የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የአንደኛ ዜና መዋዕል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
አይሁዳውያን ከባቢሎን ግዞት ወጥተው ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ 77 ዓመት ገደማ ሆኗቸዋል። በገዥው በዘሩባቤል ዳግም የተገነባው ቤተ መቅደስ ደግሞ 55 ዓመት አስቆጥሯል። አይሁዳውያኑ የተመለሱበት ዋነኛ ምክንያት በኢየሩሳሌም እውነተኛውን አምልኮ መልሶ ለማቋቋም ነው። ይሁን እንጂ ሕዝቡ ለይሖዋ አምልኮ የነበረው ቅንዓት ቀዝቅዟል። ስለዚህ አስቸኳይ ማበረታቻ ያስፈልጋቸው የነበረ ሲሆን ይህንንም ማበረታቻ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሆነው ከአንደኛ ዜና መዋዕል መጽሐፍ አግኝተዋል።
አንደኛ ዜና መዋዕል የዘር ሐረጉን ዝርዝር ሳይጨምር ንጉሥ ሳኦል ከሞተበት ጊዜ አንስቶ ንጉሥ ዳዊት እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ያሉትን የ40 ዓመት ገደማ ታሪክ ይሸፍናል። ይህ መጽሐፍ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ460 በካህኑ ዕዝራ እንደተጻፈ ይታመናል። አንደኛ ዜና መዋዕል የእኛንም ትኩረት የሚስብ ነው፤ ምክንያቱም በቤተ መቅደሱ ይቀርብ ስለነበረው አምልኮ እንድናስተውል ከመርዳቱም በላይ የመሲሑን የዘር ሐረግ በዝርዝር ይዞልናል። አንደኛ ዜና መዋዕል መጽሐፍ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ክፍል እንደመሆኑ መጠን እምነታችንን ያጠነክራል፤ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለንንም እውቀት ያሳድግልናል።—ዕብራውያን 4:12
ጠቃሚ የሆነ የስም ዝርዝር
ዕዝራ ያሰፈረው የዘር ሐረግ ዝርዝር ቢያንስ ቢያንስ ሦስት ጥቅሞች አሉት፦ መብት ያላቸው ብቻ በክህነት እንዲያገለግሉ ለመከታተል፣ እያንዳንዱ ነገድ ሊያገኝ የሚገባውን ውርስ ለመወሰን እና የመሲሑን የትውልድ መስመር ዘገባ ጠብቆ ለማቆየት ይረዳል። የዘር ሐረጉ ከአይሁዳውያን ታሪክ ተነስቶ ወደኋላ እየቆጠረ እስከ መጀመሪያው ሰው ይደርሳል። ከአዳም ጀምሮ እስከ ኖኅ ድረስ አሥር ትውልድ፣ እስከ አብርሃም ድረስ ደግሞ ሌላ አሥር ትውልድ አለ። ዘገባው የእስማኤልን፣ የአብርሃምን ቁባት የኬጡራንና የዔሳውን ልጆች ከዘረዘረ በኋላ በእስራኤል 12 ልጆች የዘር ሐረግ ላይ ትኩረት ያደርጋል።—1 ዜና መዋዕል 2:1
ይሁዳ የዳዊት የንግሥና መሥመር መገኛ ስለሆነ የዘር ሐረጉ በሰፊው ተዘግቧል። ከአብርሃም እስከ ዳዊት 14 ትውልድ ያለ ሲሆን እስራኤላውያን በግዞት ወደ ባቢሎን እስከተወሰዱበት ድረስ ደግሞ ሌላ 14 ትውልድ ይገኛል። (1 ዜና መዋዕል 1:27, 34፤ 2:1-15፤ 3:1-17፤ ማቴዎስ 1:17) ከዚያም ዕዝራ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያሉትን ነገዶች የትውልድ ሐረግ ከዘረዘረ በኋላ የሌዊን ልጆች የዘር ሐረግ አስፍሯል። (1 ዜና መዋዕል 5:1-24፤ 6:1) ቀጥሎም ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምዕራብ ስላሉት አንዳንድ ነገዶች አጭር መግለጫ ሰጠና የብንያምን የዘር ሐረግ በዝርዝር አስቀመጠ። (1 ዜና መዋዕል 8:1) ከባቢሎን ምርኮ በኋላ መጀመሪያ ላይ ወደ ኢየሩሳሌም የገቡት ሰዎች ስም ዝርዝር ተመዝግቧል።—1 ዜና መዋዕል 9:1-16
