ጸንታችሁ ቁሙ፣ የሕይወትንም ሩጫ አሸንፉ
ማዕበል የሚያናውጠውን ባሕር አቋርጠህ ማለፍ ቢኖርብህ በምን ዓይነት መርከብ መጓዝ ትመርጣለህ? በአሮጌ ጀልባ ወይስ በጥሩ ሁኔታ በተገነባ ጠንካራ መርከብ? ኃይለኛውን ሞገድ ያለ ችግር ማለፍ ስለሚያስችልህ መርከቡን እንደምትመርጥ የታወቀ ነው።
በዚህ ተነዋዋጭና አደገኛ ሥርዓት ውስጥ ስንኖር እንድንጨነቅ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ለምሳሌ ያህል ወጣቶች መላ ቅጥ የሌላቸው ሐሳቦችና ዝንባሌዎች በተስፋፉበት በዚህ ዓለም ውስጥ ግራ ሊጋቡና ስጋት ሊያድርባቸው ይችላል። በቅርቡ በክርስትና ጎዳና መመላለስ የጀመሩ አንዳንድ ግለሰቦች አሁንም ያለመረጋጋት ስሜት ይሰማቸው ይሆናል። ለብዙ ዓመታት አምላክን በጽናት ሲያገለግሉ የኖሩ አንዳንድ ታማኝ ክርስቲያኖች እንኳ የጠበቋቸው ነገሮች ሙሉ በሙሉ ሳይፈጸሙ መቅረታቸው ፈተና ሆኖባቸው ይሆናል።
እንዲህ ዓይነቶቹ ሁኔታዎች አዲስ አይደሉም። ሙሴን፣ ኢዮብንና ዳዊትን የመሳሰሉ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ግራ የተጋቡባቸው ጊዜያት ነበሩ። (ዘኍልቍ 11:14, 15፤ ኢዮብ 3:1-4፤ መዝሙር 55:4) ቢሆንም በአኗኗራቸው ለይሖዋ ያደሩ መሆናቸውን አሳይተዋል። እነርሱ የተዉት ግሩም ምሳሌ እኛም ጸንተን እንድንቆም የሚያበረታታን ቢሆንም ሰይጣን ዲያብሎስ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ከምናደርገው ሩጫ ሊያደናቅፈን ይፈልጋል። (ሉቃስ 22:31) ከአቋማችን ፍንክች ሳንል ‘በእምነት ጸንተን መቆም’ የምንችለው እንዴት ነው? (1 ጴጥሮስ 5:9) እንዲሁም የእምነት አጋሮቻችንን ማበርታት የምንችለው እንዴት ነው?
ይሖዋ ጸንተን እንድንቆም ይፈልጋል
ለይሖዋ ታማኞች ከሆንን ጸንተን እንድንቆም ምንጊዜም ይረዳናል። መዝሙራዊው ዳዊት በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም ተስፋውን በአምላክ ላይ ጥሎ ስለነበር “[ይሖዋ] ከጥፋት ጕድጓድ ከረግረግም ጭቃ አወጣኝ፣ እግሮቼንም በድንጋይ ላይ አቆማቸው፣ አረማመዴንም አጸና” በማለት ዘምሯል።—መዝሙር 40:2
ይሖዋ ‘መልካሙን የእምነት ገድል በመጋደል የዘላለም ሕይወትን አጥብቀን ለመያዝ’ የሚያስችለንን ብርታት ይሰጠናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:12) እንዲሁም ከአቋማችን ፍንክች ሳንል መንፈሳዊ ውጊያችንን በድል ለመወጣት የሚያስፈልገንን ሁሉ ያደርግልናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ወንድሞቹ ‘በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረቱ’ እንዲሆኑና ‘የዲያብሎስን ሽንገላ ለመቃወም የሚያስችላቸውን የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር እንዲለብሱ’ አሳስቧቸዋል። (ኤፌሶን 6:10-17) ጽናታችንን ሊፈታተነው የሚችለው ምንድን ነው? እንዲህ ዓይነቱንስ ተጽዕኖ እንዴት ልንቋቋመው እንችላለን?
