“ከየቋንቋው” የተውጣጡ ሰዎች ምሥራቹ ደረሳቸው
“ከየወገኑና ከየቋንቋው ዐሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ ዘርፍ አጥብቀው በመያዝ፣ ‘እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና አብረን እንሂድ’ ይሉታል።”—ዘካርያስ 8:23
1. ይሖዋ የተለያየ ዘርና ቋንቋ ላላቸው ሰዎች የመስበኩን ሥራ ለማስጀመር ወቅቱንና ሁኔታውን ያመቻቸው እንዴት ነበር?
ወቅቱም ሆነ ሁኔታው በጣም ምቹ ነበር። በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል የዋለው በዚያን ዕለት ነው። የማለፍ በዓልን ለማክበር ከሳምንታት ቀደም ብሎ ቢያንስ ቢያንስ 15 ከሚያህሉ የተለያዩ የሮም ግዛቶችና ከዚያ ግዛት ውጪ የመጡ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ አሕዛብ ኢየሩሳሌምን አጨናንቀዋታል። በዚያን ቀን በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ተራ ሰዎች በሮም ግዛቶች ውስጥ በሚነገሩ የተለያዩ ቋንቋዎች ምሥራቹን ሰበኩ፤ በቦታው የነበሩት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጥንቷ ባቤል ይኖሩ እንደነበሩት ሰዎች ግራ በመጋባት ሳይሆን የሚነገረው ነገር እየገባቸው አዳምጠዋል። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-12) ይህ ክስተት የክርስቲያን ጉባኤን መወለድ እንዲሁም እስከ ዘመናችን የዘለቀውና በበርካታ ቋንቋዎች የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የማስተማር ሥራ መጀመሩን የሚያሳይ ነበር።
2. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ከተለያየ ቦታ የተሰበሰቡ አድማጮቻቸውን ‘የሚያስደንቅ’ ምን ነገር አድርገዋል?
2 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በዘመኑ የነበረውን ተራ ግሪክኛ ቋንቋ መናገር ሳይችሉ አይቀሩም። እንዲሁም በቤተ መቅደሱ ይሠራበት የነበረውን የዕብራይስጥ ቋንቋ መናገር ይችላሉ። ይሁን እንጂ በዚያን የጰንጠቆስጤ በዓል ዕለት ከተለያየ ቦታ የመጡ አድማጮቻቸውን ቋንቋ በመናገር ሰዎቹን ‘አስደነቋቸው።’ ውጤቱ ምን ሆነ? ያዳምጧቸው የነበሩት ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በሰሙት እውነት ልባቸው ተነካ። ጥቂት የነበሩት ደቀ መዛሙርት በዚያን ቀን ቁጥራቸው ከ3,000 በላይ ሆነ!—የሐዋርያት ሥራ 2:37-42
3, 4. ደቀ መዛሙርት ከኢየሩሳሌም፣ ከይሁዳና ከገሊላ ሲወጡ ምሥራቹን የመስበክ ሥራ የተስፋፋው እንዴት ነው?
3 ይህ አስደናቂ ነገር ከተከሰተ ብዙም ሳይቆይ በኢየሩሳሌም የስደት ማዕበል ተነሳ፤ “የተበተኑትም በሄዱበት ሁሉ ቃሉን ሰበኩ።” (የሐዋርያት ሥራ 8:1-4) ለምሳሌ ያህል፣ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 ላይ ግሪክኛ ተናጋሪ እንደነበር የሚገመተውን የወንጌላዊውን የፊልጶስን ታሪክ እናነባለን። ፊልጶስ ለሳምራውያን ሰብኮ ነበር። እንዲሁም ስለ ክርስቶስ ለሚናገረው መልእክት በጎ ምላሽ ለሰጠ ኢትዮጵያዊ ባለ ሥልጣን ሰብኳል።—የሐዋርያት ሥራ 6:1-5፤ 8:5-13, 26-40፤ 21:8, 9
4 ሕዝብ ከሚበዛባቸው ከኢየሩሳሌም፣ ከይሁዳና ከገሊላ ክልሎች ወጥተው ሌላ የመኖሪያ ስፍራ ሲፈልጉ የነበሩት ክርስቲያኖች አዳዲስ ጎሣዎችና ቋንቋዎች ገጥመዋቸው ነበር። አንዳንዶቹ የሰበኩት ለአይሁዳውያን ብቻ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ደቀ መዝሙሩ ሉቃስ “ከቆጵሮስና ከቀሬና የመጡት አንዳንዶች ሰዎች . . . ወደ አንጾኪያ ሄደው ለግሪኮችም ጭምር በመንገር የጌታን የኢየሱስን ወንጌል ሰበኩላቸው” በማለት ዘግቧል።—የሐዋርያት ሥራ 11:19-21
የማያዳላው አምላክ ለሁሉም የሚሆን መልእክት አለው
5. ምሥራቹ የተሰበከበት ሁኔታ ይሖዋ እንደማያዳላ የሚያሳየው እንዴት ነው?