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
1:18—የሳላ አባት ቃይን ነው ወይስ አርፋክስድ? (ሉቃስ 3:35, 36) የሳላ አባት አርፋክስድ ነው። (ዘፍጥረት 10:24፤ 11:12) በሉቃስ 3:36 ላይ የተጠቀሰው “ቃይን” የሚለው ቃል “ከለዳውያን” ከሚለው ቃል ጋር ሳይምታታ አይቀርም። እንዲህ ከሆነ የመጀመሪያው ጽሑፍ “የከለዳዊው የአርፋክስድ ልጅ” የሚል ሐሳብ ሊኖረው ይችላል። አሊያም ቃይንም ሆነ አርፋክስድ የአንድ ሰው ስም ሊሆኑ ይችላሉ። “የቃይን ልጅ” የሚለው ሐረግ በአንዳንድ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ላይ እንደሌለ ማስተዋል ይኖርብናል።
2:15—ዳዊት የእሴይ ሰባተኛ ልጅ ነው? አይደለም። የእሴይ ልጆች ስምንት ነበሩ፤ ዳዊት ደግሞ የሁሉም ታናሽ ነው። (1 ሳሙኤል 16:10, 11፤ 17:12) ከሁኔታው መረዳት እንደምንችለው ከእሴይ ልጆች ውስጥ አንዱ ምንም ልጅ ሳይወልድ ሞቷል። ይህ ልጅ በዘር ሐረግ ዝርዝር ውስጥ መግባቱ የሚፈይደው ነገር ባለመኖሩ ዕዝራ ስሙን ሳይመዘግበው ቀርቷል።
3:17—በሉቃስ 3:27 ላይ የኢኮንያን ልጅ ሰላትያል የኔሪ ልጅ ተብሎ የተጠቀሰው ለምንድን ነው? ኢኮንያን የሰላትያል አባት ነው። ይሁን እንጂ ኔሪ ሴት ልጁን ለሰላትያል የዳረለት ይመስላል። ሉቃስ ዮሴፍን የማርያም አባት የኤሊ ልጅ ብሎ እንደጠቀሰው ሁሉ የኔሪን አማች ሰላትያልንም የኔሪ ልጅ ብሎ ጠቅሶታል።—ሉቃስ 3:23
3:17-19—ዘሩባቤል፣ ፈዳያ እና ሰላትያል የሚዛመዱት እንዴት ነው? ዘሩባቤል የሰላትያል ወንድም የፈዳያ ልጅ ነው። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ዘሩባቤልን የሰላትያል ልጅ ብሎ ይጠራዋል። (ማቴዎስ 1:12፤ ሉቃስ 3:27) የዚህም ምክንያት ፈዳያ ከሞተ በኋላ ዘሩባቤልን ሰላትያል ስላሳደገው ሊሆን ይችላል። ወይም ምናልባት ሰላትያል ልጅ ሳይወልድ ሞቶ፣ ፈዳያ የወንድሙን ሚስት አግብቶ በመጀመሪያ ዘሩባቤልን ስለወለደ ሊሆን ይችላል።—ዘዳግም 25:5-10
5:1, 2—ዮሴፍ የብኩርና መብት ማግኘቱ ምን ጥቅም ያስገኝለታል? ዮሴፍ ይህን መብት ማግኘቱ የሁለት ነገድ ድርሻ ያስገኝለታል። (ዘዳግም 21:17) ከዚህም የተነሳ የሁለት ነገዶች ማለትም የኤፍሬምና የምናሴ አባት ለመሆን ችሏል። ሌሎቹ የእስራኤል ልጆች ግን እያንዳንዳቸው ለአንድ ነገድ ብቻ አባት ሆነዋል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:1–9:44፦ በአንድ ወቅት በሕይወት የኖሩ ሰዎች የዘር ሐረግ መስፈሩ የእውነተኛው አምልኮ አጠቃላይ ዝግጅት የተመሠረተው በአፈ ታሪክ ሳይሆን በእውነታ ላይ መሆኑን የሚያስረዳ ነው።
4:9, 10፦ ያቤጽ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ተጨማሪ ሰዎች እንዲኖሩበት ሲል ግዛቱ እንዲሰፋለት ያቀረበውን ልባዊ ጸሎት ይሖዋ ሰምቷል። እኛም ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ ላይ በቅንዓት የምንካፈል እንደመሆናችን መጠን ጭማሪ ለማግኘት ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ይኖርብናል።