አቋማችሁን እንድታላሉ ከሚያደርጉ ተጽዕኖዎች ተጠበቁ
የምናደርገው ማንኛውም ውሳኔ ውሎ አድሮ በክርስቲያናዊ አቋማችን ላይ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ማስታወሳችን አስፈላጊ ነው። ወጣቶች እንደ ሥራ፣ ተጨማሪ ትምህርትና ትዳር ያሉ ጉዳዮችን በተመለከተ ውሳኔ ማድረግ ይኖርባቸዋል። አዋቂዎችም የመኖሪያ አካባቢን መቀየርን ወይም ተጨማሪ ሥራ መያዝን በተመለከተ ውሳኔ ማድረግ ይኖርባቸው ይሆናል። የጊዜ አጠቃቀምንና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ በየዕለቱ ውሳኔዎች እናደርጋለን። አምላክን በማገልገል ጸንተን እንድንቆም የሚያስችለንን ውሳኔ ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል? ይሖዋን ለረጅም ዓመታት ያገለገለች አንዲት ክርስቲያን እንዲህ ብላለች:- “ማንኛውንም ውሳኔ ከማድረጌ በፊት ይሖዋ እንዲረዳኝ እጸልያለሁ። ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች፣ ከጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተመሠረቱ ጽሑፎች የምናገኛቸውን ምክሮች ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው የሚል እምነት አለኝ።”
ውሳኔዎችን ስናደርግ ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን መጠየቃችን ተገቢ ነው:- ‘ይህን ውሳኔ በማድረጌ ከአምስት ወይም ከአሥር ዓመት በኋላ ይቆጨኛል? ወይስ እደሰትበታለሁ? የማደርገው ውሳኔ በመንፈሳዊነቴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር ሳይሆን ለመንፈሳዊ እድገቴ አስተዋጽኦ የሚያበረክት እንዲሆን ጥረት አደርጋለሁ?’—ፊልጵስዩስ 3:16
አንዳንድ የተጠመቁ ክርስቲያኖች ለፈተና መሸነፋቸው ወይም የአምላክን ሕግ ለሚያስጥስ ሁኔታ ራሳቸውን ማጋለጣቸው የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖራቸው አድርጓል። ኃጢአት ሠርተው ንስሐ ባለመግባታቸው ምክንያት ከጉባኤ የተወገዱ አንዳንዶች ብዙ ጥረት አድርገው ከውገዳ ከተመለሱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በተመሳሳይ ኃጢአት እንደገና ይወገዳሉ። ይህ የሆነው ‘ክፉውን ነገር ለመጸየፍና፤ ከበጎ ነገር ጋር ለመተባበር’ እንዲረዳቸው ወደ ይሖዋ ስላልጸለዩ ይሆን? (ሮሜ 12:9፤ መዝሙር 97:10) ሁላችንም ብንሆን ‘ለእግራችን ቅን መንገድ ማድረግ’ ያስፈልገናል። (ዕብራውያን 12:13) ስለሆነም የማይዋዥቅ መንፈሳዊ አቋም እንዲኖረን ሊረዱን የሚችሉ አንዳንድ ነጥቦችን እስቲ እንመልከት።
ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ለመጽናት ይረዳናል
ለሕይወት የምናደርገው ሩጫ ወጥ የሆነ ፍጥነት እንዲኖረው የሚረዳን አንደኛው መንገድ በመንግሥቱ የስብከት ሥራ የላቀ ተሳትፎ ማድረግ ነው። አዎን፣ ልባችንና አእምሯችን የአምላክን ፈቃድ በማድረግና ወደፊት በምናገኘው የዘላለም ሕይወት ሽልማት ላይ እንዲያተኩር በመርዳት ረገድ ክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ይህን በሚመለከት ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል አሳስቧቸዋል:- “የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፣ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ [“ጸንታችሁ የምትቆሙ፣” አ.መ.ት ]፣ የማትነቃነቁም፣ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።” (1 ቆሮንቶስ 15:58) “ጸንቶ መቆም” ሲባል ‘ካሉበት ፍንክች አለማለት’ ማለት ነው። ‘አለመነቃነቅ’ ደግሞ ‘ሳይናወጡ ባሉበት መቆምን’ ሊያመለክት ይችላል። ስለሆነም በአገልግሎት ራሳችንን ማስጠመዳችን ወጥ የሆነ ክርስቲያናዊ አካሄድ እንድንከተል ሊረዳን ይችላል። ሌሎች ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁት መርዳት ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን ከማድረጉም ባሻገር ደስታ ያስገኝልናል።—ሥራ 20:35