5 አምላክ ከአድልዎ ፈጽሞ የራቀ በመሆኑ እነዚህ ክንውኖች ከእርሱ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ ነበሩ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለአሕዛብ ያለውን አመለካከት እንዲያስተካክል ይሖዋ ከረዳው በኋላ “እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ በእርግጥ ተረድቻለሁ፤ ነገር ግን እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ ይቀበላቸዋል” በማለት በአድናቆት ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35፤ መዝሙር 145:9) ቀድሞ ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስም አምላክ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ . . . ይፈልጋል” በማለት ይሖዋ ከአድልዎ የራቀ መሆኑን አረጋግጧል። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) የመንግሥቱ ተስፋ ጾታ፣ ዘር፣ ብሔር ወይም ቋንቋ ሳይለይ ለሁሉም መሰበኩ ፈጣሪ እንደማያዳላ ያሳያል።
6, 7. መጽሐፍ ቅዱስ ምሥራቹ በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ቋንቋዎች እንደሚሰበክ ምን ትንቢት ይናገራል?
6 ይህ ዓለም አቀፍ መስፋፋት እንደሚኖር ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ተነግሮ ነበር። በዳንኤል ትንቢት ላይ እንደተገለጸው “ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል [ለኢየሱስ] ተሰጠው፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች ሰገዱለት።” (ዳንኤል 7:14) ይህ መጽሔት በ151 ቋንቋዎች መታተሙና በዓለም ዙሪያ መሰራጨቱ ስለ አምላክ መንግሥት እንድታውቅ አስችሎሃል፤ ይህም የዳንኤል ትንቢት እየተፈጸመ መሆኑን የሚያሳይ ሐቅ ነው።
7 መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ፣ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች በውስጡ ያለውን ሕይወት የሚያስገኝ መልእክት የሚሰሙበት ጊዜ እንደሚመጣ አስቀድሞ ተናግሯል። ዘካርያስ “በእነዚያም ቀናት ከየወገኑና ከየቋንቋው ዐሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ [‘የእግዚአብሔር እስራኤል’ አባል የሆነ በመንፈስ የተቀባ ክርስቲያን] ልብስ ዘርፍ አጥብቀው በመያዝ፣ ‘እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና አብረን እንሂድ’ ይሉታል” በማለት እውነተኛው አምልኮ በርካታ ሰዎችን ምን ያህል እንደሚማርክ ተንብዮአል። (ዘካርያስ 8:23፤ ገላትያ 6:16) ሐዋርያው ዮሐንስም በራእይ የተመለከተውን ነገር እንዲህ በማለት ዘግቧል:- “እነሆ፤ በዙፋኑና በበጉ ፊት ማንም ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ ቆመው ነበር።” (ራእይ 7:9) እንዲህ ያሉት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ተመልክተናል!
ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ምሥራቹን ማድረስ
8. በዘመናችን በስብከቱ ሥራችን ላይ ማስተካከያ እንድናደርግ የጠየቁብን የትኞቹ እውነታዎች ናቸው?
