ብቸኛው መፍትሔ!
አልዓዛር የተባለ አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ሦስት ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው በቢታንያ ከተማ ማርታና ማርያም ከተባሉ እህቶቹ ጋር ይኖር ነበር። አንድ ቀን ወዳጃቸው ኢየሱስ ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ እያለ አልዓዛር በጠና ይታመማል። ሁኔታው ያሳሰባቸው እህቶቹ ለኢየሱስ መልእክት ላኩ። ኢየሱስ መልእክቱ ከደረሰው ከሁለት ቀናት በኋላ አልዓዛርን ለማየት ጉዞ ጀመረ። ኢየሱስ በመንገድ ላይ እያለ አልዓዛርን ከእንቅልፉ ለማስነሳት እንደሚሄድ ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ ምን ማለቱ እንደሆነ ስላልገባቸው በግልጽ “አልዓዛር ሞቶአል” አላቸው።—ዮሐንስ 11:1-14
ኢየሱስ የአልዓዛር መቃብር ጋር ሲደርስ የመቃብሩ በር ተዘግቶበት የነበረው ድንጋይ እንዲነሳ አዘዘ። ከዚያም ጮክ ብሎ ከጸለየ በኋላ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” ብሎ ተናገረ። አልዓዛርም ከመቃብሩ ወጣ። ለአራት ቀናት ሞቶ የነበረው ሰው ተነሳ።—ዮሐንስ 11:38-44
ስለ አልዓዛር የሚገልጸው ዘገባ ለሞት ብቸኛው መፍትሔ ትንሣኤ እንደሆነ ያሳያል። ሆኖም አንድ ሰው ‘በእርግጥ አልዓዛር በተአምራዊ ሁኔታ ከሞት ተነስቷል?’ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ የተከናወነው ነገር እውነት መሆኑን ይገልጻል። በዮሐንስ 1:1-44 ላይ ያለውን ዘገባ ስታነብ ታሪኩ ምን ያህል በዝርዝር እንደተገለጸ መመልከት ትችላለህ። ይህ ተአምር እንደተፈጸመ ትጠራጠራለህ? ከሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ስለመነሳቱ የሚገልጸውን ዘገባ ጨምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙትን ተአምራት እውነተኝነት ትጠራጠራለህ ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 15:17) ትንሣኤ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርት ነው። (ዕብራውያን 6:1, 2) ይሁን እንጂ “ትንሣኤ” የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው?
“ትንሣኤ” ሲባል ምን ማለት ነው?
በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ “ትንሣኤ” የሚለው ቃል ከ40 ጊዜ በላይ የሚገኝ ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎም “እንደገና መነሳት” የሚል ፍቺ ካለው የግሪክኛ ቃል የተተረጎመ ነው። ከዚህ ጋር የሚመሳሰለው የዕብራይስጡ አገላለጽ “የሙታን ወደ ሕይወት መመለስ” የሚል ትርጉም አለው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ትንሣኤ የሚያገኘው ምኑ ነው? የበሰበሰውና ወደ አፈር የተመለሰው አካሉ ሊነሳ አይችልም። የሚነሳው ቀድሞ የነበረው አካሉ ሳይሆን የሞተው ግለሰብ ራሱ ነው። ስለዚህ ትንሣኤ ሲባል የአንድ ሰው የቀድሞ ባሕርያት፣ ያሳለፈው ሕይወት እንዲሁም ማንነቱን የሚለዩት ዝርዝር ነገሮች በሙሉ ይመለሱለታል ማለት ነው።
ይሖዋ አምላክ ፍጹም የሆነ የማስታወስ ችሎታ ያለው በመሆኑ ሰዎች ከመሞታቸው በፊት ያሳለፉትን ሕይወት ማስታወስ ለእሱ ቀላል ነገር ነው። (ኢሳይያስ 40:26) ይሖዋ የሕይወት ምንጭ እንደመሆኑ መጠን የቀድሞውን ስብዕና የተላበሰ አዲስ አካል በመሥራት ያንኑ ሰው ዳግመኛ ሕያው ሊያደርገው ይችላል። (መዝሙር 36:9) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ የሞቱትን ለማስነሳት ‘እንደሚናፍቅ’ ይገልጻል። (ኢዮብ 14:14, 15) ይሖዋ ሙታንን ለማስነሳት ችሎታ ብቻ ሳይሆን ፍላጎትም ጭምር እንዳለው ማወቁ በጣም ያስደስታል!