በሚስዮናዊነትና በሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች ከ30 የሚበልጡ ዓመታት ያሳለፈች ፖውሊን የተባለች አንዲት ክርስቲያን “አገልግሎት ጥበቃ እንደሆነልኝ ይሰማኛል፤ ምክንያቱም ለሌሎች መመስከር እውነትን እንደያዝኩ ያረጋግጥልኛል” በማለት ተናግራለች። ለአምልኮ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትንና ትጋት የታከለበት የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግን በመሳሰሉ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች አዘውትሮ መካፈል ተመሳሳይ እምነት ለማዳበር ያስችላል።
ፍቅር ያለው የወንድማማች ማኅበር ለመጽናት ይረዳናል
በእውነተኛ አምላኪዎች የተገነባው ዓለም አቀፋዊ ድርጅት አካል መሆን ጸንቶ ለመቆም በእጅጉ ይረዳናል። የዚህ እርስ በእርስ የሚፋቀር ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር አባል መሆን ምንኛ መታደል ነው! (1 ጴጥሮስ 2:17) ሌሎች ወንድሞቻችንም በእምነት ጸንተው እንዲቆሙ መርዳት እንችላለን።
ቅን የነበረው ኢዮብ ለሌሎች ያበረከተውን እርዳታ ተመልከት። አጽናኝ ተብዬው ኤልፋዝ እንኳን “ቃልህ የሚሰናከለውን ያስነሣ ነበር፣ አንተም የሚብረከረከውን ጉልበት ታጸና ነበር” ብሎ ለማመን ተገድዷል። (ኢዮብ 4:4) እኛስ በዚህ ረገድ ምን እያደረግን ነው? በግለሰብ ደረጃ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አምላክን በማገልገል እንዲጸኑ የመርዳት ኃላፊነት አለብን። ከእነርሱ ጋር በአንድ ላይ በምንሆንበት ጊዜ “የደከሙትን እጆች አበርቱ፣ የላሉትንም ጉልበቶች አጽኑ” የሚሉትን ቃላት በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ማድረግ እንችላለን። (ኢሳይያስ 35:3) እንግዲያው ከክርስቲያን ወንድሞችህ ጋር ስትገናኝ አጋጣሚውን ተጠቅመህ እነርሱን ለማበረታታትና ለማጠናከር ለምን ጥረት አታደርግም? (ዕብራውያን 10:24, 25) ይሖዋን ለማስደሰት ሲሉ ለሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት ያለህን አድናቆት ለመግለጽ ጣል የምታደርጋቸው የምስጋና ቃላት የጀመሩትን የሕይወት ሩጫ በድል ለመወጣት በጽናት እንዲቀጥሉ ሊረዳቸው ይችላል።
ክርስቲያን ሽማግሌዎች አዳዲሶችን በማበረታታት የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ። ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችንና ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን በማካፈልና በመስክ አገልግሎት አብረዋቸው በመሥራት ይህን ማድረግ ይችላሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ሌሎችን ለማበረታታት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ሲያገኝ በሚገባ ይጠቀምባቸው ነበር። በሮም የሚገኙ ክርስቲያኖችን በመንፈሳዊ ለማጠናከር ሲል ወደዚያ የሚሄድበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቅ ነበር። (ሮሜ 1:11) በፊልጵስዩስ የሚኖሩ ወንድሞቹና እህቶቹ ‘ደስታውና አክሊሉ’ እንደሆኑ በመቁጠር ‘በጌታ ጸንተው እንዲቆሙ’ አሳስቧቸዋል። (ፊልጵስዩስ 4:1) የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ችግር እንደደረሰባቸው ሲሰማ ‘በመከራ ማንም እንዳይናወጥ እንዲያጸናቸውና እንዲመክራቸው’ ጢሞቴዎስን ወደ እነርሱ ልኮታል።—1 ተሰሎንቄ 3:1-3
