ስለ እርሱ ወጥ የሆነ ዘገባ ሊያቀርቡ ይችላሉ ማለት ያዳግታል። ባለ ታሪኩ በገሃዱ ዓለም ኖሮ የማያውቅ ከሆነ አራት የተለያዩ ጸሐፊዎች ያንኑ ሰው በተመሳሳይ መንገድ ይገልጹታል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው።
ታሪክ ጸሐፊው ማይክል ግራንት አንድ አእምሮን የሚያመራምር ጥያቄ አንስተዋል:- “በመጥፎ ስም የሚታወቁትን ጨምሮ ከሁሉም ዓይነት ሴቶች ጋር መልካም ግንኙነት የነበረው ውብ ጎልማሳ፣ አንዳችም የስሜታዊነት፣ መስሎ የማደር ወይም አጉል ተብለጭልጮ የመታየት ዝንባሌ የማይንጸባረቅበት፣ ነገር ግን በሁሉም አጋጣሚ ራሱን ሆኖ የሚመላለስ ጠንካራ ስብዕና ያለው ሰው ስለመሆኑ ሁሉም ወንጌሎች ያላንዳች የሐሳብ መዘበራረቅ እንዴት ሊናገሩ ይችላሉ?” ትክክለኛው መልስ እንዲህ ዓይነት ሰው በእርግጥ ስለነበረና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው መሠረት ስለተመላለሰ ነው የሚል ነው።
እውነተኛው ኢየሱስና የወደፊት ሕይወትህ
መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈውን ሕይወት በትክክል የሚገልጽ ከመሆኑም በላይ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ የአምላክ አንድያ ልጅና “ከፍጥረት ሁሉ በኩር” ሆኖ ይኖር እንደነበረም ይገልጻል። (ቆላስይስ 1:15) ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት አምላክ የሰማያዊ ልጁን ሕይወት ወደ አንዲት ድንግል አይሁዳዊት ማህጸን በማዛወር ሰው ሆኖ እንዲወለድ አደረገ። (ማቴዎስ 1:18) ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት በጭንቀት ለተዋጠው የሰው ዘር የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ የሆነውን የአምላክ መንግሥት ከማወጁም በተጨማሪ ደቀ መዛሙርቱም የስብከት ሥራውን እንዲቀጥሉ አሰልጥኗቸዋል።—ማቴዎስ 4:17፤ 10:5-7፤ 28:19, 20
ኢየሱስ በ33 እዘአ ኒሳን 14 (ሚያዝያ 1 ገደማ) ዓመፅ አነሳስቷል የሚል ክስ ቀርቦበት ከተያዘና ችሎት ፊት ከቀረበ በኋላ ተሰቅሎ እንዲገደል ተደረገ። (ማቴዎስ 26:18-20, 48–ማቴ 27:50) የኢየሱስ ሞት አማኝ የሆኑትን የሰው ዘሮች ከኃጢአት በማላቀቅና በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት የሚያገኝበትን መንገድ በመክፈት ቤዛ ሆኖ አገልግሏል። (ሮሜ 3:23, 24፤ 1 ዮሐንስ 2:2) ኢየሱስ ኒሳን 16 ከሞት ከተነሣ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወደ ሰማይ አርጓል። (ማርቆስ 16:1-8፤ ሉቃስ 24:50-53፤ ሥራ 1:6-9) ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ በይሖዋ የተሾመ ንጉሥ በመሆኑ አምላክ ለሰው ልጆች የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ ለማስፈጸም የሚያስችል ሙሉ ሥልጣን አለው። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ሉቃስ 1:32, 33) አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን የአምላክን ዓላማዎች በማስፈጸም ረገድ ወሳኝ ሚና የሚጫወት ሰው እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን በእሱነቱ ተቀብለውታል። ተስፋ የተደረገበት መሲህ ወይም ክርስቶስ መሆኑን እንዲሁም ወደ ምድር የተላከው የይሖዋን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥና ለሰው ልጆች ቤዛ ሆኖ ለመሞት መሆኑን አምነው ተቀብለዋል። (ማቴዎስ 20:28፤ ሉቃስ 2:25-32፤ ዮሐንስ 17:25, 26፤ 18:37) ስለ ማንነቱ እርግጠኞች ባይሆኑ ኖሮ ከባድ ስደት እንደሚያጋጥማቸው እያወቁ ደቀ መዛሙርቱ ለመሆን አይገፋፉም ነበር። ኢየሱስ “አሕዛብን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት የሰጣቸውን ትእዛዝ በድፍረትና በቅንዓት ፈጽመዋል።—ማቴዎስ 28:19