5:10, 18-22፦ በሳኦል ዘመነ መንግሥት ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የነበሩት ነገዶች ቁጥር በጊዜው ከነበሩት አጋራውያን በግማሽ የሚያንስ ቢሆንም እንኳ ድል ነስተዋል። ይህ የሆነበት ምክንያት በእነዚያ ነገዶች ውስጥ ያሉ ደፋር ሰዎች በይሖዋ ላይ ይተማመኑና የእርሱንም እርዳታ ለማግኘት ይጠባበቁ ስለነበር ነው። እኛም በቁጥር እጅግ ከሚበልጡን ጠላቶቻችን ጋር መንፈሳዊ ውጊያ የምናደርግ እንደ መሆናችን መጠን በይሖዋ ላይ ሙሉ ትምክህት ይኑረን።—ኤፌሶን 6:10-17
9:26, 27፦ ሌዋውያን በር ጠባቂዎች ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር። ቅዱስ ወደሆኑት የቤተ መቅደሱ ሥፍራዎች የሚያስገባው በር ቁልፍ ተሰጥቷቸው ነበር። በራፎቹን በየዕለቱ በመክፈት ታማኝ መሆናቸውን አስመስክረዋል። እኛም በክልላችን ለሚገኙ ሰዎች የመስበክና ይሖዋን ወደ ማምለክ እንዲደርሱ የመርዳት ኃላፊነት በአደራ ተሰጥቶናል። ታዲያ እኛስ እንደ ሌዋውያኑ በር ጠባቂዎች እምነት የሚጣልብን መሆን አይገባንም?
ዳዊት ነገሠ
ታሪኩ የሚጀምረው ሳኦልና ሦስት ልጆቹ ከፍልስጥኤማውያን ጋር በተደረገው ውጊያ በጊልቦዓ ተራራ ላይ መሞታቸውን በሚናገረው ዘገባ ነው። የእሴይ ልጅ ዳዊት በይሁዳ ነገድ ላይ ነገሠ። ከየነገዱ የተውጣጡ ሰዎችም ወደ ኬብሮን ከመጡ በኋላ በእስራኤል ሁሉ ላይ ዳዊትን አነገሡት። (1 ዜና መዋዕል 11:1-3) ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኢየሩሳሌምን ተቆጣጠረ። ከዚያም እስራኤላውያን ‘በሆታ ቀንደ መለከት እየነፉ፣ መሰንቆና በገና እየደረደሩ’ የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም አመጡ።—1 ዜና መዋዕል 15:28
ዳዊት ለእውነተኛው አምላክ ቤተ መቅደስ መገንባት እንደሚፈልግ ተናገረ። ይሖዋ ይህን መብት ለሰሎሞን በማስተላለፍ ከዳዊት ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን አደረገ። ዳዊት በእስራኤል ጠላቶች ላይ መዝመቱን የቀጠለ ሲሆን ይሖዋም ተከታታይ ድል አጎናጽፎታል። አግባብነት የሌለው ቆጠራ ማድረጉ ለ70,000 ሰዎች መሞት ምክንያት ሆኗል። ዳዊት መሥዋዕት የሚቀርብበት መሠዊያ ለይሖዋ እንዲሠራ በመልአክ በኩል መመሪያ ከደረሰው በኋላ ከኢያቡሳዊው ከኦርና መሬት ገዛ። ከዚያም በቦታው ላይ “እጅግ የሚያምር” ቤተ መቅደስ ለመገንባት ‘ብዙ ዝግጅት’ አደረገ። (1 ዜና መዋዕል 22:5) ዳዊት በተቀናጀ መልኩ አገልግሎታቸውን እንዲያከናውኑ ሌዋውያንን ያደራጀ ሲሆን አንደኛ ዜና መዋዕል ከየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በላቀ መንገድ ስለዚህ ጉዳይ በዝርዝር ዘግቧል። ንጉሡም ሆነ ሕዝቡ ለቤተ መቅደሱ መሥሪያ የሚሆን ስጦታ ለግሰዋል። ዳዊት ለ40 ዓመት ከነገሠ በኋላ “ብዙ ዘመን ባለጠግነትና ክብር ሳይጐድልበት ዕድሜ ጠግቦ ሞተ፤ ልጁ ሰሎሞንም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።”—1 ዜና መዋዕል 29:28
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