8 በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ከአገራቸው እየተሰደዱ ነው። ግሎባላይዜሽን አዲስ የፍልሰት ዘመን ብቅ እንዲል አድርጓል። በጦርነት ቀጠናዎችና የኢኮኖሚ ድቀት ባለባቸው ቦታዎች የሚኖሩ ብዙ ሰዎች፣ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ አስተማማኝ ኑሮ ለመምራት ሲሉ ይበልጥ የተረጋጋ ሁኔታ ወዳለባቸው አካባቢዎች ይጓዛሉ። በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችና ጥገኝነት የሚፈልጉ ሰዎች ወደተለያዩ አገሮች መጉረፋቸው የባዕድ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። ለምሳሌ ያህል በፊንላንድ ከ120 የሚበልጡ ቋንቋዎች ይነገራሉ፤ በአውስትራሊያ የሚነገሩት ቋንቋዎች ቁጥር ደግሞ ከ200 ይበልጣል። በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው ሳን ዲዬጎ ከተማ ብቻ ከ100 የሚበልጡ ቋንቋዎች ይነገራሉ!
9. በክልላችን የተለየ ቋንቋ ያላቸው ሰዎች ስለመኖራቸው ምን ዓይነት አመለካከት መያዝ ይገባናል?
9 እንደ ክርስቲያን አገልጋይነታችን መጠን በክልላችን የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች መኖራቸው ለአገልግሎታችን እንቅፋት እንደሆነ አድርገን መቁጠር ይገባናል? በጭራሽ! እንዲያውም የአገልግሎት ክልላችን እንዲሰፋ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ ወይም በሌላ አነጋገር “አዝመራው ለመከር እንደ ደረሰ” የሚያሳይ ክስተት እንደሆነ አድርገን እንመለከተዋለን። (ዮሐንስ 4:35) ሰዎች የየትኛውም አገር ዜጋ ይሁኑ ምንም ዓይነት ቋንቋ ይናገሩ ለመንፈሳዊነታቸው ትኩረት እስከሰጡ ድረስ እነርሱን ለመርዳት ጥረት እናደርጋለን። (ማቴዎስ 5:3 NW) በዚህ ምክንያት በየዓመቱ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ‘ከቋንቋው ሁሉ’ የተውጣጡ ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እየሆኑ ነው። (ራእይ 14:6) ለምሳሌ ያህል በጀርመን አገር ከነሐሴ 2004 ጀምሮ የስብከቱ ሥራ በ40 ቋንቋዎች ሲከናወን ቆይቷል። በተመሳሳይ ወቅት በአውስትራሊያ የምሥራቹ ወደ 30 ገደማ በሚሆኑ ቋንቋዎች ተሰብኳል፤ ከአሥር ዓመት በፊት ይሰበክ የነበረው በ18 ቋንቋዎች ብቻ ነበር። በግሪክ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በ20 ቋንቋዎች ምሥራቹን ሰብከዋል። በምድር ዙሪያ ከሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል 80 በመቶ የሚያህሉት የሚናገሩት አብዛኛው የዓለም ሕዝብ የሚግባባበትን እንግሊዝኛ ቋንቋ አይደለም።
10. እያንዳንዱ የምሥራቹ ሰባኪ “ሕዝቦችን ሁሉ” ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ምን ሚና ይጫወታል?
10 ኢየሱስ “ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት የሰጠው ትእዛዝ በእርግጥም ፍጻሜውን በማግኘት ላይ ነው! (ማቴዎስ 28:19) ይህንን ተልእኮ በደስታ የተቀበሉት የይሖዋ ምሥክሮች በ235 አገሮች እየተንቀሳቀሱ ሲሆን ከ400 በሚበልጡ ቋንቋዎች ጽሑፎችን ያሰራጫሉ። የይሖዋ ድርጅት ሰዎችን በቋንቋቸው ለመርዳት የሚያስችሉ ጽሑፎች እያዘጋጀ ነው፤ ይሁንና እያንዳንዱ የምሥራቹ ሰባኪ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ‘ለሰዎች ሁሉ’ በደንብ በሚገባቸው ቋንቋ ለማዳረስ ቅድሚያ መውሰድ አለበት። (ዮሐንስ 1:7) ይህ የተቀናጀ ጥረት የተለያየ ቋንቋ ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከምሥራቹ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። (ሮሜ 10:14, 15) አዎን፣ እያንዳንዳችን በጣም ጠቃሚ ሚና መጫወት እንችላለን!
