ሕሊናህ በሚገባ ሠልጥኗል?
“ስህተት መሆኑን ልቤ አውቆታል” ወይም “ያልከኝን ማድረግ አልችልም፤ አንድ የሆነ ስህተት እንዳለበት ቀልቤ ነግሮኛል” ብለህ ታውቃለህ? ይህ፣ አንድ ነገር ትክክል ወይም ስህተት መሆኑ እንዲታወቅህ አሊያም እንዲሰማህ የሚያደርግ እንዲሁም የሚከላከልልህ ወይም የሚከስህ የሕሊናህ “ድምፅ” ነው። አዎን፣ ሕሊና በተፈጥሮ ያገኘነው ነገር ነው።
የሰው ልጆች ከአምላክ ቢርቁም እንኳ ትክክልና ስህተት የሆነውን የመለየት ችሎታ አላቸው። ይህም የሆነው ሰው በአምላክ አምሳል በመፈጠሩና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ጥበብና ጽድቅን የመሰሉ አምላካዊ ባሕርያትን ለማንጸባረቅ በመቻሉ ነው። (ዘፍጥረት 1:26, 27) ይህን አስመልክቶ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ሕግ የሚያዝዘውን ነገር በተፈጥሮ ሲያደርጉ፣ ሕግ ባይኖራቸውም እነርሱ ለራሳቸው ሕግ ናቸው። ኅሊናቸው ስለሚመሰክር፣ ሐሳባቸው ስለሚከሳቸው፣ ደግሞም ስለሚከላከልላቸው የሕግ ትእዛዝ በልባቸው የተጻፈ መሆኑን ያሳያሉ።”a—ሮሜ 2:14, 15
ከመጀመሪያው ሰው አዳም የተወረሰው ይህ ተፈጥሯዊ የሥነ ምግባር ደንብ የትኛውም ዓይነት ዘርና ብሔር ላላቸው ሰዎች እንደ “ሕግ” ወይም የሥነ ምግባር መመሪያ በመሆን ያገለግላል። ይህ ራሳችንን መርምረን በራሳችን ላይ እንድንፈርድ የሚያደርግ ችሎታ ነው። (ሮሜ 9:1) አዳምና ሔዋን የአምላክን ሕግ በጣሱ ጊዜ መሸሸጋቸው እንዲህ ዓይነቱ ችሎታ እንደነበራቸው ያሳያል። (ዘፍጥረት 3:7, 8) ንጉሥ ዳዊት ሠራዊቱን በመቁጠር ኃጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ የተሰማው ስሜት ሕሊናችን እንዴት እንደሚሠራ የሚያሳይ ሌላው ምሳሌ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዳዊትን ኅሊናው እንደወቀሰው’ ይናገራል።—2 ሳሙኤል 24:1-10
ራስን መመርመርና የራስን የሥነ ምግባር አቋም መመዘን መቻል በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሚያስገኝ የንስሐ ዝንባሌ እንድናፈራ ይረዳናል። ንጉሥ ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ቀኑን ሙሉ ከመቃተቴ የተነሣ፣ ዝም ባልሁ ጊዜ፣ ዐጥንቶቼ ተበላሹ፤ ኀጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፤ በደሌንም አልሸሸግሁም፤ ደግሞም ‘መተላለፌን ለእግዚአብሔር እናዘዛለሁ’ አልሁ፤ አንተም የኀጢአቴን በደል፣ ይቅር አልህ።” (መዝሙር 32:3, 5) ስለሆነም ጥሩ ሕሊና ያለው ሰው ኃጢአት ሲሠራ ሕሊናው የአምላክን ይቅርታ ማግኘቱና መንገዶቹን መከተሉ ያለውን አስፈላጊነት እንዲገነዘብ በማድረግ ወደ አምላክ እንዲመለስ ይረዳዋል።—መዝሙር 51:1-4, 9, 13-15
በተጨማሪም ሕሊናችን አንድ ዓይነት ምርጫ ወይም ሥነ ምግባርን የተመለከተ ውሳኔ ስናደርግ ማስጠንቀቂያ ወይም መመሪያ ይሰጠናል። ዮሴፍ ዝሙት ስህተትና መጥፎ እንዲሁም በአምላክ ላይ የሚፈጸም ኃጢአት መሆኑን አስቀድሞ ያወቀው ሕሊናው እንዲህ ዓይነት አመራር ስለሰጠው ሊሆን ይችላል። ከጊዜ በኋላ ለእስራኤላውያን በተሰጧቸው አሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ ዝሙትን የሚከለክል ቀጥተኛ ሕግ ተካትቷል። (ዘፍጥረት 39:1-9፤ ዘፀአት 20:14) ሕሊናችን እንዲወቅሰን ብቻ ሳይሆን እንዲመራን አድርገን ማሠልጠን የተሻለ ጥቅም እንደሚኖረው እሙን ነው። ሕሊናህ የሚሠራው በዚህ መንገድ ነው?