ዛሬም በሚልዮን የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸውና በቂ እውቀት ያካበቱ ክርስቲያኖች ኢየሱስ አፈ ታሪክ የወለደው ግለሰብ አለመሆኑን ይገነዘባሉ። በሰማይ የተቋቋመውና በቅርቡ የምድርን ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠረው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደሆነ አድርገው ይቀበሉታል። ይህ መለኮታዊ መንግሥት ከዓለም ችግሮች የሚያላቅቀን በመሆኑ ታላቅ የምሥራች ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች “ይህ[ን] የመንግሥት ወንጌል” ለሌሎች በማወጅ ይሖዋ የመረጠውን ንጉሥ በታማኝነት እንደሚደግፉ ያሳያሉ።—ማቴዎስ 24:14
የሕያው አምላክ ልጅ በሆነው በክርስቶስ በኩል የተደረገውን የመንግሥት ዝግጅት የሚደግፉ ሁሉ ዘላለማዊ በረከቶችን ያገኛሉ። አንተም የእነዚህ በረከቶች ተቋዳሽ ልትሆን ትችላለህ! የዚህ መጽሔት አታሚዎች እውነተኛውን ኢየሱስ እንድታውቀው ሊረዱህ ዝግጁ ናቸው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የወንጌል ዘገባዎችን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ —የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለ መጽሐፍ ከምዕራፍ 5 እስከ 7 ተመልከት።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ሌሎች የሰጡት አስተያየት
“የናዝሬቱ ኢየሱስ ዓለም ካፈራቻቸው ታላላቅ አስተማሪዎች አንዱ እንደሆነ አድርጌ እመለከተዋለሁ። . . . ሂንዱዎች የኢየሱስን ትምህርቶች በአክብሮት ካላጠኑ በስተቀር የተሟላ ሕይወት ሊኖራቸው እንደማይችል ላስገነዝባቸው እወዳለሁ።”—ሞሃንዳስ ኬ ጋንዲ፣ ዘ ሜሴጅ ኦቭ ጂሰስ ክራይስት
“በዓይነቱ ልዩ የሆነ ስብዕና፣ የተሟላ ተሰጥኦና የማይለዋወጥ ባሕርይ ያለው፣ ፍጹም እንዲሁም ሰብዓዊ ፍጡር ቢሆንም እንኳ ከሁሉም ሰብዓዊ ፍጥረታት የሚበልጥ እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸ ገጸ ባሕርይ የፈጠራ ሰው አሊያም ምናብ የወለደው ሊሆን አይችልም። . . . የኢየሱስን ዓይነት ገጸ ባሕርይ ለመፍጠር ከኢየሱስ የበለጠ ሰው ያስፈልጋል።” ፊሊፕ ሻፍ፣ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ክርስቺያን ቸርች
“በአንድ ትውልድ ውስጥ የኖሩ ጥቂት ተራ ሰዎች ይህን የመሰለ ከፍተኛ የመለወጥ ኃይልና ተወዳጅነት ያለው ሰው፣ ይህን የመሰለ ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃና ሰብዓዊ ወንድማማችነት ለመፈልሰፍ ከቻሉ በወንጌሎች ውስጥ ከተጻፉት ተአምራት በሙሉ የበለጠ እምነት የሚጠይቅ ትልቅ ተአምር ይሆናል።” ዊል ዱራንት፣ ሲዛር ኤንድ ጂሰስ
“ሃይማኖቶችን ለመመሥረት ጥረት አድርገው ያልተሳካላቸው በእውን የነበሩ ብዙ ሰዎች ከመኖራቸው አንጻር ሲታይ በጥንት ዘመን የሰዎችን ስሜት ለመማረክ ሲባል የተፈጠረ ገጸ ባሕርይ እንደሆነ የሚነገርለት ሰው ይህን ያህል ዓለምን ያጥለቀለቀ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ እንዲካሄድ ምክንያት ይሆናል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነው።” ግሬግ ኢስተርብሩክ፣ ቢሳይድ ስቲል ዋተርስ
‘የሥነ ጽሑፍ ምሁር እንደመሆኔ መጠን ወንጌሎች ምንም ይሁኑ ምን አፈ ታሪክ አለመሆናቸውን ሙሉ በሙሉ አምኛለሁ። አቀራረባቸው አፈ ታሪክ አያሰኛቸውም። አብዛኛውን የኢየሱስ የሕይወት ታሪክ አናውቅም። አፈ ታሪክ የሚጽፉ ሰዎች ደግሞ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዲፈጠር አያደርጉም።” ሲ ኤስ ሌዊስ፣ ጎድ ኢን ዘ ዶክ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወንጌሎች ኢየሱስ በተለያዩ ወቅቶች የተሰማውን ስሜት ይገልጻሉ