ክርስቲያኖች እርስ በርስ መደጋገፍ አለባቸው
“እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናል።”—ኤፌሶን 4:25
1. አንድ ኢንሳይክሎፔዲያ የሰውን አካል በተመለከተ ምን ብሏል?
የሰው አካል እጅግ አስደናቂ የፍጥረት ሥራ ነው! ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔዲያ እንዲህ ይላል:- “ሰዎች አካላችን እስከዛሬ ከተሠሩት ሁሉ እጅግ አስደናቂ ማሽን እንደሆነ ይናገራሉ። እርግጥ ነው፣ የሰው አካል ማሽን አይደለም። ሆኖም በብዙ መንገዶች ከማሽን ጋር ሊመሳሰል ይችላል። እንደ ማሽን ሁሉ ሰውነትም በበርካታ ክፍሎች የተዋቀረ ነው። እንደ ማሽን ክፍሎች ሁሉ እያንዳንዱ የሰውነት ክፍልም ከሌላው የተለየ ሥራ ያከናውናል። ሆኖም ሁሉም ክፍሎች ተቀናጅተው አንድ ላይ ስለሚሠሩ ሰውነታችን ወይም ማሽኑ ያለ ችግር ይንቀሳቀሳል።”
2. የሰው አካል ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
2 አዎን፣ የሰው አካል ብዙ ክፍሎች ወይም ብልቶች ያሉት ሲሆን እያንዳንዳቸው አንድ አስፈላጊ ነገር ያሟላሉ። ጥቅም የሌለው የደም ሥር፣ ጡንቻ ወይም ሌላ የሰውነት ብልት የለም። በተመሳሳይም እያንዳንዱ የክርስቲያን ጉባኤ አባል ለጉባኤው መንፈሳዊ ጤንነትና ውበት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አለ። (1 ቆሮንቶስ 12:14-26) አንድ የጉባኤ አባል ከሌሎቹ እንደሚበልጥ ሆኖ ሊሰማው እንደማይገባ ሁሉ ማንም ቢሆን እንደማያስፈልግ ወይም እንደማይጠቅም አድርጎ ራሱን መቁጠር አይገባውም።—ሮሜ 12:3
3. ኤፌሶን 4:25 ክርስቲያኖች እርስ በርስ መደጋገፍ እንዳለባቸው የሚያሳየው እንዴት ነው?
3 የሰውነት ብልቶች እርስ በርስ እንደሚደጋገፉ ሁሉ ክርስቲያኖችም አንዳቸው የሌላው ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ የተቀቡ የእምነት ባልንጀሮቹን “ውሸትን አስወግዳችሁ፣ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ” ብሏቸዋል። (ኤፌሶን 4:25) ክርስቲያኖች ‘እርስ በርሳቸው ብልቶች’ ስለሆኑ ‘የክርስቶስ አካል’ በሆኑት በመንፈሳዊ እስራኤል አባላት መካከል በእውነት ላይ የተመሠረተ የሐሳብ ግንኙነትና የተሟላ የትብብር መንፈስ ይታያል። አዎን፣ እያንዳንዳቸው የሌሎቹ ክፍል ናቸው። (ኤፌሶን 4:11-13) ከእነሱ ጋር በደስታ የሚተባበሩት ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም እውነተኛና ከልባቸው ድጋፍ የሚሰጡ ናቸው።
4. አዲሶችን በምን መንገዶች መርዳት ይቻላል?