መሰናክሉን ማለፍ
11, 12. (ሀ) ሌላ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች ከመስበክ ጋር በተያያዘ ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማል? መንፈስ ቅዱስስ እርዳታ የሚሰጠው እንዴት ነው? (ለ) ለሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መስበኩ ብዙውን ጊዜ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?
11 በዛሬው ጊዜ በርካታ የምሥራቹ ሰባኪዎች ሌላ ቋንቋ መማር ይፈልጋሉ፤ ይሁን እንጂ የአምላክ መንፈስ በተአምር ሌላ ቋንቋ መናገር እንድንችል ይረዳናል ብለው አይጠብቁም። (1 ቆሮንቶስ 13:8) አዲስ ቋንቋ መማር በጣም አስቸጋሪ ነው። ሌላ ቋንቋ የሚችሉ ሰዎችም ቢሆኑ የተለየ አስተዳደግና ባሕል ላላቸው ለዚያ ቋንቋ ተናጋሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ማራኪ አድርገው ለማቅረብ አስተሳሰባቸውንና አቀራረባቸውን ማስተካከል ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ከዚህም በላይ ስደተኞች በአብዛኛው ስለሚፈሩና አይናፋር ስለሚሆኑ አመለካከታቸውን ለመረዳት ከባድ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።
12 የሆነ ሆኖ ዛሬም ቢሆን የይሖዋ አገልጋዮች ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችን ለመርዳት በሚጥሩበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ አስፈላጊውን ድጋፍ ይሰጣቸዋል። (ሉቃስ 11:13) መንፈስ ቅዱስ ተአምራዊ የቋንቋ ችሎታ አይሰጠንም፤ ከዚህ ይልቅ የእኛን ቋንቋ ከማይችሉ ሰዎች ጋር የመነጋገር ፍላጎታችንን ከፍ ያደርግልናል። (መዝሙር 143:10) ለሰዎች በደንብ በማያውቁት ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ስንሰብክላቸው ወይም ስናስተምራቸው የአእምሮ እውቀት ያገኙ ይሆናል። ይሁን እንጂ የሚያዳምጡንን ሰዎች ልብ ለመንካት ብዙውን ጊዜ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መንገሩ በጣም የተሻለ ነው፤ ምክንያቱም ትምህርቱ ልባቸው የሚደርሰው፣ ለሥራ የሚንቀሳቀሱትና ተስፋቸው የሚለመልመው በቋንቋቸው ሲነገራቸው ነው።—ሉቃስ 24:32
13, 14. (ሀ) አንዳንዶች በሌላ ቋንቋ እንዲሰብኩ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? (ለ) የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የታየው እንዴት ነው?