ትክክለኛ ውሳኔ ለማድረግ ሕሊናን ማሠልጠን
ሕሊናችን ከተፈጥሮ ያገኘነው ስጦታ ቢሆንም እንኳ እክል አለበት። ፍጹም ጅምር የነበራቸው የሰው ልጆች የኋላ ኋላ “ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል።” (ሮሜ 3:23) ሕሊናችን በኃጢአትና ባለፍጽምና የቆሸሸ በመሆኑ የተዛባና መጀመሪያ በታቀደለት መልኩ በትክክል የማይሠራ ሊሆን ይችላል። (ሮሜ 7:18-23) በተጨማሪም ውጫዊ ሁኔታዎች በሕሊናችን ላይ ተጽዕኖ ሊያደርጉ ይችላሉ። አስተዳደጋችን፣ ባሕላችን፣ እምነትና የምንኖርበት አካባቢ ሕሊናችንን ይቀርጹታል። እውነት ነው በዓለም ላይ የሚታየው ወራዳ የሥነ ምግባር ደንብና እያሽቆለቆለ የሄደው የአቋም ደረጃ የጥሩ ሕሊና መለኪያ ሊሆኑ አይችሉም።
ስለሆነም አንድ ክርስቲያን ሕሊናውን ለማሠልጠን የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የማይለዋወጥና ትክክለኛ መሥፈርት ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልገዋል። እንዲህ ዓይነቱ መሥፈርት ሕሊናችን ሁኔታዎችን በትክክል እንዲያመዛዝንና ቀና የሆነ እርምጃ እንዲወስድ መመሪያ ይሆነዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ሕሊናችን አምላክ ባወጣቸው መሥፈርቶች ሲመራ “መልካሙን ከክፉው ለመለየት” በማስቻል ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ጎጂ ድርጊቶችን ከመፈጸም ይጠብቀናል። (ዕብራውያን 5:14) ሕሊናችን አምላክ ባወጣቸው መሥፈርቶች እስካልሠለጠነ ድረስ ወደ መጥፎ ሁኔታዎች ስናመራ ማስጠንቀቂያ ላይሰጠን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤ በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ይመራል” ሲል ይገልጻል።—ምሳሌ 16:25፤ 17:20
በአንዳንድ የሕይወታችን ዘርፎች የአምላክ ቃል በተግባር ብናውላቸው የሚጠቅሙን ግልጽ መመሪያዎችና ሥርዓቶች አስቀምጦልናል። በሌላ በኩል መጽሐፍ ቅዱስ ቀጥተኛ የሆነ መመሪያ የማይሰጥባቸው በርካታ ሁኔታዎች አሉ። እነዚህ ሁኔታዎች ምናልባት ሥራን፣ የጤና ጉዳዮችን፣ መዝናኛን፣ አለባበስንና አጋጌጥን በተመለከተ ከምናደርገው ምርጫ ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ማድረግ ያለብንን አውቀን ትክክለኛ ውሳኔ ላይ መድረስ ቀላል አይደለም። በመሆኑም “እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ መንገድህንም አስተምረኝ። አንተ አዳኜ፣ አምላኬም ነህና፣ በእውነትህ ምራኝ፤ አስተምረኝም” ሲል የጸለየውን የዳዊትን አመለካከት ማዳበር ይኖርብናል። (መዝሙር 25:4, 5) የአምላክን አመለካከትና መንገዶቹን ይበልጥ በተረዳን መጠን ሁኔታችንን በትክክል ማመዛዘንና ንጹህ በሆነው ሕሊናችን ውሳኔ ማድረግ እንችላለን።