4 ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በየዓመቱ ይጠመቃሉ። ወደ ‘ጉልምስና እንዲደርሱም’ ሌሎቹ የጉባኤው አባላት በደስታ ይረዷቸዋል። (ዕብራውያን 6:1-3) ለሚያቀርቧቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች መልስ በመስጠትና በአገልግሎት በማሰልጠን ሊረዷቸው ይችላሉ። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ዘወትር ተሳትፎ በማድረግ ረገድ ጥሩ ምሳሌ በመሆን አዲሶችን መርዳት እንችላለን። መከራ በሚደርስባቸው ጊዜ ማበረታቻ ወይም ማጽናኛ መስጠትም እንችላለን። (1 ተሰሎንቄ 5:14, 15) ሌሎች “በእውነት እንዲሄዱ” መርዳት የምንችልባቸውን መንገዶች መፈለግ አለብን። (3 ዮሐንስ 4) ወጣቶችም ሆን በዕድሜ የበሰልን፣ በእውነት መንገድ በቅርቡ መጓዝ የጀመርንም ሆን ለረጅም ዓመታት የተጓዝን የእምነት ባልንጀሮቻችን መንፈሳዊ ደኅንነት እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። ይህም የእኛ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ያሳያል።
አስፈላጊውን እርዳታ ሰጥተዋል
5. አቂላና ጵርስቅላ ጳውሎስን የረዱት በምን መንገድ ነው?
5 የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በመርዳት ደስታ ከሚያገኙት መካከል ክርስቲያን ባልና ሚስቶች ይገኙበታል። ለምሳሌ ያህል አቂላ እና ሚስቱ ጵርስቅላ ለጳውሎስ ድጋፍ ሰጥተውታል። በቤታቸው አሳርፈውታል፣ ድንኳን በመስፋት አብረውት ሠርተዋል እንዲሁም በቆሮንቶስ የተቋቋመውን አዲስ ጉባኤ በማጠናከር ረድተውታል። (ሥራ 18:1-4) አልፎ ተርፎም ታሪኩ ባይገለጽልንም ለጳውሎስ ሲሉ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠዋል። ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች “በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውኝ ለሚሠሩ ለጵርስቅላና ለአቂላ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ እነርሱም ስለ ነፍሴ ነፍሳቸውን ለሞት አቀረቡ፣ የአሕዛብም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የሚያመሰግኑአቸው ናቸው እንጂ እኔ ብቻ አይደለሁም” ብሎ በጻፈ ጊዜ እነሱም ሮም ውስጥ ነበሩ። (ሮሜ 16:3, 4) እንደ አቂላና ጵርስቅላ ሁሉ በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችም በተለያዩ መንገዶች ጉባኤዎችን ያንጻሉ እንዲሁም የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ይረዳሉ። አንዳንድ ጊዜም ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች በአሳዳጆች እጅ ጭካኔ የተሞላበት ድብደባ ወይም ግድያ እንዳይፈጸምባቸው አሳልፈው ላለመስጠት ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ይጥላሉ።
6. አጵሎስ ምን ዓይነት እርዳታ ተሰጥቶታል?
6 አቂላና ጵርስቅላ የኤፌሶንን ሰዎች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተምር የነበረውን አንደበተ ርቱዕ አስተማሪ አጵሎስንም ረድተውታል። በዚህ ጊዜ አጵሎስ የሚያውቀው በቃል ኪዳኑ ሕግ ላይ ለተፈጸመው ኃጢአት ንስሐ መግባትን የሚያመለክተውን የዮሐንስን ጥምቀት ብቻ ነበር። አቂላና ጵርስቅላ፣ አጵሎስ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ስለተገነዘቡ “የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል ገለጡለት።” ክርስቲያናዊ ጥምቀት ውኃ ውስጥ መጥለቅንና መንፈስ ቅዱስ መቀበልን እንደሚያጠቃልል አስረድተውት መሆን አለበት። አጵሎስ የተማረውን በሥራ ላይ አውሏል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በአካይያ “አምነው የነበሩትን በጸጋ እጅግ ይጠቅማቸው ነበር፤ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ከመጻሕፍት እየገለጠ ለአይሁድ በሁሉ ፊት በጽኑ ያስረዳቸው ነበርና።” (ሥራ 18:24-28) የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚሰጧቸው ሐሳቦች አብዛኛውን ጊዜ በአምላክ ቃል ላይ ያለን ግንዛቤ እንዲያድግ ሊረዳን ይችላል። በዚህ ረገድም እርስ በርስ መደጋገፍ ይኖርብናል።
ቁሳዊ እርዳታ መስጠት
7. የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች የእምነት ባልንጀሮቻቸው ቁሳዊ እርዳታ ባስፈለጋቸው ጊዜ ምን አድርገዋል?