ሐዋርያው ጳውሎስና ሐዋርያው ጴጥሮስ የእምነት ወንድሞቻቸው የሚያደርጉትን ታማኝነት የተሞላበት ጥረት ያደንቁ ነበር። (ቆላስይስ 2:5፤ 1 ተሰሎንቄ 3:7, 8፤ 2 ጴጥሮስ 1:12) እኛም በተመሳሳይ በወንድሞቻችን ድክመት ላይ ሳይሆን ባሏቸው ግሩም ባሕርያትና በአቋማቸው ጸንተው በመኖር ይሖዋን ለማስከበር በሚያደርጉት ተጋድሎ ላይ ትኩረት እናድርግ።
የሌሎች ጉድለት ብቻ የሚታየን ወይም መንቀፍ የሚቀናን ከሆነ አንዳንዶች በእምነት ጸንተው ለመቆም የሚያደርጉትን ትግል ይበልጥ እናከብድባቸዋለን። ወንድሞቻችን በዚህ ሥርዓት ውስጥ ‘የተጨነቁና የተጣሉ’ እንደሆኑ ማስታወሳችን ምንኛ የተገባ ነው! (ማቴዎስ 9:36) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መጽናኛና ማበረታቻ እናገኛለን ብለው ስለሚጠብቁ ሁላችንም የእምነት ወንድሞቻችንን ለማነጽና በእውነት ጸንተው እንዲቆሙ ለመርዳት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናድርግ።
አንዳንድ ጊዜ የጉባኤው አባላት ጽናታችንን የሚፈታተን ነገር ያደርጉብን ይሆናል። ሸካራ ንግግር ወይም ደግነት የጎደለው ድርጊት ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎት እንዲያስተጓጉልብን መፍቀድ ይኖርብናል? ማንም ጽኑ አቋማችንን እንዲያዳክምብን አንፍቀድ!—2 ጴጥሮስ 3:17
አምላክ የሰጠው ተስፋ ጸንተን እንድንቆም ይረዳናል
ይሖዋ በመንግሥቱ አገዛዝ አማካኝነት የወደፊቱን ጊዜ አስደሳች ለማድረግ የገባው ቃል እስከ መጨረሻው ድረስ ጸንተን እንድንኖር የሚያስችለንን ተስፋ ይሰጠናል። (ዕብራውያን 6:19) እንዲሁም አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች ምንጊዜም እንደሚፈጽም ያለን ትምክህት ‘ነቅተን እንድንኖርና፣ በእምነት ጸንተን እንድንቆም’ ይገፋፋናል። (1 ቆሮንቶስ 16:13፤ ዕብራውያን 3:6) አምላክ የገባው ቃል የሚፈጸምበት ጊዜ እንደዘገየ ሆኖ ሲሰማን እምነታችን ሊፈተን ይችላል። ስለዚህ በሐሰት ትምህርቶች ተታልለን ተስፋችንን እንዳናጣ ራሳችንን መጠበቃችን በእጅጉ አስፈላጊ ነው።—ቆላስይስ 1:23፤ ዕብራውያን 13:9
ይሖዋ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ እምነት ባለማሳደራቸው ምክንያት የጠፉት እስራኤላውያን ለእኛ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ሊሆኑን ይገባል። (መዝሙር 78:37) እንደ እነርሱ ከመሆን ይልቅ በዚህ የመጨረሻ ዘመን አምላክን በጥድፊያ ስሜት በማገልገል ጸንተን የምንቆም እንሁን። አንድ ተሞክሮ ያካበተ የጉባኤ ሽማግሌ “እያንዳንዱን ቀን የምኖረው የይሖዋ ታላቅ ቀን በቀጣዩ ዕለት እንደሚመጣ አድርጌ ነው” በማለት ተናግሯል።—ኢዩኤል 1:15
አዎን፣ ታላቁ የይሖዋ ቀን በጣም ቀርቧል። ይሁን እንጂ ወደ አምላክ እስከቀረብን ድረስ የሚያስፈራን ነገር አይኖርም። ከጽድቅ መሥፈርቶቹ ጋር ተስማምተን የምንኖርና ጸንተን የምንቆም ከሆነ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የምናደርገውን ሩጫ በድል ማጠናቀቅ እንችላለን!—ምሳሌ 11:19፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:12, 17-19
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያን ወንድሞችህ ጸንተው እንዲቆሙ ለመርዳት አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ እያደረግህ ነውን?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
The Complete Encyclopedia of Illustration/J. G. Heck