13 በርካታ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በጎ ምላሽ እንደሚሰጡ መመልከታቸው ይህንን የአገልግሎት መስክ ሥራዬ ብለው እንዲያያዙት አድርጓቸዋል። ሌሎች ደግሞ ይበልጥ የሚበረታቱት አገልግሎታቸው ጥረት የሚጠይቅና አስደሳች ሲሆን ነው። በደቡብ አውሮፓ የሚገኝ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ “ከምሥራቅ አውሮፓ ከሚመጡት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ የእውነት ጥማት አላቸው” ሲል ጽፏል። ለመስማት ፈቃደኛ የሆኑ እንዲህ ያሉ ሰዎችን መርዳት እንዴት ያረካል!—ኢሳይያስ 55:1, 2
14 ሆኖም በዚህ ሥራ ውጤታማ ተሳትፎ እንድናደርግ ቆራጦች መሆንና የራሳችንን ጥቅም መሠዋት ያስፈልገናል። (መዝሙር 110:3) ለምሳሌ ያህል በጃፓን የሚገኙ ብዙ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦች፣ ቻይናውያን ስደተኞች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያውቁ ለመርዳት በትልልቅ ከተሞች ያሉትን ምቹ መኖሪያዎች ትተው ወደ ሩቅ ቦታዎች ተጉዘዋል። በምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ ጠረፍ የሚገኙ የምሥራቹ ሰባኪዎች ፊሊፒናውያንን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት በየጊዜው ከአንድ እስከ ሁለት ሰዓት ያህል በመኪና ይጓዛሉ። በኖርዌይ የሚገኙ ባልና ሚስት አንድን አፍጋኒስታናዊ ቤተሰብ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናሉ። የይሖዋ ምሥክሮቹ ባልና ሚስት በእንግሊዝኛና በኖርዌይ ቋንቋ የተዘጋጀውን አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለ ብሮሹር ይጠቀማሉ።a የሚያጠኑት አፍጋኒስታናውያን ደግሞ ዳሪ ከሚባለው ቋንቋቸው ጋር በጣም ተቀራራቢ በሆነው ፋርስኛ ቋንቋ በተዘጋጀ ብሮሹር አንቀጾቹን ያነብባሉ። የሚነጋገሩት ግን በእንግሊዝኛና በኖርዌይ ቋንቋ ነው። የውጪ ዜጎች ምሥራቹን ሲቀበሉ መመልከት፣ የራስን ጥቅም የመሠዋትና ራስን ከሁኔታዎች ጋር የማስማማት መንፈስ ላሳዩ ሰዎች ትልቅ እርካታ ያስገኝላቸዋል።b
15. በበርካታ ቋንቋዎች እየተካሄደ ባለው የስብከት ሥራ ሁላችንም መካፈል የምንችለው እንዴት ነው?
15 በዚህ በተለያዩ ቋንቋዎች በሚካሄደው እንቅስቃሴ መካፈል ትችላለህ? የትኞቹ ባዕድ ቋንቋዎች በአካባቢህ በብዛት እንደሚነገሩ በመመርመር ለምን አትጀምርም? ከዚያም በእነዚህ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ትራክቶችን ወይም ብሮሹሮችን መያዝ ትችላለህ። በ2004 ለሰዎች ሁሉ የሚሆን ምሥራች የተባለ ቀላልና ጠቃሚ መልእክት የያዘ ቡክሌት ወጥቶ ነበር፤ የቡክሌቱ መልእክት በበርካታ ቋንቋዎች በመጻፉ የመንግሥቱን ተስፋ ለመስበክ በጣም ጠቃሚ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል።—በገጽ 32 ላይ የሚገኘውን “ለሰዎች ሁሉ የሚሆን ምሥራች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
‘መጻተኛውን መውደድ’
16. ኃላፊነት ላይ ያሉ ወንድሞች ባዕድ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ለመርዳት ራስ ወዳድነት የሌለበት አሳቢነት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
16 ሌላ ቋንቋ ተማርንም አልተማርንም፣ በአካባቢያችን የሚኖሩ የውጪ ዜጎችን መንፈሳዊ ትምህርት በማስተማሩ ሥራ ረገድ ሁላችንም እርዳታ ማበርከት እንችላለን። ይሖዋ “መጻተኛን ውደዱ” በማለት ሕዝቡን አዝዞ ነበር። (ዘዳግም 10:18, 19) ለምሳሌ ያህል፣ በሰሜን አሜሪካ በሚገኝ አንድ ትልቅ ከተማ አምስት ጉባኤዎች በአንድ የመንግሥት አዳራሽ ይጠቀማሉ። በብዙ ጉባኤዎች በየዓመቱ የስብሰባ ሰዓት ለውጥ እንደሚደረግ ሁሉ በዚህም አዳራሽ በቻይንኛ የሚደረገው የእሁድ ስብሰባ ወደ ማምሻው ላይ መቀየር ነበረበት። ሆኖም ከምግብ ቤት ጋር የተያያዘ ሥራ ያላቸው ብዙዎቹ ቻይናውያን ስደተኞች በዚህ ሰዓት መሰብሰብ አይችሉም። የሌሎቹ ጉባኤዎች ሽማግሌዎች በደግነት ማስተካከያ በማድረጋቸው የእሁዱን የቻይንኛ ስብሰባ በጠዋት ለማድረግ ተቻለ።
17. አንዳንዶች ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ቡድን ለመርዳት ጉባኤ መቀየር ቢፈልጉ ምን ሊሰማን ይገባል?