7 የፊልጵስዩስ ጉባኤ አባላት ጳውሎስን በጥልቅ ይወድዱት የነበረ ከመሆኑም በላይ በተሰሎንቄ እያለ የሚያስፈልጉትን ቁሳዊ ነገሮች ልከውለት ነበር። (ፊልጵስዩስ 4:15, 16) በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ወንድሞች ቁሳዊ እርዳታ ባስፈለጋቸው ጊዜ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ከአቅማቸው በላይ እንኳ ሳይቀር ለመስጠት ዝግጁነታቸውን አሳይተው ነበር። ጳውሎስ በፊልጵስዩስ የሚኖሩ ወንድሞቹና እህቶቹ ባሳዩት ግሩም ዝንባሌ ልቡ በጥልቅ ከመነካቱ የተነሳ ለሌሎች አማኞች በምሳሌነት ጠቅሷቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 8:1-6
8. አፍሮዲጡ ምን ዓይነት ዝንባሌ አሳይቷል?
8 ጳውሎስ ታስሮ በነበረበት ወቅት የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ቁሳዊ እርዳታ ከመላካቸውም በላይ አፍሮዲጡንም ልከውለታል። ጳውሎስ “እናንተ ልትሰጡኝ ያልቻላችሁትን አገልግሎት [አፍሮዲጡ] ለማሟላት ሲል ለሕይወቱ እንኳ ሳይሳሳ፣ ለክርስቶስ ሥራ ከሞት አፋፍ ደርሶ ነበርና” ብሏል። (ፊልጵስዩስ 2:25-30 አ.መ.ት፤ 4:18) አፍሮዲጡ ሽማግሌ ይሁን ወይም የጉባኤ አገልጋይ ምንም የምናውቀው ነገር የለም። ይሁን እንጂ የራሱን ጥቅም የሚሠዋና ሌሎችን ለመርዳት ፈቃደኛ የሆነ ክርስቲያን ነበር። ጳውሎስ የእሱ እርዳታ አስፈልጎት ነበር። በጉባኤያችሁ ውስጥ አፍሮዲጡን የመሰለ ክርስቲያን ይኖር ይሆን?
‘የብርታት ምንጭ’ ነበሩ
9. አርስጥሮኮስ በምን ረገድ ምሳሌ ይሆነናል?
9 እንደ አቂላ፣ ጵርስቅላና አፍሮዲጡ የመሳሰሉ አፍቃሪ ወንድሞችና እህቶች በማንኛውም ጉባኤ ውስጥ ከፍ ተደርገው ይታያሉ። አንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቻችን ደግሞ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን ክርስቲያኑን አርስጥሮኮስን ይመስሉ ይሆናል። እሱና ሌሎች ክርስቲያኖች ‘የብርታት ምንጭ’ መሆናቸውን አሳይተዋል። ይህንንም ያደረጉት ማጽናኛ ወይም ጠቃሚ የሆነ መሠረታዊ እርዳታ በመስጠት ሊሆን ይችላል። (ቆላስይስ 4:10, 11 NW ) አርስጥሮኮስ ለጳውሎስ እርዳታ በመስጠት በችግር ጊዜ የማይከዳ ወዳጅ መሆኑን አስመስክሯል። ምሳሌ 17:17 ላይ የተጠቀሰው ዓይነት ሰው ነበር:- “ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል።” ሁላችንም ለክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ‘የብርታት ምንጭ’ ለመሆን ጥረት ማድረግ አይገባንም? በተለይ መከራ ለሚደርስባቸው ክርስቲያኖች የእርዳታ እጃችንን መዘርጋት ይገባናል።
10. ጴጥሮስ ለክርስቲያን ሽማግሌዎች ምን ምሳሌ ትቷል?