ሙታንን በማስነሳቱ ሥራ ኢየሱስ ክርስቶስም ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ኢየሱስ አገልግሎቱን ከጀመረ ከአንድ ዓመት ብዙም ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ “አብ ሙታንን እንደሚያስነሣ፣ ሕይወትንም እንደሚሰጥ፣ ወልድም ደግሞ ለሚፈቅደው ሁሉ ሕይወትን ይሰጣል” በማለት ተናግሮ ነበር። (ዮሐንስ 5:21) የአልዓዛር ታሪክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሙታንን ለማስነሳት ፍላጎትም ሆነ ችሎታ እንዳለው አያሳይም?
በውስጣችን ያለና ከሞትን በኋላ በሕይወት የሚቀጥል ነገር አለ የሚለውን ሐሳብ በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል? የትንሣኤ ትምህርት የሰው ነፍስ ወይም መንፈስ አይሞትም ከሚለው መሠረተ ትምህርት ጋር ይጋጫል። በውስጣችን የማይሞት ነገር ካለ ትንሣኤ የሚያስፈልግበት ምክንያት ምንድን ነው? የአልዓዛር እህት ማርታ፣ ወንድሟ ከሞተ በኋላ በመንፈሳዊ ዓለም ውስጥ እየኖረ ነው የሚል እምነት አልነበራትም። ከዚህ ይልቅ በትንሣኤ ላይ እምነት ነበራት። ኢየሱስ “ወንድምሽ ይነሣል” ባላት ጊዜ ማርታ “በመጨረሻው ቀን፣ በትንሣኤ እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” ብላ መልሳለታለች። (ዮሐንስ 11:23, 24) አልዓዛርም ቢሆን ሲነሳ ከሞት በኋላ ስላለ ሕይወት ምንም የተናገረው ነገር የለም። አልዓዛር ሞቶ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን ግን ምንም አያውቁም” ይላል፤ “ልትሄድበት ባለው መቃብር ውስጥ መሥራትም ሆነ ማቀድ፣ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ የለም።”—መክብብ 9:5, 10
እንግዲያው በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ለሞት ብቸኛው መፍትሔ ትንሣኤ ነው። ታዲያ እስከዛሬ ከሞቱት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች መካከል ትንሣኤ የሚያገኙት እነማን ናቸው? ከተነሱስ በኋላ የት ይኖራሉ?
ትንሣኤ የሚያገኙት እነማን ናቸው?
ኢየሱስ “መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ [የኢየሱስን ድምፅ] የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ . . . [ሙታንም] ይወጣሉ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 5:28, 29) በዚህ ተስፋ መሠረት በመቃብር ውስጥ ያሉ ማለትም ይሖዋ የሚያስባቸው ሁሉ ይነሳሉ። ታዲያ እስከዛሬ ከሞቱት ሰዎች መካከል አምላክ የሚያስባቸውና ትንሣኤ የሚያገኙት እነማን ናቸው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዕብራውያን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ላይ አምላክን በታማኝነት ያገለገሉ ወንዶችና ሴቶች ስም ተዘርዝሮ ይገኛል። እነዚህም ሆኑ በቅርብ ዓመታት የሞቱት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ይነሳሉ። ምናልባት ባለማወቅ የአምላክን የጽድቅ መሥፈርቶች ሳያሟሉ የቀሩ ሰዎችስ? አምላክ ከሚያስባቸው ሰዎች መካከል ይኖሩ ይሆን? አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን እንደሚነሡ” ተስፋ ስለሰጠ ብዙዎቹ ትንሣኤ ያገኛሉ።—የሐዋርያት ሥራ 24:15
ይሁን እንጂ ትንሣኤ የማያገኙ ሰዎችም አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “የእውነትን ዕውቀት ከተቀበልን በኋላ ሆን ብለን በኀጢአት ጸንተን ብንመላለስ፣ ከእንግዲህ ለኀጢአት የሚሆን ሌላ መሥዋዕት አይኖርም፤ የሚቀረው ግን የሚያስፈራ ፍርድ . . . ነው” ይላል። (ዕብራውያን 10:26, 27) አንዳንዶች ይቅር የማይባል ኃጢአት ፈጽመዋል። እንደዚህ ያሉት ሰዎች በሔዲስ (መቃብር) ውስጥ ሳይሆኑ የዘላለም ጥፋትን በሚያመለክተው በገሃነም ውስጥ ናቸው። (ማቴዎስ 23:33) ይሁን እንጂ ትንሣኤ ያገኛል ወይም አያገኝም ብለን በማንም ሰው ላይ ከመፍረድ መቆጠብ አለብን። ፈራጁ አምላክ ነው። እርሱ ማን በገሃነም ውስጥ እንዳለና ማን በሔዲስ ውስጥ እንዳለ ያውቃል። ከእኛ የሚጠበቀው ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ነው።
ትንሣኤ አግኝተው በሰማይ የሚኖሩት እነማን ናቸው?