17 አፍቃሪ የበላይ ተመልካቾች ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ቡድን ለመርዳት ጉባኤ መቀየር ለሚፈልጉ ብቃትና ችሎታ ያላቸው ወንድሞችና እህቶች አድናቆታቸውን ይገልጹላቸዋል። እንዲህ ያሉ ልምድ ያካበቱ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ጉባኤያቸውን ሊያጎድሉ ይችላሉ፤ ቢሆንም የበላይ ተመልካቾች የልስጥራንና የኢቆንዮን ሽማግሌዎች ተሰምቷቸው የነበረው ዓይነት ስሜት አላቸው። እነዚህ ሽማግሌዎች ጢሞቴዎስ ለጉባኤያቸው በረከት ቢሆንም የጳውሎስ የጉዞ ጓደኛ እንዳይሆን ለማከላከል አልሞከሩም። (የሐዋርያት ሥራ 16:1-4) በስብከቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት የሚካፈሉትም ቢሆኑ የውጪ አገር ዜጎች የተለየ አስተሳሰብ፣ ባሕል ወይም ልማድ ያላቸው መሆኑ ተስፋ አያስቆርጣቸውም። ከዚህ ይልቅ ለምሥራቹ ሲሉ ያለውን ልዩነት ለመቀበልና ጥሩ ግንኙነት ለመመሥረት የሚችሉበትን መንገድ ይፈልጋሉ።—1 ቆሮንቶስ 9:22, 23
18. ለሁሉም የተከፈተው ታላቅ የሥራ በር ምንድን ነው?
18 በትንቢቱ መሠረት ምሥራቹ ‘በየቋንቋው’ እየተሰበከ ነው። በውጪ አገር ቋንቋ መስክ የሚሠራው ሥራ ወደፊትም እድገት እንደሚያስገኝ የሚያሳይ ፍንጭ አለ። በሺዎች የሚቆጠሩ ብልህ የመንግሥቱ ሰባኪዎች በዚህ “ታላቅ የሥራ በር” ገብተዋል። (1 ቆሮንቶስ 16:9) ሆኖም በእነዚህ ክልሎች ውስጥ እድገት እንዲገኝ ይበልጥ የሚያስፈልግ ነገር እንዳለ የሚቀጥለው ርዕስ ያሳያል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
b ተጨማሪ ምሳሌዎችን ለማግኘት በሚያዝያ 1, 2004 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 24-28 ላይ የወጣውን “ትናንሽ ነገሮችን መሥዋዕት ማድረጋችን የተትረፈረፈ በረከት አስገኝቶልናል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ለማንም ሰው ባለማዳላት ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
• በክልላችን የሚገኙ የእኛን ቋንቋ የማይናገሩ ሰዎችን እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?
• ለሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መስበክ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
• በአካባቢያችን ላሉት የውጪ አገር ዜጎች አሳቢነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሮም
እስያ
ቀርጤስ
ሊቢያ
ፍርግያ
ጵንፍልያ
ኢየሩሳሌም
ይሁዳ
ግብፅ
ጳንጦስ
ቀጶዶቅያ
መስጴጦምያ
ሜድ
ኤላም
ዐረብ
ጳርቴና
[የውኃ አካላት]
ሜዲትራንያን ባሕር
ጥቁር ባሕር
ቀይ ባሕር
የፋርስ ባሕረ ሰላጤ
[ምንጭ]
በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተከበረው የጰንጠቆስጤ ዕለት ከ15 የሮም ግዛቶችና ከዚያ ግዛት ውጪ የተሰበሰቡ ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ምሥራቹን ሰምተዋል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙ የውጪ አገር ዜጎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በደስታ ይቀበላሉ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአምስት ቋንቋዎች የተጻፈ የመንግሥት አዳራሽ ምልክት