10 በተለይ ደግሞ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለመንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው የብርታት ምንጭ መሆን ይገባቸዋል። ክርስቶስ ሐዋርያው ጴጥሮስን “ወንድሞችህን አጽና” ብሎታል። (ሉቃስ 22:32) ጴጥሮስ በተለይ ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ እንደ ዓለት የጠነከሩ ባሕርያትን በማንጸባረቁ ወንድሞቹን ማጽናት ችሏል። ሽማግሌዎች፣ የእምነት ባልንጀሮቻችሁ የእናንተ ድጋፍ ስለሚያስፈልጋቸው በተቻላችሁ መጠን በፈቃደኝነትና በርኅራኄ ወንድሞቻችሁን አጽኑ።—ሥራ 20:28-30፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3
11. የጢሞቴዎስን ባሕርይ መመርመራችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
11 የጳውሎስ የጉዞ ባልደረባ የነበረው ጢሞቴዎስ ለሌሎች ክርስቲያኖች በጥልቅ የሚያስብ ሽማግሌ ነበር። ጢሞቴዎስ አንዳንድ የጤና እክሎች የነበሩበት ቢሆንም እንኳ ጽኑ እምነት አሳይቷል፤ እንዲሁም ‘ከጳውሎስ ጋር ለወንጌል አገልግሏል።’ ከዚህም የተነሳ ሐዋርያው ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች “እንደ እርሱ ያለ፣ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ፣ ማንም የለኝም” ለማለት ችሏል። (ፊልጵስዩስ 2:20, 22፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:23፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:5) እኛም የጢሞቴዎስ ዓይነት መንፈስ በማሳየት አብረውን ይሖዋን ለሚያመልኩ ክርስቲያኖች በረከት መሆን እንችላለን። እርግጥ፣ ያሉብንን ሰብዓዊ ድክመቶችና የሚያጋጥሙንን ልዩ ልዩ ፈተናዎች በጽናት መወጣት አለብን። ሆኖም ጠንካራ እምነት እንዲሁም ለመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፍቅራዊ አሳቢነት ማሳየት እንችላለን፤ ግዴታችንም ነው። የእኛ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ምንጊዜም መርሳት የለብንም።
ለሌሎች አሳቢነት ያሳዩ ሴቶች
12. ዶርቃ ከተወችው ምሳሌ ምን ልንማር እንችላለን?
12 ለሌሎች አሳቢነት ካሳዩ ፈሪሃ አምላክ ከነበራቸው ሴቶች መካከል ዶርቃ ትገኝበታለች። ዶርቃ በሞተች ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ጴጥሮስን አስጠርተው ወደ ሰገነት አወጡት። እዚያም “መበለቶችም ሁሉ እያለቀሱ ዶርቃ ከእነርሱ ጋር ሳለች ያደረገቻቸውን ቀሚሶችንና ልብሶችን ሁሉ እያሳዩት በፊቱ ቆሙ።” ዶርቃ ከሞት የተነሳች ሲሆን ‘መልካም ነገር የሞላባት ሆና ምጽዋት ማድረጓን’ እንደቀጠለች አያጠራጥርም። ዛሬ ባለው የክርስቲያን ጉባኤም እንደ ዶርቃ ለሌሎች ልብስ የሚሰፉ ወይም ፍቅራዊ ደግነትን የሚያሳዩ ሴቶች ይገኛሉ። እርግጥ ነው፣ በአንደኛ ደረጃ የሚያከናውኑት መልካም ሥራ መንግሥቱን መስበክና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መካፈል ነው።—ሥራ 9:36-42፤ ማቴዎስ 6:33፤ 28:19, 20
13. ልድያ ለክርስቲያን ባልንጀሮቿ አሳቢነት ያሳየችው እንዴት ነው?