11:11—በ2 ሳሙኤል 23:8 ላይ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 800 እንደሆነ ሲናገር እዚህ ላይ 300 የተባለው ለምንድን ነው? የዳዊት ሦስት ኃያላን ሰዎች አለቃ ያሾብዓም ወይም ዮሴብ በሴትቤት ነበር። የቀሩት ሁለት ኃያላን ደግሞ ኤልዔዘር እና ሣማ ናቸው። (2 ሳሙኤል 23:8-11) በሁለቱ ታሪኮች ላይ የቁጥር ልዩነት የተፈጠረው ግለሰቡ በተለያዩ ጊዜያት የፈጸማቸውን ድርጊቶች ስለሚዘግቡ ሊሆን ይችላል።
11:20, 21—ከሦስቱ የዳዊት ኃያላን ሰዎች አንጻር ሲታይ የአቢሳ ሥልጣን ምን ነበር? አቢሳ፣ ዳዊትን ካገለገሉት ሦስት ኃያላን ሰዎች መካከል አንዱ አይደለም። ይሁን እንጂ በ2 ሳሙኤል 23:18, 19 (በግርጌ ማስታወሻው) ላይ እንደተገለጸው አቢሳ የ30 ጦረኞች አለቃ በመሆኑ ከማናቸውም በላይ ስመ ጥር ነበር። አቢሳ ከያሾብዓም ጋር የሚመጣጠን ጀብዱ ስለፈጸመ ሦስቱ ኃያላን ሰዎች ካላቸው የማይተናነስ ዝና ነበረው።
12:8—የጋድ ተዋጊዎች ፊታቸው እንደ “አንበሳ ፊት” እንደሆነ የተገለጸው ለምንድን ነው? እነዚህ ብርቱ ተዋጊዎች በምድረ በዳ የዳዊት ደጋፊዎች ነበሩ። ከዚህም የተነሳ ፀጉራቸው ረዝሞ ነበር። ፀጉራቸው መጎፈሩ እንደ አንበሳ አስፈሪ መልክ እንዲኖራቸው አድርጓል።
13:5—“የግብፅ ወንዝ” ምንድን ነው? አንዳንዶች ይህ መጠሪያ የናይልን ወንዝ የተወሰነ ክፍል እንደሚያመለክት ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ቦታው ‘የግብፅን ወንዝ ደረቅ መደብ’ ማለትም ተስፋይቱን ምድር በስተ ደቡብ ምዕራብ የሚያዋስነውን ረዥምና ጠባብ ሸለቆ እንደሚያመለክት ይታመናል።—ዘኍልቍ 34:2, 5፤ ዘፍጥረት 15:18
16:30—በይሖዋ ፊት “ትንቀጥቀጥ” የሚለውን አነጋገር መረዳት የሚኖርብን እንዴት ነው? እዚህ ጥቅስ ላይ ‘መንቀጥቀጥ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ቀጥተኛ ፍቺው “ከባድ ሕመም” ማለት ሲሆን ይህ ደግሞ ለይሖዋ መሰጠት ያለበትን ጥልቅ ፍርሃትና ልባዊ አክብሮት ለማመልከት የገባ ዘይቤያዊ አነጋገር ነው።
16:1, 37-40፤ 21:29, 30፤ 22:19—ታቦቱ ወደ ኢየሩሳሌም ከመጣበት ወቅት ጀምሮ ቤተ መቅደሱ እስኪሠራ ድረስ በነበረው ጊዜ ውስጥ በእስራኤል አምልኮ ለማከናወን ምን ዝግጅት ተደርጎ ነበር? ዳዊት ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም አምጥቶ እርሱ በተከለው ድንኳን ውስጥ ካስቀመጠው በኋላ ታቦቱ ለብዙ ዓመታት የቆየው በማደሪያው ይኸውም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አልነበረም። ታቦቱ ወደ ኢየሩሳሌም ከመጣ በኋላ የቆየው በድንኳን ውስጥ ነበር። የመገናኛው ድንኳን ግን ሊቀ ካህኑ ሳዶቅና ወንድሞቹ በሕጉ መሠረት መሥዋዕት ያቀርቡበት በነበረው በገባዖን ቀርቶ ነበር። በኢየሩሳሌም የሚገነባው ቤተ መቅደስ እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ይህ ዝግጅት ቀጥሎ ነበር። የቤተ መቅደሱ ግንባታ ሲጠናቀቅ ገባዖን የነበረው የመገናኛ ድንኳን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲዛወር የተደረገ ሲሆን ታቦቱ ደግሞ በቤተ መቅደሱ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ተቀመጠ።—1 ነገሥት 8:4, 6
ምን ትምህርት እናገኛለን?