በመሆኑም አንድ ዓይነት ጥያቄ ሲደቀንብን ወይም ውሳኔ ማድረግ ሲያስፈልገን ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ እንደሆኑ ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ሁኔታዎች የሚከተሉት ሊሆኑ ይችላሉ:- የራስነትን ሥልጣን ማክበር (ቈላስይስ 3:18, 20)፤ በሁሉ ነገር ሐቀኛ መሆን (ዕብራውያን 13:18 NW)፤ መጥፎ የሆነውን መጸየፍ (መዝሙር 97:10)፤ ሰላምን መሻት (ሮሜ 14:19)፤ ለባለ ሥልጣናት መታዘዝ (ማቴዎስ 22:21፤ ሮሜ 13:1-7)፤ አምላክን ብቻ ማምለክ (ማቴዎስ 4:10)፤ የዓለም ክፍል አለመሆን (ዮሐንስ 17:14)፤ ከመጥፎ ጓደኝነት መራቅ (1 ቆሮንቶስ 15:33)፤ በአለባበስና በአጋጌጥ ረገድ ልከኛ መሆን (1 ጢሞቴዎስ 2:9,10)፤ እንዲሁም ሌሎችን ላለማሰናከል መጣር (ፊልጵስዩስ 1:10)። ከሁኔታው ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለይቶ ማወቅ ሕሊናችን እንዲሠለጥንና ትክክለኛ ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል።
ሕሊናህን አዳምጥ
ሕሊናችን እንዲረዳን ከፈለግን የሚሰጠንን ማስጠንቀቂያ ተቀብለን ተግባራዊ ማድረግ ይገባናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ከሠለጠነው ሕሊናችን መጠቀም የምንችለው ማስጠንቀቂያውን ሰምተን አፋጣኝ ምላሽ ስንሰጥ ብቻ ነው። የሠለጠነ ሕሊና የአንድን መኪና ሁኔታ ከሚቆጣጠሩ ጠቋሚ መሣሪያዎች ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የዘይት ግፊት አመልካቹ የዘይቱ ግፊት መቀነሱን የሚጠቁም የማስጠንቀቂያ መብራት እያሳየን ነው እንበል። በዚህ ወቅት ለሁኔታው ትኩረት ከመስጠት ይልቅ መኪናውን ማሽከርከር ብንቀጥልስ? በሞተሩ ላይ ከባድ ጉዳት ሊደርስ ይችላል። በተመሳሳይም ሕሊናችን ወይም በውስጣችን ያለው ድምፅ አንድ የተሳሳተ እርምጃ እየወሰድን እንዳለ የሚጠቁም ማስጠንቀቂያ ይሰጠን ይሆናል። ሕሊናችን ያደረግነውን ወይም ልንወስደው ያሰብነውን እርምጃ ከቅዱስ ጽሑፋዊ መሥፈርቶችና የሥነ ምግባር ደረጃዎች ጋር በማወዳደር ልክ እንደ ጠቋሚ መሣሪያው የማስጠንቀቂያ መብራት ያሳየናል። ማስጠንቀቂያውን ሰምተን እርምጃ መውሰዳችን መጥፎ ድርጊት ከሚያስከትልብን መዘዝ የሚጠብቀን ከመሆኑም ባሻገር ሕሊናችን በተገቢው ሁኔታ መሥራቱን እንዲቀጥል ያደርገዋል።
ማስጠንቀቂያውን ችላ ብንልስ? ቀስ በቀስ ሕሊናችን ይደነዝዛል። ሕሊናን በተደጋጋሚ ችላ ማለት ወይም አፍኖ መያዝ የሚያስከትለው ውጤት ሰውነትን በጋለ ብረት ከመጥበስ ጋር ይመሳሰላል። በተጠበሰው የሰውነት ክፍል ላይ ያሉት የነርቭ ሴሎች ስለሚሞቱ ሥፍራው ይደነዝዛል። (1 ጢሞቴዎስ 4:2) የደነዘዘ ሕሊናም ኀጢአት ስንሠራ አይወቅሰንም እንዲሁም ኀጢአቱን እንዳንደግም ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ያቆማል። ጠባሳ ያለበት ሕሊና መጽሐፍ ቅዱስ ትክክልና ስህተት ስለሆኑ ነገሮች ያወጣውን የአቋም ደረጃ ችላ ስለሚል መጥፎ ሕሊና ይሆናል። በተጨማሪም ባለቤቱ ‘ደንዝዞ’ ከአምላክ ስለራቀ ሕሊናው የረከሰ ነው ሊባል ይችላል። (ኤፌሶን 4:17-19፤ ቲቶ 1:15) እንዴት ያለ አሳዛኝ ውጤት ነው!