13 ፈሪሃ አምላክ የነበራት ልድያ ለሌሎች አሳቢነት የምታሳይ ነበረች። የትያጥሮን ተወላጅ ስትሆን ጳውሎስ በ50 እዘአ በፊልጵስዩስ በሰበከበት ወቅት በዚያ ትኖር ነበር። ልድያ ወደ ይሁዲነት እምነት የተለወጠች ሳትሆን አትቀርም። ሆኖም በፊልጵስዩስ የነበሩት አይሁድ ጥቂት ከመሆናቸውም በላይ በከተማው ውስጥ ምኩራብ አልነበረም። ሐዋርያው ለእሷና ለአምላክ ያደሩ ለነበሩ ለሌሎች ሴቶች ምሥራቹን የሰበከላቸው ወንዝ አጠገብ ለአምልኮ ተሰብስበው በነበረበት ወቅት ነው። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት። እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ:- በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፣ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን።” (ሥራ 16:12-15) ልድያ ለሌሎች ደግነት የማድረግ ፍላጎት ስለነበራት ጳውሎስና አብረውት ያሉት ወንድሞች እሷ ቤት እንዲያርፉ ግድ ብላቸዋለች። በዛሬው ጊዜ ደግና አፍቃሪ የሆኑ ክርስቲያኖች ተመሳሳይ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ሲያሳዩን ምንኛ አመስጋኞች ነን!—ሮሜ 12:13፤ 1 ጴጥሮስ 4:9
ወጣቶች—እናንተም ታስፈልጉናላችሁ
14. ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕፃናት ምን አመለካከት ነበረው?
14 የክርስቲያን ጉባኤን ያቋቋመው ደግና አዛኝ የሆነው የአምላክ ልጅ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። አፍቃሪና ሩኅሩኅ ስለሆነ ሰዎች ከእሱ ጋር ሲሆኑ ደስ ይላቸው ነበር። በአንድ ወቅት አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ኢየሱስ ይዘው ሲመጡ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ እንዳይቀርቡ ከለከሏቸው። ኢየሱስ ግን “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና። እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አላቸው።” (ማርቆስ 10:13-15) የመንግሥቱን በረከቶች ለመውረስ እንደ ሕፃናት ትሑትና እሺ ባዮች መሆን አለብን። ኢየሱስ ሕፃናቱን አቅፎ በመባረክ ለእነሱ ያለውን ፍቅር አሳይቷል። (ማርቆስ 10:16) በዛሬው ጊዜ ስላላችሁት ልጆችስ ምን ማለት ይቻላል? በጉባኤው ውስጥ ተወዳጅና ተፈላጊ ስለመሆናችሁ ፈጽሞ አትጠራጠሩ።
15. ስለ ኢየሱስ ሕይወት ከሚናገረው ከሉቃስ 2:40-52 ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? ለልጆችስ የሚሆን ምን ምሳሌ ትቷል?
15 ኢየሱስ ገና ልጅ ሳለ ለአምላክና ለቅዱሳን ጽሑፎች ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። የ12 ዓመት ልጅ እያለ ከወላጆቹ ከዮሴፍና ከማርያም ጋር ሆኖ የማለፍን በዓል ለማክበር ከመኖሪያቸው ከናዝሬት ተነስተው ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዙ። ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ወላጆቹ ኢየሱስ አብረዋቸው ከሚጓዙት ሰዎች መካከል እንደሌለ አወቁ። በመጨረሻም በቤተ መቅደሱ ከሚገኙት አዳራሾች በአንዱ ውስጥ ተቀምጦ የአይሁድ መምህራንን ሲያዳምጥና ሲጠይቅ አገኙት። ኢየሱስ፣ ዮሴፍና ማርያም የት ሊያገኙት እንደሚችሉ አለማወቃቸው አስገርሞት “በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?” ሲል ጠየቃቸው። አብሯቸው ወደ ቤት ተመለሰ፣ ይታዘዛቸውም ነበር እንዲሁም በጥበብና በአካልም ያድግ ነበር። (ሉቃስ 2:40-52) ኢየሱስ በመካከላችን ለሚገኙ ልጆች ምንኛ ግሩም ምሳሌ ትቶላቸዋል! በእርግጥም ወላጆቻቸውን መታዘዝና መንፈሳዊ ነገሮች የመማር ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል።—ዘዳግም 5:16፤ ኤፌሶን 6:1-3
16. (ሀ) ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ እያስተማረ ሳለ አንዳንድ ልጆች ምን ብለው ተናገሩ? (ለ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣት ክርስቲያኖች ምን የማድረግ መብት አላቸው?