13:11፦ የምናደርገው ጥረት ሳይሳካ ሲቀር ከመበሳጨትና በይሖዋ ላይ ከማማረር ይልቅ ሁኔታውን መርምረን የችግሩ መንስኤ ምን እንደሆነ ለማስተዋል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ዳዊትም እንዲህ እንዳደረገ ጥያቄ የለውም። ከስህተቱ ተምሮ በተገቢው መንገድ ታቦቱን በተሳካ ሁኔታ ወደ ኢየሩሳሌም አምጥቷል።a
14:10, 13-16፤ 22:17-19፦ መንፈሳዊነታችንን የሚነካ ማንኛውንም ነገር ከማድረጋችን በፊት ሁልጊዜ ይሖዋን በጸሎት መጠየቅና መመሪያውን ለማግኘት መጣር ይኖርብናል።
16:23-29፦ የይሖዋ አምልኮ በሕይወታችን ውስጥ አንደኛውን ቦታ መያዝ ይኖርበታል።
18:3፦ ይሖዋ የገባውን ቃል የሚፈጽም አምላክ ነው። “ከግብፅ ወንዝ ጀምሮ እስከ ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ” የሚሸፍነውን መላውን የከነዓን ምድር በዳዊት አማካኝነት ለእስራኤላውያን በመስጠት ለአብርሃም የገባውን ቃል ፈጽሟል።—ዘፍጥረት 15:18፤ 1 ዜና መዋዕል 13:5
21:13-15፦ ይሖዋ መቅሰፍቱ እንዲቆም ለመልአኩ ትእዛዝ የሰጠበት ምክንያት የሕዝቦቹ ስቃይ ስለተሰማው ነው። በእርግጥም የይሖዋ ‘ምህረት ታላቅ ነው።’b
22:5, 9፤ 29:3-5, 14-16፦ ዳዊት የይሖዋን ቤተ መቅደስ እንዲሠራ ተልዕኮ ባይሰጠውም እንኳ የለጋስነት መንፈስ አሳይቷል። ለምን? ምክንያቱም ሁሉን ነገር ያገኘው በይሖዋ ደግነት እንደሆነ በመገንዘቡ ነው። እኛንም እንዲህ ዓይነቱ የአመስጋኝነት ስሜት ለጋስ እንድንሆን ሊያነሳሳን ይገባል።
24:7-18፦ የይሖዋ መልአክ ለመጥምቁ ዮሐንስ አባት ለዘካርያስ ተገልጦለት ዮሐንስ የሚባል ልጅ እንደሚወልድ ባበሰረው ጊዜ ዳዊት ካህናቱን በ24 ምድብ በመከፋፈል ያቋቋመው ዝግጅት ይሠራበት ነበር። ዘካርያስ “ከአብያ የክህነት ምድብ” እንደመሆኑ መጠን ተራው ደርሶ በቤተ መቅደስ ውስጥ እያገለገለ ነበር። (ሉቃስ 1:5, 8, 9) እውነተኛው አምልኮ የሚያጠነጥነው በእውነተኛ ባለታሪኮች እንጂ በልብ ወለድ ገጸ ባሕርያት ዙሪያ አይደለም። በዘመናችን በሚገባ ከተደራጀው የይሖዋ አምልኮ ጋር በተያያዘ ‘ከታማኝና ልባም ባሪያ’ ጋር በታማኝነት መተባበራችን የተትረፈረፈ በረከት ያስገኝልናል።—ማቴዎስ 24:45 የ1954 ትርጉም
ይሖዋን “በበጎ ፈቃድ” እናገልግለው
አንደኛ ዜና መዋዕል ያቀፈው የዘር ሐረግ ዝርዝሮችን ብቻ አይደለም። ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ስለማምጣቱ፣ ስላገኛቸው ታላላቅ ድሎች፣ ለቤተ መቅደሱ ግንባታ ስላደረገው ዝግጅትና የሌዋውያንን የክህነት አገልግሎት ምድብ ስለማደራጀቱ ጭምር የሚተርክ መጽሐፍ ነው። ዕዝራ በአንደኛ ዜና መዋዕል ላይ ያሰፈራቸው ነገሮች ሁሉ እስራኤላውያን በቤተ መቅደስ ውስጥ ለሚከናወነው የይሖዋ አምልኮ ያላቸውን ቅንዓት እንዲያቀጣጥሉ በመርዳት ረገድ ሳይጠቅማቸው እንዳልቀረ እሙን ነው።