እስከ ዛሬ ከተከናወኑት ሁሉ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ‘እርሱ በሥጋ ቢሞትም በመንፈስ ግን ሕያው ሆኗል።’ (1 ጴጥሮስ 3:18) ከእሱ በፊት ከሰው ልጆች መካከል ማንም እንዲህ ዓይነት ትንሣኤ አላገኘም። ኢየሱስ ራሱ “ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር፣ ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም” ብሏል። (ዮሐንስ 3:13) ስለዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ መንፈሳዊ አካል ይዞ የተነሳው የሰው ልጅ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 26:23) ይሁን እንጂ ሌሎችም ከእሱ በኋላ እንደሚነሱ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። “እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ መጀመሪያ በኵራት የሆነው ክርስቶስ፣ ከዚያም በኋላ እርሱ ሲመጣ የክርስቶስ የሆኑት” ይላል።—1 ቆሮንቶስ 15:23
“የክርስቶስ የሆኑት” አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለልዩ ዓላማ ከሞት ተነስተው በሰማይ ሕይወት ያገኛሉ። (ሮሜ 6:5) ከክርስቶስ ጋር አብረው በመግዛት “በምድር ላይ ይነግሣሉ።” (ራእይ 5:9, 10) ከዚህ በተጨማሪ ካህናትና ነገሥታት ሆነው የሰው ዘር ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም የወረሰውን ኃጢአት ውጤቶች በማስወገዱ ሥራ ይካፈላሉ። (ሮሜ 5:12) ከክርስቶስ ጋር ነገሥታትና ካህናት ሆነው የሚገዙት ቁጥራቸው 144,000 ነው። (ራእይ 14:1, 3) እነዚህ ሰዎች ከሞት በሚነሱበት ጊዜ ምን ዓይነት አካል ይሰጣቸዋል? መጽሐፍ ቅዱስ “መንፈሳዊ አካል” እንደሆነ ይናገራል። ይህ ደግሞ በሰማይ እንዲኖሩ ያስችላቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 15:35, 38, 42-45
የ144,000ዎቹ ክፍል የሆኑት ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ የሚሄዱት መቼ ነው? አንደኛ ቆሮንቶስ 15:23 “እርሱ [ክርስቶስ] ሲመጣ” ወይም ሲገኝ እንደሆነ ይነግረናል። ከ1914 ጀምሮ የተከናወኑት የዓለም ሁኔታዎች የክርስቶስ መገኘትም ሆነ ‘የሥርዓቱ መደምደሚያ [NW]’ በዚሁ ዓመት መጀመሩን በግልጽ ያሳያሉ። (ማቴዎስ 24:3-7) ስለዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች ለሰዎች በማይታይ ሁኔታ ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ መሄድ ጀምረዋል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ይሆናል። ይህ ደግሞ ሐዋርያትና ሌሎች የጥንት ክርስቲያኖች በሰማይ ለመኖር ትንሣኤ አግኝተዋል ማለት ነው። ታዲያ፣ አምላክ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመግዛት ተስፋ የሰጣቸው አሁን በሕይወት ያሉ ክርስቲያኖች ሲሞቱ ትንሣኤ የሚያገኙት መቼ ነው? “በቅጽበተ ዐይን” ማለትም ወዲያው እንደሞቱ ይነሳሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:52) አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የ144,000ዎቹ ትንሣኤ በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያላቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ከሚያገኙት ትንሣኤ ስለሚቀድም “ፊተኛው ትንሣኤ” እና ‘የመጀመሪያው ትንሣኤ’ ተብሎ ተጠርቷል።—ፊልጵስዩስ 3:11 NW፤ ራእይ 20:6
ትንሣኤ አግኝተው በምድር ላይ የሚኖሩት እነማን ናቸው?