16 ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን በትምህርት ቤት እንዲሁም ከወላጆቻችሁ ጋር ከቤት ወደ ቤት እየሄዳችሁ ስለ ይሖዋ ትመሰክሩ ይሆናል። (ኢሳይያስ 43:10-12፤ ሥራ 20:20, 21) ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ቀናት በፊት በቤተ መቅደሱ ውስጥ እየመሰከረና ሰዎችን እየፈወሰ በነበረበት ጊዜ አንዳንድ ልጆች “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ” በማለት ጮኸዋል። የካህናት አለቆችና ጻፎች ይህን ሲሰሙ ተናድደው “እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን?” ሲሉ ተቃውሞ አሰሙ። ኢየሱስ “እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን?” ሲል መለሰላቸው። (ማቴዎስ 21:15-17) እንደነዚህ ልጆች ሁሉ በጉባኤ ውስጥ የምትገኙ ወጣቶችም አምላክንና ልጁን የማወደስ ታላቅ መብት አላችሁ። የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሆናችሁ ከጎናችን ቆማችሁ ስትሠሩ ማየት እንፈልጋለን።
መከራ በሚከሰትበት ጊዜ
17, 18. (ሀ) ጳውሎስ በይሁዳ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ገንዘብ እንዲዋጣ ያስተባበረው ለምን ነበር? (ለ) በይሁዳ ለሚኖሩ አማኞች በፈቃደኝነት የተሰበሰበው መዋጮ ከአይሁድና ከአሕዛብ ለመጡ ክርስቲያኖች ምን ትርጉም ነበረው?
17 ሁኔታችን ምንም ይሁን ምን ችግር የደረሰባቸው ክርስቲያን ባልንጀሮቻችንን እንድንረዳቸው ፍቅር ይገፋፋናል። (ዮሐንስ 13:34, 35፤ ያዕቆብ 2:14-17) ጳውሎስ ከአካይያ፣ ከገላትያ፣ ከመቄዶንያና በእስያ ክልል ከሚገኙ ጉባኤዎች እርዳታ እንዲያሰባስብ ያነሳሳው በይሁዳ ለሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች የነበረው ፍቅር ነው። በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ደቀ መዛሙርት የደረሰባቸው ስደት፣ የሕዝብ ዓመፅና ረሐብ “መከራ፣” “ጭንቀት” እና ‘የገንዘብ ንጥቂያ’ እንዳስከተለባቸው ጳውሎስ ገልጿል። (ዕብራውያን 10:32-34፤ ሥራ 11:27–12:1) በመሆኑም በይሁዳ ለሚገኙ ችግረኛ ክርስቲያኖች ገንዘብ እንዲዋጣ አስተባብሯል።—1 ቆሮንቶስ 16:1-3፤ 2 ቆሮንቶስ 8:1-4, 13-15፤ 9:1, 2, 7
18 በይሁዳ ለሚኖሩ ቅዱሳን በፈቃደኝነት የተሰጠው መዋጮ ከአይሁድና ከአሕዛብ በመጡ የይሖዋ አምላኪዎች መካከል ጠንካራ የወንድማማች አንድነት መኖሩን ያረጋግጣል። በተጨማሪም ከአሕዛብ የመጡ ክርስቲያኖች ገንዘብ አዋጥተው መላካቸው የእምነት ባልንጀሮቻቸው ከሆኑት የይሁዳ ክርስቲያኖች ላገኙት መንፈሳዊ ብርሃን አመስጋኝነታቸውን እንዲያሳዩ አስችሏቸዋል። በመሆኑም በቁሳዊም ሆነ በመንፈሳዊ ያላቸውን ተካፍለዋል። (ሮሜ 15:26, 27) በዛሬው ጊዜ በችግር ላይ ለወደቁ የእምነት ባልንጀሮቻችን መዋጮ የምናደርገው በፈቃደኝነትና በፍቅር ተነሳስተን ነው። (ማርቆስ 12:28-31) በዚህ ረገድም አንዳችን የሌላው ድጋፍ ያስፈልገናል፤ ይህም በመካከላችን እኩልነት እንዲኖርና ‘ጥቂት ያለው እንዳይጎድልበት’ ለማድረግ ያስችላል።—2 ቆሮንቶስ 8:15