ዳዊት ምንጊዜም የይሖዋ አምልኮ በሕይወቱ ውስጥ ትልቁን ቦታ እንዲይዝ በማድረግ ረገድ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል! ልዩ የሆኑ መብቶችን ለማግኘት ከመሻት ይልቅ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ይጣጣር ነበር። እኛም ይሖዋን “በፍጹም ልብና በበጎ ፈቃድ” እንድናገለግል ዳዊት የሰጠንን ምክር በሥራ ላይ እንድናውል ተበረታተናል።—1 ዜና መዋዕል 28:9
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ዳዊት ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት ስላደረገው ሙከራ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የግንቦት 15, 2005 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 16-19ን ተመልከት።
b ዳዊት ተገቢ ያልሆነ ቆጠራ ከማድረጉ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ትምህርት ለማግኘት የግንቦት 15, 2005 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 16-19ን ተመልከት።
[ከገጽ 8-11 የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ከአዳም እስከ ኖኅ ያለው ትውልድ (1,056 ዓመታት)
4026 ከክ.ል.በ. አዳም
130 ዓመታት ⇩
ሴት
105 ⇩
ሄኖስ
90 ⇩
ቃይናን
70 ⇩
መላልኤል
65 ⇩
ያሬድ
162 ⇩
ሄኖክ
65 ⇩
ማቱሳላ
187 ⇩
ላሜሕ
182 ⇩
በ2970 ከክ.ል.በ. ኖኅ ተወለደ
ከኖኅ እስከ አብርሃም ያለው ትውልድ (952 ዓመታት)
2970 ከክ.ል.በ. ኖኅ
502 ዓመታት ⇩
ሴም
100 ⇩
በ2370 ከክ.ል.በ. የጥፋት ውሃ መጣ
አርፋክስድ
35 ⇩
ሳላ
30 ⇩
ዔቦር
34 ⇩
ፋሌቅ
30 ⇩
ራግው
32 ⇩
ሴሮሕ
30 ⇩
ናኮር
29 ⇩
ታራ
130 ⇩
በ2018 ከክ.ል.በ. አብርሃም ተወለደ
ከአብርሃም እስከ ዳዊት፦ 14 ትውልድ (911 ዓመታት)
2018 ከክ.ል.በ. አብርሃም
100 ዓመታት
ይስሐቅ
60 ⇩
ያዕቆብ
c.88 ⇩
ይሁዳ
⇩
ፋሬስ
⇩
ኤስሮም
⇩
አራም
⇩
አሚናዳብ
⇩
ነአሶን
⇩
ሰልሞን
⇩
ቦዔዝ
⇩
ኢዮቤድ
⇩
እሴይ
⇩
በ1107 ከክ.ል.በ. ዳዊት ተወለደ