ቅዱሳን ጽሑፎች አብዛኞቹ የሞቱ ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው በምድር ላይ እንደሚኖሩ ይናገራሉ። (መዝሙር 37:29፤ ማቴዎስ 6:10) ሐዋርያው ዮሐንስ ከሞት ስለተነሱ ሰዎች ያየውን አስደሳች ራእይ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “ባሕርም በውስጡ የነበሩትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ውስጥ የነበሩትን ሙታን ሰጡ፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተፈረደበት። ከዚያም በኋላ ሞትና ሲኦል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ፤ የእሳቱ ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው።” (ራእይ 20:11-14) በሔዲስ ወይም በሲኦል ማለትም በመቃብር ውስጥ ያሉት አምላክ የሚያስባቸው ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በሙሉ ከሞት ይነሳሉ። (መዝሙር 16:10፤ የሐዋርያት ሥራ 2:31) ከዚያም እያንዳንዱ ሰው ትንሣኤ ካገኘ በኋላ በሚሠራው ነገር መሠረት ይፈረድበታል። ታዲያ በዚያን ጊዜ ሞትና ሔዲስ ምን ይሆናሉ? ወደ “እሳት ባሕር” ይጣላሉ፤ ይህም ማለት በአዳም ኃጢአት ምክንያት የሰው ልጆች ዳግመኛ አይሞቱም።
የሚወደውን ሰው በሞት ያጣ ማንኛውም ሰው ስለ ትንሣኤ ተስፋ መማሩ ምን ያህል ደስተኛ እንደሚያደርገው አስብ! ኢየሱስ በናይን ትኖር ለነበረችው መበለት አንድ ልጅዋን ከሞት ሲያስነሳላት ምን ዓይነት ደስታ ተሰምቷት እንደነበረ መገመት ይቻላል! (ሉቃስ 7:11-17) የ12 ዓመቷንም ልጅ ወደ ሕይወት በመለሳት ወቅት ወላጆቿ ምን እንደተሰማቸው መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽ “በሁኔታው እጅግ ተደነቁ [“ፈነደቁ፣” NW]” ይላል። (ማርቆስ 5:21-24, 35-42፤ ሉቃስ 8:40-42, 49-56) እኛም አምላክ ቃል በገባልን አዲስ ዓለም ውስጥ የምንወዳቸውን ሰዎች በትንሣኤ በመቀበል እንደሰታለን።
ታዲያ ስለ ትንሣኤ እውነቱን ማወቃችን በአሁኑ ጊዜ በእኛ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? “አብዛኞቹ ሰዎች ሞትን ስለሚፈሩ ጭራሽ ስለ ሞት ማሰብ አይፈልጉም” ሲል ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ ይናገራል። ለምን? ምክንያቱም ሞት ለብዙ ሰዎች የሚያስፈራና የማይታወቅ ነገር ወይም ምስጢር ነው። ሙታን ስላሉበት ሁኔታና ስለ ትንሣኤ ተስፋ እውነቱን ማወቃችን ‘የመጨረሻውን ጠላት ሞትን’ እንኳ እንዳንፈራ ብርታት ይሰጠናል። (1 ቆሮንቶስ 15:26) በተጨማሪም የቅርብ ወዳጃችንን ወይም ዘመዳችንን በሞት ብናጣ እንኳ ሐዘኑን ለመቋቋም ያስችለናል።
ታዲያ የሞቱ ሰዎች በምድር ላይ ለመኖር የሚነሱት መቼ ነው? በአሁኑ ጊዜ ምድር በዓመጽ፣ በግጭትና በደም መፋሰስ የተሞላች ከመሆኗም በላይ ተበክላለች። ሙታን ዳግመኛ ሕያው የሚሆኑት በእንደዚህ ዓይነቱ ምድር ላይ ከሆነ የሚያገኙት ደስታ ጊዜያዊ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ፈጣሪ በአሁኑ ጊዜ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለውን ዓለም በቅርቡ እንደሚያጠፋው ቃል ገብቷል። (ምሳሌ 2:21, 22፤ ዳንኤል 2:44፤ 1 ዮሐንስ 5:19) አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ ለመፈጸም የቀረው ጊዜ አጭር ነው። ከዚያም አምላክ በሚያመጣው ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠሩ የሞቱ ሰዎች ይነሳሉ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብዛኞቹ የሞቱ ሰዎች በምድር ላይ ለመኖር ይነሳሉ