19, 20. የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት የይሖዋ ሕዝቦች እንዴት እርዳታ እንደሚለግሱ የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።
19 ክርስቲያኖች እርስ በርስ መደጋገፍ እንዳለባቸው ስለምንገነዘብ በእምነት ለሚዛመዱን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ ለመስጠት ዝግጁ ነን። ለምሳሌ ያህል በ2001 መባቻ ላይ ኤል ሳልቫዶር በከባድ የመሬት መንቀጥቀጥና መንሸራተት በተመታች ጊዜ የሆነውን ነገር ተመልከት። እንዲህ የሚል ዘገባ ወጥቶ ነበር:- “በመላው ኤል ሳልቫዶር ወንድሞች መልሶ የማቋቋም ሥራ ማካሄድ ጀመሩ። ከጓቲማላ፣ ከዩናይትድ ስቴትስና ከካናዳ የመጡ ወንድሞች እኛን ለመርዳት ተረባርበዋል . . . በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ500 የሚበልጡ ቤቶችና 3 የሚያማምሩ የመንግሥት አዳራሾች ተገንብተዋል። እነዚህ የራሳቸውን ጥቅም የሠዉ ወንድሞች በትጋት ያከናወኑት ሥራና በመካከላቸው የነበረው የትብብር መንፈስ ከፍተኛ ምስክርነት ለመስጠት አስችሏል።”
20 ከደቡብ አፍሪካ የመጣ አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “አብዛኛውን የሞዛምቢክ ክፍል ያወደመው ኃይለኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ በርካታ በሚሆኑ ክርስቲያን ወንድሞቻችን ላይም ጉዳት አስከትሏል። በሞዛምቢክ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ወንድሞች የሚያስፈልጓቸውን አብዛኞቹን ነገሮች ለማሟላት ዝግጅት አድርጓል። ይሁን እንጂ ለችግረኛ ወንድሞች የሚሰጡ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ የተለበሱ ልብሶች እንድንልክላቸው ጠየቁን። በሞዛምቢክ ለሚገኙ ወንድሞቻችን የሚላክ 12 ሜትር ርዝመት ያለው ዕቃ መያዣ ሙሉ ልብስ መሰብሰብ ችለናል።” አዎን፣ በዚህ ረገድም ቢሆን እርስ በርስ መደጋገፍ አለብን።
21. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
21 ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሁሉም የሰውነት ክፍሎች አስፈላጊ ናቸው። የክርስቲያን ጉባኤን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በጉባኤ ውስጥ ያሉት ሁሉ እርስ በርስ መደጋገፍ አለባቸው። በተጨማሪም በአንድነት ማገልገላቸውን መቀጠል አለባቸው። የሚቀጥለው ርዕስ እንዲህ ማድረግ የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ያብራራል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• በሰው አካልና በክርስቲያን ጉባኤ መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?
• የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች የእምነት ባልንጀሮቻቸው እርዳታ ባስፈለጋቸው ጊዜ ምን አድርገዋል?
• ክርስቲያኖች እርስ በርስ መደጋገፍ እንዳለባቸውና ይህንንም እንዳደረጉ የሚያሳዩ አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አቂላና ጵርስቅላ ለሌሎች አሳቢነት አሳይተዋል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ሕዝቦች መከራ በሚደርስበት ጊዜ ወንድሞቻቸውንም ሆነ ሌሎችን ይረዳሉ