“በጎ ኅሊና ይኑራችሁ”
በጎ ወይም ንጹሕ ሕሊና እንደያዙ መኖር ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ንጹሕ ኅሊና እንዲኖረኝ ሁልጊዜ እጥራለሁ” በማለት ገልጿል። (የሐዋርያት ሥራ 24:16) ጳውሎስ ክርስቲያን እንደመሆኑ መጠን አምላክን ላለማሳዘን ሲል ያለመታከት ራሱን ይመረምርና አካሄዱን ያስተካክል ነበር። የምንሠራው ነገር ትክክል መሆንና አለመሆኑን የሚወስነው አምላክ እንደሆነም ያውቅ ነበር። (ሮሜ 14:10-12፤ 1 ቆሮንቶስ 4:4) በመሆኑም “ስለ ራሳችን መልስ መስጠት በሚገባን በእርሱ ፊት ሁሉም ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው” ብሏል።—ዕብራውያን 4:13
ጳውሎስ ሰዎችን ቅር የሚያሰኝ ነገር ማድረግ እንደማይገባንም ተናግሯል። ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ ስለ መብላት” የሰጣቸው ማሳሰቢያ ለዚህ ተስማሚ ምሳሌ ይሆናል። ጳውሎስ ለማስገንዘብ የፈለገው ነጥብ አንዳንድ ድርጊቶች ከአምላክ ቃል ጋር የማይቃረኑ ቢሆኑም እንኳ የሌሎችን ሕሊና ግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ መሆኑን ነው። ይህን አለማድረግ ‘ክርስቶስ የሞተለት ወንድማችን በመንፈሳዊ እንዲጠፋ’ ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ በተጨማሪም ከአምላክ ጋር ያለንን ወዳጅነት ያበላሽብናል።—1 ቆሮንቶስ 8:4, 11-13፤ 10:23, 24
በመሆኑም ሕሊናህን ማሠልጠንህን አታቋርጥ እንዲሁም ምንጊዜም በጎ ሕሊና ይኑርህ። ውሳኔ ስታደርግ የአምላክን መመሪያ ለማግኘት ጥረት አድርግ። (ያዕቆብ 1:5) የአምላክን ቃል አጥና፤ በተጨማሪም መመሪያው አእምሮህንና ልብህን እንዲቀርጽ ፍቀድለት። (ምሳሌ 2:3-5) ከበድ ያሉ ጉዳዮች ሲገጥሙህ ከሁኔታው ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በተገቢው መንገድ መረዳትህን ለማረጋገጥ የጎለመሱ ክርስቲያኖችን አማክር። (ምሳሌ 12:15፤ ሮሜ 14:1፤ ገላትያ 6:5) ውሳኔህ ሕሊናህ ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድርና ከሌሎች ከሁሉም በላይ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለህን ግንኙነት እንዴት እንደሚነካው አስብ።—1 ጢሞቴዎስ 1:5, 18, 19
ሕሊናችን ከአፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ከይሖዋ አምላክ ያገኘነው ድንቅ ስጦታ ነው። ይህን ስጦታ ከሰጪው ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ በመጠቀም ወደ ፈጣሪያችን ይበልጥ እንቅረብ። በድርጊታችን ሁሉ “በጎ ኅሊና” እንዲኖረን በመጣር በአምላክ አምሳል መፈጠራችንን በግልጽ እናሳይ።—1 ጴጥሮስ 3:16፤ ቆላስይስ 3:10
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እዚህ ላይ ሕሊናን ለማመልከት የተጠቀሰው ግሪክኛ ቃል “ከሥነ ምግባር አኳያ ትክክልና ስህተት የሆነውን ለመለየት የሚረዳ የተፈጥሮ ችሎታ” (ዘ አናሊቲከል ግሪክ ሌክሲከን ሪቫይዝድ፣ በሃሮልድ ሞልተን)፤ እንዲሁም “በሥነ ምግባር ረገድ ጥሩና መጥፎ የሆነውን የመለየት ችሎታ” (ግሪክ-ኢንግሊሽ ሌክሲከን፣ በጆሴፍ ሄንሪ ቴየር) የሚል ትርጉም አለው።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሕሊናህ የሠለጠነው እንዲወቅስህ ብቻ ሳይሆን እንዲመራህ ጭምር ነው?
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሚገባ የሠለጠነ ሕሊና ማግኘታችን የተመካው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በመማራችንና ተግባራዊ በማድረጋችን ላይ ነው
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሕሊናህ የሚሰጥህን ማስጠንቀቂያ ችላ አትበል